UNESCO ባወጣዉ
ዘገባ አማካይነት በሳምንት አንድ ጋዜጠኛ እንደሚሞት ይፋ አድርጓል፡፡ የዚህ አንድ ጋዜጠኛ ህይወት የሚቀጠፈዉ ወይም ለመስዋዕትነት
የሚቀርበዉ ለአድባር ወይም ለአምልኮ ጣዖት አይደለም፤
ለሙያዉ ክብር ሲል እንጂ፡፡ ይህ ጋዜጠኛ ሥራን ለመስራት ላይ ታች ሲል ህይወቱ
በአንባገነኖች መዳፍ ዉስጥ ትወድቃለች፡፡
በአለም አቀፉ ደረጃ የፕሬስ ነፃነት በሚከበርበት ዕለት በወጣዉ መረጃ መሰረት
በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር ከ2006 እስከ 2012 ድረስ 502 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን አሟሟታቸዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡መረጃዉም
ከዚህ እንደሚከተለዉ ተቀምጧል፡-
ዘመን
|
የሟች ቁጥር
|
2006
|
70
|
2007
|
59
|
2008
|
48
|
2009
|
77
|
2010
|
65
|
2011
|
62
|
2012
|
121
|
ይህ ድርጊት
እየተፈፀመ ያለዉ በታዳጊ አገራት እና ዲሞክራሲ ባልተስፋፋባቸዉ አገሮች ብቻ አይደለም፡ ባደጉት አገሮችና ዲሞክራሲ ጥርሱን በነቀለባቸዉም
አገራት ጭምር እንጂ፤ ይህ ደግሞ ለእንደ እኛ አገር እጅግ ትልቅ
ስጋት ነዉ፡፡
ይህ መረጃ የሚያሳየን ይህቺ ዓለም ለጋዜጠኞችና ለኢየሱስ ክርስቶስ (አንዳች
ሀሰት ያልተገኘበት) እንዳልተመቸች ነዉ የምንመለከተዉ ከዚህ በመነሳት አገራችን ኢትዮጵያም “ጋዜጠኞቿን በልታ ዝም የምትል አገር”
እስከመባል ደርሳለች፡፡ ቀደምቶቻችን እነ ጳዉሎስ ኞኞ ፣ ብርቅዬዉ በዓሉ ግርማ እና ሌሎቹም በጋዜጠኝነት ህይወት ዘመናቸዉን ያጠናቀቁት፣
በስቃይ በመከራ እና በስደት ነዉ፡፡ ዛሬም ሙያዊ ፈለጋቸዉን በመከተል ገሚሶቹ እየተሰደዱ ብዙሃኑ ደግሞ እየታሰሩ ጥቂቶችን በመተካት
“እንኖራለን” ሳይሆን “እንሞታለን ገና” እያሉ ሰይፍ እንዳየ ሰማእት በደስታ ፅዋቸዉን እየጨለጡት ነዉ፡፡ UNESCO ያሰራጨዉን
ዘገባ በማየት እዉነትን እየዘገቡ ለሞት፣ለመከራ፣ለስደት፣ …ስንቃቸዉን እየቋጠሩ ተዘጋጅተዋል፡፡
የሚገርመዉ ነገር
ነፃ ፕሬስ እየታወጀ ነፃ ዘገባ መከልከሉ፣ ነፃ ፕሬስ ይስፋፋ እየተባለ ጋዜጠኞች መገደላቸዉ እና መታሰራቸዉ፣ ዲሞክራሲን እያስፋፋን
በህግ እዉቅናን ሰጥቶ መሰረት እየጣሉ አዋጆች ድሞክራሲ እንዲያድግ እየደሰኮሩ በአንፃሩ በፍጥነት እንዳያድግ እና እንዳይራመድ የሚሰነከሉ
ተደርገዉ መሰራታቸዉ፣ጋዜጠኞቻችንን ከአሸባሪ ፈርጆ የእስር ቤት ሲሳይ ማድረግ ምድርቱ ጋዜጠኛ እንዳይወጣባት (እንዳታፈራ) ማድረጋቸዉ
ዘግናኝ ነገር ነዉ፡፡
ከዚህም ባሻገር
ነገሥታትንና መዃንንትን መሪዎችንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉን ዱካቸዉን በመከተል ታሪኮቻቸዉን በልብ ወለድ መልክ የሚፅፉና ለዓለም የሚናኙ፣
