ማክሰኞ 19 ማርች 2013

ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ



ከሳጥናኤል ማስታወቂያ ሚኒስተር የወጣ
ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ
        ማስታወቂያ ድርጅታችን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ክፍት የሥራ ቦታዎች ሠራተኞችን አወዳድሮ ለመቅጠር ይፈልጋል፡፡
1.  ለክፋት ማበልፀጊያ ማዕከል፡- በዕውቀቱ ወይም በጉልበቱ በማጭበርበር ወይም በመጭበርበር ዲግሪ የተመረቀ ዕውቀትን የዛቀ በተንኮል ጥበብ የመጠቀ ከአጉል ሱሶች ማለትም፡- ከፍቅር፣ ከደግነት ከእውነትና ከጋራ ዕድገት የራቀ ከሚኖርበት ክልል በማንኛውም የማኅበራዊ ግንባታ ሂደት ውስጥ ያልተሳተፈ መሆኑን መረጃ ማቅረብ የሚችል፡-
·        ዕድሜ፡- በዚህች ዓለም ላይ ቢያንስ ለግማሽ ቀን የኖረ
·        የሥራው ዓይነት፡- ነገር ጉንጎና
·        ደሞዝ፡- እንደሌብነት
·        የሥራው ቦታ፡- ሥራ ከማይሠራባቸው ከተሞች ባንዱ
2.  ለዕብዶች ተራድኦ ድርጅት- አንድ ካልታወቀ ዩኒቨርስቲ በማስትሬት ድግሪ ተመርቆ ‹‹ኑሮኝነት›› ሙያ .ኤች. ያለው ከሰው ልጅ ጋር በመኖር ቢያንስ የአምስት ደቂቃ ልምድ ያለው፡-
·        ዕድሜው፡- ያልታወቀ
·        የሥራ ዓይነት፡- ገላጋይነት
·        ደሞዝ፡- የአንድ ሺህ ብር ጫት
·        የሥራው ቦታ፡- መንጨቆረር
3.  የሽርደዳና የአቃቂር ማምረቻ ፋብሪካ- አንድ እንደ ዘንድሮ ሰው ‹‹ምላሱ መንታ አንዱ ለፍቅር አንዱ ላሜታ›› የሆነ ‹‹ሄደ ተናገሩ መጣ ዝም በሉ›› ጠንቅቆ የሚያውቅ የነገርን ፊደል የለየ ሆኖ ቢያንስ የአምስት ዓመት የቅናት ልምድ ያለው የመላዕክት ሆነ የዲያብሎስን ቋንቋ አሳምሮ መናገር የሚችል፡-
·        ዕድሜ፡- እንደምላሱ
·        የሥራ ዓይነት፡- ጥሬ የሠው ሥጋ ዘልዛይነት
·        ደሞዝ፡- በንትርክ
·        የሥራ ቦታ፡- አዲሱ የነገር ቄራ


