ቅዳሜ 22 ኦገስት 2020

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል ሁለት)

 

ትልቁ ዋርካ ዛፍ በእድሜ ብዛት ወገባቸው ቢንቋቋም ተነስተው ከመቆም፣ ሥርአት ከማክበር፣ ለተተኪ ትውልድ አርአያ ከመሆን፣ የተረከቡትን ሥርአት ከማስረከብ ያገዳቸው አልነበረም።
ይህ ተግባር ሰወች ዘንድ ቢኖር አለም እንዴት ለሰወች ምቹ በሆነች ... አለም መሪ እንጂ አርአያ የለትም ለዚያውም በአግባቡ ከመሩ ማለት ነው።
እርሳቸው ተነስተው ሲቆሙ ሰብሳቢም፣ ተሰብሳቢም ሁሉም በክብር ከመቀመጫቸው ተነሳላቸው።
አይገባም ቁጭ በሉ፣
በእግዚአብሔር ተቀመጡ፤
ፈጣሪ ያክብራችሁ፣ የኔን እድሜ ይስጣችሁ፣ እኔ ያየሁትን እዩ፣ እኔ ያገኘሁትን ክብር አግኙ። በሉ ተቀመጡ ... አሉ ትልቁ የዋርካ ዛፍ እሳቸው ሲነሱ ተሰብሳቢው የተጠለለባት የዋርካ ዛፍ አንሳ ታየች።
በትህትና ዝቅ ብለው ሁሉንም እጅ ነሱ።
እርጋታቸው፣ ግርማ ሞገሳቸው፣ ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ልብ ያርዳል ... እንደ ማእበል ያናውጻል። ግን ትልቁ ዛፍ የቁጣ ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም። ንቀት የሚባል ነገር በጭራሽ አያውቁም። እውቀት እና ጥበብ እርሳቸው ዘንድ ናት። የሚናገሩት ቃል ከቅርንጫፍ አንስቶ ሥር ድረስ ዘልቆ ይገባል።
እንደ አዋቂ ሳይሆን እንዳላዋቂ ነው የሚናገሩት ነገር ግን አንዲት መሬት ጠብ የምትል ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም።
አሉ እንጂ ጥራዝ ነጠቆች፣ ሰወች ... ከእውቀት ነጻ የሆኑ ደፋሮች ትህትና በልባቸው ሳይሆን በአጥራቸው ያልዞረ።
አልፎ አልፎ ከአንደበታቸው የሚወጣ ምርቃት ሊረግፍ የደረሰ የደረቀ ቅጠል እድሜ ያረዝማል፣ ልምላሜ ይሰጣል፣ ያበቡትን እንዲያፈሩ፣ ያፈሩትን ፍሬያቸው እንዲበዛ ያደርጋል።
አይራገሙም።
አይሳደቡም።
አይበሳጩም።
የእድሜያቸው መርዘም፣ የቁመታቸው ትልቀት፣ የቅጠላቸው ውበት፣ የቅርንጫፎቻቸው ብዛት ምሥጢሩ ይህ ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ጊዜ ሁሉንም ታዳሚ ዛፎች ዘወር ብለው ቃኙዋቸው፤ "በእርግጥ አሉ ... " ትልቁ ዋርካ ዛፍ። በእርግጥ በእድሜ እበልጣችኋለሁ። ጓደኞቼ በእድሜ ብዛትም ይሁን አሁን እዚህ በሚጠቃቀሱትም ምክንያት አጠገቤ የሉም። በሕይወት የሉም። በቁም ግን የተወሰኑት አሉ። ልጆቼ በሕይወት መኖርና በቁም መኖር ይለያያል። እናንት በሕይወት ስላላችሁ ነው እዚህ የታደማችሁት በቁም ያሉት እዚህ ሊገኙ አልቻሉም። የተለያዩ ችግሮች ጠፍንገው ይዘዋቸዋልና።
አንድ አርሶ አደር ትዝ አለኝ ወቅቱ አከባቢው ረሃብ ያንዧበበት ነበር፤ ታድያ ሰውየው እጃቸው ላይ የሚላስ የሚቀመስ ባይኖራቸውም ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል ነበራቸውና ሲደርስ ብድሬን እመልሳለሁ እያሉ እየተበደሩ ያንን ክፉ ቀን ያልፉት ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ታድያ እኚህ አርሶ አደር ወደ እርሻ ስፍራቸው ሄደው ዘወር ዘወር እያሉ ይመለከቱት ጀመር። ታድያ የተበደሩትንና የበሉትን ማሳው ላይ ያለውን ሲመለከቱ የሚተርፋቸው ያለ አልመስል ሲላቸው። "ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል" ብለው ወደቤታቸው ተመለሱ።
እስኪ ወደ ሰፈራችን፣ መንደራችን፣ አገራችን እንመልከት ማነው በቁም ያልተበላ? ፖለቲካ ያልበላው? ዘረኝነት ያልበለው? መንደርተኝነት ያልበላው? ... የቆምን መስሎናል ተበልተን፣ ተባልተን አልቀናል።
ሁላችን ባለእዳ ነን፣
የልጆቻችንን አገር የደም ምድር አድርገናል፣
ወደፊት መጓዝ ቢሳነን እንደሎጥ ሚስት ታሪክን ወደኋላ ማየት ላይ ተጠምደናል፤
ሽማግሌው ዋርካ እንዲህ አሉ፦ችግሮቹ ሰው ሰራሽ፣ እንስሳ ሰራሽ፣ ተፈጥሮ ሰራሽ፣ እጽዋትን የሚያጠቃ በሽታ ወዘተ... እያልን ልንዘረዝራቸው እንችል ይሆናል። ችግሩ ምክንያቱ አይደለም እዚህ አለመገኘታቸው፣ እኛ ለተቀመጥንበት አላማ ለአንዴና ለዘለዓለም መቀመጥ አለመቻላቸው ነው።
