መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ስለበግ እና እረኛ ተጨንቆ እንዳልሆነ እሙን ነው በጎች ያለው ምዕምናንን እረኞች ያላቸው ካህናትን፣ ጳጳሳትን ፣ (ፓትሪያሪክን)፣ መምህራነ ወንጌልን እንደሆነ የቤተክርስቲያን አስትምህሮ ያመሰጥረዋል፡፡
ምነው ታዲያ ዕረኛን አስቀድሞ በጎችን አስከተለ ወይንስ መጽሐፍ ፀሐፊዎች ተሳስተው ነው? /Typing Error/ ይሆን? ቢሉ መጽሐፍ አልተሳሳተም የታይኘ ሥህተትም አይደለም፡፡ እናስ ምንድን ነው ቢሉ የባህል ልዩነት ነው ፡፡ እስራኤላውያን በጎችን ከለምለም መስክ ሲያሰማሩ እንዲሁም ከነጣቂ ተኩላ ሲጠብቁ ከበጎች ፊት ለፊት በመሄድ እንደሆነና በጎችም ጠባቂያቸውን (እረኛቸውን) እንደሚከተሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ደግሞ ይህ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በጎች ከፊት እረኞች ከኃላ ይከተላሉና፡፡የእስራኤላዊያን በጎች እረኛውም በጎቹን ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ በሥም በሥማቸው ይጠራቸዋል በጎቹም ድምፁን ያውቃሉ እረኛቸውን ያውቁታል እርሱ ካሰማራቸው ሥፍራ ወደየትም ሥፍራ አይሄዱም ወደ ሌላ ክልል በመግባት እረኛቸውን አምቧጓሮ ውስጥ አይከቱትም እረኛቸውም ከለምለም መሥክ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ስለሚያውላቸው አይራቡም አይጠሙም ኢትዮጵያውያን በጎችና እረኞች ግን ከዚህ ሁኔታ እጅግ የፀዱ ናቸው በጎችም በግ አይደሉም እረኛውም እረኛ አይደለም እንኳንስ በጎቹ እረኛውም በጎችም በግ አይደሉም እረኛውም በጎቹን በሥማቸው ሊጠራቸውና ሊለያቸው ይቅርና ጭራሹን በጎቹም እረኛቸውን አይከተሉም እረኛም የሌላቸው ይመስል ያጠራጥራሉ መዋያ ለምለም መሥክም የላቸውም፡፡ የበግም ጠባይ የላቸውም እንደ ፍየል ይቅበዘባዛሉ እንጂ፡፡
እስራኤላዊ እረኛ በጎቹን ሲመራ መንገድ ሲያመላክት ከለምለም መስክ ከንፁህ መጠጥ ሥፍራ ሲያደርስ ኢትዮጵያዊ በግ በተራው የተገላቢጦሽ እረኛውን ይመራል በጉ እረኛውን የሚያደርስበት ግብ (Goal)ሥለሌለው እርሱ ሳሩን ሲግጥ እንደ ፍየል ቅጠል ሲቀነጥስ እረኛው ከመንገድ ይቀራል በጎችም ጫካ ይገባሉ እረኛ የላቸውምና መሪያቸው መንገድ ሥቶ ቀርቷልና ተኩላና ቀበሮ አንድ እያሉ በልተው ይጨርሷቸዋል፡፡
