በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ እጅግ የከበርሽ ፀጋን የተመላሽ ሆይ ምስጋና የባህርይ ገንዘቡ ከሆነው ልጅሽ ቀጥሎ የምትመሰገኚ የአምላክ እናት ሆይ አመሰግንሻለሁ፡፡
ልጅሽ ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከምድር አሸዋ እጅግ የበዛ ሐጢያቴን ሳይመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ እስከዛሬ እያወኩኝ በድፍረት ሳላውቅም በስህተት የሰራሁትን በደል ሳስብብኝ ለዚህች ሰዓት ያደረሰኝ በአንቺ ምልጃና ፀሎት ነውና፡፡
ድንግል ሆይ ‹‹አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ ከአዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ›› ብለው አባቶች አመሰገኑሽ እመብርሃን በእውነት ያለሐሰት ከበደሌ ብዛት ካንቺ ምልጃ አንፃር የአዳም ሳይሆን ተስፋነትሽ የኔ የብቻዬ ነው ድንግል ሆይ ራስን መውደድ እንዳይሆንብኝ ግን ይህ ርኅራኄሽ ይህ ምልጃሽ ለአዳም ዘር ሁሉ ይሁን፡፡
ድንግል ሆይ ስምሽን ባነሳሁና ባሰብኩ ቁጥር ውስጤ ስለሚረበሽ ከጎኔ በመሆን አይዞህ በይኝ አፅናኚኝ ተስፋህ እኔ ነኝ በይኝ ተስፋዋ ለመነመነ ግራ ቀኟ ለጨለመባት ሕይወት ረሐብና ጥም ላጠቃት ነፍሴ መፅናኛሽ አለኝታሽ እኔ ነኝ በያት፡፡
የአምላክ እናቱ ሆይ ልጅሽ ከቅዱሳኑ ጋር ከነቢያትና ከወዳጆቹ ከመላዕክት ጋር ዘወትር በሕይወቴ እንድስተናገድ በእኔነቴ ላይ እንድነግስ ደግሞም በሚገለጥበት ሰዓት ከቀኙ ሊያቆመኝ የሚችለውን መልካም ሥራ ሠርቼ ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ ርስቱን ከሚያወርሳቸው ጋር እንዲደምረኝ ተማልደሽ አማልጅኝ፡፡
የኃጥአን ተስፋ የሆንሽው ሆይ በሐጢያት ስወድቅ ኃይልና ብርታት ሁኚኝ ከሐጢያትም ሥፍራ ተነስቼ ሐጢያቴን በማመን ሐጢያቴ የሚሰረይበትን ንሰሐ እንድገባ አበርቺኝ ከልጅሽም ጋር ሕብረት አንድነትን ልፈጥር የምችልበት ከሐጢያት ሁሉ የምነፃበትን መለኮት የተዋሃደው የልጅሽን ሥጋና ደም የመመገቡን ፀጋ አድይኝ፡፡
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዳለሽ ‹‹…. ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ መዓትን ያይደለ ምህረትን አሳስቢ ለጻድቃን ያይደለ ለተዳደፉት አሳስቢ›› ለኔ ለሐጢያተኛው ዘወትር እንድታሳስቢ በግብፅ በረሃ መሰደድሽን መራብ መጠማትሽን ልጅሽን ለማዳን ብለሽ ከላይ በአናትሽ የገባው የፀሐይ (ብርሃን) ግለት እግርሽን የቀቀለውን ረሞጫ አሳስቢ ምንም እንኳን ኃጢያቴ ቢበዛ የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስምና ሁሉ ቢቀር ለንሰሐ የምበቃበትን ልቦና አሰጪኝ ንሰሐ ዘማዊን ድንግል እስከ ማድረግ ደረጃ ያደርሳልና፡፡
እመብርሃን በዶኪማስ ቤት በሠርጉ በተጠራሽ ከልጅሽ ከወዳጆቹ ከቅዱሣን ጋር በሠርጉ በታደማችሁ ጊዜ ድግሱ አልቆበት በተዋረደ ጊዜ አንቺም ጭንቀቱን ተመልክተሸ ወደ ልጅሽ ነግረሽ ቤቱን በረከት በበረከት እንዳደረግሽ ውሀውን ወደ ወይን እንዳስለወጥሽ እኔም በዚህ ምድር ስኖር ሕይወቴ ባዶነት ይሰማዋልና ምግባር ትሩፋት የለኝምና እጅግም የማሳፍር ሆኛለሁና በጣምም ተዋርጃለሁና ከውርደት አድኝኝ ጎደሎ ያይደለ ሙሉ አድርጊኝ በምግባር በትሩፋት አትረፍርፊኝ ከሐፍረት ሰውሪኝ ውሃ … ውሃ ያለው ሕይወቴንም አጣፍጪው፡፡
