ስኬት ምንድን ነው?
አንዳንዶች በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ብዙ ብለዋል፣ ሌሎች ደግሞ በተግባር ይህንን ይመስላል ብለው አመላክተዋል። በሁለቱም መንገድ የተገለጡትን የስኬት ፍቺ ገሚሶች ሲስማሙበት ገሚሶች ደግሞ እንደማይስማሙ ይገልጣሉ። ምን አልባት በዚህ ላይ የተጠና ጥናቶች ለማግኘት አልጣርኩም እንጂ ከሁለቱም በተቃራኒ የሆነ አይጠፋም።
ብቻ ስለ ስኬት ብዙዎች በተለያየ ቃላት መጽሐፍ ጽፈውለታን፣ ሕዝባዊ ንግግር አድርገውበታል፣ በድምጽ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ስልጠናዎች ተሰጥተውበታል፣ ምድራችን ላይ የሚፈለፈሉት ቢዝነሶች ሁሉ ሲጀመሩ ስኬታማ እንደሚያደርጉ ተነግሮላቸው፣ ተዘምሮላቸው፣ ተጨፍሮላቸው ወዘተ ነው መጨረሻቸው ገሚሶቹ በኪሳራ እና በውድቀት ቢዘጉም። (እዚህ ጋር ትርፋማነት ስኬት ነው ወይ ብዬ ጥያቄ አንስቼ አልፋለሁ።)
ስለስኬታማነት ወይም ስለ ስኬት ሌሎች ሁለት በትዳር የተጣመዱትን፣ የተሳሰሩትን፣የተጋመዱትን፣ ቃልኪዳን የገቡትን ሰዎች የሕይወት ጉዞ እንደ ስኬት ይቆጥሩታል። ልብ ብላችሁ ጥንዶቹ አብረው የሆኑበትን ተመልከቱልኝ የተጣመደ፣ የተሳሰረ፣ የተጋመደ እነዚህን ቃላት ስፈትሽ ነፃነት ይጎድለዋል አስጨናቂ አስገዳጅ ነገር ይታይበታል። የትዳር ዘመናቸው ምን ይመስላል? በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ መውጣት መግባታቸው ምን ይመስላል? ደስተኛ ናቸው ወይ? እነዚህን ሳንመልስ አምስት፣ አስር፣ ሃያ አምስት አመትን ብቻ ዕድሜ ስላስቆጠሩ ስኬታማ ይባላሉ?። አለመፋታት፣ አንድ ቤት መጋራት፣ በአንድ በጀት መተዳደር፣ ዕድሜ መቁጠር ብቻ ስኬታማ ያስብለናል ብዬ አሁንም በጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ። በቅንፍ ውስጥ ግን (የገባነውን ቃል ኪዳን እያሰብን በባህልም ይሁን በየእምነታችን አስተምህሮ መኖርን አምኜ እቀበላለሁ አከብራለሁ)
በዘመናችን አብዛኞች ገንዘብ፣ ቤት፣ መኪና፣ ቆንጆ ሚስት፣ ሐብታም ባል፣ ብዙ ልጆች ካሉዋቸው ስኬታማ የሆኑ የሚመስላቸው ብዙ ዘመን አመጣሽ ወጣቶች ተበራክተዋል። ስኬት ለነርሱ ይህ ነው። ቤቱን ከየት አመጣኸው? መኪናውን እንዴት ገዛኸው? ኧረ መንጃ ፈቃዱን እንዴት አወጣኸው የሚሉት ነገሮች ከተነሱ በየራሳቸው ችግር አለባቸው። ከድሃ ቤተሰብ የተወለደ አንድ የሰላሳ አመት ወጣት የስድስት ሚሊዮን ብር መኪና ሲነዳ፣ የሃያ እና የሰላሳ ሚሊዮን ብር መኖሪያ ቤት ሲኖረው ቤቱ ውስጥ የሶስት እና አራት መቶ ሺ ብር ሶፋ ላይ ሲቀመጥ ወዘተ ይህ ወጣት ስኬታማ ነው?። እንዴት? የሚጠይቅ ትውልድ የለም እንጂ ጉዱ ብዙ ሊሆን ይችላል። እርሱ እንዲህ ሲያድግ ሲመነደግ አገሩ አታድግም። ለምን? የሐብት ምንጩ ሕጋዊ ስላልሆነ ሰርቶ ካገኘው ግብር ስለማይከፍል ወዘተ። ( አገር የምታድገው አንዱ እና ዋነኛው በእኔ አረዳድ በግብር ከፋዮች ነውና)
