ሐሙስ 19 ጃንዋሪ 2023

እንኳን አደረሰን

 እንኳን ለጥምቀት በዓል አደረሰን።

በጥምቀት ልጅነትን የሰጠን ፥ በጥምቀት ሓጥያታችንን የደመሰሰልን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

ሐሙስ 28 ጁላይ 2022

ስኬት ምንድን ነው?

 ስኬት ምንድን ነው?

አንዳንዶች በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ብዙ ብለዋል፣ ሌሎች ደግሞ በተግባር ይህንን ይመስላል ብለው አመላክተዋል። በሁለቱም መንገድ የተገለጡትን የስኬት ፍቺ ገሚሶች ሲስማሙበት ገሚሶች ደግሞ እንደማይስማሙ ይገልጣሉ። ምን አልባት በዚህ ላይ የተጠና ጥናቶች ለማግኘት አልጣርኩም እንጂ ከሁለቱም በተቃራኒ የሆነ አይጠፋም። 


ብቻ ስለ ስኬት ብዙዎች በተለያየ ቃላት መጽሐፍ ጽፈውለታን፣ ሕዝባዊ ንግግር አድርገውበታል፣ በድምጽ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ስልጠናዎች ተሰጥተውበታል፣ ምድራችን ላይ የሚፈለፈሉት ቢዝነሶች ሁሉ ሲጀመሩ ስኬታማ እንደሚያደርጉ ተነግሮላቸው፣ ተዘምሮላቸው፣ ተጨፍሮላቸው ወዘተ ነው መጨረሻቸው ገሚሶቹ በኪሳራ እና በውድቀት ቢዘጉም። (እዚህ ጋር ትርፋማነት ስኬት ነው ወይ ብዬ ጥያቄ አንስቼ አልፋለሁ።) 


ስለስኬታማነት ወይም ስለ ስኬት ሌሎች ሁለት በትዳር የተጣመዱትን፣ የተሳሰሩትን፣የተጋመዱትን፣ ቃልኪዳን የገቡትን ሰዎች የሕይወት ጉዞ እንደ ስኬት ይቆጥሩታል። ልብ ብላችሁ ጥንዶቹ አብረው የሆኑበትን ተመልከቱልኝ የተጣመደ፣ የተሳሰረ፣ የተጋመደ እነዚህን ቃላት ስፈትሽ ነፃነት ይጎድለዋል አስጨናቂ አስገዳጅ ነገር ይታይበታል። የትዳር ዘመናቸው ምን ይመስላል? በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ መውጣት መግባታቸው ምን ይመስላል? ደስተኛ ናቸው ወይ? እነዚህን ሳንመልስ አምስት፣ አስር፣ ሃያ አምስት አመትን ብቻ ዕድሜ ስላስቆጠሩ ስኬታማ ይባላሉ?። አለመፋታት፣ አንድ ቤት መጋራት፣ በአንድ በጀት መተዳደር፣ ዕድሜ መቁጠር ብቻ ስኬታማ ያስብለናል ብዬ አሁንም በጥያቄ  ማንሳት እፈልጋለሁ። በቅንፍ ውስጥ ግን (የገባነውን ቃል ኪዳን እያሰብን በባህልም ይሁን በየእምነታችን አስተምህሮ መኖርን አምኜ እቀበላለሁ አከብራለሁ) 


