በአንድ አፍ ሁለት ምላስ
አስገዳጅ ሕግ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሆነ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ጤና ሚኒስተር ከሰኞ ጀምሮ እንደሚተገብር የጋራ መግለጫ ሰጥቷል።
ምክንያቱ ደግሞ ከህብረተሰቡ ልቅ እንቅስቃሴ በመነሳት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጠን መጨመር፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰወች መጨመር፣ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰወች ቁጥር መጨመር፣ ተጎጂዎችን ተንከባክቦ ማከሚያ ሥፍራዎች መሙላት፣ የጤና ባለሙያዎች እረፍት አልባ አገልግሎት ማብቂያ ማጣት፣ የኢኮኖሚ ድቀት ወዘተ ናቸው።
በሳምንት ውስጥ ወደ 13ሺ የሚጠጉ ሰወች በቫይረሱ ተይዟል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንደሌለው ማሳያዎች ብዙ መሆናቸው እሙን ቢሆንም ህብረተሰቡ ሕይወቱን በኪራይ መልክ ያገኘው ይመስል የሚጠበቀውን ያህል ጥንቃቄ እያደረገ አይደለም።
ለምሳሌ በዛሬው ዕለት በሸገር ባስ በነበረኝ እንቅስቃሴ ሰአት እንኳን ኮቪድ 19 ያለ በሠላማዊ ወቅት ሊጭን ከሚገባው በላይ ነው።
የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተለመደው ሁኔታ አሰራራቸው ያለምንም ጥንቃቄ በአንድ ክፍል ውስጥ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ተጨናንቀው መስኮት ሳይከፍቱ የእለት ተለት ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የንግድ ስፍራዎች፣ የግብይት ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሌሎችም ሕዝብ የሚንቀሳቀስበት ሥፍራዎች እንቅስቃሴዎች እንደወትሮው የሰው ትርምስ ይታይባቸዋል።
ይህንን በታዘብኩበት ሰአታት ውስጥ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር እና አቃቤ ሕግ የጋራ መግለጫ እንዳወጡ ሰማሁ። በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ብዬዋለሁ። መነሻዬም ክልከላውም ልል ቁጥጥሩም ከራሱ ስፍራ ስለሆነብኝ ነው።
ብዙዎች በሕክምና ላይ ናቸው፣ ብዙዎች ታመው ድነዋል፣ ሌሎች ሞተዋል፣ ሌሎቻችን በመያዘ እና ባለመያዝ ሁለት ምርጫ መካከል ነን። የትኛውን መምረጥ እንዳለብን የታመነ ቢሆንም ህብረተሰቡ ያለው የቫይረሱ ንቀት እና ጥንቃቄ አልባ እንቅስቃሴ ስጋት ያጭርብኛል።
መንግሥት ያቀደውን ለማሳካት ከሚረዱት አካሄዶች አንዱ የሚያስተዳድረውን የትራንስፖርት አገልገሎት ሰጪ ተቋም ሸገር ባስ፣ አንበሳ ባስ ላይ የተሳፋሪውን ቁጥር በመቀነስ ርቀትን መጠበቅ አንዱ መንገድ ነበረ። ነገር ግን ሲሆን አይታይም።
ለዚህም ነው በመነሻዬ ላይ መንግሥት ቁርጠኝነት ይጎድለዋል ያልኩት። ህዝቡም አንድ ነፍስ ብቻ እንዳለው እና አንዴ ካመለጠች መተኪያ የላትምና መልእክቴን አድርሱልኝ።
• አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ
• ማስክ እናድርግ
• እጃችንን በውሃ እና በሳሙና በደንብ እንታጠብ ካልሆነም ሳኒታይዘር እንጠቀም
መንግሥትም በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ከሚሆንብን ሕዝብህን ለመታደግ ቁርጠኝነትህን አሳየን። አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰድክ ትውልዱን ታደግ።
በአንድም በሌላም እንናገራለን:ጆሮ ያለዉ ይስማ:ልብ ያለዉ ልብ ይበል፡፡ የታዘብነዉን የምንናገርበት፣ የምናዉቀዉን ለትምህርት እና ለእርምት የምናዉልበት ከወገንተኝነት ነፃ የሆነ መድረክ ነዉ፤ …ሁሌም ቢሆን አስተያየቶችን እና መልዕክቶችን ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡
እሑድ 28 ማርች 2021
በአንድ አፍ ሁለት ምላስ
ዓርብ 26 ማርች 2021
አነጋገራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደተቀመመ ይሁን
አነጋገራችሁ ሁሌ በጨው እንደተቀመመ ይሁን
እንደ እግዚአብሔር ቃል አነጋገሩ ሁሌ በጨው እንደተቀመመ የሚጣፍጠኝ ዴል ካርኒንግ የሚባል ሰው አለ።
አብዛኞቻችሁ ታውቁታላችሁ ፤ የመጽሐፍ ደራሲ ነው።
ምክሮቹ፣ ተግሳጾቹ እና ዘዬዎቹ በትንሽ መጽሐፍ ተሰድራ እንደ ብሉያት እና ሐዲሳት መጻሕፍት ከዘመን ዘመን ትሻገራለች።
"የጠብታ ማር" ትሰኛለች።
በተደጋጋሚ አንብቤዋለሁ፣ ብዙ ጊዜ ገዝቼ ለሰው በስጦታ መልክ ሰጥቼዋለሁ፣ ብዙ ጊዜ ከመጽሐፍ መደርደሪያ ላይ ጠፍቶብኛል፣ ዘወትር ለምን ብዬ ጠይቃለሁ፣ ሁሌም ሳነበው አዲስ ይሆንብኛል።
ምሥጢሩ አልገባኝም።
ይኸው ዛሬም ምሥጢሩን እየፈለኩ አንድ ነገር ብልጭ አለብኝ። " እንደ አነጋገራችን አስተሳሰባችንም በጨው እንደተቀመመ ጣፋጭ ይሆን ዘንድ።
በጨው የተቀመመ ነገር ከመጣፈጡም ባሻገር እንደ እናቶቻችን ሙያ ከሆነ አይበላሽም፣ ረጅም ጊዜ ይቆያል፣ ለብዙ ጊዜ የሚቆይ ረጅም መንገድ የሚያስጉዝ ስንቅ ይሆናል።
ከመቆየቱ ያለመበላሸቱ ድንቅ ነገር ነው።
ጨው ሲንተራሱት ጸጉር የሚመልጥ ካልጣፈጠ ድንጋይ ነው ብለው የሚጥሉት ነገር እንዲህ ትልቅ ተግባር ሲኖረው እጅግ ድንቅ ነው። ዋጋውም ከማጣፈጫዎቹ ሁሉ እጅግ ርካሽ ነው።
የሰው አንደበትም፣ አስተሳሰብም፣ ቃላትም እንዲሁ ዋጋቸው ትንሽ ውጤታቸው ትልቅ የሆኑትን መተግበር ተስኖን አለማችን መራር ሆናለች።
አነጋገራችን እና አስተሳሰባችን ዘወትር በጨው የተቀመመ ጣፋጭ ይሁን።
የትናንቱን እና የዛሬውን በማሰብ አስተሳሰባችንን ከማጥበብ ነገን እያሰብን ሐሳባችንን፣ ቃላቶቻችንን የጣፈጡ እንዲሁም ሰፊ እናርጋቸው።
ሰናይ እለተ ሰንበት ይሁንልን።
ይቆየን።
@deressereta
የጾም ምግብ ቤቶች
የጾም ምግብ ቤቶች
በየከተማችን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የአጽዋማት ጊዜ ጠብቀው ምግብ ቤቶች በአዲስ መልክ ማስታወቂያ መስራት የተለመደ ነው።
አንዱን ብንመለከት የአብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ የጾም ቡፌ፣ በየአይነቱ፣ ዓሣ አዘጋጅተናል። የምትል ትገኝበታለች።