የቆንጆዋን ሚስት እና የሐብታሙን ባል ጉዳይ እንዝለል እና ብዙ ልጅ መውለድ ስኬት ነው? (ቆንጆ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ ድሮ ያደኩበት ቤት ውሃልክ የሌለው፣ ግድግዳው በፍልጥ እና ማገር የቆመ፣ በጭቃ እና ጭድ ተመርጎ እና ተለስኖ በእበት እየተለቀለቀ የሚያሸበርቅ እና በሚደምቅ ቤት ውስጥ ነው ያደኩት ለዚያውም ቤቱ የቆመበት ቦታ ምስጥ የሚፈላበት ቦታ ነበረ ግን ቤቱ ዛሬም ድረስ አለ። ቤታችን ጅብሰም ቦርድ፣ ቻክ፣ ቀለም ወዘተ አያውቅም አብዛኞቻችን ታሪካችን ይህን ይመስላል መዳረሻችንም እንዲሁ አንድ ነው ብዙም ያልተራራቀ ምክንያቱም ምንጫችን አንዲት ድሃ አገር እና ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ስለሆነ። እናቴ አያቴ እህቴ አሳዳጊዬ ወዘተ የፀጉር ዊግ፣ ቻፕስቲክ እና ሊፒስቲክ፣ ሜካፕ እና ፋውንዴሽን፣ ወዘተረፈ አያውቁም ግን ሲበዛ ቆንጆ ናቸው። የዛሬ ሚስቶች ግማሾቹ እንደ ዘመኑ ቤት የተዋቡትና የደመቁት ቆመው የሚሄዱት ከጥፍራቸው፣ ጸጉራች፣ ፊታቸው፣ዳሌያቸው፣ ሁለመናቸው በጀሶ እና ቻክ (ፊታቸው ስለሚቀባቡት ቅባት ለመግለጥ ነው) ተሰርቶ በቀለም ያበደ ነው። ቆንጆ ተብለው እነርሱን ነው እንግዲህ ማግባት እንደ ስኬት የሚታዩት። (እነዚህ እህቶች በእንቅልፍ ሰአት ላያቸው እና በከተማዋ ሲናኙ ላያቸው ለየቅል ናቸው ለእናንተ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ስለሆነ ይቅርብኝ) አሁንም ልጠይቅ "ቆንጆ ሴት ወይም ሐብታም ወንድ" ማግባት ስኬት ነው?
እናንተም እንደ እኔው ስኬት ትርጉሙ ጥያቄ ካጫረባችሁ እውነት ስኬት ትርጉሙ ምንድን ነው? እኔ እጠይቃለሁ።
አንዳንዶች ዘመንኛዎች የገንዘብ ነጻነት፣ የጊዜ ነጻነት ካለህ ስኬታማ ነህ ይሉኛል። እንዴት ነው የገንዘብ ነጻነት እና የጊዜ ነጻነት የሚኖርህ? (በአንድ ወቅት በኔትወርክ ማርኬቲንግ ውስጥ እሰራ ነበረ ገንዘብ አገኝ ነበረ ግን ነጻ አልነበርኩም። ምናልባት ሕሊና ስለ ነበረኝ መሰለኝ።) ዛሬ ላይ ገንዘብ የምናገኝባቸው መንገዶች ከሕሊና ዳኝነት ነጻ ያደርጉን ይሆን? እያልኩ እጠይቃለሁ። ሶስት እና አራት መቶ ብር ይሸጥ የነበረን ዘይት አንድ ሺ ብር ሸጦ ገንዘብ መሰብሰብ ገንዘብ ቢያስገኝ የገንዘብ ነጻነት ይሰጥ ይሆን? ሕሊና ቢስ ከሆንን አዎ።
ፋርማሲ ከፍተህ ወገንህ በመድሃኒት እጦት ሲማቅቅ የመድኃኒቱ ከገበያ ላይ መጥፋትን አጋጣሚ ተጠቅመህ ከመደርደሪያ ላይ አንስተህ ደብቀህ አጋጣሚውን ተገን አድርገህ ተደራድረህ ዋጋውን ከፍ አድርገህ ስትሸጥ ገንዘብ ልታገኝ ትችላለህ ግን ሕሊና ካለህ የገንዘብ ነጻነት አይኖርህም።
