አያ ሆ÷ ሆ÷ ማታ ነው ድሌ፣
ድሌ ማታ ነው ድሌ
እያሉ መጨፈር ከዘመናት ጀምሮ ዛሬ ድረስ የድል አድራጎቶችን ጭፈራ ነው። ትዝ ይለኛል ልጅ ሳለሁ ክረምት ሲገባ ሰፈር
በሚገኙት ትናንሽ ሜዳዎች ጭቃ በጭቃ በሆነች በካልሲ በተጠቀለለች ፌስታሎች ውስጧን በሞሏት የጨርቅ ኳስ ጭቃ መስለን ጭቃ አክለን፣ ጭቃ በጭቃ በሆነ ሜዳ ተጫውተን አመሻሽ ላይ ድል ቀንቶን የተወራረድንበትን
ቆርኪ በልተን ከሲጋራ ማሸጊያ የውስጠኛው ክፍል (አልሙንየም) የተሰራ ዋንጫ ተሸልመን ሰፈሩን «አያ ሆ ሆ ማታ ነው ድሌ ፣……» በሚለው ጭፈራ
ስንቀውጠው ቡድናችንን ጮቤ ስናስረግጥ ተጋጣሚ ቡድናችንን አንገት ስናስደፋና ስናሸማቅቅ፣ የተሸነፍን ቀን ደግሞ በለስ የቀናቸው
እንዲሁ በተራቸው ሲያሸማቅቁን ፣ ለሌላኛው ቀን ውድድር በድል ማግስት ባሉት ቀናት በዚያኔው የእግር ኳስ ሜዳ ቋንቋ ኮንዲሽን(condition) እየተባለ የምናገኛትን ቅራሪ ከተገኘም
ጠላ ከመጠጣት ታቅበን የቡድናችንን ድል ለማስጠበቅ ከተቻለም ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ ተመካክረን፣ ስፖርት ሰረተን፣ ተጨማሪ ስልጠና
ከኛ ከፍ በሚሉ ወንደሞቻችን ወስደን ፣ከዚያች የጨርቅ ኳስ ሻል ያለ ኳስ ለመስራት አሮጌ አንድ እግር ካልሲ ቃል ተገብቶልን፣ ድጋሚ
ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ በልበ ሙሉነት እንገባ ነበር። በቃ የትናንት ነገር በሙሉ ነበር አይደል የሚባለው የታሪክ መኅደር ላይ ሰፍሮ
ታሪክ እሰኪሆን የሚገርመው ነገር «ነበር» የሚለው ነገር በኛ ዘመን ብቻ ሳይሆን በኛም ሰፈር ይሁን ከኛ ሠፈር ወጭ አገርም እንበል
ጥሎብን የጨወታ ነገር ሲነሳ እግር ኳስ አልተሳካልንም እንዲያውም አሁን በቅርቡ በተካሄደው ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አገራችን ኢትዮጵያ
ያለፈችው ከ30 ዓመት በኃላ በመሆኑ ደስታችን የዓለም ዋንጫ የበላን መስሎብን ነበር፣ የዚህ ደስታ ምሥጢሩ ይህ ሁሉ ወጣት እንደ
እኔ የልጅነት ጊዜ በሰፈር ጫወታ ከሲጋራ ወረቀት ከተሰራ ዋንጫ በቀር አንስቶ ስለማያውቅ ነው። ግዴለም አይሳካ የዋንጫ ነገር እድላችን
ወይም ዕዳ ክፍላችን አይደለም ምናልባት ከኛ ሰፈር ቢቀር ከሌላ ሰፈር እርሱም ይቅር ከኛ አገር ቢጠፋ ከሌላ አገር ከአማራ ከኦሮሞው
ከጉራጌው ከደቡብ ከትግሬው ከሰፈር አንዳንድ ሰው ያቺን የጨርቅ ኳስ ሲረግጥና ሲራገጥ ዋንጫ ሲያነሳ ሲጥል፣ ሲጨዋት ሲያጫወት፣
የመስመር የመሀል ዳኛ ሆኖ ሲዳኝ ካደገው ትውልድ ብዙ አይደለም ይኸንን 30 ዓመት ሙሉ አስራ አንደ ሰው ይጥፋ? ምናለ የሰው ልጅ
