ማክሰኞ 22 ዲሴምበር 2020

የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ

 "የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።" 

/ማቴ 14፣36/
ደረሰ ረታ
13/04/2013ዓ.ም
$$$$$$$$$=====
በዓለም ላይ ብዙ ሐኪሞችና ብዙ ባለ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ሐኪሞቹ መድኃኒት ያዝዛሉ እንጂ ራሳቸው መድኃኒት አይሆኑም፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሐኪምም መድኃኒትም ነው፡፡
እሱ የሥጋና የነፍስ መድኃኒት ነው፡፡ ሥጋ በቊስል፣ ነፍስ በኃጢአት ሲታመሙ ገዳዩን ገድሎ የሚያድነው መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የድንግል ማርያም ልጅ ብቻ ነው፡!!

ሕክምናው ሲያድን ሲፈውስ ጠባሳ አያስቀርም።
ሲያድን ቀስ ብለህ አይደለም የምታገግመው አልጋህን ተሸክመህ ነው የምትሄደው። አስታማሚዎችህ ለርሱ ሲነግሩት ነው አንተ እቤት ሆነህ ከበሽታህ የምትገላገለው። እመን እንጂ ሲምርህ የጠሉህ ሁሉ ናቸው ጠብ እርግፍ የሚሉልህ፣ የገፉህ ያገለሉህ ሁሉ መንገድ ይመሩሃል፣ መንገድ ይለቁልሃል፣ በወንበራቸው ያስቀምጡሃል። ጠረንህን አጥፍቶ የማይታመን መአዛ ያውድሃል።

በእጁ መዳን ከእርሱ ወዲያ አዳኝ ከእርሱ መድኃኒት እንደሌለ ካመንክ እንኳንስ ዳሰኸው ጨርቁን ነክተህ ጥላው ሲያርፍብህ ስሙን ስተጠራ ትድናለህ።

ድንቅ አይበልህ እንኳን እርሱ በእርሱ የሚያምኑ ለሥሙ የሚገዙ እርሱ የሚያደርገውን ከርሱም በላይ ያደርጉ ዘንድ ስልጣን ተሰጥቷቸዋልና። ቅዱሳኑም ያድናሉ በጨርቃቸው እራፊ/ቁራጭ እና በጥላቸው ሳይቀር።

እነርሱ ስሙን ጠርተው ''በኢየሱስ ስም'' ሲፈውሱ አጋንንትን ሲያሳድዱ እርሱ ግን በሃይሉ እና በስልጣኑ በእርሱ ፈቃድ በአባቱ በአብ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ይህን ያደርጋል።

በዚህ የመጽሐፍ ክፍል ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙዎችን እያዘነላቸው አድኗቸዋል። አንደኛው ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የሆነውን ቅዱስ ጴጥሮስን ሲሆን ሌላኛዎቹ የጌንሴሬጥ ሰዎችን ነበረ። የመጀመሪያ ሰው ቅዱስ ጴጥሮስ የእጁን ተአምራት የቃሉ ትምህርት የተከታተለ ብዙ ልምድ የነበረው ሲሆን የጌንሴሬጥ ሰዎች ይህ እድል ከዚህ ቀደም አልነበራቸውም። ይህንንም እድል ያገኙት ከታንኳ ወርዶ ወደ መንደራቸው ገብቶ ባገኙት ጊዜ ነበረ።

እነዚህንም ከመፈወሱ አስቀድሞ ከቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቀብር መልስ ብዙዎችን እንደፈወሰ መጽሐፍ ይናገራል።በዚሁ ምእራፍ ቁጥር 14 ላይ ''ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።'' ይለናል።

እነዚህ የጌንሴሬጥ ሰወች ማን እንደሆነ ባወቁ ጊዜ በአከባቢው ባሉ በሽተኞች ዘንድ ሁሉ ሰው ላኩ የታመሙትንም ሁሉ በአንድ ሰበሰቧቸው።

ከባንኮክ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከኤሸያ እውቅ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ስለመጣ፤ አልያም የኩላሊት፣ የልብ፣ የዲስክ መንሸራተት፣ የውስጥ ደዌ እስፔሻሊስት ቡድን ስለመጣ ብለው አልነበረም የሰበሰቧቸው በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዙትን ሁሉ እንጂ።ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበሽታ ላይ ሳይሆን በመፈወስ ላይ ስፔሻላይዝ ያደረገ ነውና።

የተሰበሰቡት ሁሉ፦''የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ '' በእርሱ ዘንድ የካርድ የከፈለ የመድኃኒት መግዣ ያለው ጥሩ ዘመድ ያለው ሳይሆን የሚድነው ሁሉም ነው። ለዚህም ነው ማቴዎስ ''የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ'' ያለን።

