ረቡዕ 24 ጃንዋሪ 2024

ቃና ዘገሊላ

 ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡



የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡

በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ›› ‹‹የጌታ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐ 2÷1) እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጉ ላይ ታድማ ነበር፡፡ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ሥርዓት ስላልሆነ፤ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሰርጉ ታድመዋል፡፡ ይህም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ (ተገቢ ስላልሆነ) ነው፡፡ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረ ባማረ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አስተናባሪዎቹ በጭንቀት ባሕር ሰጥመው ምን እንደሚያደርጉ ግራ በገባቸው በጠበባቸው ጊዜ የችግር ጊዜ ደራሽ የኃዘን ጊዜ አፅናኝ የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረ በፀጋ የተሞላች ናትና (ሉቃ 1÷28) ማንም ሳይነግራት የልቦናቸውን ጭንቀት አይታ፣ ጎዶሎአቸውን ተመልክታ ወደ ልጇ ወደ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹ወይንኬ አልቦሙ›› ‹‹ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል›› አለችው፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለሊቀ ምርፋቅ (ለአሳዳሪው) እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል አንተ ግን መልካሙን እስከ አሁን አቆይተሃል›› አለው፡፡ ወይኑም በሰው እጅ ያይደለ በሠማያዊው አባት የተዘጋጀ ስለነበር ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር፡፡


‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?››

ይህንን የጌታችንን ንግግር ብዙዎች በዘመናችን ሲሣሣቱበት ይታያል ፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ይህንን የተናገረው እናቱን ሊያቃልል ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ይህን አረፍተ ነገር መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተናጠል ስንመለከት ‹‹አንቺ ሴት›› ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› (ዘፍ 2÷23) በመሆኑም ጌታ አንቺ ሴት ማለቱ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ መንሣቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ዐረፍተ ነገር የንቀት ስለመሰለን ብቻ ‘ የዳቦ መልክ የያዘ ድንጋይ፤ ዳቦ ነው እንደማይባል’ የንቀት ንግግር ነው ልንል አይገባም፡፡ ጌታም እንዲህ ሲል ውኃውን ወይን አድርግላቸው ብትይኝ አላደርግም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጽፎ እንደሚገኘው በዕብራውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡ለአብነት ይሆን ዘንድ ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡-

የሰራፕታዋ ሴት በ 1ነገ 17÷18 ላይ እንደምናገኘው ልጇ በሞተባት ጊዜ ኤልያስን በሐዘን በለቅሶ እንዲህ ብላ ነበር ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› ትወልጃለሽ ብለህ የወለድኩት ልጅ ምን በድዬህ ምንስ አስከፍቼህ ሞተብኝ? ስትል ነው እንጂ አባባሏ የንቀት ወይም የማቃለል አይደለም፡፡

በጌርጌሴኖን አንድ አጋንንት ያደረበት ሰው ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› አለው፡፡ እውነት ይህ ቃል የንቀት ይመስላልን? የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ብሎ አምላክነቱን እየመሰከረ ሊያቃልለው ይችላልን? ደግሞስ ላለመጥፋት ፍፁም የሚፈልግ ሰው ሊያድነው ሥልጣን ያለውን ሊንቅ ይችላልን? አይችልም፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው ምን አጠፋሁ ስለምን ልታጠፋኝ ወደድክ በማለት መፍራት መራዱን ነው፡፡ (ሉቃ 8÷28-29) ስለሆነም ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የንቀት አለመሆኑን ከሁለቱ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን፡፡ እመቤታችን እና ጌታ በንግግር አልተቃረኑም ንግግራቸው የፍቅር ነበር፡፡ ንግግራቸው የመግባባት ስለነበር ነው ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ካላት በኋላ ዘወር ብላ አገልጋዮቹን የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ያለችው፡፡

‹‹ጊዜዬ አልደረሰም›› ጌታ ይህን ቃል የተናገረው ስለ ብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ጊዜዬ አልደረሰም ማለቱ፡-

