ሰላምና ጤናን ዘወትር የምመኝልሽ
ቤተልሄም እንደምን ሰንብተሻል
አሁንም ደግሜ እላለሁ ሰላም ጤና ዕድገት ብልጽግና የእግዚአብሔር ቸርነት ካንቺ ጋር ይሆኑ ዘንድ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡
የእንጀራ ቤት እያሉ የሚጠሩሽ ከኢየሩሳሌምም በስተደቡብ 10ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኚ
እነ ቢታንያ÷ ቁምራን÷ ኬብሮን… የሚያዋስኑሽ የአባቶቻችን
አምላክ ልዑለ ባህርይ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚለመንባቸው የያዕቆብ የሥጋው ቁራጭ የአጥንቱ ፍላጭ የደሙ ምጣጭ /ሚስት/ ዐረፍተ ዘመን
ሲገታት መዋቲ ሥጋዋ ግብዐተ መሬት የተከናወነብሽ ቅድስት ሀገር፤
በመሳፍንትም
ዘመን የኢብዳንና የቦዔዝ÷ የሩት የእሴይና የዳዊት ከተማ የነበርሽ÷ ልዑል እግዚአብሔር "እንደ ልቤ የሚሆን የእሴይን ልጅ አገኘሁ" የተባለለት÷ ንጉስ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል የተቀባብሽ፣
ነቢያት ትንቢት ተናግረው ይወርዳል፣ ይወለዳልም በማለት ሱባኤ ገብተው መድህኒዓለም ክርስቶስ የተወለደብሽ፤ በመወለዱም እረኞቹ በኋላም
ስብአ ሰገል መጥተው የጎበኙሽ ጌታንም ሲያገኙ ያመሰገኑብሽ÷ተድላ ደስታ የተፈፀመብሽ ሰውና መላዕክት በአንድነት ህብረት የፈጠሩብሽ÷
በአንድ ቋንቋ በአንድ ዜማ አምላከ አማልክት የሆነ ጌታን ያመሰገኑብሽ÷ ቤተልሔም ዛሬን እንደምን ደረስሽ? እድሜያቸው ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ህፃናትን ሄሮድስ ባያስፈጃቸውና ደስታው
ወደ ሃዘን ባልተለወጠና በጉያቸው ህፃን ታቅፈው የሰነበቱ እናቶች የሃዘን ፍም በማህፀናቸው÷ የሐዘን በትር ጀርባቸውን÷ የሃዘን
ሰይፍ በጉያቸው ተሰንዝሮ ሃዘንን ባያከናንባቸው ኖሮ ምንኛ ደስ ባለ፤ አንቺ ቅድስት ሃገር ቤተልሔም ዛሬስ መንደሮችሽ፣ ጉድባዎችሽና
አደባባዮችሽ ሐዘን ነው ደስታ የተንሰራፋባት? ነገሥታትና መኳንንቶችሽስ እንደምን ሰንብተዋል? እንደዚያኔው ‹የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ›
እንዲሉ የሄሮድስ የልጅ ልጅ ይሆኑ? ወይስ?... ሕዝቦችሽስ እንደምን
ናቸው? ከብቶችሽስ?
መልአኩ
የዳዊት ከተማ በሆንሽ በቤተልሔም በከብቶች በረት በግርግም መወለዱን ለመልዓክ ፍራት ማራቅ ልማዱ ነውና ‹‹አትፍሩ›› እያለ ታላቅ
የምሥራችን ‹‹እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ
ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› ሉቃስ 2÷10-11 በማለት የተናገረ መልዓክ ዛሬስ እየመጣ ሕዝቦችሽን ከፍርሃት ያድናቸዋል?
የምስራችን ያበስራቸዋል?