በሰውኛ ምን ይባላል መሰላችሁ " ይህንን እናንተ የምታዩትን፣ የምትሰሙትን ብዙዎች ሊያዩ ሊሰሙ ወደዱ አላዩም አልሰሙም። ይህንን ያዩ አይኖቻችሁ የሰሙ ጆሮዎቻችሁ ንኡዳን ክቡራን ናቸው" ይባላል።
ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ ምንም እንኳን ሰወች፣ ተፈጥሮ፣ እንስሳት የሚያደርሱብን በደል እጅግ ቢበረታም ዛሬ ይህን በደል ለማስቆም መሰባሰባችን መነጋገራችን ትልቅ ነገር ነው። ይህን ሽተው ያላዩ ይኽን የመሰለ እድል ያልገጠማቸው ቤተሰቦቻችን እጽዋት እንዲሁ እድሜያቸው ተቀጭቷል፤ ገሚሶችም ለሌሎች መኖር እነርሱ ትልቁን የመኖር ጉጉታቸውን መስዋእት አድርገዋል።
እኛ እድለኞች ነን። እድላችንን እንዳያመልጠን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። መደማመጥ መከባበር ይገባናል። አንዱ ሲናገር ሌላው አድማጭ መሆን አለበት። የሌላውን ሐሳብ እናክብር። አንዳችን ለአንዳችን እንደምናስፈልግ እንመን። በተናጠል መቆም ለአጥቂዎች ተጋላጭ ከመሆን የዘለለ ጥቅም እንደሌለው ልብ እንበል።
እስኪ ከሰወች እንማር፤ ሰወች ክቡር ሆነው ከአንድ አዳም ተፈጥረው ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ ሄደው ዘር ይቆጥራሉ፣ ነጭ ጥቁር ይላሉ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ እያሉ ይከፋፈላሉ።
እስኪ ማን ይሙት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚያውም የሰው ዘር መገኛ በሆነች በሉሲ አገር እንዴት ይከፋፈላል?
በየእምነት ተቋሞቻቸው ስለ ሥነ ፍጥረት እየተማሩ የሰው ልጅ ከአንድ አዳም እንደተገኘ እየተናገሩ መከፋፈልን ከወዴት አመጡት? ከመከፋፈልስ ምን አተረፉ?
ወገኖቼ አሉ እኝህ ታላቅ ዋርካ፦
ምንም እንኳን የረባ ከእናንተ የተሻለ ሐሳብ ባይኖረኝና እድሜ ቢገፋ አሁንም ከእናንተ እኩል የመኖር ጉጉት እንዳለኝ አውቃለሁ።በአጭሩ መቀጨት አልፈልግም። ዝምታው በረጅም ሳቅ ተሰበረ። በጭበጨባ እና በሳቅ አጀቧቸው።
ተናጋሪው ዋርካ እውነቴን ነው ምን ያስቃችኋል? መኖር እኮ የሚጣፍጠው ጣእሙ የሚገባችሁ ስትኖሩ ነው። እኔ ረጅም እድሜ ስለኖርኩ በቃኝ ከማለት ይልቅ የመኖር ትርጉም ስለገባኝ ለመኖር እጓጓለሁ።
ሌሎች እኛን የማጥፋት እና እኛን በአጭሩ የመቅጨት ምክንያት ከመኖር ጉጉታቸው የመነጨኮ ነው ከክፋት አይደለም። ከእኛስ መካከል አሉ አይደል ለመኖር ሲሉ የነፍሳትን እድሜ የመኖር ተስፋ በአጭሩ የሚቀጩ ... የነርሱን ከርሱ ለይታችሁ አትዩት፤ ይልቅስ ... የዛፎች ጉርምርምታ ሐሳባቸውን ገታባቸው። እርሷቸውም ከመናገር ተቆጠቡ ... የአነጋገራቸው አድናቂ፣ የምልካተቸው ተማራኪ ንግግራቸውን እንዳናጠባቸው ትልቁ ዋርካ አወቁ።
አመሰግናለሁ።
አመሰግናለሁ።
ይበቃል፤ ይበቃል ጓዶች።
" ... ይልቅስ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ ወደ ውጭ ከማየት አስቀድመን ወደ ውስጥ እናተኩር፤" ብለው ንግግራቸውን ገታ አደረጉት።
አዳማጭን ገረመሙት ....
ሰብሳቢዎችንም በአይናቸው ቃኟቸው...
ሁሉም እየተከታተላቸው ነው ...
ሐሳባቸው ጭንጫ መሬት ላይ እንዳልወደቀ ልብ አሉ።
" ... ልብ ብላችሁ አዳምጡኝ፤ ሐሳቤን እዚህ ጋር ስለሆነ ልብ ብላችሁ አዳምጡ። አልደግመውም።
ጸጥታ ሰፈነ ... አድማጭ የተናጋሪውን የመፍትሔ ሐሳብ ለመስማት ጓጓ፤
ተናጋሪው ዋርካ ዛፍ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ ጉሮሮቸውን ጠራረጉ። አሁንም ደግሜ እላለሁ። ልብ ብላችሁ አድምጡኝ፥ ወደ ራሳችን እንመልከት።
ለክፍል ሶስት ይቆየን። የኚህን ትልቅ ዋርካ የመፍትሔ ሐሳብ እንቃኛለን።
ይከታተሉን።
ሐሳብ አስተያየትዎን ከመስጠት አይቆጠቡ።
መልካም ቀን ይሁንልዎ።
ደረሰ ረታ
ነሐሴ 10/2012 አ.ም.

