እሑድ 22 ፌብሩዋሪ 2015

ዋጋ ሲተመን!




ሰዉየዉ ቤታቸዉን ለመሸጥ ቆርጠዉ ተነስተዋል፤ የመንደሩ ሰዉና ደላላ ከጠዋት የእርሳቸዉን ቤት መሸጥ መነጋገሪያ ከማድረጉ ባሻገር የማሻ ልመንህ ዋጋዉን ጣሪያ ማስነካት ገዢዎችን ከስፍራዉ ዝር እንዳይሉና ቤቱን እንኳን መግዛት ማየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዕድሜ ጠና ያለ ሰዉ መጥቶ ደጅ ይጠፋል(ያንኳኳል) የቤቱ ጠባቂም ደጁን ይከፍትና ማንን ፈልገዉ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡ የቤት ገዢ መሆናቸዉን እና የቤቱን ባለቤት (ሚስትየዉን ) እንደሚፈልጉ ይነግሩትና ይጠራላቸዋል፡፡
ሁለቱ ሰወች ስለቤቱ ጥሩነት ግቢዉም ሰፊ መሆኑን ነገር ግን ዋጋ እጅግ ዉድ እንደሆነ አዉርተዉ ገዢዉ ሴትዬዋን ለባለቤታቸዉ ዋጋዉን እንዲቀንሱላቸዉ አደራ ጭምር ነግረዉ ይሄዳሉ፤ ሚስትም ቀን እንደተባሉት አባወራ ወደቤት ሲገቡ የእግር ዉሃ  አቅርበዉ እግር እያጠቡ (ጊዜዉ እንደዛሬ የሴቶች እኩልነት ባልነበረበት ሰዓት /ፍቅር እንዲህ ዝቅ ብለዉ የሚገልፁበት ወቅት/ ወንዶች የበላይ ነን ብለዉ የሚመኩበት ዘመን/ ነበር) ቀና ይሉና ባሻዬ ዛሬኮ አንድ ሰዉ መጥቶ ቤቱን እንደሚሸጥ ጠየቀኝ እኔም እንደሚሸጥና እርሶ የሚሉትን ዋጋ ነገርኳቸዉ፤
ምን ማለት ነዉ " አንተ የምትለዉን "ማለት አንቺስ የቤቱ ባለድርሻ አይደለሁም ነዉ ወይስ ነገሩ እንዴት ነዉ?
"ማለቴ" እያሉ ቀጠሉ ሴትዮዋ ፈራ ተባ እያሉ " ሰዉየዉ እንዳሉት ዋጋዉ ትንሽ ወደድ ብሏል ለማለት ፈልጌ ነዉ"
አንቺ ሴትዮ በጤናሽም አይደለሽ? አንዴ አንተ እንዳልከዉ፣ አንዴ ደግሞ ሰዉየዉ እንዳለዉ የሚያሰኝሽ ምንድን ነዉ? ገዢ ነሽ ሻጭ?
እህ እንደዛ አላልኩም እርሶም ያሉት ዋጋ እንኳን ለገዢነት ለሻጭም ጥሩ አይደለም ይወደዳል እዚህም እንደሆነ ይህን ያህል ዋጋ ያወጣ ቤት ስላላየሁ ነዉ እንደዛ ማለቴ ሰዉየዉም ሲያዩዋቸዉ ገዢ ይመስላሉ ስለዚህ የሚሉትን ቁርጥ ያለ ዋጋ ይንገሩዋቸዉና እንሽጥ ለማለት ነዉ፡፡
እንግዲህ እኔ ያልኩትን ብያለሁ! የሚገዛ ከመጣ እንሸጣለን አለበለዚያ ቤታችን ከእኛ ጋር እነሱም ገንዘባቸዉ ከራሳቸዉ ጋር ምን ያጋጨናል ገዢ ከጠፋ እኛዉ እንኖርበታለን ምን አስጨነቀን ባዶዉን አይሆን፤
ካሉ ጥሩ! ብለዉ ሴትዮዋ እግር አጥበዉ እንደጨረሱ እራት አቅርበዉ በልተዉ ከጨረሱ በኋላ ወደ መኝታ ሄዱ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ የሁነ ሰዉ እንዲሁ መጣ! ዋጋ ተነጋገሩ ሳይስማሙ ቀሩ ሄደ!
በሌላኛዉም ቀን ብዙ ሰዎች መጡ ሳይስማሙ ቀርተዉ ተመልሰዉ ሄዱ!
