ዛሬ ለየት ባለ መልኩ የምንመለከተዉ በልዩ አፃፃፉ እና በብዙ ተከታዮቹ የሚታወቀዉ ስለ
ዘመድኩት በቀለ (ዲያቆን/መምህር) ሲሆን እንደሚታወቀዉ በተደጋጋሚ ፌስቡኩን እንደሚዘጋ የሚታወቅ ሲሆን ወደፊትም እንደሚዘጋበትና
አገልግሎቱን እንደሚያቋርጥበት ይታወቃል ስለዚህ ሌላ መፍትሔ ማምጣት ግድ ሆኗል፡፡
ራሱ ዘመድኩን እንዲህ ያቀርበዋልና ስሙት፤ ተከተሉት፡፡
ወደፊት ልንሠራቸው ያቀድናቸውን ዕቅዶች በሙሉ አስፍሬያለሁና ጦማሯን አንብቧት። ለሌሎችም #SHARE በማድረግ አጋሯት።
#ETHIOPIA | ~ እንዴት ናችሁልኝሳ ? ሀገሩ፣ መንደሩ፣ ሰፈሩ፣ ቀዬው ሰላም ነው? እኔማ አምላክ ክብር ይግባው ደህና ነኝ።
ይኸው ፌስቡክ ድራሽ አባቴን ቢያጠፋኝም እኔ ዘመዴ፣ የድንግል አሽከር የማይሰበረውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንደያዝነ፣ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ውበት አጊጠን፣ እንደ መስከረም ወር ጠሐይ ፈክተን፣ በገነት መካከል እንደ ቆመ የወይራ ዛፍ ለምልመን፣ እንደ ኃያሉ አንበሳ እያገሳን፣ እንደ ነብር፣ እንደ አቦ ሸማኔ እየፈጠንነ፣ እንደ ንስር ታድሰን እነሆ በአዲስ ጉልበት፣ በአዲስ ወኔ፣ አለን ነበረን እንል ከነበረው አቅም ላይ እጥፍ ጨምረን፣ እንደ አልማዝ እንደ ዕንቁ እያንጸባረቅን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የፌስቡክን ኳራኒትን ፈጽመን ይኸው ዳግም ተከስተናል።
እንደተለመደው እንደ አማኝነታችን ስለ ቅድስት የኢትየጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፣ የኢትዮጵያ ዜጋ በመሆናችን ደግሞ ስለ ውቢቷ ሃገራችን መወያየታችንንና መመካከራችንን፣ መሟገት፣ መፋጨታችንንንም አጠንክረን እንቀጥላለን። መፋታት፣ ማፈግፈግ፣ መሸሽ፣ ማምለጥና፣ ማስቀየስም የለም። ሰምና ወርቅ ፈልግ የሚል ጦማር እኔ ጋር አይሠራም። እንደ ሐረር፣ እንደ ሲዳሞ ግሩም ጣዕም ያለው ቡና አስሬ ተለክቶ እንደተለቀመ፣ ታጥቦ ተቀሽሮ፣ ተቆልቶ፣ ተወቅጦ ተፈልቶ እንደወረደ ቡና ጦማሬን ትጠጡት፣ ፉትም ትሉት ዘንድ ከሃገረ ጀርመን፣ ከራየን ወንዝ ማዶ ለእናንተ መቅረቡን ይቀጥላል።