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ (ክፍል አንድ)

 

እራስን ተጠያቂ ማድረግ መለማመድ
ክፍል አንድ
ነሐሴ 10/2012 አ.ም
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ዛፎች ስለሆነባቸው፣ እየሆነባቸው ስላለ፣ ሊሆንባቸው ስላለው ጉዳይ ለመምከር ስብሰባ ተቀመጡ።
አጀንዳዎቻቸውን አንድ በአንድ ነቅሰው አውጥተው ከተወያዩ እና በብዙ ጉዳይ መግባባት ላይ ከደረሱ በኋላ በአንደኛው አብይ ጉዳይ ላይ መግባባት ባለመደረሱ ምክንያት ስብሰባው አጀንዳውን በይደር አሳድሮ ተስማምቶ ተበተነ።
በበነጋታው በተለመደው ሰአት፣ በተለመደው ቦታ፣ ሁሌም በስብሰባው ላይ የሌሎች ዛፎች ጥቃት የኛም ጥቃት ነው የነርሱ ጉዳት እኛንም ያገባናል የሚሉ ገንቢ ሐሳብ ለመስጠት ውይይቱን በሐሳባቸው ለማዳበር፣ የተጣመመውን ለማቃናት፣ የጎበጠውን ለማቅናት፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ ወዘተ የሚገኙ የተለመዱ ዛፎች በመሰብሰቢያው ዋርካ ጥላ ስር ተሰድረዋል።
ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው በሰአታቸው ቢገኙም ጸሐፊው የክብር መዝገቡን ይዞ በሰአቱ ባለመገኘቱ የስብሰባው መጀመሪያ ሰአት ወደፊት ገፍቷል።
በዚህም የተነሳ ብዙዎች ዛፎች ማጉረምረም ጀምረዋል። ከየቦታው የግል ወሬ፣ ሐሜት፣ በትናንትናው እለት ፋይላቸው የተዘጉትን ጉዳዮች በተናጠል እያነሱ ክርክር ጦፏል፣ አስተያየት ሰጪ ዛፎችን ትችት እና ድጋፍ በየቦታው ይወራ ጀመር፣ ገሚሱ ስብሰባው ላይ መገኘቱን እየኮነነ ያልተገኙትን ዛፎች ማድነቅ ተያይዞታል፣ ...
ከመድርኩ ላይ ተገማሽረው የተቀመጡት ምክትል ሰብሳቢ ጠና ያሉ ዛፍ የጊዜውን መሄድ ጀንበሯን በመመልከት ወደ ዋናው ሰብሳቢ ጆሮ ጠጋ በማለት አንሾካሸኩ ዋና ሰብሳቢው ዛፍም ሰአቱ በመሄዱ እና በጸሐፊው ማርፈድ መጨነቃቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል። ከአንደበታቸው አውጥተው አይናገሩት እንጂ ብስጭትም ይታይባቸዋል። ምላሻቸውን ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ ገለጡላቸው።
ተሰብሳቢው ጫጫታው የንብ መንጋ መስሏል ድምጹ በአራቱም አቅጣጫ ይተማል። አንዳንዶችም አርፋጆች እየተንጠባጠቡ ያልተጀመረውን ስብሰባ ምንም እንዳልተፈጠረ ማርፈዳቸው እንኳን ሳይታወቃቸው ይቀላቀሉ ጀመር።
የስብሰባው አጀንዳ ይለያይ እንጂ የስብሰባው ይዘት እና የተሰብሳቢ ግዴለሾች መብዛት ከሰው ልጅ ስብሰባ ጋር ብዙ አንድ የሚያደርገው ነገር አለ።
ጸሐፊው እየተንጎማለሉ በተሰብሳቢው መካከል አአልፈው መድረኩ ላይ ተሰየሙ፤ መዝገባቸውን ገለጥ ገለጥ አደረጉ፣ ከደረት ኪሳቸው የንባብ መነጥራቸውን አወጡ ... "ጸጥታ" አሉ። ፍየል ከመድረሷ ... አሉ አበው። የሰማቸው አልነበረም። አሁንም "ጸጥታ" አሉ ... ድምጹ በረታ። ድምጻቸውን ለማስተካከል በሚመስል ሁኔታ ጉሮሯቸውን ጠራረጉ። ይኸን ጊዜ የድምጡ ሃያልነት ጋብ እያለ መጣ።
ሰብሳቢው ዛፍ የምንተፍረታቸውን ተሰብሳቢውን ይቅርታ ጠየቁ።
የተሰብሳቢው ዛፍ ቁጣ ጨመረ፣ ማጉረምረሙ በረታ፣ ተቃውሞቸውን በጭብጨባም በፉጨትም ገለጡ ... ተቃውሞው ጸሐፊው አርፍደው መጥተው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው እንዴት ከኛ እኩል የተገኙት ሰብሳቢ ይቅርታ ይጠይቃሉ አይነት እንድምታ አለው።
ስብሰባው ተጀመረ።
ሐሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ።
ጉርምርምታ አልፎ አልፎ እንዳለ ነው፤ ከሚሰጠው አስተያየት በይዘትም በጥራትም ጉርምርምታው ውስጥ ይንጸባረቅ ነበር። ነገር ግን እጃቸውን አውጥተው የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው አይናገሩም፣ አስተያየታቸውን አይሰጡም፣ ወይ ተቋውሟቸውን አይገልጡም። ዛፎችንም ከሰው የሚያመሳስላቸው ጸባይ ያለ ይመስላል።
