ባለፈዉ በሁለት ተከታታይ ክፍል ስለ ቅዱስ መስቀል ተመልክተን በክፍል ሦስት እንደምንገናኝ ተቀጣጠረን ተለያይተን ነበር
እግዚአብሔር ፈቅዶ አባቶቻችን እና ወንድሞቻችን በቃልና በመጽሐፍ ያቆዩልንን ትምህርት ሳልጨምር ሳልቀንስ ለንባብ እንዲመች በክፍል
በክፍል አቅርቤላችኋለሁ፤ ክፍል ሦስት እነሆ! በክፍል አራት ያገናኘን፡፡
3ኛ. ቅድስት
እሌኒና መስቀለ ክርስቶስ
ጌታችን መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በሐዋርያት
ስብከት የወንጌሉ ፋና ለዓለም ሲበራ በዕፀ መስቀሉ ልዩ ልዩ ተአምራት ይደረጉ ነበር፡፡ አስቀድመዉ ጌታን የሰቀሉ አይሁድ አሁን
ደግሞ በሰቀሉበት መስቀል ተአምራት ሲደረግ በማየታቸዉ በቅንአት መስቀሉን ከኢየሩሳሌም አጠገብ ቀብረዉ በአዋጅ ቆሻሻ በየእለቱ እንዲደፋበት
አደረጉ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሥራዉን የሚሰራበት የራሱ ጊዜ አለዉና በ327ዓ.ም.
የታላቁ ንጉስ የደጉ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒን አስነሣ፡፡ እርሷም አስቀድማ ከአረማዊዉ ንጉስ ቁንስጣ የወለደችዉ ልጅዋ
ክርስቲያን ከሆነላት ከቁስጥንጥንያ ወደ ኢየሩሳሌም ተሻግራ የጌታችንን ዕፀ መስቀል ልታወጣ ብፅዐት ገብታ ነበር፡፡ በልዑል እግዚአብሔርም
ፈቃድ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ስለሆነላት በመስከረም 17 ቀን ቁፋሮዉን አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን አወጣችዉ፡፡
መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል ቆሻሻ እየተደፋ ስለተከመረበት
ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በኢየሩሳሌም በነበረዉ አበዉ መሪነት ደመራ አስደምራ፣ ዕጣን አስጨምራ፣ ጸሎት
ስታስደርግ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ መስቀሉ በተቀበረበት ቦታ ላይ ሰገደ፡፡ በጢሱ ምልክትነትም ቦታዉ ስለታወቀ ለሰባት ወራት
ያህል ተራራዉ ተቆፍሮ ሊወጣ በቅቷል፡፡ ዛሬ በክርስቲያኖች ዘንድ ደመራ የሚደመረዉም ይህንኑ ለማስታወስ ነዉ፡፡
መስከረም 17 ቀን ወይም በዋዜማ፣ በዓለ መስቀሉን ስናከብር ከመስቀሉ ቀጥለን የምናስባት ቅድስት እሌኒ ናት፡፡ ቅድስት
ዕሌኒ የመስቀሉ ጥበብ ተገልጾላት ክብሩና ሞገሱ በግልጽ ታይቶአት፣ መድኋኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀል የት
ባገኘሁት እያለች ለብዙ ጊዜ ታስብና ትመኝ ነበር፡፡ በተለይም ልጄ መምለኬ እግዚአብሔር ንጉስ ቈስጠንጢኖስ፣ መክስምያኖስ ከሚባል
ጠላቱ ጋር ሲዋጋ፣ …
በ14ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግስት ግማደ መስቀሉ
ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ አፄ ዳዊትም ግማደ መስቀሉን አምጥተዉ በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር ሊያሳርፉት ያልሞከሩት ቦታ አልነበረም፡፡
ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸገረ፡፡ በመጨረሻ ግን ፡- « መስቀሌን
በመስቀልያ ሥፍራ አስቀምጠዉ » የሚል መልዕክት ከእግዚአብሔር ስለተነገራቸዉ፣ በግሸን ደብረ ከርቤ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን
አስቀመጡት፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያዉ ይገኛል፡፡
አወጣጡም ከዚህ እንደሚከተለዉ ነዉ፡-
« ዝንቱ
ትእምርተ መስቀል ትመዉእ ፀረከ፡፡ » በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትክን ድል ትነሳለህ፤ በሚል ራዕይ የእግዚአብሔር መልዐክ
የመስቀሉን ቅርፅ በብርሃን ሰሌዳ ስላሳየዉ ራዕዩ የእግዚአብሔር ኋይል መሆኑን በመገንዘብ፣ በሰንደቅ ዓላማዉ፣ በጋሻዉ፣ በጦሩ፣
በፈረሶቹ፣ሽልማትና በሠራዊቱ ትጥቅ ሁሉ መስቀልን አርማ በማድረግ በጠላቱ ላይ በዘመተ ጊዜ፣ ቃሉን የማያጥፍ እግዚአብሔርም ኋይለ
መዊዕ ሰለሰጠዉ ጠላቱን ድል ነስቶ መንግስቱን አደላድሎ ለክርስቲያኖችም የነፃነት አዋጅ አዉጆ በሰላም እንዲኖር ማድረጉን ካየች
በኋላ፣ ለመስቀለ ክርስቶስ የነበራት ክብርና ፍቅር በእጅጉ እየመጠቀ ሊሄድ ችሏል፡፡
መስቀል ክርስቶስ በአይሁድ ክፋትና ምቀኝነት ምክንያት መቃብር ተፈርዶበት
ማንም አይሁዳዊ የቤቱን ጥራጊ መስቀሉ ከተቀበረበት ስፍራ እንዲደፋ ሕግ ሆኖ ከሶስት መቶ ዓመታት በላይ ሲሰራበት የኖረ መሆኑ፣
ቅዱስ መስቀሉ በተቀረበት ቦታ ላይ የተሰበሰበዉ የቤት ጥራጊ ተራራ አክሎ የተፈጥሮ ጋራ እንጂ የመስቀል መቃብር ይሆናል ብሎ መገመት
እስከማይቻል ድረስ ደርሶ ነበር፡፡ ቅድስት እሌኒ ግን መስቀሉን ከአይሁድ በቀር ሌላ ሊያጠፋዉ የሚያስብ እንደማይኖር ተረድታለችና
አረጋዊያን አይሁድን አጥብቃ መመርመርን መረጠች፡፡ በዚህ መሰረት ከተጠየቁ አረጋዊያነ አይሁድ መካከል አንድ ሥሙ ኪራኮስ
የሚባል አረጋዊ፣ ከአያት ቅድመ አያቱ የሰማዉን ምሥጢር ነገራት፤ የመስቀሉ መቃብር ከተራሮቹ አንዱ መሆኑን አሳወቃት፡፡
« አረጋዊ
አንገሐ ገይሠ ብእሲ ዘስሙ ኪራኮስ ዘዕጣን አንፀረ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል» ስሙ ኪራኮስ የሚባል ሽማግሌ ሰዉ መስቀሉ የሚገኝበትን ምሥጢር ለንግስት እሌኒ
ይነግራት ዘንድ ማልዶ ገሰገሰ፤ ዕጣንም መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ በማመልከት ጢሱ ሰገደ፡፡ አይሁድ በጎልጎታ የቀበሩት ዕፀ መስቀልም
ዛሬ ተገኘ፡፡ (እንዳለ ቅዱስ ያሬድ)
ቅድስት ዕሌኒ ዕጣን አጢሳ ፈጣሪዋን በጸሎት ብትለምን ምልክት እንደምታገኝ
ተገልጾላትና አበዉን ሰብስባ የዕጣኑ ጢስ ሰማይ ደርሶ ለመስቀሉ በመስገድ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ በትክክል አመለከተ፡፡
ከዚህ በኋላ ቅድስት እሌኒ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን በመገንዘብ ተራራዉን
የማስቆፈር ሥራዋን ቀጠለችበት፡፡ ነገር ግን ተራራዉ ሲቆፈር፣ ከፊሉ ስራዉን የሞኝነት ሲለዉ፣ ሌላዉ ደግሞ ተስፋ በማስቆረጥ ሥራዉን
