ዓርብ 29 ማርች 2013

ይድረስ …

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ እጅግ የከበርሽ ፀጋን የተመላሽ ሆይ ምስጋና የባህርይ ገንዘቡ ከሆነው ልጅሽ ቀጥሎ የምትመሰገኚ የአምላክ እናት ሆይ አመሰግንሻለሁ፡፡
ልጅሽ ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከምድር አሸዋ እጅግ የበዛ ሐጢያቴን ሳይመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ እስከዛሬ እያወኩኝ በድፍረት ሳላውቅም በስህተት የሰራሁትን በደል ሳስብብኝ ለዚህች ሰዓት ያደረሰኝ በአንቺ ምልጃና ፀሎት ነውና፡፡
ድንግል ሆይ ‹‹አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ ከአዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ›› ብለው አባቶች አመሰገኑሽ እመብርሃን በእውነት ያለሐሰት ከበደሌ ብዛት ካንቺ ምልጃ አንፃር የአዳም ሳይሆን ተስፋነትሽ የኔ የብቻዬ ነው ድንግል ሆይ ራስን መውደድ እንዳይሆንብኝ ግን ይህ ርኅራኄሽ ይህ ምልጃሽ ለአዳም ዘር ሁሉ ይሁን፡፡
ድንግል ሆይ ስምሽን ባነሳሁና ባሰብኩ ቁጥር ውስጤ ስለሚረበሽ ከጎኔ በመሆን አይዞህ በይኝ አፅናኚኝ ተስፋህ እኔ ነኝ በይኝ ተስፋዋ ለመነመነ ግራ ቀኟ ለጨለመባት ሕይወት ረሐብና ጥም ላጠቃት ነፍሴ መፅናኛሽ አለኝታሽ እኔ ነኝ በያት፡፡
የአምላክ እናቱ ሆይ ልጅሽ ከቅዱሳኑ ጋር ከነቢያትና ከወዳጆቹ ከመላዕክት ጋር ዘወትር በሕይወቴ እንድስተናገድ በእኔነቴ ላይ እንድነግስ ደግሞም በሚገለጥበት ሰዓት ከቀኙ ሊያቆመኝ የሚችለውን መልካም ሥራ ሠርቼ ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ ርስቱን ከሚያወርሳቸው ጋር እንዲደምረኝ ተማልደሽ አማልጅኝ፡፡
የኃጥአን ተስፋ የሆንሽው ሆይ በሐጢያት ስወድቅ ኃይልና ብርታት ሁኚኝ ከሐጢያትም ሥፍራ ተነስቼ ሐጢያቴን በማመን ሐጢያቴ የሚሰረይበትን ንሰሐ እንድገባ አበርቺኝ ከልጅሽም ጋር ሕብረት አንድነትን ልፈጥር የምችልበት ከሐጢያት ሁሉ የምነፃበትን መለኮት የተዋሃደው የልጅሽን ሥጋና ደም የመመገቡን ፀጋ አድይኝ፡፡
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዳለሽ ‹‹…. ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ መዓትን ያይደለ ምህረትን አሳስቢ ለጻድቃን ያይደለ ለተዳደፉት አሳስቢ›› ለኔ ለሐጢያተኛው ዘወትር እንድታሳስቢ በግብፅ በረሃ መሰደድሽን መራብ መጠማትሽን ልጅሽን ለማዳን ብለሽ ከላይ በአናትሽ የገባው የፀሐይ (ብርሃን) ግለት እግርሽን የቀቀለውን ረሞጫ አሳስቢ ምንም እንኳን ኃጢያቴ ቢበዛ የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስምና ሁሉ ቢቀር ለንሰሐ የምበቃበትን ልቦና አሰጪኝ ንሰሐ ዘማዊን ድንግል እስከ ማድረግ ደረጃ ያደርሳልና፡፡