ጉርምርምታው ይኑር እንጂ ስብሰባው ቀጥሏል አስተያየቶችም ከየቦታው ይሰጣሉ።
አለመግባባቶች በረቱ፤
ደርበብ ያሉት ምክትል ሰብሳቢ ተናጋሪውን ዛፍ እና የሚያጉረመርሙትን በመሃል እያቋረጡ፥ ይቅርታ ዛፎች ሳቋርጣችሁ እጅግ እያፈርኩ ነው። ጭርንጫፎቻቸውን በሐዘኔታ እየነቀነቁ "ምን ነካን?
ኧረ ተው ሰሚ ምን ይለናል?
ተመልካችስ ቢሆን?
ለአገር ምድሩ ለሰው ቢባል ለእንስሳ ስንት አይነት መድሃኒት እየሆንን እንዴት ለራሳችን ጊዜ አንዲት መፍትሔ እንጣ ... ዛፎች? ኧረ ተው ኧረ እግዜሩስ ምን ይላል? ከምድር በታች ያሉትስ አባቶቻችን አያዝኑብንም?" አሉ እጅግ በመከፋት።
ስብሰባው ቀጠለ፤
ስርአት አልበኛው እና ቆንጠር ቆንጠር የሚሉት አጭሩ ጸሐፊ ቆጣ ብለው "ስርአት ይዛችሁ ስብሰባውን ትከታተሉ እንደሁ ተከታተሉ አንዳንድ የምትረብሹ ዛፎችም አደብ ብትገዙ ይሻላል። አይ የምትሉ ከሆነ ደግሞ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ቅጣቱን መጣል አቅቶን አይደለም ትዕግስታችን በርትቶ እንጂ ..."
የተሰብሳቢው ጫጫታ የጸሐፊውን ንግግር አቋረጣቸው፤ ጸሐፊው አርፍደው ከመምጣታቸው ይቅርታ አለመጠየቃቸው ከዚያም አልፎ ተርፎ ሥርአት ለማስያዝ ስለቅጣት ማንሳታቸው ዛፎችን አስቆጣቸው።
ሰብሳቢው ራሳቸውን ታመሙ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡት ስብሰባ በመዘግየት ተጀምሮ በጭቅጭቅ እና በንትርክ አጀንዳው ላይ ረብ ያለው ሐሳብ ሳይነሳ ሰአቱ ነጎደ።
ለግላጋ ቁመና ያላቸው ዛፍ ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ እርሳቸው ከመቀመጫቸው ብድግ ሲሉ የመሰብሰቢያው ዋርካ ቅጠሎች ረገፉ፤ ጎንበስ ብለው ተሰብሳቢውን ይቅርታ ሲጠይቁ ጸጥታ ሰፈነ፣ ሠላም ወረደ በጫጫታው ምክንያት እየጨመረ የመጣ ሙቀት ረገብ አለ።
ስብሰባው በተለመደው ግርማ ሞገሱ ተጀመረ ስርአት ነገሰ።
ተናጋሪ ሲናገር አድማጭ ጸጥ አለ፤
አስተያየቱን ሲጨርስ ደጋፊ ሲያጨበጭብ ተቃዋሚ አልያም ሌላ አስተያየት ያለው እጅ በማውጣት ሐሳቡን መሥጠት ቀጠለ።
ይሁን እንጂ ምንም የረባ፣ ለመፍትሔ የቀረበ አስተያየት እስከ አሁን አልተሰነዘረም።
ሁሉም አስተያየቶች ከመፍትሔው ይልቅ ችግሩ ላይ ያጠነጠኑ ውይይቶች ነበሩ።
እርግጠኛ ሆኖ ከሚናገረው ይልቅ ይመስለኛል እያለ የሚናገረው አስተያየት በቁጥር ይበዛ ነበር።
ጊዜው እየገፋ ተሰብሳቢውም እየተሰላቸ ሰብሳቢዎችም ስብሰባው በይደር እንዳይቀጥል በስጋት እየተዋጡ ተሰብሳቢዎችም ጉዳያቸውን ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ስብሰባውን እየተው ሹልክ እያሉ መውጣት ጀምረዋል።
ይህ ድርጊት ደግሞ የሰብሳቢዎችን እና የቀሩትን ተሰብሳቢ ቀልብ እየሰረቀው መጣ።
አስተያየት ስጪዎች ሐሳብ ከመጨረሳቸው የተነሳ ይሁን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ምክንያት እየተነሱ እገሌ እንዳለው እያሉ አስተያየት በመሥጠት ተሰብሳቢውን አሰለቹት፦
"አካሄድ" አሉ ጸሐፊው "እባካችሁ ጊዜያችሁን ለመጠቀም ሌሎች ያነሱትን ሐሳብ ስለያዝን አትድገሙት አዲስ ሐሳብ ከሌላችሁ ስብሰባውን እንጠቅልለው" አሉ። ሲመጡ አርፍደው ለመሄድ ፈጣን የሆኑ ኮሚቴ እግዜር ይሰውር።
ሰብሳቢው ስብሰባውን እየመሩ እንደሆነ ለማጠየቅ በተረጋጋ መንፈስ "ግድየለም ይምሽ ይኸንን ጉዳይ ሳንቋጭ ለተበዳዮች መፍትሔ ሳናመጣ፣ እንባቸውን ሳናብስ፣ እልቂታቸውን ማቆም ቢያቅተን መቀነስ የሚያስችል መፍትሔ ሳናመጣ ጉባኤው አይፈታም" አሉ።
አስተዋይ ይኑር።
በእድሜ ጠና ያሉት ዋርካ ወገባቸው እየተንቋቋ ከመቀመጫቸው ብድግ እንደማለት አሉ፥
ሁሉም ዛፍ በአንድ ድምጽ ይቀመጡ አይነሱ ... በአባቶቻችን ተቀምጠው ይናገሩ ... አሏቸው።
ግድየለም እግዜሩም እናንተም እንድትሱሙኝ ቁሜ ልናገር ብለው ተነሱ።
በክፍል ሁለት የቀረውን እንድንቀጥል ይቆየን።
የቴሌግራም አድራሻዬ ይከታተሉኝ።
ለሎሎች ይደርሳቸው ዘንድ ማጋራትን አይርሱ።
ሐሳብ አስተያየትዎን ለመስጠት አይቆጠቡ።
ነሐሴ 10/2012 አ.ም
ደረሰ ረታ

