ሐሙስ 14 ሜይ 2020

ዘመድኩን በቀለ: ከራየን ወንዝ ማዶ


ዛሬ ለየት ባለ መልኩ የምንመለከተዉ በልዩ አፃፃፉ እና በብዙ ተከታዮቹ የሚታወቀዉ ስለ ዘመድኩት በቀለ (ዲያቆን/መምህር) ሲሆን እንደሚታወቀዉ በተደጋጋሚ ፌስቡኩን እንደሚዘጋ የሚታወቅ ሲሆን ወደፊትም እንደሚዘጋበትና አገልግሎቱን እንደሚያቋርጥበት ይታወቃል ስለዚህ ሌላ መፍትሔ ማምጣት ግድ ሆኗል፡፡
ራሱ ዘመድኩን እንዲህ ያቀርበዋልና ስሙት፤ ተከተሉት፡፡
         ወደፊት ልንሠራቸው ያቀድናቸውን ዕቅዶች በሙሉ አስፍሬያለሁና ጦማሯን አንብቧት። ለሌሎችም #SHARE በማድረግ አጋሯት።
#ETHIOPIA | ~ እንዴት ናችሁልኝሳ ? ሀገሩ፣ መንደሩ፣ ሰፈሩ፣ ቀዬው ሰላም ነው? እኔማ አምላክ ክብር ይግባው ደህና ነኝ።
ይኸው ፌስቡክ ድራሽ አባቴን ቢያጠፋኝም እኔ ዘመዴ፣ የድንግል አሽከር የማይሰበረውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንደያዝነ፣ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ውበት አጊጠን፣ እንደ መስከረም ወር ጠሐይ ፈክተን፣ በገነት መካከል እንደ ቆመ የወይራ ዛፍ ለምልመን፣ እንደ ኃያሉ አንበሳ እያገሳን፣ እንደ ነብር፣ እንደ አቦ ሸማኔ እየፈጠንነ፣ እንደ ንስር ታድሰን እነሆ በአዲስ ጉልበት፣ በአዲስ ወኔ፣ አለን ነበረን እንል ከነበረው አቅም ላይ እጥፍ ጨምረን፣ እንደ አልማዝ እንደ ዕንቁ እያንጸባረቅን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የፌስቡክን ኳራኒትን ፈጽመን ይኸው ዳግም ተከስተናል። 
እንደተለመደው እንደ አማኝነታችን ስለ ቅድስት የኢትየጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፣ የኢትዮጵያ ዜጋ በመሆናችን ደግሞ ስለ ውቢቷ ሃገራችን መወያየታችንንና መመካከራችንን፣ መሟገት፣ መፋጨታችንንንም አጠንክረን እንቀጥላለን። መፋታት፣ ማፈግፈግ፣ መሸሽ፣ ማምለጥና፣ ማስቀየስም የለም። ሰምና ወርቅ ፈልግ የሚል ጦማር እኔ ጋር አይሠራም። እንደ ሐረር፣ እንደ ሲዳሞ ግሩም ጣዕም ያለው ቡና አስሬ ተለክቶ እንደተለቀመ፣ ታጥቦ ተቀሽሮ፣ ተቆልቶ፣ ተወቅጦ ተፈልቶ እንደወረደ ቡና ጦማሬን ትጠጡት፣ ፉትም ትሉት ዘንድ ከሃገረ ጀርመን፣ ከራየን ወንዝ ማዶ ለእናንተ መቅረቡን ይቀጥላል።

እኔ በሁሉ ነገር ልክ ነኝ ብልም በሁሉ ነገር ልክ ነኝ ማለት ግን አይደለም። ተፈጥሮአዊም አይደለም። እንኳን እኔ ዘመን እና ጊዜ ዕድል ሰጥተውኝ በፌስቡክ ላይ ዊኒጥ ዊኒጥ፣ እምቡር እምቡር የምል ተራና እዚህ ግባ የማልባል መሃይምገደሉ የሆንኩ ሶዬ ይቅርና በብዙ እውቀት የተመሉ፣ ተፕሮፌሰር፣ ተዶክተርነት ማዕረግ የደረሱት እንኳ ምሉዕ አይደሉም። የሰው ምሉዕ፣ የሰው ፍጡም የለም። ሰው ሰው ነው። እናም በሁሉም ነገር ልክ አልሆንም። እንደዚያ ብለው የሚያስቡም ፍፁም ውሸታሞች ናቸው። እኔን ፍፁም አድርገው የሚቆጥሩኝ ሁሉ አጭበርባሪ ጠላቶቼ ጭምር ናቸው። ነገር ግን ከነጉድለቴ፣ ከነ ስህተቴም ቢሆን ለጓደኞቼ፣ በእምነት ለምትመስሉኝ፣ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለምትተሳሰሩኝ ሁሉ እኔው ዘመዴ እሻላችኋለሁ። እኔ እንደመስታወት አገለግላችኋለሁ። መስታወት ለሌላው ውበትን፣ መልክን ያሳያል። የመስታወትን ውበቱን የሚጠብቅለት በመስታወቱ የሚጠቀም ሰው ነው። አትስበሩኝ። ሌላ መስታወት ሳትተኩ አንዷን መስታወታችሁ ላይ ዱላ አታብዙ። ይልቅ መስታወቱ ላይ ያለ ቆሻሻ ካለ ተባብራችሁ አጽዱት። እናም መስታወታችሁን አትስበሩ።
