ዓርብ 15 ሜይ 2020

ለምን ትኖራለህ? ወዴት ነህ? ምን ይታይሃል?


ለምን ትኖራለህ
ወዴት ነህ?
ምን ይታይሃል?
          በሳይንሱ ክፍለ ዓለም ስንጓዝ የሰው ልጅ ለመኖር ኑሮን ወይም ሕይወትን ለማሸነፍ በቂም ባይሆን አስፈላጊ የሚሆኑት ምግብ መጠለያ ልብስ ወሳኞች ናቸው ይህንን ለማሟላት ‹‹ጥራህ ግራህ›› ብላ ተብሏልና ይወጣል ይወርዳል ላቡን ያነጠፈጥፋል የሰው የበታችና የበላይ ይሆናል ለመኖር ለብቻውም በሕብረትም ይሁን ብቻ ይለፋል፡፡ ከሳይንሱ ዓለም መለስ ብለን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንመለከትና ወደ ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 4÷4 አካባቢ ስናነብ ‹‹ሰው ከእግዚአብሄር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም …›› የሚል እናገኛለን በዚህም መሠረት ቅድም ከተጠቀሰው በተጨማሪ የእግዚአብሔር ቃል /ቃለ ወንጌል/ ያስፈልገናል/ ለመኖር ማለት ነው፤ ግን ለምን እንኖራለን?

