ማክሰኞ 2 ኤፕሪል 2013

በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ 1

በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ
‹‹…. የምነቅፍብህ ነገር አለኝ…››

ወቅቱ የዚህ የሽብር ወቅት መገባደጃ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት በር መክፈቻ ሰሞን ነበር እኔ አንተ እነዚያ በአጠቃላይ ሁላችንም በአብተ ክርስቲያናት ጥላ ሥር መሰባሰብ የጀመርነው ጊዜውን እንደማትዘነጋው ተስፋ አለኝ በአሥራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ ውስጥ፤ በአብያተ ክርስቲያናት አጸድ ሥር እየተሰባሰብን የቤተክርስቲናችንን ጥንታዊ የአባቶቻችንን ቋንቋ ወንጌልን እየተማርን በየመንገዱ በየጓዳው በየትምህርት ቤቱ በየመንደሩ ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ ማነው? …›› የሚለውን መዝሙር እየዘመርን አንገት ደፍተን እጅ እየተነሳሳን ትህትናን እየሰበክን ሰንበት ት/ቤት መማርን የጀመርንበትን ሠሞን የዛሬውን አያድርገውና ሲጠሩን አቤት ሲልኩን ወዴት የምንልባትን ሰሞን የጠዋት ተማሪ ከሆንን አሥራ አንድ ሰዓት ለሚጀመረው መርሐ ግብር አሥር ሰዓት ስንሄድ ስምንት ሰዓት ለሚጀመረው የቅዳሜና እሁድ ጉባኤ ምሳችንን በልተን አረፍ እንኳን ሳንል በረን ከቤተክርስቲያን የምንገኝበት ወቅት ያለጥርጥር እንደማትዘነጋው እገምታለሁ በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ ከአፍ እስከ ገደፍ ጢም የሚለው የቤተክርስቲያን ደጃፍ ሁለት ሦስት ሆነን ከጀመርንበት እስከ አሁኑ ያለውን እዚያው ስላለህ በደንብ አድርገህ ታውቀዋለህ የፆምና የፀሎቱንስ ነገር ቢሆን ቀጥ ብለን ሳንነቀነቅ ሳንሰስት አንድ መዝገበ ፀሎት ሙሉ ሲጥ አድርገን ጨርሰን የዕለቱን መዝሙረ ዳዊት ደግመን ኪዳን አድርሰን ቅዳሴ አስቀድሰን እንደማይበቃን ታስታውሳለህ ሱባኤስ ቢሆን ላባችን የክረምት ጎርፍ እስኪመስል በኛ ላይ እስኪወርድ የጣቶቻችን አንጓ የፆም ወቅት አሻራን ይዘው እስኪቀሩ የምንሰግደውስ ስግደት በቃችሁ ‹‹ትሞታላችሁ›› እየተባልን እንኳን ለዚያውም ያለጥሬ ንክች አናደርግም የምንለው የፆም ወቅት ትዝ ይልሃል? … ስንቱን ላንሳው ብቻ ሁሉም ትዝ ይለኛል የእንግዳ መስተንግዶውስ እቤታችን የመጣውን እግሩን አጥበን ያለንን አብልተን እንደ አባቶቻችን ሥርዓት አልጋም ይሁን ምንጣፋችንን ለቀን የምናስተኛው በጉባኤም እንግዳ መምህር ሲመጣ ተራችንን ለቀን አስተምሩን የምንለው ትዘነጋዋለህ … አገልግሉስ ስንባል የሁለትና የሦስት ሰዓት መንገድ ሁለት ሁሉት ሆነን እንደ ሐዋርያት በፍቅር የጀመርንባቸውን ሰሞን ታስታውሰዋለህ … ወንድማለም ብቻ ምን ዋጋ አለው የአንድ ሰሞን ሰዎች ብቻ ሆነን ‹‹ሠሞነኛ›› የሚል ቅጥያ ሥም ይዘን ቀረን፤
‹‹ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል›› እንዲሉ አበው ሲተርቱ ጀማሪ አርበኞች ብቻ ሆነን ቀረን፤ ከትናንቱ ቦታ ጠፍተን ከትናንቱ ዓላማችን ተናውፀን የሩቅ ተመልካች ሆነን ቀርተናል በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ ምናልባት እኔኮ አንተ እንደምትለው በነበር የቀረሁ አይደለሁም፡፡ ዛሬም አለሁ አገለግላለሁ፤ እፆማለሁ፤ እፀልያለሁ፣ እሰግዳለሁ፣ ሱባኤም ሲኖር እመጣለሁ ትለኝ ይሆናል ወንድማለም ሁለመናህ ይገባኛል ሃሳብህ ሃሳቤ ግብርህ ግብሬ ነው ምንም አይጠፋኝም ግና ትላንት በነበርክበት እምነት ዛሬ አለህ? በትላንትና በዛሬ አድራጎትህ መካከል ባለው ለውጥ አታፍርበትም ሕሊናህን አልሸጥክም ‹‹ሰው ምን ይለኛል?