አንዳንዴ ስለ ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያዊነት ፣ ስለ ክርስትና ፣ ስለ እስልምና እና ሌሎችም ማሰብ ይከብዳል። ፖለቲካውንማ ተውት የእረኞች ጨዋታ አድርገውታል፤ እረኞችስ ቀን ተጫውተው ማታ ሲበተኑ ነገ በሌላ ጨወታ እና ቅኝት ነው የሚመለሱትና።
ግራ የገባው አንዲት አገር ኢትዮጵያን ይዞ በየመንደር ለዚያውም ለመንደሩ አንዳች ፋይዳ በሌለው ጉዳይ መከፋፈሉ፣ ሁሉም ነፍሱን አስይዞ የሚወራረድባት የመኖሩ ምክንያት እምነት ይኖረውና ከየእምነቱ አስተምህሮ ውጪ ሲጓዝ ከማየት የበለጠ ግራ የገባ ነገር የለም።(ለኔ)
አሁን በሰሞኑ በውስጥ ብዙ መልእክቶች ከየእምነቱ ሰዎች ይደርሱኛል። (ለመረጃ ይሁን ሊያናግሩኝ እንደሆነ እንጃ) እኔ ግን ኢትዮጵያ ከመቶ አመት በፊት ስለነበረችበት ሁኔታ የተጻፉ ታሪኮችን፣ ግለ ታሪኮችን በማንበብ ላይ ነበርኩ። (የዛሬውን ያህል ቅጥ ያጣ ነገር አላነበብኩም) አልፎ አልፎ እንዲህ የከረፋ ታሪክም ባይሆን የሽፍቶችን ታሪክ ለማየት ችያለሁ። ( እምነትን ሽፋን እና ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ የዛሬዎቹ ወሮበላዎች ግን የትናንቱን ሽፍቶች ያስንቃሉ)
ኢትዮጵያኮ ከጣልያን ወረራ ቀደም ብሎ እና ከዚያ ኋላ አውራጃ ከአውራጃ የሚያገናኝ የረባ መንገድ አልነበራትም፤ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብዛኛው የገጠር ከተሞቻችን የጤና ተቋም አልነበራቸውም። በሽተኞች እና ነፍሰጡሮች ለሕክምና በቃሬዛ ነበር የሚጓጓዙት።(ከምኔው ለጥፋት ደረስን ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ባንኮችን እና ሌሎች የግል ተቋማትን ለማፍረስ ፈጠንን?)
በእኔ አረዳድ ከሆነ ልሳሳትም እችላለሁ ባለኝ መረጃ ንጹህ ውሃ መጠጣት የስላጣኔ እና የእድገት ምልክት በሆነባት አገር እየኖርን እንዴት ብለን የሌለንን እናጠፋለን? መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ዮኒቨርስቲ ወዘተ የስኬት መለኪያ በሆነበት አገር እንደ ቅርስ ልንንከባከበው ሲገባ እንዴት በአስርት አመታት የገነባነውን በሰአታት ለማፍረስ እንነሳለን? እንዴትስ ነው ሙስሊሞች/ ክርስቲያኖች ይህን አደረጉት ታስብላለህ?
ታድያ እንደዚህ አይነት አገር ውስጥ የሚኖር ሕዝብ፣ ሐይማኖተኛ አገር ከማፍረስ ይልቅ መገንባት አይሻለውም ነበረ። (አገር እና ሕዝብ ሲኖር ነውና ሁሉም ነገር የሚኖረው)
ብዙ ጊዜ የሚጠቀስ ነገር ልጥቀስላችሁ ከአገር ወጥተን ባህር ስንሻገር ፓስፖርት ነው የምናሳየው ፓስፖርታችን ላይ ኢትዮጵያዊ መሆናችን እንጂ ሌላ ነገራችን አይጠቀስም። እውቅናችንም ሆነ እውቅና መነፈጋችን በአገራችን ላይ የተመረኮዘ ነው። ነገር ግን የኔ እምነት የበላይ ካልሆነ፣ እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ካልገዛ ይህቺ አገር አገር አትሆንም የሚል ትምክህት አለብን። (የት ልንደርስ ነው?)
ይህን አስተምህሮ ነቢዩ መሐመድም ሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ አላስተማሩትም። መቸስ ከሁለቱ አስተምሮ ውጪ የሆነ ጥቂት ነው። ለእስልምናው ቤተክርስቲያን ወይም ቸርች አቃጥሎ ጥቅሙ ምንድንነው ከፊቱ ያለው ታሪክ ምንም ይሁን ምንም። ለክርስቲያኑ ቀኝህን ለመታ ግራህን ስጥ የሚል ወንጌል እየሰበከ እና እየተሰበከ ሙስሊሙን ማሳደድ ከምን ከየት የመጣ ነው?
አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ከሰአታት በፊት ደረሰኝ ሙሲሊሞችን እንደማይወክል ጠንካራ እምነት አለኝ። ለፖለቲካ ትርፍ የሚባሉትንም አይወክልም የፖለቲካ ዲሲፕሊን አይደለምና። ከአንድ ደቂቃ በታች ነው በግርድፉ እንዲህ ይላል[ "ቤተክርስቲያንን አታቃጥሉ ቤተክርስቲያንን ለምን ታቃጥላላችሁ? ቤተክርስቲያንን አትንኩት ባለበት ይሁን እነርሱን ካጠፋን በኋላ ቤተክርስቲያኑ ወደ መስጊድነት እንቀይረዋለን። አላህን እያመሰገነ ቅዱስ ገብርኤል ወደ መስኪድነት እንደተቀየረ ይናገራል"] እኔ እስከማውቀው እስልምና አስተምሮ ካልሆነ በቀር በግድ አያሰልምም።
ብዙ ነገር ማለት ቢቻል እንኳን ብዙ የሚከለክሉኝ ሥነምግባሮች እና አስተምህሮዎች ስላሉኝ ብዘለው እመርጣለሁ። ስለ ራሴ ጉዳይ እንደ እግር እሳት ሲያንገበግበኝ ስለ ወንድሞቼም እንዲሁ ይገደኛልና።
ክርስቲያን እንደመሆኔ መጠን አስር የምገዛለት ህጎች አሉኝ አምስቱ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ሲሆን አምስቱ ስለ ወንድም ፍቅር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን የምወደውን ያህል የሰውን ልጅ (ከእምነቱ፣ ብሔሩ እና የፖለቲካ አመለካከቱ ጨምሮ) የመውደድ ግዴታ አለብኝ።
ለአንድ ክርስቲያንም ይሁን ሙስሊም እንዴት ቤተክርስቲያን፣ ቸርች እና መስኪድ እንደሚገነባ በደንብ ያውቀዋልና አንዳቸውንም ለማቃጠል፣ ለማፍረስ ይቅርና አንዲት ጠጠር ለማንሳት አይዳዳውም።
አንዳንድ የአለም ክፍሎች ላይ አብያተክርስቲያናት ወደ ሙዚየም እና መስጊድነት እንደተቀየሩ አውቃለሁ። ነገር ግን ይህ ተግባር የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም። ይሁን ከተባለ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ይኽ መዘንጋት የለበትም። (አንዱ ከሰሞኑ የተነሳውን ግርግር ታሳቢ አድርጎ ስለሚከተለው ጥፋት ሲናገር ለነበረው ምላሽ ሲሰጥ "ማንም ውሃ እና ቅጠል ይዞ አይወጣም " ሲል ሰማሁ። እውነት ነው ድንበር ሲታለፍ ሁሉም እሳት ጎርሶ እሳት ይተፋልና ዳፋው ከባድ ነው።) ከዚህ ማንም አያተርፍም።
አንድ ወደሚያደርገን አገራችን ጉዳይ ስንመጣ አገር ፈርሳ የት ሆነን ልናመልክ ነው? እምነት የላኩልን ሰዎች እንደሆነ እምነት ይልኩልን እንደሆነ እንጂ አገር ስትፈርስ አንዳችንንም አይቀበሉንም። ይህን አንዘንጋ። አጥፊዎችም ስለ ጥፋታችን ዶላር ይከፍሉን እንደሆነ እንጂ አገር ቆርሰው አይሰጡንም። ይህ የሚጠፋን አይመስለኝም።
አንዳንድ የዋሆች የሚሆነው ሁሉ ለፖለቲካ ትርፍ እንቅስቃሴ ብቻ የሆነ ብቻ ይመስላቸዋል። አትሳሳቱ አይደለም ባይባልም ብቻውን ግን አይደለም። ሁለቱ ቤተ እምነቶች መቸም በእምነት ደረጃ አይጋጩም። የቤተእምነቱ ሰወች እንደሚያራምዱት ተለጣፊ ዓላማ ግን ላይጋጩ የሚችሉበት ሁኔታ የለም አይባልም። እኛ ግን ዓላማችንን እና ሚናችንን እንለይ ሐይማኖተኛ ነን ካልን የእምነት አስተምሮውን እንከተል፣ ፖለቲከኞች ነን ካልን እምነቱን እና ፖለቲካውን አንቀላቅል።