መገኛ ከምንሆንና የቺው ሉሲም የኛ አገር ሰው ሆና ከምታስቅቀን፣ሄዳ ቀረች ብለን ከምታጨናንቀን የእግር ኳስ አገር በሆንን። እንደው ዝም ብለን የአውሮፓና የእንግሊዝ፣ የአርሰናልና የማንችስተር
ደጋፊ አገር እንሁን? ኧረ ምነዉ ፈጣሪስ ምነው ዝም አለን? ቸሩ መድኃኒአለም የነገሩህን የማትረሳ የለመኑንህ የማትነሳ ብዙ አይደለም
እባክህ ለአፍሪካ ዋንጫ አስራ አንድ ሰው ሥጠንና ተጠባባቂ ይቆይ ግደለም ከዛም የአፍሪካን ዋንጫ በልተን ከድል ማግስት ስለትህን
አንድ ባኮ ሻማ ለማምጣት አብቃን። ጎበዝ ስለትህን ይሰማህ በሉኝ። አሜን ይስማን።
ወደ ባለፈው ድላችን ወደ «ጀግኖች» ልጆቻችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዝና፣ ከ30 ዓመት በኃላ እነ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ደምሴ ዳምጤ፣...
ኧረ ስንቱ ደግሞ የናፈቁትን ድልና ደስታ ሳያዩት እኛ በስታድዮም ተገኝተን በቴሌቪዥን ተመልክተው ደስ እንዲለን ያደረጉት የጀግኖቹ
ታሪክ አይረሴ ነው። አዳነ ግርማንና ሳልሃዲን ሰይድ እግዜር ይስጣቸው እነርሱ ባይፈጠሩ በዚያች የጨርቅ ኳስ ተጫውተው ባያድጉ ለዚህ
ታላቅ ብሔራዊ ቡድን ባይታጩ ምን ይዉጠን ነበር? ኧረ የሆነው ሆነና የአፍሪካው ዋንጫ እንዴት ሆነ? ቀኑ ቀርቧል አሁንም የድል
ማግስቱን ደስታ እንጂ ከድል በኋላ ያለውን የአፍሪካ ዋንጫን የተመለከተ ዝግጅትም ይሁን የወዳጅነት ጨዋታ የለም። እነ ናይጄሪያን
የመሰሉ የኛ ተጋጣሚዎች ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትም የወዳጅነት ግጥሚያም አውሮፓ እንዲገቡ እስከ ዋንጫውም በዚያው ዝግጅት እንደሚያደርጉም
ሚዲያዎቻችን ያለ መታመኑ ጠዋት ማታ እየዘገቡ ይገኛሉ የኛዎቹስ የት ነው ያሉት? እንደሚባለው (ወሬ አርጎ ያስቀረውና) እንደ ሴካፋው
ዋንጫ እንደ ጨርቅ ኳስ እንኳን ከቅራሪና ጠላ መታቀብ አቅቷቸዋል የሚባለው እውነት ይሆን? ኮንዲሽን፣ትሬንግ፣ የወንድማማችነት ግጥሚያ
ምናምን ቀረ እንዴ? እንደከዚህ በፊቱ ወር ሳምንታት ሲቀሩት ይሆን ብሔራዊ ቡዱኑ ተሰባስቦ ተለማምዶ ለድል የሚበቃው? ሰዎች ይህ
ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራና ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብቻ ተሯርጦ አሰልጥኖ ባለሃብቶች
ከአሸነፋችሁ ብለው ቃል ገብተው ሸልመዉና ጋብዘው ብቻ ታሪክ ይቀየር፣ ድል ይገኝ ይሆን? አይታየኝም።
ለኢትዮጵያ ህዝብ 30 ዓመት ጠብቆ በ31ኛ
ዓመቱ ለዋንጫ ማጣሪያ ማለፍ ብቻ በቂ ድል አይደለም፤ ደስታችን በዚህ መቆም የለበትም። ትልቅ የታሪክ የቤት ሥራ (የአፍሪካ ዋንጫን)