አንድ ቀን ግን የመጡት ሰዉ አጥብቀዉ ተከራከሩአቸዉ ገዢም እንደሆኑ አስረግጠዉ ነገሩአቸዉ፤ ባለቤትየዉም እንድዲህ ቤቱን ከወደዱት ገንዘብ መያዝ ሳይሆን ወጣ አድርጎ መግዛት ነዉ እያሉ ከረር ብለዉ ተናገሩ፡፡ ሰዉየዉ እንዲቀንሱላቸዉና ቀብድም ሰጥተዉ ሊሄዱ እንደሚፈልጉ ቢነግሯቸዉ ሻጭ አሻፈረኝ አሉ፡፡
ከገዢ ጋር የመጡት ሰዉ ሁለቱን ለማስማማት የተወሰነ ሙከራ አደረጉ ግን ሰሚ አላገኙም፤ ሻጭ ይልቅስ የምተገዙ ከሆነ በደንምብ ዙሪያዉን እዩት፣ የግቢዉንም ስፋት ተመልከቱት፣ ካርታዉም በጄ ነዉ፣ ደግሞ በዚህ ላይ እዚህ ግቢ ዉስጥ ያለ አትክልት አመቱን ሙሉ ገበያ አያስመኛችሁም ከጊቢዉ ዞርዞር ብላችሁ ብትመለከቱ የምታጡት ነገር የለም፡፡ይልቅስ ንትርኩን ትተን ተስማምተን እናንተም ቤታችሁን ዉሰዱ እኔም የሚደርሰኝን ነገር ስጡኝና ወደሚሄድበት ልሂድ በማለት ነገሩን ቋጩት፡፡
ገዢ የሚለዉ ቢጠፋዉ "ለመሆኑ ዋጋዉ እንዲህ ጣሪያ የነካዉ ይሄ ቤቴ (ሊገዛዉ እንደሆነ ሲወስን ነዉ ቤቴ ማለት የጀመረዉ) የተለየ ከሌላዉ ምን የተለየ ቢኖረዉ ነዉ?" ብሎ ጠየቀ፤
ምን ቀረዉ ሰፊ መሬት አለህ፣ ይህን የሚያክል ትልቅ በዚህ ግቢ ላይ የተንጣለለ ቤት አለዉ፣ የአትክልቶቹን ነገር አታንሳዉ ይህ ሁሉ ተደምሮ ብለዉ ድምር ዋጋዉን ነገሩት፤
"የተቀረዉስ ገንዘብ?" ገዢ ጠየቀ
የተቀረዉማ ሰፈሩን እንደምትመለከተዉ ጥሩ መኖሪያ ነዉ፣ አየሩንም ልብ ብለህ ካየኸዉ ጤና ነዉ! እነዚህም የየራሳቸዉ ዋጋ አላቸዉ ብለዉ ዋጋቸዉን ነገሩት፤ አሁንም ሂሳቡን ቢያሰላዉ ዋጋዉ እኩል አልመጣም " የቀረዉስ?" አላቸዉ
"የቀረዉ ደግሞ በሶስቱም ማዕዘን ያሉ ጎረቤቶችህ ዋጋቸዉ ከቤቱ በላይ ነዉ ሰወች እንዳይመስሉህ  አብረሃቸዉ መኖር ስትጀምር እንዲያዉም ከመላዕክት ጋር የተጎራበትክ ነዉ የሚመስልህ እነሱም በዚህ ቤት ዋጋ መጨመር ላይ ትልቅ ድርሻ አላቸዉ፡፡እንዲያዉም እንዳልጎዳህ ብዬ ነዉ እንጂ ያንሳቸዋል! ያንሳቸዋል፤ የጎረቤቶችህ ዋጋቸዉ የሶስቱንም ደምሬ በቤቱ ላይ 200 መቶ ሺ ብር ጨምሬበታለሁ ጠቅላላዉን ስትመታዉ (ሰትረደምረዉ) ልክ አይመጣም?"
ይመጣል!
"እና ያተረፍኩብህ ነገር አለ?"
የለም!
"በል እንግዲህ የምትገዛ ከሆነ ይኸዉልህ ቤቱ ፡የማትገዛ ከሆነ ደግሞ…."
አላስጨረሳቸዉም ለቀብድ የሚሆን በእጁ የያዘዉን ጥሬ ገንዘብ ሰጥቶ ነገ ተመልሶ አጠናቆ እንደሚከፍል ተናግሮ እየተገረመና እየተደመመ ከስፍራዉ ጠፋ፡፡
ሁላችንም የምንፈልገዉ እና የጎደለብን እንዲህ አይነት ቤት እና ሰፈር ነዉ፤ የገዛናቸዉና የሸጥናቸዉ ቤቶች የህን አሟልተዉ ይሆን?
ምንደሮቻችንስ ዝም ብለን በዘልማድ ስንኖርባቸዉ ስለኖርን ነዉ ወይንስ እዉነት መኖሪያ ሰፈር ናቸዉ? ልጆች አድገዉ ለቁምነገር የሚበቁበት ናቸዉ?ጎረቤቶቻችንስ፣ እኛስ ብንሆን ለጎረቤትነት ብቁ ነን? ለኛ ዋጋ ቢወጣልን ዋጋ እናወጣለን ይሆን ወይስ ኪሳራ?