በዘመናችን አብዛኞች ገንዘብ፣ ቤት፣ መኪና፣ ቆንጆ ሚስት፣ ሐብታም ባል፣ ብዙ ልጆች ካሉዋቸው ስኬታማ የሆኑ የሚመስላቸው ብዙ ዘመን አመጣሽ ወጣቶች ተበራክተዋል። ስኬት ለነርሱ ይህ ነው። ቤቱን ከየት አመጣኸው? መኪናውን እንዴት ገዛኸው? ኧረ መንጃ ፈቃዱን እንዴት አወጣኸው የሚሉት ነገሮች ከተነሱ በየራሳቸው ችግር አለባቸው። ከድሃ ቤተሰብ የተወለደ አንድ የሰላሳ አመት ወጣት የስድስት ሚሊዮን ብር መኪና ሲነዳ፣ የሃያ እና የሰላሳ ሚሊዮን ብር መኖሪያ ቤት ሲኖረው ቤቱ ውስጥ የሶስት እና አራት መቶ ሺ ብር ሶፋ ላይ ሲቀመጥ ወዘተ ይህ ወጣት ስኬታማ ነው?። እንዴት? የሚጠይቅ ትውልድ የለም እንጂ ጉዱ ብዙ ሊሆን ይችላል። እርሱ እንዲህ ሲያድግ ሲመነደግ አገሩ አታድግም። ለምን? የሐብት ምንጩ ሕጋዊ ስላልሆነ ሰርቶ ካገኘው ግብር ስለማይከፍል ወዘተ። ( አገር የምታድገው አንዱ እና ዋነኛው በእኔ አረዳድ በግብር ከፋዮች ነውና) 


የቆንጆዋን ሚስት እና የሐብታሙን ባል ጉዳይ እንዝለል እና ብዙ ልጅ መውለድ ስኬት ነው? (ቆንጆ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ ድሮ ያደኩበት ቤት ውሃልክ የሌለው፣ ግድግዳው በፍልጥ እና ማገር የቆመ፣ በጭቃ እና ጭድ ተመርጎ እና ተለስኖ በእበት እየተለቀለቀ የሚያሸበርቅ እና በሚደምቅ ቤት ውስጥ ነው ያደኩት ለዚያውም ቤቱ የቆመበት ቦታ ምስጥ የሚፈላበት ቦታ ነበረ ግን ቤቱ ዛሬም ድረስ አለ። ቤታችን ጅብሰም ቦርድ፣ ቻክ፣ ቀለም ወዘተ አያውቅም አብዛኞቻችን ታሪካችን ይህን ይመስላል መዳረሻችንም እንዲሁ አንድ ነው ብዙም ያልተራራቀ ምክንያቱም ምንጫችን አንዲት ድሃ አገር እና ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ስለሆነ። እናቴ አያቴ እህቴ አሳዳጊዬ ወዘተ የፀጉር ዊግ፣ ቻፕስቲክ እና ሊፒስቲክ፣ ሜካፕ እና ፋውንዴሽን፣ ወዘተረፈ አያውቁም ግን ሲበዛ ቆንጆ ናቸው። የዛሬ ሚስቶች ግማሾቹ እንደ ዘመኑ ቤት የተዋቡትና የደመቁት ቆመው የሚሄዱት ከጥፍራቸው፣ ጸጉራች፣ ፊታቸው፣ዳሌያቸው፣ ሁለመናቸው በጀሶ እና ቻክ (ፊታቸው ስለሚቀባቡት ቅባት ለመግለጥ ነው) ተሰርቶ በቀለም ያበደ ነው። ቆንጆ ተብለው እነርሱን ነው እንግዲህ ማግባት እንደ ስኬት የሚታዩት። (እነዚህ እህቶች በእንቅልፍ ሰአት ላያቸው እና በከተማዋ ሲናኙ ላያቸው ለየቅል ናቸው ለእናንተ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ስለሆነ ይቅርብኝ) አሁንም ልጠይቅ "ቆንጆ ሴት ወይም ሐብታም ወንድ" ማግባት ስኬት ነው? 


