ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።
| |||
እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው።
| |||
ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ።
| |||
ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤
| |||
ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም።
| |||
ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥
| |||
ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ።
| |||
በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤
| |||
ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና።
| |||
ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ።
| |||
ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤
| |||
ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።
| |||
እርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው።
| |||
ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።
| |||
ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው።
| |||
ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።
| |||
መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።
| |||
ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።
| |||
ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።
| |||
ኢየሱስም ዳግመኛ። ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው።
| |||
ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።
| |||
ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።
| |||
ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም።
| |||
ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ። ጌታን አይተነዋል አሉት። እርሱ ግን፦ የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው።
| |||
ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።
| |||
ከዚያም በኋላ ቶማስን። ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።
| |||
ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።
| |||
ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።
| |||
ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤
| |||
ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።
|
መዝሙረ ዳዊት
| ||
"እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው ..."
|
‹‹እንደተናገረ ተነስቷል›› ማቴ 28÷6
በሞቱ ሞታችንን ድል የነሳ በትንሣኤው ክብርን ያጎናፀፈን የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤
ሰላምና ጤና ዘወትር ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ ሽንገላ ባልተሞላበት ልቤ ዘለዓለም እመኝላችኋለሁ፡፡
‹‹ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱን ተወ፡፡›› እንዲል ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ የሰውን ልጅ በዕለተ ዓርብ ከአፈር ሰርቶ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎበት ሕይወትን የዘራ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ በደል የሞትን ጽዋ በቀራንዮ አደባባይ በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ተጎነጨው ክብር ምሥጋና ለርሱ ይሁንና፡፡
‹‹… በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር፡፡›› እንዲል ማቴ 16÷21 በቃሉ የታመነ አምላክ ነውና ቃሉን ጠብቆ በተሰቀለ በሶስተኛው ቀን መቃብር ፈንቅሉልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ እንደተናገረ ተነስቷል፡፡
በትንሣኤው ዕለት በበነጋው /ሲነጋ/ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም የጌታን ቃል ጠብቀው ቀን ቆጥረው እንደተናገረ መነሳቱን ለማየት ወደ መቃብር ሥፍራ አመሩ፤ በሥፍራውም ነጫጭ የለበሱ የእግዚአብሔር ሁለት መላዕክትና የጌታን ሥጋ ይጠብቁ የነበሩ የጦር ትጥቅ የለበሱ ወታደሮች ከሥፍራው ነበሩ፡፡ ሁለቱ ሴቶች ግን ከሥፍራው እንደ ደረሱ ጌታን አላገኙትም ነበር እርስ በርስም ተያይተው በሆነው ነገር ተደናገጡ እጅግም ፈሩ ለመልዓክ ፍርሃትን ማራቅ ልማዱ ነውና ‹‹እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሉ አውቃለሁና እንደተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም የተኛበትን ሥፍራ ኑና እዩ፡፡›› አላቸው፡፡ ‹‹… ከተነሳሁም በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ …›› እንዳላቸው ከትንሣኤው በኋላ ከወንድሞቹ /ከሐዋርያት ጋር ሊገናኝ ወደ ገሊላ ሄዳEል፡፡
ትንሣኤ የሚለው ቃል ተንሥአ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡
ልበ አምላክ ዳዊት በትንቢት አስቀድሞ መዝ 77÷65 ‹‹እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ …›› እንዳለው ‹‹ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩር ሆኖ ተነስቷል፡፡ 1ኛ ቆሮ 15÷20 ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ለሞታችን ጌታ በኩል /የመጀመሪያ/ ሆኖ ከተነሳ በትንሣኤው እንድንመስለው በሞቱም ልንመስለው ይገባል መጽሐፍ እንደሚተርክልን ያለበደል ያለ ሐጢአት እንደሞተ ሁሉ እኛም ያለ ሐጢያት ወደ መቃብር ልንወርድና የክብር ትንሣኤንም ልንጠባበቅ አንድም ዳግም ከመቃብር በላይ የሚቀር መልካም ሥም ነውና መልካም ሥም ሊኖረን ይገባል፡፡
ትንሣኤ ስንል ሁለት ዓይነት ትንሣኤ አለ፡-
1. የክብር ትንሣኤ
2. የሃሳር /የውርዳት/ ትንሣኤ ለጊዜው የመጀመሪያው በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
የክብር ትንሣኤን የሚነሳ ሰው፡-
- ቢሞት እንኳን ህያው ነው፡፡ ኤፌ 2÷8
- ከኃጢአት ሥራ በንሰሐ ተመልሷልና ሞት በእርሱ ስልጣን የለውም ራዕ 20÷6
ከኃጢአት መመለስ በራሱ ትንሣኤ ነውና ሉቃ 15÷11-30 ይኸውም ትንሣኤ ልቡና ይባላል ማሰብ ማስተዋል ያቃተው ክፉና ደጉን መለየት የተሳነው ልብ እውነትን ከሐሰት የደባለቀ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ከሆነ ባህርይ መመለስ በተናገሩት መጽናት ለአለሙት ህይወት ፀንቶ መቆም እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች በአጠቃላይ ትንሣኤ ልቡና ይባላሉ ለክብር ትንሣኤም ያበቁናል፡፡ በሕገ እግዚአብሔር እየኖሩ በንሰሐ መመላለስ በራሱ ትንሣኤ ነውና ሮሜ 13÷1 ሁላችንም በሕገ እግዚአብሔር ፀንተን ኖረን የክብር ትንሣኤው ተሳታፊ ለመሆን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁን፡፡
ትንሣኤ /የትንሣኤ በዓል/ ምን ያስተምረናል?
