ይድረስ ለበረሃው ጓዴ…
ምናልባት ይህች መልዕክቴን የያዘች ደብዳቤ በጅህ እንደገባች ከምን ትዝ ብሎህ ፃፍክልኝ ሳትለኝ አልቀረህም ከጊዜው ርቀት የተነሳ ምንም እንኳን ከተለያየን 2000 ዓመታት ገደማም ቢሆንም አብረን ያሳለፍነው የበረሃው ጓደኝነታችን አይረሳኝም ምናልባት አንተ ጥንታዊ ግብርህን ብትቀይርም ታሪክህም ቢቀየር ይህንን ደብዳቤ ስታነበው ትዝ እንደሚልህ እገምታለሁ ያለጥርጥርም በመተማመን ያኔ ያሳለፍናቸው ‹ደስታን› በሚፈጥሩት የግፍ ሥራዎቻችን በጣም እንደምትፀፀት፤ ጓዴ እንኳን አንተ እኔ ራሴ ዛሬ የማይረባ ጸጸት ሆኖ ነው እንጂ እየጸጸተኝ ነው ያለው፤ ታዲያ ምን ዋጋ አለው ብለህ ነው የመጸጸቻው ጊዜው ያለፈኝ የመጨረሻው ሰዓት ያኔ ፍርዳችንን በኢየሩሳሌም አደባባይ ያለበደሉ ከእኛ ጋር ሦስተኛ በመሆን ፍርድን ከተቀበሉ ጋር ዋጋችንን ስንቀበል ከኅልፈተ ሕይወታችን በፊት ስትፀፀት ነበር እኔን ያመለጠኝ፡፡
የበረሃው ጓዴ ለመሆኑ ምቾቱ ተድላ ደስታው እንዴት ይዞሃል?
የእኔን ስቃይ ሃዘን መከራ እንዳልነግርህ የሚደርስብኝ ሁሉ ግፍ እንዳላጫውትህ እንዳለ እንዳላዋይህ አንተም ታውቀዋለህ አንድም ሃሜት ባህሪህ እንዳልሆነ አውቄዋለሁና ይቅርብኝ በሌላ በኩል ‹‹ከወደቁ በኃላ መንፈራገጥ ለ…›› እንዳይሆነብኝ በዝምታ ባልፈው ይሻለኛል፡፡
ጓዴ፡- ወደዚህ ወደ ድቅድቁ ጨለማ ማረፊያ ከመጣሌ በፊት ያለህበት የተድላ የደስታ ሥፍራ አስጎብኚዎቼ እንዲቆጨኝ ወስደው አሳይተውኝ ነበር ምን ዋጋ አለው ታዲያ … በነበር ነብሮ ቀረ እንጂ፡፡
ዛሬም በዚያ ሆነህ ከጓደኞችህ ጋር ስትደሰት በሩቅ ሳይህ እናቱ እንደሞተችበት ልጅ በዚህ በጨለማ ቁጭ ብዬ በመኮራመት እቀናብሃለሁ መቸስ አንተ በእኔ እንኳን ልትቀና ቀርቶ ጊዜ ኖሮህም አታስበኝም ለመሆኑ ያኔ አንተ እንደዚያ ስትራራ ስትጸጸት ልቤን ምን ይሆን የዳፈነው? … ጓዴ እንኳን ላንተ ለእኔም ዛሬ ድረስ ግራ ሆኗል በልተወው፤ …
የኔን ኑሮ ልፃፍልህ ብል በምን ቃል እንደምገልፅልህ ግራ ይገባናል መፃፌን ያዩ ነፍሳትም መከራው የሚቀልባቸው እየመሰላቸው የእናንም ፃፍልን ብለው ስለሚያስቸግሩኝ ይቅርብኝ ማንም የማይጋራኝን የበረሃውን ትዝታ ለምጣው አሁንም ከ2000 ዓመት በላይ ወደ ኋላ ልመልስህ ወደ ግብፁ በረሃ ያኔ እንኳን እነዚያ የሚያሳዝኑ እናት እና ልጅ ያ ደግሞ ሽማግሌው አንድም ሴት አለች ስማቸውን ባላነሳልህም ሕፃኑ ከ30 ዓመት በኃላ በኢየሩሳሌም ከኛ ጋር መከራን የተቀበለው ሲሰደዱ በበረሃ አግኝተናቸው የእግሩን ጫማ የወርቁን ማለቴ ነው ወስጄባቸው ሕፃኑ እናት አምራ ያለቀሰችው ትዝ ይልሃል የደነገጠችውስ ድንጋጤ ታስታውሳለህ እኔ አልረሳውም ዛሬ ዛሬ እየመጣ ሰላም ባጣሁበት ስፍራ እርሱም አብሮ ተዳምሮ ሰላም ይነሳኛል፡፡ ደግነትህ አይታየኝም ነበር ደግኮ ነበርክ ከምን እግር ጥሎህ ከኔ ጋር እንደዋልክ እንጃ እንጂ የዋህ እኮነህ ከደግነት ከየዋህነትህ የተነሳ ነበር የወስድኩትን የወርቅ ጫማ ከዚያ በፊት በቁመናው የለወጥከኝ የቱን ትቼ የቱን ላንሳ ዛሬ የምቀባጥርብህ ይቀልልኝ እንደሆነ ብዬ እኮ ነው . . .
