አንድ ትውልድ ለመፍጠር ቢያንስ ሃያ እና
ሰላሳ ዓመት ያስፈልገዋል። ዓብይ ርዕሳችን ምንም እንኳን ሥለትውልድ ቢያወሳ ርዕሰ ጉዳያችን ግን በጥቂት ሶስት ነገረ ልብ ልንል
ግድ ይላል። ቀጣዩ ማለት ማን ነው? የትኛውስ ትውልድ
ነው? ቀጣዩ ትውልድ የምንለው ጊዜስ በራሱ ከመቼ ይጀምራል? የሚሉት ጥቂቶች ናቸው። ለምን ይህንን ጉዳይ እንዳነሳ ያስገደደኝን
ነገር ማካፈሉ ጥቂት ሥለተነሳሁበት ነገር ማብራሪያ የሚሰጥ ይመስለኛል። ጊዜው ምሽት 3፡15 ሠዓት ነው የሰዉ ልጅ ወደቤት ለሚሰባሰብበት
ተጠናቆ የሚገባበት ሰዓት ነው (በጊዜ ወደ ቤታቸዉ የሚገቡትን አይመለከትም፤ ችግር፣የማያስገባቸውንም የመጠለያ ችግር አጋጥሟቸው መኖሪያቸውን ጎዳና ያደረጉትንም አያከትትም።) ይህንና
የሚገቡትን ይዘን የማይገቡትን ትተን ጎዞ በታክሲ ወደ ቤት፡፡ የአብዛኞቻችንን መጓጓዣ የሆነውን ታክሲ ወይም ሌሎች የትራንሰፖርት
አገልግሎት መስጫዎችን ተጠቅሞ መሄድ ግድ ይላል፡፡ ጎዞዉ ሊጀመር
ሰው መሟላት ግድ ይላል ታክሲዉ ከያዛቸው ሰዎች መካከል በአንድ
መቀመጫ ላይ የተቀመጥነው አራት ነበርን ሶስት ትናንሽ ልጆች በግምት እድሚያቸው አምስት፤ ስድስት እና ዘጠኝ አመት ናቸው። ከሥራ
ነበር የሚመለሱት መቼስ በጠፋ ስራ እለት እለት የስራ አጥ ቁጥር በሚጨምረበትና ኮብልስቶን ለማንጠፍ ለዪኒቨርስቲ ተማራቂዎች ሞያ
በጠየቀበት አዲስ አበባ እደሜያቸው ከአስር አመት በታች በሆኑ ህፃናት ከስራ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኃላ ወደ ቤት መግባት አጃኢብ
የሚያስብል ጉዳይ ነው። ነገሩ ወዲህ ነው የዘጠኝ አመቱ ልጅ የመጣው ከጎጃም ነው አመት ከመንፈቅ ሆኖታል አዲስ አበባን ሀገሩ ካደረገ
ወላጆቹ ይህን አለም መሰናበታቸውን እንጂ መቼ እንዳረፉ ጊዜውን በውል አያውቀውም ድሮ ነው የሞቱት ይላል የወላጆቹ በሕይወት አለመኖር
ሲገልፅ ሁለቱ ጨቅላ ህፃናት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ የአክስትና
የአጎት ልጆች ናቸው እንደሱ አገላለፅ በእነሱ ትከሻ ላይ ነው ያለሁትም ብሎኛል፡ በአክስቱና በአጎቱ ላይ ሁለቱ ህፃናት ግራና ቀኝ
ጉልበቱ ላይ ተኝተዋል፡፡ እሱ በሚያንቀላፋበት ሰዓት እሱ ተሽሎ የሁለት ህፃናትን እንቅልፍ በእቅፉ ለማስተናገድ ሕይወት አስገድደዋለች።
ላወራቸው የምፈልገው ጉዳይ ስለነበረ ቀሰቀስኳቸው
ከየት ነው የምትመጡት?
ከሥራ፤
የምን ሥራ?
ማስቲካ ስንሸጥ ቆይተን
ለምን ትሸጣላችሁ? (አይባልም ግን ጥያቄ ማንሳቴ ካልቀረ ብዬ ቀጠልኩ እንጂ) ተቀባብለው በሚያሳዝን ሁኔታ መለሱልኝ
ያሉኝን አልነግራችሁም ሁሉም ቤት አለና።
ስንት ሸጣችሁ?