›› በሚል ትብታብ አልተተበተክም ለኃጢአት ተገዢ አልሆንክም ነፍስህን እንደያኔው ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥተህ ነው ያለኸው ሰው ሰራሽ ሮቦት አልመሰልክም? … ወንድማለም ብቻ ባጠቃላይ በሁለት እግር የሚንቀሳቀስ ሰው መሰል እንስሳ መስለሃል ‹‹ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንስሳትን መሰለ›› እንዳለው ልበ አምላክ ዳዊት፤ ደግሞስ ያኔ የምትፆመው የፆም ሰዓት፣ የጸሎት ብዛት፣ የስግደቱ መጠን፣ ለአገልግሎት ያለህ ፍቅርና ትህትና፣ አኗኗርህን የቤተክርስቲን መምጫ ሰዓትህ ለውጥህ በአጠቃላይ ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል የክርስትና ሕይወት ፍሬህ ከትናንቱ ዛሬን ስንት አፍርተህ ተገኝተሃል ሰላሳ፣ ስልሳ ወይስ መቶ ያማረ ፍሬ አልያም ዝም ብሎ ገለባ ወደ እሳት የሚጣል እንክርዳድ ብቻ ለማንኛውም መልሱ ላንተው ትቼ ትዝ ማሰኘቱን አሁንም እቀጥላለሁ፡፡
በቅርቡ የማውቅህ ወንድሜ ለመሆኑ ‹‹መሰባሰባችንን አንተው›› የሚለው የልበ አምላክ ዳዊትና የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አባታዊ መልዕክትን ዛሬ ዛሬ እንዴት ነው እየተጠቀምከበት ያለኸው? በመንፈሳዊ ሕይወት ልትጎለብትበት፣ ለአገልግሎት ልትበረታበት፣ እርስ በርስ ልትተያዩበት፣ ኤልያስ አንዱ ለአንድ መሰናክል ሊሆንበት፣ ልትተጫጩበት፣ ወሬ ልታወሩበት፣ ልትደልቱበት፣ … ወይስ ለምንድን ነው? ወንድማለም ‹‹ይህ ምስጢር ታላቅ ነው›› ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመሰከረለትን ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ጋብቻ መልካም መኝታውም ንፁህ ይሁን›› ብሎ ያስጠነቀቀውን አንተ በቤተክርስቲን ምስጢርና ስርዓት ሽፋን ምን እየሰራህ ነው ያለኸው በውኑ የምታደርገውን ድርጊት እግዚአብሔር የወደደው ይመስልሃል? ‹‹… አይዞሽ መንፈሳዊ ሕይወትሽ ሳይዘናጋ ሥጋዊ ኑሮሽም ሳይጓደል አብረን እንኖራለን›› ብለህ ሔዋንን የምትሸነግልበት የሽንገላ ከንፈርህ መቼ ድረስ የሚቆይ የትስ የሚያደርስህ ይመስልሃል? ልብ በል ወንድሜ ከዚህም ባሻገር የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የሆነውስ ሆኗል አንዳንዶች እንደሚሉትም ‹‹ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም›› ብለን እኔና አንተ ልንቀመጥ አንችልም ላለፈው ላፈሰሰው ሕይወታችን በንሰሐ እያደሰን ለሚመጣው ሕይወታችን ደግሞ በሥጋና ደሙ አንፀን የምንቆይ መሆን ግዴታችን ነውና፡፡
በቅርብ የማውቅህ ወንድሜ አድርጌአለሁ ለውጥ አሳይቻለሁ የሚል ስሜት በላይህ ይሰማኛል እውነት ነው አድገሃል ለውጥም አሳይተሃል ከዚህ ወዲያ ማደግ ከዚህ ወዲያ መለወጥ ምን አለ? እንደ ካሮት በትዕቢት ፈርጥመህ ቁልቁል ወደታች አድገሃል እንደ እስስት ገላ ዘመኑን የጉባኤውን መሳሳት የሰውን መዳከም ተመልክተህ ከቀድሞ ምግባርህ ርቀህና ቀርተው ለውጥ አሳይተሃል? … ወንድማለም የእናቴ ልጅ መቼ ይኼ ብቻ ‹‹ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርት ነን መናፍቃንን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ ታግሠህማል›› እውነት ነው የእናቴ ልጅ በቤት ቁጭ ብለህ እስከ አንድ ቀን በደንብ እስከምትጠፋበት ዕለት ድረስ ከደሞዝህ አሥራት በኩራት የመክፈል ሥራህንና ድካምህ በእውነት እኔም ሳልቀር በቀሪ ደረሰኝህ አውቃለሁ እኪነኩህ ብቻ ድረስ አፍንጫህ ላይ ያለችውን ትዕግሥትህን በደንብ አድርጌ አውቃለሁ ይልቁንም አፅራር ቤተክስቲን መናፍቃንን በትምህርተ ወንጌል ልትገስፅ እየተገባህ ብርቱ መሰል ደካማ ትዕግስትህንም አውቃለሁ ዳሩ ግን ‹‹በእውነት ስለ እውነት ስለክርስቶስ መንግሥት ጸንተህ አልደከምክምና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃል፡፡›› አንተም አትሰለችም ብዕሬም አትነጥብም ደግሜ እፅፋለሁ፤ ተለውጠህ ቆየኝ፡፡
በቅርብ ለማውቅህ ወንድሜ ከቅርብ ከምታውቀኝ ወንድምህ