የበረሃ ጓዴ፡- ሥራ ፈት ሰው ምን ሥራ አለው ብለህ ነው፡፡ ይኸውልህ ከዚህ ከጨለማው ቁጭ ብዬ ደብዳቤ መፃፍ ሆኗል ሥራዬ ባለፈው ላንተ እንደፃፍኩልህ ለጳውሎስም ፅፌለት ነበር ያንተ መልሱ ባይደርሰኝም የጳውሎስ ደርሶኛል ምን አለኝ መሰለህ ጳውሎስ ለካስ እኔ ብቻ ኤደለሁም የምፅፍለት ዴማስም ጽፎለት ኖሮ ‹‹መጣሁ ቆየኝ …›› የሚል አንድ ደብዳቤ ጽፎልኛል አለኝ በመገራም እባካችሁን አትገረሙብኝ የጨነቀው ሠው ብዙ ይቀባጥራል ጨንቆን ነው የምናስጨንቃችሁ፡፡
የበረሃ ጓዴ፡- ሥራ ፈት ሰው ምን ሥራ አለው ብለህ ነው፡፡ ይኸውልህ ከዚህ ከጨለማው ቁጭ ብዬ ደብዳቤ መፃፍ ሆኗል ሥራዬ ባለፈው ላንተ እንደፃፍኩልህ ለጳውሎስም ፅፌለት ነበር ያንተ መልሱ ባይደርሰኝም የጳውሎስ ደርሶኛል ምን አለኝ መሰለህ ጳውሎስ ለካስ እኔ ብቻ ኤደለሁም የምፅፍለት ዴማስም ጽፎለት ኖሮ ‹‹መጣሁ ቆየኝ …›› የሚል አንድ ደብዳቤ ጽፎልኛል አለኝ በመገራም እባካችሁን አትገረሙብኝ የጨነቀው ሠው ብዙ ይቀባጥራል ጨንቆን ነው የምናስጨንቃችሁ፡፡
ይህንን ደብዳቤ ሥፅፍና ሥልክ እንዴት በጭንቀት መሰለህ እንኳን መላክ መፃፍ አይቻልም በድብቅ ነው ከፃፍኩት ቆይቻለሁ የምልከው ሰው አጥቼ ድንገት አንዲት ቆንጆ ሴት ሥሟ ክርስቶስ ሰምራ የምትባል ወደኛ መጥታ ነበር ድንገት አግኝቻት በርሷ በኩል ልኬነው ያኔ በረሃ ያገኘናት የሕፃኑ እናትም አንዳንድ ቀን መጥታ በሩቅ አያታለሁ ስለማፍርና እንደገናም ከነፍሳትም ብዛት ወደርሷ መሄድ መንገዱ ስለሚጣበብ ወደርሷ መቅረብ አልቻልኩም ከወንዶችም አንድ እግሩ የተቆረጠ ይመጣል ብቻ ብዙ የሚመጡና ነፍሳትን ይዘው የሚመጡ አሉ ለማንኛውም ይህቺ ደብዳቤዬ ከአንተ ዘንድ እንደ ደረሰች ከዕለታት በአንደኛው ቀን እኔም እመጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጓዴ የሚሆን ከሆነ ምን አለ ሲመጡ እንዲወስዱን ብትነግርልኝ?...
በተረፈ ነገር አላበዛብህም በዚሁ ይብቃንና አንተም ሁኔታዎችን ብትገልፅልኝ ስለምወድ ፃፍልኝ እንግዲህ ከዚህ ከተፈረደብን ፍርድ ከዚህ ጉስቁልና ይግባኝ ብዬ መውጣት የማይቻል ቢሆንም አሁን ባልኩህ መንገድ ብትሞክርልኝ ተስፋ ይኖረኛልና አደራ አደራ …
እባክህ እባክህ ወንድሜ እኔ ከዚህ ሆኜ ብጮህ የሚሰማኝ የለም አንተ ሳትሻል አልቀረህም ሥራም ቢበዛብህ ከዚህ ሆኜ በምድር ያሉት ይታዩኛል የኔን አይነት ኑሮ የሚኖሩ እባክህ ሰውም ቢሆን ልብህ አንድ በላቸው በዚሁ ከቀጠሉ ማለቃቸው ነው፤ የኛስ የዚያኔው ሽፍትነት በማናውቀው ሰው ላይ ነው ያሁኑ ግን እርስ በርስ ሆኗል የሰው ነፍስ እጅግ የረከሰችበት ዘመን ሆኗል መተዛዘን ጠፍቷል ከበደላቸውም ምክንያት እግዚአብሔርም ርቋቸዋል፡፡ ፊቱንም ከነርሱ አዙሯል እንደኔ ከመሆናቸው በፊት ስለህያው ነፍስ ብለህ ታደርጋቸው፡፡
ደህና ሁን የበረሃው ጓድህ፡፡
ካንተው ጓደኛ ዳክርስ በገነት ላለው ጥጦስ