ሴት ሐዋርያ



ቤተክርስትያን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተመሰረተች መሰረቶቿ ከዐለት እጅግ የጠነከሩ፡ ሐዋርያት ከዳር ዳር ተዘዋዉረዉ ወንጌልን በማስተማር ያፀኗት፡ ሰማዕታት ደማቸዉን አፍሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ያቆዩዋት፡ ደናግላን÷ መናኞች÷ባህታዉያን በገዳም ጤዛ ልሰዉ ድንጋይ ተንተርሰዉ ድምፀ አራዊቱን ፀበ አጋንንቱን ታግሰዉ በፆምና በጸሎት ያቆዩዋት  ቅድስት ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ደጅ ነች፡፡ ከነዚህ ቤተክርስትያንን ለዛሬ ካደረሱት መካከል ሴቶች ከፊሉን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ሴቶች (እናት፡ ሚስት፡ እህት፡ … ከመሆን ባሻገር ይልቁንም በአገራችን በኢትዮጵያ ትልቅ ተሳትፎ በሁሉም ስፍራ ሲያበረክቱ ይታያሉ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የገጠሯ ሴት በብዙ ቦታ ጉልህ ድርሻ አላት፡ ልጅ ወልዳ አሳድጋ እድሜዉ ለአቅመ ትምህርት ሲደርስ እርሷ ሳትማር ልጇን ለትምህርት ያላትን ቋጥራ ከየኔታ ጋር ሰዳ ፊደል ቆጥሮ፡ መዝሙረ ዳዊት ደግሞ፡ ቅዳሴ ተምሮ፡ ቅኔ ተቀኝቶ፡ … ቤተክርስትያንን እንዲያገለግል ወይም እርሱም መፅሓፍ ዘርግቶ እንዲያስተምርና ተተኪ እንዲያፈራ የምታደርግ የቤተክርስትያን ባለዉለታ እና መከታ የሆነች ሴት ናት፤ ከዚህም ባሻገር የበረቱት እንደ እማሆይ ጀማነሽ ያሉቱ መፅሃፍ ዘርግተዉ ደቀመዛሙርት ሰብስበዉ አስተምረዉ የሚያስመረቁ ሴቶች አልታጡም ይህ ሰማአዕትነት፡ ሐዋርያነት ነዉ፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስም ብዙ መልካም ስራን የሰሩ ለቤተክርስትያን ማገር ዋልታ የሆኑ ብዙ ተጠቃሽ ሴቶች አሉ፡ የሐዋርያትን ፍኖት ተከትለዉ ከጌታ እግር  ስር የተማሩ 36ቱ ቅዱሳን እንስት ሌላ ተጠቃሽ ሴቶች ናቸዉ፡፡
     ዛሬም ቤተክርስቲያን ልጆቿን የእግዚአብሔር መንግሥት የምታስወርስ የሴት ሐዋርያ ትፈልጋለች /ያስፈልጋታል/፡፡
ሴት፡- ስንል ሌላ ተዓምር ማለታችን አይደለም እግዚአብሔር በመልኩና በአርአያው በመጀመሪያ ከወንድ የፈጠራት ፍጥረት ማለት ነው፡፡ ሴት /ሔዋን/ የህያዋን ሁሉ እናት ከአባታችን ከአዳም የግራ ጎን በተፈጠረች ጊዜ የቤተክርስቲያን መጽሐፍት /ታሪክ/ እንደሚነግረን ስላሴ የሰውን ልጅ እንፍጠር ብለው በተመካከሩ ሰዓት አብና መንፈስ ቅዱስ አዳም ደካማ ባህርይ /የሚሳሳት/ ስለሆነ አንፈጥርም ሲሉ ወልድ እዋሰዋለሁ ብሎ ሊፈጠር ችሏል፤ ለዚህ ድካሙ ረዳት አጋዥ ትሆነው ዘንድ የተፈጠረችለት የመዳን የብርታት የጥንካሬ ሐዋርያ ሌላ ወንድ አልነበረም ሴት /ሔዋን/ እንጂ፤
          ዛሬም ደካማውን መሳት ያለበትን አዳም ልትጥለው ልትገረስሰው ምክንያተ ስህተት የምትሆንበት ሳይሆን