ይቀጥላል

‹‹ስመ አምላክ ነጋድያን ይታቀቡ››

ንግድ› የሚለውን ቃል ስንመለከት ሐሳባችን ወደብዙ አቅጣጫ ሳይበታተን አልቀረንም ወደ ብዙ ቦታም ሳንደርስ አልተቀመጥንም ከአነስተኛ ሱቅ እስከ ታላላቅ መደብሮች ወይም ጉምሩክ ድረስ ከጉልትም አንስተን እስከ ወደብ ላይ የሚለዋወጡት የንግድ ሥራዎች ሳንቃኝ አልቀረንም አልያም ደግሞ በብሉይ ኪዳን የነበረውን የከሊዳውያን ዑር፣ የግብፅ ጢሮስና ሲዶና እስራኤልን እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ዘመን ለእስራኤል ሃገር በሮሚና በኢጣልያ የሚደረገው ታላላቅ የንግድ ሥራ በአይነ ሕሊናችን ሳንቃኝ አልቀረንም፡፡ በአጭር ቃል ከነዚህ ሁሉ እንደምንገነዘበውና እኛም እንደምናከናውነው አንድን ነገር በአንድ ነገር መለወጥ ወይም አንድ ነገር በብር መሸጥ ማለት ንግድ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ንግድ የሚለው ቃል በብዙ አይነት መንገድ ስያሜውን ሊያገኝ ይችላል፡፡