እግዚአብሔር ነገሮችን የሚያከናውንበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በመሆኑም ይህን ተአምር የምፈፅምበት ጊዜዬ አልደረሰም ሲል ነው፡፡

አንድም ጋኖቹ ውስጥ የቀረ ወይን ስለነበረ ባለው ላይ አበርክቶ እንጂ ውኃውን ወደ ወይን አልለወጠውም እንዳይሉ ወይኑ ከጋኑ ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ ድረስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡

አንድም ይሁዳ ከሠርግ ቤት ወጣ ብሎ ነበርና ወደ ሠርግ ቤቱ እሰኪመለስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡ ይሁዳ በቃና የገለጠውን ምስጢር ለእኔ ስላላሣየኝ ተከፍቼበት ከተአምራቱ ቢያጎድለኝ በሞቱ ገባሁበት፤ ሸጥኩት እንዳይል ምክንያት ለማሳጣት እንዲህ አድርጓል፡፡

አንድም እውነተኛ የሕይወት ወይን የሆነውን ደሜን የምሠጥበት ጊዜ ገና ነው ሲል፡፡

የድንግል ማርያም አማላጅነት በገሊላ ቃና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ቤት ሣለ የወይኑን ማለቅ የማይመለከት ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእናቱን የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሊገልጥ ስለወይኑ ማለቅ እስክትነግረው ድረስ አንዳች ነገር አላደረገም፡፡ ኋላ ግን የጭንቀት አማላጅ ድንግል ማርያም ስለ ወይኑ አሰበች ልጇ ወዳጇን ለመነች፡፡ እርሱም የእናቱን ልመና ተቀብሎ ተአምራቱን ፈፀመ፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሣይነግሯት በልብ ያለውን የምታውቅ የምትመረምር እናት ናትና የሠርጉ አስተናባሪዎች ይሄ ጎደለ ሣይሏት የልቦናቸውን ሐዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን ሞልታለች፡፡ያስጨነቃቸውንም አርቃለች፡፡ በችግራቸው ደርሳላቸዋለች፡፡ ታዲያ ሳይነግሯት የልቡናን አይታ ከማለደች ስሟን ጠርተው ለሚለምኗትማ እንዴት አብልጣ አታማልድ?

ልጅ እናቱን ‹አንቺ ሴት› ብሎ መጥራት በእኛ ሀገር ባሕልና በብዙ ቋንቋዎች ባሕል ፈጽሞ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ በተለይ በአደባባይ ሲሆን ይከብዳል:: ጌታ እናቱን ካልጠፋ ስም ለምን እንዲህ ብሎ ጠራት? 


አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚዳኘው በተጻፈበት ቋንቋ (Source language) እንጂ በተተረጎመበት ቋንቋ ባሕል አይደለም፡፡ ይህ አነጋገር በአይሁድ ዘንድ እና የዮሐንስ ወንጌል ላይ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ የሚሠጠው ትርጉም በእኛ ዘንድ ካለው ትርጉም የተለየ ነው፡፡ 


በግሪኩ ‹‹አንቺ ሴት›› (gune = woman") ተብሎ የሚጻፍ ሲሆን ጌታችን እመቤታችንን ‹‹አንቺ ሴት›› ብሎ በጠራበት ሥፍራ ግን በግሪኩ ‹አንቺ ሴት› የሚለው ንባብ የተጻፈው ‹አንቺ ሴት ሆይ› (gynai "Dear woman") በሚል የአክብሮት አጻጻፍ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገር ደግሞ ነገሥታት ለንግሥቶቻቸው በሚጽፉአቸው ደብዳቤዎችም ላይ ጭምር ይጻፍ የነበረ እንደሆነ የቋንቋው ባለቤቶች የሆኑት ግሪካውያን አገናዝበው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ አውግስጦስ የተባለው ንጉሥ ለግብፃዊቷ ንግሥት ለክሊዮፓትራ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመው ቃል የግሪኩን ‹gynai› /ጋይናይ /አንቺ ሴት ሆይ/ የሚለውን የአክብሮት አጠራር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡


ጌታችን በቃና ሰርግ ቤት ‹አንቺ ሴት› ብሎ የተናገረው ንግግር የቁጣ አነጋገር ነው የሚሉ ሰዎችን ሃሳብ እንዳንቀበል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር ለእናቱ የተናገረው በቃና ሰርግ ቤት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር ቆማ መከራውን እያየች በጽኑ ኀዘን ላይ እያለች ‹‹አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ›› በማለት ዮሐንስን ለእርስዋ እርስዋን ለዮሐንስ ሠጥቷል፡፡


በልጅና በእናት መካከል ባለው ሥነ ልቡናዊ ትስስር ምክንያት ለእናት የልጅዋን ስቃይ ቆሞ መመልከት እጅግ ከባድ ስቃይን ያስከትልባታል፡፡ እመቤታችን እያንዳንዱ ችንካር በተወደደ ልጅዋ እጅ ውስጥ ሲቸነከር ልብዋ በኀዘን ይቸነከር ነበር፡፡ ታዲያ ‹አንቺ ሴት› የሚለው አነጋገር የቁጣ አነጋገር ከሆነ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ‹በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ እያለፈባት› ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል? 


በሰርግ ቤት ውስጥስ ስለጠየቀችው ተቆጣ ይባል ፤ በመስቀል ሥር የልጅዋን ስቃይ በዝምታ ስትመለከት የነበረችን እናት ልጅዋ በስቃዩ መካከል ትንፋሹን ሰብስቦ ‹‹ተቆጣት›› ብሎ ሊነገር እንዴት ይችላል? በስተግራው የተሰቀለው ወንበዴ ‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህም› ብሎ ሲሰድበው መልስ ያልሠጠ ‹ከቁጣ የራቀ› አምላክ በእርሱ ስቃይ እየተሰቃየች ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል? (ሉቃ. ፳፫፥፴፱) ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ከእናቱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ‹እናቴ› ብሎ በመጥራት ወይም ‹ማርያም› በማለት ፈንታ ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር መጠቀሙ እመቤታችን በኦሪት ዘፍጥረት በተጠራችበት ስም ለመጥራት እና እርስዋ ትንቢት የተነገረላት ዳግሚት ሔዋን ፣ ጌታችንም የዕባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘርዋ መሆኑን የሚያስረዳን ነው፡፡


በሊቃውንት ዘንድ የወንጌል መቅድም (Protevangelium / Protogospel) ወይም ‹የመጀመሪያው የነገረ ሥጋዌ ትንቢት› በመባል የሚታወቀው ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።›› የሚለው ትንቢት በእርስዋ መፈጸሙን ከምንረዳበት መንገድ አንዱ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› ብሎ በመጥራቱ ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፭) 


በዕለተ አርብ በዕባብ የተመሰለው ዲያቢሎስ የጌታችንን ‹ሰኮና› በአይሁድ አድሮ ሲቀጠቅጥ ዋለ፡፡ ‹ዘርዋ› የተባለው ጌታም የዕባቡን ራስ እንዲሁ በመስቀሉ ቀጠቀጠው፡፡ በዚህ ወቅት እናቱን ደግሞ ‹አንቺ ሴት› ብሎ ጠራትና በትንቢቱ ላይ ያለችው ‹ሴቲቱ› እርስዋ መሆንዋን አስረዳን፡፡

የጻፈውን መተርጎም ልማዱ የሆነው ዮሐንስም ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ በሚያደርግ ሁኔታ የሴቲቱን ፣ የልጅዋን እና የቀደመውን ዕባብ ማንነት በአንድ ምእራፍ ላይ አብራርቶ በራእዩ ጽፎልናል፡፡ ‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። ... ዘንዶውም (እርሱም የቀደመው ዕባብ) በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ›› በማለት የዘፍጥረቱን ትንቢት በመተርጎም ሴቲቱ በእርግጥም ‹አሕዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ የወለደችው› እመቤታችን መሆንዋን አስረድቶአል፡፡ (መዝ. ፪፥፱) ስለዚህ ጌታ ‹አንቺ ሴት› ማለቱ ጾታን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን እመቤታችን የትንቢቱ ፍጻሜ መሆንዋን የሚያስረዳ የክብር አነጋገር ነው፡፡ (ራእ. ፲፪፥፩-፲፰)