እመብርሃን በዶኪማስ ቤት በሠርጉ በተጠራሽ ከልጅሽ ከወዳጆቹ ከቅዱሣን ጋር በሠርጉ በታደማችሁ ጊዜ ድግሱ አልቆበት በተዋረደ ጊዜ አንቺም ጭንቀቱን ተመልክተሸ ወደ ልጅሽ ነግረሽ ቤቱን በረከት በበረከት እንዳደረግሽ ውሀውን ወደ ወይን እንዳስለወጥሽ እኔም በዚህ ምድር ስኖር ሕይወቴ ባዶነት ይሰማዋልና ምግባር ትሩፋት የለኝምና እጅግም የማሳፍር ሆኛለሁና በጣምም ተዋርጃለሁና ከውርደት አድኝኝ ጎደሎ ያይደለ ሙሉ አድርጊኝ በምግባር በትሩፋት አትረፍርፊኝ ከሐፍረት ሰውሪኝ ውሃ … ውሃ ያለው ሕይወቴንም አጣፍጪው፡፡
ድንግል ሆይ ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆቹ መካከል ሥምኦንና ሌዊ በሴኬም ልጆች ላይ እጃቸውን ባነሱ ሰዓት እንደረገማቸውና እንደለያቸው ከዘመናት በኋላ እስራኤላውያን ጣኦትን ሲያመልኩ እግዚአብሔርም ሲቆጣ ሙሴም ከፊታቸው ቆሞ ‹‹የእግዚአብሔር ወገን የሆናችሁ ተለዩ›› ባለ ጊዜ የሌዊ ነገድ ራሱን ለእግዚአብሔር ቢለይ እግዚአብሔር መረጠው አከበረው በመጨረሻም ርስትን ሲከፋፈሉ ሌዊን ካህን አድርጎ እንደሾመ እንደባረከ እንዲያገለግላቸው እንደመረጠው ሌሎች ርስት ሲከፋፈሉ እግዚአብሔር ለአንተ ርስትህ እኔ ነኝ እንዳለው ባንቺ አማላጅነት ሐጢያቴና በደሌ ከሌዊ እጅግ የበዛውን ልጅሽን ታሪኬን በደሌን እንዲቀይረው እኔም እንድቀየር አድርጊኝ እንደ ሌዊ አገልጋይ ካህን አድርጊኝ ባልልም ሐጢያቴን እንዲያቀልልኝ አሳስቢ ለሌዊ ርስቱ እንደሆነ ርስትህ እኔ ነኝ ይለኝ ዘንድ አሳስቢ፡፡ እኔ በኃጢያት ማኛ የተጣልኩትን ልጅሽ በፍፁም ፍቅሩ ሁለት እጄን ይዞ እንዲያወጣኝ አሳስቢልኝ፡፡
ድንግል ሆይ በቀረውስ ምስኪን ሰው ድሃ ሰው ከባለ ፀጋ ፊት ሲቆም ብዙ ነገር ይለምናልና ባለፀጎችም መመፅወት ባህሪያቸው ነውና ከባለፀጎች ሁሉ ባለፀጋ ከሆነው ልጅሽ ዘንድ የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ አሰጭኝ፡፡
ቅድስት የምትሆን የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን ባርኪያት ሕዝቦችዋን ከጦርነት ከእልቂት ከረሃብ ከቸነፈር ከበሽታ ከክህደት ሁሉ እንዲሠውራት ለልጅሽ አሳስቢ፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያንና አድባራትንና ገዳማትን ጠብቂልን ጉባኤያትን ማኅበራትን የወንድሞችን ሕብረት አጠናክሪ ከጠላት የፈተና ጦር ሠውሪያቸው፡፡
እኛ ልጆችም የእምነት የምግባር የትሩፋት ሠው እንድንሆን አሳስቢ፤ በሩቅም በቅርብም ያሉትን እንድናስባቸው ያሳሰቡንን ሁሉ አስቢ፡፡
ድንግል ሆይ በተረፈው በተሰጠሸ ቃልኪዳን መሠረት በሠላም ውዬ እንድገባ በቀንና በሌሊት ጥበቃሽ አይለየኝ ልጅሽ ለአንደበቴ ለልቡናዬ ለእግሬ ጠባቂ መላዕክትን እንዲያቆም መልካም ፈቃዱ ይሁን፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን አሜን፡፡
ከተስፈኞች አምባ