ይድረስ ለፈጣሪ

ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ተስፋዬ ማን /ምንድን/ ነው? ከወደየትስ ነው?
እንደምን አደርክ እንደምን ዋልክ እንዳልልህ ባህሪህን መመራመር አይቻለኝም ስለጤንነቴም እንዳልነግርህ ሁሉን የምታውቅ ቸር አምላክ ነህ እንዳላምንህ ሁሉን ነገር ሳይጠይቁህ በልግስና አውቀህ የምትሰጥ ነህ ስላደረክልኝ ዋጋ እንዳልከፍልህ እንደምድራዊ ነገስታትና መኳንንት እጅ መንሻን የምትሻ አይደለህምና ብቻ የባህርይ ገንዘብህ የሆነውን ምስጋና ብቻ ላቅርብልህ ዘወትር ከኔ ሳትርቅና ሳትለየኝ የረድኤት እጅህ ሳይታጠፍብኝ የምህረት አይንህ ከእኔ ሳይነቀል እንዲሁ የምትናፍቀኝ ከውኃ ጥማት ከእንጀራ ረሃብ ሁሉ የምትብስብኝ መለኪያ መጠን የሌለው ፍቅርህ የሚስበኝ አምላኬ ሆይ አስቀድመህ ሰማይና ምድርን ፣ በምድርም ላይ የሚመላለሱ በእግር የሚሽከረከሩ በልባቸው የሚሳቡ በክንፋቸው የሚበሩ በሰማይና በምድር ለኔ ፈጠርክ፣ እፅዋትንም ሳይቀር ከአዝርዕት ጋር እመገባቸው እገለገልባቸው ዘንድ ለእኔ አዘጋጀህ /አደረግህ/ ከዚያን ባሻገርም ከሁሉ በላይ ራስህን በማዕከለ ምድር በቀራንዮ አደባባይ አይሁድ ምራቃቸውን እየተፉብህ እንደብርሃን የሚያበራ ፊትክን በጥፊ ተፀፋህ ቸርና ለጋስ እጆችህን የወንጀለኞች መቅጫ በነበረው አሁን ግን ትምክህታችን በሆነው መስቀል ቀኝና ግራ እጆችህን ቸነከሩህ ደረትክን በጦር ተወጋህ ደምህን አፍስሰህ ሥጋህን ቆርሰህ ለኔ ተሰዋህ፤
ለእውራን ብርሃን ለአንካሶች መሄጃቸው ጤና ላጡ ጤናቸው ሰላም ላጡ ሰላማቸው የሆንክ ደግ አምላክ ሆይ ለእንደኔ አይነቱ ደካማ ፍጡር ብርታት የሆንክ አምላኬ ሆይ ባህሪህን ካላስቆጣሁና ካላስከፋሁህ አንድ ነገር እጠይቅሃለሁ፤ እባክህ አምላኬ ሆይ ተስፋዬ ምንድን ነው? ማንስ ነው? ከወደየትስ ነው? ብዬ ጥያቄ ሳቀርብልህ ዘወትር የማይለኝን አፅናኝ መልስህን ከምድር በማንጋጠጥ የምጠይቅህ የዘወትር ጠያቂህ /ለማኝህ/ ምዕመን ነኝ፡፡
ተፃፈ ለልዑል አምላክ