እንዲሁም ለአዳም ሔዋን በተሠጠችው ጊዜ ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።›› ማለቱ (ዘፍ. ፪፥፳፫) ሴት የሚለውን ቃል ትርጉም ጾታን ከመግለጽ በላይ ‹ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽም ከአጥንቴ› የሚል የእኔነት ትርጉም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ የመጀመሪያው አዳም ከጎኑ ሔዋንን ያስገኘ ሲሆን ሁለተኛው አዳም ግን ከሁለተኛዋ ሔዋን የተገኘ ነው፡፡ ሆኖም ሁለተኛው አዳምም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ የሁላችንን እናት ጥምቀትን (ቤተ ክርስቲያንን) አስገኝቷል፡፡ 


- ከአንቺ ጋር ምን አለኝ


‹‹ከአንተ / ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ስድስት ቦታ ፣ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በአምስት ቦታዎች ተጽፎ የምናገኘው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ዐረፍተ ነገር በየተጻፈባቸው አገባቦች (contexts) ሁለት ዓይነት ትርጉም የሚሠጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው አገባብ አለመግባባትን የሚገልጽ አነጋገር ሲሆን ፤ ሁለተኛው አገባብ ደግሞ አክብሮትን ወይም ሰላም ጠያቂነትን የሚያሳይ አነጋገር ነው፡፡


አለመስማማትን የሚያሳይ የተግሣጽ ንግግር ሆኖ የምናገኘው በነቢዩ ኤልሳዕ ታሪክ ነው፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መፍትሔ ለመጠየቅ መጥቶ ነበር፡፡ ኢዮራም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አድርጎ ስለነበር ኤልሳዕ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ›› ብሎ መልሶለት ነበር፡፡ ኢዮራም ኤልሳዕን ለማነጋገር ሲሞክርም ኤልሳዕ በቁጣው ጸንቶ ‹‹አብሮህ ያለውን የይሁዳን ንጉሥ ባላፍር ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር፡፡›› ብሎታል፡፡ (፪ነገሥ. ፫፥፲፫)


በዚህ ታሪክ ውስጥ በግልጽ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል ‹ከአንተ ጋር ምን ኅብረት አለኝ?› በሚል አገባብ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይም እግዚአብሔር የጢሮስ ፣ የሲዶናና የፍልስጤም ግዛትን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ስላደረሱት በደል እንደሚፋረዳቸው በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ፈጥኜ ብድራታችሁን በእናንተው ላይ እመልሳለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህም ስፍራ እንዲሁ ይህ አነጋገር ከቁጣ ጋር ተነግሮ ይገኛል፡፡ (ኢዮ. ፫፥፬)

ሁለተኛው አገባብ ደግሞ ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ትርጉም የሚሠጠው አገባብ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ለእርሱ የተቆረቆሩ የጽሩያ ልጆች የሰደበውን ሳሚን ‹እንምታው ፣ እንግደለው› ሲሉ ‹‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?›› ብሎ ከልክሎአቸዋል፡፡ (፪ሳሙ. ፲፮፥፲) ተሳዳቢው ሳሚ መጥቶ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቅም ዳግመኛ ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት ይገባዋል›› አሉ፡፡ 


ይህን ጊዜ ዳዊት ‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን?›› (፪ሳሙ. ፲፱፥፳፪)

በእነዚህ የንጉሡ ንግግሮች ውስጥ ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል በአክብሮት የተነገረ ባይሆንም መልእክቱ ግን ‹ምን ጠብ አለኝ› ማለት መሆኑን ከአገባቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ምናልባት የመጨረሻው አገባብ ቁጣ ያዘለ ቢመስልም እንኳን እየተናገረ ያለው ለእርሱ ከእርሱ በላይ ለተቆረቆሩት ታማኝ ወታደሮቹ ጋር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ እርሱም ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?›  ያለውን  ‹ለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ?› ብሎ በማብራራት የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ ‹ከእናንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› እንደሆነ አሳይቶአል፡፡


