ማክሰኞ 16 ኦክቶበር 2012

.ጐልማሳ ተረታ በጐረምሣ




31 ዓመት ፣ ሁለት መንግሥት፣ ብዙ ምኞት፣ ብዙ ጥረት ብዙ ሙከራ፣ ብዙ ሽንፈት…..ሶስት ዓሥርት ዓመታትን የዳፈነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለራሱም የናፈቀውን ድል ለኢትዮጵያ ህዝብም ያለውን የእግር ኳስ ፍቅርና ድል ከትውልድ ወደ ትውልድ ከመንግሥት ወደ መንግሥት ሲቀያየር የነበረውን ጉጉቱን ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዲስ አበባ  እስታዲየም ከቀኑ ዓሥር ሰዓት ጀምሮ  ከሱዳን  አቻው  ጋር  ያደረገውን ትንቅንቅ በ2ለ0 90 ደቂቃውን ሲያጠናቅቅ በየቤቱና በየቦታው ድምፁን አጥፍቶ  በድጋፍና በጉጉት ሲከታተል የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር ዳር እንዲነቃነቅ አድርጐታል፡፡  ዋልያዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለአገር  ክብር፣ ለትውልድ ታሪካዊ የሆነውን ድል ለማስመዝገብ የቻሉት ከተለያየ ቡድን ተውጣጥተው በአንድ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሠልጥነው አሥራ አንድ በመሆን ተጫውተው በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ በጨዋታና በግብ ብልጫ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ እንድትሳተፍ አብቅተዋታል፡፡
     ብሔራዊ ቡድኑ ጐል አስገብቶ ማሸነፍ አሸናፊነትን ማሥቆጠር ብቻ  አልነበረም የሠራው:ለ31 ዓመታት የተዳፈነውን የተናፈቀውን ለአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ፣አንገት ደፍተንበት ተስፋ ቆርጠንበት የነበረውን የእግር ኳስ ነገር በቃ አከተመለት የተባለውን ዋልያዎቹ አባቶቻችን የፈፀሙትን በታሪክ የሠማነውን መላው ኢትዩጵያዊ የናፈቀውን እኛም ናፍቆናልና ለድል ደርሰናልና አይዞሽ አንገትሽን ደፍተሽ ካቀረቀርሽበት ቀና እናደርግሻለን፣ የጓጓሽውን እናሳይሻለን በማለት ቃል ገብተው ቃላቸውን ጠብቀው  ቃላቸውን ፈፅመው አኰሯት ህዝቧን አስደሰቱት፡፡
     በግማሽ 45 ደቂቃ ያልታየው ተስፋ የደበዘዘው ድባብ ዳግም አንገታችንን የሚያስደፋ አስመስሎት ነበር የአዳነ ግርማ ሙከራውን ለጐል አለማብቃትም ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍለንም ነበር፣ ነገር ግን ያ ከዋልያዎቹ ሲጠበቅ የነበረው የሁለት ግብ አብላጫ ድል የማታ ማታ እውን ሆኖ ወንዱን ከሴት፣ወጣቱን ከአዛውንቱ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሠዓት ጀምሮ ከእስታዲዮም አንሥቶ በቴሌቭዠንና በሬድዮ ሲከታተል የነበረውን ሁሉ አስፈንጥዞታል፡፡
     የአገር ኩራት የሆኑትን ዋልያዎች ለመደገፍ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ሣይሆን ከመላ አገሪቱ  የመጡ ወጣቶችና አዛውንቶች ነበሩ፣ በዋዜማው ከምሽቱ 5 እና 6 ሰዓት ጀምሮ የእስታድየም መግቢያ ትኬት ለመግዛት ተራ ሲጠብቁ ያደሩ ጥቂት አልነበሩም፡፡  ከሃያ ሁለት ሺ የማይበልጡ ተመልካቶችን የመያዝ አቅም ያለው የአዲስ አበባ እስታድየም እስከ 30 ሺ  የሚጠጉ ተመልካቶችን ተጨናንቆ  በመያዝ  ሲያስተናግድ ከዚያ በላይ ብዙ ጊዜ እጥፍ በጉይዋ የያዘችው አዲስ አበባ ዳግም በቴሌቭዠን መስኮት ለዘጠና(101) ደቂቃ ስታስኮመኩም ነበረች፡፡  አመሻሽ ላይ ግን በውስጥም በውጭም የነበረውን ህዝብ ጮቤ አስረገጡት ዋልያዎቹ፡፡
     ዋልያዎቹ አገርን ወክለው ሲጫወቱ ሌላ ጊዜ በዚሁ አዲስ አበባ  እስታድየም እንደጠላት እየተያዩ የሚፋለሙ  የተለያየ ቡድን ተጫዋቾች ዛሬ ግን የጋራ  አገራቸውን ጉዳይ በአንድነት በመሆን ጉዳየቸው በማድረግ አንዱ ከሌላ ቦታ መጥቶ አጥቂ ፤ ሌላው ተከላካይ ፤ሌላኛው ወገን አማካይ ከአንደኛው ቡድን የመጣው ዳግም በረኛ የቀረው ደግሞ ተጠባባቂ በመሆን አገርን ለድል ህዝብን ለደስታና ለኩራት በአንድነት አደባባይ ወጥተው እንዲዘምሩና እንዲጨፍሩ አድርገዋል አንድ ሆነው ለአገር በመስራትና ውጤትን በማምጣት እምዬ ኢትዮጵያ አንገቷን ያስደፋት ለዘመናት የናፍቋት ህዝቦችን በሰቀቀን በጉጉት እንዲያልቁ ያደረጋቸው ከዛሬ ነገ ታሪክ ይቀየራል እያለ ዓመታት በተቀየረ ቁጥር የሚያስናፍቃቸው ብዙ አገር አለ ከጫፍ ጫፍ አንድ ሆነን ልንወጣበትና ድል ልናደርገው የሚገባ ጥንተ ጠላታችን ድህነት፣ ጦርነት፣ እርስበርስ መጠላላትና መከፋፋል፣ በሽታ…. እነዚህ ሁሉ እንደ እግር ኳስ ድል በአገራችን በኢትዮጵያ  ከተናፈቁ ዘመናት ተቆጥረዋል መገላጫዋ  በረሃብ ህዝቦቿ የሚረግፋ በእርስበርስ ጦርነት የምትታመስ በሽታ የሚያጠቃት፣ በመከፋፍል ያለቁ…… የሚለው መለያችን ከሆነ ሰነበቱ፡፡ ይህን ዘመናት ያስቆጠረ ታሪክ ለመቀየር፣ የናፈቀንን አንድነት ለማምጣት፣ ስማችንን ለማደስ አንገታችንን ቀና አድረገን ደርታችንን ነፍተን በዓለም አደባበይ ለመታየትና ለመናገር፣ እኛ ኢትዮጵያውያን  ነን ርሃብ ጦርነት በሽታ የትናንት ታሪካችን እንጂ የዛሬ ማንነታችን አይደለም ዛሬ እኛ ኩሩ ህዝብ ነን፣ ትናንት ተከፋፍለን እርስበርስ ብንዋጋም ዛሬ ግን እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅራችን ለዓለም ምሳሌ መሆን የምንችል ነን፣ ትናንት የዓለም ቁንጮ እንዳልነበርን ዛሬ የዓለም  ጭራ ብንሆንም ነገ ግን ታሪካችን ተቀይሮ ሁላችንን ለልማት ጠንክረን በመነሳታችን የትናንቱ ቦታችን የዓለም ቁንጮነትን እንይዛለን በድህነታችን ብዙዎች ጣታቸውን እንዳልቀሰሩብን ነገ ግን ለዓለም የምንደርስና ተምሳሌት የምትሆን  ኢትዮጵያን እንፈጥራታለን ለማለት ኢትዮጵያዉያን በልባችን የሞላውን ልዩነትና ክፋት በማስወገድ ለአንድ አገራችን/ኢትዮጵያ/ዓላማ ስንል ሁሉን ወደ ጐን በመተው እንደ ኢትዮጵያ  እግር ኳስ ብሔራዊ  ቡድን ተግትን ቀሪውን አርባ አምስት ደቂቃ  ልንጫወት  ግድ ይላል ያለፈው 45 ደቂቃ አርኪ ተስፋሰጪ  አልነበረም ንጉሱ በደርግ ደርግ  በኢህአዴግ ኢህአዴግ ደግሞ በእርስበርስ መተካካት ጊዜው ባክኗል እንደ አዳነ ግርማ ሙከራን ለጐል አለማብቃተና መሳሳት ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል እነደነበረ በደርግ ጊዜ በጦርነት በምርጫ 1997 ዓ.ም. በወጣቱ ሞት እስርና እንግልት የኢትዮጵያ ራዕይ ለማሳካት ብዙ ተከፍሏል ዛሬም እንዲሁ፣ አሁን ግን ረጋ ብለን የምናስብበት የዕረፍት ሰዓት የሚተኙበት የሚቀመጡበት ሳይሆን እርስ በርስ የሚመክሩበት  ደካማን የማያጠነክሩበት ተቀያሪ የሚቀይሩበት  ከአሰልጣኝ ምክርና ተግሣፅ  ማበረታቻ የሚያገኙበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ ያለነው ሆኖም ጊዜው አጭር ነው፡፡