ለሶስት ሰላሳ ብር ( ልብ በሉ ጠቅላላ ገቢያቸው ሰላሳ ብር ነው ዋናው ስንት እንደሆነ ትርፉ ስንት እንደሆነ ሂሳቡን
ምቱልኝ እነዚህ ልጆች ስንት ሰዓት ነው የወጡት? ምን በልተው ዋሉ? እራታቸውንስ ምን ይበሉ ይሆን?... እግዚአብሔር ይወቀው።)
ስንተኛ ክፍል ነህ? (ለትልቁ ልጅ ያቀረብኩለት ጥያቄ ነው)
አራተኛ ክፍል
ጎጃም እያለህ ትማር ነበር ?
አልማርም ወላጆቼ ከሞቱ ቆይተዋል ብዬህ የለ?
ታዲያ እንዴት አራተኛ ክፍል ገባህ?
አምና (2004 ዓ.ም) አንደኛ ስገባ የትምህርት ሁኔታዬን አይተው አሳለፉኝ አሁንም ጎበዝ መሆኔን ሲያዩ ሶስተኛ ክፍል
ገባሁ መጨረሻ ላይ ግን የሚቀጥለው አራተኛ ትገባለህ አሉኝ አሁን (በ2005 መሆኑ ነው) አራተኛ ክፍል እየተማርኩ ነበር ።
ታጠናለህ ወይ እንዴት ጎበዝ ልትሆን ቻልክ?
(ለኔ ጥያቄ ነበር የእኔንና የእሱን ጥያቄ ከፊሉ ሰው እያዳመጠ ነው።)
አጠናለሁ አሁን ስገባ እነሱ ይተኛሉ (የተኙትን ሁለት ህፃናት እያመለከተ) እኔ ወደ ጥናት ነው የምሄደው( እዚህ ጋር የራት ነገር አልተነሳም እራት ይበላ ይሆን ካልበላ በምን አቅሙ ያጠናል ጥናት እንደሆነ በልቶም አልሆነም «ጎበዝ» ብዬ ነበር ማለፍ የምችለው ከዚህ ወዲያ አቅሙ የለኝምና)
አጠናለሁ አሁን ስገባ እነሱ ይተኛሉ (የተኙትን ሁለት ህፃናት እያመለከተ) እኔ ወደ ጥናት ነው የምሄደው( እዚህ ጋር የራት ነገር አልተነሳም እራት ይበላ ይሆን ካልበላ በምን አቅሙ ያጠናል ጥናት እንደሆነ በልቶም አልሆነም «ጎበዝ» ብዬ ነበር ማለፍ የምችለው ከዚህ ወዲያ አቅሙ የለኝምና)
አዲስ አበባ እንዴት ልትመጣ ቻልክ?
ጠፍቼ አጎቴን ተከትዬ ነው የመጣሁት
ለምን ? እንዴት?
(ታሪኩ ብዙ ነው የነገረኝ ለፅሁፍ እንዲመች ግን ላሳጥረው)
ከእነሱ ጋር ለመኖር ሰው የለውምና አንድም የሚያበላው አንድም የሚያስተምረው ከሀገሩ ተሰደደ በምሽት አዲስ አበባ ጎዳናዎች
ላይ ከኑሮ ጋር ትግልን ማስቲካ በመሸጥ ተያያዘው።
ኑሮ ኖርክ ተብሎ የእለት ጉርሱን የአመት
ልብሱን መሸፈኛ ሊያመጣ ነጋዴ ሆነ፤ መምጣት ሳያሻው ህይወት ወደዚህ ምድር ጠርታዉ ፍዳውን ሊያል፤ እንደ ሰው ተፈጥሮ እንደ ሰው
ሳይከበር ሊኖር ትንቅንቅ ተያይዞታል ፍጥጫውን ቀጥሏል እድሜህ ስንት ነው? የሚለው ጥያቄ እንኳን በቂ ምላሽ አልነበረውም እኔንጃ
አላውቀውም ከማለት ውጭ።
አለም ለህጻናት መብት ይከበር፣ ጉልበታቸው
አይበዝበዝ፣ ግፍ አይዋልባቸው፣እነሱ ለመኖር፣ለመብላት፣ለመማር መብት...ወዘተ አላቸው፣ በሚባልበት 21ኛው ክ/ዘመን በሺህ የሚቆጠሩ
ህፃናት ግን ጉልበታቸው ያለአግባብ እየተበዘበዘ፣ የመማር፣የመብላትና የመጠጣት መብታቸዉ እየተነፈገ፣በበሽታ እየተጠቁ፣ ለስደት እየተዳረጉ፣...
