ሐሙስ 20 ማርች 2025

ክርስቲያናዊ ሕይወት እና ሥነምግባር

 

ክርስቲያናዊ ሕይወት እና ሥነምግባር

ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁልጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡

1. ሕገ እግዚአብሔር

መጀመሪያውና ዋነኛው የክርስቲያን ሥነ ምግባር መለኪያው ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ አንድ ሰው ምናልባትም ሕይወቱ በሰው ፊት ሲታይ የሚያስደስት በአፍአ ያለው ጠባዩ እንከን የማይወጣለት ሊሆን ይችላል፡፡ በሕገ እግዚአብሔር ተመዝኖ ካላለፈ ዋጋ የለውም። በሰው ፊት መልካም ሆኖ የሚታይ ምግባር እግዚአብሔርን ሊያስደስት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ፡፡ኤፌሶን.66

ፈሪሳውያን ከእነርሱ ውጪ የሆነውን ሁሉ የናቁ ያለእኛ ሕገ እግዚአብሔርን አክባሪ ከእኛም በላይ ጻድቅ የለም ባዮች ነበሩ፡፡ነገር ግን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችና ሥራቸው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ እንዲያውም ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም ማቴ.520 በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቀ፡፡

እንዲያውም ከእነርሱ እርሾ /ትምህርት/ እንዲጠበቁ አስጠነቀቃቸው፡፡ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁማቴ.166 አለ፡፡ከዚህም ሌላ ብዙ ሠርተናል ሥነ ምግባራችን አስደሳች ነው እያሉ ለመወደስ በኩራት ይቀርቡ የነበሩትን ሁሉ አፍረው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ማቴ.1916-22 የንጉሥ ሳዖል ሥራ በራሱ በንጉሡ አሳብ ሲመዘን ምክንያታዊና ትክክልም ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ሊያስደስት አልቻለም፡፡ ቃሉን ስላላከበረ ለእርሱም ስላልታዘዘ ንቀኸኛልና ንቄሃለሁ ተባለ፡፡ ከንግሥናውም ወረደ፡፡ 1ኛሳሙ.1510-22 ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ዕብ.116

§  ክርስቲያን በጉዞው ሁሉ በጭፍን በራሱ እውቀት ብቻ አይመራም፡፡

§  በቃለ እግዚአብሔር ሕይወቱን እየመዘነ ሊራመድ ያስፈልጋል፡፡

§  በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ ራሳችሁን ፈትኑ፡፡ 2ቆሮ.135

§  የክርስትና እምነት እያጸኑና እየጠነከሩ እየበሰሉ የሚጓዙበት ሕይወት ነው፡፡

§  በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ከትላንት ዛሬ ከአምና ዘንድሮ አድጐ ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡

§  ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ጐልምሱ ጠንክሩ1ቆሮ.16 በሃይማኖት መጠንከር ሲባል በጊዜውም /በተመቸ ጊዜ/ አለ ጊዜውም /ባልተመቸ ጊዜ/ መጠንከር ይገባል፡፡ በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና፡፡ 2ኛጢሞ.42 እንዲል፡፡

§  ከሰው ሕግ ይልቅ የእግዚአብሔር ሕግ ቅርብ ነው፡፡ ከሰው ሕግ መደበቅ መሸሽ ይቻላል፡፡ ከእግዚአብሔር ግን ማምለጥ አይችልም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ሥራ በእርሱ ዘንድ የተገለጠች ናት፡፡ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን ማንም አያየኝም ኀጢአት እንሥራ ብላ ለሁለት ዓመታት ባባበለችው ጊዜ ኩፋ.2725 እግዚአብሔር ከእርሱ እንደማይለይ እያንዳንዱም ሥራው በፊቱ የተገለጠ እንደሆነ ያመነው ኀጢአትን እንዴት እሠራለሁ በማለት መለሰላት፡፡ ዘፍ.399 መዝ.1382-12

ስለዚህ ክርስቲያናዊ አኗኗራችን መልካም ምግባራችን ትክክለኛ የሚሆነው በእግዚአብሔር ሲመዘን ብቻ ነው፡፡ ብልጣሶርን በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ ዳን.527 የተባለው ለዚህ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሕግ ተለዋዋጭና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሕገ እግዚአብሔር ግን በዘመናት ብዛት የማይሻርና ቋሚ በመሆኑ ምግባራችን ከዚህ አንጻር ሊለካ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሠላም ነው፡፡ሮሜ.856