* ሰሞኑን ዲ/ን ዳንኤልና ፕሮፌሰር መስፍን መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ በሚላዉ የፕሮፌሰር መጽሓፍ ላይ ሲነጋገሩ ነበር፤ ብዙዎችም አስተያየት ሰተዋል፡፡ እኔም እንዲህ ብያለሁ፡እነሆ፡-
ለኔ ሁለቱም የአገር ቅርሶቼ ናቸዉ፤ ይህን ያልኩበት የራሴ የሆነ ምናልባት ሌሎችም ሊጋሩት አልያም ላይጋሩት የሚችሉት ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይኸዉም ሁለቱም ሰዎች በአገራችን ጉዳይ ላይ በማህበራዊ ነክ ጉዳዮች ላይ ብዙ ፅፈዋል ፣ አስተያየት ሰተዋል ተችተዋል. ጥናታዊ ፅሁፎችን አቅርበዋል፣ ወዘተ… ሆኖም ግን

* የየራሳቸዉ ደካማ ነገር የላቸዉም ማለቴ አይደለም፡ ይኖራቸዋል! ነገር ግን እነደ ጸሐፊነታቸዉ (አይከን) እንደ መሆናቸዉ መጠን በጣም ጥንቃቄ ሊያደረጉ ይገባ ነበር አሁን ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ሊከባበሩና ሊደማመጡ ነገሮችን በጥሞና ሊከታተሉ ይገባል፣ ከመናገርና ከመጻፍ ለቆጠቡ ይገባል (ፕሮፌሰርን ማለቴ ነዉ) ዲ/ን ዳንኤል የመሰለዉን መናገር ይችላል ፕሮፌሰር ግን የጻፈዉን ነገር ተደፈርኩ በሚል ስሜት ሳይሆን በእርጋታና በጥሞና ቢያዩት፤ መልሱን የተጠቀሙበትን ቃላትም ቢፈትሹት ይሻል ነበር ይሁን ያ አልፋል፣ ያላለፈ ነገር ግን ይቅርታ ብሎ በጠረጴዛ ዙርያ ታሪክን መፈተሽ ይቻላል፡፡

* ህብረተሰቡን መወረፍም፣ ሌላ ስም መስጠትም አግባብ አይደለም እንዲያዉም እንበል ከተባለ የታሪክ መክሸፍ ሳይሆን የግለሰብን ማንነት መክሸፍና መዉረድ (መዝቀጥ) አይተንበጣል፤ ተሳዳቢነትና ንቀት የምንም ምልክት አይደለምና፡፡ ለዚህ ትዉልድ ምንም እንኳን ያደረግንለት ጥቂት ነገር (የምናቀዉን ነገር የሰጠነዉ ) ቢኖርም ከዚህ ህዝብ የተሰወረና እኛ ጋር ብቻ ያለ ነገር የለም! ያገኘነዉ ከህዝብ ነዉና ህብረተሰቡም ከኛየተሻለ ነገር አለ፡ አልፃፈዉም እንጂ፤ እዉቀቱን ገበያ ላይ አላዋለዉም እንጂ፡፡ ስለዚህ አንዱን ጥሎ ሎላዉ አንጠልጥሎ ጉዞ አይቻልምና ያለተገነዘቡአቸዉን ነገሮች ወደ ኋላቸዉ ተመልሰዉ ይመልከቱ!!!!!! መልዕክቶ ነዉ፡፡

ዓርብ 22 ማርች 2013

“መልዐኩ እና ደራሲዉ”ክፍል ሁለት!