እናንተም እንደ እኔው ስኬት ትርጉሙ ጥያቄ ካጫረባችሁ እውነት ስኬት ትርጉሙ ምንድን ነው? እኔ እጠይቃለሁ። 


አንዳንዶች ዘመንኛዎች የገንዘብ ነጻነት፣ የጊዜ ነጻነት ካለህ ስኬታማ ነህ ይሉኛል። እንዴት ነው የገንዘብ ነጻነት እና የጊዜ ነጻነት የሚኖርህ? (በአንድ ወቅት በኔትወርክ ማርኬቲንግ ውስጥ እሰራ ነበረ ገንዘብ አገኝ ነበረ ግን ነጻ አልነበርኩም። ምናልባት ሕሊና ስለ ነበረኝ መሰለኝ።) ዛሬ ላይ ገንዘብ የምናገኝባቸው መንገዶች ከሕሊና ዳኝነት ነጻ ያደርጉን ይሆን? እያልኩ እጠይቃለሁ። ሶስት እና አራት መቶ ብር ይሸጥ የነበረን ዘይት አንድ ሺ ብር ሸጦ ገንዘብ መሰብሰብ ገንዘብ ቢያስገኝ የገንዘብ ነጻነት ይሰጥ ይሆን? ሕሊና ቢስ ከሆንን አዎ። 


ፋርማሲ ከፍተህ ወገንህ በመድሃኒት እጦት ሲማቅቅ የመድኃኒቱ ከገበያ ላይ መጥፋትን አጋጣሚ ተጠቅመህ ከመደርደሪያ ላይ አንስተህ ደብቀህ አጋጣሚውን ተገን አድርገህ ተደራድረህ ዋጋውን ከፍ አድርገህ ስትሸጥ ገንዘብ ልታገኝ ትችላለህ ግን ሕሊና ካለህ የገንዘብ ነጻነት አይኖርህም። 


ግብይት ሰጥቶ መቀበል ነው፤ አገልግሎት ወይም እቃ ትሰጣለህ ተመጣጣኝ ገንዘብ ትቀበላለህ። የገንዘብ ነጻነት አገኘን እያሉ የሚደሰኩሩት ቢሮ ከመክፈት ከመደራጀት እና ወገን ከማጭበርበር እና የሌላቸው ገንዘብ ነጥቀው ባዶ እጃቸውን ከማስቀረት በቀር ምንም ሳያደርጉልህ እነርሱ ስለተካኑበት ይበለጽጋሉ አንተ ባለ እዳ እና ጭንቀታም ትሆናለህ። 


(በአንድ ወቅት ሰዎች አገኙኝ ሰበኩኝ የገንዘብ ነጻነት እና የጊዜ ነጻነት እፈልግ ስለነበረ ጓጉቼ ሶስት እና አራት ሺ ብር ከፍዬ የተባለውን ስልጠና ወሰድኩ ስልጠናው ስለ ግል ሕይወታቸው ዲስኩር ብቻ ነበረ በእብሪት በትእቢት በማን አለብኝነት የተሞላ ግን ውጤት አልነበረውም። የሚያወሩትን በሕይወትህ ውስጥ መሬት አያወርዱትም ከሰጡህ ተስፋ እና ምኞት ጋር አያገናኙህም። እነርሱ ግን ገንዘብ ያገኛሉ ነጻነቱን ባያገኙትም።) ምን አልባት እንደፈለጉት የሚመዠርጡት ገንዘብ ይኖራቸው ይሆናል። ጥያቄዬ ስልጠና ብቻ ሰው ይቀይራል ወይ? ነው። የገንዘብ እና የጊዜ ነጻነት ይሰጣል ወይ? መማር ሰው ከለወጠ ከአስራ ሁለት እስከ አስራ ስድስት አመት በአማካይ አብዛኛው ባዶ ኪሱን የሚወዛወዝ ወጣት ዕድሜውን በትምህርት እና በስልጠና አሳልፏል። የተባለው የገንዘብ ነጻነት ግን የለም። ታድያ መማር መሰልጠን ስኬታማ አያደርግም ማለት ነው? ሌላኛው ጥያቄዬ ነው። 


በኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ስኬታማ የሚያደርጉ አስር ሚስጢሮች ብሎ መጽሐፍ የጻፈ እንጂ "ስኬታማ" የሆነው አስሩም መንገዶች አስሩን ያነበቡ ሰዎች ስኬታማ ሲሆኑ ማየት ከባድ ነው። 


ታድያ ስኬታማነት ምንድን ነው? እንዴትስ ስኬታማ ይኮናል? የሁላችሁንም ስኬት አስተያየት እጠብቃለሁ። 


ስኬት ዘርፈ ብዙ ነው። በየዘርፉ ስኬታማ የሆናችሁ የሕይወት ልምዳችሁን አጋሩን። 


ቢያንስ አንድ ሰው ስኬታማ ነኝ ብሎ ሲያስብ ራሱን እንዲፈትሽልኝ የምፈልገው የግል ሕይወቱ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ሕይወቱን፣ የፋይናንስ አቅሙን እና ምንጩን ሕጋዊ አግባብነቱን፣ አካላዊ ጤንነቱን እና ሕሊናው ንጹህ መሆኑን፣ ወዘተ ግምት ውስጥ እንዲሆን ይፈለጋል።


ለኔ ስኬት ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ሆነው ከዚያ ባሻገር ግን ከደስታህ ይልቅ ለሌሎች ደስታ የምትጥር ከሆነ፣ የሌሎች ሐዘን እና ችግር ወደ ራስህ ተጋብቶ ከጎናቸው ለመፍትሔ መቆም የምትችል ከሆነ፣ ካገኘኸው የዕለት ጉርስ የአመት ልብስ ለሌለው ያለምንም ወረታ መድረስ ስትችል፣ ፍርድ ተጓደለ ድሃ ተበደለ ብለህ የምታስብ የበኩልህንም ጥረት ስታደርግ፣ ደስታህ ሌሎች ሲደሰቱ ከሆነ፣ ከላይ በጥቂቱ ለተዘረዘሩት ችግሮች መንስኤው አንተ ካልሆንክ ወዘተረፈ አንተ ስኬታማ ነህ። 


አበቃሁ መድረኩን ለእናንተ ትቼዋለሁ። 


ይቆየን።

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት

 አንዳንዴ ስለ ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያዊነት ፣ ስለ ክርስትና ፣ ስለ እስልምና እና ሌሎችም ማሰብ ይከብዳል። ፖለቲካውንማ ተውት የእረኞች ጨዋታ አድርገውታል፤ እረኞችስ ቀን ተጫውተው ማታ ሲበተኑ ነገ በሌላ ጨወታ እና ቅኝት ነው የሚመለሱትና።


ግራ የገባው አንዲት አገር ኢትዮጵያን ይዞ በየመንደር ለዚያውም ለመንደሩ አንዳች ፋይዳ በሌለው ጉዳይ መከፋፈሉ፣ ሁሉም ነፍሱን አስይዞ የሚወራረድባት የመኖሩ ምክንያት እምነት ይኖረውና ከየእምነቱ አስተምህሮ ውጪ ሲጓዝ ከማየት የበለጠ ግራ የገባ ነገር የለም።(ለኔ)


አሁን በሰሞኑ በውስጥ ብዙ መልእክቶች ከየእምነቱ ሰዎች ይደርሱኛል። (ለመረጃ ይሁን ሊያናግሩኝ እንደሆነ እንጃ) እኔ ግን ኢትዮጵያ ከመቶ አመት በፊት ስለነበረችበት ሁኔታ የተጻፉ ታሪኮችን፣ ግለ ታሪኮችን በማንበብ ላይ ነበርኩ። (የዛሬውን ያህል ቅጥ ያጣ ነገር አላነበብኩም) አልፎ አልፎ እንዲህ የከረፋ ታሪክም ባይሆን የሽፍቶችን ታሪክ ለማየት ችያለሁ። ( እምነትን ሽፋን እና ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ የዛሬዎቹ ወሮበላዎች ግን የትናንቱን ሽፍቶች ያስንቃሉ)