ለማሰናከል በሥራዉ ላይም እንቅፋት መፍጠሩን ተያያዘዉ፡፡ ቅድስት እሌኒ ግን ከእግዚአብሔር የማረጋገጫ ምልክት አግኝታለችና ጥረቷን
በእምነት ቀጠለች፡፡ መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም. የተጀመረዉ
ቁፋሮ ከ6 ወር ብርቱ ጥረት በኋላ መጋቢት 10 ቀን 327 ዓ.ም. መስቀሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተገኘ፡፡
በቁፋሮ የተገኘ መስቀሎችም ሦስቱ ነበሩ(ሁለቱ ወንበዴዎች ግራ እና ቀኝ
የተሰቀሉበት መስቀል)፤ እነዚህም አንዱ የጌታ መስቀል ሲሆን ሁለቱም የሁለቱ ሽፍቶች መስቀሎች ናቸዉ፡፡ በዚህ ጊዜ የጌታችንን መስቀል
ለይቶ ለማወቅ ችግር ሆኖ ነበር፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር የታመነ ልብ፣ ምንም ቢቸግር የችግሩ መፍትሔ ከእግዚአብሔር መሆኑን ያዉቃልና በቅድስት እሌኒ አዕምሮ አንድ ሐሳብ ተቀረፀ፡፡ ይኸዉም
መስቀለ ክርስቶስ ኋይሉን የሚያሳይበትና ራሱን የሚገልፀበት ሁኔታ እንዳለ የሚያስገነዝብ ሐሳብ መሰረት መስቀሎቹ ምልክት እንዲያሳዩ
ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ የሁለቱም ሽፍቶች መስቀሎች ምንም ዓይነት ምልክት ያላሳዩ ሲሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ግን
ሙታን ተነስተዋል፤ ዐይነ ሥዉራን አይተዋል፤ ሽባዎች ተነስተዉ ሮጠዋል በአጠቃላይ በመስቀል ክርስቶስ ልዩ ልዩ ተአምራት ታይቷል፡፡
ብዙ በረከትም ተገኝቷል፡፡
ቅድስት እሌኒም ይህንን ክብር ያደላትን ፈጣሪዋን በማመስገን መስቀለ ክርስቶስን
በወርቅና በዕንቊ አስጊጣ በኢየሩሳሌም በክብር እንዲቀመጥ አደረገች፡፡መስቀሉ ተቀብሮበት በነበረበት ቦታ ላይም « ትንሣኤ ክርስቶስ
» ተብሎ የተሰየመ ትልቅ ቤተክርስቲያን አሰራች፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን መስቀሉ ወደ ፋርስ በምርኮ ተወስዶ ከቆየ በኋላ እንደገና
ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ የተባሉ አባት መጽሔተ አሚን በሚል ጽሑፋቸዉ እንዲህ ይላሉ፡-
« እሌኒ
ንግሥት ከመቃብር ያወጣችዉ መስቀለ ክርስቶስ በወርቅና ዕንቁ ሸልማና አጊጣ በኢየሩሳሌም አስቀምጣዉ ሲኖር፣ ኮስሮኤል የሚባል የፋርስ
ንጉሥ 62000(ስልሣ ሁለት ሺህ ) ክርስቲያኖችን አስገድሎ ከሶስት ሺህ በላይ የሆኑትን ማርኮ ኢየሩሳሌምን በማቃጠል መስቀለ ክርስቶስን
ከብዙ ንዋየ ቅድሳት ጋር ዘርፎ ወስዶት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች በዚህ እያዘኑ ሳለ ፈቃደ እግዚአብሔር ያነሣሣዉ ሕርቃል የሚባል ንጉስ በ628ዓ.ም. ወደ ፋርስ ዘምቶ ኮስሮኤልን ድል አድርጎ የጌታችንን
መስቀል አግኝቶ ሲመለስ መስቀሉን ራሱን ተሸክሞ ከፋርስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ አለጫማ በእግሩ በመጓዝ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ኢየሩሳሌም
ከተማ በደረሰ ጊዜም የከተማዉ ህዝብ ሁሉ ከደስታዉ ብዛት የተነሳ መብራት፣ ችቦና ጥዋፍ እያበራ ንጉሡንና መስቀሉን በዕልልታ ተቀበለ
