ሰኞ 23 ኖቬምበር 2020

በአባቴ ቤት እንጀራ የሚተርፋቸው አገልጋዮች ስንት ናቸው?

 በአባቴ ቤት እንጀራ የሚተርፋቸው አገልጋዮች ስንት ናቸው?

ሉቃስ 15: 17

ጌታችን መድኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በተመላለሰበት በዘመነ ሥጋዌው ለሶስት ዓመት ከሶስት ወር አስተምሯል።

እርሱም በሚያስተምርበት ወቅት የአምስት ገበያ ያሕል ሕዝብ ይከተለው ነበር ብሎ መጽሐፍ ይነግረናል።

ከነዚህ የቃሉን ትምህርት ከሚማሩት ከእጁ በረከት ከሚሳተፉት መካከል ገሚሱ ሃጥያተኞች ስለነበሩ ሊከሱት ይከተሉት በነበሩት መካከል ተቀባይነትን አላገኘም ፤ እጅግም አስነቀፈው። እንዴት ሃጢያተኞችን ሰብስቦ ያስተምራል ብለው አሙት። ወንጀሉት።

ክብር ይግባውና ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነርሱን ትችት ወደ ጎን በመተው ይልቅስ መድሃኒት የሚያስፈልገው ለጤነኞች ሳይሆን ለበሽተኞች እንደሆነ በመንገር ከክፋታቸው ይመለሱ ዘንድ አስተማራቸው። እኔ ሐጥአንን ልጠራ መጣሁ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም እንዲል ከሃጢያተኞች ጋር ዋለ። እነርሱም አጉረመረሙ። በማጉረምረማቸው ምክንያት ሶስት ምክንያታዊ የሆነ ትምህርት በምሳሌ አስተማረ።

፩ኛ. አንድ ሰው መቶ በጎች ነበሩት ቀኑን ሙሉ በለመለመ መስክ እያሰማራ ከምንጭ ውሃ እያጠጣ ዋለ ሲመሽም ወደ በረታቸው ያጉራቸው ዘንድ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከመሸ ከደከመውም በኋላ አንደኛው በግ እንደጠፋበትም ተረዳ ዘጠና ዘጠኙን በበረት ቆልፎባቸው በጨለማ አንዱን በግ ፍለጋ ወጣ። ያንን በግ እሲኪያገኝ ድረስ በከባድ ድካም ውስጥ ሆኖ ፈለገው። አገኘውም። እጅግም ደስ አለው። ጎረቤቶቹንም ጠርቶ አንዱ በጌ ጠፍቶ ነበር ተገኝቷል ከኔ ጋርም ደስ ይበላችሁ አላቸው።

፪ኛ. አንዲት ሴት አሥር ሳንቲሞች (ድሪም) ነበሯት ከአሥሩ ሳንቲሞች አንዱ ጠፋባት መብራት አብርታ ፈለገችው፣ የቤቱንም ቆሻሻ ጠርጋ ወደ አንድ ጥግ ሰበሰበች ፈለገችው አገኘችውም እርሷም እንደ ባለ በጉ ጎረቤቶቿን ጠርታ አንድ ድሪም ጠፍቶብኝ ነበር አገኘሁት ከኔ ጋር ደስ ይበላችሁ አለቻቸው።

፫ኛ. አንድ ባለጸጋ ሰው ሁለት ወንድ ልጆች ነበሩት ይህ ሰው የሃብቱ ወራሾች እነዚህ ልጆች ብቻ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ሐብት የሚወረሰው አባትየው ሲሞት ነው። ትንሹ ልጅ ከአባቱ የሚደርሰውን ሐብት ንብረት ተመኘ አባቱንም ቢያይ ቢያይ አይሞትም እጅግም ቸኮለ። ስለዚህ ወደ አባቱ በመሄድ የሚደርሰውን አንድ ሶስተኛውን ይሰጠው ዘንድ ጠየቀ አባቱም ኩፍሎ ሰጠው። ሐብቱንም ይዞ ወደ አንድ እሩቅ አገር ሄደ። በልቶ ጠጥቶበት ከጋለሞታዎችም ጋር አባክኖት በአጭር ጊዜ ጨረሰው።