ኢትዮጵያኮ ከጣልያን ወረራ ቀደም ብሎ እና ከዚያ ኋላ አውራጃ ከአውራጃ የሚያገናኝ የረባ መንገድ አልነበራትም፤ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብዛኛው የገጠር ከተሞቻችን የጤና ተቋም አልነበራቸውም። በሽተኞች እና ነፍሰጡሮች ለሕክምና በቃሬዛ ነበር የሚጓጓዙት።(ከምኔው ለጥፋት ደረስን ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ባንኮችን እና ሌሎች የግል ተቋማትን ለማፍረስ ፈጠንን?)


በእኔ አረዳድ ከሆነ ልሳሳትም እችላለሁ ባለኝ መረጃ ንጹህ ውሃ መጠጣት የስላጣኔ እና የእድገት ምልክት በሆነባት አገር እየኖርን እንዴት ብለን የሌለንን እናጠፋለን? መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ዮኒቨርስቲ ወዘተ የስኬት መለኪያ በሆነበት አገር እንደ ቅርስ ልንንከባከበው ሲገባ እንዴት በአስርት አመታት የገነባነውን በሰአታት ለማፍረስ እንነሳለን? እንዴትስ ነው ሙስሊሞች/ ክርስቲያኖች ይህን አደረጉት ታስብላለህ?


ታድያ እንደዚህ አይነት አገር ውስጥ የሚኖር ሕዝብ፣ ሐይማኖተኛ አገር ከማፍረስ ይልቅ መገንባት አይሻለውም ነበረ። (አገር እና ሕዝብ ሲኖር ነውና ሁሉም ነገር የሚኖረው)


ብዙ ጊዜ የሚጠቀስ ነገር ልጥቀስላችሁ ከአገር ወጥተን ባህር ስንሻገር ፓስፖርት ነው የምናሳየው ፓስፖርታችን ላይ ኢትዮጵያዊ መሆናችን እንጂ ሌላ ነገራችን አይጠቀስም። እውቅናችንም ሆነ እውቅና መነፈጋችን በአገራችን ላይ የተመረኮዘ ነው። ነገር ግን የኔ እምነት የበላይ ካልሆነ፣ እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ካልገዛ ይህቺ አገር አገር አትሆንም የሚል ትምክህት አለብን። (የት ልንደርስ ነው?)


ይህን አስተምህሮ ነቢዩ መሐመድም ሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ አላስተማሩትም። መቸስ ከሁለቱ አስተምሮ ውጪ የሆነ ጥቂት ነው። ለእስልምናው ቤተክርስቲያን ወይም ቸርች አቃጥሎ ጥቅሙ ምንድንነው ከፊቱ ያለው ታሪክ ምንም ይሁን ምንም። ለክርስቲያኑ ቀኝህን ለመታ ግራህን ስጥ የሚል ወንጌል እየሰበከ እና እየተሰበከ ሙስሊሙን ማሳደድ ከምን ከየት የመጣ ነው?


አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ከሰአታት በፊት ደረሰኝ ሙሲሊሞችን እንደማይወክል ጠንካራ እምነት አለኝ። ለፖለቲካ ትርፍ የሚባሉትንም አይወክልም የፖለቲካ ዲሲፕሊን አይደለምና። ከአንድ ደቂቃ በታች ነው በግርድፉ እንዲህ ይላል[ "ቤተክርስቲያንን አታቃጥሉ ቤተክርስቲያንን ለምን ታቃጥላላችሁ? ቤተክርስቲያንን አትንኩት ባለበት ይሁን እነርሱን ካጠፋን በኋላ ቤተክርስቲያኑ ወደ መስጊድነት እንቀይረዋለን። አላህን እያመሰገነ ቅዱስ ገብርኤል ወደ መስኪድነት እንደተቀየረ ይናገራል"] እኔ እስከማውቀው እስልምና አስተምሮ ካልሆነ በቀር በግድ አያሰልምም። 