ዓርብ 29 ማርች 2013

ይድረስ …

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ እጅግ የከበርሽ ፀጋን የተመላሽ ሆይ ምስጋና የባህርይ ገንዘቡ ከሆነው ልጅሽ ቀጥሎ የምትመሰገኚ የአምላክ እናት ሆይ አመሰግንሻለሁ፡፡
ልጅሽ ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከምድር አሸዋ እጅግ የበዛ ሐጢያቴን ሳይመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ እስከዛሬ እያወኩኝ በድፍረት ሳላውቅም በስህተት የሰራሁትን በደል ሳስብብኝ ለዚህች ሰዓት ያደረሰኝ በአንቺ ምልጃና ፀሎት ነውና፡፡
ድንግል ሆይ ‹‹አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ ከአዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ›› ብለው አባቶች አመሰገኑሽ እመብርሃን በእውነት ያለሐሰት ከበደሌ ብዛት ካንቺ ምልጃ አንፃር የአዳም ሳይሆን ተስፋነትሽ የኔ የብቻዬ ነው ድንግል ሆይ ራስን መውደድ እንዳይሆንብኝ ግን ይህ ርኅራኄሽ ይህ ምልጃሽ ለአዳም ዘር ሁሉ ይሁን፡፡
ድንግል ሆይ ስምሽን ባነሳሁና ባሰብኩ ቁጥር ውስጤ ስለሚረበሽ ከጎኔ በመሆን አይዞህ በይኝ አፅናኚኝ ተስፋህ እኔ ነኝ በይኝ ተስፋዋ ለመነመነ ግራ ቀኟ ለጨለመባት ሕይወት ረሐብና ጥም ላጠቃት ነፍሴ መፅናኛሽ አለኝታሽ እኔ ነኝ በያት፡፡
የአምላክ እናቱ ሆይ ልጅሽ ከቅዱሳኑ ጋር ከነቢያትና ከወዳጆቹ ከመላዕክት ጋር ዘወትር በሕይወቴ እንድስተናገድ በእኔነቴ ላይ እንድነግስ ደግሞም በሚገለጥበት ሰዓት ከቀኙ ሊያቆመኝ የሚችለውን መልካም ሥራ ሠርቼ ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ ርስቱን ከሚያወርሳቸው ጋር እንዲደምረኝ ተማልደሽ አማልጅኝ፡፡
የኃጥአን ተስፋ የሆንሽው ሆይ በሐጢያት ስወድቅ ኃይልና ብርታት ሁኚኝ ከሐጢያትም ሥፍራ ተነስቼ ሐጢያቴን በማመን ሐጢያቴ የሚሰረይበትን ንሰሐ እንድገባ አበርቺኝ ከልጅሽም ጋር ሕብረት አንድነትን ልፈጥር የምችልበት ከሐጢያት ሁሉ የምነፃበትን መለኮት የተዋሃደው የልጅሽን ሥጋና ደም የመመገቡን ፀጋ አድይኝ፡፡
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዳለሽ ‹‹…. ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ መዓትን ያይደለ ምህረትን አሳስቢ ለጻድቃን ያይደለ ለተዳደፉት አሳስቢ›› ለኔ ለሐጢያተኛው ዘወትር እንድታሳስቢ በግብፅ በረሃ መሰደድሽን መራብ መጠማትሽን ልጅሽን ለማዳን ብለሽ ከላይ በአናትሽ የገባው የፀሐይ (ብርሃን) ግለት እግርሽን የቀቀለውን ረሞጫ አሳስቢ ምንም እንኳን ኃጢያቴ ቢበዛ የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስምና ሁሉ ቢቀር ለንሰሐ የምበቃበትን ልቦና አሰጪኝ ንሰሐ ዘማዊን ድንግል እስከ ማድረግ ደረጃ ያደርሳልና፡፡
እመብርሃን በዶኪማስ ቤት በሠርጉ በተጠራሽ ከልጅሽ ከወዳጆቹ ከቅዱሣን ጋር በሠርጉ በታደማችሁ ጊዜ ድግሱ አልቆበት በተዋረደ ጊዜ አንቺም ጭንቀቱን ተመልክተሸ ወደ ልጅሽ ነግረሽ ቤቱን በረከት በበረከት እንዳደረግሽ ውሀውን ወደ ወይን እንዳስለወጥሽ እኔም በዚህ ምድር ስኖር ሕይወቴ ባዶነት ይሰማዋልና ምግባር ትሩፋት የለኝምና እጅግም የማሳፍር ሆኛለሁና በጣምም ተዋርጃለሁና ከውርደት አድኝኝ ጎደሎ ያይደለ ሙሉ አድርጊኝ በምግባር በትሩፋት አትረፍርፊኝ ከሐፍረት ሰውሪኝ ውሃ … ውሃ ያለው ሕይወቴንም አጣፍጪው፡፡
ድንግል ሆይ ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆቹ መካከል ሥምኦንና ሌዊ በሴኬም ልጆች ላይ እጃቸውን ባነሱ ሰዓት እንደረገማቸውና እንደለያቸው ከዘመናት በኋላ እስራኤላውያን ጣኦትን ሲያመልኩ እግዚአብሔርም ሲቆጣ ሙሴም ከፊታቸው ቆሞ ‹‹የእግዚአብሔር ወገን የሆናችሁ ተለዩ›› ባለ ጊዜ የሌዊ ነገድ ራሱን ለእግዚአብሔር ቢለይ እግዚአብሔር መረጠው አከበረው በመጨረሻም ርስትን ሲከፋፈሉ ሌዊን ካህን አድርጎ እንደሾመ እንደባረከ እንዲያገለግላቸው እንደመረጠው ሌሎች ርስት ሲከፋፈሉ እግዚአብሔር ለአንተ ርስትህ እኔ ነኝ እንዳለው ባንቺ አማላጅነት ሐጢያቴና በደሌ ከሌዊ እጅግ የበዛውን ልጅሽን ታሪኬን በደሌን እንዲቀይረው እኔም እንድቀየር አድርጊኝ እንደ ሌዊ አገልጋይ ካህን አድርጊኝ ባልልም ሐጢያቴን እንዲያቀልልኝ አሳስቢ ለሌዊ ርስቱ እንደሆነ ርስትህ እኔ ነኝ ይለኝ ዘንድ አሳስቢ፡፡ እኔ በኃጢያት ማኛ የተጣልኩትን ልጅሽ በፍፁም ፍቅሩ ሁለት እጄን ይዞ እንዲያወጣኝ አሳስቢልኝ፡፡
ድንግል ሆይ በቀረውስ ምስኪን ሰው ድሃ ሰው ከባለ ፀጋ ፊት ሲቆም ብዙ ነገር ይለምናልና ባለፀጎችም መመፅወት ባህሪያቸው ነውና ከባለፀጎች ሁሉ ባለፀጋ ከሆነው ልጅሽ ዘንድ የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ አሰጭኝ፡፡
ቅድስት የምትሆን የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን ባርኪያት ሕዝቦችዋን ከጦርነት ከእልቂት ከረሃብ ከቸነፈር ከበሽታ ከክህደት ሁሉ እንዲሠውራት ለልጅሽ አሳስቢ፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያንና አድባራትንና ገዳማትን ጠብቂልን ጉባኤያትን ማኅበራትን የወንድሞችን ሕብረት አጠናክሪ ከጠላት የፈተና ጦር ሠውሪያቸው፡፡
እኛ ልጆችም የእምነት የምግባር የትሩፋት ሠው እንድንሆን አሳስቢ፤ በሩቅም በቅርብም ያሉትን እንድናስባቸው ያሳሰቡንን ሁሉ አስቢ፡፡
ድንግል ሆይ በተረፈው በተሰጠሸ ቃልኪዳን መሠረት በሠላም ውዬ እንድገባ በቀንና በሌሊት ጥበቃሽ አይለየኝ ልጅሽ ለአንደበቴ ለልቡናዬ ለእግሬ ጠባቂ መላዕክትን እንዲያቆም መልካም ፈቃዱ ይሁን፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን አሜን፡፡
ከተስፈኞች አምባ