መጽሐፍ የምድሩ ለሰማዩ ምሳሌ ነው እንዲል የኢትዮጵያውን በጎች ህይወት ለኢትዮጵያውን ምዕመናን ኑሮ ምሳሌ የሆነ የሚመስልበት ጊዜ እሩቅ አይደለም፡፡ የቀደሙ የንፁሐን አባቶቻችን አምላክ ትጉሕ የማያንቀላፋ መልካም እረኛችን ልዑል ባህርይ እግዚአብሔር ካልታደገን በስተቀር አሥራት አድርጐ ለእናቱ የሰጣትን ይህቺን አገር እግዚአብሔር ያለ መሪ፣ ያለእረኛ፣ ያለጠባቂ አያስቀራት፡፡ የስላሌው ሀገረ ስብከት የስብከት ወንጌል ኃላፊ እና ሰባኬ ወንጌል የነበሩት ነፍሳቸውን እግዚአብሔር በገነት ያኑርልንና መጋቢ ምሥጢረ አባ ወርቅነህ ውቤ እንዲህ ይሉ ነበር ‘’ድሮ ፈረሱ ጋሪውን ይጐትት ነበር ዛሬ፣ ዛሬ ግን ጋሪው ፈረሱን መጐተት ጀምሮአል’’ እንዲህ ከመሆን ይጠብቀን፡፡ አባት፣ መምህር፣ ካህን፣ጳጳስ፣ ሊቀጳጳስ፣ፓትሪያሪክ፣አያሳጣን፡፡ ወደነው አብረን ኖረን ሲለየን የሚያሳዝነን እንጂ የምናዝንበት፡ እሰይ ተገላገልን፣ ነቀለልን፣……. እያልን የምንለው ይነሳልን ብለን ሰላማዊ ሰለፍ የምንወጣበት ሳይሆን ሲመጣ መጣልን ብለን የምንቀበለው ሲሄድ ሄደብን ብለን በጸሎት በምሥጋና የምንሸኘው አባት ይስጠን፡፡ በለመለመ መሥክ ሰብስቦ የቃሉን ወተት እየመገበ የማያሰድገንን ለንስሐና ለሥጋ-ወደሙ የሚያበቃንን አባት አያሳጣን የተሰበሰበን ከሚበትን፣ ለተኩላ አሳልፎ ከሚሰጥ፣የተኩላ ካባ ደርቦ ከበጎች መሐል ከሚገባ ነጣቂ ተኩላ ይሠውረን፣ ከማስታረቅ ይልቅ ፀብ አጫሪ፣ ፀብ ያለሽ በደቦ ከሆነ ይጠብቀን፡፡
ሃብተወልድና ሥመ-ክርስትናን ካገኘንባት፣ በክርስቶስ ደም ከተመሰረተች ከቅድስት ቤተክርስቲያን ፀንተን እንድንቆይ የሚያደርጉ እረኞች አስተደዳሪዎችን ካህናትና ሰባኪዎችን…….. እግዚአብሔር ያድለን፡፡
ምነው እነዲህ ለማለት በቃህ ትሉ ይሆናሉ አዎ ነገርን ነገር ያመጣዋልና በባለፈው የምሥራቁ ፀሐይ በሚል የግብፁን 117ኛፓትሪያሪክ ሲኖዳ 3ኛ እረፍተ ሥጋ አሥመልክቶ በፃፍኩት በመነሳት የተቀጣጠለው መንፈሳዊ እሳት ወላፈን ገረፈኝ ለዚያ ነው እንዲህ ለማለት የናፈኩት፡፡ እኚህ ሰው ኢትዮጵያዊ አይደሉም ወይ እንደ ጥነቱ ግብፅ ጳጳስ አትልክልን ወይንም እስከዚህ ወደ ኢትዮጵያ በየጊዜው እየተመላለሱ አልባረኩን አላስተማሩን ታዲያ ምነው በኢትዮጵያውያን ልብ እንዲህ ሠረፁ ሞታቸው እንዲህ አንገታችንን አስደፋን ሐዘናችንስ እንዲህ በረታ አነጋጋሪስ ጉዳይ ለምን ሆነ፣ እንደሆነ ሰው ሟች ነው አልኩና ራሴን መረመርኩት አንድ ነገር ልቤን ነካኝ ሌላ ምንም አይደለም እውነተኛ የበጎች እረኛ ሥለነበሩ፣ በጎቻቸውን ምዕመናንን በአግባቡ ሥለሚመሩ፣ስለበጎቻቸው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እውነተኛ አባት ስለነበሩ በጎቻቸውን ከለምለም መስክ ከንፁህ የመጠጥ ውሃ ሥፍራ ሥለሚያውሏቸው ብዙ መፃህፍትን ፅፈው ለዓለም