እሑድ 8 ኦገስት 2021

ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር

 "ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር"

በደረሰ ረታ


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አባቷ ኢያቄም እናቷ ሐና በመባል የሚጠሩ ሲሆን የተጸነሰችሁ እንዲሁ በሐጢያት ሳይሆን " ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉዋት" በተባለው አምላካዊ ሕግ እንጂ። ኦሪት ዘፍጥረት 1፥28

ኦ ድንግል አኮ በፍትወት ደነሰ ዘተፀነስኪ ድንግል ሆይ " ዘርዕ ዘይወፅእ እምስካበ ተአዳዌ ሕግ ይከውን ለቅጥቃጤ ወለሐሳር" ለሐሳር ለመከራ የተጸነስሽ አይደለሽም።

አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ከሐና ከኢያቄም ሕጋዊ በሆነ ሩካቤ ተወለድሽ እንጂ።

የእመቤታችን ቅድመ አያቶች (በጥሪቃ እና ቴክታ ) ባለጸጎች ነበሩ። ልጅ ግን አልነበራቸውም።

ሕልም አይተው እንደ ህልሙ መሰረት ቴክታ ጸነሰች፤ ሄእማንን ወለደች።

ሄኤሜን ዴርዴን፣ ዴርዴ ቶናህን፣ ቶናህ ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች።

ሐናም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ ነገዱ ከይሁዳ የሆነ ኢዩአቄምን አገባች። እርሷም እንደ አያቶቿ መካን ሆነች።

ሐና ልጅ ስላልነበራት እጅግ ታዝን ነበረ አንገቷንም ደፋች። ከዕለታት በአንደኛው ቀን ከቤተ እግዚአብሔር ሄዳ እጅ ነሳች። ስትመለስ ርግቦች ሲጫወቱ አይታ ፈጣሪዋን " ሁሉን ሁለት ሁለት አድርገህ ፈጥረሃል ሐና ባሪያህን ግን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታል። " በማለት አምርራ አለቀሰች።

ሐናና ኢያቄም ከቤተ እግዚአብሔር ሱባኤ ገብተው የሰው መሳቂያ መሳለቂያ እንዳይሆኑ ዕድሜ ዘመናቸውንም አንገታቸውን ደፍተውም እንዳይኖሩ ተማጸኑ፣ ወንድ ልጅ ቢወልዱ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንደሚሆን ሴት ልጅ ቢወልዱ መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ ሐር ፈትላ ትኖራለች ብለው ስለት ተሳሉ።

ወዲያው ነሐሴ ሰባት ሐና የዓለሙን መድኅን የወለደችውን ማርያምን ጸነሰች። እመቤታችንም ገና በእናቷ ማኅጸን ሳለች ብዙ ተአምራትን ታደርግ ጀመር። ይህን የሰሙ አይሁድ በምቀኝነት ተነሱባቸው። በድንጋይ ወግረው በእሳት ፈጅተው ሊገድሏቸው መከሩባቸው። የእግዚአብሔር መልአክም በማህጸን ካለችው የዓለም መድኃኒት እንደሚወለድ ያውቅ ነበረና ወደ ሊባኖስ ተራራ ሂዱ ብሏቸው በዚያ እያሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች።

የእመቤታችን መጸነስ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የነበረ ነገር ሳይሆን በአባቶች ትንቢት ሲነገር የኖረ ነበር። እመቤታችንም በተወለደች ዕለት ብርሃን ወርዷል፤ተድላ ደስታ ሆኗል።

የእመቤታችን አስተዳደግ ልቡናቸውን እንዳደነደኑ የዕብራውያን ሴቶች ልጆች እንዳደጉት በቧልት በጨዋታ በዋዛና በፈዛዛ አልነበረም። በንጽሕና በቅድስና ሆና በቤተመቅደስ አድጋለች እንጂ። ምድራዊ ኅብስትን፣ ምድራዊ መጠጥን ተመግባ ጠጥታ አይደለም። ሰማያዊ ኅብስትን ተመግባ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ጠጥታ አደገች እንጂ።

