ማክሰኞ 18 ዲሴምበር 2012

ከድል ማግስት


        አያ ሆ÷÷ ማታ ነው ድሌ፣
          ድሌ ማታ ነው ድሌ
እያሉ መጨፈር ከዘመናት ጀምሮ ዛሬ ድረስ የድል አድራጎቶችን ጭፈራ ነው። ትዝ ይለኛል ልጅ ሳለሁ ክረምት ሲገባ ሰፈር በሚገኙት ትናንሽ ሜዳዎች ጭቃ በጭቃ በሆነች በካልሲ በተጠቀለለች ፌስታሎች ውስጧን በሞሏት የጨርቅ ኳስ ጭቃ መስለን  ጭቃ አክለን፣ ጭቃ በጭቃ በሆነ ሜዳ ተጫውተን አመሻሽ ላይ ድል ቀንቶን የተወራረድንበትን ቆርኪ በልተን ከሲጋራ ማሸጊያ የውስጠኛው ክፍል (አልሙንየም) የተሰራ ዋንጫ ተሸልመን ሰፈሩን «አያ ሆ ሆ ማታ ነው ድሌ ፣……» በሚለው ጭፈራ ስንቀውጠው ቡድናችንን ጮቤ ስናስረግጥ ተጋጣሚ ቡድናችንን አንገት ስናስደፋና ስናሸማቅቅ፣ የተሸነፍን ቀን ደግሞ በለስ የቀናቸው እንዲሁ በተራቸው ሲያሸማቅቁን ፣ ለሌላኛው ቀን ውድድር በድል ማግስት ባሉት ቀናት በዚያኔው የእግር ኳስ  ሜዳ ቋንቋ ኮንዲሽን(condition) እየተባለ የምናገኛትን ቅራሪ ከተገኘም ጠላ ከመጠጣት ታቅበን የቡድናችንን ድል ለማስጠበቅ ከተቻለም ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ ተመካክረን፣ ስፖርት ሰረተን፣ ተጨማሪ ስልጠና ከኛ ከፍ በሚሉ ወንደሞቻችን ወስደን ፣ከዚያች የጨርቅ ኳስ ሻል ያለ ኳስ ለመስራት አሮጌ አንድ እግር ካልሲ ቃል ተገብቶልን፣ ድጋሚ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ በልበ ሙሉነት እንገባ ነበር። በቃ የትናንት ነገር በሙሉ ነበር አይደል የሚባለው የታሪክ መኅደር ላይ ሰፍሮ ታሪክ እሰኪሆን የሚገርመው ነገር «ነበር» የሚለው ነገር በኛ ዘመን ብቻ ሳይሆን በኛም ሰፈር ይሁን ከኛ ሠፈር ወጭ አገርም እንበል ጥሎብን የጨወታ ነገር ሲነሳ እግር ኳስ አልተሳካልንም እንዲያውም አሁን በቅርቡ በተካሄደው ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችው ከ30 ዓመት በኃላ በመሆኑ ደስታችን የዓለም ዋንጫ የበላን መስሎብን ነበር፣ የዚህ ደስታ ምሥጢሩ ይህ ሁሉ ወጣት እንደ እኔ የልጅነት ጊዜ በሰፈር ጫወታ ከሲጋራ ወረቀት ከተሰራ ዋንጫ በቀር አንስቶ ስለማያውቅ ነው። ግዴለም አይሳካ የዋንጫ ነገር እድላችን ወይም ዕዳ ክፍላችን አይደለም ምናልባት ከኛ ሰፈር ቢቀር ከሌላ ሰፈር እርሱም ይቅር ከኛ አገር ቢጠፋ ከሌላ አገር ከአማራ ከኦሮሞው ከጉራጌው ከደቡብ ከትግሬው ከሰፈር አንዳንድ ሰው ያቺን የጨርቅ ኳስ ሲረግጥና ሲራገጥ ዋንጫ ሲያነሳ ሲጥል፣ ሲጨዋት ሲያጫወት፣ የመስመር የመሀል ዳኛ ሆኖ ሲዳኝ ካደገው ትውልድ ብዙ አይደለም ይኸንን 30 ዓመት ሙሉ አስራ አንደ ሰው ይጥፋ? ምናለ የሰው ልጅ መገኛ ከምንሆንና የቺው ሉሲም የኛ አገር ሰው ሆና ከምታስቅቀን፣ሄዳ ቀረች ብለን ከምታጨናንቀን የእግር ኳስ  አገር በሆንን። እንደው ዝም ብለን የአውሮፓና የእንግሊዝ፣ የአርሰናልና የማንችስተር ደጋፊ አገር እንሁን? ኧረ ምነዉ ፈጣሪስ ምነው ዝም አለን? ቸሩ መድኃኒአለም የነገሩህን የማትረሳ የለመኑንህ የማትነሳ ብዙ አይደለም እባክህ ለአፍሪካ ዋንጫ አስራ አንድ ሰው ሥጠንና ተጠባባቂ ይቆይ ግደለም ከዛም የአፍሪካን ዋንጫ በልተን ከድል ማግስት ስለትህን አንድ ባኮ ሻማ ለማምጣት አብቃን። ጎበዝ ስለትህን ይሰማህ በሉኝ። አሜን ይስማን።
          ወደ ባለፈው ድላችን ወደ «ጀግኖች» ልጆቻችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዝና፣ ከ30 ዓመት በኃላ እነ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ደምሴ ዳምጤ፣... ኧረ ስንቱ ደግሞ የናፈቁትን ድልና ደስታ ሳያዩት እኛ በስታድዮም ተገኝተን በቴሌቪዥን ተመልክተው ደስ እንዲለን ያደረጉት የጀግኖቹ ታሪክ አይረሴ ነው። አዳነ ግርማንና ሳልሃዲን ሰይድ እግዜር ይስጣቸው እነርሱ ባይፈጠሩ በዚያች የጨርቅ ኳስ ተጫውተው ባያድጉ ለዚህ ታላቅ ብሔራዊ ቡድን ባይታጩ ምን ይዉጠን ነበር? ኧረ የሆነው ሆነና የአፍሪካው ዋንጫ እንዴት ሆነ? ቀኑ ቀርቧል አሁንም የድል ማግስቱን ደስታ እንጂ ከድል በኋላ ያለውን የአፍሪካ ዋንጫን የተመለከተ ዝግጅትም ይሁን የወዳጅነት ጨዋታ የለም። እነ ናይጄሪያን የመሰሉ የኛ ተጋጣሚዎች ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትም የወዳጅነት ግጥሚያም አውሮፓ እንዲገቡ እስከ ዋንጫውም በዚያው ዝግጅት እንደሚያደርጉም ሚዲያዎቻችን ያለ መታመኑ ጠዋት ማታ እየዘገቡ ይገኛሉ የኛዎቹስ የት ነው ያሉት? እንደሚባለው (ወሬ አርጎ ያስቀረውና) እንደ ሴካፋው ዋንጫ እንደ ጨርቅ ኳስ እንኳን ከቅራሪና ጠላ መታቀብ አቅቷቸዋል የሚባለው እውነት ይሆን? ኮንዲሽን፣ትሬንግ፣ የወንድማማችነት ግጥሚያ ምናምን ቀረ እንዴ? እንደከዚህ በፊቱ ወር ሳምንታት ሲቀሩት ይሆን ብሔራዊ ቡዱኑ ተሰባስቦ ተለማምዶ ለድል የሚበቃው? ሰዎች ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራና ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብቻ ተሯርጦ አሰልጥኖ ባለሃብቶች ከአሸነፋችሁ ብለው ቃል ገብተው ሸልመዉና ጋብዘው ብቻ ታሪክ ይቀየር፣ ድል ይገኝ ይሆን? አይታየኝም።
          ለኢትዮጵያ ህዝብ 30 ዓመት ጠብቆ በ31ኛ ዓመቱ ለዋንጫ ማጣሪያ ማለፍ ብቻ በቂ ድል አይደለም፤ ደስታችን በዚህ መቆም የለበትም። ትልቅ የታሪክ የቤት ሥራ (የአፍሪካ ዋንጫን) አስቀምጠን መጠቶ ቤት ልንገኝ የተጣለብን ኃላፊነት አይፈቅድም ቆይ ምን ተገኘና ነው ስፖርተኛ መጠጥ ጠጪ፣ሰካራም የሚሆን እንዴትስ ሆኖ ነው የ80 ሚሊየን ህዝብ አደራ ተሸክሞ ሲጠጣ የሚመሸው እንዴትስ ነው መጠጥ ቤት የሚገባው? ለመሆኑ ጉሮሮአችን እንኳን አልኮል ሊንቆረቆርበትና ልንሰክር ይቅርና እንቅልፍ በዓይናችን ሊመጣ ሃይልና ብርታት ይኖረዋል? ወይንስ ይህ ድል ሆነና በቅቶን ነጋና ጮቤ እንረግጣለን? ሌላው ይቅር ደስታችንንም ይተውት የሆነው ሁሉ ሆኖ ምኑ ነው የመጠጥ ደስታው? እንዴት ልንመርጠው ቻልን? መስከሩን ነው? መንገዳገዱንና በሰው ፊት መቅለሉን ነው? ወድቆ መጎዳቱን አዕምሮን መቆጣጠር ተስኖን ከሰው ጋር መጋጨትና ማስቀየሙን  ነው ወይንስ ምኑን ወደድንለት?