ለቀሪው 45 ደቂቃ ተግትን ለመሥራት ታሪክ ለመቀየር የጠፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥም በአንድነት የምናረካበት ለአገር የምንሰራበት ልዩነትን አጥብበና ወደጐን በመተው ለአገር ክብርና ጥቅም ሲባል አንድነትን በመፍጠር አንተ የእገሌ ነህ አንተ የእንቶኔ ነህ ውጤት ልመባባሉን ትተን መድረክ ቅንጅት አንድነት ፣ኢህአዴግ፣ኦነግ፣ ኦብነግ….. ወዘተ የሚባሉት ድርጅታዊ ስሞች ትተን ኢትዮጵያዊነትን ይዘን ለአንዱ አገራችን ለሠፊው ህዝባችን ቅድምያ በመሥጠት ልንሥራ ናስመዘግብ ይገባል እንደ ከዚህ ቀደሙ ሆድ የሚነፋ ተስፋ ህበረተበቡ አያሻውም አገርም አያስፈልገውም፡፡
      የኢትዮጵያን ህዝብ እንደምናየው ለአትሌቱም፡ ለእግር ኳሱም፡ ለአባይም….. ድጋፉን በነቂስ ያሳያል ባለሀብቱም ለድጋፍ እጁን ይዘረጋል፡ቃል ይገባል፡ከዚህ ቀደም እንዳስለመዱት ለተጫዎችቹ የተለያዩ ስጦታዎችን ለማበርክት ቃል የገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡  ታዲያ የፓለቲካ መሪዎቻችን፣ የሃይማኖት አባቶቻችን መከፋፈሉን ትተው እርሰ በርስ መነቋቆሩን አቁመው በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው በአንድ አላማ ለአንዲት አገራቸው ለሠፊው ህዝባቸው ቢተጉ እውን ኢትዮጵያ ሥሟ በርሃብና በእርስበርስ ጦርነት ይነሳ ነበር በፍፁም  ሃያ እና ሰላሳ አባላት  የያዘ አንድ ቡድን የደገፈና ለድል ያበቃ ህዝብ፣ ቡድኑን በመምራትና በማሰልጠን ለድል ያበቃ አንድ አሰልጣኝ  ሰ31 ዓመታት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ካቀደጀና ለአፍሪካ ዋንጫ ካበቃ አንድ የአገር መሪ ደግሞ ከሚኒስተሮችና በተለያየ ደረጃ ላይ በመሆን የሚሰሩትን ባለስልጣናት በመያዝ 80 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጐኑ በማሰለፍ ኢትዮጵያን  መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ማሰለፍ ፣ ህዝቦቿን ደግሞ እስር በርስ የሚፋቀሩ አገርን ለማልማት ጠንክረው የሚሰሩ ዜጐች ማድረግ ይችላል፡፡  የፓለቲካ ልዩነትን ወደ ጐን በመተው አገርንና ህዘብን  በማሰብ መከፋፈል  ያሳደጋት አገር፣ እርስ በርስ ጦርነት ያለማት አገር የለችም ስለዚህ ትናንት  አልፋል በትናንት በሬም ያረሰ የለም ዛሬ ደግሞ 45 ደቂቃ ግማሹ ዘመናችን ተጋምሷል በቀሪው ጊዜአችን አመርቂ ውጤት ለማምጣት የጐሪጥ መተያየቱን ትተን ተናበን ወደ ድል ለማምራት አንዱ እንሁን ህዝቡን ለጦርነት ሣይሆን ለልማት እንጠቀምበት በድጋሜ ዛሬ ላይ ሆነን የምንሥተው ሥተት እንደትናንቱ በቸልታ የሚታለፍ ሣይሆን ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍለን ከተለወጥን ዳግም ከድህነት ታሪክ ወደ መካከለኛ ገቢ የምንሸጋገርበት አለበለዚያ ግን ባለንበት የምንረግጥ ባስ ካለም እጅግ ወደታች የምንዘግጥበት ሰዓት ነው፡፡
    በአገራችን ላይ የተንሰራፋው ችግር የጐልማሳ ዕድሜ የያዘው በተተኪው ትውልድ በጐረምሣው ታሪክ ሆኖ ሊቀር ጊዜው  አሁን ነው የመተካካቱ ጅማሬ  አኩሪ  በሆነ መልኩ ሊቀጥል ግድ ይላል አሰልጣኝ ሠውነት ቢሻው በጥንካሬ ቡድናቸውን በታክቲክ  በቴክኒክ በሞራል በአካል ብቃት  በአሰላለፍ…… ወዘተ ብቁ በማድረግ ከድል እንደበቁት ሁሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ብሔራዊ የአገር ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን፣ ክቡራት ሚኒስተሮችን አምባሳደሮችን፣… ወዘት ለልማቱ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ብቁና ትጉህ ቀና ቡድን ሊያበቁ የሚገባበት ሰዓት አሁን ሉ፡፡  ለአገር ዕድገት የተናጠል ሣይሆን የጋራ /የቡድን/ ሥራ የሚሠራበት ሠዓት ላይ እንደሚገኙ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
     አሁን ጊዜው የፓለቲካ ልዩነት ወደጐን የሚባልበት የአገር አንድነትንና ልማትን አንግበን የምንነሣበት ሰዓት ላይ ነው ያለነው እገሌም እንቶኔም ማንመ ይሁን ምንም በጥላቻ መፈራረጅ አቁመን በፍቅርና በአንድነት መንፈስ ለአንዲት ኢትዮጵያ  ለሠፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል መሥራትና ማልማት ብቻ በግብ ብልጫ ለድል መብቃት እገሌ የሚባል ድርጅት አባል ግብ አስቆጠረ መሆኑ ቀርቶ ኢትዮጵያ አሸነፈች የሚለው ሊቀድም ይገባል፡፡  የባከነ ሰዓት ላይ ነውና ያለነው ጠላትን በመከላከል ክፍተትን በመሸፈን አስተማማኝ ውጤትነ ለማምጣት መከላከልን መሠረት ያደረገ ጥቃት በድህነት  ላይ በጦርነትና በረሃብ ላይ በድንቁርና እና በበሽታ ጥቃት መፈፀም ግዴታ ነው ፡፡
     ብሔራዊ ቡድናችን ለዚህ ድለ እስከሚበቃበት በብሔራዋ ቡድኑ ብዙ አጥቂዎች ተከላካዮች አማካዮች ነበሩት ይበልጡኑ ደግሞ ግብ በማግባት የሚታወቁ ነገር ግን በጉዳት በተለዩበት ሰዓት እነርሱን ሳናሳልፍ እንዴት ብሔራዊ ቡድኑን ለጨዎታ እናሰልፋለን ብሎ ህዘቡ ሲጨነቅ ቡድኑ ግን አጥቂያችን ቢጐዳ አንበላችን መካከላችን ባይኖር እኛም ግብ ማስቆጠር እንችላለን አምበልም ከመካከላችን ማፍራትና መተካት እንችላለን፣ የቡናው ባይኖር የጊዮርጊሱ ከዚያም ቢጠፋ የደደቢቱ ወይም የስኳር ፋብሪካው አለ በማለት በልብሙሉነት  የአገራቸው ታሪክ እንደቀየሩና የ31 ዓመቱን ክብሯን መልሰው ለማምጣት እንደበቁ መላው ኢትዮጵያዊ በክቡር ጠቅለይ ሚኒስትሩ እና በብፁዕ ፓትራያሪኩ ድንገተኛ ህልፈት ህይወት ቢደናገጥና ተስፋ ቢቆርጥ የተያዘው ልማት እንደማይደናቀፍ እኛም አለን በማለት ከየድርጅቱ የጐደለውን አሟልተውና የተሻለ ቡድን በመፍጠር የአገርን ሥምና ታረክ መጠበቅ ግድ ይላል ኢትዮጵያዊነት የሚለካበት ጊዜው አሁራ ነውና እነዚህ  ሠዎች ቢኖሩ መልካም ነበር  ባይኖርም ግን እንሰራለን እንለወጣለን የአንድ ሠው አስፈላጊነት አለ የማይባል ቢሆንም አገር ግን በአንድ ሠው ራዕይና ግብ የትም አትደርስም በህብረትና በአንድነት እንጂ እነዚሀ ሠዎች ለአገር ያላሠለሰ ጥረት ቢያደርጉም ዛሬ የሉም እነርሱ የሉምና አገር እጃን አጣጥፋ ትቀመጣለች ማለት አይደለም ተጫዋቶቹ የብሔራዊ ቡድኑ አባል ናቸው እንጁ ብሔራዋ ቡድኑ የነርሱ /የግለሰቦች/ ነው ማለት እንዳልሆነ እንዲሁ እነዚህ መሪዎች የአገርና የህዝብ ሀብት ናቸው እንጂ አገር የነርሱ የግል ጥቅም የነርሱ የአዕምሮ ውጤት ናት ማለት አይደለም ምናልባት የላቀ አስተዋፅኦ አድርገው ይሆናል አድርገዋልም ነገር ገን በነርሱ ህልፈተ ህይወት የአገር ጉዳይ ተዳፈነ ማለት አይደለም ጥቂቶች ቢያልፋ በብዙሃን ይተካልና፡፡
     በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አጥቂው በጉዳት ከሜዳ ስለወጣ አለበለዚያም በቅያሬ ከሜዳ ስለወጣ ተከላካዩ መከላከሉን በረኛው ግብ መጠበቁን አማካዩ አቀብሎ ተተኪው ግብ አያስቆጥርም ማለት እንዳልሆነ እንዲሁ የተያዘውን መርኃ ግብር ልማት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የቀድሞዎቹ ባለድርሻ አካላት አዲሶቹም ተሻሚዎች ነባሮችን ተክተው ዕቅዱን አያስፈፅሙም ማለት  አይደለም፡፡  በእግር ኳስ ሜዳ አጥቂው ሲወጣ ሌላ አጥቂ ይመጣል እንጂ የማጥቃት  ሞያውን ለብሔራዊ ቡድኑ ይዞ የግድ የአጥቂውን የማልያ ቁጥር ይዘህ ካልመጣህ  ሥምህን ካላስቀየርክ እንደማይባል እንዲሁ የጠቅላይ ሚንስትሩን ሥም ብሔር አስተሳሰብ እምነት አቋም፣ ቋንቋ፣…… ይዘው መምጣት አይጥበቅባቸውም ዋናው አላማቸው  ግብና ውጤት እንጂ፣ ተቀያሪው ሲመጡ ያሰሩትን  ሊፈቱ፣ የነፈጉትን ሊሰጡ፣ የሾሙትን ሊሽሩ፣ ያጥላሉትን ሊወዱ፣ ያራቁት ሊያቀርቡ፣ የሠቀሉትን ሊያወርዱ… ህጉ ይፈቅድላቸዋል የርሳቸው ለምድ ለብሰው ሊመጡ አይገደዱም ተተኩ ሳይሆን የሚባለው በምትሃተዊ መንፈስ ተቀየሩ እንጂ ስለዚህ ብሔራዊ ቡድን ጨወታ ላይ የቡድን ውጤት አሳምሮ አገርን ለድል ለማብቃት የመተካካቱን ሥራ በጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ምናልባት እንደብሔራዊ ቡድናችን ተጫዎቻችን በጉዳት አለበለዚያም በቀይ ካርድ ከሜዳ ስናጣ ባለሙያውን በረኛ መቀየር አቅቶን ተጫዎች ውጤቶን ለማስጠበቅ  ለቁጥር ያህል ብቻ ሲባል ሙያው ያልሆነውን ተጫዎች በመተካት ታሪክ ሊያበላሽ የሚችል ዋጋ ልንከፍል እንችላለንና ብሔራዊ ቡድኑም ፓርላማውም ይህን ልብ ይበሉት፡፡ 
     ወደ ማጠቃለያው ማንሳት የምሻው ዐብይ ጉዳይ የብሔራዊ ቡድናችንን ደስታ የህዝባችንን ተሰፋ ታሪክን እንደነበር ሊያስቀጥልና የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ህልማችንን ሊያደበዝዝ የነበረው የመጨረሻ የሱዳን አቻችን ሙከራ ግብ መሆን ነበር ሴኔጋላዊዉ ዳኛ የጫወታውን ፍፃሜ ማብሰሪያ ፊሽካ ባይነፋ ኖሮ ይህ የሚያመለክተው አሁንም  በእግር ኳሳችን ላይ ምንም አንኳን ድልን መጐናፀፍ ብንችል ጠንክረን ያልስራነውና ያልደፈነው ክፍተት እንዳለ ያሳየናል  ስለዚህ የብሔራዊ ቡድኑ ዛሬም ለደቡብ አፍሪካው የዋንጫ ትንቅንት የበለጠ ሊራ ህዝቡም ከሜዳ ውጭም ሊያበረታቸውና ሊደግፋቸው ሊመክራቸውና ሊገስፃቸው ለድል ሊያበቃቸው የሚገባውን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል፡፡  ልብ ብለን ልናጤነው የሚገባው ይህ ትውልድ ሊቀይረው ያልቻለውን ጉዳይ ዋጋ እንከፍልበት ነበር  የተዘናጋንባት የመጨረሻ ግብ ታሪክ ታዝባ፣ ደስታን ታጨልም፣ ሌሎች ችግሮችንም ታመጣ ነበር፡፡
      እንዲሁ ደግሞ የአገራችንን ልማት፣የድህነት ቅነሣ የበሸታን ማስወገድ፣ የጦርነትን በሰላም መተካት…… ሁሉ ትናንት መልካም ጅማሬ ሊኖረው ይችላል፣ ይህ ግን አስተማማኝ አይደለም በአገር ጉዳይ ተዘናግተን ሌላ ነገር ላይ አትኩሮታችን ከተሰረቀ በግለሰብ ጉዳይ ላይ ከደረግን አርን ወደኃላ ልናስቀራት የትናንት ታሪካችንን ልንደግም የህዝቡን የረጅም ዘመን ናፎቆት ተስፋ ልናጨልምበት ነው ማለት ነው ይህን ድህነት ጐልማሣውን በጐረምሣው ጥረታችን ታሪክ እናድርገው እስኪ ጠቅለል አናድርገው የአይናለምንና የአዲስህንፃን የበረኛነት እኔ ነኝ  እኔ ነኝ የአገርን ድል ለማስጠበቅ የነበረ ትንቅንቅ መቃኘት ይቻላል፡፡  በረኛችን ደማል ተጐድቶ ከሜዳ መውጣት እንዳለበት አሠልጣኝ ሠውነት ቢሻው እንደሰማ ዓይናለም በረኛ መሆኑን ከዚህ ቀደም በነበረው ታሪኩ ያውቀው ስለነበር ጓንት አጥልቆ ማልያ ቀይሮ ካጠናቀቀ በኃላ አዲስ ህንፃ በልበ ሙሉነት በመምጣት እኔኮ በበረኛነት አሪፍ ነኝ በመለት ክፍተቱን ሊሞላ ዝግጁ መሆኑን ለሠውነት ይነግረዋል፣ ሠውነትም በቃ አንዴ መድቤአለሁ አላለም ተነጋገሩበት ብሎ አድሉን ለተጫዎቶቹ ሠጠ ዓይናለም ከእኔ አዲስ ይበልጣል በማለት ማልያውን አወለቀ ተጫዎቶቹን አዲስን ደገፋ ጨዋታውን ቀጠሉ በድል ተጠናቀቀ፡፡
    ይህ አጋጣሚ በአሜሪካ የኘሬዘዳንታዊ ምርጫ በ2001 ዓ.ም. ሲካሄድ የነበረውን ቅስቀሳ ለኘሬዘዳንትነት ዕጩ የነበሩት ማኬ ከእኔ ባራክ ኦባማ ይበልጣል በማለት ከግል ሥልጣን ይልቅ አሜሪካንን አስቀድመው ነበር፡፡  ዓይናለምም ከእኔ አዲስህንፃ ይበልጣል በማለት ታሪክ ደገመ፡፡  ኢትዮጵያን በመጪው ዘመን ታሪኳን ለመቀየር ዉጤታማ ለማድረግ ፍቅር እንጂ ፀብ አይጠቅማትም አንተ ትብስ አንች ትብስ ከኔ አንተ ትሻለለህ አንተ ትክክል ነህ መባባል አንጂ መናቆር የጐሪጥ መተያየት የትም አያደርሳትም እንደ ዓይናለም ያ ተጫዎች፣ መሪ፣ የፓለቲካ አራማጅ፣ የሃይማኖች ሰባኪ፣ የለውጥ አርበኛ፣ ኢንቨስተር፣የመንግሥት ሠራተኛ፣ አባወራና እማወራ …..ወዘተ ነው የሚያስፈልጋት የግል ክብር ማድመቂያ ማለያችንን አውልቀን፣ የሥልጣን ዘመናችንን በቃ ብለን፣ ከተቆናጠጥነው መድረክ ወርደን ማይኩን ለሌላ በማቀበል ከአኔ ወንድሜ/እህቴ ይሻላል ትሻላለች፣ ከዚህኛው የፓሊተካ ፖርቲ ይኸኛው ይልቃል ከዚህኛው ያኛው ይሻላል እርሱ ስልጣኑን ይረከብ እኛ ደግሞ በመደገፍ አብረን እንስራ ልንል ይገባል፡፡ የህዝብን ድጋፍ ሳይዙ ሥልጣን ለመቆናጠጥ መጣር፣ በራስ መተማመንን ሣይዙ ለሥልጣን መደናበር በቃ ህዝቡን የልማት ሠራዊቱን በተለያዩ ነገሮች ማደናቀፍና ማሸማቀቅ ጣልቃ ገብነት ይቁም እንደ ሠውነት ቢሻው ራስን ዝቅ በማድረግ እናንተ በፍቅር አድርጉት ከእኔ አናንት ትሻላላችሁና፣ ጉዳዩ የጋራችን ነውና በማለት ድሉን በፍቅር የሚያደምቅ መር፣ ባለሥልጣን፣ የሥራ ኃዥለፊ፣ የቡድን መሪ ያሻናል፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያን በጦርነት በአንባገነንነት እኔ ብቻ አውቅለተለሁ በሚል መንፈስ መምራት ሊያከትም  በፍቅርና በህብረት የምንመራበት የምናስተዳድርበት ሰዓት ነው ይህን የሚደግፍ ማልያውን አውልቆ ለሚሻለው ብቁ ለሆነው  ይስጥ፡፡
ጆሮ ያለው ይስማ ልብ ያለው ልብ  ይበል ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!፡፡