2. ሕገ ልቡና

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ የሚመራመር ክፉና በጎውን ለይቶ የሚያውቅ አእምሮ ሰጥቶታል፡፡ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፡፡ መዝ.13910 እንዲል፡፡ በተጨማሪም ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡ መዝ.118105 ብሏል፡፡ ሕግ ለሙሴ ከመሰጠቱ በፊት ደጋግ አባቶች በዚህ ሕግ እየተመሩ እንደሚገባ ኖረዋል፡፡

የሰው ልጅ ማንም ባያስተምረውና ባይነግረው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ያውቃል፡፡እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን እያንዳንዱም ወንድሙን እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና ይላል እግዚአብሔር፡፡ኤር.3134

ምሳሌ፤

አቤልከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየል እና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡ዘፍ.44-5

ሄኖክአካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና፡፡ዘፍ.524

ኖኅኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኘ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡ዘፍ.69

እነዚህና ሌሎችም በሕገ ልቡና ተመርተው መልካም ተግባር የፈጸሙና እግዚአብሔርም ሥራቸውን የወደደላቸው ናቸው፡፡ ዕብ.114-7

የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በራቀ ቁጥር ግብሩ ወደ እንስሳነት ይለወጥና የሚወቅሰው ኅሊና እንኳን ያጣል፡፡ የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡ መዝ.4812 ናቡከደነፆር በበደል ላይ በደል በመጨመሩ ለእግዚአብሔር ሕግ አልገዛም በማለቱ ግብሩ ሁሉ የእንስሳ ሆነ፡፡ ዳን.432 ስለዚህ ክርስቲያን በመጽሐፍ ከተጻፈው የእግዚአብሔር ሕግ በተጨማሪ በልቡናው ለተቀረጸው ሕግ ይገዛል፡፡ ራሱንም እየመረመረ ይጓዛል አጥፍቶም እንደሆነ ማንም ሳይፈርድበት በራሱ ላይ ይፈርዳል፤ ንስሐ ይገባል የጠፋው ልጅና በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ለዚህ ምስክር ይሆኑናል፡፡ ሉቃ.1511-19 ሉቃ.2341

 3. የሰው ሕግ

ይህን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የአንድ ሀገር መንግሥት ወይም የሚያስተዳድር አካል ሕዝቡን ለማስተዳደር የሚያወጣው ሕግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኅብረተሰቡ በባሕሉ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውና በወረቀት ያልተጻፈው ሕግ ነው፡፡በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ 2ኛተሰ.215 እንዲል፡፡

ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ሕግ እንደሚገዛ ሁሉ የሰውንም ሕግ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ አላጣላው ድረስ ሊያከብር ይገባል፡፡ አንድ ሰው ምንም ብጾም ብጸልይ፣ ለእግዚአብሔር እገዛለሁ ቢል የሚያስተዳድረውን አካልና የኅብረተሰቡን መልካም ባሕል ካፈረሰ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሩን ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡ በሥራ ቦታ የታዘዘውን ካልፈጸመ የሥራ ሰዓት ካላከበረ፣ በቤተ ክርስቲያን ያለውን ምግባሩን በሌላ ሥፍራ ካልገለጸው ዋጋ አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሔር እንደሚገዛ ሁሉ በሰውም ፊት ያለነቀፋ ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ በእነርሱም መካከል የሕይወት ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ ፊል.215 ሐዋርያው ከዚህም በተጨማሪ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንብሏል፡፡ 2ቆሮ.820 ይህ ሲባል ኀጢአትም ሲሆን የሰው ሕግ ወይም ባሕል ነውና ሁሉን መፈጸም አለበት ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ ከአንድ በላይ ማግባት፣ ጫት መቃም፣ ባሕል በሆነበት አካባቢ የሚኖር ክርስቲያን ከሰው ጋር ለመኖር በሚል ሰበብ ይህንና ይህን የመሰለ የአረማውያኑን ኑሮ ይኑር ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ክርስቲያን በእንዲህ ዓይነት ሰዎች መካከል ሲኖር የቅድስናን ሕይወት በተግባር በመኖር ማንነቱን ሊገልጥ ያስፈልጋል፡፡ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡ማቴ.516

ከዚህ አንጻር ብዙ ወጣቶች ሕገ እግዚአብሔርን ከኑሮአቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ሲከብዳቸው ይታያሉ፡፡ በእምነት የጸኑትን ሠለስቱ ደቂቅን፣ ዮሴፍን ሶስናን አይመለከቱም፡፡ እንኳን ክርስቲያን የሚለውን ስም የተሸከሙ ሲጠራም የሰሙት የማይመስሉ አሉ፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የምንኖረው ኑሮ እንደመሆኑ መጠን የግል መንፈሳዊ ሕይወትና ማኅበራዊ ኑሮ በማለት በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡

. የግል መንፈሳዊ ሕይወት፡-

የግል መንፈሳዊ ሕይወት ማለት እኛ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረን ሕይወት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ግንኙነት ይመሠረታል፡፡ አንድ ሰው ፍቅሩ እግዚአብሔር ከሆነ ምግባሩ መንፈሳዊ ሕይወቱ ይህንኑ የሚገልጥ ይሆናል፡፡

አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው ሕይወት የጠበቀ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ፤

ቃለ እግዚአብሔር፣

ንስሓ፣

ቅዱስ ቁርባን፣

ጸሎት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡

Ø  ቃለ እግዚአብሔር ለአንድ ክርስቲያን የሕይወት መስመሩን የሚያቃናለት ነው፡፡ቃልህ ተገኝቷል እኔም በልቸዋለሁ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ በስምህ ተጠርቼአለሁና ቃልህ ሐሴትና የልብ ደስታ ሆነኝ፡፡ ኤር.1516

Ø  ንስሓ ማለት መጸጸት ማለት ነው፡፡

Ø  የክርስትና ሕይወት የንስሓ ሕይወት ነው፡፡

Ø  በንስሓ የበደለ ከበደሉ ይነጻል፡፡

Ø  ኀጢአተኛውም ጻድቅ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለግል መንፈሳዊ ሕይወት ሥራችሁን አቅኑ፡፡ኤር.1811

Ø  ከንስሐ በኋላ ቅዱስ ቊርባን መቀበል ያስፈልጋል፡፡የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡ዮሐ.653

እንግዲህ ቃሉን ሰምተን ንስሓ ገብተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል የግል መንፈሳዊ ሕይወታችን የተስተካከለ ይሆናል፡፡ የግል መንፈሳዊ ሕይወት ጽናት ደግሞ ለማኅበራዊ ኑሮአችን ወሳኝ ነውና፡፡ ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ ይህንም አዘውትር፡፡ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፡፡ በእነዚህ ጽና ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ፡፡1ጢሞ.415

. ማኅበራዊ ኑሮአችን

ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮው ከሌሎች ጋር በሠላምና በፍቅር ሊኖር እንዲሁም አልጫውን ዓለም በምግባሩ ሊያጣፍጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ውስጥ ሊይዝ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-

ዓላማ

ራስን መግለጽ

ታማኝነት

ፍቅር

ትእዛዙን ማክበር

1.    ዓላማ

ክርስቲያን እንደ ውኃ ላይ ኩበት እየተንሳፈፈ ወንዙ ወደ ሚወርድበት አቅጣጫ አይጓዝም፡፡ እንደሚወዛወዝ ዛፍም ወደ ነፈሰበት አያጋድልም፡፡ የራሱ የሆነ ውሳጣዊ ዓላማና አቋም አለው፡፡ በምትሄድበት ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፡፡ ኢያሱ.17 ከዚህ የተነሣ ክርስቲያን፡-

§  የሚሠራውን በጽናትና በትጋት ይሠራል፡፡

§  የጀመረውን ከፍጻሜ ያደርሳል፡፡

§  በመከራ አይናወጥም፡፡

§  መስሎ ለማደር እንደ ጊዜው አይለወጥም፡፡

§  በዓላማ ስለሚጓዝ ዓላማውን ያሳካል፡፡

§  ክርስቲያን ምን ዓይነት ዓላማ ሊኖሩት ያስፈልጋል?