* ሰሞኑን ዲ/ን ዳንኤልና ፕሮፌሰር መስፍን መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ በሚላዉ የፕሮፌሰር መጽሓፍ ላይ ሲነጋገሩ ነበር፤ ብዙዎችም አስተያየት ሰተዋል፡፡ እኔም እንዲህ ብያለሁ፡እነሆ፡-
ለኔ ሁለቱም የአገር ቅርሶቼ ናቸዉ፤ ይህን ያልኩበት የራሴ የሆነ ምናልባት ሌሎችም ሊጋሩት አልያም ላይጋሩት የሚችሉት ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይኸዉም ሁለቱም ሰዎች በአገራችን ጉዳይ ላይ በማህበራዊ ነክ ጉዳዮች ላይ ብዙ ፅፈዋል ፣ አስተያየት ሰተዋል ተችተዋል. ጥናታዊ ፅሁፎችን አቅርበዋል፣ ወዘተ… ሆኖም ግን

* የየራሳቸዉ ደካማ ነገር የላቸዉም ማለቴ አይደለም፡ ይኖራቸዋል! ነገር ግን እነደ ጸሐፊነታቸዉ (አይከን) እንደ መሆናቸዉ መጠን በጣም ጥንቃቄ ሊያደረጉ ይገባ ነበር አሁን ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ሊከባበሩና ሊደማመጡ ነገሮችን በጥሞና ሊከታተሉ ይገባል፣ ከመናገርና ከመጻፍ ለቆጠቡ ይገባል (ፕሮፌሰርን ማለቴ ነዉ) ዲ/ን ዳንኤል የመሰለዉን መናገር ይችላል ፕሮፌሰር ግን የጻፈዉን ነገር ተደፈርኩ በሚል ስሜት ሳይሆን በእርጋታና በጥሞና ቢያዩት፤ መልሱን የተጠቀሙበትን ቃላትም ቢፈትሹት ይሻል ነበር ይሁን ያ አልፋል፣ ያላለፈ ነገር ግን ይቅርታ ብሎ በጠረጴዛ ዙርያ ታሪክን መፈተሽ ይቻላል፡፡

* ህብረተሰቡን መወረፍም፣ ሌላ ስም መስጠትም አግባብ አይደለም እንዲያዉም እንበል ከተባለ የታሪክ መክሸፍ ሳይሆን የግለሰብን ማንነት መክሸፍና መዉረድ (መዝቀጥ) አይተንበጣል፤ ተሳዳቢነትና ንቀት የምንም ምልክት አይደለምና፡፡ ለዚህ ትዉልድ ምንም እንኳን ያደረግንለት ጥቂት ነገር (የምናቀዉን ነገር የሰጠነዉ ) ቢኖርም ከዚህ ህዝብ የተሰወረና እኛ ጋር ብቻ ያለ ነገር የለም! ያገኘነዉ ከህዝብ ነዉና ህብረተሰቡም ከኛየተሻለ ነገር አለ፡ አልፃፈዉም እንጂ፤ እዉቀቱን ገበያ ላይ አላዋለዉም እንጂ፡፡ ስለዚህ አንዱን ጥሎ ሎላዉ አንጠልጥሎ ጉዞ አይቻልምና ያለተገነዘቡአቸዉን ነገሮች ወደ ኋላቸዉ ተመልሰዉ ይመልከቱ!!!!!! መልዕክቶ ነዉ፡፡

ዓርብ 22 ማርች 2013

“መልዐኩ እና ደራሲዉ”ክፍል ሁለት!