ገንዘቡ ሲያልቅ ጓደኞቹም ከአጠገቡ አንድ በአንድ እየሸሹት ብቻውን ቀረ። ሀብቱም አልቆ ባዶ እጁን ቀረ፣ ተራበ፣ ተጠማ፤ መጠለያም አጣ። ወቅቱም በአገሩ ድርቅ ተከስቶ ነበርና ረሐብ ሆነ። ያስጠጋው ዘንድ ወደ አንድ ሰው ዘንድ ሄደ። እርሱም አስጠጋው ሰውየው ላስጠጋበት ዋጋ ይሆነው ዘንድ አሳማዎቹን እንዲጠብቅለት አደረገው።

አሳማ እጅግ አስጠሊታ ከመሆኑ የተነሳ እስራኤላውያን አሳማ መጠበቅ አይወዱም። የነካው ይረክሳል፣ ሥጋውንም አይበሉትም። ይህ የባለጸጋ ሰው ወጣት ልጅ ውሎና አዳሩ እጅግ በሚገማ የአሳማ በረት ውስጥ ሆነ። ወቅቱ ድርቅ እና ረሐብ የነበረበት ወቅት ስለሆነ እጅግ ከመራቡ የተነሳ አሳማው ከሚበላው ይመገብ ዘንድ ይመኝ ነበር።
ርሐብና እና ጽም እጅግ ጸናበት። ችግርም ጸናበት።
በስተ መጨረሻ ወደ ልቡም ተመለሰ። እንዲህም አለ፦ በአባቴ ቤት እንጀራ የሚተርፋቸው አገልጋዮች ስንት ናቸው? ተነስቼ ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ አባቴ ሆይ የሚገባኝን ሁሉ ወስጄ ሄጃለሁ ከእንግዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ብሎ ወደ አባቱ ዘንድ ሄደ። አባቱም በርቀት ተመለከተው እጅግም አዘነለት ወደ እርሱም ሮጦ አቀፈና ሳመው።
ልጁም አባቴ ሆይ ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው።
አባትም ከሁሉ የሚበልጠውን ልብስ አምጡና አልብሱት፣ ለእግሩ ጫማ ስጡት፣ የሰባውን ፊሪዳ አምጡና እረዱለት እንብላ እንጠጣ ደስም ይበለን። ልጄ ሙቶ ነበር ሕያው ሆኗል፣ ጠፍቶ ነበር ተገኝቷል፤ አለ።
እቤት የነበረው፣ ከአባቱ ሐብት ንብረት ያልተካፈለው ትልቅ ልጅ እርሻ ዉሎ ወደ ቤት ሲመጣ ከቤታቸው ቅጽር ድምጽ ሰማ፣ ያልተለመደ ድምጽ ነው የዘፈን ድምጽ፣ የደስታ ድምጽ የምስራች የያዘ ድምጽ፣ እኛ ቤት ምን ተፈጠረ? ምንስ ክስተት ተከሰት? እኔ ከቤት ከወጣሁ እኔ የማላውቀው ነገር ምንስ ተፈጠረ ብሎ ጠየቀ፤ ከጎረቤትም ልጅ መጣና ወንድምህ ነው አለው።

ወንድሜ ምን ሆነ?
ወንድሜስ ከዚህ የት አለ? ብሎ ጠየቀ።

የጠፋው ወንድምህ ተገኝቷል፤ አባትህም ተደስቷል። ለወንድምህ መምጣት በቤታችሁ ትልቅ ደስታ ሆኗል። አባትህም ትልቁን ፊሪዳ ለወንድምህ አርዶለታል። አዲስ ልብስም አልብሶታል። ለጣቱም ቀለበት አጥልቆለታል ብሎ ወሬውን አደረሰው።

ወንድሙም እጅግ አዘነ፣ እኔ በዚህ ቤት ስኖር ሥጥር ሥግር አንዳች ቀን ትልቅ እና የሰባ ፊሪዳ አይደለም ግለግል እንኳን ታርዶልኝ አያውቅም፣ አዲስ ልብስ እና የጣት ቀለበት አልተገዛልኝም። ሐብት ንብረቱን ተካፍሎ ቤቱን ጥሎ የሄደን ልጅ ተመልሶ መቀበሉ ስለምን ነው በማለት አኮረፈ ወደ ቤትም አልገባም አለ።

