እሑድ 13 ኤፕሪል 2014

ሆሳዕና በአርያም

ሆሳዕና በዓብይ ፆም ሰባተኛዉ ሳምንት ሲሆን ሆሳዕና ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠዉ ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነዉ፡፡ስለሆሳዕና ከወንጌላዉያን ከሉቃስ በቀር ሶስቱም ወንጌላዉያን ፅፈዉ እናገኘዋለን፤ ማቴዎስ 21 ቁጥር 9-15፤ማርቆስ 11 ቁጥር 9 እና ዮሐንስ 12 ቁጥር 13 ናቸዉ፡፡
የእስራኤል ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ ‹‹ሆሣዕና›› በማለት እየጮሁ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አጅበዉ ተቀብለዉት ነበር፡፡ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ ከኢየሩሳሌም አቅራቢያ ሲደርስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ከፊት ለፊታቸዉ ከምትገኝ መንደር ልኮ አህያ እና ዉርንጫ ከታሰረችበት ፈተዉ ይዘዉለት እንዲመጡ አዘዛቸዉ፡፡ አህያይቱን ይዘዉለት በመጡ ጊዜ ‹‹እነሆ ንጉስሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በዉርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ›› ትንቢተ ዘካርያስ 9 ቁጥር 9 እንደተባለዉ በአህያይቱ ጀርባ ላይ በመሆን ወደ ከተማይቱ ገባ፡፡
ኢየሱስ ወደ ከተማዉ ሲገባ (ከኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ድረስ አስራ ስድስት ምዕራፍ ተጉዟል፤ አስራ አራቱን በእግሩ ሲጓዝ ሁለቱን ምዕራፍ ግን በሁለቱ አህያ ጀርባ ላይ በጥበብ በአንድነት ተቀምጦ ሄደ፡፡) ህዝቡ ልብሱን ከአህያዉ ጀርባ ላይ አድርጎለት እና እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ የለባትም ብለዉ የዛፍ ዝንጣፊ በየመንገዱ እያነጠፉ ተቀበሉት፤(የዛፍ ቅጠል አይደለም የሰሌን ዝንጣፊ ነዉ ቢሉ አብርሃም ይስሐቅን፣ይስሐቅም ያዕቆብን፣በወለዱ ጊዜ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ አመስግነዋልና እስራኤላዉያንም ሆሳዕና በአርያም እያሉ በነሱ ልማድ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘዉ አመስግነዉታል፡፡ ስለምን በሰሌን ቅጠል/ዘንባባ ይዘዉ አመሰገኑት ቢሉ ዘንባባ እሳት አይበላዉም ለብልቦ ብቻ ይተወዋልና አንተም ባህሪህ ረቂቅ የማይመረመር ነዉ ሲሉት ነዉ፤ ) ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ ህዝቡ ‹‹ይህ ማን ነዉ?›› እያሉ ሲጠይቁ ነበር፡፡ ገሚሲቹም የፊቱን ወዝ አይተዉ ‹‹ነቢይ ነዉ›› ሲሉም ተደምጠዋል፤ … ኢየሱስም ወደ ከተማዉ ከገባ በኃላ ወደ ቤተመቅደስ ነበር ያመራዉ፡፡(በአህያ ጀርባ ላይ ሆኖ ቤተመቅደስን ሶስቴ ዞሮዋል፤)‹‹ … ወደ መቅደስ ገባና (ብሩን ለወርቅ ወርቁን ለብር የሚለዉጡበትን ሥፍራቸዉን አፈረሰባቸዉ፤ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአልና እናንተ ግን የወንበዴዎች ጋሻ የሌባ ዋሻ አደረጋችኋት›› አላቸዉ፡፡ ገበያ የተሠረቀዉን የተቀማዉን ይሸጡበታልና እንዲህ አለ፡፡
( በዚህ ጊዜ የተፈፀመዉ ምሥጢራት በቤተክርስቲያን አባቶች ሲነገር አስራ ስድስቱ ምዕራፍ አስሩ የአስርቱ ቃላት፣ አራቱ የኪዳንት ሲሆን እነሱም፡- ኪዳነ ኖኅ፣ክህነተ መለከ ጼዴቅ፣ ግዝረተ አብርሃም እና ጥምቀተ ዮሐንስ ናቸዉ፡፡ ሶስቴ ቤተመቅደስን መዞሩ የስላሴ ሶስትነት ምሳሌ ነዉ፡፡ )
በመቅደስ ቆይታዉ ዓይነ ሥዉራንንም ፈዉሷቸዉ ነበር፤ … ህጻናትም ‹‹ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ›› እያሉ አመሰገኑት፡ አመሻሽ ላይም ትቷቸዉ ቢታንያ ሄዶ አደረ፡፡