ዓርብ 15 ማርች 2013

የመወለድ ሳምንት! እስከ መጋቢት 22 2013



የመወለድ ሳምንት!     እስከ መጋቢት 22 2013



ወደ ኋላ ረጅም ዓመት ስንመለስ ግጥም እጽፍ እንደ ነበረ ትዝ ይለኛል!
እንዲሁ ደሞ ከረጅም ዓመት በኋላ እንዴት እንዳቆምኩት በማይታወቅ ሁናቴ አቁሜ እራሴን አገኘሁት! ካለመፃፍ መፃፍ ቢሻልም የኔ ግን እንኳንም ቀረ ሽ ሽ ሽ ት ት ት ይበዛዋልና (በሳድስ ነዉ የሚያልቁት ማለቴ ነዉ) ከሳድስ ጋር የተቆራኘ ነገር ኖሮኝ ሳይሆን ለግጥም ሳድሶች ቤት ለመምታት ቀለል ስለሚሉ እንጂ፤ አሁንም የግጥም ዛሬ (ዛር) ሳይሆን ቅዠቴ ሲነሳብኝ ከዚያ የተሻለ አልፅፍም ጥሎብኝ ግን እንደ ግጥም ነፍሴን የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ማንበብ እወዳለሁ ጊዜዉ አለፈብኝ እንጂ ገጣሚ ሳላፈቅር እቀራለሁ ብላችሁ ነዉ? (ሳቁልኝ ወይም ሳቁብኝ ጎበዝ ይህንን በግጥም ፍቅር እብደቴን) .. … …
ከዚያ በኋላ እንዲሁ የግጥም ፍቅሬ ወረት ሆነና ስሙን ጠንቅቄ ወደማላቀዉ ( ጓደኞቼ ሥነ-ፅሁፍ ወደሚሉት) አዘነበልኩ፤ የሆነ ጊዜ ወደ 1992 ዓ.ም. አካባቢ ይመስለኛል ባልንጀራዬ፣ በጣም የምወዳት እህቴ እና ባለዉለታዬ (መምህር አፀደ ማርያም ስሻዉ በአሁኑ ሰዓት ኮኮበ ፅባህ ት/ቤት በማስተማር ላይ ትገኛለች)(እባካችሁ አመስግኑልኝ) እባክህ ፃፍ ፃፍ ስትለኝ አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ መፃህፍትን ስትገዛልኝ፣ ስታበረታኝ … … …. ለዚህ በቅቼላት ድፍን አንድ ዓመት ሞላኝ የሚገርመዉ ግን ዛሬ ድረስ ምን እያረኩ እንደሆንኩ አለማወቋ ነዉ፤ መቸስ ለምስጋና ከተነሳሁ አይቀር እንዲሁ ቁጭ ብዬ ስቧጭር የነበሩትን ነገሮች እስኪ ላንብብልህ እያልኩት የማስቸግረዉንና የግድ በሚያሰኝ መልኩ እንዲህ እንድፅፍ አለበለዝያ ለመፅሔት እና ጋዜጣ አዘጋጆች እንድልክ (ለማናቸዉም አላኩትም እንጂ) ይጎተጉተኝ የነበረዉን ወንድሜ መታገስን፣ በኮምፒዉተር ፅሁፎቼን ትፅፍ የነበረችዉን ወ/ት ፅዮን ፍቅሩን፣ ከምንም በላይ በቃላት ገልጬ የማልጨርሳቸዉን ድርጊቶች በማድረግ በመራዳት ያልተለየችኝን እቴነሽ እጅጉን፣ዉድ ጊዜአቸዉን እንደ መስዋዕት በግ የሰዉልኝ ቤተሰቦቼንና በቃላት ያልጠቀስኳቸዉና በልቤ ዘወትር ያላችሁትን ምስጋናዬ በእግዚአብሔር ሰፊ እጅ ይሰጣችሁ፡፡ከምንም በላይ ደግሞ Ethiopia,USA,Germany,Russia,Switzerland,Sweden,Israel,Italy,Unite Kingdom,France,… በመሆን ወርቅ የሆነ ጊዜአችሁን በመሰዋት ስታነቡ የነበራችሁትን ከመቀመጫዬ ተነስቼ እጅ እነሳለሁ፡፡
ቀጠል አድርጌ ሳክልም ስጀምርም ስጨርስም ሁሌ የማመሰግነዉ አምላኬ በመካከል እጅግ ተስፋ የሚያስቆሩረጡ ሂደቶችን እንዳልፍ ብርታቱን ስለሰጠኝ ዛሬ እንደደረስኩ ልነግራችሁ ወዳለሁ፡፡ ይህ እንደ መፃፍ ባይቆጠርም መቸስ እንኳን ረዘም ያለ ነገር ደብዳቤም መፃፍ ይከብድ እንደነበር አዉቅ ስለነበር ብርታት ስለሆነኝ አምላኬ ምስጋና ያስፈልገዋል፡፡ መቼ ይህ ብቻ ፡-

በቂ መረጃ ሳጣ፣
የማፅፍበትን ገንዘብ ሳጣ፣
የሚፅፍልኝ ሰዉ ሲቸግረኝ፣
ሙያዊ የምክር አገልግሎት የሚሰጠኝ የሰዉ ያለህ ስል፣
የፃፍኩትን አንባቢ ሲጠፋ፣
የምፅፈዉ ጉዳይ ኖሮኝ ጊዜ ስቸገር ፤ …
አምላኬ ሁሉ ቦታ የክብር ስፖንሰርና አጋር በመሆን ከአጠገቤ ስለነበር ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

ድካሜንስ ለምን አልናገርም፡-

የጀመርኩትን ቀኑን ጠብቄ አለማዉጣት፣
ይቀጥላል እያልኩ በዚያዉ መጥፋት፣
ያልበሰሉ ፅሆፎችን መልቀቅ፣
አስፈላጊ መረጃዎችን በጊዜዉ አለማድረስ፣… እነዚህ ሁሉ እኔ የማዉቃቸዉ ሲሆኑ እናንተ የምታዉቁት እጅግ ከዚህ ይበዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡በቀጣዩ ዘመናችን አብረን ስለምንዘልቅ፣ ስለምንሰራ፣ ይህ መጦመሪያ የሁላችንም እንደመሆኑ መጠን ጥሩ ነገር አብረን እንደምንሰራ ተስፋ አለኝ፡፡
ይህንን ጦማር የጀመርኩት በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር መጋቢት 22 2012 ነበር ይህ ሳምንት የዚህን ጦማር መወለድ እያሰብን አስተያየቶችን በመስጠት፣ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ያመለጡንን ወደ ኋላ እየተመለስን በማንበብ፣ … የምናከብርበት ሳምንት ነዉ፡፡ክቡራን አንባቢዎቼ አሁንም እንኳን ለጦማራችን አንደኛ ዓመት አደረሰን፡፡



ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...