ኦ! ቤተልሔም



ሰላምና ጤናን ዘወትር የምመኝልሽ ቤተልሄም እንደምን ሰንብተሻል አሁንም ደግሜ እላለሁ ሰላም ጤና ዕድገት ብልጽግና የእግዚአብሔር ቸርነት ካንቺ ጋር ይሆኑ ዘንድ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡
          የእንጀራ ቤት እያሉ የሚጠሩሽ ከኢየሩሳሌምም በስተደቡብ 10ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኚ እነ ቢታንያ÷ ቁምራን÷ ኬብሮን… የሚያዋስኑሽ የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባህርይ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚለመንባቸው የያዕቆብ የሥጋው ቁራጭ የአጥንቱ ፍላጭ የደሙ ምጣጭ /ሚስት/ ዐረፍተ ዘመን ሲገታት መዋቲ ሥጋዋ ግብዐተ መሬት የተከናወነብሽ ቅድስት ሀገር፤
          በመሳፍንትም ዘመን የኢብዳንና የቦዔዝ÷ የሩት የእሴይና የዳዊት ከተማ የነበርሽ÷ ልዑል እግዚአብሔር "እንደ ልቤ የሚሆን የእሴይን ልጅ አገኘሁ" የተባለለት÷ ንጉስ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል የተቀባብሽ፣ ነቢያት ትንቢት ተናግረው ይወርዳል፣ ይወለዳልም በማለት ሱባኤ ገብተው መድህኒዓለም ክርስቶስ የተወለደብሽ፤ በመወለዱም እረኞቹ በኋላም ስብአ ሰገል መጥተው የጎበኙሽ ጌታንም ሲያገኙ ያመሰገኑብሽ÷ተድላ ደስታ የተፈፀመብሽ ሰውና መላዕክት በአንድነት ህብረት የፈጠሩብሽ÷ በአንድ ቋንቋ በአንድ ዜማ አምላከ አማልክት የሆነ ጌታን ያመሰገኑብሽ÷ ቤተልሔም ዛሬን እንደምን ደረስሽ? እድሜያቸው ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ህፃናትን ሄሮድስ ባያስፈጃቸውና ደስታው ወደ ሃዘን ባልተለወጠና በጉያቸው ህፃን ታቅፈው የሰነበቱ እናቶች የሃዘን ፍም በማህፀናቸው÷ የሐዘን በትር ጀርባቸውን÷ የሃዘን ሰይፍ በጉያቸው ተሰንዝሮ ሃዘንን ባያከናንባቸው ኖሮ ምንኛ ደስ ባለ፤ አንቺ ቅድስት ሃገር ቤተልሔም ዛሬስ መንደሮችሽ፣ ጉድባዎችሽና አደባባዮችሽ ሐዘን ነው ደስታ የተንሰራፋባት? ነገሥታትና መኳንንቶችሽስ እንደምን ሰንብተዋል? እንደዚያኔው ‹የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ› እንዲሉ የሄሮድስ የልጅ ልጅ ይሆኑ? ወይስ?...  ሕዝቦችሽስ እንደምን ናቸው? ከብቶችሽስ?
          መልአኩ የዳዊት ከተማ በሆንሽ በቤተልሔም በከብቶች በረት በግርግም መወለዱን ለመልዓክ ፍራት ማራቅ ልማዱ ነውና ‹‹አትፍሩ›› እያለ ታላቅ የምሥራችን ‹‹እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› ሉቃስ 2÷10-11 በማለት የተናገረ መልዓክ ዛሬስ እየመጣ ሕዝቦችሽን ከፍርሃት ያድናቸዋል? የምስራችን ያበስራቸዋል?