1.1.        መንግሥተ ሰማያትን መውረስ፡-

አንድ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣው ለጊዜያዊ ችግሩ ብቻ መፍትሔ ለማግኘት አስቦ ሳይሆን ሰማያዊ ክብርና ዋጋ ለማግኘት ነው፡፡ ድንኳን የሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን፡፡ 2ቆሮ.51

1.2.        የሚታወቅና ግልጽ ዓላማ፡-

ክርስቲያን ያለ ዓላማ በጭፍን አይጓዝም፡፡ ሳይታሰብ በድንገት በአጋጣሚ የሚል ነገር በርሱ ዘንድ እምብዛም ቦታ አይኖረውም፡፡ የሚታወቅ ግልጽ ዓላማ ኖሮት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሳካለት ይጸልያል፡፡ ሳታቋርጡ ጸልዩ፡፡ 1ተሰ.518 ከዚህ አንጻር አንዱን ዓላማው አድርጎ ይጓዛል። ጋብቻ ወይም ምንኩስና መካከል ሆኖ አያወላውልም፡፡

2.    ራስን መግለጽ

ክርስቲያን በሄደበት ሁሉ ማንነቱን መግለጥ አለበት፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ መሰወር አትችልም፡፡ ይህም ሲባል እኔ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን ነኝ እያለ በማወጅ ወይም በማስታወቂያ ሳይሆን አኗኗሩ ማንነቱን ይገልጠዋል፡፡ ይህም ኑሮው በቤተሰብ፣ በት/ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ወዘተ…… መገለጥ አለበት፡፡

3.    ታማኝነት

እውነተኛ ክርስቲያን

o   ምሎ የማይከዳ፣

o   አደራ የማያጥፍ፣

o   የማይወላውል ለምስክርነት የሚበቃ ነው፡፡

ታማኝ ሰው መልካም የሚለውን ይናገራል፡፡ የሚናገረውን ይሠራል በሃላፊነት ቢቀመጥ ያለ አድልዎ ወገናዊነት ያስተዳድራል፡፡ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ፡፡ ማቴ.2521 ይባልለታል፡፡ ታማኝነት ለራስ ታማኝመሆን ለእግዚአብሔር ሰዎች በመታመን ይገለጣል፡፡ ይህም በትዳር፣ በሥራ፣ በተሰጠው ሃላፊነት መታመን አለበት፡፡

v  ምሳሌ ዮሴፍ ዘፍ.399 " በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሰራለሁ"

4.    ፍቅር

ክርስቲያናዊ ፍቅር የያዘ ሰው በሰውና በእግዚአብሔር ፍቅር ያለነቀፋ ይኖራል፡፡ ፍቅር የክርስቲያንነታችን መገለጫ ነው፡፡ አምላክን ከዙፋኑ ያወረደው ራሱንም እስከ ሞት አሳልፎ ለሰው ልጅ እንዲሰጥ ያደረገው ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ፍቅር ከሌለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የለውም ማለት ይቻላል፡፡የምናፈቅረው ማንን ነው? እግዚአብሔርን፡- እግዚአብሔርን ማፍቀር ሲባል እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ማፍቀር ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፍቅረ እግዚአብሔርን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

ትእዛዙን ማክበር

የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መውደድ

5.    ትእዛዙን ማክበር

እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን በመፈጸም ይገለጣል፡፡ ትእዛዙ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፡፡ ዮሐ.1421

የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መውደድ የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መውደድ የሚለውን በሦስት ከፍለን መመልከት እንችላለን።

  • *    ቅዱሳንን መውደድና ማክበር
  • *    ሀገርን መውደድ
  • *    ቤተሰብን መውደድ
  • *    የሰዉ ልጅን ሁሉ መዉደድ

5.1.        ቅዱሳንን መውደድና ማክበር፡-

ቅዱሳን እግዚአብሔር የመረጣቸው ያከበራቸውና የወደዳቸው ናቸው፡፡ የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗልና አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው የጠራቸው እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ያጸደቃቸው እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡ሮሜ.829 ፍቅረ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑ ቅዱሳንን በማክበር እንገልጻለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የትሕትናና የኦርቶዶክሳዊነት ውጤት ነው፡፡

5.2.        ሀገርን መውደድ፡-

ሀገር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሰጠው ሀገር ሆኖ እርሱን ሊያመሰግን ሀገሩን ሊወድ ግዴታ አለበት፡፡ ሀገር ከሌለ ሠላም ካልሆነ እግዚአብሔርን በደስታ ማመስገን አይቻልምና፡፡ ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድ፡፡ መዝ.1365

5.3.        ቤተሰብን መውደድ፡-

ክርስቲያን እምነትን፣ ምግባርን፣ ሥርዓትን በመጀመሪያ የሚማረው ከቤተሰቡ ነው፡፡ ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ነቢዩ ሙሴ የእግዚአብሔርን፣ የወገንን፣ የሀገርን ፍቅር የተማረው ከእናቱ ነውና፡፡ ወልደው፣ አሳድገው፣ አስተምረው ለትልቅ ደረጃ ያበቁትን ቤተሰቡን ክርስቲያን ሊወድ ይገባዋል፡፡ ስለ ቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢኖር ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው፡፡ 1ጢሞ.58