በዓለማችን፣ በአህጉራችን፣ በአገራችን፣ በከተማችን፣ በመንደራችን፣ በቤታችን ሥንት ሰው አለ በደዌ የተያዘ? ሥንት ሰው አለ መዳን የሚገባው? የጌታን መምጣት ወደ እኛ መቅረብ ሰምቶ ወጥቶ አይቶ ማንነቱን ተረድቶ መፈወሰ፣ መዳን ያለበት፤ ጌታ በደጅ ቆሟል ሁላችንም ከማዳኑ እንሳተፍ።

ጥቂት የማይባሉ አዳኙን አምላክ (ሎቱ ስብሐት) ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና እንደ ፍጡር እያዩት አማላጅ ይሉታል።እንደ ጌንሴሬጥ መንደር ሰዎች ማንነቱን የምንለይበትን አእምሮውን ለብዎውን ፈጣሪ ያድለን።

ወደ ጌንሴሬጥ ከመግባቱ አስቀድሞ ቅዱስ ጴጥሮስንና የተቀሩትን ደቀመዛሙርት አግኝቷቸው ነበረ።

"ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።
ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር።ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፡— ምትሐት ነው፡ ብለው ታወኩ፥ በፍርሃትም ጮኹ።ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና፡አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፡ አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፡— ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ፡ አለው። እርሱም፡— ና፡ አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፡— ጌታ ሆይ፥ አድነኝ፡ ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፡— አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።
ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። በታንኳይቱም የነበሩት፡— በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፡ ብለው ሰገዱለት።ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ።"

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የለመኑት ፈቃዳቸውን እንደፈጸመላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ ማሳያ ነው በባህሩ ላይ እንዲራመድ ፈቅዶለታልና፤ ለተራቡት በልተው ጠግበው እስኪተርፋቸው መግቧቸዋል። ማእበሉን ጸጥ አድርጓል። ከዚህ በኃላ ነው የእግዚአብሔር ልጅነቱን ሲያምኑ ማዳኑን ያሳያቸው፤ የዳሰሱትም ሁሉ የዳኑት።

እኛ የአዲስ ኪዳን ትውልድ ሁላችን በአባቶቻችን በኩል ኢየሱስ ክርስቶስን አይተነዋል፣ ዳሰነዋል፣ አብረን በልተን ጠጥተናል፣ ስንቶቻችን መዳን ተደሮጎልናል?

የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዳወቁ የልብሱን ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበረ፤ እግዚአብሔር ዛሬ በአካለ ሥጋ በመካከላችን ቢመላለስ/ ለጸሎት በፊቱ ስንቆም የምንለምነው ምን ይሆን?

መዳን?

ብርና ወርቅ?

ቤትና መኪና?

ስልጣን?

ረጅም እድሜ?

ወይስ ... ምን ይሆን ልንለምነው የምንከጅለው?

ጌታን የአምስት ገበያ ያህል ሰው ይከተለው ነበረ ይላል ቅዱስ መጽሐፍ ነገር ግን ከ120 ቤተሰብ ውጭ ያለው አብዛኛው ገሚሱ ውብ ነበረና ደም ግባቱን ለማየት፣ ገሚሱ ደግሞ የእጁን በረከት እና ተአምራት ለመካፈል እና ለማድነቅ፣ የተቀሩትም ከቃሉ ትምህርት ስህተት ለመቃረም ነበረ።

እኛስ፥
• ክርስቲያን የመሆናችን ዋናው ዓላማ ምንድነው ?
• ለምንድንነው የምንከተለው?
• ግባችን ምንድነው ?
• አሁን የት ነው ያለነው?
• ከክርስትና ዓላማችን አንጻር አካሄዳችን እንዴት ነው?
• እያንዳንዳችን አሁን በዚህ ሰአት በፊቱ ለፍርድ ብንጠራ ምን ይለን ይሆን? ኑ እናንት የአባቴ ብሩካን የምንባል ነን? ወይስ,... ካልሆነ እስክንጠራ ምን እያደረግን ነው? (የንስሐ ፍሬ እናፍራ)
የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (እግዚአብሔር ወልድ) ማዕበሉን ጸጥ ያድርግልን፤ ከውስጥ ከውጭ የሚንጠንን የፍርሃት ማዕበል ቀጥ ያድርግልን። በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኝነት የተያዙትን ይፈውስልን፤ በዘረኝነት ደዌ በጽንፈኝነት ደዌ ከመመታት እግዚአብሔር ይጠብቀን። በክርስትና ሕይወታችን መጡ ሄዱ፣ ነበሩ የሉም፣ አመኑ ካዱ ከመባል ይሰውረን። ማመናችን፣ እርሱን መከተላችን ቸርነቱ ተጨምሮበት ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርልን። እረኛው እንደተመታበት መንጋ ከመሆን ይጠብቀን።

በእዝነ ልቡናችን አይተነዋል፣ ሰምተነዋል፣ ዳሰነዋልና መዳን ይሁንልን።
በቀረው ዘመናችን ንሰሐ ገብተን ለዘለዓለም የማያስጠማውንና የማያስርበውን ሥጋውና ደሙን ተመግበን ለርስቱ ወራሾች ለመሆን ያብቃን።
ይቆየን።
@ deressereta


ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...