ኢየሩሳሌም፡- ከባህር ወለል በላይ 750 ሜትር ገዳም ከፍ ብላ የምትገኝ ከተማ ናት፤ የስሟ ትርጓሜ ‹‹የሰላም ከተማ›› ማለት ነዉ፡፡
የእስራኤል ህዝብ፡- አስራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ቤተሰብ ናቸዉ፤እስራኤል ማለት ያዕቆብ ማለት ነዉና ህዝቡ በሱ ስም ይጠራል፡፡
በአህያ ላይ መቀመጡ፡- ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ነዉ፤ምሳሌዉ ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብዕ/መጥፎ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠዉ፡ ዘመኑ የሰላም የሆነ እንደሆነ ደግሞ በአህያ ተቀምጠዉ መነሳንስ ይዘዉ ይታዩ ነበርና የሰላም ዘመን ዘመነ ምህረት መጥቷል ሲል በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ጌታ ራሱ ሰላም ሆኖ ሳለ እንደምን በአህያ ላይ ተቀምጦ መጣ ቢሉ ምሥጢሩ ባህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝምና፤ እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነዉ በአህያ ላይ ተቀምጦ መምጣቱ፡፡ አንድም ነቢያት ደመና እየጠቀሱ፣ በእሳት ሰረገላ፣ በመርከብ ሲጓዙ ታናሽ በሆነች በአህያ ተቀምጦ መምጣቱስ እንደምን ነዉ ቢሉ ንጹሐን በሆኑ ታናናሾች አድሬባቸዉ ኖራለሁ ሲል ነዉ፡፡
የሁለቱ አህያ ምሳሌነት ደግሞ ትልቋ ሸክም የለመደች የምትጫን ስትሆን ትንሿ ደግሞ ሸክም ያለመደች መሆኗ ትልቋ ህግን መሸከም የለመዱ የእስራኤል ምሳሌ፣ ትንሿ መሸክም ያልጀመረችዉ ደግሞ የአህዛብ ምሳሌ ነች፡፡ አህዛብ ሕግ መጠበቅ ያልለመዱ ናቸዉና፡፡ አንድም ትልቋ መሸከም የለመደችዉ የኦሪት መተግበር የተለመደዉ የሕገ ኦሪት ምሳሌ ሲሆን ትንሿ ደግሞ መሸከም ያልመድችዋ መተግበር ያልተለመደዉ የአዲስ ኪዳን ሕግ ምሳሌ ናት፤
የአህያ ከእስር መፈታት፡- ሰዉ ሁሉ ከማዕሰረ ሃጥያት ተፈተዉ መምጣታቸዉን ለማጠየቅ የተደረገ ምሥጢር ነዉ፤ እስራኤል ዘነፍስ  የተባልን እኛን ከሃጥያት ቁራኝነት ሊፈታን በአህያ ዉርንጫ ላይ ተቀምጦ መጣ፡፡
ልብሳቸዉን ከአህያዋ ጀርባ ላይ ማድረጋቸዉ፡- ኮርቻ ስለሚቆረቁር ጨርቅ/ልብስ አይቆረቁርምና የማትቆረቁር ህግ ልሰራላችሁ መጣሁ ሲል ነዉ፤ አንድም ልብስ የሰዉነትን ነዉር እንዲሰዉር አንተም ከባቴ አበሳ ነዉራችንን የምትሰዉር ነህ ሲሉ ልብሳቸዉ አነጠፉለት፡፡
ሆሳዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ እያልን እናመሰግንሃለን፤ ለክብርህ ይሆን ዘንድ ልብሳችንን አዉልቀን እናነጥፋለን … ዘንባባ ይዘንም እንቀበልሃለን፡፡አበሳችንን ልትደመስስ ራስህን ዝቅ አድርገህ የመጣህልን ልዑለ ባሕሪ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን! በቤተመቅደስ ተገኝተህ ቤትህን ከሌቦች ዋሻነት እንዳፀዳኸዉ እንዲሁ ዛሬም በቤትህ ተገኝተህ ሌቦችን ከቤተመቅደስ አስወጣልን፡፡ በስምህ እየነገዱ በስምህ ጥቅም የሚያጋብሱትን፣ ከአስመሳይ አገልጋዮች ሰዉረን ፣  ቃልህን ባስተማሩ በአጸፋዉ ገንዘብ የሚጠይቁትን ቃልህን ከመዳኛነት ወደ ገንዘብ ማጋበሻነት የቀየሩትን አስታግስልን፡፡ ስምህን መነገጃ ያደረጉትን ስመ አምላክ ነጋድያንን ልብ ስጣቸዉ፤ ከተያዝንበት የሃጥያት ቁራኝነት ፍታን፣የአህያይቱን ትንሽነት ሳትንቅ በጀርባዋ ተቀምጠህ ወደ ቤተመቅደስ እንደገባህ አሁንም ጌታ ሆይ በሃጥያት መተዳደፉችንን ተመልክተህ ሳትንቀን በልባችን ንገስበት፣ ህጻናት እና ድንጋይ እንዲያመሰግኑህ የፈቀድክ ለምስጋና አንቃን፣ እንድናመሰግንህ ፍቅርህን በልቦናችን ምስጋናህን በአንደበታችን አሳድርብን፡፡
ሆሳዕና በአርያም! ጌታ ሆይ አሁን አድነን! ጌታ ሆይ ጤናችንን አሁን መልስልን!