ያተረፋ ቃለ እግዚአብሔርን ያስተማሩ የተጣላ ያስታረቁ በፆምና በፀሎት የጉ ያለ ሐሜትና ያለ ውዳሴ ክብር የእግዚአብሔር አገልጋይ በመሆናቸው በእውነት ያለ ሐሰት አምላካቸውን ያገለገሉ በመሆናቸው ነው በዚያ አረማዊ በበዛበት ፈተናው በጠነከረበትና መውጫ መግቢያቸው በጠበባት አገር በማፅናናትና በመንፈሳዊ ህይወት በማትጋት ለ88 ዓመታት በመትጋታቸው ነው፣…… ሌላ ምንም አይደለም አለኝ ውስጤ ራሴን ጥያቄዬን ሲመልስልኝ ለዚህም ነው ያለቀሰ ነው ያዘነው መንፈሳዊ ቅናት አንገብግቦኝ ታዲያ ኢትዮጵያዊው ምዕመን ምነው እረኛ አልባ ሆነ የቅዱስ ጴጥሮስ ምትክ በጎቹን የሚያስማራ ጠቦቶቹን የሚጠብቅ ኢትዮጵያ ምነሙ አጣች ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዝረጋለች የተባለው ለከንቱ ነውን አይደለም እናንተ እሰራኤልያውያን እንደ ኢትዮጵያውን ከቶ አትሆኑልኝም ያለን እግዚአብሔር ያለ እረኛ፣ ያለመሪ፣ያለአስተዳዳሪ፣ ሊያስቀረን ይሆን አይደለም፡፡ አምላካችን በቃለ የታመነ አምላክ ነውና፡፡
ታዲያ ይኼ ለራሱ ላልሆነ ወገን እንባውን የሚራጭ፣ ደረቱን የሚደቃ አንገቱን በሐዘን የሚደፋ ምዕመን ምነው እውነተኛ እረኛ አጣ ከፊት ለፈት እየሄደ መንገድ የሚመራው መሥዋዕትንትን እየተቀበለ ለመሥዋዕትነት የሚያተጋው ፀንቶ የሚያፀናው ታምኖ እንዲታመን የሚያደርግው ቤተክርስቲያንን ጠብቆ ለተተኪ የሚያስረክብ፣ ከውስጥ እና ከውጭ ጠላት የሚጠብቃት እረኛ ምነው ቤተክርስቲያን አጣች ልጆቿስ ሥለምን በዱር እንዲባዝኑና እንደቅበዘበዙ ሆኑ ቤት እንደሌላቸውስ ሆነው ከደጅ ሲቀሩ እገዲአብሔር ተመልክቶ ዝር አለ
1. ምዕመኑ በራሱ በዚህ ዓለም ሲኖር እነደ አርግብ የዋህ እንደ ዕባብ ብልህ መሆን ስላቃተውና ጅልና ተንኮለኛ ስለሆነ እግዚአብሔር ከጥፋቱ ሊመልሰው
2. ምዕመኑ ራሱ በግ የመሆኑን ጠባይ ትተ ለእረኛው አስቸጋሪ ፍየል ሥለሆነ እግዚአብሔር ሲቆጣ በትር አያነሳምና ወደ ራሳችን ልቡና እስክንመለስና ንስሐ እስክንገባ እረኞቹ ከፊታችን ገለል በማድረግ የሌሉ አስመሰላቸው እንጂ እግዚአብሄር ልጆቹን እነዲሁ አይጥልም የሚታይ እረኛ ባይኖር በሥውር ይጠብቃቸዋልና፡፡
3. እረኛው በጎቹን ለተኩላና ለቀበሮ ትቶ ሲሄድ አስደንግጦ ከሚመልሰው በጎቹን ራሱ እየታደጋቸው እረኞቹን እስኪመለሱ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በመንገድ ይከተላቸዋል፣ መልሶም በጎቹን ከመንጋው እረኛውንም ከሙያው ይመልሰዋል ትዕግሥቱ ብዙ ነውና፡፡