ቅዳሜ 13 ኦክቶበር 2012

ፍቅር በFace book ክፍል ሁለት


በክፍል አንድ “ፍቅር በFace book” በሚለው እውነተኛ ታሪክ ላይ መሰረት ያደረገ ክፍል ማቅረባችንን ሳሙኤል በFace book ላይ የተዋወቃትንና ሳይስቡት ፍቅር ውስጥ ገብተው በኃላም ሕይወትን የመጀመር አዝማሚያ አሳይተው ከትውልድ ቀዬው ከአዲስ አበባ ተነስቶ የፍቅረኛው ልታገኘው እንደልፈልገች እንዳፌዘችበት፣ ደግሞ የህይወቱን ቁስል እንዳደማችበት ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በብዙ ልመና ሆስፒታል በር ላይ ሰላም ብሏት እንዳተመለሰና ተስፋ ቆርጦ እንደነበር ተመልክተናል ቀጣዩ የሳሙኤል ገጠመኝ ምን ይመስላል? አብረን የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡

        ‹‹ሴት ልጅን ያመነ ጉም የዘገነ አንድ ነው›› ስልህ እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ አይደለም ወይንም ለሴቶች ጥላቻ ኖሮኝ በዚህ ተነስቼ አይደለም ወይንም ለሴቶች ጥላቻ ኖሮን በዚህ መንገድ ለመግለጽ ፈልጌ አይደለም ከሴቶች ተሽዬ ለመገኘት የጥላቻ ሰው ሳይሆን የፍቅር ሰው ሆኜ መገኘት እንዳለብኝ ከልቤ አምናለሁ ይህንን ስልህ የተቀደሱ ንዑዳን ክቡራን ናቸውና ፍቅር ይገባቸዋል እያልኩህ አይደለም፡፡ ይገርምሃል ከረጅም አመታት በፊት ለሴቶች ልዩ ክብርና ፍቅር ….ነበረኝ አሁንም ቢሆን ተረቶች ሁሉ ከብዙ ሰው ጋር ያጋጩን ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር በራስህ እስካልደረሰ በስተቀር ስሜቱ አይገባህም ቁስሉ አይጠዘጥዝህም … አሁን ለአንተ የምነግርህን ነገር ለአስር ሰው ባወራላቸው በእርግጠኝነት ሁሉመን ‹‹የአንተ በምን ይለያል በሰው ከደረሰው የተለየ ምን ደረሰብህ? ይኼ ደግሞ ሰው ሆነህ ስትኖር የሚያጋጥም ነገር ነው ….›› እያሉ እንደሚያረክሱብኝ ይገባኛል፤ እኔኮ ከህመሜ ፈውሱን ተበድያለሁና ካሳ ክፈሉኝ ወይም ፍረዱልኝ እያልኩ አይደለም ቢያንስ ጭንቀቴን ስሙኝ ነው እያልኩ ያለሁት እግዚአብሔር ከዚህ ይሰውርህና አንተ ግን እየሰማኸኝ ውስጤን ተንፍሼልሃለሁ አንተም ልብ ብልህ ትማርበታልህ ከበተራታህም ሎሎችን ታስተምርበታለህ፡፡

        ‹‹ምን ሆኖ ነው ገና ለገና ያፈቀርኳት ልጅ ላገኝህ አልፈልግም ስላለች ወይም ስለጠላችው ወይም ስለከዳችው እንደዚህ የሚሆነው?›› ትል ይሆናል በለኝ ግዴለም እኔ ግን ያጋጠሙኝን ገጠመኞች ላጫውትህ ገና አሥራ ስምንት አመት ሳይሞላኝ አንዲት የሶስት ልጆች እናት ትዳሯን እስከ ልጆቿ በትና ጎረምሳ ተከተትላ ስትሄድና ለአስታራቂ ሽማግሌ ስታስቸግር አውቃለሁ እንዲሁ ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ፍቅሯን አጣጥማ ሳትጨርስ አንድ ልጅ ወዳው በፍቅር ላይ ፍቅር እያስጨነቃቸው ጮቤ እየረገጡ ሳለ ምንም ሳይጎድልባት ጨዋ ቤተሰብ አሳድጓት የተማረ ሁሉ የሞላው ይህ ጉደለው የማይባል ከልቧ የምታፈቅረውን አግብታ ከሌላ ወንድ ጋር ተኝታ ተያዘች ባልም ፍቅርን እንደሻማ ያልብሳችሁ ብሎ መርቆ ፈታት በተከበረበት አገር አንገቱን አስደፋችሁ ገና ለጋ ፍቅሩን ቀነጠሰችበት የጋለውን ሥሜቱን ቀዝቃዛ ውሃ ደፋችበት ሌላናዋ ደግሞ እንዲሁ ከት/ት ቤት ጀምሮ ፍቅረኛዋ የነበረውን አገር ምድሩ እንደባልና ሚስት ሲመለከታቸው በነበረበት በትውልድ አገራቸው በክብር በስነ ሥርዓት ተጋብተው ልጅ ለመውለድ አርግዛ ሳለች ይጋጫሉ እርሱም ከርቀት ከሚሰራበት ቦታ ይቅርታ ለመጠየቅ ለዕርቅ ደከመኝ ሰለቸን ሳይል ይመጣል ይታረቃሉ ይሄዳል ደግመው ይጣላሉ ደግሞ ይመጣል ይሄዳል ተሰቃየ ጉልበቱ በመንገድ አለቀ ግን ምንም ለውጥ የላትም ከትዳር በኋላ ፍቅራቸው ያልተዳፈነ እሳት ሆነ ቢጭሩት የማይቀጣጠል በስተመጨረሻ በፍርድ ቤት ከሰሰችሁ በመሃል ልጅም ተወለደ የፍቺ ደብዳቤም ደረሰው ፍርድ ቤት ጊዜ ሰጣቸው ልጁንም እያሳደገ ተቆራጭ እያደረገ ፍቅሩን ደጅ እየጠና ቆየ ያሰበው ግን አልተሳካም ተፋቱ ልጄን ልውሰድና ላሳድግ ብሎ ሲጠይቅ ያንተ አይደለም ተባለ እናስ የማነው ተብሎ ሲጠየቅ የሁለቱም ጓደኛ የነበረ ቤተኛ የሆነ ይህን ያደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ በጫጉላቸው ጊዜ እንኳን እንደ ወንድም እንደ ወዳጅ አብሮ ሲጫወት አብሮ ሲበላ ሲጠጣ እያደረ እየሰነበተ ትዳርን ያላመደ ባልንጃራቸው ልጅ እንዳሆነ መጨረሻም ፊርማቸውን እንኳን ሳይቀዱ አብራው መኖር ጀመረች ባለቤት ተብዬ ጓደኛዬም ልቡ ተሰበረ ሥሜቱ ተነካ ክብሩን ተነካ ይኼ የምንግርህ ጥቂቱ ነው ምናልባት አዲስ ነገር ነው ወይ? ወንዱስ ቢሆን? ልትለኝ ትችላለህ፤ ወደ እኔ እንምጣ ደግሞ የልጅነት ፍቅረኛዬ ሠንቄ ከነበረው ከሕይወት ዓላማዬ አደናቅፋ የፍቅርን ፊደል አስቆጥራ የፍቅርን ጽዋ አስጎንጭታን እያጣጣምኩት እያለሁ ልትለየኝ ልትጠላኝ ምላ ተገዝታ ያጋጠማትን የአሜሪካ ኑሮ ዕድል ተጠቅማ ከሄደች በኋላ ከወራት በኋላ የውሃ ሽታ የሆነችብኝ ምን ባደረኳት ነው? ቃሏን ለምን አጠፈች? እኔኮ የዶላር ችግር የለብኝም የፍቅር እንጂ፣ እኔኮ አሜሪካ እንድታኖረኝ አይደለም ህልሜ በልቧ እንድታኖረኝ በልቤ እንድትነግስ እንጂ ፡፡ ዛሬ ደግሞ ፍቅርን እንደምፈራ እየነገርኳት ህመም አለብኝ ቁስሌ እንዳያገረሽብኝ እያልኳት ከተማፅኖ ጭምር እያፈቀርኳት እንዲህ ማድረግ ምን ይሉታል? ምን በደልኳት? ታዲያ ‹‹ሴት ያመነ ብል ይፈረድብኛል? እስኪ ፍረደኝ! በል እስቲ ህሊናህ ያለህን ፍርድ በይንብኝ በል እባክህ ጥፋቱ ያንተ ነው ብለህ ጥፋቴን ቦታውን ጠቁመኝ እያለ ሲቃ እየተናነቀው ራሱን መቆጣጠር አቅቶት ድምጹ ሌሎችን እስኪረብሽ ድረስ ከፍ በማድረግ ትናንት ያገኘሁት ሣይሆን የጥንት ጓደኛው ያህል ስሜቱን መቆጣጠር እስኪሳነው ህመሙን ጭንቀቱን ተነፈሰልኝ፡፡