ብዙ ነገር ማለት ቢቻል እንኳን ብዙ የሚከለክሉኝ ሥነምግባሮች እና አስተምህሮዎች ስላሉኝ ብዘለው እመርጣለሁ። ስለ ራሴ ጉዳይ እንደ እግር እሳት ሲያንገበግበኝ ስለ ወንድሞቼም እንዲሁ ይገደኛልና። 


ክርስቲያን እንደመሆኔ መጠን አስር የምገዛለት ህጎች አሉኝ አምስቱ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ሲሆን አምስቱ ስለ ወንድም ፍቅር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን የምወደውን ያህል የሰውን ልጅ (ከእምነቱ፣ ብሔሩ እና የፖለቲካ አመለካከቱ ጨምሮ) የመውደድ ግዴታ አለብኝ።


ለአንድ ክርስቲያንም ይሁን ሙስሊም እንዴት ቤተክርስቲያን፣ ቸርች እና መስኪድ እንደሚገነባ በደንብ ያውቀዋልና አንዳቸውንም ለማቃጠል፣ ለማፍረስ ይቅርና አንዲት ጠጠር ለማንሳት አይዳዳውም።


አንዳንድ የአለም ክፍሎች ላይ አብያተክርስቲያናት ወደ ሙዚየም እና መስጊድነት እንደተቀየሩ አውቃለሁ። ነገር ግን ይህ ተግባር የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም። ይሁን ከተባለ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ይኽ መዘንጋት የለበትም። (አንዱ ከሰሞኑ የተነሳውን ግርግር ታሳቢ አድርጎ ስለሚከተለው ጥፋት ሲናገር ለነበረው ምላሽ ሲሰጥ "ማንም ውሃ እና ቅጠል ይዞ አይወጣም " ሲል ሰማሁ። እውነት ነው ድንበር ሲታለፍ ሁሉም እሳት ጎርሶ እሳት ይተፋልና ዳፋው ከባድ ነው።) ከዚህ ማንም አያተርፍም።


አንድ ወደሚያደርገን አገራችን ጉዳይ ስንመጣ አገር ፈርሳ የት ሆነን ልናመልክ ነው? እምነት የላኩልን ሰዎች እንደሆነ እምነት ይልኩልን እንደሆነ እንጂ አገር ስትፈርስ አንዳችንንም አይቀበሉንም። ይህን አንዘንጋ። አጥፊዎችም ስለ ጥፋታችን ዶላር ይከፍሉን እንደሆነ እንጂ አገር ቆርሰው አይሰጡንም። ይህ የሚጠፋን አይመስለኝም።


አንዳንድ የዋሆች የሚሆነው ሁሉ ለፖለቲካ ትርፍ እንቅስቃሴ ብቻ የሆነ ብቻ ይመስላቸዋል። አትሳሳቱ አይደለም ባይባልም  ብቻውን ግን አይደለም። ሁለቱ ቤተ እምነቶች መቸም በእምነት ደረጃ አይጋጩም። የቤተእምነቱ ሰወች እንደሚያራምዱት ተለጣፊ ዓላማ ግን ላይጋጩ የሚችሉበት ሁኔታ የለም አይባልም። እኛ ግን ዓላማችንን እና ሚናችንን እንለይ ሐይማኖተኛ ነን ካልን የእምነት አስተምሮውን እንከተል፣ ፖለቲከኞች ነን ካልን እምነቱን እና ፖለቲካውን አንቀላቅል።


ወጣቶች ትልቅ የሆነ የአገርም ሆነ የሐይማኖት አደራ አለባችሁ። በአስተውሎት ተንቀሳቀሱ እንጂ እንደ መንጋ አትነዱ። እምነትንም ሆነ አገርን ተገን አድርገው የሚዘውሩን ጊዜያቸውን እንደ ሸንኮራ ምጥጥ ስላደረጉት ነውና እኛ ግን ጊዜያችንን ልንሰዋላቸው ዓላማቸውን ልናስፈጽም አይገባም።