አባቱም ስለ ትልቁ ልጅ ተጨነቀ ሊያግባባውም ሞከረ። ስለ ጠፋው ልጁ/ወንድሙ መገኘት ሊነግረው ሞከረ።

ትልቅ ልጅ፦ ልጅህ ሲመጣ የሰባውን ፍሪዳ አረድክለት፣ ለጣቱም ቀለበት አጠለክለት፣ አዲስ ልብስም እንዳለበስከው ሰማሁ ... እኔ እስከ ዛሬ እንደ ባሪያ ሳገለግልህ ነበር አንድም ቀን ለእኔ እና ጓደኞቼ አንዲት ጠቦት አላደረክም ገንዘቡን ከጋለሞታዎች ጋር ሲበትን ለኖረው ልጅህ እንዴት እንደዚህ ታደርግ ዘንድ ልብህ ፈቀደ አለው።

አባትም ልጄ አንተ እስከ ዛሬ ከኔ ጋር ነበርክ የእኔ የሆነው ሁሉ ያንተ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ወንድምህ ( ትልቅ ልጅ ወንድሙን ስለ ተናደደበት አባቱን ልጅ አለው አባት ግን ወንድም በማለት አስታወሰው) ሞቶ ነበር ሕያው ስለሆነ ጠፍቶ ነበር ስለተገኘ ደስ ሊለን ሐሴትም ልናደርግ ይገባል አለው።

ከላይ በተጠቀሱት ምሳሌዎች የጠፉ ሶስት ነገሮችን ተመልክተናል።
1. በመጀመሪያ በግ ጠፋ
2. በመቀጠል ድሪም (ሳንቲም) ጠፋ
3. በስተ መጨረሻ ሰው ነው የጠፋው
እግዚአብሔር በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 15 በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙትን ሁሉን ጠቅልሎ ሊይዝ በሚችል መልኩ ያስተማረበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። እዚህ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ሳይቀር በጣም ወርቃማ ምሳሌዎች ናቸው።

ይህ የትምህርት ክፍል ከመደነቁ ባሻገር በሕይወታችን ውስጥ የሚያሳየን ትልቅ ምሥጢር አለ። ይኸውም አንድ ክርስቲያን ከቤተክርስቲያን እንዴት አድርጎ እንደሚጠፋ፣ ሕይወቱ እንዴት እንደሚቅበዘበዝ፣ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚፈልገን፣ እንዴትስ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደምንመለስ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። (ጽሑፉ ረዘመ እኔ ረጅም ጽሑም አልወድም የምትል ከሆነ ከዚህ ምሥጢር አትሳተፍም)

በምሳሌው በመጀመሪያ የጠፋው እንስሳ ነው፣ በመቀጠል የጠፋው እቃ ሲሆን በመጨረሻም የጠፋው ሰው ነው።

• ሰወች ስንጠፋ ሰው ሆኖ የማይበድል እንጨት ሆኖ የማይጨስ የለም እያልን እንጠፋለን።
• አንዳንዴ ከሰውነት ክብር ዝቅ ብለን የእንስሳ ተግባር ስንከውን እንገኛለን። (አውሬያዊ ጭካኔ ይታይብናል።)
• አንዳንዴ ከእንስሳት ዝቅ ብለን እቃ የምንሆንበት አጋጣሚ አለ። እንስሳት በዘር አይጣሉም እኛ ግን ከነርሱ አንሰን በዘር እንጣላለን። አንበሳ ምን ቢከፋ ምን ቢርበው አንበሳን አይበላም እኛ ግን እርስ በርስ እንበላላለን። የማንጠቅም ርካሽ የምንሆንበት ጊዜ አለ።
እግዚአብሔር በነዚህ ምሳሌ እንደምንመለከተው ሊያስተምረን የፈለገው እንደ እንስሳም ብትጠፉ እፈልጋችኋለሁ፣ እንደ እቃም ብትጠፉ እፈልጋችኋለሁ፣ እንደ ሰውም ብትጠፉ እፈልጋችኋለሁ ሲል ነው። አንዳንዴ ከሰውነት ክብር ወርደን እንደ እንስሳ የምንሆንበት ጊዜ አለና። " ሰው ክቡር ሆና ሳለ እንስሳትን መሰለ" እንዲል። ከእንስሳም ዝቅ ብለን በእቃ ልክ ስንገኝ እንደሚፈልገን ያጠይቃል።