ዓርብ 11 ኤፕሪል 2014

ቴሌና መብራት የዘመን መቀሶች

አሁን አሁን ትናንት ተገናኝተን ዛሬ ስንገናኝም ጭምር ሳይቀር ጠፋህ/ሽ መባባል ባህላችን እየሆነ እንደመምጣቱ ያህል ተገናኝተንም ስንለያይ ስልክ እንዳለዉ እንኳን እርግጠኞች ሳንሆን ‹‹ደዉላለሁ›› መባባሉን እንደ ቻዉ እየቆጠርነዉ መጥተናል፡፡ እንደዚያ ሲሆን እኔም የዚያዉ አካል ነኝና ትናንት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አብረን አመሽተን ከተለያየን በኃላ ካልሸኘሁሽ/ህ ሳንባባል ተለያይተን ሁለታችንም ወደ ታክሲ መያዣችን ተበተንን፤ (ተበተኑ አይደል የሚለዉ ፌዴራል ፖሊስ ሁለት ሆነን ስንቆም እኔም በቅጂ አማርኛዉን ተጠቅሜያለሁ፤) እኔም መንገዴን አጋምሼ ሁለተኛዉን ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝን የህዝብ ትራንስፖርት ከያዝኩ በኃላ ትራንስፖርት አግኝታ ወደቤቷ መግባቷን መጠየቅ ስለነበረብኝ ደወልኩ፤ የባጡን የቆጡን እያወራን መግባት አለመግባቷን ሳልጠይቅ ስልኩ ተቋረጥ፡፡ ብለዉ ብሰራዉ የቴሌ ኔትወርክ ሞቼ እገኛለሁ እናንተን ካገናኘሁ ብሎ ድርቅ አለ፤ አንዴ ‹‹የደወሉላቸዉን ደንበኛ ማግኘት አይችሉም›› ስትለኝ፣አንዴ ‹‹መስመሮቹ ሁሉ ለጊዜዉ ተይዟል›› ስትለኝ ፣ ተማርሬ ቆይቼ ደዉላለሁ ብዬ ተዉኩት …. ቆይቼ ለመሞከር ባስበኩት መሰረት የስልኬን ቁልፍ ከፍቼ ስሞክር ጢጢጥ እያለ ዝግት ፣ጢጢጥ እያለ ዝግት …. ነገሩ አልገባህ ሲለኝ ተዉኩት፡፡ እንዲህ እና እንዲህ እያልኩ ወደ ሰፈር ስቃረብ ይባስ መብራትም ጠፍቶ ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› አይደል የሚባለዉ ‹‹እንኳንም እናቴ ሞታብኝ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል›› ያለዉ ቴሌ እንኳንስ መብራት ኃያል መብራት አጥፍቶበት እያለም በቅጡ የማይሰራዉ የቴሌ ኔትወርክ ከጓደኛዬ ጋር እንዳንገናኝ ለያቶን አደረ፡፡
መቸስ እግዚአብሔር እንደ መብራት ኃይልና እንደ ቴሌ አይደለምና የጨለማዉን አስፈሪ ግርማ ሞገስ በብርሃን ተካዉና ቀኑን በብርሃን ሞልቶ ዛሬን በሰላም አገኘናት፤ ‹‹ጥረህ ግረህ የላብህን ወዝ ብላ›› ተብለናልና ቀኑን ሙሉ ላይ ታች ስንል ዉለን ከስራ መልስ፡፡ መቸስ ቴሌን ትላንት ለያይተኸናል ብለን አናኮርፈዉ ነገር ባቆራረጠን መስመር ዳግም ለመገናኘት የሞባይሌን ቁልፎች ተጭኜ
