ረቡዕ 28 ማርች 2012

“አንቀጽ 39 እና ደቡብ ሱዳን”


 “አንቀጽ 39 እና ደቡብ ሱዳን”
ደቡብ ሱዳን የአፍሪካን እና የዓለምን ቁጥር በአንድ እንደጨመረች የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ እንዲሁ በቅርቡ ደግሞ በፌዴራሊዝም ከሚመሩ በዓለም ላይ ካሉ ከ193 አገሮች 28ቱን ተቀላቅላ 29ኛ እንደምትሆን ተስፋ ይጣልባታል፡፡

መቸስ ነገርን ነገር ያመጣዋልና በቅርቡ ፌዴራሊዝም ቃሉ የመጣው ፌዴራል ከሚለው እንደወጣ ፌዴራል የሚለውም ለጊዜው ቃሉ የየት አገር እንደሆነ ከዘነጋሁት አገር ፌዴክስ እንደተወረሰ ሰማሁ ፌዴክስ ማለትም ‹ቃልኪዳን› ‹‹ስምምነት›› ማለት እንደሆነ ነግረውኛል፡፡

ወደ ሱዳን ጎረቤት አገራችን እንመለስና ከአንድ ሁለት ይሻላል በማለት ተስማሙና ጥንታዊቷ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚል ኬክ ጋግረው ሰው ጠርተው ሥም ተከፋፈሉ እንዲያውም የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ተጋብዘው በመገኘት የስምምነት ፊርማቸውን አድምቀዋል የደቡብ ሱዳንን መወለድ የደስታ መግለጫ እኛንና መንግሥታቸውን በመወከል እንዳደረሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ህፃን ልጅ ዓይን እንደሚያጠቃው በእኛ አገር በእነርሱ አገር ደግሞ ህፃን አገር ዓይን ያጠቃዋል መሰል በሁለቱ አገር አዋሳኝ ላይ ተጣሉ፡፡ ምነው ምን ሆናችሁ ባለፈው ደስ ብሎን ኬክ ቆርሰን በልተን ሻምፓኝ ተራጭተን ጠጥተን በአገራችሁ በአገራችን ቋንቋ ዘፈን ጨፍረን እስክስታ ወርደን ዓለም በሙሉ ጉድ ብሎ እኛ ስንት ኃያልን አገራት በህገ መንግሥታቸው አንቀጽ 39 የ ‹‹… እስከ መገንጠል ድረስ›› መብትን አርአያ ይሆኑናል ብለን ስንጠብቅ አንዲት አፍሪካዊት አገር ቀደመች ብለን በቅናት አረን ተቃጥለን ሳናበቃ ምነው ምን ነካችሁ ብለው ውስጣቸው ደስ እያለው የዓለም መንግሥታት የሃዘን መግለጫቸው ላኩላት እናት ዓለም ኢትዮጵያ ደግሞ መቸስ የእናትን ነገር እናቶች ያውቋታል ሥፍሥፍ ብላ አጥንታቸውን ሲከሰክሱ ደማቸውን ሊያፈሱ ቃል የገቡ ጀግኖች ልጆች አሏትና እዚች ሱዳን ሰላም ጠፍቷልና ትንሽ የተቀያየሙ ስለመሰለኝ ሠላም አስከብሩ ብላ ልጆቿን በነዳጅ እየተቀጣጠለ ወዳለ የከሰለ እሳት ለብቻቸው ጥቂቶች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተሰው ይህቺ ሱዳን ባመጣችው ጣጣ፡፡

ሱዳን በሰሜን ከግብፅ በሰሜን ምሥራቅ ከቀይ ባህር በምሥራቅ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ቻድ በምዕራብ በደቡብ ከደቡብ ሱዳን ትዋሰናለች፡፡ ሱዳን ከአረብ ባህል ጋር ተዋህዳ ያለችና የምትጠቀምባቸውም ቋንቋ በአብዛኛው አረብኛና እንግሊዘኛ ነው የምትመራው በፕሬዝዳንቷ አማረ ኢል-በሽር እና በምክትሉ አሊ ኦስማን ጠሃ ነው ጠቅላላ የመሬት ስፋቷ 1,886,068 ኪ.ሜትር ስኮር እንዲሁም ጠቅላላ የህዝብ ብዛቷ በ2008 30,894,000 እንደሆነ ይገመታል፡፡