በጠፉት ሶስት ምሳሌዎች በመጀመሪው ላይ ፈላጊው እረኛ ነው፣ ሁለተኛ ላይ እናት ነው፣ በሶስተኛው ላይ አባት ነው።

የሁላችን አባትም እናትም የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ነው። "አባታችን ሆይ " በሉ ብሎ እንዳስተማረን። ሊቃውንቱም እግዚአብሔር እናት እና አባት ብቻ ሳይሆን አያታችንም ነው ይሉናል።

ለዚህም ምሳሌ ሲጠቅሱ እንዲህ ይላሉ፦

እግዚአብሔር ራሱን በብዙ ምሳሌ እንዲመስል (በዶሮ በወፍ እየመሰለ እንዲያስተምር) ዶሮ ጫጩቶቿን ከእቅፎቿ በታች እንድትሰበስብ እንዲሁ የአለሙ መድህን እግዚአብሔር እኛን ይሰበስበናል።

ዶሮ ለጫጩት እናትም አያትም እንደሆነች እርሱ እናታችንም አያታችንም ነው። ምድራዊ እናት እና አባት በዋልንበት አይዉሉም በአደርንበት አያድሩም። እግዚአብሔር ግን በዋልንበት የሚውል ባደርንበት የሚያድር መልካም አባታችን/እረኛችን ነው። " እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል በእረፍት ዉሃ ዘንድ ይመራኛል" እንዲል

እረኛ በጎቹን ቀን ከጠበቀ ሌሊት ይተኛል፣ እግዚአብሔር ግን እኛን ሲጠብቅ አይተኛም። "ሕዝቤን የሚጠብቅ አያንቀላፋም" ይላልና።

እረኛ በጉን ጠብቆ ካሳደገ በኋላ አርዶ ይበላዋል አልያም አርደው ለሚበሉት አሳልፎ ይሸጠዋል። እረኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ስለ መልካም እረኝነቱ በሰላሳ ብር ስለ በደላችን ተሸጠ። ተላልፎ ተሰጠ። ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹ የሸጡት እረኛ ነው።

እረኛው በጎቹን አርዶ ሲበላ የእኛን እረኛ ግን እኛ ተሰልፈን በቤተክርስቲያን ምሥጢር አርደን እንበላዋለን። የእረኛ ፍቅር እስከ ማረድ ነው። የእኛ እረኛ ግን ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ እስከ መስጠት ነው።

ነገር በምሳሌ እንዲሉ ምሳሌው እንዲህ ነው፥

እረኛው እግዚአብሔር ነው
መቶ በጎች የተባሉት ሰውና መላእክት ናቸው።
አንድ በግ ጠፋ የተባለው ሰው ነው ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ናቸው።

ይሕ ምሳሌ የማዳኑን ሥራ ነው የሚያሳየን።

እኛ ሰዎች እንዴት ከቤተክርስቲያን እንጠፋለን ካልን፥

1ኛ. እንደ በግ ነው፦ በግ የሚጠፋው አውቆ አይደለም። የሚበላው ሣር የሚጠጣው ውሃ ፈልጎ የፊት የፊቱን ብቻ እያየ ሳያስበው ነው። እኛም ከቤተክርስቲያን ርቀን የሄድነው፣ ጠፍተን የሰነበትነው እንዲሁ እንደ በጉ ነው ሳናውቅ እንደምንጠፋ ሳናውቅ/ የጸናን ስለሚመስለን/የቆምን ስለሚመስለን ነው።

በጉ ስለሚበላ ስለሚጠጣ ሲል እንደ ጠፋው እኛም በእንጀራ ጉዳይ ከቤተክርስቲያን የጠፋን አለን። (ቢዚ ነኝ፣ ሥራ ይበዛብኛል፣ አይመቸኝም፣ እቤት ስገባ ይመሻል፣ ጠዋት ከቤት የምወጣው በሌሊት ነው፣ ቅዳሜና እሁድ ይደክመኛል፣ ማህበራዊ ጉዳይ አለብኝ፣ ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ፣ ልጅ አሳድጋለሁ ወዘተ እያልን በሰበብ ጠፍተናል። ከአንዱ ሥራ ሌላ ሥራ፣ ከአንዱ ትምህርት ሌላ ትምህርት እያልን ላንመለስ ሄደናል።)