          ፌዴሬሽኑስ ምን እያደረገ ነው? ሥለጠና አያስፈልግም? በጀት የለው ይሆን እንዴ? ማን ያውቃል? ወይ እንደ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችን የዜግነት ችግር ይኖርባቸው ይሆናል? (በሌላው ዘርፍ የሆነ ችግር ሲነሳ ሀሜት ከተማዋን ሲንጣት እንደዚህኮ የሆነው እገሌ የተባለ ሚኒስተር ወይም ዴኤታ በአባቱ ወይም በእናቱ ኤርትራዊ ስለሆነ ነው የሚባል የልማት እንቅፋት የሆነ ልማታዊ ቀልድ አለ፤) ታዲያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ራሱ የኢትዮጵያዊነት ችግር ይኖርበት ይሆን? መቸስ ያን ሰሞን ማነች ይህቺ ሱዳን ከምትባለው ጉረቤት አገር ልነጋጠም ያልን ሰሞን 31 ዓመት ከመጠበቃችን ይልቅ የዕሁድ ሠዓት እንደረዘመብን ባያውቁ ሳይሰሙ አይቀሩም፤ ለነርሱም ቢሆን በዘመናቸው የተሰራ የሚመዘገብ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ አልፈለጉ ይሆን? ማን ይህን ከድልማግስት እዚም ያደረገባቸው? ለነገሩ ድልና የድል ማግስት በኢትዮጵያ ችግር አለባቸው ሰሞኑን ሰፈራችን አንድ ነገር ሲገርመኝ ነበር የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ለማሰራት ገንዘብ ለማዋጣት ተስማምተን ማዋጣት ከአሥር ዓመት በላይ ይሆነዋል፣ ረጅም ጊዜ እንዲያውም በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች በቃ ገንዘባቸውን ይመለስልን እያሉ ሲማረሩ ከርመው አሁን መንገዱ ከተሰራ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል እንኳንስ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ መንገድ ብሩ ከመበላት አምልጦ መንገዱ ተሰርቶ ሲያልቅ ይቅርና ልጁ KG ጨርሶ አንደኛ ክፍል ሲገባ ይመረቃልና እኛም የአሥር ዓመት ተቀማጭ ገንዘባችን ለቁም ነገር ሲውል የማያገባቸው ግን በገቡበት ሰው አማካኝነት ሊመረቅ ሁለት ሁለት መቶ ብር ከአመት በፊት ተዋጣ ቀን ይመርቁት ሌሊት ሳናውቅ ተራዝሟልም ሳንባል ከረምን። እርም ብለን የተውነውን የመንገድ ምርቃት እንደ አዲስ ከቀበሌ መጥተው ከአንድ ጎረቤቴ ጋር ቆመን እየተጫወትን «መዋጮ» ማለት ሰውየዉ«የምን መዋጮ» ዓይናቸውን በጨው የታጠቡትም (የመንገድ ማስመረቂያ» ሰውየው ከረር በማለት (መክረር እኛ ሠፈር ብርቅ አይደለም ኑሮ ያለከረረው ማን አለና) «የትኘውን የቀለበት መንገድ እየፈረሰ ያለውን ከመስቀል አደባባይ ሳሪስ ያለው የሚፈርስ መንገድ የማስረሻ ምርቃት » በማለት በአሽሙር መልክ ጎሸም አደረጓት።
«አይ አይደለም የሰፈራችሁን»
«ከሁለት ዓመት በፊት የተሰራውን»
«አዎ » እያለች ስለተረዷት ፈገግ አለች።
«ታዲያ ለምን አዋጣለሁ»
«ለምርቃቱ ነዋ ሰሞኑን ባለሥልጣኖች መጥተው ይመርቁታል»
«ድጋሚ.» ብለው ከዓመት በፊት የከፈሉበትን ደረሰኝ ከኪሳቸው አውጥተው አሳዮዋት፤ ነገሩ ሥላልተሳካ
«ይቅርታ» ብላቸው ለመሄድ ስትል 
«ቆይ ነይ ወደዚህ፤ ለመሆኑ ማን ነው የሚመጣው»
እየሳቀች «እኔንጃ ማን እንደሚመጣ እንኳን አላውቅም»
«እኛንም ይፈሩናል እንዴ ማንነታቸውን ሳያሳውቁ ድግስ ደግሱና ድንኳን ጥላችሁ ጠብቁን የሚሉት? እኛኮ የልማት አጋሮቻቸውኮ ነን እነርሱ ያቅዳሉ እኛ አዋጥተን እንሰራለን ነው ወይስ እንደ ቻይና ማበደር ነበረብን? ለማንኛውም የሚመጣውን ባለሥልጣን አትመርቅ ርገመው አደራህን ረግመኸው ሂድ የመረቃችሁትን አንድም የረባ ነገር የለምና በይልኝ ጎሽ የኔ ልጅ ።»
          የቀበሌዋ የመዋጮ መልዕክተኛ እየሳቀች (እየፈራች ነበር የምትስቀው ነገሩ የሚያስቅ ሆኖባት ነው እንጂ) ወደ ቀጣዩ ቤት አመራች፤