ሌላው ማሳያ ደግሞ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ ንግግር ነው፡፡ ኒካዑ ካልተዋጋሁህ ብሎ ለመጣበት ለኢዮስያስ ፡- ‹‹የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት።›› (፪ዜና ፴፭፥፳፩) ይህ አነጋገር በትሕትና እና ‹ሆይ› በሚል የአክብሮት አጠራር የቀረበ ነው፡፡ በግልጽ ‹ልዋጋ የተነሣሁት ከሌላ ጋር ነው ፤ ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝና ነው የምዋጋው!› ነው ያለው፡፡ በእውነቱ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ማለት ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ማለት መሆኑን ለማስረዳት ከዚህም የተሻለና ግልጽ ታሪክ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢዮስያስ የተነሣው ለጠብ ነው፡፡ ኒካዑም በአክብሮት የነገረው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ብሎ ነው፡፡


እንደተጨማሪ ማሳያ የምናገኘው ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስን በቤትዋ የተቀበለችው የሰራፕታዋ መበለት የተናገረችው ነው፡፡ ይህች ሴት ኤልያስ በቤትዋ በመገኘቱ በቤትዋ ያለው ምግብ ተባርኮ በረሃብ ዘመን እየተመገቡ ከከረሙ በኋላ ልጅዋ በጠና ታመመ፡፡ ይህን ጊዜ ሴቲቱ ወደ ኤልያስ ቀርባ ፡- 


‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።›› (፩ነገሥ.፲፯፥፲፰)

ይህች ሴት ለነቢዩ በአክብሮት ያለችው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ነው፡፡ የቁጣና የተግሣፅ ንግግር ነው እንዳይባል መቼም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ...›› ብሎ የሚጀምር ቁጣ የለም፡፡ እንዲያውም በአንድ ሰው ስንቆጣ ማዕረጉን ትተን እንናገራለን እንጂ ማዕረግ ጠብቆ ቁጣ የለም፡፡


ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለውን ቃል የተናገሩት ዛሬ በወዳጆቻቸው አድረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ማለት ስድብ ነው› እያሉ የሚበጠብጡን አጋንንት ናቸው፡፡ ከአዋቂ ጋር እንደ አዋቂ ፤ ካላዋቂ ጋር እንደ አላዋቂ ሆኖ ማደናቆር የአጋንንት ልማድ ነውና እነሱ በሚገባ ትርጉሙን ተረድተው እየተንቀጠቀጡ ለጌታ የተናገሩትን የአክብሮት አነጋገር ለእመቤታችን ሲሆን ትርጉሙ ሌላ ነው እያሉ ያውካሉ፡፡


‹‹እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።›› (ማቴ. ፰፥፳፱)


‹‹እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።›› (ማር. ፩፥፳፬)


‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤›› (ማር. ፭፥፯)


‹‹ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ።›› (ሉቃ. ፬፥፴፬)


‹‹ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ›› (ሉቃ. ፰፥፳፰)


ምንም እንኳን አጋንንትን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ክብር ባንሠጣቸውም ‹የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው› እንዲል (ትምህርተ ኅቡዓት/ትር.) የአጋንንቱ ንግግር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ› የሚለው ቃል በአክብሮት ሊነገር የሚችል ‹ምን ጠብ አለኝ› የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡ 


ምክንያቱም ‹ከአንተ ጋር ምን አለን› ከማለታቸው ጋር ‹ኢየሱስ ሆይ ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሱ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ‹እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ› የሚል ልመና ተከተለ፡፡ ልመናውም ከእግሩ ሥር እስከ መደፋት ድረስ የደረሰ ነበር፡፡ መቼም ከእግር ሥር ተደፍቶ የቁጣ ንግግር መናገር የማይታሰብ ነው፡፡


