ክፍል ሁለት!
“መልዐኩ እና ደራሲዉ”
“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ ምድርም ባዶ ነበረች
፡ … … ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ አንድ ቀን፡፡” ዘፍጥረት11፡1-5
እንደ ፈረንጆቹ
ዘመን አቆጣጠር ማርች 22-2012 ምክሰኞ ቀን “የደረሰ
ረታ እይታዎች” በምትሰኝ ጥቂት መጦመርያ መጦመርን “ሀ” ብዬ ስጀምር “መልዐኩ እና ደራሲዉ” ፤ “… … … የእግዚአብሔር መልዐክ ጋር የመጀመሪያዉን
የደራሲዉን እና የመልዐኩን ግንኙነት እዚህ ላይ በማቆም በቀጣዩ ምዕራፍ እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን! ” በማለት ተሰነባብተን እንደነበር
የአንድ አመት ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡እነሆ መቸስ እንደማይሞላ፤ መልዐክና ደራሲም ተገናኝተዉ በቀላሉ አይለያዩምና ፤ይኸዉ ዘግየቼም
ቢሆን ድፍን አንድ አመት በመዘግየት ክፍል ሁለትን ይዤላችሁ መጣሁላችሁ፡፡
እንኳን ለጦማርችን አንደኛ
ዓመት አደረሰን! መልካም ንባብ፡፡
“መልዐኩ
እና ደራሲዉ”
መልዐኩ፡-“ አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን
መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጅህ ሥራዎች ናቸዉ” እንዲል መፅሐፍ በመዝሙረ ዳዊት 101፡25 ከመፍጠርህ አንስቶ ሥትኖርበት የነበረዉን
ምድር አሁን ዳግሞ ያለህበትን ሰማይ በአንድነት ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸዉ እግዚአብሔር ነዉ፡፡
ደራሲዉ፡-እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን
ሲፈጥር ይህን ሰማያዊ ዓለምና ያኛዉን ዓለመ ምድር (ምድራዊ ዓለም) ሥንት ፍጥረት በመፍጠር ሊሞላዉ ቻለ፡፡
መልዐኩ፡-ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር የፈጠረዉ
ፍጥረት ሁሉ ቢቆጠር ፍጥረት በሙሉ ቆጥሮ አያጠናቅቀዉም፤ ነገርግን እንደ ሥነ-ፍጥረት ሥርዓት ብዙዉን አንድ ፡ብዙዉን አንድ እያልን
ሥንቆጥረዉ በ22ቱ አርዕስተ አበዉ ምሳሌ 22 ናቸዉ፡፡
ደራሲዉ፡-አርዕስተ በዉ የሚባሉት እነማን
ናቸዉ?ምንስ ነዉ?
መልዐኩ፡-አዳም፣ሴት፣ሄኖስ፣ቃይናን ፣መላልኤል፣
ያሬድ ፣ሄኖክ ፣ማቱሳላ፣ ላሜህ ፣ኖህ ፣ሴም፣ አርፋክስድ፣ ቃይናን፣ ሳላ፣ ኤቦር፣ ፋሌቅ፣ ራግዉ፣ ሴሮህ፣ ናኮር፣ ታራና አብራም…
ናቸዉ፡፡
ደራሲዉ፡-22ቱንም ፍጥረታት በአንድ ቀን
ፈጥሮ አጠናቀቀ?