በየእምነት ተቋማቱ ያላችሁ ወጣቶች፣ አስተማሪዎች፣ አባቶች አስቀድማችሁ የእምነቱ አስተምሮ ምን ይላል? ብላችሁ ጠንቅቃችሁ እወቁ። አንዳንዴ የራስን እምነት የሚያስተምር ግልብ 'መምህር' ከማዳመጥ የሰከነ አስተዋይ የሌላ ቤተእምነት መምህር መስማት ያስመኛል።


አንዳንዱ አስተምህሮው የማይለውን ሲደሰኩር ወጣቱ እውነት እየመሰለው ይከተዋል። ለ"መስዋዕትነት" ይሯሯጣል።


ስለመስዋዕትነት ሌላ ጊዜ የምናወራው ነገር ቢሆንም ቅሉ አሁን ላይ በየትኛውም ቤተእምነት በተነሳ ግርግር እየተነሳን የምንማገደው መስዋዕትነት እንዳልሆነ አስረግጬ እናገራለሁ። መስዋዕትነት ስለሚያምኑት ነገር ዋጋ መክፈል ነው።እኛ በቤተእምነታችን አጥር ሥር ስናልፍ ስናገድም ኖረን አንዳች የእምነት ምልክት በሕይወታችን ሳይኖር እንደ እሳት እራት ግርግር ውስጥ ገብተን የሞትን እንደሆነ እንደሁ መስዋዕት የሚለው ስም ሲለጠፍልን ስሙን እናገኝ እንደሆነ እንጂ ክብሩን አናገኝም።

እንደ ወንድምነቴ የምመክረው መጀመሪያ በመስኪዱ፣ በቤተክርስቲያን ፣ በቸርች ተገኝተህ ተማር ሕይወቱን ኑረው ከዚያ በኋላ በእምነትህ የሚመጣውን ተቀበል ከዚያም መስዋዕት ሁኑ፤ ጽድቅም ሆኖ ይቆጠርልሃል። አለበለዚያ ግን ደምህ ደመከልብ ነው የሚሆነው።


ሁላችንም አገራችንን ዘብ እንቁምላት የየቤተእምነቶቻችንን ጉዳይ አንገት መድፊያ አንሁን።


ለክርስቲያኖች አንድ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር፣ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፣ በሐሰት አትመስክር የሚለውን ቀዳሚ ሕግ ጠብቅ።


ይኽን ካደረክ የማንም ሐብት ንብረት አይዘረፍም፣ የሰውልጅ ሕይወቱ እንዲሁ በከንቱ አይቀጠፍም፣ የሴትልጅ ክብር በየመንገዱ አይገሰስም/አትደፈርም፣ ለወንድምህም ወዳጁ እንጂ ጠላቱ አትሆንም፣ ስለእውነት እንጂ ስለቡድንህ ፍርድ አይዛባምና።


እንዲህ ስላልሆነ በዘመናችን መኪኖቻችን በስንት ቁልፍ እና ቴክኖሎጂ ጭምር ተጠብቀው ይሰረቃሉ፣ እህቶቻችን በነጻነት አይንቀሳቀሱም አልፎ ተርፎም ይደፈራሉ፣ በየእምነት ቤቶች በተፈጠረ ችግር ሰዎች ይገደላሉ፣ አካል ይጎላል፣ ንብረት ይወድማል፣ የመንጋ ፍርድ ይፈረዳል። 99% አማኝ ያለባት አገር ነች ተብላ የምትታማ አገር አለችን።ለዚህ አፍራለሁ።