ክፍል ሁለት!
መልዐኩ እና ደራሲዉ
“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ ምድርም ባዶ ነበረች ፡ … … ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ አንድ ቀን፡፡” ዘፍጥረት11፡1-5
እንደ ፈረንጆቹ  ዘመን አቆጣጠር ማርች 22-2012 ምክሰኞ ቀን  “የደረሰ ረታ እይታዎች” በምትሰኝ ጥቂት መጦመርያ መጦመርን  “ሀ” ብዬ ስጀምር  “መልዐኩ እና ደራሲዉ” ፤ “… … … የእግዚአብሔር መልዐክ ጋር የመጀመሪያዉን የደራሲዉን እና የመልዐኩን ግንኙነት እዚህ ላይ በማቆም በቀጣዩ ምዕራፍ እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን! ” በማለት ተሰነባብተን እንደነበር የአንድ አመት ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡እነሆ መቸስ እንደማይሞላ፤ መልዐክና ደራሲም ተገናኝተዉ በቀላሉ አይለያዩምና ፤ይኸዉ ዘግየቼም ቢሆን ድፍን አንድ አመት በመዘግየት ክፍል ሁለትን ይዤላችሁ መጣሁላችሁ፡፡
እንኳን ለጦማርችን አንደኛ ዓመት አደረሰን! መልካም ንባብ፡፡
“መልዐኩ እና ደራሲዉ”
መልዐኩ፡-“ አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጅህ ሥራዎች ናቸዉ” እንዲል መፅሐፍ በመዝሙረ ዳዊት 101፡25 ከመፍጠርህ አንስቶ ሥትኖርበት የነበረዉን ምድር አሁን ዳግሞ ያለህበትን ሰማይ በአንድነት ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸዉ እግዚአብሔር ነዉ፡፡
ደራሲዉ፡-እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ሲፈጥር ይህን ሰማያዊ ዓለምና ያኛዉን ዓለመ ምድር (ምድራዊ ዓለም) ሥንት ፍጥረት በመፍጠር ሊሞላዉ ቻለ፡፡
መልዐኩ፡-ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር የፈጠረዉ ፍጥረት ሁሉ ቢቆጠር ፍጥረት በሙሉ ቆጥሮ አያጠናቅቀዉም፤ ነገርግን እንደ ሥነ-ፍጥረት ሥርዓት ብዙዉን አንድ ፡ብዙዉን አንድ እያልን ሥንቆጥረዉ በ22ቱ አርዕስተ አበዉ ምሳሌ 22 ናቸዉ፡፡
ደራሲዉ፡-አርዕስተ በዉ የሚባሉት እነማን ናቸዉ?ምንስ ነዉ?
መልዐኩ፡-አዳም፣ሴት፣ሄኖስ፣ቃይናን ፣መላልኤል፣ ያሬድ ፣ሄኖክ ፣ማቱሳላ፣ ላሜህ ፣ኖህ ፣ሴም፣ አርፋክስድ፣ ቃይናን፣ ሳላ፣ ኤቦር፣ ፋሌቅ፣ ራግዉ፣ ሴሮህ፣ ናኮር፣ ታራና አብራም… ናቸዉ፡፡
ደራሲዉ፡-22ቱንም ፍጥረታት በአንድ ቀን ፈጥሮ አጠናቀቀ?
መልዐኩ፡-መፅሀፍ በአንድቅ ተደርሶ ታትሞ ለአንባቢያን እንደማይደርስ ሁሉ ይህም ዓለም በአንድ ቀን ተፈጥሮ አልተጠናቀቀም ፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በጊዜ ሠርክ ጀምሮ በዕለተ ዓርብ ለፍጥረት ስድስተኛ ለቀመር አራተኛ ማለት ነው፡፡
በዕለተ እሁድ ሥምንት ሲፈጥር እነዚህም አራቱ ባህርያተ ሥጋ እና ጨለማ፣ ሰባቱ ሰማያት፣ መቶው ነገድ መላእክት እና ብርሃን ናቸው፡፡ አራቱ ባህርያት ሥጋ የሚባሉት ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት ናቸው፡፡ በባህርዬ አራት ነገሮች አሉብኝ ሲልም ፈጥሮአቸዋል፡- እነዚህም ኃያል ነኝ ሲል እሳትን ፈጠረ፤ እሳትን ውኃ ካልከለከለው ቆላ ደጋ ሳይል እንዲያጠፋ እግዚአብሔርም ቸርነቱ እስካልከለከለዉ ድረስ ሰማይንና ምድርን በአንድነት ሊያጠፋ ይቻለዋልና እንዲህ አለ፡፡

