በዓላትና አከባበራቸዉ
ወደ አዲስ ዓለም ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ደብረ
ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ለማቅናት 12፡00 ሰዐት ከመኖሪያ ሰፈሬ የመገናኛ ታክሲ በመያዝ ጉዞዬን ከጀመርኩ ከ1፡15 ሰዓት
በኃላ ጦርኃያሎች ደረስኩ፤ ከጦር ኃይሎች 18 በመባል ወደ ሚጠራዉ ሰፈር በመጓዝ ላይ እያለሁ አደባባዩን ሳልሻገር መዳረሻዉ ላይ
ወቅቱ የጥምቀት ወቅት ቀኑም የጥምቀት ዋዜማ (ከተራ) ነበርና፡፡ በዚህ ዘመን ወጣቱ ትዉልድ የሃይማኖተኝነት (በዓልን የማክበር
)ሞራሉ የተነቃቃበት ወቅት ነዉና የተለያዩ ባነሮችን፣ሰንደቅ ዓላማዎችን፣የታቦቱ መዉጫ መግቢያ ላይ ሻማዎችን ማብራት ፣ የተለያዩ
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችንና መፈክሮችን አሳትሞ ቲሸርቶችን መልበስ የጥምቀት በዓል መድረሱን ማብሰሪያ ምልክቶች ናቸዉ፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማክበር ከንጋት ጀምሮረዉ መንገዱን
እያፀዱና እያሸበረቁ ከሚገኙት መካከል አምስት የማይሞሉት በነጭ ቀለም
የቀለበት መንገድ ማካፈያዉ ላይ የተለያዩ ጥቅሶችን እየፃፉ ተመለከትኩ ጥቅሶቹም እንዲህ የሚሉ ይገኙበታል ፤ “ያለ ወላዲተ አምላክ
አማላጅነት ዓለም አይድንም” ፣ “እመን እንጂ አትፍራ” ፣ “የፈራ ይመለስ” ፣ ….. በሃይማኖቱ ጥላ ስር ላለነዉ አዎ እጅግ በጣም
ጥሩ ነዉ፡፡ መቸስ በዚህ ዓለም ስንኖር ሁላችን በመልክ እንደመለያየታችን በባህሪ ፣ በአስተሳሰብ፣በሃይማኖት፣በህይወት ፍልስፍናችን፣
በትዕግስታችን …. ወዘተ ልዩነት እንዳለብን የሚዘነጋ አይደለም፡፡ይልቁንም
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሃይማኖት ዙሪያ ምን ዓይነት ችግሮች እየተፈጠሩ
እንደሆነ የምንዘነጋዉ አይመስለኝም፡፡ይባስ ብሎ በወጣቱ ላይ የጥምቀት ወቅት ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ምን ዓይነት ጠባሳ ጥሎ እንዳለፈ
የቅርብ ዓመታት ትዝታችን ነዉ፤ጥቅስም ካየን “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች” የሚለዉ በመንግስት በኩል (ሥልጣን ላይ ከነበሩ
ግለሰቦች ) ሥልጣናቸዉን ተገን በማድረግ ምዕመኑን፣ የሃይማኖት አባቶችን ምን ያህል ሲዘልፉ፣ ሲያስፈራሩ፣ሌላም ሌላም ሲያደርጉ
እንደነበረ ከህሊናችን የሚጠፋ አይደለም፡፡ ታዲያ ዛሬም ምንም እንኳን ሃይማኖታችን የማያሳፍር የተናገርነዉ ከእዉነት ያልራቀና ዉሸት
የሌለበት ቢሆንም አካሄዳችን ግን ጥንቃቄ የተሞላዉና ብልህነት ያልጎደለዉ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡(ምነዉ ቢሉ ሃይማኖተኝነት
አክራሪነት፣ አሸባሪነት፣… የሚሉ ስያሜን ያሰጣልና) እንደ ርግብ
