ሐሙስ 29 ኦክቶበር 2020

ሁለት ምርጫ አለን

 ሁለት ምርጫ አለን

ደረሰ ረታ
19/2/2013

ሕጻናት ንጽሕ ናቸው፤ ለዚህም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲያስተምር " እንደ ሕጻናት ካልሆናችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት አትወርሱም" ሲል ያስተማረው።

ሕጻናት:-
ከእናት እና ከአባታችሁ ማንን ትወዳላችሁ?
ከከረሜላ እና ከቸኮሌት የቱን ትመርጣላችሁ?
ከእናት ከአባት ከእህት ወንድማችሁ ማንን የበለጠ ትወዳላችሁ?
ወዘተረፈ
ተብለው ለምርጫ ሲጠየቁ
እናቴንም አባቴንም፣
ከረሜላም ቸኮሌትም፣
እናቴንም አባቴንም እህት ወንድሜንም ይሏችኋል።
ደግማችሁ ከሁለቱ አንዱን ምረጡ ብላችሁ ስታስገድዷቸው ሁሉቱንም/ሁሉንም ብለው ድርቅ ይላሉ። ሕጻናት ንጽህ ናቸውና። እምቢ ብትሏቸው እንኳን እምቢ ተጣልቼሃለው/ሻለሁ ብለው ጥለዋችሁ ይሄዳሉ አንዱን ብቻ አይመርጡም። ሌላኛውን ማጣት አይፈልጉምና።

እኛስ?

ከገንዘብና ከሰው፣
ከእምነትህ እና ከፖለቲካ፣
ከአገርህ እና ከጥቅምህ፣
ከወንድምና ከእህትህ፣
ከሥራህ እና ከሃላፊነትህ፣
ወዘተረፈ
ተብለን ስንጠየቅ ምላሻችን ብለን የምንሰጠው ይበልጣል ብለን ያሰብነውን አንዱ ነው እንጂ ምንም አይነት ማስረጃ አግኝተን አይደለም።ተልቀናል/አድገናል ብለን ስለምናስብ ስሌት ( calculation) ውስጥ እንገባለን።

አለማወቃችን ግን ከልጆች የዋህነት እና የልብ ንጽሕና ስለማይበልጥ ምርጫችን ስሕተት ይኖርበታል። በምሳሌ ስንመለከት ጥያቄው ከእናት እና ከአባት ለመምረጥ ምን መስፈርት ተቀምጦልን ነው አንደኛቸውን የመረጥነው? ከገንዘብ እና ከሰው እንዴት ልንመርጥ ቻልን? ሁለቱን አንድ የሚያደርጋቸው ምን መለኪያ ተገኝቶ ነው? እነዚህም እስኪ ይቅሩና ማን ነው አንዱን ብቻ ምረጡ ያለን? እንዲሁ ከሁለት ነገሮች መካከል አንዱን መምረጥ በምርጫ ሕግ ሥለምናውቅ እንጂ።

ሕጻናት ግን በቅንነት እና በፍቅር ሁለቱንም ይመርጣሉ።

አንዳንዶች ሰውን ከገንዘብ፣ ገንዘብን ከሰው ጋር ያነጻጽሩልንና አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ አድርገው በግድ አንዱን ምረጥ ይሉናል። ሁለቱም አስፈላጊነታቸውና መለኪያቸው ለየቅል ነውና።

ስለዚህ እንደ ሕጻናት ስንሆን ሁሉም የኛ ይሆናል። በ"እውቀት" ውስጥ ያጣነውን በየዋህነት እና በቅንነት ውስጥ ሁለቱንም እናገኘዋለን።

ሕይወትን በስሌት መኖር ሐጥያት ባይሆንም ቅሉ በየዋሕነት ሁለቱንም መምረጥ ግን ብልሕነት ነው ሁለቱንም ያስገኘናል እንጂ አያሳጣንም።