4. ይሁዳን ከ12ቱ ሐዋሪያት ዕድል ፈንታ ፅዋ ተርታ ቢያስገባው ፈጣሪውን በ 30 ብር ሽጦ እንደተለየ በርሱ እግርም ማትያስን እንደተከ እንዲሁ በነዚህ እረኞች ፈንታ እተካለሁ ሲል አንድም የእናንተ ዋጋችሁ በከንቱ አይቀርም ሲል ነው
5. በጎችን ቢሰትኑና ሲበጠብጡ ዝምታው የትዕግሥቱን ብዙት ምህረት ቸርነቱ እስከምን ድረስ እንደሆነ ለንስሐም ምን ያህል ጊዜ እንደጠበቀን ለማሳወቅ ወዘተ ሲሆን ታዲያ የኛ አባቶች ፣ የኛ መምህራን ፣የኛ የቤተክርስቲያን እና የቤተክህነት አሥተዳዳሪዎች ከእግዚአብሔር መንግሥት ይልቅ የዚህ ዓለም ነገር ለምን ታያቸው ለምንስ እንደ ዴማስ በዚህች ዓለም ማብረቅረቅ ተታለሉ ያለዋጋ በከንቲ የማይተው አምላክ እያላቸው በ12ቱ የፍርድ ወንበር ላይ የማስቀመጥ ሥልጣን የሚሰጥ ኃይል ጌታ እያላቸው ለዚህች ዓለም ሀብት ንብረት ፣ሥልጣን ሹመት ሽልማት ምነው ተማረኩ በፍቅር የሚወደን ይህን ህዝብ ሥለምን ያለጠባቂ አስቀሩት ለምንስ ተነሱልን፣ሂዱልን፣ አትምጡብኝ እያለ ምሬቱንና ሐዙኑን በአደባባይ እሰኪገልጥ አስመረሩት ነጣቂ ተኩላዎች ከመንጋው መሐል ገብትው ሲያምሱ እነዴት በሩን ከፍተው ዝም አሉ እንዴትስ ሲያተራምሱ ዝም ለማለት ታገሱ በርባን ይፈታ ኢየሱስ ይሰቀል ዓይነት ፍርድ ሲጓደለ ንፁሐን ሲታሰሩ ተኩላዎች እንደበግ ሲቆጠሩና የተኩላዎች ካባ ሳይገለጥ የበጎች ቆዳ ሲገፈፍ እንዴት አስቻላቸው
ሐሰተኞች እንዴት በጥቂት ድምፅ አሸነፋ የእውነት ድምፅ ወዴት ገባ የሐሰተኞች መስካሪዎች ኃይላቸው እንደምን በረታ ምንውስ ፍርድ ተዛባ አባቶቻችን ክብራቸው በነውራቸው ምነው ሆነብን ሃሳባቸውስ ሥለምን ምድራዋና አላማዊ ሃብት ንብረት ሥልጣን ዝና ጥቅም ክብር ሆነ የኛ ግፍ ነው ወይስ የነርሱ በደል
ጌታ ሆይ እኛን በጎች አድርገን እውነተኛ የበግ ጠባቂም ስጠን አሜን፡፡ እረኞቻችን ከግብፁ አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊ ምን ይማሩ ይሆን ምንስ መማር አለባቸው እኛ በጎችስ ከግብፃዊያነ ምዕመናን ምን መማር ይጠበቅብን ይሆን እረኞቻችን አኛን በየትኛው መስክ ሊያሰማሩን ይገባል መን ከፊት ይምራ ማንስ ከኃላ መከተል አለብት እግዚአብሔር በጎቹን ያለ እረኛ ለምን ተዋቸው እነዚህንና ሌሎችንም ጉዳዮች በማንሳት እንወያይበት አሥተያየቶቻችሁን ፃፋልኝ፡፡
አሁንም ደግሜ እላለሁ የበጎች መልካም እረኛ የነበሩትን የግብፁን ፓትሪያሪክ አቡነ ሲኖዳን እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በእቅፍ ያኑርልን ለግብፃውያንም መፅናናትን ያድልልን መልካም እረኛም ይሥጥልን አሜን:: ይቆየን፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