የዋሆች እንደ እባብ ብልሆች ሁኑ ይላልና መፅሐፍ፤
ከተፃፈዉ ጥቅስ እና የተፃፈበትን ስፍራ ሳይ ስሜትና
ሃይለኝነት ነዉ ወይንስ የሃይማኖት ጥንካሬያቸዉን ያሳያል የሚል ጥያቄ አጫረብኝ በርግጠኝነት ልናገር የምችለዉ ማንም ሰዉ የጥምቀትን
በዓል በሥጋ ፈረንጆች እንደሚያከብሯቸዉ የተለያዩ በዓላትን እንደማናስብና እንደማናከብር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እዉነትም እንደዚህ
የምናከብር ከሆነ ዙሪያችንን መቃኘት አለብን ጥቅሱን የፃፍንበት መንገድ ምንም እንኳን የታቦት መዉጫ መግቢያ ቢሆንም ቅሉ በቅርበት ግን “መስጂድ” አለ በሰፈሩ ያሉትም
የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸዉ፤ (ይህን ስል ሙስሊም ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያንን በማነፅ ሳይቀር ይተባበሩ እንደ ነበር መዘንጋትም
የለብንም ትናንትም ዛሬም ነገም ወንድማማችነታችን ይቀጥላል አንዳንዶችም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ቤተክርስቲያን የሚያቃጥሉ ክርስትናን በማሳደድ እና ምዕመናንን አሳዶ በማጥፋት ፅድቅ የሚገኛ የሚመስላቸዉ አሉ) ሆኖም ግን
ሙስሊም ወንድሞቻችን ይህንን ጥቅስ ሲወጡ ሲገቡ ሲያዩት በደስታ ይቀበሉታል፣ያዩታል፣ያነቡታል፣ደግ አደረጉ እንኳን ፃፉት ይላሉ?
እንጃ፤ እኛስ የፃፍነዉን ቢያጠፉት በፀጋ እንቀበለዋለን? መቻቻል የተሞላባት ሃገር ተብላ ብትወደስ እንኳን ይህንን ያህል እንቻቻላለን
? መቻቻል እስከ ምን? ”ሃይማኖት የግል አገር የጋራ” ተብሎ እንደሚነገር መዘንጋት ያለብንም አይመስለኝም፤ይህ እንዲህ ካለ ታዲያ
በጋራ አገር ላይ ዛሬ ለበዓል ሰቅለነዉ ነገ የማናወርደዉን ነገር ቋሚ ነገር ላይ መፃፍ ነገር መፈለግ አያስመስልብንም? ጥበብስ
አልጎደለዉም? የዋህነት ነዉ ወይስ ልጅነት (አለመብሰል) ይሆን?(ልጅነት ከሆነ ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት አባቶችን እናማክር
የዋህነት ከሆነ ብልህነትን እናክልበት)፤አንድ ሞኝ የተከለዉን ጦር ብዙ ሰዉ አይነቅለዉም ይባል የለ? ልብ እንበል፡፡
ስለበዓል ካነሳን ስለክርስቲያናዊ በዓል አከባበር
አንስተን ማለፉ መልካም ይመስለኛል፤ እንግዲህ በዓል ስንል የደስታ/የዕረፍት/ቀን ማለት ነዉ፡፡ በሳምንት በወር በዓመት የሚከበር
ሲሆን ይኸዉም የበዓሉን ምክንያት በማሰብ በእልልታና በጭብጨባ በዘፈንና በዝማሬ ገበሬ ከመቆፈር የቤት ሰራተኛ ከመፍጨት የሚያርፍበት
ዕለት ነዉ፡፡ምንም እንኳን ትርጉሙ እንዲህ ቢሆንም በዓልን ስናከብር የምናጓድለዉና የምናሟላዉ በስርዓት የምንሆንበት ከሥርዓት
/ትዉፊት/ ዉጭ የምንሆንበት ይኖራል፡፡ በዓላት የተደነገጉት እና የተሰሩት እንዲሁ ለከንቱ አይደለም በበዓሉ ዕለት ከሚከበረዉ ጉዳይ