እሑድ 7 ጁን 2020

[በዓለ ጰራቅሊጦስ] ✍️ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ


♥️ በሐዋርያት ሥራ ምዕ ፩፥፲፬ ላይ እንደተጻፈ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በአርባኛው ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቢታንያ በማውጣት “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ እስኪያደርጉ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ አዝዞ በምስጋና ዐረገ፡፡

♥️ ስለምን እንዲኽ አዘዛቸው? ቢሉ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት ፈሪዎች ነበሩና ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ባልተቀበለ ሰውነታቸው አይሁድ መከራ አጽንተውባቸው ሃይማኖታቸውን እንዳይክዱ፡፡

♥️ዳግመኛም ኅሊናቸውን በተመስጦ ለማቆየት፡፡
❤️ ሌላው መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው በጽርሐ ጽዮን ነውና ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወሩ እንዳይቀርባቸው ነው፡፡

♥️12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት፣ 36ቱ ቅዱሳት አንስት በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ኹነው በይሁዳ ምትክ ማትያስን አስገብተው፤ ሰማይ ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ የተሸከመች የድንግልና ጡቶቿን ያጠባች ቅድስት ድንግል የሌለችበት ጉባኤ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተለየ ነውና የመስቀል ሥር ስጦታቸውን “የኢየሱስ እናት ማርያምን” ይዘው በአንድ ልብ ኾነው በጸሎት መትጋት እንደዠመሩ ሉቃስ ጽፏል (የሐዋ ፩፥፲፬)፡፡

♥️ ከዚያም ልክ በሦስት ሰዓት “መጽአ ግብተ እምሰማይ ድምፅ ከመ ድምፀ ነፋሰ ዐውሎ” ይላል ከወደ ሰማይ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ነጒዶ ተሰምቶ ያሉበትንም ቤት መላው ይኽም የሚያስተምረን ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የኾነች እመቤታችን ያለችበትና የምትጠራበት ጉባኤ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንዳለበት ያሳየናል፤ ይኽም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አስቀድሞ በኤልሳቤጥ ሲታወቅ ገና እመቤታችን ደርሳ ሰላምታን ስትሰጣት ቅዱስ ወንጌል “በኤልሳቤጥ ላይ መንፈስ ቅዱስ መላባት” በማለት እንደመሰከረ እናያለን (ሉቃ ፩፥፵፩)፡፡

♥️ ጌታ በዐረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ስለምን ወረደ ቢሉ፡-
1ኛ)10ሩን ሕዋሳት 10ሩን ቃላት በእውነት ብንጠብቅ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጠን ለማጠየቅ፡፡
2ኛ) ከ10ኛው መዐርግ የገባን እኛ ነበርንና ከጥንተ ቦታችን ክብራችን እንደተመለስን ለማጠየቅ ነው፡፡

♥️ ይኸውም ለሐዋርያት በአምሳለ ነፋስ የተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ነው ለምን በነፋስ አምሳል ተገለጸ ቢሉ መተርጉማነ መጻሕፍተ ሐዲሳት ያመሰጥሩታል፦
✔️ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነውና፤
✔️ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤
✔️ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥኣን ይለያልና፤

✔️ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥፅ ዛፍ ሲያናውፅ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጒም ነውና፤
✔️ነፋስ መንቅሂ ነው መንፈስ ቅዱስም መንቅሂ ነውና፤ ✔️ነፋስ መዐዛ ያመጣል መንፈስ ቅዱስም መዐዛ ጸጋን ያመጣልና ነው፡፡

♥️ ከዚያም “ወአስተርአይዎሙ ልሳናተ እሳት ክፉላት ከመ እሳት ዘይትከፈል” ይላል እንደ እሳትም የተከፋፈለ ልሳን ኹኖ በያንዳንዳቸው ላይ ተቀምጦባቸዋል፤ ይኸውም ልሳን ላንቃ ማለት ቋንቋን ማውጫ መነጋገሪያ እንደኾነ ኹሉ ሰዎች የሚግባቡበት ትክክለኛ መግባቢያ የኾነ፤ ሊጻፍ ሊሰማ ሊያግባባ የሚችል የቋንቋ ሀብትን መንፈስ ቅዱስ በእሳት ላንቃ አምሳል አሳድሮባቸዋል፡፡

♥️ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል መውረዱ ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኸውም እሳት ምሉእ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉእ ነውና፤
✔️ እሳት በምላቱ ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገለጽም መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጉም እንጂ ዐድሮ ሳለ አይታወቅምና፤
✔️ እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው ኋላ በዕንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል መንፈስ ቅዱስም በ፵ በ፹ ቀን በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤

✔️ እሳት ጣዕምን መዐዛን ያመጣል መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን መዐዛ ጸጋን ያመጣልና፤
✔️እሳት በመጠኑ የሞቁት እንደኾነ ሕይወት ይኾናል ከመጠን ዐልፎ ቢሞቁት ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደኾነ ሕይወት ይኾናል በማይገባ ከተጻፈው ወጥተው የመረመሩት እንደኾነ ይቀሥፋልና፤

✔️እሳት ያቀረቡለትን ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡለትን መሥዋዕት ይቀበላልና፤ ✔️እሳት ውሃ ገደል ካልከለከለው ኹሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ኹሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋልና፤

✔️እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምስጢርን ይገልጻልና፤
✔️እሳት የበላው መሬት ለእኽል ለተክል ይመቻል መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ይመቻልና ርሱ ባወቀ በእሳትና በነፋስ አምሳል ወርዷል፡፡

♥️ ከዚያም በኹሉም መንፈስ ቅዱስ መልቶባቸው ዓለም በሚሰማው ኹሉም በሚረዳው በ፸፪ቱ ቋንቋ ተናግረዋል፤ በሐዋርያት 72 ቋንቋ አልተከፈለባቸውም፤ የቀሩት ግን ከ15 በታች የወረደ የለም እንጂ 20ም 30ም 40ም 50ም 60ም የተገለጠላቸው አሉ፡፡

♥️ እስራኤል ከምርኮ መልስ በኋላ በወደዱት ሀገር በሕጋቸው ይኖራሉ፤ ለበዓለ ፋሲካ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ፤ በዓለ ፋሲካን አክብረው ከዚያ አያይዘው ሰባት ሱባዔ ቈጥረው በ50ኛዪቱ ዕለት በዓለ ሰዊትን ያከብሩ ነበርና በዓለ ፶ን ለማክበር ከየዓለማቱ የመጡት በእጅጉ ተገርመው:- “እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?፤ የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች በኹለት ወንዝም መኻከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊብያ ወረዳዎች የምንኖር በሮሜም የምንቀመጥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” በማለት በእጅጉ ተደነቁ፡፡