ይገኛሉ።
ይህንን አስከፊ ጉዳይ በምን እንቀይረው?
እንዴትስ እንቀይረው? ቀጣዩን ትውልድ ምን እናወርሰው? ...
ይህ ትውልድ ወደድንም ጠላንም ተፈጥሯል ህይወቱን
ልናስቀጥለው ግድ ይላል፤ ከጨቅላዎች ህፃናት እስከ ወጣቱ ትውልድ ድረስ ያሉት የነገውን አለም ተሳታፊና ተረካቢዎች ናቸው። ታዲያ
ይህ ትውልድ መጪው የዚች አለም ዕጣ ፋንታ በእጅ ያለ ከሆነ ዓለሙን የሚያስቀጥለው እሱ ከሆነ አንድም የትኛውን ዓለም እናውርሰው?
በሌላ በኩልም እራሱ ትውልድስ ከእኛ የሚወርሰው ያዘጋጀንለት ምን ነገር አለ? ረሃብ፣ጦርነት፣ድርቅ፣ስደት፣የጎዳና ላይ ኑሮ፣ልመና፣ለጉልበት
ብዝበዛ፣ወይም የተሻለች ብሩህና፡ ልምላሜ፡ እድገትና ብልፅግና የሞላባት ዓለም???
ለእነዚህ ሶስት ህፃናት ከአንድ ቤት ጉልበታቸው
መበዝበዝ፣በምሽት ጎዳና ላይ ማስቲካ መሸጥ፣ ሲደክሙ አምሽተው 30 ብር ብቻ ይዘው መምጣት፣ሳይበሉ መዋልና ማደር፣ወዘተ ምንን ያመለክታል?
ፍትህ መኖሩን? የህፃናት መብት መከበሩን? ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ ፍሰት መኖሩ ወይስ ደሃና ረሃብተኛ አገር መሆኗን በሁለት ዲጂት አኮኖሚያችን
ማደጉስ? ለእነዚህ ህፃናት ትርጉሙ ምንድነው? ለተከታያይ አመታት አኮኖሚያችን ማደጉ ለቀጣዩ ትውልድ ለምግብ ፍላጎት ካላሟላ ማደግ
ቢቀርስ? ማደግ ማለት ለህንፃ መገተር ይሆን? ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው «ማከራየት ጀምረናል» የሚል ፅሁፍ የተለጠፈበት ህንፃ
ነው?
ይዘው የመጡት 30 ብር ዋናውን ጨምሮ የቤተሰብ
እራት ያበላቸዋል ወይስ የኑሮ ሥጋት ይጨምራባቸዋል? ይህ 30 ብር የዚህን ቤት ህይወት ይታደግ ይሆን? ይሕ ህፃን ለትምህርት ብሎ
የተሰደደውን ስደት ድካም ዋጋ ይከፍለው ይሆን? እንደእኔ እይታ ከዚህ ባሻገር አንድ ነገር ተመለከትኩ ምን? አትሉኝም ከንቱ ልፋት እንጂ ተመጣጣኝ ክፍያ እንደማይከፈለን
ማነው በስራው መጠን ኢትዮጵያ ምድር ላይ የተከፈለው ከሌባ ከሙሰኛ እና ከአጭበርባሪ በቀር ለምንድን ነው ለመንግስት ሰራተኛ በስራው
እርካታ የሌለው ለምንድነው ዛሬ ዛሬ የቤት ሰራተኛ ማግኘት አዲስ አበባ ላይ ችግር የሆነውና ወጣት ሴቶች ከገጠርና ከከተማ ወደ
አረብ አገር የሚፈልሱት? ሰው ከመስሪያ ቤት መስሪያቤት ለምን ይፈልሳል?
ክፍያ ስለማይከፈለው ነው? ይህንኑ ነው እነዚህ ሶስት ነፍስ ያላወቁ ህፃናት ላይ ያየነው
ጉልህ ነገር። እንዲያውም በአንድ ሰሞን ዐብይ መወያያ የነበረው የአየር መንገዳችን ፈጣን እድገት የመጣው በስራ ብቻ
ሳይሆን ለሰራተኞቹ የድካማቸውን ያህል ተመጣጣኝ ክፍያ ባለመክፈሉና
ጉልበታቸውን በመበዝበዙ ነው የሚል ተቃዉሞ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር። እውን አየር መንገድ ብቻ ነው? የኢትዮጵያ መብራት ኃይል
ኮርፖሬሽን፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት
ወዘተ...ውስጣቸው ቢፈተሽ የሰራተኞቻቸው ብሶት ቢፈተሽ ደሞዝ አይከፈለንም ነው ጥያቄው ባንኮቸስ ብንል ኧረ ስንቱን ሆድ ይፍጀው።
በኢትዮጵያ ጉልበት ብዝበዛ፣ በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሥራ አጥ፣ ረሃብ፣በሽታ፣ስደት፣...