          በዚህ ሰሞን የኛ ሰፈር የዉስጥ መንገድ ተመረቀ፣ ቶታል ጎጃም መውጫ ከውንጌት ጋር የሚገጥመው ቀለበት መንገድ ተመረቀ፣ ሰሜን መናፈሻ ጋር ቀበሌው ውስጥ የተሰራው ህነፃ ተመረቀ፣ ከሰሜን ሆቴል ዝቅ ብሎ ያለው 3ኛ እየታባለ የሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ተመረቀ ሌላም እኔ የማላውቅ ምርቃት በየሰፈሩ ክፍለ ከተማውና በየክልሉ ይኖራል ግድ የለም ይመረቅ እንኳንስ ተሰርቶ ያለቀ ነገር መመረቅ ይቅርና የማይሰራ ነገርስ መሰረት ድንጋይ ይጣልበት የለ፤ (እንዲያውም ነገርን ነገር ያነሳዋልና እኛ ሰፈር አንዴ የበሬ ግንባር የምታክል ሜዳ አለች አንዳንዴ ባለሃብቶች ህንፃ ሲገነቡ ሌሊት ሌሊት በድብቅ አፈር ይደፋባታል ጠዋት ጠዋት ወጣቶች ስፖርት ሲሰሩ ኳስ ሲጫወቱ አፈሩ እየደናቀፋቸው ይደፋበታል እሁድ እሁድ ደግሞ ኸየቦታው ጎረምሶች መጥተው በየቡድን በየቡድኑ ይራኮቱባታል። ከዚህ ሁሉ የሚገርመኝ ለምን እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ የመሰረት ድንገይ ተጥሎበታል ያኔ የመንገድ ምርቃቱ ቀን የሆነ  ነገር ጨርቅ ለብሶ ተሰቅሎ አየሁና ነገሩ እንዴት ነው ብዬ ወሬ ለመቃረም ጠጋ ብዬ የሰፈር ሰው ጠየኩ ምን እንደሆነ የሚያውቅ አጣሁ አሁንም ፈቅ አልኩና የሰፈር ሱቅ በር ላይ የቆሙ ምንድን ነው አልኳቸው እነርሱም በፊት የነበረውን በእመነ በረድ የተጻፈውን ማንሳታቸውን እንጂ አዲሱ ደሞ ምን እንደሆነ ምን እናውቃለን ያው እንደለመዱት ሊበሉበት ይሆናል በማለት ምሬት ሲጀምሩ ነገርና ምሬት እንደ ጦር ስለምፈራ የምወዳትን ወሬ ፍለጋ ተመልሼ ወደዚያው ወደተሰቀለው ተመለስኩ ይኼ ሁላ ለወሬ ምንድን ነው እንደዚህ መሆን? ትሉኝ ይሆናል ታዲያ እኔ ቃርሜ ካላመጣሁ ማን ያወራችኃል። ለማንኛውም ያቺ የተሰቀለችዋን ነገር ጨርቁን ንፋስ  ሲያወዛውዛት የሚገርም ትልቅ ፎቶ ግራፍ አየሁ ምን አትሉም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እስታዲዮም  ልብ በሉ እኛ ሰፈር ውስጥ እዚያች የበሬ ግንባር የምታክል ሜዳ ላይ፡ ተስፋ ቆረጥኩና ቦታውን በሊዝ ቢሸጡት ይሻላል እያልኩ እየተማረርኩ ጥዬው ሄድኩ እርሱም የመሰረት ድንጋይ ተጣለ አሉ አንድ ነገር ልበላችሁና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባና ቅንፉን እንዝጋው ዞሮዞሮ ከቤት አይደል የሚባለው ዛሬ ዛሬ ወደሰፈር ስመለስ ያ ተሰቅሎ ያየሁት የእስቲዲየም የጨርቅ ላይ ዕቅድ እንደ ጠዋት ጤዛ ጠፍቶ አገኘሁት ታዲያወገኔ እውነት ይህ እስቴዲየም ይሰራል ትሉኛላችሁ? አትጨነቁ ሆዴ ነግሮኛል አይሰራም።)
          መመረቁን ይመረቅ መሰረቱም ቢሰራም ባይሰራም ይጣል ግድየለም ባይሆን እመነ በረዱን ለሚያዘጋጁት ሊሾውን የሚሰሩት የስራ እድል ተፈጥሯልና ግን አንድ ጥያቄ አለኝ አንድ ቦታ ላይ ሁለት ሶስት የመሰረት ድንጋይ ከሚጥሉ ሌላ መጣያ ቦታ የለም ወይ? ከጠፋ ከጠፋ አዲስ አበባ ውስጥ ስንቱ ቤት የመሰረት ችግር አለበት አይደል እንዴ እርሱን ለምን አያጠብቁበትም። (ኢትዮጵያዊ ምክሬ ነው ተግሳፅ አይደለም) ወይስ ግራውንድ ፕላስ የሚሰራ ልማት ይኖረዋል እንደኮንደምንዬም? ጥያቄ ቁጥር ሁለት እኔ አልኩት አላልኩት የምርቃቱ ሥነ -ሥርዓት አይደነቀፍም እንዲያው ለነገሩ አንድ ሥራ ሥንሰራ እንዳልተንከረፈፍንና የሰው ጨጓራ እንዳልመለጥን ለምርቃ እነዲህ ማጣደፍ ምን የሚሉት ነው? አንድም ደግሞ ትንሽ ነገር በሰራን ማግስት የምርቃቱ ሽርጉድ ሳያንስ የመዲናውን ኔትወርክ ስለርሱ በማውራት ማጨናነቅ ምን የሚሉት ነው? ያካበደን አልመሰለንም? ወይስ ከዚህ በኋላ የምንሰራው ነገር የለም? ይህ  እንዴት የአንድን ታላቅ መሪ ራዕይ ማሳካት የምርቃት የፌሽታ የደስታ ጋጋታ ነው እንዲህ ነው ፈለግ መከተል? ቆይ እኛ ኢትዮጵያን ከድል ማግስት ለሌላ ድል ከመዘጋጀት ይልቅ ያቺኑ ድል ይዘን አርባና ሰማንያዋን እያወጣን ጮቤ የምንረግጠው ለምንድን ነው? እስከመቼሰ ይቀጥላል?