ይባላል፡፡ በኢየሩሳሌም ያሉ ምዕመናን ክርስቲያን ሁሉ መስቀሉ ከምርኮ
ሲመለስ በዕልልታና በደስታ፣ አበባ እየያዙ በመብራት እንደተቀበሉት ሁሉ በሀገራችን በኢትዮጵያም መስከረም 16 ቀንና 17 ቀን መብራት እያበራን አበባ ይዘን በዕልልታና በሆታ በየዓመቱ በዓሉን እናከብራለን፡፡
ይህም በ629 ዓ.ም. የተጀመረዉ በዓል በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ጸንቶ ይኖራል፡፡ » በማለት ጽፋል፡፡ መጽሔተ አሚን
ገጽ 55 እና 56
በእርግጥ እኛ ኢትዮጵያዉያን ዓለምን በሚያስደንቅ ሥነ-ሥርዓት፣ ደመራ
ደምረን ችቦ አብርተን ካህናት በዝማሬ (በጸሎት) ምዕመናን በሆታና በዕልልታ፣ በዓለ መስቀልን በየዓመቱ እናከብራለን፡፡ በተለይም
ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ልጆች በመላዉ አገሪቱ ለበዓሉ አከባበር ድምቀት ልዩ ፈርጥ እና ጌጥ በመሆን ከፍተኛ ድምቀትን ይሰጡታል፡፡ይህንንም
ድንቅ የመስቀሉን በዓል ለመመልከት ከመላዉ ዓለም ብዙ ቱሪስቶች ወደ አገራችን በመምጣት ስርአቱንን ይጎበኙታል፡፡
ከዚህም ሌላ አስደናቂዉ ነገር በዓሉን ማክበራችን ብቻ ሳይሆን መስቀል
የክብርና የነጻነት አርማችን መሆኑን አምነን የክብር ጌጣችን በማድረግ በንቅሳት በግንባራችን እናሳየዋለን በአንገታችን እንሸከመዋለን በተለይ ሴቶች በልብሳቸዉ
ያስጠልፉታል በየቁሳቁሱ ላይ ይስሉታል፡፡ ከእነዚህ ምልከቶች ሁሉ ቢያንስ አንዱ ስንዃ የሌለዉ ክርስቲያን በማንነቱ ያፍራል እንጂ
ክርስቲያን የሆነ መስሎ አይታየዉም፤ ለክርስቲያን ሁሉ ከመስቀል የተለየ ህይወት የለዉምና መስቀልን ይመካበታል፡፡እንመካበታለን!
ዛሬ ዛሬ ግን አንዳንዶች መንፈሳዊ ቅዱስ እና ክቡር እቃነቱን እንዲሁም መንፈሳዊ ህይወቱን እየዘነጉት በመምጣት የልብስ ማላበሻ
ቁስ ወይም ጌጥ አድርገዉት ይታያል፤ ይህ ድርጊት ከነዉርነቱም አልፎ ልናገኘዉ የሚገባንን የመስቀሉን በረከት ያሳጣናል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ከአራቱም አቅጣጫ በመሰባሰብ
በአምባሰል ተራራ ላይ ከትመዉ መስከረም 21 እና ጥር 21 ቀን በስፍራዉ በመገኘት የስፍራዉ በረከት ተቋዳሽ ለመሆን ወደ ግሸን
ደብረ ከርቤ ይጓዛሉ፡፡ በዓሉም በድምቀት ይከበራል፡፡
ስለዚህ መስቀል ዓለም የተቀደሰበት ሰይጣን ያፈረበት ኋያላችን ክብራችንና
ሕይወታችን ስለሆነ እንኮራበታለን፡፡
«የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኋይል ነዉና፡፡» 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡18
የመስቀሉን ታሪክ ጽፈዉና ደጉሰዉ ላቆዩልን ለአባቶችን ክብር ይግባቸዉ፤ በዘመኑ ላሉ ለቤተክርስቲያን መምህራን እግዚአብሔር
ፀጋዉን ያብዛላቸዉ! መልካሙን አገልግሎት የሚያገለግሉበትን ዕድሜ ይስጣቸዉ፡፡
በመጨረሻም የመስቀልን በዓል እንዴት ማክበር እንዳለብን
እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በቀጣይ የምንመለከተዉ ይሆናል፡፡ ይቆየን!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