 ‹‹ሃሎ!›› አልኳት ጓደኛዬን 
ሃሎ! አልችኝ ርቀቱ የዉጭ ስልክ እስኪመስል ድረስ በሚርቅ ድምፅ (ሰሞኑን ‹አይሰማም› ሆኗል፤ የቴሌን ኔትወርክ የለከፈዉ ልክፍት፤ ለመሆኑ 75 አካባቢ ምናምን አጠናቀኩ ያለዉ በፊት የሚሰሩትን አቋርጦ ነዉ ወይስ ለማይሰራላቸዉ ሰርቶ ነዉ ያጠናቀቀዉ? ካካካ ….. )
ሃሎ ብለን የጀመርነዉን ሃሎ እያልን እንዳይቋረጥብን ወደ ገደለዉ እንደመግባት ትላንት የተቋረጠበትን ሁኔታ አንስተን የተቋረጠዉ በኔትወርክ ምክንያት እንደሆነ፣ እቤት ስገባ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት እንዳልደወልኩ፣ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባይኖረዉም በሳምንት ይመጣልን የነበረዉ ዉሃ ሳይመጣ እንደቀረ ሳወራት በስርአት ስታዳምጠኝ ከቆየች በኃላ መጨረሴን ስታዉቅ እንደጋዜጠኛ ‹‹እንግዲህ ያሉትን ሁሉ ምሬት እና አቤቱታ የሚመስል አስተያየት ሰምተናል በእርግጠኝነት የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች በሰፈራችሁ የተከሰተዉን ችግር የኔትወርክ መቆራረጥ፣የመብራት በተደጋጋሚ መጥፋት፣የዉሃ ችግር …. ሰምተዉ መፍትሄ እንደሚሰጧችሁ እርግጠኖች ነን…. ስለደወሉ እናመሰግናለን!›› ብላ ፍርስ ብላ ሳቀችብኝ፤ እሷም እየሳቀች ወደ ቤቷ እኔም ሳወራ የቀለለኝን ድብርት ይዤ ጨለማ ወደ ነገሰበት ሰፈሬ፡፡
በአገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ያላችሁ ወገኖቻችን ለትንሣኤ በዓል ደዉላችዉ ምናልባት ቴሌ ካገናኘን ‹‹የእንኳን አደረሳችሁ›› ምኞት መግለጫችሁን ስታስተላልፉ እኛ ስለ ስልክ እና መብራት መቋረጥ ብናወራችሁ አደራችሁን ቅር እንዳትሰኙብን! ከወዲሁ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ ምን እናድርግ መንግስት አልሰማ ቢለን ለመንገደኛዉ ሁሉ እናወራ ጀመር እግረ መንገዱን መንግስት ጆሮ ይደርስ እንደሆነ ብልን፤ መንግስትም ቀጥታ ከምንነግረዉ በሃሜት መልኩ የሚወራዉን መስማት የጀመረ ይመስል ቀጥታ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ነፍጓል፡፡