ሰኞ 9 ፌብሩዋሪ 2015

ሟችና መልዐከ ሞት



ሟችና መልዐከ ሞት

እስኪ ይፍረዱ፤
እርስዎ እያሉ እነማን ይሂዱ?
ታሪኩ እንዲህ ነዉ ሰዉየዉ በዕድሜ እጅግ በጣም እጅግ የገፉ ናቸዉ ከዕለታት አንድ ቀን አጅሬ ሞት በድንገት ከተፍ ይልባቸዉና "ይነሱ ልወስድዎት ነዉ ተልኬ የመጣሁት "ብሎ በሰዉኛ ያናግራቸዋል፤ ሰዉየዉም እስከዛሬ ባላዩት እንግዳ ሰዉ እና እንዲህ አይነት አስደንጋጭ መልዕክተኛ ግራ በመጋባትም በመደናገጥም "አንተ ማነህ? ከወደየትስ ነዉ የመጣኸዉ? የላከህስ ማነዉ?" ይሉታል፡፡
መልዕክተኛዉም "እኔ መላከሞት ነኝ! የላከኝ ፈጣሪ ነዉ" ብሎ አሳጥሮ ይነግራቸዋል፤
"እህሳ ለምን መጣህ?"
"ልወስዶት ተልኬ"
"ለምን ቢባል?"
"የመሔጃ ጊዜዎት ስለደረሰ ልወስዶት… "
"በል እንግዲህ ይህን መልዕክት ይዘህ መጥተህ የለም፤ መልዕክቴንም አድርስልኝ መሔጃዬ ሲደርስ እኔ ራሴ ሰዉ እልክብሃለዉ በልልኝ" ብለዉ መልአከ ሞትን ሸኙት፤ ሞትም ተመልሶ ሄደ፡፡
ከዓመታት በኋላ ብዙ ሰዉ ከሞተ በኋላ እንዲሁ እንደከዚህ በፊቱ የነፍሳቸዉን ደጅ ይጠፋል(ያንኳኳል)
"ማነህ?"
"እኔ ነኝ!"
"አንተ ማን ….  ስም የለህም?"
"መልዐከ ሞት ባለፈዉ መጥቼ የመለሱኝ"
"ታድያ ለምን መጣህ? አትምጣ እኔ ራሴ ሰዓቴ ሲደርስ መልዕክተኛ እልክብሃለዉ ብዩህ የለ?"
"አይ ይበቃዎታል፤ እርሶ እድሜ ልክዎትን ቢጠበቁ ጊዜዬ ደርሷል ብለዉ ሰዉ አይሰዱም ይልቅስ አሁን ይነሱ እና እንሂድ አላቸዉ"
እሳቸዉ ግን በፍፁም ሊሄዱ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ መልዕክተኛዉም መልአከ ሞት እንደምንም ሊያግባባቸዉ ሞከረ፤ እሳቸዉ ግን አሻፈረኝ አሉት፡፡ ሞትም ቀረብ ብሏቸዉ
" እስኪ ይፍረዱ ፤
እርስዎ እያሉ እነማን ይሂዱ?" አላቸዉ ይባላል፡፡
አሁንም ስልጣንን መልቀቅ እና ሞትን የሚፈሩ ብዙዎች ናቸዉ፤ ሆኖም ግን መልዐከ ሞት እንዳለዉ እናንተ እያላችሁ እነማን ይሙቱ? እነማንስ ከስልጣን ይዉረዱ?
ጆሮ ያለዉ ይስማ! ልብ ያለዉ ልብ ይበል!