ጋር ህይወታችን ቁርኝት ቢኖረዉ እንጂ (ልደትን ስናከብር ሰዉ አምላክ አምላክ ሰዉ የሆነበትና ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል በማለት
ሱባኤ ገብተዉ የጠበቁት አምላክ ስለ እዳ በደላችን በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ የተወለደበትን የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ
ለማሰብ ነዉ፤ጥምቀትንም ያነሳን እንደሆነ እንዲሁ መድህነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዉና በእግዚአብሔር መካከል የነበረዉን የፀብ
ግድግዳ ለማፈረስ በሰዉ ልጆች ላይ በጠላት ዲያቢሎስ አማካይነት የተፃፈዉን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ በማዕከለ ዮርዳኖስ የተጠመቀዉን
የጥምቀት ስርአት ለማሰብ ነዉ፤ ትንሳኤም ሆነ ሌሎችም እንዲህ ከመዳን ጋር ተያያዥነት ያለዉ ምሥጢር አላቸዉ እንዲሁ በከንቱ የተፈጠሩና
ለመብላትና ለመጠታት ሆዳችን እንዲሞላ ደረታችን እንዲቀላ የተሰሩ አይደሉም፡፡ )በህይወታችንም ለዉጥ ያመጡ ዘንድ እንጂ፡፡
በበዓላት ዕለት ለምሳሌ ስግደት የለም፣ ክስና/ፍርድ አይካሄድም፣ የሥጋ ስራም አይከናወንም፣ በራስ ስሜት መጓዝ ፈፅሞ የተከለከለ
ነዉ፡፡ ዉሎአችንም በቤተክርስቲያን እለቱን እያሰብንና የሚበላ የሚጠጣዉን የሚላስ የሚቀመስ ከሌላቸዉ አጉራሽ ካጡ ጋር በደስታ ያለሐዘን
በነፃነት ልናከብር ልናስብም ሳንጨነቅ ሳናስጨንቅ መዋል አለብን፤ ቢሆንም ይመረጣል፡፡ደስታችንም ገደብ ያለዉና ሥርዓት ያለዉ መሆን
አለበት፡፡ታቦት አንግሶ በዓል አክብሮ ለመመለስ ተነስተን እግዚአብሔርን አስከፍተን፡ሥጋችንን አድክመን መምጣት የለብንም፡፡
በዓል ዛሬ የተጀመረ አይደለም በኦሪት ጊዜም የነበረ
እንጂ:- “ለእስራኤል
ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው።” ዘሌዋዉያን 23፡2
የበዓሉ ደስታና ምሥጢር በእኛ ሊገለጥ ይገባል
በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን በአለባበሳችን፣ በዕረፍታችን፣ በአንድነታችን … ሊገለጥ ይገባል፤በዓል የመንግስት ሰማያት ምሳሌ ነዉና፡፡የበዓል
ዉሎአችን የእግዚአብሔርን የክብር ጊዜ የሚቀንስ የሚጋፋ ትርጉም አልባ የሚያደርግ መሆን የለበትም፡፡በአገራችን የበአል አከባበር
ርቀት ሳይበግረዉ ቋንቋ እና ባህል የመሬት አቀማመጥ የአየር ንብረት ሳይለየዉ ምሥጢራቸዉ እና ሥርአታቸዉ ባህላቸዉ አንድ ነዉ፡፡እኛ
ግን ዛሬ ዛሬ ስንታይ ትናንት በዓላትን ከሚያከብሩት አባቶቻችን ጋር ተመሳሳይነት የለንም ዥንጉርጉር ብለናል፤ አንድነታችንም ጠፍቷል
፣ተከፋፍለናል፣እኔ የአጵሎስ ነኝ እኔ የኬፋ ነኝ ማለት ይታይብናልና እግዚአብሔር አምላክ አንድነታችንን ይመልስልን፡፡
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰን!!!!!