መንግስታችን ለብቻችን ሆነን ያወራነዉን ነገር እምቢ ስላልከኝ ይኸዉ ሰዉ ፊት ታዛቢ አስቀምጬ ነዉ የምነግርህ እኛ ሰፈር ዉሃ፣መብራት፣ ስልክ …አማሮናልና መላ በለን! ድሮ ‹‹ወጥ እና ወንድም ማስፈራሪያ ነዉ›› እየተባልን ነበር ያደግነዉ አሁን ግን እራት ሰዓት ላይ ሻማ ይለኮስና አለበለዚያም የአንደኛችን የሞባይል ብርሃን ተጠቅመን እራት ስንበላ ዉሃ ቀርቦልን ‹‹ብርሃንና ዉሃ … ማስፈራሪያ ነዉ›› እንባል ጀምረናል፡፡ እንዲያዉም ሌላ ሰፈር እንደሰማሁት በእኛ ጊዜ ቀን  ላይ ስናጠፋ ማታ ጨላማ ሲሆን በር ተዘግቶብን በጨለማ ጨለማ ላይ በመቆም እንቀጣ ነበር፤ ዛሬ ይኸዉ ‹‹ደግ›› ልበለዉ እንጂ ደግ ዘመን ላይ ስንደርስ ህፃናት በመብራት/በብርሃን ይቀጡ ጀምረዋል ‹‹መብራት አብርቼ ነዉ የማስቀምጥህ እየተባለ›› አሉ፡፡ ብርሃንም እንደ ድሮ ጨለማ ለማስፈራሪያ ሆነ ሲባል ሰምቻለሁ… አቤት መጨረሻችን …እግዚኦ!
ምን እንደምፈራ ታዉቃልችሁ ዛሬ መብራት ሰፈራችን የለም፣ ዉሃ ተረኛ አይደለንም እንደምንለዉ ሁሉ ፈጣሪ የአፌን አይቁጠረዉና ዳቦ፣ እንጀራ፣ ጤፍ፣ስንዴ፣ሽንኩርት፣ዘይት …. ገበያ ላይ የሚገኙት በወረፋ እንዳይሆን ነዉ፡፡ ፈጣሪ ክፉዉን አርቆ ደጉን ያቅርብልን!
መብራት ኃይልን እንደ ቴሌ ፈርሶ በመሰራት ሰበብ ህዝቡን አያሳቁብን!(እንደምርቃት ነገር ስለሆነ አሜን እንበል ጎበዝ የደረሰበት ያዉቃልና እንኳን ፈርሶ የሚሰራ መስሪያ ቤት ፈርሶ የሚሰራ ቤት ራሱ በጣም ችግር አለዉና፤) በየሄድንበት ሁሉ ስለ ዉሃ፣መብራት እና ኔትወርክ መጥፋት የምናወራበት ሳይሆን አገራችን ነዳጅ አግኝታ ስለሱ የምናወራበትን ዘመን ያቅርብልን! (አሜን!)
የአባይ ግድብ በጠንካራ ክንዳችን ተገንብቶ መብራት ከሚጠፋበት ይልቅ የምንሸጥበትን ቀን ቅርብ ያድርገዉ! (አሜን!)
 ሳንቲም የሚሸጡ ልጆች ወልደን ከማሳደግ አገራችን ኢኮኖሚዋ ጣሪያ ነክቶ ለዜጎቿ የዜግነታቸዉ የምትከፍል አገር ያድርግልን!(አሜን!)
ዜጎቿ ተሰደዉ ሞቱ፣ገደሉ፣ራሳቸዉን አጠፉ፣ሲሰደዱ በረሃ ላይ ሞቱ፣ …. ከመባል ተላቀን ምዕራባዊያን ፣ አዉሮፓዉያን በዲቪ የሚመጡባት፣ ስራ አጥ በዛብን ብለዉ ለስራ ፍለጋ የሚሰደዱባት ያድርግልን!(አሜን!)
መንግስት ለመገልበጥ፣ ስልጣን ለመንጠቅ፣ … ብለን ከመሯሯጥ እግዚአብሔር ሰዉሮን መሪዎቻችን የስልጣን ዘመኔ ተጠናቋል የሚተካኝን መሪ ምረጡ ብሎ ለምርጫ ቦርድ ሲያሳዉቅ ‹አንተዉ ምራን›፣ ተመችተኸናል እባክህ አንድ የስልጣን ዘመን ድገም ‹‹በሞቴ አፈር ስሆን›› ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ስልጣን መልቀቁን የምንቃወምበት፣ የሰልፍ ፍቃድ የምንጠይቅበትን  ዘመን ፈጣሪ ያምጣልን!(አሜን!)  