በአጠቃላይ ከላይ ባየነው የአገባብ ዝርዝር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ለሚለው ንግግር የሚያመዝነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል ነው፡፡ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ጌታችን ለእናቱ የተናገረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገርም ከአገባቡ እንደምንረዳው ሌሎች ስለ እርሱ በፍርሃት የተናገሩትን የአክብሮት የተነገረ ሲሆን ትርጉሙም ‹የጠየቅሽኝን እንዳላደርግልሽ የሚከለከለኝ ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳን መልሱ የእምቢታ ቢሆን ኖሮ አንደኛ እመቤታችን ልመናዋን ቀጥላ ‹እባክህን ልጄ ሆይ› ብላ ለማሳመን ትሞክር ይሆናል እንጂ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ ለአገልጋዮቹ በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝነት ትእዛዝ ልትሠጥ አትችልም ነበር፡፡


ሁለተኛ ደግሞ ጌታችን ከዚያ በኋላ ጋኖቹን ሙሉ ብሎ ተአምራቱን አያደርግም ነበር፡፡ እንዲያውም ጌታችን ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም› ያላት በቁጣና በእንቢታ ከሆነ ለአገልጋዮቹ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ መናገርዋ የበለጠ ቁጣውን የሚያነድ ነበር የሚሆነው፡፡ ለእርስዋ እንቢ እያላት ቁጣውን ከምንም ሳትቆጥር ሌሎች ሰዎችን ማዘዝዋ የበለጠ አያስቆጣም ወይ ሊባል ይችላል? ይህ ሁሉ የሚያሳየን ጌታችን አንዳች የቁጣ ንግግር አለመናገሩን ነው፡፡


አባ ጊዮርጊስም የጌታችን መልስ የጠብ ሳይሆን እንዲያውም የጥልቅ ፍቅር መሆኑን ሲገልጽ  ‹‹በልቡ ውስጥ ለተከማቸ ፍቅሯ በሚሻል /በሚመጥን/ ነገር መለሰላት›› ‹‹ወአውስኣ ዘከመ ይኄይስ ለዘዝጉብ ፍቅረ ዚኣሃ ውስተ ልቡ›› ብሏል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር) ስለዚህ ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ› የሚለውን ንግግር የቁጣ ንግግር አድርጎ መተርጎም ጥቅሱን ከአገባቡ የወጣ ጥቅስ (Text out of context) ያደርገዋል፡


+ ጌታችን እናቱን ተቆጥቷት ይሆንን? +

የቃና ሰርግ ቤት ታሪክ ለጊዜው እናቆየውና አንድ ልጅ በአደባባይ በሰዎች ፊት እናቱን በምንም ምክንያት ቢቆጣ እንኳን ከሃይማኖት አንጻር ከሥነ ምግባርም አንጻር የሚደገፍ ሥራ አይደለም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ‹እናቱን በቁጣ ተናገራት› የሚለው አስተሳሰብም እንዲሁ ብዙ የሚያመጣው ጣጣ አለ፡፡ 


‹‹እናትና አባትህን አክብር›› ‹‹እናቱን የሰደበ ይሙት›› የሚለውን ሕግ የሠራ አምላክ ‹እኔን ምሰሉ› እያለ ለሰው ልጆች አርኣያ ሊሆን በመጣበት በዚህ ዓለም ራሱ እናቱን በአደባባይ በሰው ፊት ያቃልላታል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድና ለብዙ ሰዎች የኃጢአትን በር ወለል አድርጎ ከፍቶ መረን የሚለቅ ነው፡፡ (ዘጸ. ፳፥፲፪ ፣ ፳፩፥ )

