ባለፈዉ በሁለት ተከታታይ ክፍል ስለ ቅዱስ መስቀል ተመልክተን በክፍል ሦስት እንደምንገናኝ ተቀጣጠረን ተለያይተን ነበር
እግዚአብሔር ፈቅዶ አባቶቻችን እና ወንድሞቻችን በቃልና በመጽሐፍ ያቆዩልንን ትምህርት ሳልጨምር ሳልቀንስ ለንባብ እንዲመች በክፍል
በክፍል አቅርቤላችኋለሁ፤ ክፍል ሦስት እነሆ! በክፍል አራት ያገናኘን፡፡
3ኛ. ቅድስት
እሌኒና መስቀለ ክርስቶስ
ጌታችን መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በሐዋርያት
ስብከት የወንጌሉ ፋና ለዓለም ሲበራ በዕፀ መስቀሉ ልዩ ልዩ ተአምራት ይደረጉ ነበር፡፡ አስቀድመዉ ጌታን የሰቀሉ አይሁድ አሁን
ደግሞ በሰቀሉበት መስቀል ተአምራት ሲደረግ በማየታቸዉ በቅንአት መስቀሉን ከኢየሩሳሌም አጠገብ ቀብረዉ በአዋጅ ቆሻሻ በየእለቱ እንዲደፋበት
አደረጉ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሥራዉን የሚሰራበት የራሱ ጊዜ አለዉና በ327ዓ.ም.
የታላቁ ንጉስ የደጉ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒን አስነሣ፡፡ እርሷም አስቀድማ ከአረማዊዉ ንጉስ ቁንስጣ የወለደችዉ ልጅዋ
ክርስቲያን ከሆነላት ከቁስጥንጥንያ ወደ ኢየሩሳሌም ተሻግራ የጌታችንን ዕፀ መስቀል ልታወጣ ብፅዐት ገብታ ነበር፡፡ በልዑል እግዚአብሔርም
ፈቃድ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ስለሆነላት በመስከረም 17 ቀን ቁፋሮዉን አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን አወጣችዉ፡፡
መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል ቆሻሻ እየተደፋ ስለተከመረበት
ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በኢየሩሳሌም በነበረዉ አበዉ መሪነት ደመራ አስደምራ፣ ዕጣን አስጨምራ፣ ጸሎት
ስታስደርግ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ መስቀሉ በተቀበረበት ቦታ ላይ ሰገደ፡፡ በጢሱ ምልክትነትም ቦታዉ ስለታወቀ ለሰባት ወራት
ያህል ተራራዉ ተቆፍሮ ሊወጣ በቅቷል፡፡ ዛሬ በክርስቲያኖች ዘንድ ደመራ የሚደመረዉም ይህንኑ ለማስታወስ ነዉ፡፡
መስከረም 17 ቀን ወይም በዋዜማ፣ በዓለ መስቀሉን ስናከብር ከመስቀሉ ቀጥለን የምናስባት ቅድስት እሌኒ ናት፡፡ ቅድስት
ዕሌኒ የመስቀሉ ጥበብ ተገልጾላት ክብሩና ሞገሱ በግልጽ ታይቶአት፣ መድኋኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀል የት
ባገኘሁት እያለች ለብዙ ጊዜ ታስብና ትመኝ ነበር፡፡ በተለይም ልጄ መምለኬ እግዚአብሔር ንጉስ ቈስጠንጢኖስ፣ መክስምያኖስ ከሚባል
ጠላቱ ጋር ሲዋጋ፣ …