አስቀምጠን መጠቶ ቤት ልንገኝ የተጣለብን ኃላፊነት አይፈቅድም ቆይ ምን ተገኘና ነው ስፖርተኛ መጠጥ ጠጪ፣ሰካራም የሚሆን እንዴትስ
ሆኖ ነው የ80 ሚሊየን ህዝብ አደራ ተሸክሞ ሲጠጣ የሚመሸው እንዴትስ ነው መጠጥ ቤት የሚገባው? ለመሆኑ ጉሮሮአችን እንኳን አልኮል
ሊንቆረቆርበትና ልንሰክር ይቅርና እንቅልፍ በዓይናችን ሊመጣ ሃይልና ብርታት ይኖረዋል? ወይንስ ይህ ድል ሆነና በቅቶን ነጋና ጮቤ
እንረግጣለን? ሌላው ይቅር ደስታችንንም ይተውት የሆነው ሁሉ ሆኖ ምኑ ነው የመጠጥ ደስታው? እንዴት ልንመርጠው ቻልን? መስከሩን
ነው? መንገዳገዱንና በሰው ፊት መቅለሉን ነው? ወድቆ መጎዳቱን አዕምሮን መቆጣጠር ተስኖን ከሰው ጋር መጋጨትና ማስቀየሙን ነው ወይንስ ምኑን ወደድንለት?
ፌዴሬሽኑስ ምን እያደረገ ነው? ሥለጠና አያስፈልግም?
በጀት የለው ይሆን እንዴ? ማን ያውቃል? ወይ እንደ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችን የዜግነት ችግር ይኖርባቸው ይሆናል? (በሌላው ዘርፍ
የሆነ ችግር ሲነሳ ሀሜት ከተማዋን ሲንጣት እንደዚህኮ የሆነው እገሌ የተባለ ሚኒስተር ወይም ዴኤታ በአባቱ ወይም በእናቱ ኤርትራዊ
ስለሆነ ነው የሚባል የልማት እንቅፋት የሆነ ልማታዊ ቀልድ አለ፤) ታዲያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ራሱ የኢትዮጵያዊነት ችግር ይኖርበት
ይሆን? መቸስ ያን ሰሞን ማነች ይህቺ ሱዳን ከምትባለው ጉረቤት አገር ልነጋጠም ያልን ሰሞን 31 ዓመት ከመጠበቃችን ይልቅ የዕሁድ
ሠዓት እንደረዘመብን ባያውቁ ሳይሰሙ አይቀሩም፤ ለነርሱም ቢሆን በዘመናቸው የተሰራ የሚመዘገብ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ አልፈለጉ
ይሆን? ማን ይህን ከድልማግስት እዚም ያደረገባቸው? ለነገሩ ድልና የድል ማግስት በኢትዮጵያ ችግር አለባቸው ሰሞኑን ሰፈራችን አንድ
ነገር ሲገርመኝ ነበር የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ለማሰራት ገንዘብ ለማዋጣት ተስማምተን ማዋጣት ከአሥር ዓመት በላይ ይሆነዋል፣ ረጅም
ጊዜ እንዲያውም በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች በቃ ገንዘባቸውን ይመለስልን እያሉ ሲማረሩ ከርመው አሁን መንገዱ ከተሰራ ሁለተኛ ዓመቱን
ይዟል እንኳንስ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ መንገድ ብሩ ከመበላት አምልጦ መንገዱ ተሰርቶ ሲያልቅ ይቅርና ልጁ KG ጨርሶ አንደኛ ክፍል