ክፍል ሁለት!
መልዐኩ እና ደራሲዉ
“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ ምድርም ባዶ ነበረች ፡ … … ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ አንድ ቀን፡፡” ዘፍጥረት11፡1-5
እንደ ፈረንጆቹ  ዘመን አቆጣጠር ማርች 22-2012 ምክሰኞ ቀን  “የደረሰ ረታ እይታዎች” በምትሰኝ ጥቂት መጦመርያ መጦመርን  “ሀ” ብዬ ስጀምር  “መልዐኩ እና ደራሲዉ” ፤ “… … … የእግዚአብሔር መልዐክ ጋር የመጀመሪያዉን የደራሲዉን እና የመልዐኩን ግንኙነት እዚህ ላይ በማቆም በቀጣዩ ምዕራፍ እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን! ” በማለት ተሰነባብተን እንደነበር የአንድ አመት ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡እነሆ መቸስ እንደማይሞላ፤ መልዐክና ደራሲም ተገናኝተዉ በቀላሉ አይለያዩምና ፤ይኸዉ ዘግየቼም ቢሆን ድፍን አንድ አመት በመዘግየት ክፍል ሁለትን ይዤላችሁ መጣሁላችሁ፡፡
እንኳን ለጦማርችን አንደኛ ዓመት አደረሰን! መልካም ንባብ፡፡
“መልዐኩ እና ደራሲዉ”
መልዐኩ፡-“ አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጅህ ሥራዎች ናቸዉ” እንዲል መፅሐፍ በመዝሙረ ዳዊት 101፡25 ከመፍጠርህ አንስቶ ሥትኖርበት የነበረዉን ምድር አሁን ዳግሞ ያለህበትን ሰማይ በአንድነት ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸዉ እግዚአብሔር ነዉ፡፡
ደራሲዉ፡-እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ሲፈጥር ይህን ሰማያዊ ዓለምና ያኛዉን ዓለመ ምድር (ምድራዊ ዓለም) ሥንት ፍጥረት በመፍጠር ሊሞላዉ ቻለ፡፡
መልዐኩ፡-ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር የፈጠረዉ ፍጥረት ሁሉ ቢቆጠር ፍጥረት በሙሉ ቆጥሮ አያጠናቅቀዉም፤ ነገርግን እንደ ሥነ-ፍጥረት ሥርዓት ብዙዉን አንድ ፡ብዙዉን አንድ እያልን ሥንቆጥረዉ በ22ቱ አርዕስተ አበዉ ምሳሌ 22 ናቸዉ፡፡
ደራሲዉ፡-አርዕስተ በዉ የሚባሉት እነማን ናቸዉ?ምንስ ነዉ?
መልዐኩ፡-አዳም፣ሴት፣ሄኖስ፣ቃይናን ፣መላልኤል፣ ያሬድ ፣ሄኖክ ፣ማቱሳላ፣ ላሜህ ፣ኖህ ፣ሴም፣ አርፋክስድ፣ ቃይናን፣ ሳላ፣ ኤቦር፣ ፋሌቅ፣ ራግዉ፣ ሴሮህ፣ ናኮር፣ ታራና አብራም… ናቸዉ፡፡
ደራሲዉ፡-22ቱንም ፍጥረታት በአንድ ቀን ፈጥሮ አጠናቀቀ?
መልዐኩ፡-መፅሀፍ በአንድቅ ተደርሶ ታትሞ ለአንባቢያን እንደማይደርስ ሁሉ ይህም ዓለም በአንድ ቀን ተፈጥሮ አልተጠናቀቀም ፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በጊዜ ሠርክ ጀምሮ በዕለተ ዓርብ ለፍጥረት ስድስተኛ ለቀመር አራተኛ ማለት ነው፡፡
በዕለተ እሁድ ሥምንት ሲፈጥር እነዚህም አራቱ ባህርያተ ሥጋ እና ጨለማ፣ ሰባቱ ሰማያት፣ መቶው ነገድ መላእክት እና ብርሃን ናቸው፡፡ አራቱ ባህርያት ሥጋ የሚባሉት ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት ናቸው፡፡ በባህርዬ አራት ነገሮች አሉብኝ ሲልም ፈጥሮአቸዋል፡- እነዚህም ኃያል ነኝ ሲል እሳትን ፈጠረ፤ እሳትን ውኃ ካልከለከለው ቆላ ደጋ ሳይል እንዲያጠፋ እግዚአብሔርም ቸርነቱ እስካልከለከለዉ ድረስ ሰማይንና ምድርን በአንድነት ሊያጠፋ ይቻለዋልና እንዲህ አለ፡፡