          አንድ ነገር ስጠረጥር ድሮ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለን የመጀመሪያውን ፈተና እንደምንም አሥር ከአስር አለበለዚያም ዘጠኝ ወይንም ስምንት ካመጣን እርሷን ለቤተሰብ እናሳያለን ጉራችን መከራ ነው ቤተሰብም ልጄ ጎበዝ ነው አስር ከአስር አመጣ ብሎ ሰፈር ውስጥ ለቅሶና ድገስ ላይ ሳይቀር ያወራል። ከረሜላ ወይም የሆነ ነገር እንሸለማለን አባትም እርሱን አትናገሩብኝ እናትም ከሌሎች ልጆቿ ለይታ ለዚያ ልጅ ምርጥ ምርጡን ስትል ልጅየው ድጋሚ አስር ለማምጣት አይጥር፣ ፈተናም እንዳለበት የሚናገረው ተው አጥና ብሎ የሚመክረው የለም እንዲያውም የተቆጣውን ሰዉ ተመልሰን በቁጣ እናስደነግጠዋለን የምንባንነው ወላጅ አምጣ የተባለ ቀን አለበለዚያም ሰኔ 30 መጥቶ የልጆች ውጤት ተሰጥቶ መውደቁን የሰማን ቀን ምን ማድረግ እንዳለበት ከቤት አልፎ አክስትና አጎት ጉረቤት ድረስ መነጋገሪያ ይሆናል ይህንንም የታደለው ነው ባኖ ወደ መፍትሄና ጥፋትን ወደማረም የሚመጣው የባሰበት በመምህራንና በትምህርት ቤት ያመካኛል፣እኔ ልጄን አውቀዋለሁ እያሉ ከአስር አስር የመጣበትን ውጤት አንጠልጥለው ይጮሃሉ ከዘጠና ግን ሥንት እንዳመጣ በጭራሽ አያውቁም ያጥና አያጥና አያውቁም፣ክፍል ገብቶ ይማር አይማር የቤት ሥራ ይስራ አይስራ አያውቁም፡ ሌላው ቀርቶ ያንን አስር ከአስር እንኳን እንደመጣ አያውቁም የእግር ኳሱም ይሁን የልማቱ ጉዳይ ብዙም አይለይም አንድ ናቸው። ለመሆኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ማለፋችንን እንጂ እንዴት እንዳለፍን በጠቅላላ ካስገባነው ይልቅ የገባብን ጠቅላላ ግብ ስንት እንደሆነ ሁሉንም ትተን ከሱዳን ጋር በተጫወትን ምሽት የመጨረሻዋ ፊሽካ ስትነፋ የገባችሁ ግብ ተቆጥራ ቢሆን ኖሮ ድል አልነበረም ልማታችንን ስናስበው የክሊኒኩ መገንበታ እንጂ ሲገነባ ስንት እንደፈጀ ፣ መንገዱ ሲዘረጋ መንገዱ ማለቁን እንጂ ስንት ዓመት እንደፈጀ ብናስብ እንኳንስ ጮቤ ልንረግጥና ልንፈነጥዝ ይቅርና ባለሥልጣኑ በቦታው ቆሞ  ባልመረቀ ስለዛ መንገድም ደግሞ አንስተው በሚዲያ ባላወሩት ነበር። ነገር ግን እንደትልቅ ድል ሌላውን ልማት አቁመን በዚህ ድል መጨፈርን ሞያ አድርገናል።
          ከዚህ ቀደም ካለው ስህተታችን ተምረን ለነገ ተግተን የምንሰራ ቢሆን ኖሮ በደርግ ዘመን(በ1977 ዓ.ም) የነበረውን ድርቅ ተመልከተን በኢህአዴግም ደርቅ ተምሶ ባልመጣ ነበር፤ በአንዱ ክልል ያስቸገረ አገር የፈታ የወባ ወረርሽኝ እዚያው  እንዳለ በቅጡ ተረባርበን እንደሚሆን አድርገነው ቢሆን ዛሬ በአራቱም ማዕዘን ፋታ አይነሳንም ነበር። ድሮ በአባቶቻችን ዘመን ጣሊያንን በጨበጣ ድል ማድረጋችንን መታሰቢያ ባናደርግና ተምረንበት ቢሆን ከአርባ ዓመት በኃላ ተመልሳ ጣሊያን ባለደፈረችን፣ በደርግም ከሱማሌ ጋር የነበረው ችግር ከትናንት መማር ቢኖርበት እስከ ኢህአዴግ ዘመን ባልዘለቀ ነበር፣ አሁንም በዘመነ ኢህአዴግ ከኤርትራ ጋር በባድመ ምክንያት ያ ሁሉ ደም የፈሰሰው ያ ሁሉ ወጣት የተሰዋው ያ ሁሉ የአገር ሃብትና ንብረት ጊዜን ጨምሮ በከንቱ የወደመው ኢህአዴግ ከደርግ ውደቀት በኋላ መማር ተስኖት በድል ማግስት ባሳየው ደካማ ጎን ምክንያት ነው።
          ለኢትዮጵያ ህዝብ ለኢትዮጵያ ወጣት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ የነማንችስተር (ዩናይትድና ሲቲ) የአርሰናልና የባርሴሎና፣ የቼልሲና የሊቨርፑል...ድልና ዋንጫ ምናችን ነው? የደቡብ አፍሪካ የኢፓርታይድ ነጻነት ፣ የአሜሪካ ሰላማዊና ዲሞክራሲያው ምርጫ፣ የቻይናና የኮርያ ፈጣን እድገት... ምናችን ነው? እኛን የራበን፣ እኛን ያመመን፣ እኛን ያናፈቀን የራሳችን የአገራችን የህዝባችን የወገናችን የሆነ ልማት፣ ዲሞክራሲ፣ፈጣን ዕድገት ሰላማዊ ምርጫ፣ ዘለቄታ ያለው ድል (ተከታታይነት ያለው) ሰላም ነዉ።የሃይማኖት ነፃነት፡ የፖለቲካ እኩልነት…..ወዘተ ናቸዉ፡፡ከድል ማግሰት ሌላም ዉድድር እንዳለብን ከመዘንጋት ይሰዉረን፡፡

ለቀጣይ ትውልድ ምን እናውርስ?


          አንድ ትውልድ ለመፍጠር ቢያንስ ሃያ እና ሰላሳ ዓመት ያስፈልገዋል። ዓብይ ርዕሳችን ምንም እንኳን ሥለትውልድ ቢያወሳ ርዕሰ ጉዳያችን ግን በጥቂት ሶስት ነገረ ልብ ልንል ግድ ይላል።  ቀጣዩ ማለት ማን ነው? የትኛውስ  ትውልድ ነው? ቀጣዩ ትውልድ የምንለው ጊዜስ በራሱ ከመቼ ይጀምራል? የሚሉት ጥቂቶች ናቸው። ለምን ይህንን ጉዳይ እንዳነሳ ያስገደደኝን ነገር ማካፈሉ ጥቂት ሥለተነሳሁበት ነገር ማብራሪያ የሚሰጥ ይመስለኛል። ጊዜው ምሽት 3፡15 ሠዓት ነው የሰዉ ልጅ ወደቤት ለሚሰባሰብበት ተጠናቆ የሚገባበት ሰዓት ነው (በጊዜ ወደ ቤታቸዉ የሚገቡትን አይመለከትም፤ ችግር፣የማያስገባቸውንም የመጠለያ ችግር አጋጥቸው መኖሪያቸውን ጎዳና ያደረጉትንም አያከትትም።) ይህንና የሚገቡትን ይዘን የማይገቡትን ትተን ጎዞ በታክሲ ወደ ቤት፡፡ የአብዛኞቻችንን መጓጓዣ የሆነውን ታክሲ ወይም ሌሎች የትራንሰፖርት አገልግሎት መስጫዎችን ተጠቅሞ መሄድ ግድ ይላል፡፡ ጎዞዉ ሊጀመር  ሰው መላት ግድ ይላል ታክሲዉ  ከያዛቸው ሰዎች መካከል በአንድ መቀመጫ ላይ የተቀመጥነው አራት ነበርን ሶስት ትናንሽ ልጆች በግምት እድሚያቸው አምስት፤ ስድስት እና ዘጠኝ አመት ናቸው። ከሥራ ነበር የሚመለሱት መቼስ በጠፋ ስራ እለት እለት የስራ አጥ ቁጥር በሚጨምረበትና ኮብልስቶን ለማንጠፍ ለዪኒቨርስቲ ተማራቂዎች ሞያ በጠየቀበት አዲስ አበባ እደሜያቸው ከአስር አመት በታች በሆኑ ህፃናት ከስራ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኃላ ወደ ቤት መግባት አጃኢብ የሚያስብል ጉዳይ ነው። ነገሩ ወዲህ ነው የዘጠኝ አመቱ ልጅ የመጣው ከጎጃም ነው አመት ከመንፈቅ ሆኖታል አዲስ አበባን ሀገሩ ካደረገ ወላጆቹ ይህን አለም መሰናበታቸውን እንጂ መቼ እንዳረፉ ጊዜውን በውል አያውቀውም ድሮ ነው የሞቱት ይላል የወላጆቹ በሕይወት አለመኖር ሲገልፅ ሁለቱ ጨቅላ  ህፃናት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ የአክስትና የአጎት ልጆች ናቸው እንደሱ አገላለፅ በእነሱ ትከሻ ላይ ነው ያለሁትም ብሎኛል፡ በአክስቱና በአጎቱ ላይ ሁለቱ ህፃናት ግራና ቀኝ ጉልበቱ ላይ ተኝተዋል፡፡ እሱ በሚያንቀላፋበት ሰዓት እሱ ተሽሎ የሁለት ህፃናትን እንቅልፍ በእቅፉ ለማስተናገድ ሕይወት አስገድደዋለች።
          ላወራቸው የምፈልገው ጉዳይ ስለነበረ ቀሰቀስኳቸው
ከየት ነው የምትመጡት?