ሰኞ 2 ፌብሩዋሪ 2015

ከማይረባ ፍቅር የረባ ጥል ይሻላል



ነገሩ እንዲህ ነዉ ወደ ስራ ገበታችን ለመሄድ ለገሃር ባቡር ጣቢያ የከተማ አዉቶቡስ እየጠበቅን እንገኛለን፤ 36 ቁጥር ያለወትሮዋ በጣም ከማርፈድዋ የተነሳ መሰላቸትም ድካምም ይታይብናል አንድ ልጅ'ግር ከሰልፉ መካከል ደክሞኛልና አረፍ ልበል በማለት ከፊቱና ከኋላዉ ላሉት ወረፋ ጠባቂዎች አሳዉቆ እዛዉ አከባቢ ድንጋይ ላይ አረፍ አለ፡፡ ሰልፉ እጅግ እየረዘመ ከመሄዱ የተነሳ አንድ አዉቶቡስ ብቻ የሚችለዉ አይመስልም ነበር፡፡
ቀርታ አልቀረችም ተስፋ ቆርጠን ሳናበቃ መጣች፤ ሁሉም ኪሱን ፣ ቦርሳዉን ፣ …. መፈታተሸ ጀመረ ተልመጥምጦ የነበረዉ ሰልፍ ቀጥ አለ፤ ፀጥታ ነግሶበት የነበረዉ ስፍራ አዉራዉ እንደተነካ የንብ መንጋ ታወከ፡፡ ቲኬት ቆራጩ ጎልማሳ እስክርቢቶዉን ከደረት ኪሱ አዉጥቶ ጆሮግንዱ ላይ ሻጥ አድርጎ ሰልፉን እኩል ገምሶ ጀብነን ብሎ ቆመ፡፡ ሰዉ ከቅድሙ ይልቅ ደሙፈላ፣ በዉስጣቸዉ ማጉረምረም የጀመሩትን ሳንቲም አምጡ አታምጡ ላይ ንትርኩ ጨመረ፡፡ በዚህ መካከል ያ ወጣት ወደሰልፉ ተመለሰ ከኋላ ከረጅም ርቀት ላይ ከሰልፉ ሌላኛዉ ጠርዝ ላይ "ተመለስ" የሚል ጩኸት ሰልፉን ድንጋጤ ፈጠረበት፤ ሁልም ሰዉ ድምፁ ወደ ተፈጠረበት  አቅጣጫ አይኑን ላከ ሰዉየዉ እየተንደረደሩ ሲመጡ ጤነኛ አይመስሉም ነበር፡፡"ዉጣ ብዬሃለዉ ዉጣ!" ጩኸቱ በረታ፣ እስከዚህ ሰዓት የጉዳዩ ባለቤት ጉዳዩን ልብ አላለዉም እጁን ሳንቲም ካስቀመጠበት ኪሱ ከቶ እያለ ክንዱን አፈፍ አርገዉ ያዙት …. በድንጋጤ እጁን እንኳን ሳያወጣ ደርቆ ቀረ፡፡ "ዉጣ! ባለጌ! እኛ እዚህ ቆመን የማነህ ፈጣጣ ከየትም መጥተህ ዘዉ የምትለዉ?"
እኔ ነዉ?
"ከአንተ ጋር እያወራሁ እኔ ነዉ ትላለህ ? ደፋር! "
ምን አደረኩ?
" ዉጣ ሰልፉን አትረብሽ"
ለምን?
" ሰዉዬ ነግሬሃለዉ በሰላም እንሂድበት ሰልፉን አትረብሽብን"