ማክሰኞ 19 ማርች 2013

12 ምክሮች ለወንዶች


12 ምክሮች ለወንዶች
       ቤተሰብ መሥርተው ሲኖሩ ትዳር ሁልጊዜ በሰላም የታጀበና የሠመረ ነው ብለው ካሰቡ ለትዳርዎ መሣካት ምን እርምጃ እንደወሰዱ በአንዳፍታ ያስቡ አልያም ሁልጊዜ ንጭንጭ ንትርክና ሰላም አልባ ትዳር ይዘው እርስዎና ቤተሰብዎ በጭንቀት የሚጓዙ ከሆነ ለመፍትሔው የሚቀጥለውን ጽሁፍ በርጋታ ያንብቡ ባሎች ደስተኛና የተቃና ትዳር ጤናማ የሆነ የባልና የሚስት ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚከተሉትን 12 ነጥቦች መከተል አለባቸው ይህንን ሲያደርጉ ታዲያ በግላዊ ሰመመን ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡ በዚህም መሠረት እንዲህ ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡
1.  የትዳር ጓደኛዎ እንደማንኛውም ሰው ተፈቃሪና ተከባሪ ለመሆን እንደሚሹ አምነው ይቀበሉ፡፡
2.  ባለቤትዎ የግልፈተኛነት ስሜትና የኢኮኖሚ ድቀት እንኳን ቢደርስባቸው ፍቅሬ ሳይቀንስ ጠንክሬ በመስራት ጥሩ ሚስት አደርጋታለሁ ይበሉ፡፡
3.  ባለቤትዎ የትዳር ጓደኛዎ እንጂ በእናት ምትክ የመጡ ያለመሆናቸው ይረዱ፡፡
4.  ሕይወት ጣፋጭነት የሚኖረው በትዳር መሆኑን አይዘንጉ፡፡
5.  ሚስትዎ ጓደኛዎ መሆናቸውን አምነው ለጥሩ ጓደኛ የሚሰጠውን ክብር ይስጧቸው፡፡
6.  በማንኛውም ነገር ባለቤትዎ የእርስዎን ሃሣብና መንገድ ይከተላሉ ብለው መጠበቅ አይገባዎትም፡፡
7.  ወንዶችና ሴቶች እንደ ጾታቸው እንደሚለያዩ ሥጋዊና /አካላዊ/ ውስጣዊ ስሜታቸውም እንደሚለያይ መገንዘብ እንዳለበት አይዘንጉ፡፡
8.  የሴትን ሥነ-ልቦና ማድነቅና ከዚያም ስለባለቤትዎ ፀባይ አስተያየት መስጠት የማይጎዳ መሆኑን አይዘንጉ፡፡
9.  ሚስቴን ባንቋሽሻት ወይም ብሰድባት ፍቅርና አክብሮት መጠበቅ አልችልም ብለው ያስቡ፡፡
10.             ሚስቴ እኔን በጎ እንደማሰብና የማደርገው ድርጊት ሁሉ ከሰው ያልተለየ ቀና መሆኑን እንደምታስብ ማወቅ አለብኝ በማለት ራስዎን በራስዎ ያሳምኑ፡፡
11.             ትህትና ስጦታ ማበርከትና ደግነት ማሣየት ማስፈለጉን አይርሱ፡፡
12.             ሚስትዎን ማስተማር ድርሻዎ ነው፡፡ የእረፍት ስሜት ሳይሰማት ወሲብ የፍቅር መግለጫና ለጤንነትም አስፈላጊ መሆኑን ማሳወቅ እንዳለብዎት አይርሱ፡፡

ይድረስ ለበረሃው ጓዴ…



  