እኔ እንደ ማር ያለ ነኝ። ሰፈፍ የሞላብኝ ማር። ወለላውን ማሬን ለመብላት ከፈለክ ሰፈፉን የግድ ገለል፣ ገፋ፣ ማድረግ አለብህ። ስድብ ነው፣ ቁጣ ነው፣ ፉከራ ነው የምትለውን ሰፈፌን ገፋ አድርገህ ማርማሩን ዝቀህ ብላኝ። እንዳገኘህ ከነ ሰፈፉማ አትዋጠኝ። ደጋግመህ አንብበኝ። ሰፈፉን ወዲያ ገፋ አድርገህ፣ እንትፍ፣ እንትፍ አድርገህ ወለላ ማሩን ብቻ ጠጣው። እንጂ ማር አገኘሁ ብለህ ወደ አፍህ እንዳገኘህ አትሞጅረኝ። አላምጠህ የሚዋጠውን ዋጥ፣ የሚተፋውን ትፋ። እንጂ ዝም ብለህ የዘመዴ ጦማር ወለላ ማር ነው ብለህ አትጎስር። ነግሬሃለሁ።
አሁን በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ እያነበበኝ እንደሆነ እረዳለሁ። ተረድቻለሁም። ይሄ ሁሉ የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ እወቅ ተረዳ። አንዳንዶች የዘመድኩን ተከታታዮች የበዙት ስለሚሳደብ ነው። ስለሚቆጣ ነው። ዘረኛ ስለሆነ ነው ይሉኛል። እስቲ እንደኔ ተሳድባችሁ፣ እንደ እኔ ተቆጥታችሁ፣ እንደ እኔ ዘረኛ ሆናችሁ ህዝብን ለመሰብሰብ ሞክሩ። እስቲ ሠርታችሁ አሳዩኝ። እኔ ዘመዴ እንደ እርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይነቴ፣ አማኝነቴ ብዙ ሚልየን የተዋሕዶ ልጆች ብግልጥም በሽፍንፍን፣ በክንብንብ፣ ከመጋረጃ ጀርባ ተደብቀውም ቢሆን ያነቡኛል። ሼር አያድርጉ፣ አስተያየት አይስጡ እንጂ ድብን አድርገው ያነቡኛል። በሃገር ጉዳይ በመጣፌ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከቤተ መንግሥት እስከ ቀበሌ ሊቀመንበር ድረስ፣ እስላም ክርስቲያን ሳይሉ ይመለከቱኛል። እናም ለዚህ ሁሉ ተመልካች የሚመጥን አቀራረብ ይዤ መቅረብ ደግሞ የግድ ይለኛል። የግድም ነው።
በቀጣይ በአየር ላይ ወሬ፣ ዛቻ፣ ፉከራ፣ ቀረርቶ፣ ሽለላ ብቻ አይኖርም። እሱ እንዳለ ሆኖ መጠኑን እየቀነስኩ መሬት ላይ ወርደን ተግባራዊ ሥራ መጀመር እንዳለብን ወስኛለሁ። ደግሞ የግድ ነው። ይሄን ሁሉ የሰው ሃብትም ማባከን የለብኝም። ይህን አድርግ ስለው የሚያደርግ፣ ንስሐ ግባ፣ ቁረብ፣ አስቀድስ፣ ጹም ጸልይ ስለው እሺ፣ በጄ የሚለኝ ህዝብ ካለኝ በቀጥታ ወደ ሥራ፣ ወደሚታይ፣ ወደ ሚዳሰስ ተግባር ማሰማራት አለብኝ። አዎ እንዲያ ማድረግ አለብኝ። እናደርገዋለንም።
ደግሞስ ወሬ ብቻውን ምን ያደርጋል? ሥራም እኮ ያስፈልጋል። ስንት ዓመት ፌስቡክ ላይ አወራን፣ ተቀደድን፣ ፎከርን፣ አሽካካን። አሁን ደግሞ ፌስቡክን ራሱን ተአምር እንሥራበት እንጂ። እናም 600 40 ሰው የጎደለውን ይህን የፌስቡክ ቤተሰቤን ይዤማ ወደ መሬት መውረድ አለብኝ። ለኢትዮጵያ ሃገሬም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖቴም ቋሚ ለትውልድ የሚሸጋገር ሃውልት ተክዬ ማለፍም አለብኝ። የግድም ነው። ከእግዚአብሔርም ጋር እናሳካዋለን። በድንግል በወላዲተ አምላክ ምልጃ፣ በቅዱሳኑ ጸሎትም እናሳካዋለን።