ሰዉየዉ እጅግ ትልቅ ከመሆናቸዉም የተነሳ አብዝቶ መናገርም "ባህላችን " ስላልሆነ ለረጅም ሰከንዶች ዝምታን መረጠ ሰልፉ ግን ስራዉን አላቆመም ልጁም ወደፊት ሰዉየዉም ሰልፉን እየታከኩ ፣ልጁን እየተሳደቡ እና እያመናጨቁ ወደፊት እያመሩ ነዉ፤
ከሰልፉ ኋለኛዉ ክፍል እንደገና በዕድሜ የሚቀርቧቸዉ ሰዉ " እስካሁን ሰማኖት ልጁወረፋዉ ነዉ እርሶ ወደ ቦታዎ ይመለሱ"
"ይቺ ደሞ ምን ትላለች? አንቺ ደሞ ምንሽ ተነካ?"
"ምንም አልሆንኩ! ልጅ ከሁላችን በፊት እዚህ ቆሞ ነበር ደከመዉ ከፊትለፊቱና ከኋላዉ ላሉት አሳዉቆ አረፍ አለ፤ ተራዉ ሲደርስ መጣ አንተ ምን ቤት ነህ ከኋላዉ መተህ ቡራከረዩ የምትለዉ? ዉጣ!"ልጁ ልቡ ተረጋጋ ስድቡና አላስፈላጊዉ ትችት ከርሱ ላይ ዘወር አለለት፡፡
ሰዉየዉ ግን አሁንም ሊበርዱ አልቻሉም ፤ ልጅየዉ ጎረቤቱ የሆነች ልጅ ታማ ሆስፒታል አድሮ ነዉ የመጣዉ ምንም እንኳን እንቅልፉም ድካሙም ቢኖርበት ስራ ስለነበረዉ ላለመቅረት ነበር ወደ ስራዉ ለመሄድ አዉቶቡስ እየጠበቀ የነበረዉ እና ሰልፍ ላይ ይህ ችግር የተፈጠረዉ፡፡
አባባ አላቸዉ፤ እኔኮ እያጭበረበርኩ አይደለም ተሰልፌ ነበር ሲደክመኝ  አረፍ ለማለት አስፈቅጄ ነዉ የሄድኩት እባክዎ በኔ የተነሳ አይጣሉ፡፡
"ዝም በል! አይናዉጣ!"
በቃ! እንዲያዉም ይሄ ሁሉ ፀብ እንዲህ ደክሞኝ እና እንቅልፍ ይዞኝ እያለ ስራዬን አክብሬ ወደ ስራ ገበታዬ ባልኩኝ ነዉ አይደል? ጥሩ ምክንያት ሆኑኝ በቃ አልሄድም! አያዉቁኝም አይደል?እኔም ከዛሬ በፊት አይቼዎት አላዉቅም፣ በዕድሜም ሆነ በሰፈር አንገናኝም፣ ጎረቤት ሆነን ቢሆን ኖሮ ጉድ በፈላ ነበር፤ ነገር ግን ከዛሬ ወዲህ አንገናኝም፡፡ ብዙ ፀቦች አይቼ አዉቃለሁ የእኔ እና የእርስዎ ፀብ ግን ይለያል ፀብ በደላላ የሚፈልጉ ነዉ የሚመስሉት ለነገሩ ከማይረባ ፍቅር የረባ ጥል ይሻላል፤ሰዉ እንደ እኔ እርሶ የረባ ፀብ ከተጣላ በሰፈር ሰዉ በሽማግሌ ይታረቃል አስመሳይ ፍቅር ግን ከሆነ እዉነተኛ ፍቅር ሳይፋቀሩ እንዲሁ ያልፋሉ ብሏቸዉ አመስግኖ ጥሏቸዉ ሄደ፡፡
ከማይረባ ፍቅር የረባ ጥል ይሻላል! አለቀ፡፡