ማስታወቂያዎቹ ለጾም እና ጸዋሚ "ተጨንቀው" ምግብ እንደ ማዘጋጀታቸው ጥራጥሬ፣ ሽንብራ፣ ደረቅ ቂጣ አያዘጋጁም። ዝግጅቱ ለጾም ሳይሆን ለመብል ነውና።
ፍትሐ ነገሥት ስለ አጽዋማት በሚናገረው አንቀጹ አንቀጽ 15 ላይ በ572ኛው ቁጥር ላይ " በእነዚህ በታዘዙት ጾሞች ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ይጹም ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው። " ይላል።
ግእዙ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦" ... ወኢይብልዑ ቦሙ ሥጋ ዘእንበለ ዓሣ ..." እዚህ ጋር ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን "ዘእንበለ" ፍችው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል። ቤተክርስቲያኒቱ ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ከመጽሐፍ ጠቅሳ ዓሣ የሥጋ ዘር ነውና። ደምም አለውና ጾም እንደሆነ በሲኖዶስ ደንግጋለች።
ፍትሐ ነገሥትም በዚሁ አንቀጽ ቁጥር 584 ላይ " በጾም ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል። ከመብላት በጣም ይሻላል።" ይለናል።
ነገር ግን ጸዋሚው የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጅ ራሱ ለምግብ ሲቀመጥ ዓሣ አልጾምም ሲል ይደመጣል። ለነፍሱ ሊያደላ በሚገባው ወቅት ለሥጋው ያደላል።
"ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው።" በሚለው ቃል ዓሣን አልጾምም የሚለው "ጸዋሚ" ከፍ ብሎ " ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ይጹሙ " የሚለውን አያነበውም፤። አይተገብረውም።
" ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሰረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኀይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ " የተሰራ መንፈሳዊ ተግባር እንደመሆኑ መጠን በጾም ወቅት መከልከል ከሚገባን ነገር ሁሉ ልንከለከል ይገባናል፣ በደላችንን ለማስተስረይ ንሰሐ ገብተንም ልንጾም ይገባል፣ ወደን ፈቅደን ሕግንም ለሰራልን ልንታዘዝ ይገባል፣ ሥጋችንንም ለነፍሳችን ልናስገዛም ይገባል።
ጾም ከምግብ መክልከል ሥጋን ማድከም ነፍስን ማለምለም እስከሆነ ድረስ ምግብ ቤቶቻችን በአንጻሩ ምነው በምግብ ማስታወቂያ ለዚያውም ለመጾም በማይጋብዙ የምግብ ዝርዝሮች ጠብ እርግፍ አሉ?
የምግብ ቤቱን አነሳን እንጂ ከወትሮው በተሻለ በየሁላችን ቤት ከፍስኩ ጊዜ ይልቅ የምግብ አይነቱ በጾም ወቅት አይደለምን? ከዚህ ምን እናተርፋለን? ወይንስ እንዲሁ እንዘጭ እንዘጭ ነው?
መጾም ይገባልና ከመብላትም በጣም ይሻላልና ጾመን በረከትን እናግኝ፣ በደላችንንም እናስቀር፣ ስንጾም ብልቶቻችን ሁሉ (ዓይን፣ ጆሮ፣እግር፣ አንደበት፣ወዘተ) ይጹሙ።
የጾም ምግብ ቤቶችም በስመ ጾም ከመነገድ ቢታቀቡ መልካም ነው፤ እኛም ስንመገብ በማካካሻ መልክ በሚመስል ባንመገብ መልካም ነው።