ዘመናችንን እንዳናጣጥምበት መቀስ የሚሆኑብንን እግዚአብሔር ያርቅልን!(አሜን!)

ዓርብ 4 ኤፕሪል 2014

ክፍል ሁለት ….. …. አጋጣሚ፤

ባለፈዉ  በ " ክፍል አንድ " የአንዲትን ወጣት የህይወት አጋጣሚ በራሷ አንደበት ስትተርክልን እንደነበረ ክፍል አንድን የተከታተለ የሚያስታዉሰዉ ነገር ነዉ፤ዛሬም ቀጣዩን የህይወቷን አጋጣሚ እንዲህ በአንደበቷ ታጫዉተናለች፡፡ መልካም ንባብ!
እንግዲህ የአጋጣሚ ነገር የት እንደሚጥል አይታወቅም አሁን ሳወራህ በህይወቴ ያሳለፍኳቸዉ ነገሮች ሁሉ ህልም ነዉ የሚመስሉኝ፤
በዕድሜዬ ሁለት አስርት ዓመታትን ሳስቆጥር በሰፈርና በሃይስኩል እንዲሁም ብዙ የፍቅርም የጥላቻም የሃዘንም ገጠመኞች አሉኝ፡፡ እንደ ፍቅር ግን ሬት የለም ሬት! እዉነቴን ነዉ የምልህ ፍቅር ሬት ነዉ! ሰወች የት አባታቸዉ አይተዉ ስለጣፋጭነቱ እንደሚያወሩኝ አላወቅም፤ ምናልባት የፍቅር ህይወታቸዉን በተገላቢጦሽ የኖሩ ሰወች እዉነት መስሏቸዉ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰወች ስንባል ይልቁንም ሴቶች የሌላኛዉን የወንዱን ማለቴ ነዉ ህይወት ስለማንኖርለት፣ ህመሙን ስለማንታመምለት፣ ስቃዩን ስለማንሰቃይ ነዉ እንጂ አጋራችን/ፍቅረኛችን እኮ በኛ በሴቶች የተነሳ ሙት ነዉ! የለምኮ ሞቷል! በድኑኮ ነዉ አጠገባችን የቆመዉ…. … ፤ ለሞቱ ደግሞ ተጠያቂዎቹ እኛዉ ነን፡፡
የአሻራ ምርመራ የለም እንጂ በነፍሱ ዉስጥ፣ በደሙ ዉስጥ፣ በስራስሮቹ ፣ ከኪሱና በዋሌቱ ዉስጥ ተጣብቀን ደሙን የመጠጥን እኛ ነን፤ ሴቶች …. … ግን የዋሁ ወንድ ነገር ተገላብጦበት ህይወት አደንዝዛዉ ያለእኛ መኖር እንደማይችል በበድን ምላሱ ለሃጩን እያዝረበረበ ይነግረናል፤ እኛም ሰምተን እንዳልሰማ ይህ ደምፅ የሙት ነዉ ብለን ሳንቃወም ስጋዊና ደማዊ ሰዉነታችን በሙቀት ይቀልጣል፡፡
ዉዴ! ነፍሴ! ማሬ! ሃኒ!.... በሚሉ ጉንጫልፋ ቃላት እያንቆለጳጰሰን እኛን ሲያጣ መኖር እንደማይችል፣ ነፍሱ እንደምትወጣ ያለመጠራጠር ያወራል…. የሞተዉኮ ገና ከሴት እንደተገናኘ ነዉ…. አላወቀም እንጂ ሞትኮ ወደ ገነት ዘዉ ብሎ የገባዉ …. አዳምን ጠርንፎ ከገነት ያስወጣዉ …. ቁልቁል ተዘቅዝቆ ሱባኤ የገባዉ … ወንድነቱን ሁሉ ረስቶ እንደ ሴት ለነገሩ ያኔ ሴት አልነበረችም  የማያዉቀዉን ማንባት የተለማመደዉ ሔዋን ከመጣች በኃላ ነዉ፡፡
… … …
የድሮ ልጆችኮ እየተባለ ይደሰኮራል እንጂ ድሮኮ ነበር ገና ተማሪ ቤት ሲከፈት በእንቁጣጣሽ ጭፈራ ያገኘናትን ድቃቂ ሳንቲም በመያዝ አይናችን የገባዉን ጠጠር ከረሜላ፣ የጉንፋን ከረሜላ እና ድቡልቡሏን ማስቲካ በመግዛት ወንዶችን ስናማልል የነበረዉ፤ ማን አለ አሁን ይህን ዘመን በክፉ የሚያነሳ? ማንም! … ታዉረን ስለነበረ ነዉ ምክንያቱ! እና ግን ከዛን ጊዜ ጀምሮ በዛ ጨቅላ አዕምሮ ነበር ወንዶችን የምናጠምደዉ …. … ካካካ ….(ደማቅ ሳቅ)