የፌስቡክ ተከታታዮቼ ከበቂ በላይ ናቸው። ለወሬ ከሚከታተሉኝ ውስጥ 50 ሺው እንኳ ሌላ ሌላ ቢሆን 500 ሺው ኦርቶዶክሳዊ የተዋሕዶ ልጅ ነው ብዬ አስባለሁ። ይሄን ቁጥር ይዞ የሚከታተለኝ ሁሉ ወዳጄ ነው፣ ጦማሬ ይዋጥለታል ማለትም አይደለም። ሆኖም ግን ይሄንን ቁጥር የያዘውን ህዝብ በጸሎትም ሆነ በምክር አለዝቦ ወደ ተቀደሰው ዓላማና ዕቅዳችን ማምጣት ግን ይቻላል። ደግሞም 10 ምርጥ፣ 1 የምርጦች ምርጥ ከተገኙ በቂዎች ናቸው። ቡድኑ ውጤታማ የሚሆነው በቲ ፎዞ ጩኸት ብቻም አይደለም። ከዚህም በላይ ሌላው ቢቀር 12 የተለዩ በፈጣሪ የተመረጡ ምርጥ ሰዎች ከተገኙም በቂ ነው። አሸናፊነት በበዛ እኮ አይደለም።
የቴሌግራም ግሩፑ 200 ህዝብ ባላይ እንዳይሳተፍ በራሱ በቴሌግራም ካምፓኒ የተገደበ ነው። ዓመት ሁለት ዓመት ይፈጅ የነበረውን እሱን ደግሞ 36 ሰዓታት ውስጥ አሳክተን ዓለሙን ሁሉ ጉድ አስብለናል። አሁን ደግሞ ቴሌግራም ቻናላችንን እንከፍትና ዓለምን ጉድ እናሰኛለን። በዓለም ላይ ብዙ የቴሌግራም ቻናል ተከታታይ ያለው ተቋም በሃገረ ህንድ የሚገኘውና “HINDI HD MOVIES” በመባል የሚታወቅ ተቋም እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንድ ነጥብ ምናምን ቢልዮን ህዝብ ባለባት በሃገር ህንድ 4 ሚልየን ተከታታይ ማፍራት ማለት በጣም ትንሽ ነው።
እናም እኛ ይሄን ሪከርድ ለመስበር እንሠራለን ማለት ነው። ቻናላችንን እናስተዋውቅና ኦርቶዶክሳዊ የተዋሕዶ ልጅ የሆነ በሙሉ ለሥራ ይገባበታል። ሌላውም ቢሆን ለትዝብት፣ ለወሬ ቢገባና ቢከታተለው ግድ የለንም። የተደበቀ ሴራ፣ ምስጢራዊ እንቅስቃሴም ስለማናደርግ ግድ አይሰጠኝም። ሁሉ የሚያውቀው እንደ ፀሐይ ብሩህ የሆነ ማኅበር ስለሆነ የምናቋቁመው ግድ አይሰጠንም። እኛ ግን በቴሌግራም ቻናል እንሰባሰባለን። አንድ ሚልየን የተዋሕዶ ልጆች በቴሌግራም ተሰባስበን በትንሹ መቶ መቶ ብር ብናዋጣ እንኳ በአንድ ጊዜ በቀላሉ አንድ መቶ ሚልየን ብር አገኘን ማለት ነው። ይሄ በትንሹ ነው። ዶላርና ዩሮ ሲመነዘር ደግሞ አስቡት። 10 መቶ ሚልዮን የሚሰጠውን ደግሞ አስቡት።
አስራታችንን ለቤተ ክርስቲያን ከትርፋችን ደግሞ ለማኅበሩ ገቢ እያደረግን፣ እያዋጣን የአብነት ትምህርት ቤቶቻችንንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ደጉመን፣ ከችግር፣ ከረሃብና ከበሽታ አላቀቅን ማለት ነው። እናም በቀጣይ የቴሌግራም ቻናላችንን አስተዋውቃችሁና የተገደበ የሰው ቁጥር ስለሌለው፣ በዚያ ላይ ከእኔና ከተመረጡ ሰዎች በቀር ሁሉም ሰው ስለማያወራበት ወደዚያ እንሸጋገራለን። የህንድንም የአፍሪካና የአውሮጳ የአሜሪካ የእስያና የአረቡንም ዓለም የቴሌግራም ቻናል ሪከርድ እንበጣጥሳለን። ደግሞ ለሪከርድ።
ማኅበራችን ዛሬ 8 ሰዓት ላይ እኔም በስልክ በቴሌ ኮንፈረንስ በምገኝበት በጸሎት የሚባርኩ አባት ባሉበት፣ የሕግ ባለሙያዎቹ ያዘጋጁት መተዳደሪያ ደንብ በአዲስ አበባ ከተማ ለመጨረሻ ውይይት ቀርቦ ፍጻሜውን ያገኛል። ከዚያ ወደ ቤተ ክህነቱም፣ ወደ ቤተ መንግሥቱም ቀርቦ ሕጋዊነቱን ያስጸድቃል። ከዚያ በቀጥታ ወደ ሥራ ይገባል።