        ይኸውልህ ደረሰ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስብው የርሷ የባህሪ ለወጥ የጀመረው አንድ ቀን ድንገት ይሁን አስባበት አላውቅም ‹‹ታገባኛለህ? አለችኝ እውነቴን ለመናገር እርሷን ማግባት የኔ ሥራ እንጂ የርሷ ጭንቀት አልነበረም ምክንያቱም ወድጃታለሁና፡፡ ነገር ግን መዋሸት አልፈልግምና ሁሉን ነገር ዘርዝሬ ነገርኳት ደሞዜ ስንት እንደሆነ ከዚያ ላይ የተጣራ የሚደርሰኝን ለቤተሰብ የቤት ወጪ ሥንት እንደምሰጥ የዓባይ  ግድብ የቦንድ ግዢ……. ተቆራርጦ ሥንት እንደሚቀረኝ ነገርኳት ከተወሰነ ወራት በኋላ የዓባይም እንደሚያልቅ ነገሮችም ሲስተካከል እንደምንነጋገር ሆኖም  ግን የኔና የርሷ መጨረሻ አብሮ በትዳር እንደሆነና ዛሬ ግን ልዋሻት እንደማልፈልግ አጉል ቃል እንደማልገባ ነገሮችን አስተካክዬ እኔ ራሴ ልታገባኝ እንደምትፈልግ እንደምጠይቃት ነገርኳት የተወሰነ ቅሬታ አነበብኩባት ከኔ ጭንቀትና እውነት ውሸትና ቅሬታ ሽንገላ በሥሜት ‹‹አዎ አገባሻለሁ›› እንድላት ፈለገች ይሁን እንጂ የከፋ ነገር በመካከላችን አልነበረው የሆዷን እግዜር ይወቀው እንጂ እንዲያውም ብር ልላክልህ ትለኝ ሁሉ ነበር፡፡

        የኔ ፍቅር ከቀን ወደቀን እየጨመረ ሲመጣ በመካከላችንም የነበረው እንቅፋት የፍቅር ችግር ሳይሆን በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል ስለነበር ወደያው አንድ ነገር ወሰንኩ ስራ ማፈላለግና የተሻለ ደመወዝ ተከፋይ መሆን እንዳለብኝ ምክንያቱም ጥሩ የስራ ልምደና የት/ት ደረጃ አለኝና የሚገርመው በወራት ውስጥ የምፈልገውን ሥራ ከእጥፍ በላይ በሆነ ወርኃዊ ደመወዝ ተቀጠርኩ ወደ ድሬደዋ የፍቅር አገር የመጣሁት ስራ ከመጀመሬ በፊት ይህንን የምስራች ለፍቅሬ ልነግራት ታገቢኛለሽ ወይ ብዬም የትዳር ጥያቄ ላቀርብላት፣ እመጣለሁ ብዬ ቃል የገባሁትንም ቃልኪዳኔን ለመፈጸም ለድርብ ድርብርብ ደስታ ነበር ጉዞዬ ከአ.አበባ ድሬደዋ ነገር ግን በድሬደዋ ሙቀት ውስ ፍቅራችን ለፍሬ እንደ ደረሰ ሰብል ታጭዶ ተወቅቶ ወደ ጎተራ ሳይገባ ውርጭ መታውና ልቤን ደግሞ የፍቅር ጦር አደማው ላይሻለኝ ላይጠገን ልቤ ተሰበረ ‹‹ ጉም ጨበጥኩልህ ሥቅሥቅ  ብሎ አለቀሰ፡፡ ግራ መጋባት በሚታይብኝ ሁኔታ ‹‹አይዞህ›› እያልኩ ለማጽናናት እንዳያለቅስም ‹‹አታልቅስ›› በማለት አባበልኩት፡፡

        ደረሰ ተወኝ እባክህ ለምን አላላቅስ ለምንስ አላነባ ምን ቀረኝ ፣ጌታዬኮ አብሬያት እንድኖር ከግራ ጎኔ አጥንት ከፍሎ የሰጠኝ ሴትን ነው፡ ታዲያ ሴቶች እንዲዘህ እንደጉም አልጨበጥ ካሉ  ወንድ ላግባ እንዴ?! ምን ለማለት ነው አታልቅስ የምትለኝ እያፅናናኽኝ እያበረታኸኝ ነው? ወይስ በቁስሌ  ላይ እንጨት እየቆሰቆስክበት ነው?

        እምባ ተናነቀኝ የወንድ ልጅ ሐዘን እና ጉዳት አሳዘነኝ እኔም የራሱን ጥያቄ መልሼ ራሴን ግን ለምን? አልኩት፤ታዲያ አሁን ምን እያደረክ ነው? በማት በጥያቄ መልክ ጨዋታ ለመቀየር ሞከርኩ ከሐዘኑ የማስወጣበትን መንገድ እየፈለኩ፡፡

        ‹‹አሁን ምን አደርጋለሁ እቅዴን ምኞቴን ተስፋዬን ውሃ ባለው መነሻዬን ራስ ሆቴል አድርጌ ዳቻቱ ሰፈር፣ መጋላ፣ ኮኔል ድልድይ፣ ከዚራ፣ ለገሃር፣ ሃምበር ዋን፣ ሃራር መውጫ፣ ታይዋን፣ ሳቢያን፣...ወዘተ እያልኩ ላይ ታች ሥል ውዬ ዛሬ ደግሞ ራስ ሆቴል አርፋለሁ፤ የከፋው (ግራ የገባው) ቱሪስቱ ታውቃለህ እንደዚያ ሆኛለሁ፡፡

        አይዞህ ታሪክ ይቀየራል ራስህን አትጉዳ በትዕግስት ነገሮችን በሙሉ መርምራቸው ደግ ሴቶች በሙሉ አንድ አይደለሙ ወላድ በድባብ ትሂድ እዛው አዲስ አበባ የአገርህን ልጅ ታፈቅራለህ አይዞህ!