ከሥራ፤
የምን ሥራ?
ማስቲካ ስንሸጥ ቆይተን
ለምን ትሸጣላችሁ? (አይባልም ግን ጥያቄ ማንሳቴ ካልቀረ ብዬ ቀጠልኩ እንጂ) ተቀባብለው በሚያሳዝን ሁኔታ መለሱልኝ ያሉኝን አልነግራችሁም ሁሉም ቤት አለና።
ስንት ሸጣችሁ?
ለሶስት ሰላሳ ብር ( ልብ በሉ ጠቅላላ ገቢያቸው ሰላሳ ብር ነው ዋናው ስንት እንደሆነ ትርፉ ስንት እንደሆነ ሂሳቡን ምቱልኝ እነዚህ ልጆች ስንት ሰዓት ነው የወጡት? ምን በልተው ዋሉ? እራታቸውንስ ምን ይበሉ ይሆን?... እግዚአብሔር ይወቀው።)
ስንተኛ ክፍል ነህ? (ለትልቁ ልጅ ያቀረብኩለት ጥያቄ ነው)
አራተኛ ክፍል
ጎጃም እያለህ ትማር ነበር ?
አልማርም ወላጆቼ ከሞቱ ቆይተዋል ብዬህ የለ?
ታዲያ እንዴት አራተኛ ክፍል ገባህ?
አምና (2004 ዓ.ም) አንደኛ ስገባ የትምህርት ሁኔታዬን አይተው አሳለፉኝ አሁንም ጎበዝ መሆኔን ሲያዩ ሶስተኛ ክፍል ገባሁ መጨረሻ ላይ ግን የሚቀጥለው አራተኛ ትገባለህ አሉኝ አሁን (በ2005 መሆኑ ነው) አራተኛ ክፍል እየተማርኩ ነበር ።
          ታጠናለህ ወይ እንዴት ጎበዝ ልትሆን ቻልክ?
(ለኔ ጥያቄ ነበር የእኔንና የእሱን ጥያቄ ከፊሉ ሰው እያዳመጠ ነው።)
          አጠናለሁ አሁን ስገባ እነሱ ይተኛሉ (የተኙትን ሁለት ህፃናት እያመለከተ) እኔ ወደ ጥናት ነው የምሄደው( እዚህ ጋር የራት ነገር አልተነሳም እራት ይበላ ይሆን ካልበላ በምን አቅሙ ያጠናል ጥናት እንደሆነ በልቶም አልሆነም «ጎበዝ» ብዬ ነበር ማለፍ የምችለው ከዚህ ወዲያ አቅሙ የለኝምና)
          አዲስ አበባ እንዴት ልትመጣ ቻልክ?
ጠፍቼ አጎቴን ተከትዬ ነው የመጣሁት
          ለምን ? እንዴት?
(ታሪኩ ብዙ ነው የነገረ ለፅሁፍ እንዲመች ግን ላሳጥረው)
ከእነሱ ጋር ለመኖር ሰው የለውምና አንድም የሚያበላው አንድም የሚያስተምረው ከሀገሩ ተሰደደ በምሽት አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከኑሮ ጋር ትግልን ማስቲካ በመሸጥ ተያያዘው።
          ኑሮ ኖርክ ተብሎ የእለት ጉርሱን የአመት ልብሱን መሸፈኛ ሊያመጣ ነጋዴ ሆነ፤ መምጣት ሳያሻው ህይወት ወደዚህ ምድር ጠርታዉ ፍዳውን ሊያል፤ እንደ ሰው ተፈጥሮ እንደ ሰው ሳይከበር ሊኖር ትንቅንቅ ተያይዞታል ፍጥጫውን ቀጥሏል እድሜህ ስንት ነው? የሚለው ጥያቄ እንኳን በቂ ምላሽ አልነበረውም እኔንጃ አላውቀውም ከማለት ውጭ።
          አለም ለህጻናት መብት ይከበር፣ ጉልበታቸው አይበዝበዝ፣ ግፍ አይዋልባቸው፣እነሱ ለመኖር፣ለመብላት፣ለመማር መብት...ወዘተ አላቸው፣ በሚባልበት 21ኛው ክ/ዘመን በሺህ የሚቆጠሩ ህፃናት ግን ጉልበታቸው ያለአግባብ እየተበዘበዘ፣ የመማር፣የመብላትና የመጠጣት መብታቸዉ እየተነፈገ፣በበሽታ እየተጠቁ፣ ለስደት እየተዳረጉ፣... ይገኛሉ።
          ይህንን አስከፊ ጉዳይ በምን እንቀይረው? እንዴትስ እንቀይረው? ቀጣዩን ትውልድ ምን እናወርሰው? ...
          ይህ ትውልድ ወደድንም ጠላንም ተፈጥሯል ህይወቱን ልናስቀጥለው ግድ ይላል፤ ከጨቅላዎች ህፃናት እስከ ወጣቱ ትውልድ ድረስ ያሉት የነገውን አለም ተሳታፊና ተረካቢዎች ናቸው። ታዲያ ይህ ትውልድ መጪው የዚች አለም ዕጣ ፋንታ በእጅ ያለ ከሆነ ዓለሙን የሚያስቀጥለው እሱ ከሆነ አንድም የትኛውን ዓለም እናውርሰው? በሌላ በኩልም እራሱ ትውልድስ ከእኛ የሚወርሰው ያዘጋጀንለት ምን ነገር አለ? ረሃብ፣ጦርነት፣ድርቅ፣ስደት፣የጎዳና ላይ ኑሮ፣ልመና፣ለጉልበት ብዝበዛ፣ወይም የተሻለች ብሩህና፡ ልምላሜ፡ እድገትና ብልፅግና የሞላባት ዓለም???