ይህንን የመሰለ ይዘት ቢኖራትም ሊከፋፈሉና ሁለት መንግሥት ሁለት አገር ከመሆን ያገዳቸው አልነበረም በ2011 በምርጫ አብላጫውን ድምፅ መገንጠል እንፈልጋለን በማለት ተስማምተው ተገነጠሉ የሚገርመው ነገር በዓለም ላይ በአፍሪካ አይደለም አንድም፡- አንድም አገር በህገ መንግሥቱ መገንጠልን አስመልክቶ ያካተተ አገር ከኢትዮጵያ በቀር ያፀደቀ አገር የለም ነገር ግን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሠላም ወዘተ… ጥያቄ ካስነሳ እኩልነት ከጠፋ እና መገንጠል ከፈለጉ ማንንም ሊያግድ እንደማይችል ሱዳኖች አሳይተዋል፡፡ ከዚያም ቀደም ብላ የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት የመገንጠልን አቋም በአንቀፅ 39 ከማካተቱ በፊት ኤርትራ ተገንጥላለች፡፡ ከነዚህ ሁሉ በመቅዳት ካናዳ ውስጥም የመገንጠል ሃሳብ ተነስቶ ንቅናቄው የተጀመፈ ቢሆንም የህዝብ ድምፅ እየተሰበሰበ ባለበት ሰዓት አንገነጠልም በአንድነት መቀጠል እንፈልጋለን ባዩ በመብዛቱ ወይም አብላጫውን ድምፅ በመያዙ ሊቀር ችሏል፡፡ ይህንን ንቅናቄ የገታው የአንቀጽ 39 የመገንጠል መብት በህገ መንግሥታቸው የመካተትና ያለመካተት ጉዳይ አልነበረም ያስቀረው ወደ አገራችን ጉዳይ ስንመለስ ብዙዎችን ያነጋገረና ያስቀየመ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ለምርጫ ቅስቀሳ ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ ያደረገ አንቀፅ ቢኖር አንቀጽ 39 ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአንቀጽ 39 ጉዳይ የመፈለግ ያለመፈለግ፣ የመውደድ እና የመጥላት ጉዳይ፣ የማውጣትና ያለማውጣት ጉዳይ ወዘተ… እንደፈለገው የሚያደርገው አይደለም ዛሬ መንግሥትም ህዝብም መኖሩን ጠልቶ እናውጣው ቢል የዘጠኙም ብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች ሊስማሙ ግድ ይላል አንቀፁን ለማውጣት ይሁንታቸው ወሳኝነት አለው፡፡ ነገር ግን ቢቀመጥስ ምን አጎደለ? ባለፈው ዓመታት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ምን አጠፉ? አንቀጹ ከመደንገጉ በኃላ ማን ተገነጠለ ይልቅስ ለመንግሥትም ለህዝብም እንደ ማስጠንቀቂያ /ማስፈራሪያነት/ ከማገልገል ውጪ እስኪ ይህ አንቀጽ ወጣ እንበል የመረረው እኩልነት የተነፈገ ነፃነት የጠማው ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካው ችግር ያጋጠመው ለመገንጠል ቢፈልግ አንቀጹ ላይ የለም ብሎ የሚከለከለው አለን? መኖሩስ እንዲገነጠል ያበረታታው አለን? (አደራችሁን ከፖለቲካው መንፈስ ነፃ በመሆን ተመልከቱት) ባለትዳሮች ትዳር ሲበቃቸው በቂ ምክንያት ኖራቸውም አልኖራቸውም የሚፈቱት ‹‹ፍቺ›› በህገ መንግሥቱ ስለተደነገገ አይደለም እነርሱ ስለፈለጉ እንጂ፣ ካናዳውያን መገንጠል ፈልገው ያልተገነጠሉት ህገ መንግሥቱ ስላልፈቀደላቸው አይደለም ህዝቡ ድምፅን በድምፅ ስለሻረ እንጂ፣ ደቡብ ሱዳን ከዋናው ሱዳን የተገነጠለችው አንቀጽ 39 በህገ መንግሥታቸው ስለ ነበረ አይደለም መገንጠል ስለፈለጉ ድምፅን በድምፅ ስለረቱ አብላጫውን ድምፅ ስላገኙ ህዝቡ በመገንጠል አቋም ላይ አንድ ስለሆነ እንጂ፡፡ የኢትዮጵያም ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም አብሮ ለመኖርም ለመገንጠልም የጋራ አቋማቸውና አንድነታቸው ይወስነዋል፡፡ ለዚህችም አገር ከድህነት ጋር ለምታደርገው ትግል ትንሳኤም ይሁን ውድቀት የህዝቧ አንድነት በድህነት ላይ ሆ! ብሎ መነሳት ወሳኝ ነው ሆ! ብለን ከምንወድቅ ሆ! ብለን እንነሳ ሆ! ብለን ከመገንጠል ሆ! ብለን አንድ እንሁን አንድ ያድርገን፡፡