ማክሰኞ 19 ማርች 2013

12 ምክሮች ለወንዶች


12 ምክሮች ለወንዶች
       ቤተሰብ መሥርተው ሲኖሩ ትዳር ሁልጊዜ በሰላም የታጀበና የሠመረ ነው ብለው ካሰቡ ለትዳርዎ መሣካት ምን እርምጃ እንደወሰዱ በአንዳፍታ ያስቡ አልያም ሁልጊዜ ንጭንጭ ንትርክና ሰላም አልባ ትዳር ይዘው እርስዎና ቤተሰብዎ በጭንቀት የሚጓዙ ከሆነ ለመፍትሔው የሚቀጥለውን ጽሁፍ በርጋታ ያንብቡ ባሎች ደስተኛና የተቃና ትዳር ጤናማ የሆነ የባልና የሚስት ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚከተሉትን 12 ነጥቦች መከተል አለባቸው ይህንን ሲያደርጉ ታዲያ በግላዊ ሰመመን ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡ በዚህም መሠረት እንዲህ ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡
1.  የትዳር ጓደኛዎ እንደማንኛውም ሰው ተፈቃሪና ተከባሪ ለመሆን እንደሚሹ አምነው ይቀበሉ፡፡
2.  ባለቤትዎ የግልፈተኛነት ስሜትና የኢኮኖሚ ድቀት እንኳን ቢደርስባቸው ፍቅሬ ሳይቀንስ ጠንክሬ በመስራት ጥሩ ሚስት አደርጋታለሁ ይበሉ፡፡
3.  ባለቤትዎ የትዳር ጓደኛዎ እንጂ በእናት ምትክ የመጡ ያለመሆናቸው ይረዱ፡፡
4.  ሕይወት ጣፋጭነት የሚኖረው በትዳር መሆኑን አይዘንጉ፡፡
5.  ሚስትዎ ጓደኛዎ መሆናቸውን አምነው ለጥሩ ጓደኛ የሚሰጠውን ክብር ይስጧቸው፡፡
6.  በማንኛውም ነገር ባለቤትዎ የእርስዎን ሃሣብና መንገድ ይከተላሉ ብለው መጠበቅ አይገባዎትም፡፡
7.  ወንዶችና ሴቶች እንደ ጾታቸው እንደሚለያዩ ሥጋዊና /አካላዊ/ ውስጣዊ ስሜታቸውም እንደሚለያይ መገንዘብ እንዳለበት አይዘንጉ፡፡
8.  የሴትን ሥነ-ልቦና ማድነቅና ከዚያም ስለባለቤትዎ ፀባይ አስተያየት መስጠት የማይጎዳ መሆኑን አይዘንጉ፡፡
9.  ሚስቴን ባንቋሽሻት ወይም ብሰድባት ፍቅርና አክብሮት መጠበቅ አልችልም ብለው ያስቡ፡፡
10.             ሚስቴ እኔን በጎ እንደማሰብና የማደርገው ድርጊት ሁሉ ከሰው ያልተለየ ቀና መሆኑን እንደምታስብ ማወቅ አለብኝ በማለት ራስዎን በራስዎ ያሳምኑ፡፡
11.             ትህትና ስጦታ ማበርከትና ደግነት ማሣየት ማስፈለጉን አይርሱ፡፡
12.             ሚስትዎን ማስተማር ድርሻዎ ነው፡፡ የእረፍት ስሜት ሳይሰማት ወሲብ የፍቅር መግለጫና ለጤንነትም አስፈላጊ መሆኑን ማሳወቅ እንዳለብዎት አይርሱ፡፡

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...