የሌላቸዉን ተጋድሎ እና ደግነት ከቅዱሳን ድርሳናት ባልተናነሰ ሁኔታ የሚዘግቡ፣ፈጣሪ ለሰዉ ልጅ ካደረገዉ ይልቅ መሪዎች አደረጉ
የሚሉት መብዛታቸዉ፣መሪዎቻችንንና ገዢዎቻችን ህዝቦቻቸዉ አናት ላይ ካካቸዉን እንዲጠፈጥፉ አድርገዋቸዋል፡፡
በዚያዉ ልክ ደግሞ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ዉጭ ዘወትር ብዕራቸዉ ፡ ሽብር፣ሰቆቃ፣ፍጅት፣እልቂት፣…
ብቻ የሚነዙ ጥቂቶች አይደሉም፤ ምላስ የሞቀ ስፍራ ላይ ተቀምጣ
በዓለም ላይ ክብሪት እንደምትጭር እና እንደምታጫርስ ለሚልዮኖች ህልፈት፣ለሰላም መጥፋትና አለመረጋጋት፣ለጦርነቶችና ለዕልቂቶች መነሾ
የሆኑ አልታጡም፡፡
የሆነዉ ሆኖ ይህቺ ዓለም ከእዉነተኞቹ ጋዜጠኞች ዉጭ ነፍስ የተለየዉ በድን
እንደማለት ነዉና ነፃ ፕሬስ ነፃነታቸዉ የተጠበቀ ጋዜጠኞች ያስፈልጓታል፤ ያስፈልጉናል፡፡መሪዎችም በተስተካከለ መንገድ ለመጓዝ ፣መንግስታቸዉ
እንዲፀና፣ ግዛታቸዉ እንዲሰፋ፣ … ጋዜጠኞችና ነፃ ፕሬስ የግድ ያስፈልጓቸዋል፡፡
እዉነተኛ ጋዜጠኝነት ማለት መሪዎችን እየተከተሉ ዛሬ ወደ ዉጭ ሲበሩ እነ እገሌ
ሸኟቸዉ፤ እዛ ሲደርሱ እነ እገሌ ተቀበሉዋቸዉ … ወዘተ ማለት አይደለም፡፡በካሜራም የስብስባዉን አዳራሽ የተሰብሳቢዎችን ማንነትና
ብዛት (እስኪ ይህ ዜና ነዉ ለእስታትስቲክስ የሚረዳ መረጃ ነዉ?)ከየት አገር እንደመጡ መናገር አይደለም ዘገባና ጋዜጠኝነት፡፡
ይህ አይደለም “ነፃ ፕሬስ” የሚያስፈልገዉ ፎቶ ለማንሳትና ቪድዮ ለመቅረፅ ፎቶ “ማንሳት የተከለከለ ነዉ” የሚል ነገር እስከሌለ
ድረስ፤ ዘገባ የስብሰባዉ አጀንዳ፣የተነሱት ጉዳዮች፣ያለፉት ሃሳቦች፣ የተጣሉትና በቀጠሮ የተለያዩባቸዉ መሰረታዊ ሃሳቦች፣የተነሱት
አጀንዳዎች ህዝባዊና አገራዊ ፋይዳዎች መዳሰስ ይኖርባቸዋል፤ መሪዎቻችን ስብሰባዉ ላይ ተገኛተዉ መጡ ወይንስ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም
ነገር አድርገዉ መጡ? ወይስ እነርሱም እንደ ጋዜጠኛ ያዩትንና የሰሙትን ሊነግሩን ሄደዉ መጡ? አለበለዚያ ለመዝናናት ከመሄድ አይተናነስምና
ጉዞዉም አገራዊ ፋይዳ ሊኖረዉ ይገባል፡፡
ለማንኛዉም በአንድም ይሁን በሌላ በእስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኞች እግዚአብሔር
ያፅናቸዉ፣የመፈቻ ቀናቸዉን ያቅርብልን፣ የሞቱትንም ነፍሳቸዉን ይማራቸዉ፣ቤተሰቦቻቸዉንም እግዚአብሔር ያበርታቸዉ፣የተሰደዱትንም ለወገኖቻቸዉ
ጠቃሚ ስራን እንዲሰሩ ወደ አገራቸዉ ይመልሳቸዉ፡፡ ለመላዉ ዓለምም በዲሞክራሲያዊ መንፈስና ስርአት የበለፀገ ነፃ ፕሬስ ያድልልን፡፡
ለፕሬስ
ትንሳኤ በሰላም ያድርሰን!!!!!!!!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