የሆነዉ ሆነ ቀጣዩን ትውልድ ምን እናውርስ?
እርስ በርስ የተከፋፈለች አገር? በሽታና ጦርነት ያደቀቃት አገር ? መቼስ የቀጣዩ ትውልድ ልመናን አናወርስም ቃል ገብተናልና ልማትን
እንደምናወርሳቸው እርግጠኞች ነን እኔ ፍርሃት አለብኝ እኛ ነገ እንደክማለን፣እናረጃለን እናልፋለን፣ ... ይህ ትውልድ ግን ያለኃጢአቱ
ወላጁን በወባ፣በካንሰር፣በቲቢ፣በHIV ኤድስ ወዘተ ከማጣቱ ወላጅ አልባ ከመሆኑ ባሻገር የበሽታው ተጋላጭ የሆነው ጥቂት አይደለም
እድሜ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የቀረቱንስ ማን ሰብስቦ ያሳድጋቸው? ማን ነገን ያውርሳቸው? ማን የነገ ተተኪና ወራሽ እንዲሆኑያስችላቸዉ? ማን ዛሬን ብርታት ይሁናቸው? ሳይሰደዱ ባህር ማዶ ሳይናፍቁ አገሬን ብለው እዚች ወንዝ
ዳር አስቀምጣ ለምታስጠማ፣ ለም መሬት ላይ አስቀምጣ ለምታስርብ ኢተዮጵያን አልምተው በልተው ጠግበው ጠጥተው እረክተው እንዲኖሩባት ከመንገድና ከህንፃ ባሻገር የተለየ
ልማት ማን ያሳያቸው? ቀጣዩ ትውልድ እንደባለፈው ተስፋ ሳይሆን ምልክት ተጨባጭ ነገርን ይሻልና። ንጉሱም ደርግም ተስፋ በተስፋ
ሲያደርጉን አልፈዋል ከኢህአዲዴግም ተስፋ ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ የሚዳስስ ይፈልጋል፡እንፈልጋለን፡፡ በዘጠኝ በአስር በአስር አንድ
በመቶ ኢኮኖሚ የማደጉ ዜና ሳይሆን በቀን ሶስቴ መብላትን በምግብና በመጠጥ እራስን መቻል ትውልዱ ይሻል። እንፈጽማለን፡እናስፈፅማለን፡
እናስቀጥላለን የሚሉ ተስፋዎች ሳይሆን የተፈጸመና የሚቀጥል ነገር ሊወርስ ይገባዋል ይህ መጪ ትውልድ።
እርግጥ ነው መንገዱ ተገንብቷል ህንፃዎች
ተሰርቷል ትምህርት ቤቶች፣ሆስፒታሎችና
ክሊኒኮች ታንፀዋል ነገር ግን ቀጣዩን ትውልድ ለመንገድ ርዝማኔ ሳይሆን የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍለት ይሻል፤ ህንፃዎች መገንባት
ብቻ ሳይሆን ለመጠለያ ችግር መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እንዲዳረስ ይፈለጋል። እንዲሁ የተገነቡት ትምርህት ቤቶች ጥራት ያለው
ትምህርት የተስተካከለ የትምህርት መርሃ ግብር እንዲሰጠው በጉጉት ይጠባበቃል ሆስፓተሎቹም ሆኑ ኪሊኒኮቹ በቂ አገልግሎት ለሁሉም
ከተሟላ መሳሪያና ባለሙያ ከተገቢው መድሃኒት ጋርና በመልካም አስተዳደር የመጠበቅ ጉዳይ ነው አለበዚያ ለህንጻ መገተር ጤና አይሆንም
ከምንም በላይ ከመሰረታዊ ነገሮች አንዱ ንጹ ውኃ ያለው አካባቢ ልናወርሰው
ይገባናል ውሃ ለማግኘት ወረፋ፣ ዳቦ ለመግዛት ወረፋ፣ ለትራንስፖርት ይዘን ለመሄድ ሰልፍ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊዘልቅ አይገባም ለሁሉም
ሰው መልእክት ነው።
ለቀጣዩ ትውልድ ልናወርሰው ከሚገባቸው አንገብጋቢ
ጉዳይ ውስጥ እንደ ዳቦና ውኃ በሰልፍ ብዛትና በወረፋ የሚገኘውን የፍትህ ጉዳይ መንግሥት አትኩሮት ሊሠጠው ይገባል። ወላጆች በህገ