ተማሪ ቤቴ



ተማሪ
ቤቴ


የማሪያም መቀነት በሰማይ ላይ ዉበት ፈጥራ በ..ር……ቀት ያየናት እንደሆነ
እኔ ነኝ እኔ ነኝ…እኔ ነኝ… በሚል በፍቅር እንጋጫለን እኔ ነኝ ቀድሜ ያየሁት ለማለትና የቀዳሚነቱን ስፍራ ለማግኘት፤(በሰማይ ላይ ይታዩ የነበሩ የቃል ኪዳን ምልክቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ላይታዩ የማሉ ይመስል ሰማዩ ጠቁሯል )
ከእንቅልፉ ዘግይቶ የተነሳ ቁርሱን አልበላ ያለ ትምህርት እንዳይረፍድበት ግማሽ ዳቦ ይቆረስና ይዘህ ብረር ይባላል፡፡በትናንሽ መዳፎቹ ብርር…….ርር እያለ እየከነፈ እየበረረ ……እ ….የ ….ቆነጠረ …… እየበላ….. እያስጎመጀን……እየበረረ ወደ እኛ ያቀናል …. ጥላ ስር…… ዛፎቹ…. ጎጆዎቹ ስር….. ….. ልንሰባሰብ ….. ፊደል ልንዘራ ….ልንበትን ልናጭድ ልንወቃ …. ደግመን ልንዘራ……
በርቀት ያየነዉ እንደሆነ ገሚሶቻችን ደስ ሲለን ገሚሶች ደግሞ እንደማብሸቅ ይቃጣናል፤
እንቅልፋሞ … እንቅልፋም …እን…ቅ…ልፋም እንቅልፋም …. እያልን ከፊት ከፊት እንሮጣለን ትንሽ ከኛ አቅሙ ሻል ካለ መግቢያ ቀዳዳ እስኪጠፋን እንሮጣለን (እንደዛሬዉ በሰርቪስ ፣ በኮንትራት ታክሲ ፣ ወላጅ እግረመንገዳቸዉን ጣል አርገዉ መሄድ የለም )
 ከፍሎ እንደ ሚሰጠን ያወቅን ደግሞ ወደርሱ ሮጥ ብለን ያልከፋዉን ሰዉ ለጥቅማችን ስንል አይዞህ በማለት እናባብለዋለን ፤ ከወዳጆቻችን ስለ ዳቦ እንኳረፋለን
አለሁልህ በሚል ስሜት ፀጉሩን እየደባበስን ከጎናችን ሸጉጠን እጅ እጁን እናያለን እርሱም የልማዳችንን የባቄላ ፍሬ የምታክል ዳቦ ቆርሶ ያቀምሰናል(ያሻጽትተናል)
እቺን ብቻ
ቆረስ ያደርግና ይጨምራል
ለኔስ ሌላኛዉ ይጠይቃል
ቆርሶ ይሰጠዋል
ሌላኛዉም ሲበር ይመጣል
ዳቦ የያዘበትን እጆች ወደኋላ ይደብቃቸዋል
ሲሮጥ የመጣዉ ክፍት ይለዉና አይኖቹ እምባ እንደማቅረር ይላሉ

ዋጋ የሚያሰከፍሉ ጥፋቶች!

ትዉልዱ የሚከፍለዉ ነገር ግን ሊከፍለዉ የማይገባዉ ዋጋ! ይህ ትዉልድ ስለ ሃገሩና ስለ ሃይማኖቱ የከፈለዉን ዋጋ ምንም የሚወዳደረዉ የለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከማንም ክርስቲያን ልብ ዉስጥ ከማይጠፉት ከምዕመናኖቿ ጋር የተወጣቻቸዉን ሁለት ክፉ አጋጣሚ እንመልከት፡-
. የዮዲት ጉዲት
.የግራኝ መሐመድ …. እያሉ መቀጠል ይቻላል፤
ነገሥታት እና መንግስታት በመጡ ቁጥር አንዳቸዉም አልበጇትም ሊያስብል በሚችል መልኩ ጠላቶቿ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነትና በሕዝቦቿ አንድነት ግን የተቃጣባትን መከራ ሁሉ ብዙ ዋጋዎችንም ከፍላ ቢሆን ተወጥታዉ እነሆ 21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ደርሳለች ሆኖም ግን ጠላቶቿ እየበዙ ሄዱ እንጂ ወዳጅ አላፈራችም፡፡
እንደ ግራኝ መሐመድና እንደ ዮዲት ጉዲት ቀጥታ በቤተክርስቲያን ላይ ታጥቀዉ አይምጡ እንጂ ጉዳት በማድረሱ ግን (ከሁለቱ ዘመናት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በማቃጠል፣በመዝረፍ፣በማሸሽ፣ቤተክርስቲያንን በማቃጠል፣ካህናትን በማሰር፣በማወክ፣በመግደል …. ) ከትላንት ሳይብስ አይቀርም፡፡ ትላንት ርስት ጉልት የነበራት ቤተክርስቲያን ዛሬ አጥሮቿ እየተነቀሉ ይገኛል፤ ታላላቅ ሃገራዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸዉን ሥራ የሰራች ቤተክርስቲያን ለእነሱ አካሄድ ስላልተመቸች ባሏት ልጆች ዳር ድንበሯን አናስደፍርም፣ የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም ባሉ ….ወዘተ ምክንያቶች ከአሸባሪነት እየፈረጇት ይገኛል፡፡
አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብልህነት ሳይሆን ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነዉ!
ሰዉ ለሚጠቅመዉና ለተጠቀመበት ነገር ዋጋ ይከፍላል፤ መክፈልማ አለበት ህግም ያስገድደዋልና፡፡

ሐሙስ 20 ማርች 2014

Part one “… … አጋጣሚ”