ገንዘብንም ሰውንም ይዞ መኖር ይቻላልና።

ከገንዘብ እና ከጤና ምረጡ ለሚሏችሁ ገንዘብንም ጤናንም እንደምትመርጡ ንገሯቸው።

አገርና እምነትን ለሚያስመርጧችሁ ሁለቱንም እንደምትመርጡ ንገሯቸው።

ከፖለቲካ እና ከመንፈሳዊነት ሲያስመርጧችሁ ሁለቱም ምርጫችሁ እንደሆኑ አረጋግጡላቸው።

የሰውን ልጅ ትክክል የሚያደርገው ከሁለት አንዱን መምረጡ ሳይሆን የመረጠውን እንዴት ይጠቅምበታል የሚለው ነውና። አንዳንዶች ገንዘብ ሃጢያት እንደሆነ ያወሩናል ድሕነት ጽድቅ ነው ወይ? ብዬ እጠይቃቸዋለሁ።

እንደዛ ቢሆን ኖሮ ድሆች ሁሉ ጻድቅ ሐብታም ሁሉ ሐጥአን በሆኑ ነበር። ነገር ግን እውነታው ሐብትን በአግባብ መጠቀም አለመቻል ነው ጽድቁም ሐጥያቱም።

ስለዚህ ሁላችንም ሁለት ምርጫ አለን። አንድም ሁለቱን አንድም ሁሉንም መምረጥ።

#######$$#######$$$#######

እኔን ለማግኘት ጽሁፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁሉ ወደ'ኔ ይመሩዎታል።

My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

ረቡዕ 28 ኦክቶበር 2020

ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።

 ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።


ደረሰ ረታ
18/2/2013

ፍቅር ቃላት ብቻ ሳትሆን መስዋእትነትን፣ ክርስትና ምኞት ሳትሆን ሕይወት ናትና መኖርን፣ ማድረግን፣ ትሻለች። የአገር እና የቤተ እምነቶች ጥቃት፣ የክርስቲያኖችን እና የሙስሊሞች ስደትና ሞት፣ የአንድነታችን መላላት እየተመለከትን እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ ባይደረግ ኖሮ፣ እያልን ከመመኘት ባለፈ በተግባር የተፈተሸ፣በአርአያነት የተሞላ ማንነት፣ ፍቅርና ሕይወት ይፈልጋል።

ስለዚህ ባለን አጋጣሚ ሁሉ በተሰጠን እድሜና ጤና በየአጥቢያችን፣ በተለያዩ መንፈሳዊ ማህበራት፣ ተሰባስበን በያለንበት የተለያዩ ሕብረቶች በመሳተፍ መንፈሳዊነታችንን መገንባት፣ አገልግሎትን ማበርከት፣ አብያተ እምነትን እና ምእመናንን መርዳት፣ ወዘተ ይጠበቅብናል።ከአንድ ሁለት ይሻላልና።

አንዳንዶቻችን ከንፈር ስንመጥ እና ነገሮች አቅጣጫቸውን እንዲስቱ የተነሱበትን አላማ ይበልጥ እንዲያሳኩ ከማራገብ የዘለለ ፋይዳ የለንም።

አንዳንዶች ደግሞ አይተው፣ ሰምተው፣ ስሜቱን ተገንዝበው ዝምምምም የሚሉ አሉ። አይጠቅሙ አይጎዱ።

ነገር ግን ይህቺን አገር ወደፊት ለማስቀጠልም ሆነ ከጉዞዋ አደናቅፈው ወደኋላ ከሚያስቀሯት ይልቅ አፋቸውን ለጉመው ዝምታን በሚመርጡት ነው። ከአጥፊዎች ይልቅ የ"ገላጋዮች" ቁጥር እጅጉን ይልቃልና።

በልማትም ይሁን በጥፋቱ የሚሳተፉ፣ በማሳደድም ይሁን በማፈናቀል፣ በመግደልም ይሁን አካል በማጉደል፣ በመቀማትም ይሁን ባለማገላገል ከሚሳተፉት እንደ አገርም ሆነ እንደ መንደር ቁጥራቸው የሚበዛው አያገባንም ብለው ዝም ብለው የተቀመጡት ናቸው።