ጉዞዬን ወደ አዲስ ዓለም አቀናሁ ትራንስፖርቱ
ይፈጥናል 42 ኪ.ሜትሯን ፉት አድርጓት ደርሰናል፤
አዲስ ዓለምን ለማስተዋወቅ የዛሬ ሁለት ዓመት
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስፍራዉ ስጓዝ ከገጠመኝ ገጠመኝ ብጀምር ይሻል ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዓለም አዲስ ምድር ፀጥ ረጭ ብላለች መስከረም
20 ቀን 2004 ዓ.ም. 09፡07 ሰዓት ከኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ ሲነሱ በወለጋ ወይም በአምቦ መስመር 42/43 ኪ.ሜትር
ከተጓዙ በኋላ የአዲስ ዓለምን የገጠር ከተማ ያገኛሉ መግቢያዉ ላይ በስተግራ 10 እና 15 ደቂቃ በእግር ከተጓዙ በኋላ የሚገኘዉ
የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም (ዳግማዊት)ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ይህ ገዳም ስፍራዉ ላይ እንደ ደረሱ
መች እንደተመሰረተ ሥንት ዓመት እንደኖረ የተፃፈ የሚያነቡት የቆመ የምትጠይቁት ዙሪያዉን ከከበቡት አፀዶች በስተቀር ሰዉ ማግኘት
ያዳግታል፤( ልብ አርጉልኝ ቀኑ የእመቤታችን ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት በግሸን የሚከበርበት ዋዜማ ላይ ነን) ነገር ግን ይህንን
ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ተጠግተዉ የተሳሉት የአንበሳ፣የዛፍና የሐረግ ስዕሎች የቤተክርስቲያኑ በርና (ሰባት በሮች አሉት)መስኮቶች
ጥንታዊነቱን ይናገራሉ፡፡
ይህ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን አይደለም በዛሬዉ ዕለት
መቼም መች ቢሆን እንግዶቹን ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ የእንግዳ ማረፊያ መጠለያ ዙሪያዉን አለዉ፡፡
የሚያሳዝነዉ ነገር ይህች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን
ይህን ሁሉ ዝግጅት አድርጋ ስትጠብቅ በዚህ ታላቅ በዓል ዋዜማ ግቢዉ ፀጥ ረጭ ጭር ከማለት ባሻገር እንኳን ደህና መጡ ባይ የአገሬዉ
ሰዉ /አገልጋይ ካህናት ዲያቆናት/ አለመገኘቱ ነበር፡፡ለእግዚአብሔር የሚሆን ሰዉ ቢጠፋ ፍጥረቱ የሆኑ ጦጣዎች ሲያዩ እና ከፊትዎት
ሲዘሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ የሚሉ ይመስላል፡፡
አዲስ
ዓለም የሚገኘዉ በኦሮሚያ ክልል በኢጀሬ ወረዳ ዉስጥ ነዉ፡፡ይህ ጥንታዊ ቤተክርስቲያንም ከተማዋን መጠሪያ ከተማዋም ቤተክርስቲያኑን
መጠሪያ አድርጎ መኖር ከጀመሩ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡አዲስ ዓለም
ማርያም አዲስ ዓለም ከተማ ረጅም ዓመታትን ምንም ብታስቆጥር ምንም መስመር ላይ የተቆረቆረች ብትሆን ከገጠር ከተማነት የዘለለ ሥልጣኔ
አይታይባትም ዛሬም እንደትናንቱ ደረቷን አሥጥታ መንገዷን ዘርግታ ለሚመጣዉና ለሚሄደዉ መሸጋገሪያ ሆናለች፡፡ምናልባት ወደፊት በቅርብ
ጊዜ የክልሉ መንግስትም ሆነ የወረዳዉ አስተዳደር ሊያለማት ቁርጠኝነቱን ካሳየ ለማደግ ለመልማት እጇን የማትነሳ ፊቷን የማትነፍግ
ለምለም ምድር ናት፡፡ህዝቦቿ የዋህ ምድሯም ለምለም አዲስ ዓለም ከተማ፡፡ ይህ ትናንት በትዝታ ነበር ያለመረጃ፤ ዛሬ ደግሞ በመረጃ
አዲስ ዓለምን ይዘን እንቀርባለን፡፡ ይጠብቁን!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