የዚህ በግ ሳር መብላት ውሃ መጠጣት ክፋት የለውም ዋናው ችግር ከበረቱ መራቁ እንጂ። የኛም ችግር ሥራ መሥራታችን፣ ትምህርት መማራችን፣ ቢዚ መሆናችን አይደለም። ከቤተክርስቲያን መራቃችን እንጂ። በጉ ከበረት እየራቀ ሲሄድ ተኩላ ይበላዋል ወይም ሌባ ይሰርቀዋል የእኛም ከቤተክርስቲያን ያርቀናል ወይም በመናፍቃን ያስነጥቀናል/ያስክደናል፤ አልያም በዲያቢሎስ እንጠቀጥቃለን።

በጉ ሲጠፋበት እስኪያገኘው ድረስ ፈለገው፤ ሲያገኘውም እጅግ ደስ አለው አንስቶም በትከሻው ተሸከመው ይላል እግዚአብሔር አንድ አዳም ቢበድል ቢጠፋ እስኪያገኘው ድረስ እጅግ አሰልቺ በሆነ ትእግስት በሚጨርስ ፍለጋ ውስጥ አገኘው። ከቤቱ የጠፋን እኛንም እግዚአብሔር እስኪደክመው ሳይሆን እስኪያገኘን ድረስ ይፈልገናል። ለዚህም ነው በቃሉ ብርሃንነት ሊፈልገን በአደባባዩ አልገኝ ስንለው በማህበራዊ ሚድያ ሳይቀር ቃሉ እንዲነገረን ያደረገው። ለዚህኮ ነው ወደ እርሱ መሄድ ሲገባን ወደኛ የመጣው። እምቢ አሻፈረኝ ስንለው በመሰልቸት ሳይተው ወደ በረቱ እስክንመለስ ድረስ እየፈለገን ያለው።

አስቀድመን እንዳየነው የጠፋው በግ ሲገኝ በቤቱ ደስታ ሆነ በትከሻውም ተሸክሞ ወደ ቤቱ ወሰደው ሳያውቅ ነውና የጠፋውና። እኛንም የአለም መድሃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤቱ ስንመለስ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ዘንድ ደስታ ይሆናል ሳናውቅ ነውና የጠፋነው።

አውቆ ከመጥፋት ይሰውረን።

አሁን በዚህ ሰአት ይህን ቃል እንድናነብ ያደረገን፣ በቤቱ የሰበሰበን፣ በቤቱ እንድንኖር ያደረገን እኛ ፈቅደን መጥተን አይደለም እርሱ በፍቅር በትከሻው ተሸክሞን አምጥቶን እንጂ። ይኸን ጊዜ ከጽሁፍ ርዝመት ያልጨረሱት አሉ። አንተ እየጨረስክ ያለኸው በፍቅር በደስታ በትከሻው ተሸክሞህ ስለመጣ ነው እንጂ አንተ ከቃሉ ፍቅር ስላለህ አንተ ስለምትሻል አይደለም። እኛማ አለም እንዴት ሰነበተች?፣ የፖለቲካው ጡዘት የት ደረሰ?፣ ዋንጫውን ማን በላ?፣ ወዘተ የሚለው ሚድያ ላይ ነበርን። አሁን እዚህ የተገኘነው መርጠን አይደለም ተመርጠን እንጂ። ፈቅደን አይደለም ተፈቅዶልን እንጂ።
እኔኮ እፈልጋለሁ ለመምጣት ግን አይመራኝም እንላለን ዛሬ መርቶ ያመጣን እግዚአብሔር ነው የኛ ብርታት አይደለም። " በምህረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ" እንዲል። እየፈለጉ ያልመጡትን እግዚአብሔር ያምጣልን። የመጣነውን በቤቱ ያለነውን አያርቀን።ያጽናን።

ክፍል ሁሉት ይቆየን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...