5.4.        የሰው ልጆችን ሁሉ መዉደድ፡-

/ፍቅረ ቢጽ/ የሰውን ልጅ ሁሉ መዉደድ ፍቅረ ቢጽ ይባላል፡፡ ይህም በሥላሴ አርአያ የተፈጠረውን ሰው ሁሉ መውደድና ማፍቀር ነው፡፡ ይህም ኀጥእ ጻድቅ፣ አማኒ መናፍቅ፣ ዘመድ ባዕድ ሳይሉና ሳይለዩ ሁሉን አስተካክሎ መውደድ ነው፡፡ ይህም ትእዛዝ ጠላትን እስከ መውደድ በመድረስ ነው፡፡ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፡፡ ማቴ.544

በአጠቃላይ ክርስቲያን ከአለባበሱ ጀምሮ ውጫዊ አቋሙም ሆነ አጠቃላይ ሕይወቱ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ክርስቲያንነቱን ሊገልጥለት ይገባዋል፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ኖረው ለሰውም ብርሃን ሆኖ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆኑትን አስደሰተ የሚባለው ያን ጊዜ ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያን በምድር ሲኖር በግል ሕይወቱም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮው ምን መምሰል እንዳለበት ራሱን ከላይ በተገለጸው በሦስቱ ሕግጋት አንጻር እየመረመረ መጓዝ አለበት፡፡ በግል ሕይወቱ ዘወትር ንስሓ እየገባ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል እየጾመ፣ እየጸለየ፣ እየመጸወተ ሰማያዊ መንግሥትን ተስፋ በማድረግ ይጓዛል፡፡  በማኅበራዊ ኑሮውም ደግሞ ሰዎችን በሐዘናቸው ጊዜ ማጽናናት፣ በደስታቸው ተካፋይ መሆን፣ ከቸገራቸው ለችግራቸው ደራሽ በመሆን እውነተኛ ፍቅሩን ሊገልጽ ያስፈልጋል፡፡የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡” 2ቆሮ.410

 ምንጭ፦ የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት

ሐሙስ 6 ማርች 2025

የጋብቻ እና ቤተሰባዊ ሕይወት #1

 የሰናፍጭ ቅንጣት |Part 1 የጋብቻ እና ቤተሰባዊ ሕይወት ትምህርት

የጋብቻ እና ቤተሰባዊ ሕይወት

በዚህ ክፍል የጋብቻን ትርጉም

የጋብቻን ዓላማ

በጋብቻ ዉስጥ ስላሉ እዉነታዎች

ዓለማዊ እና መንፈሳዊ ጋብቻ ልዩነታቸዉ ምንድን ነዉ 

 ... የሚሉትና ሌሎችም ይዳሰሱበታል፡፡

 


