" የጌታ ቃል ትዝ አለው " የሉቃስ ወንጌል 22፥61
በደረሰ ረታቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስን ክርስቶስን " ሌሎች ቢክዱህ እንኳን እኔ አልክድህም " ብሎት ነበረና ጌታም " ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ " አለው።
ጊዜው ሲደርስ ጌታን ያዙት ወደ ሊቀካህናቱ ቤትም ወሰዱት
• ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር።
• ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ።
• ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች።
• አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ።
• አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ፡ አለው።
• ጴጥሮስ ግን፡— አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም፡ አለ።
• ሌላው አስረግጦ፡— እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ፡ አለ።
• ጴጥሮስ ግን፡— አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም፡ አለ።
• ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ።
• ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤
• ጴጥሮስም፡— ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው።
• ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
የቅዱስ ጴጥሮስ አቋም ከችኩልነቱ የተነሳ ወላዋይ ይመስላል፤ ችኩልነቱ እና ባለማገናዘብ የሚመልሳቸው መልስ ከፍቅር የመነጨ ነው።
መጠራጠር እና ክህደቱ የተፈጠረው ግን በፍርሃት፣ ከነበረበት ስፍራ፣ ከወቅታዊ ሁኔታው የተነሳ ነበር።
1. ጌታን ሲይዙት ርቆት መከተሉ
2. ሲበርደው እሳት ለመሞቅ ጌታን ከያዙት ወገን ከመካከላቸው መቀመጡ
3. የጌታን ወደዚህ ዓለም የመምጣት ዓላማ በአግባቡ ሳይለይ የልብ መሻቱ
እነዚህ ተደማምረው ቅዱስ ጴጥሮስ መጀመሪያ ጌታን አላውቀው፣ ቀጥሎ ራሱን ክዶ አይደለሁም፣ በመጨረሻም ጌታን ሊክደው እና አላውቀውም እንዲል አድርጎታል።
ከዘረኛ ጋር ስንውል ዘረኛ፣ ከነፍሰ ገዳይ ጋር ስንውል ነፍሰ ገዳይ፣ ከመንፈሳዊ ጋር ስንውል መንፈሳዊ እንሆናለን። ወፍጮ ቤት የዋለ አይደለም የገባ ሰው ዱቄት ሳይነካው አይወጣምና።
" ቃሌ ከሚያልፍ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል " ያለ አምላካችን ያለው ቃል ተፈጸመ። ዶሮ ሳይጮኽ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ሶስቴ ካደው።
ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው።
ጴጥሮስም የጌታ ቃል ትዝ አለው፦ ።" ዶሮ ሳይጮኽ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ "
ጴጥሮስም ወደ ውጪ ወጥቶ (ከወንበዴዎቹ ተለይቶ፣ ጌታን ሊገሉት ከሚፈልጉት አጠገብ ርቆ፣ እሳት ከሚሞቅበት ቦታ ተነስቶ ) ምርር ብሎ አለቀሰ።
የቅዱስ ጴጥሮስ መራር ለቅሶ የንሰሐ ለቅሶ ነበረ።
እኛስ?
ከቅዱስ ጴጥሮስ የሕይወት ተሞክሮ ምን ተማርን?
ጌታን በቅርበት ነው የምንከተለው ወይንስ በርቀት?
ውሎአችን ከነማን ጋር ነው?
አውቀን አምነን ነው እየተከተልነው ያለነው፣ በስሜት ነው፣ ከቤተሰቦቻችን ስለወረስን ነው፣ ወይንስ እንዴት ነው?
አሁናዊ ማንነታችን ምን ይመስላል?
ብዙዎቻችን የቅዱስ ጴጦሮስ አይነት ሕይወት ያለን ይመስለኛል፤ መመላለስ ነገር ግን መራር የንሰሐ ሕይወት የሌለን። እንደዛ ከሆነ እንመለስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰማነው የጌታ ቃል ትዝ ይበለን።
አካሄዳችንን እናቅና ( ቤተክርስቲያን መሄድ የምንፈራ፣ ማስቀደስ የምንጠላ፣ መጾም የማንችል፣ የጸሎት ሕይወት የሌለን፣ ማመን የማይታይብን፣ ውሎና አዳራችን ከማይመስሉን ጋር የሆነ፣ ከማያምኑት ጋር ወዳጅነት የመሰረትን ) እንመለስ።
ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታውን እንዲክድ ያደረገው፦
መፍራቱ፣
ከማያምኑት ጋር መቀመጡ፣
ጽኑ እምነት አለመኖሩ፣
ወዘተ ናቸው ለመካድ እና መሪር እንባን እንዲያነባ ያደረጉት።
ስለዚህ እኛም ፍርሃትን የሚያርቅ ጽኑ ፍቅር እንዲኖረን ጌታን ቀርበን እንወቀው። ከማያምኑት ጋር ውሎአችንን አናድርግ፣ ( ከላም ጋር የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትመጣለች እንዲባል) ውሎአችንን እናስተካክል።
አንዳንዶቻችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት፣ አምላክነት፣ አማላጅ አለመሆኑን፣ ማመናችንን፣ ክርስቲያን መሆናችንን ለመደበቅ እንጥራለን፣ የአንገት ማኅተማችንን እንደብቃለን፣ መጾማችንን ሳይቀር እንዋሻለን። ( የዘፈን ዳርዳሩ ... እንደሚባለው እንዳይሆን እፈራለሁ። )
በጌታ ቃል ራሳችንን እንመልከት። አንዳንዶቻችን ታሪክ ቀመስ እንሆናለን በልጅነቴ ሰንበት ተማሪ ነበርኩ፣ ዘማሪ ነበርኩ፣ ዲያቆን ነበርኩ፣ ቆራቢ ነበርኩ፣ መምህር/ አባ እገሌን አውቀዋለሁ፣ የቄስ ልጅ ነኝ ወዘተ እንላለን። አሁን የት ነን? እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ራሳችንን እንይ። እሳት ሐጢያትን እየሞቅን፣ ጌታን አሳልፈው ከሰጡ፣ ከሸጡ፣ ከገደሉ ጋር ነን? ወይስ ቃሉ ከሚነገርበት አትሮኑስ ስር ነን?
በጌታ ቃል ራሳችንን ካየነው ምንም ጥያቄ የለውም በድለናል። ( ሁሉ በደለ እንዲል የአምላካችን ቃል። ) ክደናል የሚያስብል ደረጃ ላይ ነን። እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ፈጥኖ የሚመለስ ልብ፣ የሚጸጸት ልብ፣ ወደ ንሰሐ የሚመለስ ልብ ካለን ንሰሐ እንግባ፣ አምርረን እናልቅስ፣ ያሳለፍነው ዘመን ይበቃናል እንበል።
የቀማን መልሰን፣ የበደልን ክሰን ወደ ንሰሐ ሕይወት እንገስግስ።
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምህረት ዐይኑ ይመልከተን።
አሜን።
ይቆየን።
መልካም የሕማማት ሳምንት ይሁንላችሁ።
❤❤######################❤❤
የእለት ተለት ጽሑፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች ባሉት ሁሉ እገኛለሁና ይከታተሉኝ። ከተመቸዎት ለሌሎች ያጋሩት።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)
https://www.facebook.com/deresse2020/
Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)
https://www.facebook.com/DeresseReta
Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።
https://t.me/deressereta
ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።
www.deressereta.blogspot.com
https://anchor.fm/deresse-reta/episodes/ep-ev5j5o
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