ስለ አጽዋማት ያለን አመለካከት ይቀየር የቄስ፣ የመነኩሴ፣ የሕጻናት፣ የሚባል ጾም የለም። እድሜው ሰባት አመት የሞላው የጤና እክል እና በንሰሐ አባቱ በኩል በተለያዩ ምክንያት ከሚፈቀድ በቀር ሰባቱም ጾሞች ሊጾሙ ይገባቸዋል።
" ከዚህ ከታዘዘው አብልጦ የጾመ ግን ዋጋው ይበዛለታል። " እንዲል።
አብዝተን ጾመን የበረከቱ ተሳታፊ ለመሆን ያብቃን። ጾሙ የሐጥያት መደምሰሻ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ያድርግልን።
አሜን።
ይቆየን።
@deressereta
comment እና subscribe ማድረግ አይርሱ
እነዚህን ነቢያት እኔ አላክኋቸውም
" እነዚህን ነቢያት እኔ አላክኋቸውም "
ትንቢተ ኤርሚያስ 23 : ከቁጥር 9 ጀምሮ ብናነብ እግዚአብሔር በሐሰተኞቹ በሰማሪያ ነቢያት ምን ያህል እንደተማረረ እንመለከታለን። እነዚህን ነቢያት እኔ አላክኋቸውም እስኪል ድረስ።
ወዳጄ ብዙ ሰው ያውቅህ ይሆናል፤ ታዋቂነትህም ከአገር አገር የናኘ ሊሆን ይችል ይሆናል። ብዙ ተከታዮችም ይኖርህ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ክብርህ ጥግ ደርሶ ሊሆን ይችላል።
ነገሮች ሁሉ ተቃንተውልህ የትናንት ሕይወትህ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል። የመርገም አንደበትህ የምርቃት፣ የውሸት አንደበትህ የእውነት የሆነውን ቃል ትጠቅስበት ይሆናል፣ የድህነት ታሪክህ በባለጸግነት፣ ማይምነትህ በአዋቂነት ሥም ተተክቶልህ ሊሆን ይችላል፣ የትናንቱ እግረኛ ዛሬ የዘመናዊ መኪና ባለቤት ሆነህ ሊሆን ይችላል፣ በአጠቃላይ ታሪክህ ተቀይሯል።
ስለ እውነት አንተ ተቀይረሃል?
ባለጸጋ ስትባል ነፍስህን አላጎደልካትም?
ለሌሎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ወተት ስትግት አንተ ግን ቃሉን አልተጠማህምን?
ምድራውያን ሰወች ሲያከብሩህ ዋጋህን በምድር ስትቀበል በሰማይ ያለውን የአባትህን ዋጋ አልተነጠክም?
ነብይ ነኝ ስትል፣ ሐዋሪያ ነኝ ስትል፣ ወንጌላዊ ነኝ ስትል፣ አገልጋይ ነኝ ስትል፣ አጥማቂ ነኝ ስትል፣ ባህታዊ ነኝ ስትል፣ ወዘተ ብዙዎች ሁሉን ትተው ተከትለውህ አደባባዮችህ ደምቀው መድረኮችህ ጠጠር መጣያ እንኳን ጠፍቶ ሊሆን ይችላል። ወዳጄ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ አለመታወቅ አሳፋሪ ነገር የለም።
እግዚአብሔር በሚያውቅህ ልክ እንጂ ዋጋህን የምትቀበለው በታዋቂነትህ ልክ አይደለም።መድረክህ ስትይዝ የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቀህ ማወቅህ እንጂ ታዋቂነትህ ለአድናቆትህ ሽፋን እንጂ የሚሆንህ ለመዳንህ ምክንያት አይሆንህም።
እነዚህን ነቢያት እኔ አልላኳቸውም እንደመባል አሳፋሪ ነገር የለም። አንተ ከየትኛው ነህ?
ወዳጄ አንተ የምትከተለው "አገልጋይ" ከየትኛው ወገን ነው? ተከታዮቹ ስለበዙ መድረኩ ስለደመቀ፣ ድምጹ ነጎድጓዳማ ስለሆነ፣ የልብህን መሻት ስለሚነግርህ፣ ስለማይገስጽህ፣ ወይንስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለሆነ ነው?