በአንድ አገር ሁለት አገር ሁለት መንግሥት ሁለት ህዝብ ለመፍጠር እንደተገደዱ በአንድ ቤት ጥላ ስር አንድ ከመሆን ለመቆራረስ እንደተገደዱ የመቆራረስ የመገነጣጠል ዕጣ ፈንታ ሊደርሳቸው የተቃራቡ ትዳሮችና ጎጆዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምሬት፣ ፍቅር ማጣት፣ የእኩልነት መጥፋት፣ የመለያየት መብዛት፣ ያልተንሰራፋበት በሩን ያላንኳኳበት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አለበለዚያም ራሳቸውን የሚሸነግሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለልጆቻቸው ሲሉ የሚኖሩ፣ ለሥማቸው /ሰው ምን ይለኛል/ በማለት ላም እሳት ወልዳ እንዳትልሰው … ሆነባት እንደሚባለው የሆነባቸው ቤታቸው አንቀጽ 39 እና ደቡብ ሱዳን የሆነባቸው ነፃነት እየጣማቸው የሚኖሩ የነፃነት ያለህ የሚሉ፣ ነፃነትን በልጅ፣ ነፃነትን በሥም፣ ነፃነትን በሠው ወሬ፣ የቀየሩ የትዳር አንገታቸውን የደፉ፣ የትዳር አንገታቸው /ፊታቸው/ ፅልመት የለበሰ፣ ልቡናቸው የተሰበረ፣ ጨጓራቸው የተመለጠ … ጥቂት የማይባሉ ናቸው፡፡

በሃይማኖት ውስጥ የሃይማኖት ነፃነት ያጡ፣ በፖለቲካ ውስጥ የፖለቲካ ነፃነት ያጡ (የመናገርና የመደመጥ መብት ያጡ መናገራቸው በሠዓት የተገደበባቸው ቢናገሩ አሸባሪ የተባሉ …)፣ አገር እያላቸው በአገራቸው ላይ በነፃነት የመንቀሳቀስ ነፃነት ያጡ (ሁሌ ጥላቸው የደኅነት /የፖሊሲ/ አሻራ ያጠላበት፣ ቃላቶቻቸው ሁሉ በፍተሻ በቃላት መሠንጠቂያ የግድ ማለፍ ያለበት) አንቀጽ 39 የሚያምራቸው የደቡብ ሱዳን እጣ ፈንታ የሚናፍቃቸው እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ነገር ግን በአደባባይ እንዳይናገሩ እፍራት የተሰማቸው ሠው ምን ይለናል ብለው የሚጨናነቁ እንገለላለን፣ አሸባሪ እንባላለን፣ … ብለው ዝም ያሉ …

አንዳንድ የአገራችን የፖለቲካ ተንታኝ የአንቀጽ 39 መኖር አንዳችም አሉታዊ ተፅዕኖ የለውም ይልቁንም 80 ያህል የሆኑትን ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብሮና ተፋቅሮ እንዲሁም ተቻችሎ እንዲኖር አድርጎታል በማለት ይናገራሉ ነፃነትን ከመፈቃቀርና በልማት ከመተባበር ጋር አንድነትን ያላበሰ ነው በማለትም ያክላሉ የመገንጠል ሙሉ ነፃነት እንዲሁ ደግሞ በአንድነት በፍቅር መኖርን ያላበሰ ነው ይላሉና ያጠናክሩታል፡፡ ፖለቲካ እንዲህ ከሆነ ሃይማኖት፣ ትደር፣ ጓደኝነት፣ ቤተሰብ፣ … እንዲህ ዓይነት ነፃነትና ሠላም የሚያገኘው መቼ ነው? መቼ ነው የሃይማኖት መሪዎቻችን ነፃነትን ከሠላም ጋር ከእኩልነትና ከግልፅነት ጋር የሚያጎናፅፈን መቼ ነው? የትዳር፣ የጓደኝነት፣ … አገሮቻችን ሠላምና ነፃነትን የሚሠጡን?

አከራዮቻችን ከፍለን ለምንኖርባት ጎጆአችን ነፃነት የሚሰጧት መቼ ነው? በር ለምንድን ነው በደንብ የተከፈተው? መብራት ለምን በጊዜ በራ? ውሃ ለማን ተደፋ? እንግዳ ለምን በዛ? ከመጠን በላይ ለምን ሣቃችሁ? … እየተባልን መነዝነዙ መቼ ነው የሚያበቃው? መቼ ነው ለተከራየንበት ክፍል እንደ ደቡብ ሱዳን ነፃነታችንን አውጀን በየዕለቱ አንዳንድ ነገር ሳንገብር በወር ኪራይ ብቻ የምንኖረው? መብራት ቆጠረ የቤት ኪራይ ጨምሩ፣ ውኃ ቆጠረ የቤት ኪራይ ጨምሩ መባል ስጋት መች ይሆን የሚያበቃው???

ስናጠቃልለው ደቡብ ሱዳን እና አንቀጽ 39 የመዳፍ ያለመዳፍ የመፈቀድ ያለመፈቀድ ጉዳይ አይደለም የሞደርናይዜሽን /የዘመናዊነት/ ምልክት እንጂ ዘመናዊነታችንን በዘመናዊነት (በመከባበር፣ ነፃነት አንዳችን አንዳችንን በማጎናፀፍ) እንግለፅ! ቸር ይግጠመን፡፡  

1 አስተያየት:

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...