ዓርብ 26 ማርች 2021

እግዚአብሔር ያዘዘኝን አደርጋለሁ

 "እግዚአብሔር ያዘዘኝን አደርጋለሁ እንጂ እኔ አዝዛለሁን?"


ሀብተ መርገም እና ሀብተ በረከት የተሰጠው በለአም ለባላቅ የመለሰው ምላሽ ነበረ።


እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ አሕዛብን ድል እየነሱ ሲመጡ በባላቅ ወልደ ሶፎር አገር አጠገብ በሞዓብ ሜዳ በሰፈሩ ጊዜ የእስራኤላውያንን ጥንተ ታሪክ ያውቅ ነበረና እጅግ ፈራ።


ፈርቶም አልቀረ በአሞራውያን ላይ ያደረሱት በርሱና በሕዝቡ እንዳይደርስ በለአምን ና እና ርገምልኝ አለው።


በለአምም እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሰወች እንደሆኑ የተባረኩም ሕዝብ እንደሆኑ ያውቅ ነበረና፣ እግዚአብሔርም አትርገማቸው ብሎታልና ላይረግማቸው ላይሄድ ወሰነ። 


ባላቅም ከአንዴም ሁለቴ ከጥሩ ገንዘብ ጋር ሰው ላከበት ሆኖም በለአም ሳይመጣ ቀረ፤ በመጨረሻም እግዚአብሔር በራእይ ለበለአም እንዲህ አለው " መሔዱን ሒድ ነገር ግን እግዚአብሔር የገለጠልህን ተናገር እንጂ አትራገም" አለው።


እንደሄደም እስራኤላውያንን ከአንዴም ሶስቴ መረቃቸው፥ ባላቅም ተቆጣ። "ርገምልኝ አልኩህ እንጂ መርቅልኝ አልኩህን?" አለው።


"እግዚአብሔር የገለጸልኝን እናገራለሁ እንጂ ሌላ ምን ላደርግ እችላለሁ?" ብሎ በለአም መለሰለት።


በማግስቱም እንዲሁ ሆነ ሰባት ላም፣ ሰባት ዳንግሌ ሠዋለት። በለዓምም እንደ ልማዱ ያሟርት ጀመረ። ነገር ግን ዛሬም መራገም አልተቻለውም።


መጽሐፍም እንዲህ ታሪኩን ያስነብበናል፦ " እግዚአብሔር እንደ ሰው ሐሰት አይናገርም፣ በሠራውም ሥራ አይጸጸትም እኔ እስራኤልን እንድመርቅ ትእዛዝ ተቀብያለሁና በያዕቆብ ክፋት አላይበትም። እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ ጋራ ነውና። በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፣ በእስራኤልም ላይ ሟርተኝነት አይቻልም። ይህ ሕዝብ እንደ አንበሳ ደቦል ነው። ያንበሳ ደቦል የሰበሰውን ሥጋውን ሳይበላ፣ ደሙን ሳይጠጣ እንዳይመለስ ይህ ሕዝብም አሕዛብን ሳያጠፋ አይመለስም" ይለናል 


ባላቅም ያሰበው ባይሳካ ያላሰበው እንዲሆንበት አልፈለገምና  በተስፋ መቁረጥ ውስጥ " መራገም ቢቀር እንኳን ባይሆን መመረቁን አትተውምን? ይህን ሕዝብ ለምን ትመርቀዋለህ?" አለው።


በርእሳችን እንዳነሳነው በለአም መለሰለት፥ " እግዚአብሔር ያዘዘኝን አደርጋለሁ እንጂ እኔ አዝዛለሁን?" አለው።


ድንቅ መልስ ነው።


ይህ ታሪክ በበለአምና በባላቅ መካከል፣ በእስራኤላውያን እና በባላቅ አገር ሰወች መካከል የሆነ የተመዘገበ ቢሆንም ቅሉ የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ግን ቦታ የማይገድበው ጊዜ የማይሽረው ነውና እራሳችንን እንመልከትበት።


እኛ የማንን ፈቃድ እናደርጋለን? የሥጋን ፈቃድ ነው የነፍስን ፈቃድ እንፈጽማለን? በገንዘብ እንገዛለን ለእግዚአብሔር እንገዛለን? እንመርቃለን ወይንስ እንረግማለን?


አለማችን እንዴት ሰነበተች? ብለን በእግዚአብሔር መንፈስ ብንቃኘው  በውኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚሳደብ፣ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ካህናትን እና በቤቱ የሚመላለሱትን፣ እግዚአብሔር የመረጣቸውን እና የቀባቸውን የሚያንጓጥጥ ነው የሞላው ወይንስ የሚመርቃቸው?


የባላቃዊያን ሀሳብ የፈለገውን ቢሆንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሻር አልተቻለውም። እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማንም አይቃወማቸውምና። 



ኢትዮጵያ እና ኢትዮጽያዊያንም እንደዚሁ ናቸው፤። የማንም ሰልፍ አያሸንፋቸውም። የማንም ሟርት እና እርግማን አይደርስባቸውም። አንድነታቸውና ህብረታቸውም የኢትዮጵያን ጉዞ አይገታም። እግዚአብሔር ከርሷና ከሕዝቦቿ ጋር ነውና።


እንደ ፈቃዱ ተመላልሰን የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደተባልን ጸንተን ቆይተን እግዚአብሔር አጥር ቅጥር ይሁነን። ከጠላቶቻችን ይጠብቀን፣ የተቃጣብንን ይመክትልን፣ በመርገም ፈንታ ይመርቀን፣ መውጣት መግባታችንን በአባታዊ አይኑ ይከታተልልን።


የጠላቶቻችንን ዓይን ጨለማ ጉልበታቸውን ቄጠማ ያድርግልን።


በእግዚአብሔር ማመናችን መዘባበቻ ሳንሆን መጽናኛ ይሁነን።


የአባቶቻችን በረከታቸው ጥርጥር የሌለባት ተዋህዶ እምነታቸው በረከቷ ይደርብን።


የተጀመረውን ጾም ሥጋችንን ገዝተን፣ ነፍሳችንን አበርትተን ጠላት ዲያቢሎስን ድል የምንነሳበት የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርስበት ያድርግልን።


@deressereta

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...