ይድረስ ለበረሃው ጓዴ


ምናልባት ይህች መልዕክቴን የያዘች ደብዳቤ በጅህ እንደገባች ከምን ትዝ ብሎህ ፃፍክልኝ ሳትለኝ አልቀረህም ከጊዜው ርቀት የተነሳ ምንም እንኳን ከተለያየን 2000 ዓመታት ገደማም ቢሆንም አብረን ያሳለፍነው የበረሃው ጓደኝነታችን አይረሳኝም ምናልባት አንተ ጥንታዊ ግብርህን ብትቀይርም ታሪክህም ቢቀየር ይህንን ደብዳቤ ስታነበው ትዝ እንደሚልህ እገምታለሁ ያለጥርጥርም በመተማመን ያኔ ያሳለፍናቸውደስታንበሚፈጥሩት የግፍ ሥራዎቻችን በጣም እንደምትፀፀት፤ ጓዴ እንኳን አንተ እኔ ራሴ ዛሬ የማይረባ ጸጸት ሆኖ ነው እንጂ እየጸጸተኝ ነው ያለው፤ ታዲያ ምን ዋጋ አለው ብለህ ነው የመጸጸቻው ጊዜው ያለፈኝ የመጨረሻው ሰዓት ያኔ ፍርዳችንን በኢየሩሳሌም አደባባይ ያለበደሉ ከእኛ ጋር ሦስተኛ በመሆን ፍርድን ከተቀበሉ ጋር ዋጋችንን ስንቀበል ከኅልፈተ ሕይወታችን በፊት ስትፀፀት ነበር እኔን ያመለጠኝ፡፡
       የበረሃው ጓዴ ለመሆኑ ምቾቱ ተድላ ደስታው እንዴት ይዞሃል? የእኔን ስቃይ ሃዘን መከራ እንዳልነግርህ የሚደርስብኝ ሁሉ ግፍ እንዳላጫውትህ እንዳለ እንዳላዋይህ አንተም ታውቀዋለህ አንድም ሃሜት ባህሪህ እንዳልሆነ አውቄዋለሁና ይቅርብኝ በሌላ በኩል ‹‹ከወደቁ በኃላ መንፈራገጥ …›› እንዳይሆነብኝ በዝምታ ባልፈው ይሻለኛል፡፡
       ጓዴ፡- ወደዚህ ወደ ድቅድቁ ጨለማ ማረፊያ ከመጣሌ በፊት ያለህበት የተድላ የደስታ ሥፍራ አስጎብኚዎቼ እንዲቆጨኝ ወስደው አሳይተውኝ ነበር ምን ዋጋ አለው ታዲያበነበር ነብሮ ቀረ እንጂ፡፡
       ዛሬም በዚያ ሆነህ ከጓደኞችህ ጋር ስትደሰት በሩቅ ሳይህ እናቱ እንደሞተችበት ልጅ በዚህ በጨለማ ቁጭ ብዬ በመኮራመት እቀናብሃለሁ መቸስ አንተ በእኔ እንኳን ልትቀና ቀርቶ ጊዜ ኖሮህም አታስበኝም ለመሆኑ ያኔ አንተ እንደዚያ ስትራራ ስትጸጸት ልቤን ምን ይሆን የዳፈነው? … ጓዴ እንኳን ላንተ ለእኔም ዛሬ ድረስ ግራ ሆኗል በልተወው፤
       የኔን ኑሮ ልፃፍልህ ብል በምን ቃል እንደምገልፅልህ ግራ ይገባናል መፃፌን ያዩ ነፍሳትም መከራው የሚቀልባቸው እየመሰላቸው የእናንም ፃፍልን ብለው ስለሚያስቸግሩኝ ይቅርብኝ ማንም የማይጋራኝን የበረሃውን ትዝታ ለምጣው አሁንም 2000 ዓመት በላይ ወደ ኋላ ልመልስህ ወደ ግብፁ በረሃ ያኔ እንኳን እነዚያ የሚያሳዝኑ እናት እና ልጅ ደግሞ ሽማግሌው አንድም ሴት አለች ስማቸውን ባላነሳልህም ሕፃኑ 30 ዓመት በኃላ በኢየሩሳሌም ከኛ ጋር መከራን የተቀበለው ሲሰደዱ በበረሃ አግኝተናቸው የእግሩን ጫማ የወርቁን ማለቴ ነው ወስጄባቸው ሕፃኑ እናት አምራ ያለቀሰችው ትዝ ይልሃል የደነገጠችውስ ድንጋጤ ታስታውሳለህ እኔ አልረሳውም ዛሬ ዛሬ እየመጣ ሰላም ባጣሁበት ስፍራ እርሱም አብሮ ተዳምሮ ሰላም ይነሳኛል፡፡ ደግነትህ አይታየኝም ነበር ደግኮ ነበርክ ከምን እግር ጥሎህ ከኔ ጋር እንደዋልክ እንጃ እንጂ የዋህ እኮነህ ከደግነት ከየዋህነትህ የተነሳ ነበር የወስድኩትን የወርቅ ጫማ ከዚያ በፊት በቁመናው የለወጥከኝ የቱን ትቼ የቱን ላንሳ ዛሬ የምቀባጥርብህ ይቀልልኝ እንደሆነ ብዬ እኮ ነው . . .
      