        “ምን አልክ ፍቅር?! ፍቅር እንደገና ! ሴት ልጅን እንደገና ላምናት? ይገርምሃል አንድ ጓደኛዬ በሆነ ወቅት ስለ ሴት ልጅ ያለውን መጥፎ አመለካከት ተመልክቼ እንዲራራ መልካም አመለካከት እንዲኖረው ብዙ ጥረት አደርግ ነበርና ስለሴት እናትነት፡ እህትነት፡ሚስትነት፡ ወዘተ እያነሳሁ ብዙ ብዙ ነገር እለው ነበር ዛሬም አንተ ለምን እንደዚህ እንደምትለኝ ይገባኛል፡፡ አዎ የምትለውን በሙሉ ነች አምናለሁ ነገር ግን ያ! ጓደኛዬ እንዳለኝ ሴቶች የሚመቻቸው ከርህራሄ ይል ጭካኔ፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከመግባባት ይልቅ ፀብና ክርክር፣ አብሮ ከመኖር መለያየት ይመቻቸዋል።ይኸም የመጣዉ ከጥቅም ፈላጊነታቸውና ራሳቸውን አብዝተው ከመውደዳቸው የሚመነጭ ይመስለኛል። ዛሬ ዛሬ እንደውም ከወንድ በተቃራኒ በሆኑ ቁጥር የሚወደዱና የሚፈለጉ እየመሰላቸው ሲሞላቀቁ ይታያል፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም በተቃራኒው ነው ስለዚህ አያስፈልጉኝም፡፡››

        ‹‹እስኪ የመለያየታችሁ፡ ይቅርታ የመቀያየማችሁ ዓብይ ጉዳይ ምንድን ነው ብለህ ታስባለህ?

        ‹‹ግልፅ ነውኮ ያኔ ነገሮች ባልተስተካከሉበት ወቅት ለርሷ ወቅታዊ ላልሆነ አጣዳፊ ጥያቄ አገባሻለሁ የሚል የውሸት ተስፋ ስላልሰጠኋት ነው፤ እስኪ ተመልከታት ይህቺን ሴት እኔ ያኔ ብዋሻት ዛሬ ድረስ ከኔ ጋር ነች፡ አሁን ሥመጣ በደስታ ትቀበለኛለች አዲስ አበባም ትመጣ ነበር ያፈለገንንም ነገር እናደርጋለን ደግሞ ስለ መጋባት አናነሳም በቃ! ምናልባት ‹ቆይተን መቼ ነው ታዲያ የሰርጋችን ቀን?› ትለኝ ይሆናል፡፡››

        እሷም ጥያቄዋ ስህተት ያለበት አይመስለኝም እውነትዋን ነው የማታገባት ከሆነ ለምን ጊዜዋን ታባክናለች?

        ‹‹እኔስ ምንድን ነኝ ዝም ብዬ ጊዜዬን የማባክነው የወንድ ልጅ ዕድሜ እና የዕባብ ዕድሜ አንድ ነው ያለው ማን ነው? የኛም ዕድሜ ይሄዳልኮ እንደ ሴቶቹ ባይሆንም፤ እኔ ደግሞ ራሴን እፈልገዋለሁ ዝም ብዬ አልንዘላዘልም፡፡ የማላገባትን የእኔ ያልሆነችዋን ሴት አልፈልጋትም ወንድ አዳሪ አይደለሁምኮ፡፡

ቀጣይ ጊዜህን ታድያ እንዴት ታሳልፋለህ ያለሴት መኖር ይከብዳል፡ ለምን አላስታርቃችሁም?

አመስግናልሁ፡ግን አሁን የማሰቢያ ጊዜ ነዉ የምፈልገዉ ዳግም የምሳሳትበት ጊዜ አልፈልግም፡፡…ለወንዱም ለሴቱም መልካም ዘመን እና ጣፋጭ የፍቅር ጊዜ እመኝላቸዋለሁ። እነሆ ላንተም መልካም መዝናኛ፡፡

አሜን ብዬ ምርቃት ከተቀበልኩ በሁላ ይጠቅም ይሄናል በማለት እንዲህ አስፍራለሁ፡፡

(ገጠመን የምትሉትን ፍቅር በfacebook ላኩልኝ እኔም እንዲህ ለሰፊዉ ህዝብ ጥቅም በምስጢር አቀርበዋለሁ።)

ክፍል 3 በእኛዉ ገጠመኝ እና ታሪክ ፈጣሪ ካደረሰን እናንተም ከላካችሁልኝ እንገናኛለን፡ቸር ይግጠመን።

ማክሰኞ 9 ኦክቶበር 2012

ቅዱሣት መካናት በፎቶግራፍ

  ቁልቢ ገብርኤል
                                                                        ሀረር መድኃኒዓለም
አዲስዓለም ማርያም
 

ቅዳሜ 29 ሴፕቴምበር 2012

መልካም በዓል


በመላዉ ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያን እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ  በሰላም አደረሳችሁ፡፡በጦማሩ ላይ ስለ ጦማሪው ያላችሁን አስተያየት በ e-mail:-lovelydere@gmail.com መላክ ወይም በፖስታ ቁጥር 25476 አዲስ አበባ ደረሰ ረታ በማለት መላክ ይቻላል፡፡አመሰግናለሁ፡፡ለተጨማሪ ንባብ
www.deressereta.blogspot.com ይጠቀሙ፡፡


ዓርብ 28 ሴፕቴምበር 2012

“የምናብ ለውጥ”


ይሕ ፅሑፍ ጳጉሜ 3/2004 ዓ.ም. የተጻፈ በመሆኑ የተፈጠሩ ስሕተቶች ግምት ዉስጥ ይግባልኝ!
የምናብ ለውጥ
ክቡር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ በተጠባባቂነት  የሚሰሩበትን የጠቅላይ  ሚኒስተርነት በትረ ሥልጣን በቃለ መሐላ ሙሉ በሙሉ ሲረከቡ ያደርጉታል ተብሎ ከሚጠበቀው ንግግር መካከል አንዱ፡-
ክቡር የኢፌዴሪ መንግሥት ኘሬዜዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ክቡር የኤፌዴሪ መንግሥት የተወካዮች ምከር ቤት አፈ ጉባኤ  አቶ አባዱላ ገመዳ ክቡራት ሚኒስተሮችና አምባሰደሮች እንዲሁም የተወካዮች  ምክር ቤት አባላት ክቡራን  ጥሪ የተደረገላችሁ የውጭ አገር አምባሳደሮች ኮር ዲኘሎማቶች የሐይማኖት   መሪዎች የአገር ሽማግሌዎች የተቃዎሚ ፓርቲ  ተወካዮች ከሁሉም በላይ እጅግ የማከብርህና  የምወድህ  ልታዘዝህና ላገለግልህ በዛሬዋ ዕለት በቃለ መሐላ አረጋግጨ በትረ ሥልጣኑን የተረከብኩህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፡፡
በየአላችሁበት  የእግዜአብሔር ሠላም ይብዛላችሁ፡ ጌታ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና እኛ  ህዝቦቿን ይባርከን!

Yes We Can Change!
Yes we can!
Yes we need change !