          ለእነዚህ ሶስት ህፃናት ከአንድ ቤት ጉልበታቸው መበዝበዝ፣በምሽት ጎዳና ላይ ማስቲካ መሸጥ፣ ሲደክሙ አምሽተው 30 ብር ብቻ ይዘው መምጣት፣ሳይበሉ መዋልና ማደር፣ወዘተ ምንን ያመለክታል? ፍትህ መኖሩን? የህፃናት መብት መከበሩን? ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ ፍሰት መኖሩ ወይስ ደሃና ረሃብተኛ አገር መሆኗን በሁለት ዲጂት አኮኖሚያችን ማደጉስ? ለእነዚህ ህፃናት ትርጉሙ ምንድነው? ለተከታያይ አመታት አኮኖሚያችን ማደጉ ለቀጣዩ ትውልድ ለምግብ ፍላጎት ካላሟላ ማደግ ቢቀርስ? ማደግ ማለት ለህንፃ መገተር ይሆን? ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው «ማከራየት ጀምረናል» የሚል ፅሁፍ የተለጠፈበት ህንፃ ነው?
          ይዘው የመጡት 30 ብር ዋናውን ጨምሮ የቤተሰብ እራት ያበላቸዋል ወይስ የኑሮ ሥጋት ይጨምራባቸዋል? ይህ 30 ብር የዚህን ቤት ህይወት ይታደግ ይሆን? ይሕ ህፃን ለትምህርት ብሎ የተሰደደውን ስደት ድካም ዋጋ ይከፍለው ይሆን? እንደእኔ እይታ ከዚህ ባሻገር አንድ ነገር ተመለከትኩ ምን? አትሉኝም ከንቱ ልፋት እንጂ ተመጣጣኝ ክፍያ እንደማይከፈለን ማነው በስራው መጠን ኢትዮጵያ ምድር ላይ የተከፈለው ከሌባ ከሙሰኛ እና ከአጭበርባሪ በቀር ለምንድን ነው ለመንግስት ሰራተኛ በስራው እርካታ የሌለው ለምንድነው ዛሬ ዛሬ የቤት ሰራተኛ ማግኘት አዲስ አበባ ላይ ችግር የሆነውና ወጣት ሴቶች ከገጠርና ከከተማ ወደ አረብ አገር የሚፈልሱት? ሰው ከመስሪያ ቤት  መስሪያቤት ለምን ይፈልሳል? ክፍያ ስለማይከፈለው ነው? ይህንኑ ነው እነዚህ ሶስት ነፍስ ያላወቁ ህፃናት ላይ ያየነው  ጉልህ ነገር። እንዲያውም በአንድ ሰሞን ዐብይ መወያያ የነበረው የአየር መንገዳችን ፈጣን እድገት የመጣው በስራ ብቻ ሳይሆን ለሰራተኞቹ  የድካማቸውን ያህል ተመጣጣኝ ክፍያ ባለመክፈሉና ጉልበታቸውን በመበዝበዙ ነው የሚል ተቃዉሞ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር። እውን አየር መንገድ ብቻ ነው? የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ወዘተ...ውስጣቸው ቢፈተሽ የሰራተኞቻቸው ብሶት ቢፈተሽ ደሞዝ አይከፈለንም ነው ጥያቄው ባንኮቸስ ብንል ኧረ ስንቱን ሆድ ይፍጀው። በኢትዮጵያ ጉልበት ብዝበዛ፣ በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሥራ አጥ፣ ረሃብ፣በሽታ፣ስደት፣...
          የሆነዉ ሆነ ቀጣዩን ትውልድ ምን እናውርስ? እርስ በርስ የተከፋፈለች አገር? በሽታና ጦርነት ያደቀቃት አገር ? መቼስ የቀጣዩ ትውልድ ልመናን አናወርስም ቃል ገብተናልና ልማትን እንደምናወርሳቸው እርግጠኞች ነን እኔ ፍርሃት አለብኝ እኛ ነገ እንደክማለን፣እናረጃለን እናልፋለን፣ ... ይህ ትውልድ ግን ያለኃጢአቱ ወላጁን በወባ፣በካንሰር፣በቲቢ፣በHIV ኤድስ ወዘተ ከማጣቱ ወላጅ አልባ ከመሆኑ ባሻገር የበሽታው ተጋላጭ የሆነው ጥቂት አይደለም እድሜ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የቀረቱንስ ማን ሰብስቦ ያሳድጋቸው? ማን ነገን ያውርሳቸው? ማን የነገ ተተኪና ወራሽ እንዲሆኑያስችላቸዉ? ማን ዛሬን ብርታት ይሁናቸው? ሳይሰደዱ ባህር ማዶ ሳይናፍቁ አገሬን ብለው እዚች ወንዝ ዳር አስቀምጣ ለምታስጠማ፣ ለም መሬት ላይ አስቀምጣ ለምታስርብ ኢተዮጵያን አልምተው በልተው  ጠግበው ጠጥተው እረክተው እንዲኖሩባት ከመንገድና ከህንፃ ባሻገር የተለየ ልማት ማን ያሳያቸው? ቀጣዩ ትውልድ እንደባለፈው ተስፋ ሳይሆን ምልክት ተጨባጭ ነገርን ይሻልና። ንጉሱም ደርግም ተስፋ በተስፋ ሲያደርጉን አልፈዋል ከኢህአዲዴግም ተስፋ ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ የሚዳስስ ይፈልጋል፡እንፈልጋለን፡፡ በዘጠኝ በአስር በአስር አንድ በመቶ ኢኮኖሚ የማደጉ ዜና ሳይሆን በቀን ሶስቴ መብላትን በምግብና በመጠጥ እራስን መቻል ትውልዱ ይሻል። እንፈጽማለን፡እናስፈፅማለን፡ እናስቀጥላለን የሚሉ ተስፋዎች ሳይሆን የተፈጸመና የሚቀጥል ነገር ሊወርስ ይገባዋል ይህ መጪ ትውልድ።
          እርግጥ ነው መንገዱ ተገንብቷል ህንፃዎች ተሰርል ትምህርት ቤቶች፣ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ታንፀዋል ነገር ግን ቀጣዩን ትውልድ ለመንገድ ርዝማኔ ሳይሆን የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍለት ይሻል፤ ህንፃዎች መገንባት ብቻ ሳይሆን ለመጠለያ ችግር መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እንዲዳረስ ይፈለጋል። እንዲሁ የተገነቡት ትምርህት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርት የተስተካከለ የትምህርት መርሃ ግብር እንዲሰጠው በጉጉት ይጠባበቃል ሆስፓተሎቹም ሆኑ ኪሊኒኮቹ በቂ አገልግሎት ለሁሉም ከተሟላ መሳሪያና ባለሙያ ከተገቢው መድሃኒት ጋርና በመልካም አስተዳደር የመጠበቅ ጉዳይ ነው አለበዚያ ለህንጻ መገተር ጤና አይሆንም ከምንም በላይ ከመሰረታዊ ነገሮች አንዱ ንጹ ውኃ  ያለው አካባቢ ልናወርሰው ይገባናል ውሃ ለማግኘት ወረፋ፣ ዳቦ ለመግዛት ወረፋ፣ ለትራንስፖርት ይዘን ለመሄድ ሰልፍ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊዘልቅ አይገባም ለሁሉም ሰው መልእክት ነው።