          ለምን እንኖራለን ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ ብዙ ነገሮች በህሊናችን ሊመጣ ይችላል የተወሰኑት ሲመሳሰል የተወሰኑት ይለያያል አንድ ሰው በዚህ ምድር ሲኖር ግማሹ በተድላ በደስታ በድሎት ሌላው ክፍል ደግሞ ከዚያኛው በተቃራኒ ባዶ ቤቱ ውስጥ ተኮራምቶ እግዚአብሔርን እያመሰገነና እያማረረ ይኖራል ሆኖም ግን ይህ ኑሮ ዘለቄታ ያለው ስላልሆነ ፍፃሜ ለሌለውና ሕልፈት ለሌለበት ኑሮ ራሳችንን የምናዘጋጅበት ዓለም ነው ይኸኛው ዓለም /ኑሮ/ እንግዲያውስ እንዲህ ከሆነ ለወዲያኛው ዓለም በእምነት ለምናየው ኑሮ ለመኖር ምን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል?
          ኑሮን ሥናነሳ ከዚህ ቀደም በመኖር ያሳለፉና አሁንም በመኖር ላይ ያሉትን ሰዎች ለማንሳት ግድ ነው ለምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሉቃስ 16÷19 ላይ ድሃው አልአዛርንና ሃብታሙ /ባለጸጋውን/ ነዌን ስንመለከት አልአዛር በዚህ ምድር ሲኖር በመራብ በመጠማት በመታረዝበብዙ ሥቃይና መከራ ነው የኃለኛው /የላይኛው/ ቤቱ ኑሮ ስንመለከት በተቃራኒው በተድላ በደስታ በጥጋብ በአብርሃም እቅፍ ተደስቶ ሲኖር እንመለከታለን ባለጸጋው ነዌ በዚህ ምድር ሲኖር በተድላ በደስታ በምቾት ነበር ኋላ ግን በሐሳር በሥቃይ ሲኖር እንመለከተዋለን ታዲያ ከዚህ እንደምንረዳው ይህ ዓለም ለነገው ኑሮአችን መዘጋጃ መሆኑን እንረዳለን ከዚህ በመነሳት ራሳችንን ስንጠይቅ ራሳችንን ለነገው ኑሮአችንን ስናዘጋጅ ለክብር ነው ለሐሳር የምንኖረውስ ለደስታ ነው ለሐዘን? የምንኖረው ለምንድን ነው?
          ‹‹መልካም ሥራ የክፋ ቀን ስንቅ ነውና›› ራሳችን ለነገ ክብር እናኑር ነገን ተስፋ በማድረግ ዛሬን እንኑር ራሱን ዝቅ ያደረገ ከፍ ይላልና በትህትና በክብር እንኑር በጭንቅና በመከራ ለገነት መንግሥተ ሰማያት እንኑር ‹‹ኃጢአትህንም በጽድቅ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር›› ዳን 4÷27 ይላልና በዚህ ምድር ያጡ የነጡ የተቸገሩትን በመርዳት ለላይኛው ቤት በማዘጋጀት እንኑር፡፡
          ዛሬ ራሳችንን በደንብ በሕይወት ጎዳና እየመራን በንሰሐ እየተመላለስን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርገውን የእግዚአብሔርን ሥጋና ደም እየተመገብን ከኖርን ዮሐ 6÷58 የነገው ጉዞአችን ቤታችን መኖሪያችን ወዴት እንደሆነ ከአሁኑ እናውቃለን፡፡ ዛሬን እስከምንደርስ ጊዜያችን /በዝግጅታችን/ ወዴት ነን?
          በምድራዊ ኑሮአችን ስንኖር ሰላማዊ ነዋሪዎችን ከሆንን ቀንም ሆነ ሌሊት ወደ ሕግ ዘንድ ፍርድ ቤትም ሆነ ፖሊስ ጣቢያ ብንጠራ አንፈራም አናፍርም እንደማይፈረድብን ወደ ወይኒ /እስር ቤት/ እንደማንጣል እናውቃለን በመንፈሳዊው ኑሮአችን የፍጡራኑ ሁሉ ዳኛ እግዚአብሔር በሞት /በምጽአት/ ቢጠራን ወዴት ነን? ምግባራችን ውሎአችን ከወዴት ይመድበን ይሆን? ማቴዎስ 25÷31-46 ያለውን ስናነብ እና ፍርዱን ለራሳችን ሥንሰጥ ‹‹›› ከሚባሉት ነን ወይስ ‹‹ወግዱ›› ከሚባሉት ነን? ወዴት ነን?
          ‹‹ከቃላችን በስተጀርባው የምንኖረው ሕይወታችን የነገው ማንነታችን ‹‹መግለጫ›› ነውና የምንናገር ነገር ግን ምግባር የሌለን ሰዎች ግን ዋጋችንን በአደባባይ ስለምናገኝ ከዛሬ ወዴት እንደሆንን አውቀን የዛሬውን ማንነታችን በማስተካከል ነገ ወዴት ነህ? ለሚለው ጥያቄ በጎው ነገር ሁሉ የእኛ እንዲሆን ልንዘጋጅ ይገባል፡፡ ‹‹እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ ንሰሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንሰሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ›› ዮሐ ራዕ 2÷5 ይላልና ከወዴት እንደወደቅን ከማሰብ ጋር ንሰሐ ልንገባ ይገባል፡፡
          ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ከፍሬአቸው ታውቁአቸዋላችሁ›› ብሎ እንዳስተማረ አባቶች /እናቶች/ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ይታወቃል›› እንዲሉ ሥራችን /ምግባራችን/ ሕይወታችን ስንመለከት ከአምስቱ ሠነፎች ወይም ከአምስቱ ጎበዛዝት ልጃገረዶች እራሳችን እንመድባለን ታዲያ እኛ ከነማን ወገን ነን ከጎበዞቹ ወይም ከሰነፎቹ? በዓይነ ሕሊናችንስ ምን ይታየናል? ‹‹ሰውየው አሉ ዓይኑን ይታመምና በሕክምና የሌላ እንስሳ ኤን /አርቴፊሻል/ ሲገባለት የበግ አልሆን ይልና የድመት አይን ይገባለታል ሃኪሞችም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ምን ይታይሃል ቢሉት አይጥ አለ አሉ›› ታዲያ እኛም ምንም እንኳን ኃጢያተኞች ብንሆን ደካማ ባህር ብንሆንም ከሐጢያት መላቀቅ ጭራሹን ባይቻለን በእግዚአብሔር ቤት በመገኘት ቃሉን በመስማት ንሰሐ እየገባን ለስጋ ወደሙ ልንበቃ ይገባል፤ ኃጢያት እየሰራን ገነት አይታየንምና ከኃጢአት እንራቅ የእግዚአብሄርን ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማልጅነት የቅዱሳን የመላዕክት ተራዳኢነት ተስፋ በማድረግ ገነት መንግስተ ሰማያት ሊታየን ይገባል ስምኦን አረጋዊ ‹‹ዓይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና›› እንዳለ እኛንም የእግዚአብሔር የማዳን ኃይሉ ይታየን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመብርሃን አማላጅነት ከኛ ጋር ይሁን፡፡ ለክብር ለመኖር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ወደ መንግስተ ሰማያት ለመሄድ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ለማየት አይናችን ይገለጥ እግራችን ይራመድ፡፡
አሜን፡፡ ይቆየን!!

1 አስተያየት:

  1. i was always asking my mind why am i living? why am i here? and today i got this website with help of god i understood, thanks may god be with you!!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...