“ የኢትዮጵያ ህዝብ  ሆይ አዎ መለወጥ እንችላለን! መለወጥ ያስፈልገናል፡፡”
 የተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ለብዙ ዘመን ለረጅም  ወራት ሥትረገጥ ሥትጨቆን  ብትኖርም ኢህአዴግ የድልን ካባ ከተጐናፀፈ ማግሥት ሥትናፍቅ  የኖረከውን ያንን ነፃነት፣ ዕድገት ፣ ብልፅግና  ሰላም……..ለማምጣት ድፍን  ሁለት ዓሥርት ዓመታት  አልፈውታል፡፡  ይህንንም ግሥጋሴ በፅናትና በትጋት ሲመሩት የነበሩት  ክቡር ጠቅላይ  ሚንስትራችንን በሞት ቢለዩንም ይኸውና ዛሬ በህይወት ዘመናቸው የቀረፁኝ የመንፈስ ልጃቸው ተተክቼ በትረ ሥልጣኑን ተረክቤአለሁ ፣ ቃል የምገባልህ የተጀመረውን ማስቀጠል  እንደምንችልና ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ነው፡፡
     ክብራትና ክቡራን ሚኒሰተሮች፣ የፓርላማ አባላት  በየደረጃችሁ  የመንግሥት ባለሥልጣናት  ጥያቄ አለን የመለወጥ ዓላማ አለን ወይስ ዓላማችን ምንድን  ነው  መለወጥ መለወጥ  ሥላችሁ /አንዴ ለ ን አጥብቃችሁ እንዴ አላልታችሁ  ይሁንልኝ/ መቀየር /ማሳደግ/ ቀ ን አጥብቋት መቀየር /ማደግ/ / ቀ ን ላላ አድርጓት /ያለብን ይመስልኛል ይመስለኛል አይሰራም  መቀየር ወይም መቀየር አለብን፡፡
ዓለማችን መለወጥ ማስተካከል ወይም ማስተካከለ ካልሆነ  የእኔ  የለውጥ ሂደት በእናንተ የመለወጥና/ የመለወጥ አስተሳሰብ ካልታጀበ የእኔ  ዕቅድ የእናንተም የጋራችን ካልሆነ  የእኔ የለውጥ ሂደት ጎምዛዛ እና ደብዛዛ  ይሆናል፡፡ ለዘመናት  የእኛን ለውጥ ሲጠብቅ የኖረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ መና ይሆናል የእኛም ዕጣ ፈንታ በታሪክ ተወቃሾች መሆን ነው፡፡
ክብራት ሚንስተሮች ክቡራን የፓርላማ አባላት ለውጥን  ለማምጣት የምንችለው  ሰውን  በማምጣት ሰውን በመቀያየር ብቻ አይደለም ፓሊሲዎቻችን  አፈፃፀምቻችንንም መፈተሽና መቀየር ግድ ይላል የማንቀይረው ሰው የማንቀይረው ፓሊሲ የለም ሁሉም ይቀየራለ አስፈላጊ  ሆኖ ከተገኘ እኔም እቀየራለሁ  መንግሥታችንም ይቀየራል፡፡  የሄድንበት መንገድ ትክክል አይደለም አያዋጣም ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃዋሚ ፓርቲዎች  ሣይቀሩ በሚያመጡት መልካም ኃሳብ ፈትሸንና አስተካክለን  እንጓዛለን ማለት አለብን፡፡
እንደ እህአዴግም የተጓዝንበት መንግድ ትክክለ ነወይ እንደ መንግሥትስ የቀየስነው ዓላማ ጠንካራ ነው አፈፃፀማችንስ እንዴት ነው ብለን ራሳችንን እስከ ታችኛይቱ የቀበሌ እና የጎጥ ጽ/ቤት ድረስ ልንፈትሽ አገራዊና ህብረተሰበአዊ ግዴታችን ነው ደካማ ጐናችንን ማመኑ ጥፋታችንን መረዳቱ የለውጥ ሂደታችን አንዱ አካል ነውና፡፡ ግትርንት አይሰራመ ለአገራችን ለኢትዮጵያ  እኔ ብቻ አውቅለታለሁ የምንልበት ዘመን አብቅቷል የበረሃ  ታጋይነት ብቻ በቂ አይደለም ከፈቃደ ሥጋችንና ከያዝነው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ሥልጣናችን  ጋር ልንታገል ግድ ነው፡፡
የማከብራችሁ የመንግሥት  ባለሥልጣናትና የምወዳችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆይ እኔ ዛሬ ከፊታችሁ ቆ ሜ ቃለ መሐላ የፈፀምኩር ኩራት አይደለም የሚሰማኝ ሥጋት እንጂ ይህን ሥጋቴን ዳግመ ወደኩራት መለወጥ የምችለው ከፊታችን ባስቀመጥንው ሶስት ዓመታት ውስጥ በሥራ እና በለውጥ ነውና እናንተን ከእኔ ጋር በመሆን አብረን ከእርሱ ጋር እየሠራን እንየው እንለወጥ ልትሉ ይገባል፡፡
መንግሥት መሥርተን በጋራ የምንሠራ በተለያየ የድርጅት አባልነት ያለን አለን በአጋር ድርጅትም ታቅፍችሁ ያላችሁ ሳስገነዘባችሁ የምፈልገው አንድ ጥብቅ ጉዳይ አለ፡፡  ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚናገሩትን ከእንግዲህ ልንሠማ ቦታም ልንሠጣቸው ግድ ይለናል ልንለውጣት ለቆምንላት አገራችን ኢትዮጵያ  እንርሱም እንደዜጋም ይሁን እንደተቃዋሚ የለው  አጋሮቸችን  ቻውና፡፡ ወሀትመ ለአገር ለውጥና እድገት ለሠዎች ልጆች ሠላምና እኩልነት የሚሠጕ የካበተ ልምድ  ካላቸወ ተለውጠው ከመጡ የደርግ ባለሥልጣናት ሣይቀር  በህይት ካሉ በንጉውም ዘመን ያሉ ካሉ እንቀበላለን”፡ ያቋቋምነው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ምህደሩ እዚህ ድረስ ሠፈና ጥልቅ ነው፡፡
የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት ባለፋት የሁለት ዓመት የዚህ የምክር ቤት የሥራ ዘመናችን የኢትዮጵያ  ህዝብ እና ሚዲያዎች በሥራችን ላይ ምስጋና ነው ወይስ ወቀሳ ነው የሚያቀርቡት ክስ ነው ወይስ እርካታ ነው ያላቸው ምንድን ነው እየተሰማ ያለው ሰማንያ ሚሊዮን የኢትዮጵያን ህዝብ እንደመወከላችን መንግሥታችን ዲሞክራሲያዊ እንደ መሆኑ መጣን ምን መረጃ አለን እኛስ ምን መስራታችንን ነኁወ የምናውቀው እንደ አንደ ግለሰብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዋና የምክር ቤት አባልነቴ ምን አስተዋፅኦ አድርጌአለሁ ብለን ራሳችንን ፈትሸናል ይህ ቀን ግን ራሳችንን ቆም ብለን የምንፈትቨበት ቀን ነው፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝና የምክር ፀበት አባላት በሙሉ አንድ ግዜ ከመቀመጫችሁ ብድግ በሉልኝ አመሰግናለሁ በዚያው እስኪ  እጃችሁን ወደ ኪሶቻችሁና ወደ ገንዘብ ቦርሳችሁ ከታችሁ
ተመልከቷቸው /ጠቅላይ ሚኒስትሩም እጃቸውን ወደ ኪሳቸወ ከተቱ የገንዘብ በርሳቸውንም  ፈተሹ የማን ገንዘብ ነው ኪሶቻችን ውስጥ ያሉት  መልስልኝ ጉርምርምታ ነገሰ በአዳራሹ  ጓዳች  ፀጠታ መልሰን እኔ እመለሰዋለሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የኢትዮጵያ  ሃብት ነው ለመሆነ ምን ያህል ሰርተን ነው ይህን ያህል የተከፈለን የፀዳ የላባችን ውጤት ብቻ ነው ኪሳችን ውስጥ ያለው በየግለ ሥማችን የተፃፋ የገንዘብ ማዘዥ ቼኮች የሉም በኪሳችንና በቤታችን  ጐበዝ በቃ አካሄዳችንን እንገምግም ችግር ካለብን በቃኝ ተነቅቶብኛል የጀመርኩር መንገድ አያስቀጠልኝም በማለት የለውጡን ጉዳና  ለመቀላቀል የኢትዮጵያ  ህዝብ ይቅርታ እንጠይቅ በአገሪቷ ላይም እርቀ ሰላም እናውርድ፡፡
ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የፓለቲካ ድርጅቶች የሃይማኖት ተቋማት፣………ወዘተ ሁላችሁመ አንድ የጥሪ መልዕክት አለን እንደማመጥ መስማት ወይመ ማዳመጥ ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ አንድ ነውና፡፡መደማመጥ ለመንግሥታችን ፋይዳው  ከዚህ በላይ ነው ለለውጥ የተነሳ ትውልድ አዳማጭ ካጣ ልፋቱ  በጠቅላላ ዋጋ ቢስ ይሆናል ስለዚህ ለዚህ ለውጥ  መሳካት መዳመጥም ሆነ ማዳመጥ ትልቁን  ሥፍራ ይይዛልና እንደማመጥ  ሰዎች በየእመነታቸው ወደ ፈጠረን በፀሎት የምንጨኸው የፈጠርን ይሰማናል ያዳምጠናል መልስም ይሰጠናል ያሰብነውን ያለምነውን ያቀድነውን ያሳካልናል ብለንኮ ነዉ ታዲያ ትልቅ ራዕይ ሰንቀን ረጅሙን ጐዳና ከፈታችን አስቀምጠን ሳንደማመጥ እንዴት ይሆናል፡፡