ሲገባ ይመረቃልና እኛም የአሥር ዓመት ተቀማጭ ገንዘባችን ለቁም ነገር ሲውል የማያገባቸው ግን በገቡበት ሰው አማካኝነት ሊመረቅ
ሁለት ሁለት መቶ ብር ከአመት በፊት ተዋጣ ቀን ይመርቁት ሌሊት ሳናውቅ ተራዝሟልም ሳንባል ከረምን። እርም ብለን የተውነውን የመንገድ
ምርቃት እንደ አዲስ ከቀበሌ መጥተው ከአንድ ጎረቤቴ ጋር ቆመን እየተጫወትን «መዋጮ» ማለት ሰውየዉ«የምን መዋጮ» ዓይናቸውን በጨው
የታጠቡትም (የመንገድ ማስመረቂያ» ሰውየው ከረር በማለት (መክረር እኛ ሠፈር ብርቅ አይደለም ኑሮ ያለከረረው ማን አለና) «የትኘውን
የቀለበት መንገድ እየፈረሰ ያለውን ከመስቀል አደባባይ ሳሪስ ያለው የሚፈርስ መንገድ የማስረሻ ምርቃት » በማለት በአሽሙር መልክ
ጎሸም አደረጓት።
«አይ አይደለም የሰፈራችሁን»
«ከሁለት ዓመት በፊት የተሰራውን»
«አዎ » እያለች ስለተረዷት ፈገግ አለች።
«ታዲያ ለምን አዋጣለሁ»
«ለምርቃቱ ነዋ ሰሞኑን ባለሥልጣኖች መጥተው ይመርቁታል»
«ድጋሚ….» ብለው ከዓመት በፊት የከፈሉበትን ደረሰኝ ከኪሳቸው አውጥተው አሳዮዋት፤ ነገሩ ሥላልተሳካ
«ይቅርታ» ብላቸው ለመሄድ ስትል
«ቆይ ነይ ወደዚህ፤ ለመሆኑ ማን ነው የሚመጣው»
እየሳቀች «እኔንጃ ማን እንደሚመጣ እንኳን አላውቅም»
«እኛንም ይፈሩናል እንዴ ማንነታቸውን ሳያሳውቁ ድግስ ደግሱና ድንኳን ጥላችሁ ጠብቁን የሚሉት? እኛኮ የልማት አጋሮቻቸውኮ
ነን እነርሱ ያቅዳሉ እኛ አዋጥተን እንሰራለን ነው ወይስ እንደ ቻይና ማበደር ነበረብን? ለማንኛውም የሚመጣውን ባለሥልጣን አትመርቅ
ርገመው አደራህን ረግመኸው ሂድ የመረቃችሁትን አንድም የረባ ነገር የለምና በይልኝ ጎሽ የኔ ልጅ ።»
የቀበሌዋ የመዋጮ መልዕክተኛ እየሳቀች (እየፈራች
ነበር የምትስቀው ነገሩ የሚያስቅ ሆኖባት ነው እንጂ) ወደ ቀጣዩ ቤት አመራች፤
በዚህ ሰሞን የኛ ሰፈር የዉስጥ መንገድ ተመረቀ፣
ቶታል ጎጃም መውጫ ከውንጌት ጋር የሚገጥመው ቀለበት መንገድ ተመረቀ፣ ሰሜን መናፈሻ ጋር ቀበሌው ውስጥ የተሰራው ህነፃ ተመረቀ፣
ከሰሜን ሆቴል ዝቅ ብሎ ያለው 3ኛ እየታባለ የሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ተመረቀ ሌላም እኔ የማላውቅ ምርቃት በየሰፈሩ ክፍለ ከተማውና
በየክልሉ ይኖራል ግድ የለም ይመረቅ እንኳንስ ተሰርቶ ያለቀ ነገር መመረቅ ይቅርና የማይሰራ ነገርስ መሰረት ድንጋይ ይጣልበት የለ፤
(እንዲያውም ነገርን ነገር ያነሳዋልና እኛ ሰፈር አንዴ የበሬ ግንባር የምታክል ሜዳ አለች አንዳንዴ ባለሃብቶች ህንፃ ሲገነቡ ሌሊት
ሌሊት በድብቅ አፈር ይደፋባታል ጠዋት ጠዋት ወጣቶች ስፖርት ሲሰሩ ኳስ ሲጫወቱ አፈሩ እየደናቀፋቸው ይደፋበታል እሁድ እሁድ ደግሞ