ሰኞ 26 ጃንዋሪ 2015

ሊሰራ የማይወድ አይብላ



ዳንኤል ክብረት "ቁስል ተራ " ብሎ የፃፈዉን ካነበብኩ በኋላ በልቤ ሲላወስ የነበረ ሐሳብ ስለነበር ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ልተነፍስ ተነሳሁ፤ የርሱን ሐሳብ ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ፡፡ http://www.danielkibret.com/2015/01/blog-post_20.html#comment-form ወዳጄ ዳንኤል ሥራ አልሆን ሲለን ወደ ልመና ከገባንኮ ቆይተናል፤ አንተ የአካሉን ሥትል ሰዉኮ ለመለመኛ ብሎ ልጅ መዉለድ ከጀመረ ሰነባበተኮ፡፡ በአንድ ወቅት ትራንስፖርት ዉስጥ ቁጭ ብዮ የሆነ ሰዉ ጋቢ ተከናንቦ የጉሉኮስ ዕቃ ታቅፎ አጥሚት አፉ ላይ እንደደረቀ ህፃን እየበረረ ታክሲ ዉስጥ አስጥሉኝ እያለ ገባ ከበስተጀርባዉ ስንመለከት ማንም የሚከተለዉ ሰዉ ስናጣ የባሰ አትኩሮቶቻችንን ሳበዉ …. ይህ ሰዉ ለካንስ ይህቺ ዘዴዉ የመለመኛ መንገዱ ነበረች ……. ወንበር ከመያዙ የልመና ቃላት ማዥጎድጎዱን ተያያዘዉ፤ ( ባጭሩ ታሞ ጥቁር አንበሳ ተኝቶ እንደነበረ፣ ከሁለት ወር በላይ እንደቆየ፣ ከክፍለ ሃገር እንደመጣ፣ በህመሙ ምክንያት ረጅም ጊዜ ስራ ገበታዉ ላይ ስላልተገኘ ከሥራ እንደተቀነሰ፣ በዚህ ምክንያት ቤተሰቡን ማስተዳደር ባለመቻሉ የልጆቹ እናት ጥላዉ ቤተሰቦቿ ጋር እንደሄደች፣ አሁን እንዲህ ሆኖ የተገኘበት ምክንያት ለህክናዉ የሚሆን ገንዘብ በመጨረሱና መድሐኒቱን ከወሰደ በኋላ/ በፊት የሚመገበዉ ምግብ በማጣቱ ከአልጋዉ ተነስቶ ለልመና እንደወጣ ነበር የነገረን፡፡ አስጥሉኝ ማለቱም ከሆስፒታሉ ሲወጣ ያዩት የጥበቃ ሰወችም ሆኑ ሲወጣ ያዩት የጤና ባለሙያዎችን ማለቱ ነበር፡፡) ሁላችንም ያለንን ያህል በተለመደዉ ኢትዮጵያዊ ሩህሩህ ባህሪያችን ሰጠነዉ፡፡ሰዉየዉም ለምስጋና እንኳን ጊዜ ሳያገኝ፣ ሊሄድበት የፈለገዉንም ፒያሳ ሳይደርስ እዉነት ይሁን ዉሸት ለጊዜዉ ባናዉቅም "የምበላዉ ካገኘሁ በቃ ወደ ሆስፒታል ልመለስ" ብሎ ወረደ፡፡
ከቀናት በኋላ ደግሞ ይኸዉ ሰዉ ራሱ በምሰራበት መስሪያ ቤት ጉዳይ ኖሮት ሊስተናገድ በጣም አምሮበት ጥቁር ሙሉ ልብስ በነጭ ሸሚዝ ለብሶ ጥቁር መነፅር ሰክቶ ከተፍ አለ፤ ድኖ በማየቴ ፈጣሪዬን ጤናዉን ስለመለሰለት አመሰገንኩት፡፡ ያንን ዕለት ስላደረግነዉ መልካም ነገር ደስታ እና ኩራት ተሰማኝ … … የአንድ ሰዉ ህይወት ታድገናልና፡፡ሥራ ቦታ መሆኔ ነዉ እንጂ እንኳን እግዚአብሔር ማረህ፣ እንኳን ደስ አለህ፣ … ብለዉ ደስ ይለኝ ነበር፤ ባለማለቴ እጅግ ቆጨኝ፡፡
በዚያኑ ሳምንት ቅዳሜ ዕለት አራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ሄጄ ሲኒማ አምፔር ጋር ስወርድ ወርቅ ቤቶቹ ጋር ያደፈ ጋቢ ለብሶ ያቺ የፈረደባትን የጉሉኮስ ዕቃ ታቅፎ እያቃሰተ ወገን አድኑኝ እያለ የመጀመሪያ ቀን ያቀረበዉን ምክንያት እየደረደረ ይለምናል፤ በሱ ቦታ እኔ አፍሬ እያማተብኩ አለፍኩት የዋሁ ህዝብ ጉዳዩን አላወቀ ሳይኖረዉ ካለዉ ላይ የቀረችዉን እያነሳ ሳይሳሳ ይሰጣል፡፡ የሌለዉ ከንፈሩን በሀዘኔታ እየመጠጠ "እግዚአብሔር ይማርህ እያለ ያልፋል" የሰዉ ልጅ ለምንድነዉ ርካሽ የሆነ ባህሪ የሚመቸዉ ብዬ ታዘብኩ፤ ….
ከጊዜ ብዛት ከተማ ዉስጥ ስዘዋወር በተደጋጋሚ ሳገኘዉ ባህሪዉ መጥፎ የምንለዉ አይነት ሰዉ ነበር ( ያጨሳል፣ በጣም ይጠጣል፣ ቁማር ይጫወታል፣ … ) ከረጅም ጊዜ በኋላ ለሆነ ንግስ በዓል ነጭ በነጭ ለብሶ ከጓደኞቹ ጋር አገኘሁት የኔ ቢጤ ሲለምነዉ መርጦ አዉጥቶ 10 ሳንቲም ሲሰጥ አየሁት፤ ፈራ ተባ እያልኩ "መስጠትም ታዉቅበታለህ? " አልኩት፡፡ "ምነዉ መስመር ላይ ተገጣጥመን እናዉቃለን እንዴ ?"አለኝ፤ ….
ባጭሩ ከዚህ ሰዉ ጋር ባደረግነዉ ዉይይት የቅድሙ ታሪክ ሁሉ ዉሸት እንደሆነና ከመስራት መለመን አዋጭ እንደሆነ በድፍረት ነገረኝ፤ ሰዉ ሆይ ስራ መስራትን ጠልተን ልመናን የምንኮራበት እና የምንመርጠዉ እስከ መቼ ነዉ?ልንሰራስ የማንወደዉ ለምንድን ነዉ?
ሊሰራ የማይወድ አይብላ! ያልሰራ አይብላ አላልኩም ስራ አጥቶ ሊሆን ይችላልና፤ በየስራ ገበታዉም ያላችሁ ለታይታ የምትሰሩ፣ የአለቃን ፊት እያያችሁ የምታለምጡ፣ የሰዓት መቆጣጠሪያ ላይ ለመፈረም ብቻ የምትገቡ፣ … እግዚአብሔር ልብ ይስጣችሁ፡፡

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...