♥️ ያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነሥቶ ነቢዩ ኢዩኤል በምዕ 2፡28-29 ላይ “ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ” ብሎ የተናገረው መፈጸሙን ጠቅሶ ሰፋ አድርጎ ነገረ ክርስቶስን ቢያስተምራቸው ቃሉን ተቀብለው ሦስት ሺሕ ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡

♥️ሊቃውንትም ይኽነን በመያዝ በተለይ እነቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዕለቷን “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ብለዋታል፡፡

♥️እመቤታችን በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በማርቆስ እናት ቤት በሰገነት ላይ በመስቀል ሥር በአደራ የተቀበለቻቸው በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የሚያምኑ የአደራ ልጆቿን ሐዋርያትን ይዛ እንደተገኘች ዛሬም በልጇ ደም በተመሠረተችው ሐዋርያዊት በኾነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን የልጇን የባሕርይ አምላክነት የርሷን ወላዲተ አምላክነት በመመስከር እንኖራለን፡፡

♥️ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማሕየዊ ዘሠረጸ እምአብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት” (ጌታ ማሕየዊ በሚኾን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ በነቢያት ዐድሮ የተናገረ ለርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንስገድለት እናመስግነው) አሜን።
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ዕርገተ ሕሊና - የሀሳብ ከፍታ በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ


"ዓረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ፣ ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው - ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም ወጣህ፣ ለሰው ልጆችም ጸጋህን ሰጠሐቸው" /መዝ 67/8 ፤ 18/

ጌታችን ያድነን ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ በዕለተ ትስብእቱም (ሰው በሆነባት ዕለት) ባሕርያችን አከበረ፡፡ በዚያች ሥጋችንና ነፍሳችንን በተዋሐደባት ቅጽበት ባሕረየ ሰብእ በዘባነ ኪሩብ በየማነ አብ ተቀምጧል፡፡
ሰው ሆኖም ሀፍረታችንና ውርደታችን ሁሉ ይቅር ይለንና አሳፋሪ ከመሆንም ያድነን ዘንድ እርሱ ስለእኛ ተዋረደ፣ የአይሁድን ርኩስ ምራቅ ታገሠ፤ ሐፍረትንም ሁሉ ንቆ ክብር ይግባውና ስለሁላችን ድኅነት ራቁቱን ተሰቀለ፡፡ ስለእኛ ሞተ፣ ተቀበረ፣ ተነሣ፣ በዐርባኛውም ቀን ክብር ይግባውና ዐረገ፡፡

ይህ ሁሉ ከጽንሰት እስከ ዕርገት ያለው ሰውን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከዚያም ላቅና ከፍ ወዳለ ጸጋ ለማድረስ ነው፡፡ ከእነዚህ ጸጋዎች አንዱ ዕርገተ ኅሊና ወይም የሀሳብ ከፍታ ነው፡፡

 ይህነን ከፍታ በአጭሩ በሁለት ወገን ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ አንደኛው ለሰው የተሰጠውን ጸጋ ተረድቶ በሕግ በአምልኮ እርሱን በመከተል ወደ ሰማያዊ ምሥጢራት በመመንጠቅ ነው፡፡

ይኸውም አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ከምድር እስከ ሰማይ ተዘርግታ በላይዋ እግዚአብሔር ተቀምጦባት መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት እንዳየ ቅዱሳንም እንደ መሰላሉ ቋሚዎች ባሉ ብሉይና ሐዲስ፣ በመሰላሉ ላይ እንዳሉት ርብራቦች ደግሞ በምገባራት ሠናያት (ከጾምና ከጸሎት ሳይለዩ መልካም ተጋድሎን በየደረጃው በመጋደል) ወደ እግዚአብሔር በተጋድሎ ይጓዛሉ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን፣ ትርጓሜና መሥጢራትን ተቀብለው ይዘው ይወርዳሉ፤ በትምህርትም ለሰው ዘር ያደርሳሉ፡፡ ይህ መንፈሳዊው ዕርገተ ኅሊና ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ሁላችንንም የሚመለከተው ዕርገተ ኅሊና ወይም የሀሳብ የዕቅድ የተግባር ከፍታን የሚመለከተው ነው፡፡

ይህንንም በምሳሌ አስቀድሞ አስረድቶናል፡፡ በኦሪት ዘሌዋውያን እንደተጻፈው ንጹሐን ስለሆኑት እና ስላልሆኑት፣ ስለሚበሉትና ስለማይበሉት እንሥሣት ሕግን በሰጠበት አንቀጽ ላይ ስለዐሦች የተናገረበት ክፍል ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ የሚበሉት የዐሣ ዘሮች ቅርፊትና ክንፍ ያላቸው እንዲሆኑ ታዝዟል፡፡ የዚህም ምሳሌነቱ ግልጽ ነው፡፡

ቅርፊት ለዐሣዎች ራሳቸውን ከሌላ መርዛማ የባሕር ውስጥ አውሬ የሚጠበቁበት ነው፡፡ ክርስቲያንም አብሮት በዚህ ዐለም ከሚኖር የሰው የነገር፣ የክህደትና የጥላቻ መርዝ መጠበቅ ካልቻለ ተጓድቷልና ንጹሕ አይደለም ማለት ነው፡፡

ክንፋቸው ደግሞ መንሳፈፊያቸው የባሕሩ ወለል ላይ ከመንፏቀቅ የታደጋቸውና የባሕሩ ጠለል ድረስ ከፍ ብለው ተንሣፈው ከባሕሩ ውጭ ያለውን ዐለም እንኳ ለመቃኘት የሚያስችላቸው ሀብታቸው ነው፡፡ ክርስቲያንም በሚኖርበት ዐለም በመጨረሻው በዝቀተኛው ደረጃ መሬት ለመሬት ማለትም ምድራዊና ሥጋዊ ነገርን ብቻ በመከተል ራሱን ደካማ ማድረግ የለበትም፡፡ ወደ ክፍታ ብቅ ማለት መቻል አለበት፡፡