ዶክተር አለማየሁ ዋሴ በአጭር ቃል የተናገሩት ምርጥ ገላጭ አባባል አለ። በግርድፉ መልዕክቱ እንዲህ ይላል "እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሰው በዚህምድር ላይ ያልሰራነው በደል የለም። ሰይጣን እንኳን የሚቀናብን ነን። በቀሪው ዕድምያችን ያልሰራነው ነገር ቢኖር መልካም ነገር ብቻ ነው።


ይኼ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ... ቀሪው ዕድሜያችን የክፋት ሳይሆን የመልካምነት ነው። ለዚያውም በቂ የሆነ ዕድሜ የለንም። ከበቃን ቀሪ ዘመናችንን በአንድነት መልካም ነገር እንስራ።


ለጠቢብ አንዲት ቃል ትበቃዋለችና ጠቢባን ሁኑ።

"መጀመሪያ እንድትሸነፍ የሚያደርጉህን ምክንያትህን አሸንፍ"

 ጀግናችን አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ጀግንነትን ከመቀዳጀቱ በፊት 35ኪሎ ሜትር እንደሮጠ ሆዱን አመመው፤ ይኽም ሕመም ሩጫውን እንዲያቋርጥ ሊያደርገው ከጫፍ የደረሰውን ውሳኔ እንዲቀይር ያደረገው ከላይ የጠቀስኩት የአለቃው ምክር ነበረ። 


የድል ምልክታችን አበበም ወደ ልቡ ተመልሶ ሕመሙን ችላ አለው። ሩጫውን ቀጠል፤ ዛሬ የምንኮራበትን ድል አስመዘገበ። አበበን ለድል ያበቃው በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ እንዲውለበለብ ያስቻለው ሕመሙን ማሸነፉ ነው። 


እኛም እንዳናሸንፍ የሚያደርጉን፣ የሚያዋርዱን፣ ከክብር ዝቅ የሚያደርጉን፣ መለያየት ላይ እንድናተኩር የሚያደርጉን፣ ዘረኞች እንድንሆን፣ ለኔ ብቻ እንድንል ያደረጉን ሕመሞች አሉብን። 


ድል ለመቀዳጀት፣ በዓለም አደባባይ አንደኞች እንድንሆን፣ ከፈለግን መጀመሪያ እንድንሸነፍ የሚያደርጉንን ምክንያቶች እናሸንፍ። 


መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል " ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙ" እንዚህ ቀበሮዎች ጥቃቅን መሆናቸው ሳይሆን የሚያጠፉት ሰፊ የወይን እርሻ ነው ግምት ሊሰጠው የሚገባው። በዘመናችንም ችላ የምንላቸው ጥቃቅን የመሰሉን ለዓመታት አዕምሯችን ላይ የተሰሩ ነገሮች ዛሬ ላይ ለእርስ በርስ ጦርነት፣ ለስደት፣ ለሞት፣ ለጥላቻ፣ ለዘር እልቂት እየዳረገን ይገኛል። 


እንድንሸነፍ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል አንዱ ዘረኝነት ነው፤ ለማሸነፍ ከፈለግን መጀመሪያ ዘረኝነትን የተጠናወተው ማንነታችንን ማሸነፍ ይኖርብናል። 


ሌላው ጥላቻ ነው "ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው" እንዲል መጽሐፍ ጥላቻ የዕድገት/የአሸናፊነት ጸር ነው። ስለዚህ መጀመሪያ ጥላቻን እናሸንፍ። ከዚያ ወደቀደመ ክብራችን እንመለሳለን። አለበለዚያ የሶስት ሺ ዘመን ታሪካችንን እናበላሻለን። 


ሁሌም አሸናፊ ትሆን ዘንድ የሚያሸንፍህን አሸንፍ።

መልካም ጊዜ

ደረሰ ረታ 


እንኳን ደስ አለን

 በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያጣነዉን ደስታ ዳግም እንድንጋራ ላደረጋችሁን ድንቅ አትሌቶቻችን እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እናመሰግናችኋለን፡፡

 

መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እንኳን ደስ አለን፡፡ 





ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...