አገርም ሆነ ሕዝቡ አብዝቶ የሚጎዳውም ይሁን የሚጠቀመው ባጥፊዎች ወይም ባልሚዎች ሳይሆን በብዙ ዝምተኞች ምክንያት ነው።

አብዛኛው ሰው በመኖሪያ ቤቱ፣ በመኖሪያ ሰፈሩ፣ በመሥሪያ ቤቱ፣ በእድር በማህበሩ፣ በእቁብ በስብሰባው፣ መኖሩ አይታወቅም፤ እርሱም ብቻ አይደለም ምንም አስተዋጽኦ አያደርግም።ስለዚህ ሰዎች መኖሩን አያውቁትም። በክፉም በደግም ሥሙ አይነሳም።

እኔ ግን ባለሁበት አካባቢ፣ ባለሁበት ማህበረሰብ፣ ባለሁበት መሥሪያ ቤት፣ ባለሁበት እቁብና እድር ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ቢያቅተኝ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። ኖሬ ከሌሎች በተሻለ ባልጠቅምም የለም በሚባል ግን በሥሜ ችግር እንዲፈጸም፣ በዝምታዬ ብዙዎች እንዳይጎዱ ስለምፈልግ።

እስኪ በየስብሰባው በዝምተኞች ችግር በጥቂት ተናጋሪዎች ስንት ውሳኔ እንዳለፈ፣ ስንት ጥፋት እንደተፈጸም፣ ስንት ሐብት እንደተመዘበረ፣ ስንት ሕይወት እንደተቀጠፈ፣ ስንት ትዳር እንደፈረሰ፣ ስንት ቤተሰብ እንደተበተነ፣ ስንትና ስንት ውድቀት አገሪቱ ላይ እንደ ደረሰ።

ከእድር ስብሰባ እስከ ፓርላማ ስብሰባ ስንት ዝምተኞች ስንት መኖራቸው እንኳን የማይታወቁ ሰዎች ዋጋ እንዳስከፈሉን የደረሰብን እናውቃለን።

ባላችሁበት ስፍራ፣ የሃላፊነት ቦታ፣ የተወከሉበት መድረክ፣ በተሰጠዎት አደራ፣ ... ብናገር ባልናገር ባደርግ ባላደርግ በማለትዎትና ዝም በማለትዎ ስንቶች ዋጋ ከፍለዋል? አገር ዋጋ ከፍላለች?

ትልቅ ቦታ አይሁን ተቀጥረውም ይሁን ተመርጠው፣ ተወክለውም ይሁን በበጎ ፈቃደኝነት በሚያገለግሉበት ቦታ የርስዎ ድርሻ ትልቅ እንደሆነ ያምናሉ? ሚሊዮኖች ከጀርባዎ እንዳሉ ይገነዘባሉ? የርስዎ ዝምታ፣ የርስዎ ዝንጋታ፣ የርስዎ አይቶ ማለፍና ሰምቶ መቻል ዋጋ እንደሚያስከፍል ምን ያህል ይሰማዎታል?

ባሉበት ቦታ የርስዎ እንዳሉ/መኖርዎ መታወቅ ማድረግ፣ ተጽእኖ መፍጠር፣ ድርሻዎትን በአግባቡ መወጣት፣ ... የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የግዴታ ጉዳይ እንጂ።

ብዙዎች እያሉ እንደሌሉ ተቆጥረዋል፣ ብዙዎች ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል፣ ብዙዎች እስከ መፈጠራቸው ተዘንግተዋል፣ ... በነዚህ ምክንያት አገርና ሕዝቡ ዋጋ እየከፈሉ ነው።

እኔ ባለሁበት አከባቢ መኖሬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። እርስዎስ?