የበረሃ ጓዴ፡- ሥራ ፈት ሰው ምን ሥራ አለው ብለህ ነው፡፡ ይኸውልህ ከዚህ ከጨለማው ቁጭ ብዬ ደብዳቤ መፃፍ ሆኗል ሥራዬ ባለፈው ላንተ እንደፃፍኩልህ ለጳውሎስም ፅፌለት ነበር ያንተ መልሱ ባይደርሰኝም የጳውሎስ ደርሶኛል ምን አለኝ መሰለህ ጳውሎስ ለካስ እኔ ብቻ ኤደለሁም የምፅፍለት ዴማስም ጽፎለት ኖሮ ‹‹መጣሁ ቆየኝ …›› የሚል አንድ ደብዳቤ ጽፎልኛል አለኝ በመገራም እባካችሁን አትገረሙብኝ የጨነቀው ሠው ብዙ ይቀባጥራል ጨንቆን ነው የምናስጨንቃችሁ፡፡
       ይህንን ደብዳቤ ሥፅፍና ሥልክ እንዴት በጭንቀት መሰለህ እንኳን መላክ መፃፍ አይቻልም በድብቅ ነው ከፃፍኩት ቆይቻለሁ የምልከው ሰው አጥቼ ድንገት አንዲት ቆንጆ ሴት ሥሟ ክርስቶስ ሰምራ የምትባል ወደኛ መጥታ ነበር ድንገት አግኝቻት በርሷ በኩል ልኬነው ያኔ በረሃ ያገኘናት የሕፃኑ እናትም አንዳንድ ቀን መጥታ በሩቅ አያታለሁ ስለማፍርና እንደገናም ከነፍሳትም ብዛት ወደርሷ መሄድ መንገዱ ስለሚጣበብ ወደርሷ መቅረብ አልቻልኩም ከወንዶችም አንድ እግሩ የተቆረጠ ይመጣል ብቻ ብዙ የሚመጡና ነፍሳትን ይዘው የሚመጡ አሉ ለማንኛውም ይህቺ ደብዳቤዬ ከአንተ ዘንድ እንደ ደረሰች ከዕለታት በአንደኛው ቀን እኔም እመጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጓዴ የሚሆን ከሆነ ምን አለ ሲመጡ እንዲወስዱን ብትነግርልኝ?...
       በተረፈ ነገር አላበዛብህም በዚሁ ይብቃንና አንተም ሁኔታዎችን ብትገልፅልኝ ስለምወድ ፃፍልኝ እንግዲህ ከዚህ ከተፈረደብን ፍርድ ከዚህ ጉስቁልና ይግባኝ ብዬ መውጣት የማይቻል ቢሆንም አሁን ባልኩህ መንገድ ብትሞክርልኝ ተስፋ ይኖረኛልና አደራ አደራ
       እባክህ እባክህ ወንድሜ እኔ ከዚህ ሆኜ ብጮህ የሚሰማኝ የለም አንተ ሳትሻል አልቀረህም ሥራም ቢበዛብህ ከዚህ ሆኜ በምድር ያሉት ይታዩኛል የኔን አይነት ኑሮ የሚኖሩ እባክህ ሰውም ቢሆን ልብህ አንድ በላቸው በዚሁ ከቀጠሉ ማለቃቸው ነው፤ የኛስ የዚያኔው ሽፍትነት በማናውቀው ሰው ላይ ነው ያሁኑ ግን እርስ በርስ ሆኗል የሰው ነፍስ እጅግ የረከሰችበት ዘመን ሆኗል መተዛዘን ጠፍቷል ከበደላቸውም ምክንያት እግዚአብሔርም ርቋቸዋል፡፡ ፊቱንም ከነርሱ አዙሯል እንደኔ ከመሆናቸው በፊት ስለህያው ነፍስ ብለህ ታደርጋቸው፡፡
ደህና ሁን የበረሃው ጓድህ፡፡
       ካንተው ጓደኛ ዳክርስ በገነት ላለው ጥጦስ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...