1. ፍርሃትን ያስወግዳል፣
2. በማለዳ ወደ እግዚአብሔር ቤት መገስገስን፣
3. በቃል መገኘት /‹‹ቃሉንም የሚያደርግ እርሱ ኃያል ነውና››/ ትን. ኢዩ 2÷11
4. ተስፋን ይሰጣል፣
5. ያዘጋጃል ያነቃል ያተጋል … ወዘተ
‹‹እናንተስ አትፍሩ …›› እያለ መልዓኩ ለሁለቱ ሴቶች እንደፅናናቸው ትንሣኤ በመጣ ቁጥር ይህ የመልአኩ የማጽናኛ ቃል ዘወትር እንድናስበው በፈራን በደነገጥን ቁጥር ፍርሃታችንን እንደሚያስወግድልን እንደሚያጽናናን እንማራለን፡፡
‹‹… ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ›› እንዲል እኛም ከተኛንበት እንቅልፍ የድብርትን ብርድልብስ ከደረበልን ውስጥ አምልጠን ለቆምለት ዓላማ ለፀሎት ለውዳሴ ለቅዳሴ ልክ ሲነጋ ማልደን ወደ ቤተክርስቲያን እንድናመራ ያነቃቃናል ያስተምረናልም፡፡
ከሦስት ቀን በኃላ እንዲነሳ ነግሯቸው እንደነበር ቃሉን ጠብቆ ከተናገረው አንዲት ሳያዘንፍ እንደተነሳ ሁሉ እኛም ለገባነው ቃል ኪዳን ቃላችንን እንዳናጥፍ የክርስትና መገለጫ የሆነውን እውነት ተግባራዊ እንድናደርግ በቃል መገኘትን ያስተምረናል፡፡
‹‹ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩር ሆኖ ተነስቷል›› እንዲል 1ኛ ቆሮ 15÷20 አስቀድመው ላንቀላፉት /አረፍተ ዘመን ለገታቸው፣ ለሞቱት/፣ ወደፊትም ለሚያንቀላፉት /ለሞት ወደ መቃብር ለሚሄዱት/ በዚያው ተስፋ የሌላቸውና በስብሰው እንደሚቀሩት ተስፋ እንደሌላቸው እንስሳትን እንደማይመስሉ የክብርን ትንሣኤ እንደሚነሱ ተስፋን ሰጥቶን ለክብር ለመነሳት በንሰሐ ህይወት እንድንመላለስ በትንሣኤው እንድንመስለው በሞቱም መምሰል እንዳለብን ያሳስበናል፤
በመጨረሻም የምንመለከተው ማንቃቱን ማትጋቱን ነው የትንሣኤን በአል ስንመለከት አይደለም ምድራዊ ሰዎችን ሰማያውያን መላዕክትን ሳይቀር አትግቶ በመቃብሩ ሥፍራ እንዲገኙ አድርጓቸዋል ሰዎችንም ስንመለከት በክርስቶስ የሚያምኑትን ብቻ ሳይሆን ወታደሮቹ ሳይቀር በሥፍራው ነበሩ እዚህ ላይ የምንረዳው የጌታችን ትንሣኤ ለሚያምነውም ለማያምነውም እኩል መሆኑን ነገር ግን በትንሣኤው መጠቀም አለመጠቀም የእኛ ፈንታ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡
ዛሬም ቢሆን ትንሣኤ በመጣ ቁጥር ‹‹በዓል›› መሆኑን ብቻ አስበን ለመብላትና ለመጠጣት ብቻ የምንሰናዳ እንደ ሁለቱ ሴቶች የጌታን ትንሣኤ ለማየት ከክብሩ ለመሳተፍ ነጋ አልነጋ እያሉ ሲጠባበቁ እንዳልነበር እኛ ለመብላት ለመፈሰክ ነጋ አልነጋ የምንል ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ እስከዛሬ ዝም ብሎ የቂም የበቀል የበደል የኃጢአትን ብርድልብስ ደራርቦ ሲያንቀላፋ የነበረ ልቡናችን የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ‹‹ትንሣኤ ልቡና›› ሊያደርግ በሌሊት ለፀሎት ለመትጋት ሊሰናዳ ይገባዋል፡፡
በዓሉ ይህንን የሚያበክረን ከሆነ የኛ ሕይወትና /ልብ/ና በዓሉ ምን ዓይነት ትስስር ይኖረው ይሆን? የፆም፣ የፀሎት … ልቡናችንስ ምን ይመስል ይሆን? ከሀሜት የነፃ ለይርቅታ የተሰናዳ፣ ለምሥጋና የተጋ፣ መልካም ነገር ሊያመላልስ የፈቀደ ይሆን? ዌስ ክህደትን የተሞላ ቂምን የቋጠረ የሞተ ልብ ይሆን?
በዓሉን የሰላም የጤና የብልጽግና የመላውን የንሰሐ ጊዜ ይቅር ባይ ልቡና የምንይዝበት ጊዜ ቃላችንን የምንጠብቅበት ጊዜ ለክብር ልንነሳ በመንፈሳዊ ሕይወት የምንኖርበትና ሰላሳ ስልሳ መቶ ያማረ ፍሬ የምናፈራበት ጊዜ ይሁንልን፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