ኸየቦታው ጎረምሶች መጥተው በየቡድን በየቡድኑ ይራኮቱባታል። ከዚህ ሁሉ የሚገርመኝ ለምን እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ አሁን ለሶስተኛ
ጊዜ የመሰረት ድንገይ ተጥሎበታል ያኔ የመንገድ ምርቃቱ ቀን የሆነ
ነገር ጨርቅ ለብሶ ተሰቅሎ አየሁና ነገሩ እንዴት ነው ብዬ ወሬ ለመቃረም ጠጋ ብዬ የሰፈር ሰው ጠየኩ ምን እንደሆነ
የሚያውቅ አጣሁ አሁንም ፈቅ አልኩና የሰፈር ሱቅ በር ላይ የቆሙ ምንድን ነው አልኳቸው እነርሱም በፊት የነበረውን በእመነ በረድ
የተጻፈውን ማንሳታቸውን እንጂ አዲሱ ደሞ ምን እንደሆነ ምን እናውቃለን ያው እንደለመዱት ሊበሉበት ይሆናል በማለት ምሬት ሲጀምሩ
ነገርና ምሬት እንደ ጦር ስለምፈራ የምወዳትን ወሬ ፍለጋ ተመልሼ ወደዚያው ወደተሰቀለው ተመለስኩ ይኼ ሁላ ለወሬ ምንድን ነው እንደዚህ
መሆን? ትሉኝ ይሆናል ታዲያ እኔ ቃርሜ ካላመጣሁ ማን ያወራችኃል። ለማንኛውም ያቺ የተሰቀለችዋን ነገር ጨርቁን ንፋስ ሲያወዛውዛት የሚገርም ትልቅ ፎቶ ግራፍ አየሁ ምን አትሉም ዓለም አቀፍ ደረጃውን
የጠበቀ እስታዲዮም ልብ በሉ እኛ ሰፈር ውስጥ እዚያች የበሬ ግንባር
የምታክል ሜዳ ላይ፡ ተስፋ ቆረጥኩና ቦታውን በሊዝ ቢሸጡት ይሻላል እያልኩ እየተማረርኩ ጥዬው ሄድኩ እርሱም የመሰረት ድንጋይ ተጣለ
አሉ አንድ ነገር ልበላችሁና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባና ቅንፉን እንዝጋው ዞሮዞሮ ከቤት አይደል የሚባለው ዛሬ ዛሬ ወደሰፈር ስመለስ
ያ ተሰቅሎ ያየሁት የእስቲዲየም የጨርቅ ላይ ዕቅድ እንደ ጠዋት ጤዛ ጠፍቶ አገኘሁት ታዲያወገኔ እውነት ይህ እስቴዲየም ይሰራል
ትሉኛላችሁ? አትጨነቁ ሆዴ ነግሮኛል አይሰራም።)
መመረቁን ይመረቅ መሰረቱም ቢሰራም ባይሰራም
ይጣል ግድየለም ባይሆን እመነ በረዱን ለሚያዘጋጁት ሊሾውን የሚሰሩት የስራ እድል ተፈጥሯልና ግን አንድ ጥያቄ አለኝ አንድ ቦታ
ላይ ሁለት ሶስት የመሰረት ድንጋይ ከሚጥሉ ሌላ መጣያ ቦታ የለም ወይ? ከጠፋ ከጠፋ አዲስ አበባ ውስጥ ስንቱ ቤት የመሰረት ችግር
አለበት አይደል እንዴ እርሱን ለምን አያጠብቁበትም። (ኢትዮጵያዊ ምክሬ ነው ተግሳፅ አይደለም) ወይስ ግራውንድ ፕላስ የሚሰራ ልማት
ይኖረዋል እንደኮንደምንዬም? ጥያቄ ቁጥር ሁለት እኔ አልኩት አላልኩት የምርቃቱ ሥነ -ሥርዓት አይደነቀፍም እንዲያው ለነገሩ አንድ
ሥራ ሥንሰራ እንዳልተንከረፈፍንና የሰው ጨጓራ እንዳልመለጥን ለምርቃ እነዲህ ማጣደፍ ምን የሚሉት ነው? አንድም ደግሞ ትንሽ ነገር
በሰራን ማግስት የምርቃቱ ሽርጉድ ሳያንስ የመዲናውን ኔትወርክ ስለርሱ በማውራት ማጨናነቅ ምን የሚሉት ነው? ያካበደን አልመሰለንም?