ምንም እንኳን ለውጣቸው እስከዚህም ቢሆን የድሮ ነገሥታት (መሪዎች) የህዝባቸው የልብ ትርታ ለማዳመጥ ‘’እረኛው ምን ይላል’’ እሰከ ማለት ታች ድረስ  ወረደው ያዳምጡ ነበር፡፡  ታዲያ መደማመጥ ክፉ ነገር ከሌለው ለዚያውም በመረጃ መራብ  ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት ዘመን ለምን አንደማመጥም? መዳማመጥ አለብን፡፡ አለቃ ምን ይላል? ብቻ ሣይሆን ወደታች በመውረድ ሠራተኛው፣ ህዝቡ፣ ደጋፊው፣ ተቃዎሚው ምን ይላል? ማለት ይገባል፡፡ ህዝቡ ዝም ካለ አደጋ ላይ ነንና ባለፋት ሥርዓት እንዲሁም በኛም  ዘመን የሚናገሩ ብዙዎች  የሚያዳምጡ ጥቂቶች በመሆኑ መፍትሔ እና   ለውጥ ሣይመጣ ቀርቷል፡ ዛሬ ግን ያ ዘመን  ይብቃ! መስማት (ማዳመጥ) የመፍትሔው ዋነኛ ቁልፍ ነውና የተከበራችሁ ሚኒስተሮች ማዳመጥ ከማይችሉ መሪዎች ጋር የሠራ ሠራተኛ የመደማመጥን ባህል ማዳበር አይችልምና መደማመጥን ባህላችን  እናድርግ ብዙ ሥናዳምጥ ብዙ መረጃ  ይኖረናልና፡፡
     የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ይብዛም ይነስም ይህቺን አገር በድለናታል፣ ተበዳይ ደግሞ ካሣ  ያስፈልገዋልና ይህ ጊዜ ምንም አጭር ቢሆንም ባለን አጭር ጊዜ  አገራችንንና ህዝባችንን  የምንክስበት እንጂ የምንከስበት ሰዓት ላይ አይደለም ያለነው ምን ያህል ነው ያጠፋሁት ሣይሆን  ጥፋቱ መኖሩን ማመን የጥፋቱ ምክንያት እኛው መሆናችንን ማመን በራሱ አንድ የለውጥ መጀመሪያ ነው ሌላው ዓብይ ጉዳይ የሚያጠፋትን ሠዎች ለመቅጣት ሥንል የምንዘረጋቸው መንግዶች በአገራችን ላይ ቂም እና በቀልን እንዳያሠፍኑ የተቀጣው ሠው ተምሮ ወደ ማኀበረሰቡ ተቀላቅሎ  ልማትን እና የዕድገቱን ለውጥ የሚያፈጥንበትን መንገድ ልንቀይስ   ይገባል፡፡ በዘመናችን ሠዎች የሚቀጡበት የእስር ቤት ግንባታዎችን ከማስፋፋትና የሌለንን የሠው ኃይል ለዓመታት  በአንድ ቦታ  ያለ ጥቅም ከማዋል  አስቀድመን ሠዎችን ከጥፋት ማራቁ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው ስለዚህ በዚህ የሶስት ዓመት የሥራ ዘመናችን እንዚህ እስር ቤቶች  የልማት ሀይሎች መፍለቂያ ማድረግ አንዱና ዋነኛ ሥራችን ይሆናል ሌላው አገራችን በፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች ብቻ የምትመራ ሣትሆን በፍቅር በዕድገት እና  በለውጥ ጐዳና የምንመራት ኢትዮጵያ መሆን አለባት፡፡
     ወገኔ የኢትዮጵያ  ህዝብ ሆይ ተከፋፍሎና ተቃቅሮ መኖር ከዚህ ቀደም በቅርበት ያየናቸው የአፍሪካ ህዝቦች ታሪክ  ብዙ ነገር ያስተምረናል ብዬ አስባለሁ የተደረጉት ክፋ ድርጊትና ብቀላዎች  አህጉሪቷን ለልማት  አላነሳሳትም ከጥፋትና  ከረኃብ፣ ከበሽታና ፣ ከእርሰ ብርስ  ጦርነትና ኃላቀርንት፣ ከትውልድ እልቂትና ከመበታተን / ከስደት/ አልታደጋትምና ከዚህ ክፋ  አጋጣሚዎች የመለያየትንና የክፋትን ነገር ልንማርበት ይገባል፡፡ ከቂም እና ከበቀል ይልቅ  ታሪካችንን በዕርቅ የምንቀይር ታሪክ ሠሪዎች  እንሁን፡፡  ትናንት  የተሠራውን ጥፋት እና መጥፎ ታሪክ እየዘረዘርን  የአጥፊውን ወገን በክፋ ዓይን ማየት ይቅር መካሰስ የትኛውን አገር ገነባ? የየትኛውን አገር ኢኮኖሚ  አሳደገ?
     ትናንትናን  መለወጥ ባይቻል ከትናንት መማር ግን ይቻላል  አይደል የሚባለው ከተስማማንና በግልጽ ከተነጋገርን በአንድነት እና  በቁርጠኝነት ለእምዬ ኢትዮጵያና ህዝቧ ለህዝቧ ታሪክ ለመሥራት ዝግጁ ከሆንን   ነገሮችን ሁሉ እንደምንፈልገው ማድረግ እንችላለን ታሪክ ለመቀየር ክፋ ነገሮችን  ወደ በጐ ለመገልበጥ የተነሳን ከሆንን ህዝባችንና የኢትዮጵያ  አምላክ እግዚአብሔር ከጐናችን ሆኖ  ብርታትና ሞገስ ይሆነናል፡፡  በትናንት መጥፎ ታሪካችን  ላይ  ሥንጣላ ሥንጨቃጨቅ ጥሩው ቀን ዛሬ ግን እንዳያልፍብን ጥሬዬን አቀርባለሁ፡፡
      ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝቦችን  ብሔር  ብሔረሰቦች ዛሬ የምንተራረምበትና  ጥሩ ሥራ ለመሥራት  የምንመካከርበት ቆርጠን የምንነሳበትና ቃል  የምንገባበት የለውጥ ብሥራት ዕለታችን ናት ፣ ከመላው የእትዮጵያ ህዝቦች ብሔር ብሔረሰቦች ልቡና ልትጠፋ  የማትችል ተከባብረንና ተዋደን  ልንኖርበት ቃል የምንገባበት  የደስታ ቀን ናት ተራርመን ጥሩ ሥራ መሥራት የማንችል ዜጐች ካልሆንን  እንደ ህዝብ ብዛታችን እና ብዙ  የብሔር ብሔረሰብ ሥብጥር ውጤት እንደመሆናችንን  መጠን ትናንት የነበሩት  ካጠፋት፣ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ላይ ከጠፋው ጥፋትና ከደረሰው  ውድቀት  የከፋ  ነገር ያጋጥመናል የበለጠ ነገርም ልናጠፋ እንችላለን፡፡ በውኑ የትናንትናዎቹን በምንወቅሳቸው ሚዛን ብንመዘን እኛ  ምን የተሻለ  ሥራ  ሠርተናል እነርሱን ያጋጣማቸው ነገሮች ቢያጋጥሙን እነርሱ ካጠፋት የተሻለ  ሥራ እንደምንሠራ ምን ማረጋገጫ አለን በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ሥናጠፋ ታግሶን ስናለማ አጋራችን በመሆን ከጐናችን ላልተለየ ህዝባችን ምስጋናዬና አክብሮቴ ላቅ ያለ ነው፡፡
    በመጨረሻም የተከበሩ የኢፌዴሪ ኘሬዘዳንት፣ የተከበሩ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ እና የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላትና የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ባለፋት ሁለት ዓመታት የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች ማስቀጠል  እንዳለብንና ሌሎችንም ሥራዎች ማቀድና መተግበር እንዳለብን ላሳስብ እወዳለሁ፡፡  ይልቁንም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከዳር ማድረስ እንዳለብን በአጽንኦት  አሳስባለሁ፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እምቅ እውቀቱን ይዞ  በተለያየ አጋጣሚ ጉልበቱን ጭምር  ይዞ እንደ ዓባይ ለሌላው ዓለም ሲሳይ  የሚሆነውን ህዝባችንን ልንታደገው እንደሚገባና እንደ ወንዛችን ዓባይ ሁሉ ከአባይ ወንዝ በላይ ጥቅም ያለውን ህዝባችንን በአንድነት ልንገድበው ይገባል፡፡  የዓባይ ወንዝ በገንዘብና በጉልበት ሊገደብ  ይችላል ህብረተሰብ ግን በጉልበት አይገደብም በጥበብ እና በፍቅር እንጂ  ስለዚህ አደራ የምለው በጥበብና በፍቅር በመከባበርና በመተባበር በስደት ላይ ያለውን በመሰደድ  ላይ ያለውን እምቅ ሐብት  ህዝባችንን ለእምዬ ኢትዮጵያ እናውለው እንገድበው!!!
በእኔ በኩል የሥደት ምክንያት የሆነውን በነፃነት የመኖር መሠረታዊ  ነገሮችን፣ የሚዲያ እና የነፃ ኘሬስ ነፃነትን፣ የመንግሥትን በሀይማኖቶች ጣልቃ  ገብነት ገለልተኛ መሆንና እና ሌሎችን በራሴና ከምክር ቤቱ አባላት ጋር ታምኜ ልሰራ እና ላገለግላችሁ  እንድትሰሩ ላመቻችላችሁ ቃለ እገባለሁ ፡፡(ንግግሬን እዚህ ላይ አበቃለሁ በክብር ለህዝብ ጥቅም  ከድል በኃላ ለተሰውት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን መለስ ዜናዊ ከመቀመጫችን ተነስትን  በድጋሚ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እናድርግ፣ አመሠግናለሁ፡፡)

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !
ኢትዮጵያለዘለዓለምትኑር!
ክቡር ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለ እንን ለዚህ አበቃዎት!

 

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...