ማክሰኞ 3 ዲሴምበር 2024

ትቶ እና ችሎ

 ትቶ እና ችሎ

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ


በደረሰ ረታ

ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። በምክራቸውም ይሁን በሕይወታቸው ያስተማሩን ይህንን ነው። በዘመናቸው የመጡትን ፈተናዎች በመተው እና በመቻል ነበረ ያሳለፉት። የሚተወውም ሆነ የሚቻለው ነገር እንዲህ ቀላል ሆኖ አልነበረም። ሁሉን በሚችል/በሚያስችል በአምላካቸው ቸርነት ችለውት እንጂ። የአባታችን በረከታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን።
የቤተእምነት አባቶች እንደ የ ደረጃቸው ይህ አይነት አስተዋይነት በመሪነታቸው ወቅት ይጠበቅባቸዋል። መንጋውን ለመጠበቅም ይሁን ለአስተዳደራዊ ውሳኔ ሰጪነታቸው ይህን መንገድ መከተል ግድ ነው።
በመንግሥት ደረጃም ያሉ ባለስልጣናት (የክልልም ሆነ የፌዴራል) ሕዝባቸውን ሲያስተዳድሩ፣ ውሳኔ ሲሰጡ፣ ግጭቶችን ሲፈቱ፣ ይህ የሚጠበቅባቸው ጉዳይ ነው።
የተቋማት አስተዳዳሪዎች በየእርከናቸው ሰራተኞቻቸውን ሲመሩ እና ሲያስተዳድሩ፣ ውሳኔ ሲያሳልፉ እና ልዩነቶችን የመፍትሔ አቅጣጫ ሲጠቁሙ በማስተዋል ሊሆን እንደሚገባ አስተማሪ ተግባር የሚሻ ቃል ነው ትቶ እና ችሎ መኖር።
ሰው ከብቸኝነት ወጥቶ ሁለት እና ከዚያ በላይ ሆኖ ሲኖር፣ በትዳር ሲጣመር፣ የጋራ ዓላማ ካለው ወዘተ ሁሌም ሁሉም ወገን አንድ ነገር ያስባል፤ በአንድ ነገር ላይ በእኩል ያምናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
አብሮ ለመኖር፣ የጀመሩትን ለማስቀጠል፣ ልዩነቶችን ለማጥበብ፣ ግጭቶችን ለማስቀረት አማራጭ ከሌላቸው መፍትሔዎች አንዱ ትቶ እና ችሎ መኖር ነው።
ትቶ እና ችሎ ሲባል የምንተወው እና የምንችለው ነገር የማይጠቅም እና የሚቻል ሆኖ አይደለም። ነገር ግን ሁለቱም ከአብሮነት ስለማይበልጡ እንጂ። አንድም በማጣት ውስጥ ማግኘት ስላለ እንጂ። አንድም በዚህ የተነሳ የምናገኘው ከምናጣው ነገር ስለማይበልጥ እንጂ።
በዓለም ላይ መንግሥታት ሆኑ ሁለት ተደራዳሪዎች ችግሮችን የሚፈቱት ወደ አንድ የሚመጡት win win በሆነ መንገድ ነው። win win ሲባል ሁለቱም አሸናፊ በሚሆኑበት መንገድ ነው። አሸናፊነት ስንል ሁሌም ማግኘት ማጣት የሌለበት ማለታችን አይደለም። የተወሰነ ሰጥት የተወሰነውን ተቀብሎ፤ የሆነውን ነገር እየተወ የሆነለትን አስከብሮ መሄድ እንጂ።
ለምሳሌ በትዳር ውስጥ እውነቱን ከተነጋገርን አብዛኛውን ጊዜ ከምንግባባበት የማንግባባበት ይበልጣል። ምክንያቱ ግን ስለምንጠላላ አይደለም። ከሁለት ዓለም፣ ከሁለት ቤተሰብ የአስተዳደግ ሁኔታ ውስጥ፣ ከተለያየ ልማድ እና አስተሳሰብ ካለው ማኀበረሰብ ውስጥ፣ ከተለያየ አመለካከት እና አረዳድ ውስጥ ስለመጣን እንጂ።
በየተቋማቱ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ከሚመሯቸው እና ከሚያስተዳድሯቸው ጋር የሐሳብ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ልዩነትን በተለመደ ቋንቋ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይጠበቅባቸዋል። (በጠረጴዛ ዙሪያ ሲባል ጠረጴዛ ችግሩን ይፈታዋል ማለት ሳይሆን በአንድ ጉዳይ ላይ ወደ አንድ ነጥብ ላይ መስማማትን መግባባትን ለማመላከት ነው።) በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ መሰባሰብ ችግር መፍታት እንደማይችሉ ዓለም ላይ የተከናወኑ የጠረጴዛ ውይይቶች ማሳያ ናቸው።
በጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት የሚቀመጡ ወገኖች ሊሸነፉበት የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አምነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ይህንንም ሲያደርጉ ከበስተጀርባ የሚመሩትን ሕዝብ (ሰራተኛ ) ጥቅምና እና ጉዳት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል።