ወይስ ከዚህ በኋላ የምንሰራው ነገር የለም? ይህ እንዴት የአንድን
ታላቅ መሪ ራዕይ ማሳካት የምርቃት የፌሽታ የደስታ ጋጋታ ነው እንዲህ ነው ፈለግ መከተል? ቆይ እኛ ኢትዮጵያን ከድል ማግስት ለሌላ
ድል ከመዘጋጀት ይልቅ ያቺኑ ድል ይዘን አርባና ሰማንያዋን እያወጣን ጮቤ የምንረግጠው ለምንድን ነው? እስከመቼሰ ይቀጥላል?
አንድ ነገር ስጠረጥር ድሮ የአንደኛ ደረጃ
ተማሪ እያለን የመጀመሪያውን ፈተና እንደምንም አሥር ከአስር አለበለዚያም ዘጠኝ ወይንም ስምንት ካመጣን እርሷን ለቤተሰብ እናሳያለን
ጉራችን መከራ ነው ቤተሰብም ልጄ ጎበዝ ነው አስር ከአስር አመጣ ብሎ ሰፈር ውስጥ ለቅሶና ድገስ ላይ ሳይቀር ያወራል። ከረሜላ
ወይም የሆነ ነገር እንሸለማለን አባትም እርሱን አትናገሩብኝ እናትም ከሌሎች ልጆቿ ለይታ ለዚያ ልጅ ምርጥ ምርጡን ስትል ልጅየው
ድጋሚ አስር ለማምጣት አይጥር፣ ፈተናም እንዳለበት የሚናገረው ተው አጥና ብሎ የሚመክረው የለም እንዲያውም የተቆጣውን ሰዉ ተመልሰን
በቁጣ እናስደነግጠዋለን የምንባንነው ወላጅ አምጣ የተባለ ቀን አለበለዚያም ሰኔ 30 መጥቶ የልጆች ውጤት ተሰጥቶ መውደቁን የሰማን
ቀን ምን ማድረግ እንዳለበት ከቤት አልፎ አክስትና አጎት ጉረቤት ድረስ መነጋገሪያ ይሆናል ይህንንም የታደለው ነው ባኖ ወደ መፍትሄና
ጥፋትን ወደማረም የሚመጣው የባሰበት በመምህራንና በትምህርት ቤት ያመካኛል፣እኔ ልጄን አውቀዋለሁ እያሉ ከአስር አስር የመጣበትን
ውጤት አንጠልጥለው ይጮሃሉ ከዘጠና ግን ሥንት እንዳመጣ በጭራሽ አያውቁም ያጥና አያጥና አያውቁም፣ክፍል ገብቶ ይማር አይማር የቤት
ሥራ ይስራ አይስራ አያውቁም፡ ሌላው ቀርቶ ያንን አስር ከአስር እንኳን እንደመጣ አያውቁም የእግር ኳሱም ይሁን የልማቱ ጉዳይ ብዙም
አይለይም አንድ ናቸው። ለመሆኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ማለፋችንን እንጂ እንዴት እንዳለፍን በጠቅላላ ካስገባነው ይልቅ የገባብን
ጠቅላላ ግብ ስንት እንደሆነ ሁሉንም ትተን ከሱዳን ጋር በተጫወትን ምሽት የመጨረሻዋ ፊሽካ ስትነፋ የገባችሁ ግብ ተቆጥራ ቢሆን
ኖሮ ድል አልነበረም ልማታችንን ስናስበው የክሊኒኩ መገንበታ እንጂ ሲገነባ ስንት እንደፈጀ ፣ መንገዱ ሲዘረጋ መንገዱ ማለቁን እንጂ