ድንግል ሆይ ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆቹ መካከል ሥምኦንና ሌዊ በሴኬም ልጆች ላይ እጃቸውን ባነሱ ሰዓት እንደረገማቸውና እንደለያቸው ከዘመናት በኋላ እስራኤላውያን ጣኦትን ሲያመልኩ እግዚአብሔርም ሲቆጣ ሙሴም ከፊታቸው ቆሞ ‹‹የእግዚአብሔር ወገን የሆናችሁ ተለዩ›› ባለ ጊዜ የሌዊ ነገድ ራሱን ለእግዚአብሔር ቢለይ እግዚአብሔር መረጠው አከበረው በመጨረሻም ርስትን ሲከፋፈሉ ሌዊን ካህን አድርጎ እንደሾመ እንደባረከ እንዲያገለግላቸው እንደመረጠው ሌሎች ርስት ሲከፋፈሉ እግዚአብሔር ለአንተ ርስትህ እኔ ነኝ እንዳለው ባንቺ አማላጅነት ሐጢያቴና በደሌ ከሌዊ እጅግ የበዛውን ልጅሽን ታሪኬን በደሌን እንዲቀይረው እኔም እንድቀየር አድርጊኝ እንደ ሌዊ አገልጋይ ካህን አድርጊኝ ባልልም ሐጢያቴን እንዲያቀልልኝ አሳስቢ ለሌዊ ርስቱ እንደሆነ ርስትህ እኔ ነኝ ይለኝ ዘንድ አሳስቢ፡፡ እኔ በኃጢያት ማኛ የተጣልኩትን ልጅሽ በፍፁም ፍቅሩ ሁለት እጄን ይዞ እንዲያወጣኝ አሳስቢልኝ፡፡
ድንግል ሆይ በቀረውስ ምስኪን ሰው ድሃ ሰው ከባለ ፀጋ ፊት ሲቆም ብዙ ነገር ይለምናልና ባለፀጎችም መመፅወት ባህሪያቸው ነውና ከባለፀጎች ሁሉ ባለፀጋ ከሆነው ልጅሽ ዘንድ የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ አሰጭኝ፡፡
ቅድስት የምትሆን የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን ባርኪያት ሕዝቦችዋን ከጦርነት ከእልቂት ከረሃብ ከቸነፈር ከበሽታ ከክህደት ሁሉ እንዲሠውራት ለልጅሽ አሳስቢ፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያንና አድባራትንና ገዳማትን ጠብቂልን ጉባኤያትን ማኅበራትን የወንድሞችን ሕብረት አጠናክሪ ከጠላት የፈተና ጦር ሠውሪያቸው፡፡
እኛ ልጆችም የእምነት የምግባር የትሩፋት ሠው እንድንሆን አሳስቢ፤ በሩቅም በቅርብም ያሉትን እንድናስባቸው ያሳሰቡንን ሁሉ አስቢ፡፡
ድንግል ሆይ በተረፈው በተሰጠሸ ቃልኪዳን መሠረት በሠላም ውዬ እንድገባ በቀንና በሌሊት ጥበቃሽ አይለየኝ ልጅሽ ለአንደበቴ ለልቡናዬ ለእግሬ ጠባቂ መላዕክትን እንዲያቆም መልካም ፈቃዱ ይሁን፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን አሜን፡፡
ከተስፈኞች አምባ
በአንድም በሌላም እንናገራለን:ጆሮ ያለዉ ይስማ:ልብ ያለዉ ልብ ይበል፡፡ የታዘብነዉን የምንናገርበት፣ የምናዉቀዉን ለትምህርት እና ለእርምት የምናዉልበት ከወገንተኝነት ነፃ የሆነ መድረክ ነዉ፤ …ሁሌም ቢሆን አስተያየቶችን እና መልዕክቶችን ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡
ዓርብ 29 ማርች 2013
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!
መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡
ትቶ እና ችሎ
ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...
-
የጊዜ አጠቃቀም መግቢያ ስኬታማ የጊዜ አጠቃቀም ያዳበረ ሰራተኛም ሆነ ግለሰብ ጊዜዉን በመርሃግብር እና በዕቅድ ይመራል፤ ይህ ሰዉ ህይወቱን የሚመራዉ በዕድል ሳይሆን ...
-
ሰሞኑን በዚች በምድራችን ‹‹ጫካው ለዛፎች ብቻ›› በሚል ዛፎች ተሰባስበው በዱር አራዊቶች እና አዕዋፎች ላይ የአቋም መግለጫ አወጡ አሉ፤ ከመግለጫው ሥር እንደ አብይ ርዕሰ ጉዳይ ያደረጉት ጫካው ለእኛ ለዛፎች ብ...
-
በክፍል አንድ “ፍቅር በFace book ” በሚለው እውነተኛ ታሪክ ላይ መሰረት ያደረገ ክፍል ማቅረባችንን ሳሙኤል በFace book ላይ የተዋወቃትንና ሳይስቡት ፍቅር ውስጥ ገብተው በኃላም ሕይወትን የመጀመር አዝማሚያ...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