ወጣቶች ትልቅ የሆነ የአገርም ሆነ የሐይማኖት አደራ አለባችሁ። በአስተውሎት ተንቀሳቀሱ እንጂ እንደ መንጋ አትነዱ። እምነትንም ሆነ አገርን ተገን አድርገው የሚዘውሩን ጊዜያቸውን እንደ ሸንኮራ ምጥጥ ስላደረጉት ነውና እኛ ግን ጊዜያችንን ልንሰዋላቸው ዓላማቸውን ልናስፈጽም አይገባም።
በየእምነት ተቋማቱ ያላችሁ ወጣቶች፣ አስተማሪዎች፣ አባቶች አስቀድማችሁ የእምነቱ አስተምሮ ምን ይላል? ብላችሁ ጠንቅቃችሁ እወቁ። አንዳንዴ የራስን እምነት የሚያስተምር ግልብ 'መምህር' ከማዳመጥ የሰከነ አስተዋይ የሌላ ቤተእምነት መምህር መስማት ያስመኛል።
አንዳንዱ አስተምህሮው የማይለውን ሲደሰኩር ወጣቱ እውነት እየመሰለው ይከተዋል። ለ"መስዋዕትነት" ይሯሯጣል።
ስለመስዋዕትነት ሌላ ጊዜ የምናወራው ነገር ቢሆንም ቅሉ አሁን ላይ በየትኛውም ቤተእምነት በተነሳ ግርግር እየተነሳን የምንማገደው መስዋዕትነት እንዳልሆነ አስረግጬ እናገራለሁ። መስዋዕትነት ስለሚያምኑት ነገር ዋጋ መክፈል ነው።እኛ በቤተእምነታችን አጥር ሥር ስናልፍ ስናገድም ኖረን አንዳች የእምነት ምልክት በሕይወታችን ሳይኖር እንደ እሳት እራት ግርግር ውስጥ ገብተን የሞትን እንደሆነ እንደሁ መስዋዕት የሚለው ስም ሲለጠፍልን ስሙን እናገኝ እንደሆነ እንጂ ክብሩን አናገኝም።
እንደ ወንድምነቴ የምመክረው መጀመሪያ በመስኪዱ፣ በቤተክርስቲያን ፣ በቸርች ተገኝተህ ተማር ሕይወቱን ኑረው ከዚያ በኋላ በእምነትህ የሚመጣውን ተቀበል ከዚያም መስዋዕት ሁኑ፤ ጽድቅም ሆኖ ይቆጠርልሃል። አለበለዚያ ግን ደምህ ደመከልብ ነው የሚሆነው።
ሁላችንም አገራችንን ዘብ እንቁምላት የየቤተእምነቶቻችንን ጉዳይ አንገት መድፊያ አንሁን።
ለክርስቲያኖች አንድ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር፣ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፣ በሐሰት አትመስክር የሚለውን ቀዳሚ ሕግ ጠብቅ።
ይኽን ካደረክ የማንም ሐብት ንብረት አይዘረፍም፣ የሰውልጅ ሕይወቱ እንዲሁ በከንቱ አይቀጠፍም፣ የሴትልጅ ክብር በየመንገዱ አይገሰስም/አትደፈርም፣ ለወንድምህም ወዳጁ እንጂ ጠላቱ አትሆንም፣ ስለእውነት እንጂ ስለቡድንህ ፍርድ አይዛባምና።
እንዲህ ስላልሆነ በዘመናችን መኪኖቻችን በስንት ቁልፍ እና ቴክኖሎጂ ጭምር ተጠብቀው ይሰረቃሉ፣ እህቶቻችን በነጻነት አይንቀሳቀሱም አልፎ ተርፎም ይደፈራሉ፣ በየእምነት ቤቶች በተፈጠረ ችግር ሰዎች ይገደላሉ፣ አካል ይጎላል፣ ንብረት ይወድማል፣ የመንጋ ፍርድ ይፈረዳል። 99% አማኝ ያለባት አገር ነች ተብላ የምትታማ አገር አለችን።ለዚህ አፍራለሁ።
ዶክተር አለማየሁ ዋሴ በአጭር ቃል የተናገሩት ምርጥ ገላጭ አባባል አለ። በግርድፉ መልዕክቱ እንዲህ ይላል "እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሰው በዚህምድር ላይ ያልሰራነው በደል የለም። ሰይጣን እንኳን የሚቀናብን ነን። በቀሪው ዕድምያችን ያልሰራነው ነገር ቢኖር መልካም ነገር ብቻ ነው።
ይኼ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ... ቀሪው ዕድሜያችን የክፋት ሳይሆን የመልካምነት ነው። ለዚያውም በቂ የሆነ ዕድሜ የለንም። ከበቃን ቀሪ ዘመናችንን በአንድነት መልካም ነገር እንስራ።
ለጠቢብ አንዲት ቃል ትበቃዋለችና ጠቢባን ሁኑ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