በእናት በአባቷ ቤት ሶስት ዓመት ከኖረች በኋላ የስለት ልጅ ናትና ሦስት አመት ሲሆናት አፏ እህል ሳይለምድ ልቧ ሰው ሳይወድ በቃላቸው መሰረት ወስደው ቤተመቅደስ ለካህኑ ዘካሪያስ ሰጡት በቤተመቅደስ ትኖር ዘንድ ቤተመቅደስ አስገቧት፣ በቤተመቅደስ ቅዱስ ሩፋኤል ኅብስት ሰማያዊ ፅዋዕ ሰማያዊ እየመገባት አስራ ሁለት ዓመት ኖራለች።

ዕድሜዋ አስራ አምስት አመት ሆኗታልና ጎልማሳ ስለሆነች አይሁድ ካህኑ ዘካርያስ ከቤተመቅደስ እንዲያስወጣት ዘበዘቡት እርሱም ለእግዚአብሔር አመለከተ። የአከባቢው ሰው ይጠብቋት ዘንድ እጣ ቢያወጡ በዮሴፍ ወጣበት፣ እምቢ ቢል ርግብ በራሱ ላይ መጥታ አረፈችበት፣ ዕጣ ቢጣጣሉም ደግሞ በዮሴፍ ወጥቶበታል። ምስክርነት በሶስት ይጸናል እንዲሉ እመቤታችንን የመጠበቁ ነገር በዮሴፍ ጸናበት። ሕዝቡም " በዚህም ቢሉ በዚህ እመቤታችን ላንተ ደርሳለችና ግብር ገብተን እንደሰጠንህ ግብር ገብተን እስክንቀበልህ ድረስ ይዘሃት ሂድ" አሉት። ሳይወድ በግድ ይዟት ሄደ። ዮሴፍ እመቤታችንን ወደ ቤቱ ይዟት ከሄደ በኋላ ወደ ዓለም ኑሮ አልተመለሰም። በንጽሕና በቅድስና ሲጠብቃት ኖረ።

አዳም ከበደለ ጊዜ ጀምሮ በአብ ሕሊና ስትታሰብ ኖራለችና እግዚአብሔር አብ ንጽሕና ቅድስናሽን ባየ ጊዜ አብሳሪውን  ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤልን ወደርሷ ላከው እርሱም እንዲህ አላት። " መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላእሌኪ፤ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ፤ ውእቱሰ ንጹሕ እምነ ሠለስቱ ግብራት ዘወእቶሙ ዘርዕ ወሩካቤ ወሰስሎተ ድንግልና እለ ሥሩዓን በእጓለ መሕያው ወእሙራን ቦሙ። ..." መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ ኃይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ይከለክልሻል። አካላዊ ቃል ከአባቱ እሪና ሳይለይ ካንቺ ተዋሐደ።ከምልአቱ ሳይወሰን ፀነስሽው። አካላዊ ቃል ካንቺ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዐርባ ዘጠነኛው ዓመተ ምሕረት በዘመነ ሉቃስ ጥር ሃያ አንድ ቀን በስልሳ አራት አመቷ ዐረፋለች።

ሐዋርያት አስከሬኗን ባጎበር አድርገው ወደ ጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና አስክሬኗን በእሳት አቃጥለን እናጥፋት ብለው ተማከሩ።

ታውፋንያ የተባለው ኃይለኛ ሰው ፈጥኖ መጥቶ የአልጋውን ሸንኮር ያዘው መልአከ እግዚአብሔርም በረቂቅ ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጠው። ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ በጸሎቱ ሁለት እጁን ቀጥሎለታል።

ሐዋርያት በዚህ ተደናግጠው ቢበተኑ ወንጌላዊው ዮሐንስ ከመልአክ ጋር አስክሬኗን በገነት ዕፀ ሕይወት ሥር አስቀምጠዋታል።

ቅዱስ ዮሐንስ ተመልሶ መጥቶ ሐዋርያትን አይዟችሁ እመቤታችን በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ናት ብሎ አጽናናቸው።

ሐዋርያት ቶማስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ልንቀር ነውን? ብለው በነሐሴ መባቻ በዕለተ ሰኞ ሱባዔ ገብተዋል። ሁለተኛውን ሱባዔ እንደጨረሱ በአሥራ አራተኛው ቀን መልዐኩ የእመቤታችንን አስክሬን ሰጥቷቸው ዕለቱን ቀብረዋታል።

በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ ነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ተነሥታ ዕለቱን ዐርጋለች።