መንግሥቱ መሰረት በ24 ሠዓት ውስጥ የፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት አለበት ከሚለው አንስቶ ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ
ፍርድ ሊያገኙ ይገባል የሚለውን በማጣት ከየመንገዱ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እየታፈሱ በመግባት በ24 ሠዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ባለመቅረብ፣
በማስረጃ እጦት እና ባልተስተካከለ የፍትሀ ሂደት በማረሚያ ቤት በመጉላላት ለሶስትና አራት አመታት በእስር በመንገላታት አልፎ ተርፎ
በጤና መታወክ ሳይፈረድላቸውና ሳይፈረድባቸው እዛው የሞቱበት ፡ይህንን የተሳብረ የፍርድ ሂደት ይዘው መቀጠል አይፈልግም። ቀልጣፋና
ለህገ መንግስቱ የታመነ፡ ለህብረተሰቡ ዘብ የቆመ፡ የፍትህ አካል ሊኖረው ግዴታ አለብን።
ዓለማችን አይደለም ለህፃናት ለአዋቂ አመቺ
ወደአለመሆኑ እየመጣች ባለበት በዚህ ወቅት የሙቀት መጠኗ፣የአየር መበከልን የሚያመጣውን ችግር ልንቀንስ በኑሮ የተመቻቸ ዓለምን ልናወርሳቸው ግድ ይለናል።
ከምንም በላይ የዓለም ህዝብ ከሰባት ቢለ.ዮን
በላይ በሆነበት በዚህ ዘመን የቤተሰባችንን ቁጥር በአጋጣሚ ሳይሆን በእቅድ ልንወስን ይገባናል። መግበናቸው የምናሳድግበትን፣ አስተምረን
የምናንፅበትን፣ወልደን አሳድገን የምናኖርበትን ምቹ ስፍራ ወዘተ አስቀድመን ልናቅድና ልናዘጋጅላቸው ይገባል። በዕድላቸው ይደጉ፣ሲወለዱ
የእነሱ የሚሆነው ይዘው ይመጣሉ የሚለውን አጉል ፈሊጥ... በጥሞና ልናጤነውና ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳቸውን ነገር ልናስብ ይገባል።
ለቀጣዩ ትውልድ የሚታይ የቆመ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ብቻ በቂ አይደለም። ጤናማ ህይወት ያስፈልጋቸዋል፣ በመልካም ስነ -ምግባር ላይ
የተመሰረተና አርአያ ሆኖ ሊያሳድጋቸውና ከፊለፊታቸው ያለውን ብሩህ ዓለም የሚያሳያቸው ቀዳሚ ትውልድ ይፈልጋሉ።
የእነዚህ ሶስት ህፃናት አጭር ታሪክ የሁላችንም
ታሪክ ነው ይህ ታሪካችንን ለመቀየር ታጥቀን እንነሳ የበለፀገች፡ ለምለም ኢትዮጵያን፡ በረሃብ ሳይሆን በስልጣኔዋ በስነ ምግባሯ
የታወቀች ኢትዮጵያን እንፍጠር። ይህቺ በሀይማኖቶች የከበረች፡ በብሔር ብሔረሰቦች ያጌጠች በመከባበርና በመቻቻል የተመሰረተች ኢትዮጵያን
የዲሞክራሲ ፍትህ ልማት ብልፅግና ሰላምና ጤና ሰፍኖባት እናዳማረባት ለቀጣዩ ትውልድ እናውርሳቸው።ከምንም በላይ የሃይማኖት እና
የፖለቲካ ነፃነት ለቀጣዩ ትዉልድ ያስፈልገዋልና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በጥንቃቄ ሊወገድ ይገባል፡ ምክንያቱም በሃይማኖትና በፖለቲካ
ነፃነት ትዉልድ አገርን ለመረከብ ብቁ ይሆናልና፡፡ቸር ይቆየን፤ለቀጣዩ ትዉልድ ልማትን፡ መከባበርን፡የሃይማኖት ነፃነትን፡የፖለቲካ እኩልነትን፡ የኢኮኖሚ በእኩል መከፋፈልን … እናዉርሳቸዉ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