ስለዚህም በጥቅምና በክብር፣ በጌጥና በልብስ፣ በምግብና በመጠጥ፣ በቤትና በመኪና ፍላጎት ብቻ ናላው የሚዞር ወይም ለሚያገኘው ምድራዊ ነገር ብቻ የሚንገበገብ እንስሳ መሆነ የለበትም፡፡ ይልቁንም ከራሱ አልፎ ለሌሎች፣ የእኔ ከሚላቸው ተሸግሮ ሌሎች ለሚላቸው፣ ከሰው አልፎ ለፍጥረት ሁሉ የሚያስብ ደግ መሆን አለበት፡፡

ከጊዜያዊ አልፎ ለዘላለማዊው፣ ከቅርቡ አልፎ ለሩቁ ፣ ከምድራዊው ሕይወት አልፎ ለሰማያዊው፣ ከዛሬ አልፎ ለነገ እያሰበ የሚናገር የሚሠራ የሚያቅድ ከፍ ያለ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡
በባሕርይው ምሉዕ በኩለሔ የሆነው አምላክ ያረገው እኮ የባሕርያችን የእኛን ከፍታ ለመግለጽ እንጂ እርሱማ ሁልጊዜም ልዑል ነው፡፡ በሁሉም ያለ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የተሸከመ እርሱ ነው፡፡

እንግዲያውስ ከዕርገቱ ከፍታን እንማር፡፡ የአነጋገር፣ የአስተሳሰብ የውይይት ባሕል ዝቅታ ይብቃን፡፡ ከወረድንበት አዲስ እንጦሮጦስ እንደምንም ተጎትተን እንውጣ፡፡
ከደንቁርና አዘቅትም ተንደርድረን እውጣ፡፡ ታላቂቱን ቤተ ክርስቲያን በእኛ ደንቁርናና አለማወቅ፣ አለማሰብና አለማቀድ አናሰድባት፡፡

ትልቅ ገደል ውስጥ መሆናችን ተገንዝበን ወደ ላይ ለመውጣት ከፍ ለማለት እንጣጣር፡፡ ከፍ ያደርገን ዘንድ ዐርጓልና ዝቅ ማለት ይበቃን፡፡ እንኳን ለዕርገተ እግዚእ  አደረሳችሁ፡፡

በራስ_መተማመንን (Self Confidence)


በራስ_መተማመንን (Self Confidence) ለማሳደግ የሚረዱ አስር ሙያዊ ምክሮች

 ለራስዎ ያለዎት ከፍ ያለ ግምት ሌሎች እርስዎን የሚያዩበት መንገድ ጥሩ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና አለው። በራስ የመተማመን ስሜት ሲኖርዎትም በተሰማሩበት ሥራ ላይ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ እርዳታ አለው።
ምንም እንኳን በራስ መተማመን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩት ምክንያቶች ብዙዎቹ ከእርስዎ ቁጥጥር ውጭ ቢሆኑም፣ በራስ መተማመንን ለመገንባት የሚረዱ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ። እነዚህን 10 ስትራቴጂዎች በመጠቀም ያልዎትን በራስ መተማመን ከፍ አድርገው ችሎታዎን በትክክለኛው ሁኔታ ሥራ ላይ ማዋል ይችላሉ።

1. አለባበስዎ ጥሩ ይሁን (Dress sharp)።
የእርስዎ አካላዊ ገጽታ እና አለባበስ ላይ ከማንም ሰው በላይ እርስዎ የቀረበ እይታ እና ግንዛቤ አለዎት። ስለሆነም፣ ጥሩ ሆነው እንደማይታዩ በሚሰማዎት ጊዜ፣ ከሌሎች ጋር የሚያደርጉት የሃሳብ ልውውጥ ሂደት ውስጥ ምቾት እንዳይሰማዎት ያደርጋል። ስለራስዎ ገፅታ ግን መልካም አመለካከት ሲኖርዎ ምቾትዎ ይጠበቅና ከሰዎች ጋር የሚያደርጉዋቸው ግንኙነቶች ላይ ልበ ሙል ይሆናል። የራስ ገፅታን ጥሩ ለማድረግ የሰውነትን እና የገላን ንፅህና መጠበቅ፣ ፀጉርን እና ፂምን በቅጡ መከርከም እንዲሁም በወቅቱ ተቀባይ የሆኑ ፋሺኖችን በማዎቅ እና አቅም በፈቀደ መልኩ መከተል ይረዳል። ይህ ማለት በልብስ ላይ ብዙ ገንዘብ ማውጣት አለብዎት ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ ብዙ ርካሽ ልብሶችን ከመግዛት ይልቅ፣ ጥቂት የተመረጡ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች መግዛት አለባበስን ጥሩ ለማድረግ ከመርዳታቸውም በላይ ለረጅም ጊዜ ዘመናዊ ሆነው እንዲቆዩ ስለሚያደርጉ ረዘም ላለ ጊዜ ወጪን ይቀንሳሉ።

«ደስተኛ ሕይወት»

ከጭንቀት ነፃ የሆነ «ደስተኛ ሕይወት» ለመኖር ወሳኝ የሆኑ #አሥር_የሕይወት_መርሆች

1. እራስህን ከሌላ ሰው ጋር አታፎካክር፦ ሁላችንም እንደ አሻራችን ሁሉ ባህሪያችን እና ፍላጎታችንም በጣም ይለያያል። ደስታን ከሚያጠፉ ምክንያቶች አንደኛው እራስን ከሰው ጋር ማፎካከር ነው።