ቶማስ በወቅቱ አልነበረም፤ ከሀገረ ስብከቱ ከሕንድ(ሕንደኬ) በደመነ ተጭኖ ሲመጣ እመቤታችን ስታርግ አገኛት። ከደመናው ሊወድቅ ነበረ።

እጅግ አዝኖ እመቤቴ ሆይ ቀድሞ ጌታዬ ልጅሽ ከትንሣኤው ለየኝ አሁን ደግሞ አንቺም ልትለይኝ ነበረ አላት።

አይዞህ ዕርገቴን ያየህ አንተ ብቻ ነህ፤ ጓደኞችህ ሐዋርያት አላዩም ለእነርሱም የማረጌን ነገር አንተ ንገራቸው አለችው። እንዲያምኑህም ይኸው ሰበኔን እንካ አሳያቸው ብላ ሰደደችው።

ቶማስም ሐዋርያትን የእመቤታችን ነገር ጠየቃቸው፣ ቀበርናት አሉት፤ ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆና? አላቸው።

እነርሱም አጥበን ገንዘን የቀበርናትን እኛን ካላመንክ ማንን ልታምን ነው? ከዚህ ቀደምም የልጇን ማረግ አላምን ብለህ በመጠራጠርህ እና ካላየሁ አላምንም ብለህ እጅህን ከተወጋው ጎኑ ሰደህ እጅህ ተኮማተረ። አሁንስ ምን ፈልገህ ነው የምትጠራጠረው ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ ጠየቀ።

ጓደኞቹም እንዲያምን ከመቃብሩ ስፍራ ወስደው ጉድጓዱን ቆፍረው አስከሬኗን ሊያሳዩት ባሉ እንደ ልጇ ከመቃብር የለችም። ሐዋርያት ከመቃብር አስከሬኗን ቢያጡ ደነገጡ።

ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ ስታርግ አግኝቻታለሉ ለባልንጀሮቹ የእመቤታችንን የማረግ ነገር ነገራቸው። እንዲያምኑትም ሰበኗን ሰጣቸው። እነርሱም ገንዘው የቀበሩትን ሰበኗን ቢያዩ አመኑ፤ ለበረከት ይሆናቸውም ዘንድ ሰበኗን ተካፍለው ድውይ ሲፈውሱበት፣ ሙት ሲያስነሱበት ኑረዋል።

ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር።

ቶማስ ማረጓን ብቻውን አይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በዓመቱ በነሐሴ አንድ ሱባኤ ገቡ። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ አስራ ስድስት እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ እስጢፋኖስን ዲያቆን አድርጎ ቆርቦ አቁርቧቸዋል። እርሷንም አቆረባት።

እኛም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምንገኝ ክርስቲያኖች የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለን ሱባኤ ገብተን ተገለጭልን እንላታለን። የበቁትን እየተገለጠች ታነጋግራቸዋለች። የኔ አይነቱን ሐጢያተኛ በበረከት እጆቿ ሕይወታችንን፣ ሥራችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ወዘተ ትባርካለች።

ማርያም ማለት መርህ ለመንግሥተ ሰማይ ማለት ነው። ምእመናንን እየመራች ገነት መንግሥተ ሰማያት ታገባለችና።

አንድም ፍጽምት ማለት ነው። ለጊዜው መልክ ከደም ግባት አስተባብራ ይዛ ተገኝታለች። ፍጻሜው ግን ንጽሐ ልቡና አንድ አድርጋ ይዛ ተገኝታለችና።

አንድም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው። ለጊዜው ለናት ለአባቷ ጸጋ ሀብት ሁና ተሰጥታለች። ፍጻሜው ግን ለሁላችን ተሰጥታለችና። አንድም ልዕልት ማለት ነው አርአያ ማለት ልዑል ማለት እንደሆነ። እመቤታችንንም መትሕተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ይላታልና። ተፈሥሒ ቤተ ይሁዳ ወተሐሠዪ ቤተ እስራኤል ተለአኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ማኅበረ መሃይምናን ወሕዝብ ማለት ነው።

አንድም ማሪሃም ማለት እግዝእትነ ብዙኃን ማለት ነው። አብርሃም ማለት አበ ብዙኃን ማለት እንደሆነ። ያንም በዕብራይስጥ እንጂ ይለዋል ብሎ ማርያም ማለት ቅሉ እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው።

ይቆየን።

አሜን








ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...