#$$$#####@@@@####$$$$$&&&&$$#

እኔን ለማግኘት ጽሁፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁሉ ወደ'ኔ ይመሩዎታል።

My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

ማክሰኞ 27 ኦክቶበር 2020

ከ"ሚሰበር ይሰንጠር"

 ከሚሰበር ይሰንጠር

ደረሰ ረታ
17/2/2013

አንዳንዶች ከትህትናም ይሁን ከስንፍና በተለይ መንፈሳዊ ነገሮችን ላለማድረግ እኔ ይቅርብኝ፣ እኔ ለዚህ ነገር ብቁ አይደለሁም፣ ከኔ የተሻሉ ሌሎች አሉ፤ በማለት ወደኋላ ሲያፈገፍጉ ይታያሉ።

ይሕ ተግባር ንሰሐ ለመግባት፣ ትዳራቸውን በመንፈሳዊ መንገድ ለመጀመር፣ በአገልግሎት ለመሳተፍ፣ ከዚህም አልፈው ስለአገራዊ ጉዳይ እነርሱን እንደማይመለከት ይሰማቸዋል። አገር የምትመራው በፖለቲከኞች ብቻ ይመስላቸዋል፤ ቢሆንም ቅሉ ፖለቲካን ይፈሩታል ይሸሹታልም።

ነገር ግን የእምነት ተቋምም ይሁን አገር ባላዋቂዎች ባህር ላይ እንዳለች ታንኳ ስትናጥ እነርሱም በዚህ ጉዳይ ጤናቸውን ያጣሉ። ደስታቸውም ሆነ ሰላማቸው ከሁለቱ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነውና።

ስለዚህ:-

ጸሎት ከሚቀር በዝንጉእ ልቡናም ቢሆን ይጸለይ፣
ጾም ከሚቀር ንሰሐ ባንገባም ምጽዋት ባንሰጥም እንጹም፣ በጥቂቱ ስንታመን በብዙ የሚሾም ፈጣሪ ያበረታናልና።

ሥራችን ውጤት አልባ፣ ፍሬ ቢስ ቢሆንም፣ ምንም እንኳን እኛ ብንደክምም፣ ጥቅም ባናገኝበትም እንሥራ፣ ጋን በጠጠር እንዲደገፍ አገርም የኔ ድጋፍ ያስፈልጋታልና።

ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ የሆነ ማንነት ቢኖረንም ቅሉ ተመልሶ ጭቃ ብንሆንም ንስሐ እንግባ፤ እንጹም፣ እንጸልይ፣ ሥጋውን ደሙን እንቀበል፣ እናገልግል፣ ከስንፍና በራቀ ትህትና ውስጥ ሆነን ማገልገል ይጠበቅብናል መንፈሳዊነትም ይገባናል እንበል።

ሰይጣን እና ውሻ አንድ ናቸው፤ ውሻ የእውሩን በትር እንቅስቃሴ አይቶ እንዲሸሽ አይነስውርነቱ ውሻን በበትሩ መከላከል እንዳያግደው ሁሉ እንዲሁ ሰይጣንም በኛ ጸሎት እንደዛው ነው የምንጠራው ሥመ አምላክ ሃይል አለውና። ምንም የልብ ንጽሕና ባይኖረንም የአፋችንን እንቅስቃሴ ተመልክቶ ይሸሻልና እንጸልይ። ጸሎት ካለመጸለይ ይሻላልና። አገርን ማገልገል ካለማገልገልና በሙስና አገርን ከማቆርቆዝ ይሻላልና። ሁሉም ባለበት መስክ ታማኝ ሆኖ ካገለገለ አገር ትበለጽጋለችና።

እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ በሕይወቱ ውስጥ እምነቱ የሚያስገድደውን ተግባር በትንሹም ቢሆን ቢያከናውን ካለማድረግ ይሻላል። ከ"ሚሰበር ይሰንጠር" ይላሉና አበው፤ የአገር ጉዳይ የአብያተ እምነት ጉዳይ ተሰብሮ ከሚጣል ተሰንጥሮም ቢሆን ቢቀጥል ይሻላልና። ነገ ስንጥሩ መደፈኑ አይቀርምና።

ስለዚህ ከአገር እና ከየእምነት ሥፍራችን ጋር ያለን ቁርኝት ተሰብሮ ከሚቀር ተሰንጥሮም ቢሆን ይቀጥል ነገ ሌላ ቀን ነውና።

በሌሎች አስተማሪ ጽሑፎች እንድንገናኝ ከታች ያሉትን ሊንኮች ይጠቀሙ።

My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

እሑድ 11 ኦክቶበር 2020

በኛ ይብቃ ...