2. አትኩሮትህ በሌለህ ነገር ላይ ሳይሆን ባለህ ነገር ላይ ይሁን፡- ደስተኛ ለመሆን ሁሉም ነገር ሊኖርህ አይገባም። በደንብ ካስተዋልከው አሁን ያለህ ነገር ደስተኛ ለመሆን በቂ ነው። ምክንያቱም አንተ ያለህን የሚመኙ ምስኪኖች ብዙ ናቸውና።

3. እራስህን ሁን፦ በዚህ ምድር ላይ ሌላውን ለመምሰል እንደመሞከር ከበድ ነገር ምን አለ? እውነተኛ ወዳጆችህ አንተን ባንተነትህ ይቀበሉሃል…..ከምንም በላይ እራስህን በመሆን ከራስህ ጋር ሰላም ፍጠር፡፡

4. ሁሉን ለማስደሰት አትሞክር፦ አንድ ነገር ስታደርግ ሰዎች ደስ እንዲላቸው ብለህ ሳይሆን ትክክለኛ እና አንተ ያመንክበት ነገር ስለሆነ ይሁን። ለሰው ሳይሆን ለህሊናህ ኑር።

5. የውሸት ደስታን አትፈልግ፦ በውሸት ደስታና በእውነተኛ ደስታ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። የውሸት ደስታ ጊዜያዊ በሆኑና ከውጪ በምናገኛቸው ነገሮች የሚመጣ ሃዘናችንን ለጊዜው የሚጋርድ ጊዜያዊ ማስታገሻ ሲሆን እውነተኛ ደስታ ግን ሃሳባችን፣ አላማችንና ምግባራችን ሲጣመር የሚፈጠር ስሜት ነው። ሃዘን እና መከራችንን ሳንደብቅ የምንጽናናበትም ነው፡፡

6. ማንን እንደምታገኝ አታውቅምና ለሁሉም ሰው ቅን ሁን፦ ሰዎችን አትና፤ በየትኛውም አጋጣሚ ለምታገኛቸው ሰዎች ትክክለኛውን ነገር አድርግ፡፡

7. መለወጥ የማትቻለውን ነገሮችን ተቀበላቸው፦ ከአቅምህ በላይ በሆኑ ነገሮች እራስህን አታስጨንቅ። ከአቅምህ በላይ የሆነውን ነገር ለአምላክህ/ለፈጣሪህ ስጠው።

8. የራስህ እውነተኛ ወዳጅ ሁን፦ ራስህን መውደድ ተለማመድ፤ የሚገርመው ሰዎች እራሱ ሊወዱህ የሚችሉት አንተ በመጀመሪያ እራስህን መውደድ ስትችል ነው። እራስህን ሲያጠፋ ይቅር በማለት፣ ሲደክም በማበርታት፤ ሲሳካለት በማሞካሠት ተንከባከበው፡፡

9. መልካም አስብ መልካም ተናገር፦ በመጀመሪያ ሰው ያስተሳሰቡ ውጤት መሆኑን እመን፤ አሁን የምንኖረው ህይወት ያመለካከታችን እና ያስተሳሰባቸን ውጤት ነው። ይህን ካወቅክ አስተሳሰብህን በጥንቃቄ አጢነው። ደስተኛ ለመሆን የተመረጠ አስተሳሰብ ሊኖርህ ይገባል።

10. ለምን እንደምትኖር እወቅ፦ ህይወት ማለት የተሰጠህን ሃላፊነት ለመጨረስ የተሰጠችህ ጊዜ ናት። ሃላፊነትህ ምንድን ነው? በህይወትህ ማድረግ የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው? መልሱን ካወቅክ ለህይወት ያለህ አመለካከት ይቀየራል፡፡

📌❇️ ደስተኛ ህይወትን ለሁላችንም ይስጠን ! መልካም የጤና ጊዜ!!!

ምንጭ - (ቶማስ እንደፃፈዉ፣ ፅሁፉ ከዶክተር አለ የተወሰደ)

እያንዳንዱ ትልቅ ነገር ትናንሽ መነሻዎች አሉት

እያንዳንዱ ትልቅ ነገር ትናንሽ መነሻዎች አሉት

ተፈጥሮ በኡደት (Process) የተመላች ናት፡፡ ዘመናትን በጊዜ ቀመር አስልታ ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ታሻግራለች፡፡ የኡደት ስሌትዋ ከትልቅ ወደ ትንሽ ሳይሆን ከትናንሽ ወደ ትላልቅ የሚያመራ ነው፡፡

የሰው ልጅ የዕድገት ለውጥ ዓላማ በተፈጥሮ የወረሰውን እምቅ ኃይል ከከፍተኛ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው፡፡ ኤልሳቤጥ ሃርሎክ የተባለች የሳይኮሎጂ ምሁር እንደገለጸችው ሰዎች በአእምሮ ፤ በአካል ከሌሎች የተሻሉ ሆነው ለመገኘት የሚያደርጉት ጥረት ወደ ዕድገት ለውጥ ግብ ለመድረስ የሚደርጉት ጥረት ስለሆነ እነዚህን ጥረቶቻቸውን እውን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

እዚህ ላይ ትልቁ ጉዳይ ሰዎች እራሳቸውን ለማሻሻል እምቅ አቅምና ችሎታ ካላቸው ከወዴት ነው የሚጀሚሩት የሚለው ነው፡፡ ብዙዎቻችን በስራችንና በህይወታችን የምንፈልገውንና የምንሻውን ያህል ውጤታማ መሆን ያልቻልነው ዕቅዶቻችንንና ስኬቶቻችንን ከታች ከትንንሽ ነገሮች ስለማንጀምራቸው ነው፡፡ ቀድሞ የሚታየን ትልቁ ስዕል እንጂ ወደ ትልቁ የስኬት ጎዳና ለመድረስ ከትንሽ ነገር መጀመር እንዳለብን አንገነዘብም፡፡ ከዚህ በታች ከትንንሽ ነገር ተነስተን ወደ ትልቁ ስኬት ለመጓዝ የሚረዱንን ነጥቦች እንመለከታለን፡፡

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...