ስንት ዓመት እንደፈጀ ብናስብ እንኳንስ ጮቤ ልንረግጥና ልንፈነጥዝ ይቅርና ባለሥልጣኑ በቦታው ቆሞ ባልመረቀ ስለዛ መንገድም ደግሞ አንስተው በሚዲያ ባላወሩት ነበር። ነገር
ግን እንደትልቅ ድል ሌላውን ልማት አቁመን በዚህ ድል መጨፈርን ሞያ አድርገናል።
ከዚህ ቀደም ካለው ስህተታችን ተምረን ለነገ
ተግተን የምንሰራ ቢሆን ኖሮ በደርግ ዘመን(በ1977 ዓ.ም) የነበረውን ድርቅ ተመልከተን በኢህአዴግም ደርቅ ተምሶ ባልመጣ ነበር፤
በአንዱ ክልል ያስቸገረ አገር የፈታ የወባ ወረርሽኝ እዚያው እንዳለ
በቅጡ ተረባርበን እንደሚሆን አድርገነው ቢሆን ዛሬ በአራቱም ማዕዘን ፋታ አይነሳንም ነበር። ድሮ በአባቶቻችን ዘመን ጣሊያንን በጨበጣ
ድል ማድረጋችንን መታሰቢያ ባናደርግና ተምረንበት ቢሆን ከአርባ ዓመት በኃላ ተመልሳ ጣሊያን ባለደፈረችን፣ በደርግም ከሱማሌ ጋር
የነበረው ችግር ከትናንት መማር ቢኖርበት እስከ ኢህአዴግ ዘመን ባልዘለቀ ነበር፣ አሁንም በዘመነ ኢህአዴግ ከኤርትራ ጋር በባድመ
ምክንያት ያ ሁሉ ደም የፈሰሰው ያ ሁሉ ወጣት የተሰዋው ያ ሁሉ የአገር ሃብትና ንብረት ጊዜን ጨምሮ በከንቱ የወደመው ኢህአዴግ
ከደርግ ውደቀት በኋላ መማር ተስኖት በድል ማግስት ባሳየው ደካማ ጎን ምክንያት ነው።
ለኢትዮጵያ ህዝብ ለኢትዮጵያ ወጣት የአውሮፓ
ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ የነማንችስተር (ዩናይትድና ሲቲ) የአርሰናልና የባርሴሎና፣ የቼልሲና የሊቨርፑል...ድልና
ዋንጫ ምናችን ነው? የደቡብ አፍሪካ የኢፓርታይድ ነጻነት ፣ የአሜሪካ ሰላማዊና ዲሞክራሲያው ምርጫ፣ የቻይናና የኮርያ ፈጣን እድገት...
ምናችን ነው? እኛን የራበን፣ እኛን ያመመን፣ እኛን ያናፈቀን የራሳችን የአገራችን የህዝባችን የወገናችን የሆነ ልማት፣ ዲሞክራሲ፣ፈጣን
ዕድገት ሰላማዊ ምርጫ፣ ዘለቄታ ያለው ድል (ተከታታይነት ያለው) ሰላም ነዉ።የሃይማኖት ነፃነት፡ የፖለቲካ እኩልነት…..ወዘተ ናቸዉ፡፡ከድል
ማግሰት ሌላም ዉድድር እንዳለብን ከመዘንጋት ይሰዉረን፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