ረቡዕ 24 ጃንዋሪ 2024

"ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ"

 

"ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ገላትያ 6÷14

ይህን መልእክት የጻፈልን ከሐዋርያት ጋር ለሐዋርያነት ያልተመረጠው ይልቁን ሐዋርያትን በማሳደድ የሚተባበረው ከሐዋርያት መካከል እንደ አንዱ የሚቆጠረው ቅዱስ ጳውሎስ ነው።

መልዕክቱ የተጻፈው በገላትያ ቤተክርስቲያን ለሚገኙ ምዕመናን ነው። ገላትያ፦ ቱርክ ውስጥ የምትገኝ አንድ አውራጃ ነች።

ቱርክ ቅዱስ ጳውሎስ ለወንጌል አገልግሎት ሲሰማራ ካገኛቸው ከተሞች አንዷ ነች።

በገላትያ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት በቅዱስ ጳውሎስ የተመሰረቱ ናቸው።

የገላትያ ሰዎች ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሯቸው ከሄደ በኋላ ካስተማራቸው ትምህርት ቢያፈገፍጉም (ስለግርዘት ተምረው ነበረ ያፈገፈጉት) በመጨረሻም ተጸጽተው ተመልሰዋል።

ይህ መልዕክት የመጀመሪያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት እንዳልሆነ ይነገራል። መልዕክቱ ጠጠር ያለ እና ከበድ ያለ መልእክት ነው።

የመነሻ ቃላችን ሙሉው እንዲህ ይላል።

 

"ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ"

መስቀል ዛሬ ላይ የደመራ በዓሉ በዮኔስኩ በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝጎ ይገኛል። ከዓለም ሕዝብ ውስጥ በቱሪስትነት ብዙ ሰዎች በኢትዮጵያ ተገኝተው አከባበሩን ይጎበኙታል።

እኛ ግን ከመሰረታዊው ሐይማኖታዊ በዓሉ ይልቅ በየአካባቢው ባህላዊ ነገሩ እየጎላ መንፈሳዊ ትውፊቱን ክትፎ እና ጎመን ሊከልለው ይመስላል።

በዓሉን በሚበላ በሚጠጣ ማክበሩ ክፋት ባይኖረውም ሐይማኖታዊ ዳራውን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም።የለብንምም። ለዚህ ጽሑፍ ያነሳሳኝ ሐይማኖታዊ በዓሉ እንዳለ ሆኖ አንዲት እህቴ የበዓሉ ከሐይማኖታዊነት ይልቅ ወደ መብል መጠጥ ማድላት አስገርሟት ባቀረበችው ትዝብትና እባካችሁ ሐይማኖታዊውን አስተምሮ ጻፉልን ተማጽኖዋ ነው።

ይህን መልዕክት ስጽፍ ድርሻዬን ለመወጣት እንጂ ሙሉ መልዕክቱን አስቀምጣለሁ ከማለት አይደለም። አልተጻፈም ለማለት ለመድፈርም አይደለም።

ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ መስቀል ከክርስቶስ ስቅላት በፊት በፋርስ ኢራን ያጠፉ ሰዎችን መቅጫ እንደነበረ ይነገራል።

የፋርስ ሰዎች "አርዝሙድ" የተባለ የመሬት አምላክ ያመልኩ ነበር። እነዚህ ማህበረሰቦች ያጠፋውን ሰው በመስቀል ላይ (በተመሳቀለ እንጨት ላይ ወይም ዛፍ ላይ) ይሰቅሉት ነበረ። ይኸን ማድረጋቸውም የተሰቀለው ሰው ወንጀለኛ ከመሆኑ የተነሳ ምድርን እንዳያረክሳት ከማሰብ ነው።

መጽሐፍም የእነርሱን ተግባር እንዲህ ሲል ይገልጠዋል።

"በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር" ኦሪት ዘዳግም 21÷22-23

 

በኦሪት ስርዓት መስቀል

• የበደሉ፣ ወንጀል የሰሩ፣ ዓመጸኞች፣ የሚቀጡበት ነበር

• የሚቀጣው እጅና እግሩን በማሰር አስፈሪና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በመቸንከር ነበረ

• የመስቀሉ ዓይነቶች የ'X'፣ የ'ፐ'፣ የ'+' ምልክት ቅርጽ ያላቸውና ቀጥ ያለ ዛፍ እንደነበረ ድርሳናት ይጠቁሙናል።

የኦሪቱን ታሪክ እዚህ ላይ እንግታውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ወንበዴዎችና ወንጀለኞች በመስቀል ላይ ተሰቀለ? የሚለውን ዋናውን ጉዳይ እንመልከት።

ለሞት የሚያበቃው በደል እና ወንጀል ባይኖርበትም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ነውና መሞት ነበረበት። ነገር ግን በሚያስተምርበት ዘመን ይከተሉት ከነበሩ የአምስት ገበያ መካከል ገሚሶቹ ከሚናገረው ቃል በመነሳት ሊከሱት ይፈልጉ ነበረና የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል ራሱንም ንጉስ ነኝ ይላል ብለው ከሰሱት ለሞት በማያበቃ ክስም ከሕጋቸው ውጪ ገርፈውም ሰቀሉት።