 በኛ ይብቃ ...

ደረሰ ረታ
1/2/2013

አደጋዎች በሽ ናቸው።

የትራፊክ አደጋ፣ በህክምና ስህተት የሚደርስ አደጋ፣ በብሔር ግጭት የሚደርስ አደጋ፣ በሃይማኖት ጥላቻ የሚደርስ አደጋ፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚደርስ አደጋ፣ በተፈጥሮ ክስተት የሚደርስ አደጋ፣ በሰው ሰራሽ በእቅድ የሚደርስ አደጋ፣ ወዘተረፈ በእነዚህና በሌሎች አደጋዎች የብዙዎች ንብረት ወድሟል፣ አካል ጎድሏል፣ ለስደት ተዳርገዋል፣ ለሞት ተዳርገዋል።

የተረፉት፣ የተጎጂዎች ቤተሰብ፣ የቅርብ ሰዎች በየሚድያው ይቀርቡና "በኛ ይብቃ ... ከኛ ተማሩ" ሲሉ ይደመጣል።

ከመች ወዲህ ነው ጥቃት መማሪያ የሚሆነው?

ከመች ወዲህ ነው ጥቃት መማሪያ የሆነው?

በምን መልኩ ነው መገደል መማሪያ ሊሆን የሚችለው?

እነማንስ ተምረው ድርጊታቸውን አቆሙ?

ከዚህ ልምድ የሚቀስሙት ገዳዮች ወይስ ሟች ነው ትምህርት የሚወስደው?

እኔ በበኩሌ ከዚህ አልማርም፤ በገዳዮች ስሕተት መሞት በቃኝ። በአጥፊዎች ተገፍቼ መኖር በቃኝ። በአሳዳጆች መፈናቀል በቃኝ።

እመራሃለሁ የሚለኝ መንግሥት ከስጋት ነጻ ሊያደርገኝ ይገባል፣ በዚህ ላይ ለተሰማሩት ፍርዲ ሊሰጥልኝ ይገባል፣ ሁሉንም እኔ እየሆንኩ በኔ ይብቅ እያልኩ መኖር በቃኝ።

በብሔር ግጭት የምሰደድ የምሞት እኔ፣ በፖለቲካ ሽኩቻ ንብረቴ የሚዘረፍ እና የሚወድም እኔ፣ በሐይማኖት ግጭት የምገፋ የማምለክ ነጻነቴን የማጣ እኔ፣ ... በቃኝ።

በኛ ይብቃ እያልኩ አልኖርም፤ ፍትህ ይገባኛል።

በሕክምና ስሕተት ህይወት የሚቀጥፉ፣ በፖለቲካ ቁማር ጫወታ ሕዝብ የሚያሰቃዩ አገር የሚያተራምሱ፣ በተረኝነት መንፈስ በሕዝብ ገንዘብ የሚጫወቱ፣ በግዴለሽነት በትራንስፖርት በመኪና አደጋ አካል የሚያጎድሉ ንብረት የሚያወድሙ ሕይወት የሚቀጥፉ የሚቀጡበት ሕግ ይሻሻልልን። ደማችን ፈሶ፣ ንብረታችን ተዘርፎ፣ ተስፋችን ሰልሎ፣ ሕይወታችን አልፎ አይቅር።

"በኛ ይብቃ" ይብቃን። በእነርሱም ተመጣጣኝ ቅጣት ይጣል።

#በወሊድ_ምክንያት_በሕክምና_ስሕተት_መሞት_በቃን
#በመኪና_አደጋ_መሞት_በቃን፣
#በሐይማኖት_ተለይቶ_መሞት_በቃን፣
#በእርስ_በርስ_ግጭት_መሞት_በቃን፣
#በተረኝነት_መገፋፋት_በቃን።

@deressereta

ከወደዱት ያስተምራል ብለው ካሰቡ like እና share ያድርጉ።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com 

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...