          ለቀጣዩ ትውልድ ልናወርሰው ከሚገባቸው አንገብጋቢ ጉዳይ ውስጥ እንደ ዳቦና ውኃ በሰልፍ ብዛትና በወረፋ የሚገኘውን የፍትህ ጉዳይ መንግሥት አትኩሮት ሊሠጠው ይገባል። ወላጆች በህገ መንግሥቱ መሰረት በ24 ሠዓት ውስጥ የፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት አለበት ከሚለው አንስቶ ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ ፍርድ ሊያገኙ ይገባል የሚለውን በማጣት ከየመንገዱ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እየታፈሱ በመግባት በ24 ሠዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ባለመቅረብ፣ በማስረጃ እጦት እና ባልተስተካከለ የፍትሀ ሂደት በማረሚያ ቤት በመጉላላት ለሶስትና አራት አመታት በእስር በመንገላታት አልፎ ተርፎ በጤና መታወክ ሳይፈረድላቸውና ሳይፈረድባቸው እዛው የሞቱበት ፡ይህንን የተሳብረ የፍርድ ሂደት ይዘው መቀጠል አይፈልግም። ቀልጣፋና ለህገ መንግስቱ የታመነ፡ ለህብረተሰቡ ዘብ የቆመ፡ የፍትህ አካል ሊኖረው ግዴታ አለብን።
          ዓለማችን አይደለም ለህፃናት ለአዋቂ አመቺ ወደአለመሆኑ እየመጣች ባለበት በዚህ ወቅት የሙቀት መጠኗ፣የአየር መበከልን የሚያመጣውን ችግር ልንቀንስ በኑሮ የተመቻቸ  ዓለምን ልናወርሳቸው ግድ ይለናል።
          ከምንም በላይ የዓለም ህዝብ ከሰባት ቢለ.ዮን በላይ በሆነበት በዚህ ዘመን የቤተሰባችንን ቁጥር በአጋጣሚ ሳይሆን በእቅድ ልንወስን ይገባናል። መግበናቸው የምናሳድግበትን፣ አስተምረን የምናንፅበትን፣ወልደን አሳድገን የምናኖርበትን ምቹ ስፍራ ወዘተ አስቀድመን ልናቅድና ልናዘጋጅላቸው ይገባል። በዕድላቸው ይደጉ፣ሲወለዱ የእነሱ የሚሆነው ይዘው ይመጣሉ የሚለውን አጉል ፈሊጥ... በጥሞና ልናጤነውና ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳቸውን ነገር ልናስብ ይገባል። ለቀጣዩ ትውልድ የሚታይ የቆመ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ብቻ በቂ አይደለም። ጤናማ ህይወት ያስፈልጋቸዋል፣ በመልካም ስነ -ምግባር ላይ የተመሰረተና አርአያ ሆኖ ሊያሳድጋቸውና ከፊለፊታቸው ያለውን ብሩህ ዓለም የሚያሳያቸው ቀዳሚ ትውልድ ይፈልጋሉ።
          የእነዚህ ሶስት ህፃናት አጭር ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው ይህ ታሪካችንን ለመቀየር ታጥቀን እንነሳ የበለፀገች፡ ለምለም ኢትዮጵያን፡ በረሃብ ሳይሆን በስልጣኔዋ በስነ ምግባሯ የታወቀች ኢትዮጵያን እንፍጠር። ይህቺ በሀይማኖቶች የከበረች፡ በብሔር ብሔረሰቦች ያጌጠች በመከባበርና በመቻቻል የተመሰረተች ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ፍትህ ልማት ብልፅግና ሰላምና ጤና ሰፍኖባት እናዳማረባት ለቀጣዩ ትውልድ እናውርሳቸው።ከምንም በላይ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ነፃነት ለቀጣዩ ትዉልድ ያስፈልገዋልና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በጥንቃቄ ሊወገድ ይገባል፡ ምክንያቱም በሃይማኖትና በፖለቲካ ነፃነት ትዉልድ አገርን ለመረከብ ብቁ ይሆናልና፡፡ቸር ይቆየንለቀጣዩ ትዉልድ ልማትን፡ መከባበርን፡የሃይማኖት ነፃነትን፡የፖለቲካ እኩልነትን፡ የኢኮኖሚ በእኩል መከፋፈልን … እናዉርሳቸዉ፡፡

ዓርብ 14 ዲሴምበር 2012

ኑሮ በአሜሪካ


ኑሮ በአሜሪካ
        «ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ» ይባላል ድሮ ድሮ በተረት አባቶች፡ ነገሩ ከተረትነት ወደ እውነትነት ተቀየረና አንድ ለእኛ አገር ለእውነትም የሚከብድ ለተራትነትም የማይመጥን ወሬ ቅዥት ያርገውና ከወደ አሜሪካ ነው የመጣው ተብሎ ሲወራ ጆሮዬን ጣል አድርጌ ማዳመጥ፡- «ልጅየው ከሞትና ከአሜሪካ አይቀርም ከተባለባት ምድረ አሜሪካ ሰሞኑን ሥሰማ አፍሪካዊ ስለገዛት ነው መሰለኝ ገነትም ማለት ጀምረዋል መቸስ አሉ ነው እኔ አልሰማሁም፡ ገነትም ስትሆን አላየሁም፤ ብቻ ይህ ሰው ከሄደ ዓመታት ተቆጥረዋል። ያው! እንደሚባለው የአሜሪካ  ሰው ከሄደ ዓመታት ተቆጥረዋል። ያው! እንደሚባለው የአሜሪካ ሰው ምንም አይመቸውም ጊዜም የለውም ፀበል ፀዲቅ፣ክርስትና፣ ልደት፣ለቅሶ፣40 እና 80 የሚባል ነገር እንደተለመደው መድረስ እንኳን ሊደረግ አይታሰብም። አገር ቤትም መጥቶ ቤተሰብ ለመጠየቅ የሚያደርሰው ለዚያውም እግዚአብሔር ፈቅዶ ሳይሆን የአሜሪካ መንግስትና ኑሮ ከፈቀዱ እግዜርም ለዓይነ ሥጋ ተገናኙ ሲላቸው ወላጅን ሳይሆን የልጅ ልጅን ያገናኛቸዋል። ይህ የተባለው ሰው ግን ብልጥ ነበርና ዘዴ ዘይዶ አባቱን እዚያው ከወደ አሜሪካ ይወስዳቸውና በዓይነ ሥጋ ለመገናኘት ይበቃሉ። ሰውና እንጨት ተሰባሪ ናቸውና ሰውየው ቀናቸው ደርሶ ወይም በሽታቸው ፀንቶ አሊያም አሜሪካ የምትባል አገር አልመች ብላቸው ብቻ የሆነውን እንጀላቸው ሞቱ፤ ... ልጅ እርሙን አወጣ፣ ጉረቤትም ደረሱ ጓደኞችም ግማሹ e-mail ልከውለት፣ አንዳንዶቹም ሥልክ ደወለው ለቅሶ ደረሱ አራት ነጥብ በቃ ለቅሶ አለቀ ቀብር ቀረ፤ ልጅ ሆዬ አባቱን እንዴት መቅበር እንዳለበት ለጥቂት ዳቂቆች አሰብ ካደረገ በኃላ ለቀብር ተዘጋጀ እንዳአሜሪካ በዚህ መሀል ድሮ ከአገር ቤት ሳይወጣ የሚያውቃቸው ጓደኞቹ የአባቱን መሞት ሲሰሙ ለቅሶ ሊደርሱ እርማቸውን ሊያወጡ በዚያውም የቀብር ቀንና ሰዓት ጠይቀው የቀብር ቦታውን ለይተው ሊመለሱ በድንገት ይደርሳሉ። ለቅሶ ተጀመረ «አልሰማሁም ነበረ... እኔን ያስቀድመኝ ...