የርሱ ሞት ሞታችንን ሻረልን፣ የርሱ መገረፍ ሕማማችንን አስቀረልን፣ ያጣናትን ርስት መንግስተ ሰማያትን እንድናገኝ ሆንን። በሞቱ ሕይወትን አገኘን።

መስቀል ከቀራንዮ በኋላስ፥

ዛሬም አንዳንዶች ለመስቀል ያለንን ክብር በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል፤

የመስቀልን ዋጋ  እና ፍቅር አባቱ ከተገደለበት መሳሪያ ጋር አሳንሰው ያነጻጽሩታል፤

እኛም የመዳናችንን ምክንያት የሆነውን የቅዱስ መስቀል በዓል ዘንግተን ለባህላዊው በዓል ብልጫ ሰጥተናል።

 

መስቀል ለእኛ

 

• መርገመ ኦሪት የሻረበት፣

• ሰላምና ነጻነት የታወጀበት፣

• የድኅነት የበረከት የነፃነት አርማችን፣

• የክርስቶስ ዙፋን ነው።

በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረው የትንቢት ቃል የተፈጸመቀት ነው። "በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን"  ትንቢተ ኢሳይያስ 53÷4

 

መስቀል እና ደመራ ለምን እናከብራለን?

• በመስቀሉ ኃይል አጋንንትን፣ ፀብአ አጋንንትን ድል እንነሳበታለንና እናከብረዋለን።

• መስቀሉን ስንሰብክ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን። ለዚህም በዓሉን እናከብራለን።

 

ደመራን የምናከብረው

ጌታን የሰቀሉ አይሁድ ክርስቶስ በተሰቀለበት መስቀል ተዓምራት ሲደረግ አይተው በቅናት ተቃጠሉ። መስቀሉንም በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወስደው ቀበሩት፤ በዐዋጅም የቤት ጥራጊ ቆሻሻ ለ300 ዓመት ደፉበት። ቆሻሻውም ከመብዛቱ የተነሳ ተራራ ሰራ።

ከረጅም ዓመት በኋላ በ327ዓ.ም የታላቁ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ አስቀድማ ስዕለት/ብፅአት በገባችው መሰረት (ስለቷ የአረማዊው አባቱ የቁንስጣ ልጅ በመሆኑ ልጇ ክርስቲያን እንዲሆንላት ነበረ) የተቀበረውን የክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማስወጣት በአረጋዊው ሰው ኪራኮስ ምክር እና ጥቆማ በመመራት መስከረም 16 ቀን ደመራ አስደምራ ዕጣን አስጨምራ ጸሎት ተደርጎ የዕጣኑ ጢስ የተቀበረበትን ቦታ ወዳመላከተው ተራራ በመሄድ ቁፋሮውን  መስከረም 17 አስጀመረች። መስቀሉም ከሰባት ወር በኋላ መጋቢት 10 ሊወጣ ችሏል።

መስቀሉ ተቆፍሮ ሲወጣ የተገኙት ሶስት ነበሩ። የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና አብረውት የተሰቀሉት ሁለት ወንበዴዎች።

የክርስቶስን መስቀል ከሶስቱ መለየት ለክርስቲያኖች ከባድ ነበረ፤ነገር ግን በሰራው ድንቅ ተአምራት የጌታችንን መስቀል ለመለየት ተችሏል።

• ሙት አስነስቷል፣ ዕውር አብርቷል፣ ጎባጣ አቅንቷል፣ ሽባ ተርትሯል፣ ልዩ ልዩ ተዐምራት ተደርጓል። ብዙ በረከትም ተገኝቷል።

ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን በክብር ዙሪያውን በወርቅ አስለበጠችው። "ትንሣኤ ክርስቶስ "የተባለ ቤተክርስቲያን አሰራች።

ኮስሮኤል የሚባል የፋርስ ንጉስ ክርስቲያኖችን አስገድሎ የቀሩትን ማርኮ ኢየሩሳሌምን በማቃጠል መስቀሉን ዘረፈ።

ህርቃል የሚባል ንጉስ በ628 ዓ.ም ወደ ፋርስ ዘምቶ ኮስርኤልን ድል አድርጎ መስቀሉን አስመለሰ። ሕዝቡም በዕልልታ በሆታ አበባ ይዘው በመብራት ተቀበሉት።

ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችም መስከረም 16 እና 17 ቀን ደመራ ደምረን አደይ አበባ እና ቄጠማ ጎዝጉዘን በሆታ በዕልልታ በዝማሬ እናከብራለን።

በዓሉን ማክበር በ629ዓ.ም የጀመርን እስከ ዘንድሮ ድረስ በብዙ መገፋት ውስጥ ፀንቶ ቀጥሏል።

የመስቀል መገፋት በዚህ ብቻ አላበቃም ይሁን እንጂ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዳዊት ዘመነ ንግሥና ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ ከርቤ ሊቀመጥ ችሏል።

በቦታውም በየዓመቱ በክርስቲያኖች በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል።

ደመራንም በሐይማኖት አባቶች መሪነት በሊቃውንት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ምዕመኑን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ እና በየደብሩ በዝማሬ እና በተለያዩ ትርኢት እናከብረዋለን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...