“የህዳር ሚካኤል ካለፈ አንድ ወር ሆኖታል ታህሳስ ከገባ ደግሞ 11ኛ ቀኑ ነዉ እንደከዚህ በፊቱ በፌስ ቡክ እናወራለን፣ ምሥጢሬን ሁሉ ነዉ የምነግረዉ አንድም የምደብቀዉ ነገር አልነበረኝም፤ እህቴ እቤት ዉስጥ የጤና ባለሙያ ሆና ሳለ ትንሽም ራሴን ሲያመኝ በጣምም ምቅቅ ብዬ ጨጓራዬ ሲያሰቃየኝ የማወራዉ ለሱ ነበር፡፡
በጣም እጅግ ሲበዛ በ…ጣ ም ይመክረኛል፣ ያፅናናኛል እኔም ምን እንደሆነ አላዉቅም እፅናናለሁ፣ ወዲያዉ የማላዉቀዉ ጤንነት ይሰማኛል፡፡ በነበረን ጊዜያት አንዴ ብቻ ነዉ የማደርገዉን ነገር ያልነገርኩት እሱንም አስቤዉ አልነበረም በዚያን ጊዜ ሲጠፋብኝ በጣም ቅር አለኝ፤ በነጋ ቁጥር የፀሐይ ብርሃን ሳይሆን የርሱ ድምጽ ነበር የሚናፍቀኝ፣ ስልኬን ስሰጠዉ ምንም ቅሬታ አልነበረኝም ፣ የመኖሪያ ቤቴን ሰፈር ሁሉ ስነግረዉ ደስ እያለኝ ነበር፣ አሁን ግን እነዛ ድምጾቹ የሉም ርቀዉኛል፤ የሚገርመዉ ድምፁን የምናፍቀዉ ኔትወርክ በሌለበት ስፍራ ነዉ፡፡ ተራራ ባየሁ ቁጥር ሞባይሌን እንደ አቅጣጫ መጠቆሚያ ከመዳፌ አላርቃትም ነበር፤አሁንም አሁንም ደጋግሜ አያታለሁ ቻርጅ ባየሁ ቁጥር መሰካት ነዉ ከሞባይሌ ርቄ መሄድ ጥሩ ስሜት ከማይሰሙኝ ነገሮች መካከል ዋነኛዉ ነበር፡፡ ቀናቶች እየነጎዱ ጤናዬም መለስ እያለ ስለመጣ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ፈለኩኝ እንድመለስ ያደረገኝ የጤናዬ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ እሱን የማግኘት ፍላጎቴ ካቅሜ በላይ ስለሆነብኝም ጭምር እንጂ ፡፡ ለነገሩ ወደዚህ ስመጣ ስራዬን ለቅቄ ነበር የመጣሁት ልቤ ግን ክፍል ለማለት ወደኃላ አልል አለኝና አስጨነቀኝ፡፡ደብረ ብርሃን ስደርስ ጭንቀቴ እየጨመረ ሄደ፣ መንገዱ ራቀብኝ፣

ማክሰኞ 18 ማርች 2014

ጊዜና ዘመን

ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ይታሰባል ይከወናል ትናንት ዛሬን እየሆነ ይቆጠራል፤ ትናንትናና ዛሬ ተደማምሮ ሳምንት ሳምንታትና ቀናት ተደማምረው ወራትና ዓመታትን /ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናትን/ ይሰጣሉ፡፡ ከአዳም ጀምሮ ዓመት ይቆጠራል፡፡ የዓመታት ጥርቅም ዘመን ተብሎ ይጠራል ዘመን ረጅም ጊዜ ነው ወይም አንድ አይነት አገዛዝ አምልኮ ሌላም የተደረገበት ጊዜ መጠሪያ ነው፡፡
       ዘመን የተፈጠርንበት /የተወለድንበት/ ትምህርት የጀመርንበት፣ ሥራ የያዝንበት፣ መከራን ያየንበት፣ ከውድቀታችን የተነሳንበት፣ የተማመንበት፣ የተፈወስንበትወቅት ማስታወሻ /መጠሪያ/ ሊሆን ይችላል፡፡
       ወደ ፍሬ ነገሩ ልምጣና ከብዙ ሰዎች አንደበት ስሰማና ከብዕራቸው የዕምባ ጠብቃ ሳነብ ብዙዎች ዘመንና ጊዜን ሲደግፉ በከንቱ ስሙን ሲያጠፉ ሲኮንኑ አዳምጣለሁ አነባለሁ ‹‹አይ ዘመን፣ አይ ጊዜ›› ‹‹ጊዜው ነው፣ ዘመኑ ነው›› ሲሉ ነገር ግን ጊዜና ዘመን ምን አደረገ ምንስ በደለ ጊዜና ዘመን በራሱ ምን ያመጣው ለውጥ ምንስ ያደረሰው ተፅዕኖ አለ? አንዳንድ ፀሐፍት እንደሚሉት ዘመንና አህያ አንድ ነው ይላሉ አህያ እንዳሸከሟትና የጫኑባትን ይዛ እንደምትገኝ ዘመንም

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...