• 2ኛ ቆሮንቶስ 11 : 13
" እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። "
ስለሚልባቸው በእነርሱ ላይ ያለው እናንተ እየተከተላችሁት ያለው መንፈስ የትኛው እንደሆነ መርምሩ " መንፈስን ሁሉ አትመኑ "ይላልና።
• 2ኛ ጢሞቴዎስ 3 : 1- 6
ነብያትን ነን እያሉ ምእመናንን የሚያስጨንቁ፣ ሐብትና ንብረትን የሚነጥቁ፣ ሴቶችን ከክብራቸው የሚያነውሩ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ቁጭ ብለው ሳይማሩ ቆመው የሚያስተምሩ፣ ርኩስ መንፈስ የሚጫወትባቸው ናቸው።
ገንዘብን ከመውደዳቸው የተነሳ የማያደርጉት ነገር የለም፤ ትእቢተኞች እና ተሳዳቢዎች ናቸው። ክብራቸው በነውራቸው ሐሳባቸው ሁሉ ምድራዊና ብልጭልጩ አለም የሆነ። ጽድቅን በምድራዊ ስኬታቸው የሚያወዳድሩ ከንቱዎች ናቸው።
የእግዚአብሔርም ቃል ከነዚህ ራቁ ይለናል። ተከታዮቻቸው ግን ብዙ ናቸውና የተቀሩትም የተከታዮቻቸውን ብዛት ተመልክተው ይከተሏቸዋል።
ጠማማ ትውልድ ምልክትን ይሻልና 'ድንቅ ተአምር' እናያለን፣ 'ፈውስ' እናገኛለን፣ በማለት በሐሰት ትርክታቸው ተታለው እዚያው ይቀራሉና ከነዚህ ደግሙ ራቁ ለማለት እወዳለሁ።
" ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። "
ሐሰተኛ ነቢያት እንደመኖራቸው መጠን እውነተኞች መኖራቸው እሙን ነው። ቃሉም ስለ እውነተኞቹ ነቢያት ሲናገር እናያለን ኤርሚያስ 1 : 5 እና ሕዝቅኤል 3 : 17 እንዲሁም የሐዋርያት ሥራ 9 : 15 ላይ ይመሰክርላቸዋል።
ከእናታቸው ማህጸን ጀምሮ የተመረጡ እንዳሉ የተለያየ አገልገሎትም እንደሰጣቸው ለሕቡም ጠባቂ እንዳደረጋቸው እናያለን።
ነቢዩ ኤርሚያስ ግን በእግዚአብሔር ተገብቶ እንዲህ እያለ ይናገራል።
" እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር። አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። "
ቃሉ እነዚህን ራሳቸውን ነቢያት ነን ባዮችን እግዚአብሔር እንደማያውቃቸው ያስረግጥልናል።
ስለዚህ እግዚአብሔር ቅር ከተሰኘበት መንገድ እንድንመለስ ሰውንም ከመከተል እንድንታቀብ በሐሰተኞቹም እንዳንታለል አደራ እላለሁ።
ይቆየን።
@deressereta
እግዚአብሔር ያዘዘኝን አደርጋለሁ
"እግዚአብሔር ያዘዘኝን አደርጋለሁ እንጂ እኔ አዝዛለሁን?"
ሀብተ መርገም እና ሀብተ በረከት የተሰጠው በለአም ለባላቅ የመለሰው ምላሽ ነበረ።
እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ አሕዛብን ድል እየነሱ ሲመጡ በባላቅ ወልደ ሶፎር አገር አጠገብ በሞዓብ ሜዳ በሰፈሩ ጊዜ የእስራኤላውያንን ጥንተ ታሪክ ያውቅ ነበረና እጅግ ፈራ።
ፈርቶም አልቀረ በአሞራውያን ላይ ያደረሱት በርሱና በሕዝቡ እንዳይደርስ በለአምን ና እና ርገምልኝ አለው።