የማኅበሩ የቦርድ አባላት መረጣም እየተካሄደ ነው። የማኅበሩ ቢሮ በጎአድራጊዎች ከህንጻቸው ላይ አንዲት ክፍል ይሰጡን ዘንድ ድንጋይ ተሸክሜ ገና ለልመና ብቅ እላለሁ። አይ ዕዳዬ። እስቲ እናንተም በልመና አግዙኝ። ህንጻ ሠርቶ አንድ ክፍል ለጊዜው ሊለግሰን የሚችል የተዋሕዶ ልጅ እያግባባችሁ፣ እያሳሰባችሁ ጠብቁኝ። ማዕከላዊ ቦታ ላይ፣ ለመኪና ፓርኪንግ ምቹ የሆነ ሥፍራ ላይ ህንፃ ያላቸው ዘመድ ጓደኛ ያላችሁ ሰዎች ዓላማችንን ነግራችሁ ጠይቋቸው። አትፍሩ። ደግሞ ለመጠየቅ። ወይ እሺ፣ ወይ እንቢ ነው። ከሰጠን እሰየው፣ ካልሰጠን ይቀራል። አትፍሩ ጠይቁዋቸው።
የቢልየን ብር አሴት ያላቸው ባለሃብቶች ደውለውልኛል። የአብነት ትምህርት ቤትና የተቸገሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን ላይ ልንሠራ ላሰብነው ፕሮጀክት ከገንዘብ እስከ ህይወት ለመስጠት ቁርጠኛም ፈቃደኛም መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል። ከአእምሮ በላይ የሆነና ፈጽሞ የማልጠብቃቸው ሰዎች ከምር ደውለው አውርተውኛል። በአውሮጳ እንደ ልዑል አስፋወሰን አሥራተ ካሣን የመሰሉ በአውሮጳ መንግሥታት ዘንድ የተከበሩ ሰው ደውለው ፈቃደኝነታቸውን አረጋግጠውልኛል። እንደ እውቁ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰዓሊ፣ የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በስማቸው የተሰየመላቸው የክቡር ሰዓሊ አለፈለገሰላም ልጅ በጀርመን ከፍ ያለ ስፍራ ያሉት ሲስተር መሠረት አለፈለገሰላም ደውለው በገንዘብም፣ በእውቀትም አለሁ በለውኛል። አትሌቶቹ አረንጓዴ ጎርፎቹ ወደ ማኅበሩ ጎርፈዋል። ከሊቃነ ጳጳሳት አለን ያሉ አሉ። የአይቲ ባለሙያዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ሃኪሞችና ሌሎች ባለሙያዎች ፈቃደኝነታቸውን ገልጸውልናል። የማተሚያ ቤት ባለንብረቶች እዘዙን ብለዋል። ነገርየውማ ትእዛዙ ከላይ ነው። ሁላችሁም ተዘጋጁ።
በተረፈ መጣሁ። መጣሁ ይኸው። ሰፈር መንደራችንን ሞቅ፣ ደመቅ፣ ሸብረቅ ልናደርገው መጣሁ። ሞቅ ነው የምናደርገው። ስለ ሁሉም ነገር እውነት እውነቷን፣ ሃቅ ሃቋን ብቻ እንነጋገራለን። እንወያያለን። ነጭ ነጯን ብቻ ቁጭ ቁጭ እናደርጋለን። ፌስቡክ ሲበሰጭብን ይዘጋናል። እስኪከፍተን፣ ከእስራት እስኪፈታን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም። ደግሞ በቴሌግራም ከች እንላለን። ሰይጣን አንዷን በር ቢዘጋ በሰይጣን በተዘጋው በር ደጃፍ ቆመን ስናለቃቅስ አንውልም። ያልተዘጉ በእግዚአብሔር ወለል ብለው የተከፈቱ 99 በሮች ስላሉ በዚያ ደግሞ እንገባለን።
ዳይ አዳሜ ወደ ሥራ  !!  ወደ ሥራ ተንቀሳቀስ  !!
 በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ።ኤር 1323
ሻሎም !   ሰላም ! 

ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ግንቦት 5/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...