ማክሰኞ 18 ማርች 2014

‹‹ቅዳሴ›› ክፍል -2-

አይነጋ የለ ነጋ ጊዜው 11፡30 ሰዓት ነው የሞላኋት የግድግዳ ሰዓቴ ድምፅ አሰማች እኔም ከእንቅልፌ ነቃሁ ሲረፍድብኝ እንዳላደርኩ ሳይረፍድብኝ ወደ ቅዳሴ ሄድኩ የቀን መዘውሩ ተገባዶ ሌሊቱ ለንጋት ስፍራውን መልቀቁን የተገነዘበ ሕዝበ አዳም ታጥቆ ተነስቷል ፀሐይ የንጋት ብርሃኗን ለመፈንጠቅ ሰማዩን ፏ አድርጋዋለች ነጭ ነጠላ የለበሱ ምዕመን መንገዱን ሞልቶታል አብያተ ክርስቲያናት የጥሪ ደውላቸውን (ድምፃቸውን) እያሰሙ ነው ሱቆችም የአሁኗን ንጋት በጥዋፍና ሻማ ዕጣን ሽያጭ ጀምረዋል ነዳያን ቤተክርስቲያን ጌጥ መስለው ከደጇ በረድፍ ተቀምጠዋል አስቀዳሹ እኔም አላረፈድኩም በሚል ስሜት በርጋታ እየተራመድኩ የደጃፉን በር ተሳልሜ ከግቢው ከመግባቴ ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ …›› የሚለውን የካህኑ ድምፅ በዜማ ተሰማኝ ተፈጥሮ ካስዋበው ከቤተክርስቲያኑ አጸድ ሥር ተጠንቅቄ በመቆም እጆቼን ከላይ ሆኖ ወደሚያየኝ አምላክ በማንጋጠጥ ዘረጋሁ ዙሪያው ጭር ያለው ግቢ በምዕመናን እየተጨናነቀ መጣ የቅዳሴው ‹የተሰጥኦ› ዜማ ሥፍራውን የመላዕክት ከተማ ኢዮር፣ ኤረር፣ ራማን አስመስሎታል የዕጣን የሽታ መአዛ ግቢውን አውዶታል ነፍሳችን እጅግ ተደስታለች ቅዳሴውን የሰማይ አዕዋፍ በድምፃቸው አብረው ሲያጅቡት የበለጠውን ውበት ሰጥተውታል የዕጣን ጢስ ወደላይ ማረግ የተመለከተ ልቡናችን አብሮ ከመንበረ ፀባኦት ደርሷል

‹‹ቅዳሴ››

ያለው ዕለት ለንጋቱ ቦታውን ለመልቀቅ መሰናዶውን ያጠናቀቀ ይመስላል በቤቴ መስኮት ቀዳዳ የሚገባው የንጋት ብርሃን “ነግቷል ተነስ” የሚል ሰው ያህል ከፊት ለፊት በቀዳዳው እየገባ ይጎነትለኛል የጭላንጭሉን ብርሃን ተልዕኮ የሚያጨናግፈው ድብርት “አይዞህ ተኛ ገና ነው” እያለ ያዘናጋኛል፤ አሁንም በመስኮቱ የሚገባው የብርሃን ጭላንጭል ገብቶ ገብቶ ቤቱን በሰፊው ተቆጣጥሮታል፣ አካላቴ ሁሉ ሳምንቱን መንገድ ሲጓዝ እንደከረመ አንጓዎቼ በሙሉ የመዛል ስሜት ይሰማባቸዋል፡፡ ከሁለቱ አንደኛዋ አይኔ ብቻ ብርታት ይሰማታል እንጂ ሁለተኛዋ ጭራሽ የለችም ማለት ይችላል፤ አንደኛው ሲተኛ እርሷ ነቅታለች እርሱን ለመቀስቀስ ባደረገችው ጥረት እርሷም ድካም ተሰምቷት ማሸለብ ጀመረች የሌላት ልብሴን ገላልጣ ለመውጣት ጡንቻዋን ያፈረጠመችው ክንዴ ብርድ ሲያኮማትራት ተመልሳ ከብርድልብሱ ሾልካ ገባች ገና ተመኝታ የተገናኘች ይመስል እንቅልፍ ጣማት በዚያቹ በቀጫጫ ክንዷ ራሷን በራሷ እቅፍ አድርጋ ጋደም እንዳለች የእንቅልፍ ማዕበል ይዟት ጥርግ አለ፡፡ በልቦናዋ በብርቱው ምሽት ያሰበችው የዕለት ሰንበት የቅዳሴ መርሃግብርና ጠዋት በብርሃኑ ጭላንጭል መካከል ትዝ ያላት ልቡናዋን እንደብል በልቶ ጨርሷታል ሰውነቴ ለእንቅልፍ ተማርካ ከሞቀው መኝታዋ በመሆን ቅዳሴን ታስቀድስ ጀመር፤ ልክ ከመቅደሱ ፊት እንደቆመ አስቀዳሽ አሁን ለዛለችው ገላዬ ንፍቁ ዲቆኑ “ጸልዩ በእንተ ያበውኡ መባእ …” የሚለውን አዚሞ ሕዝቡም “ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው” የሚለውን ጨርሶ ዲያቆኑ በድጋሜ “ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት” ብሏል የዛለው ገላዬም “ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ ወንሴብሐከ” ብላ ሰግዳለች

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

የመተው ጥበብ Part 4

  ምን መተው፣ ምን መያዝ፣ እንዴትስ በሰላም መኖር ? ክፍል አራት፦ ያለፈውን መተው — ያለፈው ዛሬህን እንዳይመራ ያለፈው ሕይወታችን አካል ነው። ከዚያ ተምረናል። ከዚያ ተጎድተናል። አንዳን...