መልዐኩ፡-መፅሀፍ በአንድቅ ተደርሶ ታትሞ
ለአንባቢያን እንደማይደርስ ሁሉ ይህም ዓለም በአንድ ቀን ተፈጥሮ አልተጠናቀቀም ፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በጊዜ ሠርክ ጀምሮ በዕለተ
ዓርብ ለፍጥረት ስድስተኛ ለቀመር አራተኛ ማለት ነው፡፡
በዕለተ እሁድ ሥምንት ሲፈጥር እነዚህም አራቱ ባህርያተ ሥጋ እና ጨለማ፣
ሰባቱ ሰማያት፣ መቶው ነገድ መላእክት እና ብርሃን ናቸው፡፡ አራቱ ባህርያት ሥጋ የሚባሉት ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት ናቸው፡፡
በባህርዬ አራት ነገሮች አሉብኝ ሲልም ፈጥሮአቸዋል፡- እነዚህም ኃያል ነኝ ሲል እሳትን ፈጠረ፤ እሳትን ውኃ ካልከለከለው ቆላ ደጋ
ሳይል እንዲያጠፋ እግዚአብሔርም ቸርነቱ እስካልከለከለዉ
ድረስ ሰማይንና ምድርን በአንድነት ሊያጠፋ ይቻለዋልና እንዲህ አለ፡፡ፈታሂ ትክክለኛ ፍርድ ሰጪ ነኝ ሲል ነፋስን ፈጥሯል፤ ነፋስ
ፍሬን ከገለባ ሳያዳላ እንዲለይ እግዚአብሔር እንዲሁ ፃድቅን ከኋፅእ መለየት ይቻለዋልና፡፡ ዉኋንም የፈጠረዉ ዉኋያደፈን እንዲያስለቅቅ
እኔም ነፍስን ከኋጢያት የመለየት ሥልጣን ያለኝ ነኝ፤ በማለት መንፅኂ ነኝም ሲል ዉኋን ሊፈጥር ችሏል፡፡ምድር የፈጠረዉን ፍጥረት
ሁሉ ችሎ እንዲኖር እንዲሁ እኔም በባህሪዬ ሁሉን አድራጊ ሥሆን በማያልቀዉ ትዕግሥቴ ሁሉን ችዬ እኖራለሁ ሲል ምድርን ፈጥሯል፡፡አምስተኛዉ
ፍጥረት ጨለማ ብርሃን ሲገኝ የሚጠፋ አልነበረም፤ ይህ በዕለተ እሁድ የተፈጠረ ጨለማ የሚያቃጥል ጨለማ ነበር፡፡ በኋላ በምንጎበኝ
ሰዓት የማሳይህ ሲዖል ተፈጥሮዉ ከዚህ ጨለማ ነዉ፡፡
በመቀጠልም በስድስተኛ ደረጃ የተፈጠረዉ አስቀድሜ እንደጠቀስኩልህ ሰባቱ ሰማያት ናቸዉ ሥማቸዉን ልንገርህና ሥለአፈጣጠራቸዉ
በኋላ እነግርኋለዉ፡፡ እነርሱም፡-ጥርሓ አርያም፣መንበረ መንግሥት፣ሰማይ ዉዱድ፣ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ኢዮር፣ራማና፣ኤረር በማለት ይታወቃሉ፡፡
ሰባተኛዉ ፍትረት ካየን በኋላ ሰባቱን ሰማያት ላስጎበኝህ ሥለምንሄድ ምድራዊ ያልሆነዉን ሰማያዊዉን ምግብ ተመግበህ
የክብር የሆነዉን ፀኣዳ (ነጭ) ለብሰህ እንሄዳለን፡፡እነ አብርሃም፣እነ ሙሴ፣ነቢያት፣ ከአዳም ጀምሮ ይመጣሉ፤ ኤልያስ ሰረገላዉን
ጭኖ ይመጣልና ተዘጋጅና ጠብቅ፡፡
ደራሲዉ፡-ምን ገዶኝ፤ ካንተ ጋር ምን ፀብ አለኝ? አድርግ ያልከኝን አደርግ
ዘንድ ዝግጁና ታዛዥ ነኝ፡፡ አንተ ግን ተግተህ ታስጎበኘኝ ዘንድ 22ቱን ሥነ-ፍጥረት በፈጠረ በእኔና በአንተ አምላክ እማፀንሃለሁ፡፡