እመቤታችንን የጎዱ መስሏቸው ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለው የሚሰብኩ ሰዎችም ሳያውቁት እየተናገሩ ያሉት በእመቤታችን ላይ ሳይሆን በራሱ በጌታችን ላይ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?›› ብሎ የተናገረ ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፮) ‹የሚጤስን የጧፍ ክር የማያጠፋ ፣ የተቀጠቀጠ ሸንበቆን የማይሰብር› በአነጋገሩ ጭምት ነው፡፡ ስንክሳሩም ‹‹ወንድሜ ምእመን ሆይ ጌታችን ለንጽሕት እናቱ ለድንግል ማርያም ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለቱ የክብርት እናቱን ቃል እንዳቃለለ አታስብ›› ይላል፡፡ (ስንክ. ጥር ፲፪ ቁ. ፵)

በማስከተልም ‹‹ጌታችን የሰማያዊውና የመለኮታዊ አባቱን ክብር እንደጠበቀ ይታወቅ ዘንድ እንዲሁ ከእርስዋ ፍጹም ሥጋንና ፍጽምት ነፍስን ነሥቶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደውን የእናቱን ክብር ጠበቀ፡፡ በወንጌል ይታዘዛትና ይላላካት ነበር ተብሎ እንደተጻፈ›› ይላል፡፡ (ስንክ.ጥር ፲፪ ቁ. ፵፪)  


በእርግጥም ጌታችን የባሕርይ አባቱን አብን ክብር እንደጠበቀ በራሱ አንደበት ‹‹አባቴን አከብራለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፱)  ለእመቤታችንና ለአሳዳጊው ዮሴፍም እንዲሁ ‹‹ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩) እመቤታችን በቃና ዘገሊላ ስለ ወይኑ የነገረችውም የልጅዋን መታዘዝ በልብዋ ትጠብቀው ስለነበር እና እንደሚታዘዛት ታስብ ስለነበር ነው፡፡


እስቲ ነገሩን ሌሎች ከሚያዩበት ማዕዘን ለመመልከት እንሞክር፡፡ እውነት ግን ጌታችን እናቱን ሊቆጣ የሚችልበት ምን ምክንያት ነበረው? ከላይ እንደተመለከትነው የለመነችው ስለ ራስዋ ጥቅም አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ልመናዋ ከሚያስፈልግ ነገር ውጪ ይደረግ የተባለ አላስፈላጊ የቅንጦት ልመና አይደለም፡፡ በሰርግ ቤት ሙሽሮችን ለዕድሜ ልክ ውርደት ሊዳርግ የሚችል የወይን ጠጅ እጥረት በተከሰተበት ሰዓት ‹ወይን እኮ የላቸውም› ብሎ ማመልከት እንኳን በሩኅሩኁ አምላክ ፊት ይቅርና በእኛ በጨካኞቹ የሰው ልጆች ፊት እንኳን ሊያስቆጣ የሚችል ነገር አይደለም፡፡

የለመነችው እንደ አይሁድ ምልክት ለማየት ጓጉታ አይደለም፡፡ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃውያን ‹አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ትሠራለህ?› ‹ከሰማይ ምልክት ልናይ እንወዳለን› የሚል የፈተና ጥያቄ አልጠየቀችም፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፩ ፤ዮሐ. ፮፥፳) ተአምር የማየት ምኞት አድሮበት እንደጠየቀው እንደ ሄሮድስም በአጋጣሚው ልጠቀምና ተአምር ልይ ብላም አይደለም፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፰) ደግሞስ ያለ ወንድ ዘር በማኅጸንዋ አድሮ በታተመ ድንግልና ሲወለድ ያየች እናት ሌላ ምን ተአምር ሊያስደንቃት ይችላል?


የሰርጋቸው ቀን የኀዘናቸው ቀን ሊሆን ስለተቃረበ ሙሽሮች ተጨንቃ መለመንዋ እንዴት የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል? ያለጊዜው ስለለመነችውና ስለቸኮለች ተቆጣት እንዳንል ልመናዋን ትንሽ ብታዘገየው ኖሮ ነገሩ ይፋ እየሆነ ፣ ሙሽሮቹ መዋረዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ የደረሰችው በሰዓቱ ነው፡፡ 