በለአምም እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሰወች እንደሆኑ የተባረኩም ሕዝብ እንደሆኑ ያውቅ ነበረና፣ እግዚአብሔርም አትርገማቸው ብሎታልና ላይረግማቸው ላይሄድ ወሰነ።
ባላቅም ከአንዴም ሁለቴ ከጥሩ ገንዘብ ጋር ሰው ላከበት ሆኖም በለአም ሳይመጣ ቀረ፤ በመጨረሻም እግዚአብሔር በራእይ ለበለአም እንዲህ አለው " መሔዱን ሒድ ነገር ግን እግዚአብሔር የገለጠልህን ተናገር እንጂ አትራገም" አለው።
እንደሄደም እስራኤላውያንን ከአንዴም ሶስቴ መረቃቸው፥ ባላቅም ተቆጣ። "ርገምልኝ አልኩህ እንጂ መርቅልኝ አልኩህን?" አለው።
"እግዚአብሔር የገለጸልኝን እናገራለሁ እንጂ ሌላ ምን ላደርግ እችላለሁ?" ብሎ በለአም መለሰለት።
በማግስቱም እንዲሁ ሆነ ሰባት ላም፣ ሰባት ዳንግሌ ሠዋለት። በለዓምም እንደ ልማዱ ያሟርት ጀመረ። ነገር ግን ዛሬም መራገም አልተቻለውም።
መጽሐፍም እንዲህ ታሪኩን ያስነብበናል፦ " እግዚአብሔር እንደ ሰው ሐሰት አይናገርም፣ በሠራውም ሥራ አይጸጸትም እኔ እስራኤልን እንድመርቅ ትእዛዝ ተቀብያለሁና በያዕቆብ ክፋት አላይበትም። እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ ጋራ ነውና። በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፣ በእስራኤልም ላይ ሟርተኝነት አይቻልም። ይህ ሕዝብ እንደ አንበሳ ደቦል ነው። ያንበሳ ደቦል የሰበሰውን ሥጋውን ሳይበላ፣ ደሙን ሳይጠጣ እንዳይመለስ ይህ ሕዝብም አሕዛብን ሳያጠፋ አይመለስም" ይለናል
ባላቅም ያሰበው ባይሳካ ያላሰበው እንዲሆንበት አልፈለገምና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ " መራገም ቢቀር እንኳን ባይሆን መመረቁን አትተውምን? ይህን ሕዝብ ለምን ትመርቀዋለህ?" አለው።
በርእሳችን እንዳነሳነው በለአም መለሰለት፥ " እግዚአብሔር ያዘዘኝን አደርጋለሁ እንጂ እኔ አዝዛለሁን?" አለው።
ድንቅ መልስ ነው።
ይህ ታሪክ በበለአምና በባላቅ መካከል፣ በእስራኤላውያን እና በባላቅ አገር ሰወች መካከል የሆነ የተመዘገበ ቢሆንም ቅሉ የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ግን ቦታ የማይገድበው ጊዜ የማይሽረው ነውና እራሳችንን እንመልከትበት።
እኛ የማንን ፈቃድ እናደርጋለን? የሥጋን ፈቃድ ነው የነፍስን ፈቃድ እንፈጽማለን? በገንዘብ እንገዛለን ለእግዚአብሔር እንገዛለን? እንመርቃለን ወይንስ እንረግማለን?
አለማችን እንዴት ሰነበተች? ብለን በእግዚአብሔር መንፈስ ብንቃኘው በውኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚሳደብ፣ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ካህናትን እና በቤቱ የሚመላለሱትን፣ እግዚአብሔር የመረጣቸውን እና የቀባቸውን የሚያንጓጥጥ ነው የሞላው ወይንስ የሚመርቃቸው?