ግብይት ሰጥቶ መቀበል ነው፤ አገልግሎት ወይም እቃ ትሰጣለህ ተመጣጣኝ ገንዘብ ትቀበላለህ። የገንዘብ ነጻነት አገኘን እያሉ የሚደሰኩሩት ቢሮ ከመክፈት ከመደራጀት እና ወገን ከማጭበርበር እና የሌላቸው ገንዘብ ነጥቀው ባዶ እጃቸውን ከማስቀረት በቀር ምንም ሳያደርጉልህ እነርሱ ስለተካኑበት ይበለጽጋሉ አንተ ባለ እዳ እና ጭንቀታም ትሆናለህ።
(በአንድ ወቅት ሰዎች አገኙኝ ሰበኩኝ የገንዘብ ነጻነት እና የጊዜ ነጻነት እፈልግ ስለነበረ ጓጉቼ ሶስት እና አራት ሺ ብር ከፍዬ የተባለውን ስልጠና ወሰድኩ ስልጠናው ስለ ግል ሕይወታቸው ዲስኩር ብቻ ነበረ በእብሪት በትእቢት በማን አለብኝነት የተሞላ ግን ውጤት አልነበረውም። የሚያወሩትን በሕይወትህ ውስጥ መሬት አያወርዱትም ከሰጡህ ተስፋ እና ምኞት ጋር አያገናኙህም። እነርሱ ግን ገንዘብ ያገኛሉ ነጻነቱን ባያገኙትም።) ምን አልባት እንደፈለጉት የሚመዠርጡት ገንዘብ ይኖራቸው ይሆናል። ጥያቄዬ ስልጠና ብቻ ሰው ይቀይራል ወይ? ነው። የገንዘብ እና የጊዜ ነጻነት ይሰጣል ወይ? መማር ሰው ከለወጠ ከአስራ ሁለት እስከ አስራ ስድስት አመት በአማካይ አብዛኛው ባዶ ኪሱን የሚወዛወዝ ወጣት ዕድሜውን በትምህርት እና በስልጠና አሳልፏል። የተባለው የገንዘብ ነጻነት ግን የለም። ታድያ መማር መሰልጠን ስኬታማ አያደርግም ማለት ነው? ሌላኛው ጥያቄዬ ነው።
በኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ስኬታማ የሚያደርጉ አስር ሚስጢሮች ብሎ መጽሐፍ የጻፈ እንጂ "ስኬታማ" የሆነው አስሩም መንገዶች አስሩን ያነበቡ ሰዎች ስኬታማ ሲሆኑ ማየት ከባድ ነው።
ታድያ ስኬታማነት ምንድን ነው? እንዴትስ ስኬታማ ይኮናል? የሁላችሁንም ስኬት አስተያየት እጠብቃለሁ።
ስኬት ዘርፈ ብዙ ነው። በየዘርፉ ስኬታማ የሆናችሁ የሕይወት ልምዳችሁን አጋሩን።
ቢያንስ አንድ ሰው ስኬታማ ነኝ ብሎ ሲያስብ ራሱን እንዲፈትሽልኝ የምፈልገው የግል ሕይወቱ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ሕይወቱን፣ የፋይናንስ አቅሙን እና ምንጩን ሕጋዊ አግባብነቱን፣ አካላዊ ጤንነቱን እና ሕሊናው ንጹህ መሆኑን፣ ወዘተ ግምት ውስጥ እንዲሆን ይፈለጋል።
ለኔ ስኬት ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ሆነው ከዚያ ባሻገር ግን ከደስታህ ይልቅ ለሌሎች ደስታ የምትጥር ከሆነ፣ የሌሎች ሐዘን እና ችግር ወደ ራስህ ተጋብቶ ከጎናቸው ለመፍትሔ መቆም የምትችል ከሆነ፣ ካገኘኸው የዕለት ጉርስ የአመት ልብስ ለሌለው ያለምንም ወረታ መድረስ ስትችል፣ ፍርድ ተጓደለ ድሃ ተበደለ ብለህ የምታስብ የበኩልህንም ጥረት ስታደርግ፣ ደስታህ ሌሎች ሲደሰቱ ከሆነ፣ ከላይ በጥቂቱ ለተዘረዘሩት ችግሮች መንስኤው አንተ ካልሆንክ ወዘተረፈ አንተ ስኬታማ ነህ።
አበቃሁ መድረኩን ለእናንተ ትቼዋለሁ።
ይቆየን።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