የጌታችን አሠራር እንዲህ አልነበረም፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ አማት በንዳድ በታመመች ጊዜ እንዲፈውሳት ሲለምኑት እሺ ብሎ ንዳዱን ገሥፆ አላቀቃት፡፡ (ሉቃ.፬፥፴፱) የአንድ መቶ አለቃ ልጅ በታመመ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎች ሊያማልዱ በመቶ አለቃው ተልከው መጡ፡፡ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑን በማሰብም ‹‹ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።›› የመቶ አለቃውንም ልጅ በመጨረሻ ፈወሰው፡፡ (ሉቃ. ፯፥፪-፮) እነዚህ ሰዎች ተአምር እንዲያደርግ ሲጠይቁት እሺ ያለ ጌታ እናቱ ስትለምነው ይቆጣል ብለን እንዴት እንቀበል? የአይሁድን ሽማግሌዎች እንኳን ያልተቆጣውን ጌታ በምን አንደበታችን እናቱን ተቆጣ ልንለው ይቻለናል?

ከሁሉ በላይ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን›› እንዳለው በረከሰ አንደበታችን ፣ በሚወላውል ልባችን ፣ በሚባክን ሃሳባችን ወደ እርሱ የምንጸልየውን የእኛን የኃጢአተኞቹን ጸሎት ለምን ጸለያችሁ ብሎ ያልከለከለ አምላክ ንጽሕት እናቱ በፍጹም ትሕትና ለለመነችው ልመና የቁጣ ምላሽ ሠጠ ማለት እንዴት እንደፍራለን? ዳዊት ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ›› ብሏል፡፡ እርሱ በልቡ በደል ስለሌለ ጌታ ከሰማው በሃሳብዋ ድንግል የሆነች እናቱን እንዴት አልሰማትም እንላለን? (መዝ. ፷፮፥፲፱-፳)


እመቤታችን የጠየቀችው ይህን ያህል የማይጠየቅ ነገር ነው እንዴ? የመንግሥትህን እኩሌታ ፣ የሥልጣንህን ፈንታ ሥጠኝ አላለችውም፡፡ የጠየቀችው ስለ ድሆቹ ሙሽሮች ነው፡፡ እኛ በረባ ባልረባው ስንዘበዝበው የምንውለውና የምናድረው ታጋሽ አምላክ ለእናቱ ለእኛ የሠጠውን ነገር ይነሣል ማለት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ‹አብን አሳየንና ይበቃናል› ፤ ‹እሳት ከሰማይ ወርዶ ሕዝቡን ያጥፋቸው› ፤ ‹በግራ ቀኝህ አስቀምጠን› የሚሉ ደቀ መዛሙርትን ታግሶ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ያስከተለ ጌታ ቅድስት እናቱ ተገቢ ልመና በተገቢ ሰዓት ስትለምነው ሊቆጣ አይችልም፡፡


እንደ ወንጌሉ ብቻ ከሔድን ደግሞ እመቤታችን ከዚህ በፊትና በኋላ ምንም ነገር ስትለምነው አልተጻፈም፡፡ በወንጌል ለተጻፈው ለዚህ ብቸኛ ልመናዋም መልሱ ቁጣ ነው ብለን አምነን መቀመጥ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ፈጽሞ የሚዋጥልን ሃሳብ አይደለም፡፡ በልጅነትዋ ወልዳው ለተሰደደችው ፣ በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ ላለፈባት እናቱ አንዴ ብትለምነው ተቆጣ ብለን እንዴት እንናገራለን?


ጌታችን በዚህ ሰርግ ቤት እንኳንስ እንዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚተረጉመው ‹ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግሮ ቀርቶ ፤ ለእናቱ የተናገረው በቀጥታና በግልፅ የቁጣ ንግግር ቢሆን ኖሮ እንኳን ጾመን ጸልየን ፣ ወድቀን ተነሥተን ምሥጢራዊ ትርጉሙን እንፈልጋለን እንጂ ሰማይና ምድር ቢነዋወጥ ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለን አናምንም!!!


ከዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ፌስቡክ ወሰድኩት 

(ከቃና ዘገሊላ መጽሐፍ)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...