መልዐኩ፡-ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ሥም ፣ በ99ኙ ነገደ መላዕክት ሥም፣
በ22ቱ አርዕስተ አበዉ ሥም፣ ከምድር ያለ እናት ከምድር ማህፀን እንደ አባት በወለዱት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አባትነት ሥለተፈጠረዉ በአዳም ሥም ቃል እገባልሃለሁ፡፡ እነሆ ሁሉም መጥተዋልና በቅዱስ ያሬድ ዘማሪነት በ24ቱ ካህናተ
ሰማይ አሸብሻቢነት፣ ከፊት ከኋላ ከቀኝ ከግራ እያጀብንህ ሰባቱ ሰማያትን እንጎበኛለን፡፡
በዕለተ ሰኑይ(ሰኞ) እግዚአብሔር አምላክ ሰማይ (ጠፈርን) ፈጠረ፤ በዕለተ ዕሁድ የፈጠረዉን ዉኋ ከሦስት ከፍሎ አንዱን
እጅ ዉኋ ከኤረር በታች አሰፈረዉ ስሙንም ሐኖስ ብሎታል፡፡ ይህንን ብጥብጥ ዉኋ ባቢል በሚባል ነፋስ ተሸካሚነት ከጠፈር በላይ አሰፈረዉ፡፡
ሁለተኛዉን እጅ ደግሞ በዚህች ምድር አሰፈረዉ፤ ሦስተኛዉን እጅ ከሐኖስ በታች የምናየዉ ሰማይ(ጠፈርን) ፈጠረበት፡፡ እንግዲህ ሰማይን
(ጠፈርን) ፈጠረ ሲባል ዉኋን አጠንክሮ መፍጠሩ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ስለ ሰማይ መፈጠር ይህንን ያህል ካልን ወደ ሰባቱ ሰማያት
አፈጣጠርና ባህርይ ምንነት እያወራን እንጎበኛለን፡፡
ሰባቱ ሰማያትም ሥማቸዉ አስቀድመን እንደተነጋገርነዉ ሲሆን እነዚህንም ሰማያት ሲፈጥራቸዉ ወደ ዉጭ የሚያስወጣ (የሚያሳይ)
በርም ይሁን መስኮት የላቸዉም፡፡አስቀድመን የምንመለከተዉ ይኼ ኪሩቤል የሚሸከሙት የእግዚአብሔር የክብሩ ዙፋን ሰማይ ዉዱድ ያባላል፤
ይህ ሰማይ እንደምትመለከተዉ በኪሩቤል ላይ ተዘርግቶ እንደቤተመንግስት አዳራሽ ወለል የተሰራ ሲሆን ዙፋኑም የተዘረጋበት የብርሃን
ሰማይ ነዉ፡፡ ቀጥሎ የምንመለከተዉ ደግሞ ሰማይ ዉዱድን እንደ መሠረት አድርጎ ካፀና በኋላ እንደ ግድግዳ መንበረ ስብሐትን (መንበረ
መንግሥትን) ሠርቷል፡፡ ቅርፁንም እንደ ቤተ-መቅደስ እንደ ድንኳን አድርጎ በአራት ማዕዘን ነዉ፡፡ ይህ መንበረ መንግሥት ስላሴ
በፈቀዱ ጊዜ ለቅዱሣን የሚገለጡበት (በቤተ መንግሥት ነገሥታት እንግዶችን ተቀብለዉ እንደሚያነጋግሩበት ነዉ) የከበረ ሥፍራ ነዉ፡፡
[መልዐኩም ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ ሰባት የእሳት መጋረጃ ተከፈተ ያ! ሰፊ አዳራሽ የመሰለዉ ሥፍራ ከነጭ ሐር የተሰራ የመሰለ
ልብስ የለበሱ እልፍ አዕላፋት ወተ ዕልፊት መላዕክት በሁለት ክንፋቸዉ ዓይናቸዉን ፣ በሁለት ክንፋቸዉ እግራቸዉን ፣ በሁለት ክንፋቸዉ
ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ እየተመላለሱ ቅዱስ፡ ቅዱስ፡ ቅዱስ በማለት ስላሴን ሲያመሰግኑ አዳራሹ ሲያስተጋባ አደመጥን
፡፡ ኪሩቤል በአራት ማዕዘን መንበሩን ተሸክመዉ ሥሉስ ቅዱስ ከዙፋኑ ላይ ተቀምጠዉ ያ! የእግዚአብሔር መንግሥት በሰባት የእሳት
ቅፅር ተቀፀረ፡፡ አይተን ሳንጠግብ የመንበረ ሥብሐት ደጅ ተዘግቶ ከመንበረ መንግሥት (ስብሐት) ከፍ ብሎ ጽረሐ አርያም እንደ ጣራ
እንደ ጠፈር ተሠርቶ ተቀምጧል፡፡ ይህችንም ክፍል በብርሃን ቀለም ሸልሟታል፡፡ ይህቺ ሰማይ ከሰማያት ሁሉ በላይ ናት፤ ለዚህም ነዉ
ሰማየ ሰማያት አንድም ጽርሐ አርያም የተባለችዉ አንድም የጽርሐ አርያም ተፈጥሮዋ ከሁሉም ሰማያት ይልቅ ብርሃን ናት፡፡ ከዚህም
በኋላ የሰማይ ዉዱድን ቅጽር ከጽርሐ አርያም ቅጽር ጋር አንድ አድርጎ እርሱ ባወቀዉ ማህተም ገጥሞ ትቶታል፡፡] የፅርሐ አርያምን
ዳር ድንበር መጨረሻዉን ከእግዚአብሔር በቀር ማንም አያዉቃትምና ከዚህ አልፈን አንሄድም ብንሄድም ዘልቀን አንጨርስዉም፡፡
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር በአምስተኛዉ ሰዓተ ሌሊት
ይህችን እሳት ዉዕየቷን ለይቶ ትቶ ብርሐኗን አዉጥቶ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጎዝጉዞ ዘርግቶ አንጥፎ ኢዮር
የምትባል ሰማይ ለኛ መኖርያ ሰርቷታል፤ እንደ መንበረ መንግሥትም ሰባት የእሳት መጋረጃ ጋረዳት ሰባት ቅፅር ቀጸራት፡፡ከዚኅም በኋላም
የምናያቸዉ ሁለት ከተሞች የዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላዕክት ከተማ ናቸዉ፡፡ እግዚአብሔርም እነዚህን ሶስት ከተማ ሲሰራ በነገደ እየከፋፈለ
ለየነገዱ አለቆች እየሾመ አሰማርቷል፡፡
ደራሲዉ፡-በዉኑ ይህ የማየዉ ነገር ሁሉ እዉነት ነዉ? እኔና ጓደኞቼ የጨረቃ
ብርሃን፣ የወፎች ድምፅ፣ የወንዞች ፏፏቴ፣ ተራራና ኮረብታዉ እያልን የምናሞግሳቸዉ እና የምናንቆለጳጵሳቸዉ ለካንስ ዉሸት ነዉ?
የማደንቃቸዉ ለካንስ እንዲሁ በባዶ ነዉ? የተከበርከዉ የእግዚአብሔር መልዐክ ሆይ አሁን ያሳየኸኝ ከተማ ኤረር ከተባለ ከዚህም ሌላ
እንዲሁ ያማሩና ያሸበረቁ ሁለት ከተሞች ካሉ ሥማቸዉ ማን ይባላል? ዘጠና ዘጠኙስ የመላዕክት ነገድ ከሥንት ተከፈሉ? አለቆቻቸዉስ
እነማን ይባላሉ?
ይቆየን!
ቀጣዩን በክፍል ሦስት ይዤ እቀርባለሁ፡፡
በአለም አቀፍ የዉሃ ቀን (March 22 ) ዉሃ የስጋን እድፍ እንዲያፀዳ ነፍስን ሥጋንም ፅዱ በሚያደርግ በእግዚአብሔር
ቃል ንፁሃን እንሁን፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