የባላቃዊያን ሀሳብ የፈለገውን ቢሆንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሻር አልተቻለውም። እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማንም አይቃወማቸውምና።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጽያዊያንም እንደዚሁ ናቸው፤። የማንም ሰልፍ አያሸንፋቸውም። የማንም ሟርት እና እርግማን አይደርስባቸውም። አንድነታቸውና ህብረታቸውም የኢትዮጵያን ጉዞ አይገታም። እግዚአብሔር ከርሷና ከሕዝቦቿ ጋር ነውና።
እንደ ፈቃዱ ተመላልሰን የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደተባልን ጸንተን ቆይተን እግዚአብሔር አጥር ቅጥር ይሁነን። ከጠላቶቻችን ይጠብቀን፣ የተቃጣብንን ይመክትልን፣ በመርገም ፈንታ ይመርቀን፣ መውጣት መግባታችንን በአባታዊ አይኑ ይከታተልልን።
የጠላቶቻችንን ዓይን ጨለማ ጉልበታቸውን ቄጠማ ያድርግልን።
በእግዚአብሔር ማመናችን መዘባበቻ ሳንሆን መጽናኛ ይሁነን።
የአባቶቻችን በረከታቸው ጥርጥር የሌለባት ተዋህዶ እምነታቸው በረከቷ ይደርብን።
የተጀመረውን ጾም ሥጋችንን ገዝተን፣ ነፍሳችንን አበርትተን ጠላት ዲያቢሎስን ድል የምንነሳበት የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርስበት ያድርግልን።
@deressereta
እንተወው
"እንተወው"
መጋቢ ሐኪስ እሸቱ ሁሌም በጨው እንደተቀመመ ቃላቸው ሁሌም ይጥመኛል።
እንዲህ ይላሉ፦ "እንተወው ... ካልተውንው እና የሆነብንን፣ እየሆነ ያለውን፣ ሊሆን ያለውን ካሰብን አይደለም ከሰው ጋር ያለን ጉዳይ ይቅርና ትዳራችንን እስክንፈታ ድረስ የሚሄድ ጉዳይ ነው ይላሉ።"
እውነት ነው ካልተውነው በቀር ስለ አገራችን ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች፣ ስለ አገራችን እምነቶች እና በእምነቱ ስም ስለሚተውኑ ሰወች፣ የኑሮ ሁኔታ እና ኑሮውን ስለሚዘውሩ ሰወች፣ ስለ ሶሻል ሚዲያው እና በሶሻል ሚዲያው እንጀራቸውን ስለሚጋግሩ ሰወች፣ ወዘተረፈ የምናውቀውን እንናገር ካልን ጓደኝነታችን አይደለም ትዳራችን ይፈርሳል።
መንደራችን፣ ብሔራችን፣ ቤተእምነታችን፣ ቡድናችን፣ ፓርቲያችን፣ ወዘተ ይፈርሳል።
ከመጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በተማርኩት መሠረት ስለምታውቅ፣ መረጃው ስላለህ፣ ከሁነኛ ሰው ስለሰማህ፣ አትንገር ብለው ስለነገሩህ፣ ... ሁሉ ነገር አይነገርም።
አንተ የደረሰብህ ጉዳይ ፀሐይ የሞቀው አገር ያወቀው ምስክር ጥራ ብትባል አገር ምድሩ ግልብጥ ብሎ ስለሚመሰክርልህ በሕግ ፊት ፍትህ ስለምታገኝ ሁሉ ነገር አይወራም።
መረጃ ማስረጃ አቅርበህ፣ ጠበቃ አቁመህ መርታት ስለምትችል ሁሉ ነገር አይወራም።
አንዳንዴ ጊዜ የሚፈታው፣ አንዳንዴ ለምጣዱ ሲባል አይጧን እንደምታልፋት ሁሉ ዝም ብለህ ማለፍ ትተህ የምታልፈው ነገር እንዳለ መተው ግድ የሆነበት ጊዜ እንዳለ ልብ በል።
@deressereta
ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!
መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡
ትቶ እና ችሎ
ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...
-
የጊዜ አጠቃቀም መግቢያ ስኬታማ የጊዜ አጠቃቀም ያዳበረ ሰራተኛም ሆነ ግለሰብ ጊዜዉን በመርሃግብር እና በዕቅድ ይመራል፤ ይህ ሰዉ ህይወቱን የሚመራዉ በዕድል ሳይሆን ...
-
ሰሞኑን በዚች በምድራችን ‹‹ጫካው ለዛፎች ብቻ›› በሚል ዛፎች ተሰባስበው በዱር አራዊቶች እና አዕዋፎች ላይ የአቋም መግለጫ አወጡ አሉ፤ ከመግለጫው ሥር እንደ አብይ ርዕሰ ጉዳይ ያደረጉት ጫካው ለእኛ ለዛፎች ብ...
-
በክፍል አንድ “ፍቅር በFace book ” በሚለው እውነተኛ ታሪክ ላይ መሰረት ያደረገ ክፍል ማቅረባችንን ሳሙኤል በFace book ላይ የተዋወቃትንና ሳይስቡት ፍቅር ውስጥ ገብተው በኃላም ሕይወትን የመጀመር አዝማሚያ...