እንደዚህ አይነቱ ልዩነት ጤናማ ነው። ከሁለት የሚወጣ አንድ ጥሩ እና ጠንካራ ነገር ስለሚገኝ። ይኽ እስኪሆን ደግሞ የሚያለያየንን ጉዳይ በመተው እና በመቻል ማሳለፍ ይጠበቅብናል። እኔ ብቻ የበላይ ልሁን እኔ ብቻ ላሸንፍ የምንል ከሆነ በዚህም መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ከምናገኘው/ልናስከብር ወይም ልናስፈጽም ከምንችለው በላይ እናጣለን።
ስለዚህ ነገሮችን መቋጨት ያለብን በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆን አለበት። ይህ መርህ ሁለቱንም ወገን አሸናፊ ያደርጋል።
ካልሆነስ ነው?
አያድርግብንና ከሆነ ምላሹ የከፋ ነው። አንድነት ይከፈላል፣ ትዳር ይበተናል፣ ቤተሰብ ይፈርሳል፣ ልጆች ወላጅ (እናት/አባት) አልባ ይሆናሉ፣ ጠንካራ የነበረው የኑሮ ደረጃ ይናጋል፣ አገር ማህበረሰብ ዘመድ አዝማድ መሠረቱ ይናጋል።
በጥቂት የቃላት ጦርነት የተጀመረ አለመግባባት ነፍጥ አስመዝዞ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል። ጸብ ይፈጠራል። ሥራ ይበደላል። ኢኮኖሚው ይናጋል። የሰው አኗኗር ይበላሻል። ሕይወት ይቀጠፋል። ንብረት ይወድማል። አካል ይጎድላል። እንደዚህ ሲሆን ሊተመን የማይችል ኪሳራ ይደርሳል።
መሰል ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በጥልቅ አስተዋይነት እና በበሳል አመራርነት ነው። በሳል አመራርነት እኔ ይድላኝ፣ እኔ ያልኩት ይሁን፣ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ፣ ወዘተ ሳይሆን የሚለው በመሸነፍ ለማሸነፍ ከእኔ ይቅር በማለት እያወቀ ይተዋል። ይሸነፋልም።
በትዳር ውስጥ ለሚከሰቱ ልዩነቶች በጎ አስተዋጽኦ ያላቸው ሰዎች እንዳሉት ሁሉ ተግባራቸው ከሰይጣን የሚብሱ አሉ። በሰው ቁስል እንጨት እየቆሰቆሱ የራሳቸውን የሚኖሩ ነገር ግን በሌላው ላይ ከዳር ሆነው የሚፈርዱ አሉ። ልዩነቶቻቸውን በማስፋት፣ ግጭታቸውን በማጉላት እርባና ቢስ የሆነ ፍርድ የሚሰጡ አሉ።
አጀማመሩ ትንሺ የሚመስል አፀፋው ግን ከባድ የሆነ ችግር ይዞ ይመጣል። የስነልቦና ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ወዘተ ይዞ ይመጣል። ስለዚህ ሁሉም ሰው ከእንዲዚህ አይነት ክስተት ከሚመጣ ጉዳት ራሱን ለመታደግ አስቀድሞ የሥነልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ደግ አሳቢ መስለው የተለኮሰው ላይ ቤንዚን የሚረጩ እና የሚያቀጣጥሉትን በንቃት መከታተልና ሊከላከላቸው ይገባል።
እንዲህ አይነት ተግባራት በአገራችን እንኳን በፖለቲካው፣ በየ ቤተ እምነቱ፣ በትዳር ውስጥ፣ ወዘተ ክስተቶችን መታዘብ ከጀመርን ከረምረም ብለናል። አሁንም ለነዚህ ተግባራት የሚተውን ትቶ የሚቻለውን ችሎ በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር መፍታት የሰጥቶ መቀበልን መርህን መከተል ግድ ነው። ካልሆነ ውጤቱ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል።
ሁላችንንም እግዚአብሔር ይርዳን፤ ያጋጠሙንን ችግሮች የምንተውበትን እና የምንችልበትን ጸጋ ያድለን።
ይቆየን።

ሰኞ 29 ጁላይ 2024

ሊንኩን subscribe ታደርጉ ዘንድ …

 በመላዉ ዓለም ያላችሁ የዚህ ገጽ ተከታታዮች ተደራሽነቴን ለማስፋት ያግዘኝ ዘንድ በዩቲዩብ ልመጣ ስለሆነ በቅንነት subscribe እንድታደርጉ ሊንኩን አስቀምጫለሁ፡፡

https://www.youtube.com/channel/UCAr1hYmoE-E5Cu1p8Ba8B5g




ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

እንዴት ልጆችን በሁለንተናዊ መስክ እናሳድግ?

መግቢያ   ማሳደግ የወላጅ ሥራ/ሚና ነዉ፤  ወላጅ ማለት   የሥጋ ወላጅ (እናት እና አባት)    መንፈሳዊ ወላጅ (መምህረ ንሰሐ፣ መምህራነ ወንጌል፣ ልጆችን በእለተ ሰንበት የሚያስተምሩ)    የእዉቀት ወላጅ (በትምህ...