አባዬ አባዬ...»ልጅየው ትንሽ ታገሣቸው ከሩቅ ቦታ ስለመጡ በማለት ሠዓቱን እየተመለከተ እነርሱም በአገርኛ አልቅሰው ከጨረሱ በኃላ ሴቷ ወደ ጓዳ ገባች ሀዘንተኞች ከቀብር መልስ የሚቀመሱትን ንፍሮ ለመቀቀል፣ አንደኛው ምን ሆነው ነዉ የሞቱት እያለ ይጠይቃል ሌላው እስክርቢቶ አውጥቶ የህይወት ታሪካቸውን ይፅፋል ከቀብር በኃላ ለታዳሚዎች ለማንበብ ...እንዲህ ሁሉ በሥራ በተጠመደበት እርሱ መቸኮሉን ይነግራቸዋል ወደ ሥራ ለመሄድ እነርሱም አባቱን ሊቀብሩ እንደመጡ ምናምን ሲያጫውቱት «...እንዴ! አባቴን ለመቅበር ነው የመጣችሁት? ጊዜ አላችሁ? እንግዲያውስ በቃ እናንተ አባቴን ሄዳችሁ ቅበሩልኝ እኔ ወደ ሥራ ልሂድ ይላቸዋል፤ ...» መቸስ ትስቁ ይሆናል አታፍሩም አይሳቅም ነገሩም አያስቅም እንግዲህ እዚያ አገር አሜሪካ እንዲህ ነው አሉ እንዲያውም ሲባል እንደሰማሁት መቸስ አሉ ነው፤ ያንን የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ኦባማን እንዲመረጥ ካስደረጉት ውሥጥ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያኖች ናቸው ይባላል። ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካዊ ሥለሆነ አፍሪካ ደግሞ ለአሜሪካ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ነውና የምትቀርበው ባህላችንን ይጠብቅልናል የሐዘን ፈቃድ ይሰጠናል እዚህጋ እንዲያውም እንደሚባለው ያኔ ድሬደዋን ጎርፍ ያጥለቀለቃት ጊዜ መጥቶ ሐዘናችንን በዓይኑ ስላየ ይራራልናል በማለት ነበር። የምርጫዉ ቅስቀሳ ላይ እርሱ እንዲመረጥ ላይታች ሲሉ የነበሩት አሁን እንዲያውም ስሰማ ይህንንና ሌሎች ተስፋ ያደረግናቸውን የአፍሪካን ይልቁንም የኢትዮጵያን ጉዳይ ችላ ብሏል ብለው ቂም ይዘውበታል፣ አንዳንዶችም ዋ! እያሉ ይዝቱበታል አሉ። ለዚህ ያበቃቸው ምን እንደሆነ ባላውቅም ይህን ድፍረታቸውን ግን አልወደድኩላቸውም የሰማ ቀን ግን በአመጽ መንግሥት ለመገልበጥ ጥረት አድርጋችል በማለት እንዳያስገባቸው ኦባማ ማለቴ ነው። በቅስቀሳ ወቅትም አጉል እዩኝ እዩኝ በማለት የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እያሉ ማሽቃበጡን ትተው የሄዱበትን ጉዳይ ሥራቸውን ብቻ ቢሰሩ ይሻላቸዋል ባይ ነኝ ፌዴራል ፖሊስ ጠራርጎ እንዳይወስዳቸው (ፌሬራል ፖሊስ ለመሆኑ አለ አንዴ አሚሪካ?) እንጃ እንግዲህ!
          መቸስ ዘመድ ባይኖረኝ የማውቀው ሰው አይጠፋ ብዬ ሰጋሁና እንዴት ነው ነገሩ እነዚህ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ያስጠገባቸው ዓለም በአጠቃላይ ያልደፈራትን አሜሪካንን  መሪዋን ኦባማን የተዳፈሩት አርፈው አይቀመጡምወይ ብዬ የጭንቀቴን ባማክረው የኔን ጭንቀት ከቁብም ሳይቆጥረው ምን  ይሆናሉ ብሎኝ እርፍ። እንግዲህ ዘመድ ባይኖረው ካልሆነም የሚያውቀው ነገር ይኖረዋል ብዬ እንዴት? አልኩት። እንዴት ምንም አይሆኑም ኢራቅን የመሰለች አገር ደብድባ የሳዳም ሁሴንን ክብር ያቀለለች አገር እዚሁ ፊታችን ዓለምን ሲያስጨንቁ የነበሩ የሱማልያ አሸባሪዎች ዶግ አመድ ያደረገች አሜሪካ በመሪዋ ሲመጡ እነዚህን ጭብጥ የማይሞላ ኢትዮጵያውያን እንዴት ምንም እያደረጓቸውም ?? ብዬ ቱግ አልኩላችሁ ሰውየው የባስ እግሩን አንስቶ ቢስቅ ምን ትሉታላችሁ? በአንድም በኩል ትዕግሥቴ በዝቶ በሌላ በኩልም ፍርሃቴ ፀንቶ ነው እንጂ ዘልየ ጉሮሮውን ባንቀው ደስ ባለኝ። ሳቁን አፍኖ «እድሜ ለዲሞክራሲ» ብሎኝ እርፍ «ዲሞክራሲኮ ነው ምን አስፈራቸው እንዲያውም በዚህ ሰዓት ባለቀ ሰዓት እርሱ ነው ሊፈራቸው የሚገባው የምርጫ ካርድኮ በነርሱ እጅ ናት! በምርጫ ካርዳቸው ልኩን ያሳዩታል» በማለት ወደኔ አፈጠጠ፤ «አሁንስ ገባህ?! አለኝ ተረጋግቶ እየተቀመጠ።
          ገባኝ «ገባኝ አሁን ገና» ነው ያለው ዘፋኙ? አፍሪካ አገር ውስጥ ዲሞክራሲ ሥራውን የሚጀምረው ከስንት ዓመት በላ ነዉ የምርጫ ካርዳችንስ መቼ ይሆን ዋጋ የሚኖረው? አፍሪካዊስ መች ይሆን ደፋር የሚሆነው?...
ያለቸገረኝን?
በሉ ወደ ጀመርነው ጉዳይ፤
          በዲቪውም ይሁን አጥር ዘለን የምንሄድበት (በህገ ወጥነት) አሜሪካ ይሰሩበታል እንጂ ቁጭ ብለው አይቡሉባትም አሉ። አንድ ወዳጄ አጥር ሰበሮ ከደቡብ አፍሪካ አሜሪካ ከገባ በኃላ ኑሮ በአሜሪካ እንዴት ነው? ብዬ ብጠይቀው ምን ብሎ አወጋኝ መሰለቻችሁ ሰርቶ ለማግኘት ቤተሰብም ለመርዳት እምዬ ደቡብ አፍሪካ  ለጉራ (ልጄ፣ ወንድሜ፣ እህቴ አሜሪካ አለ ለማለት) ደግሞ አሜሪካ ይሻላል ብሎኝ አያርፈውም ይቺን ይወዳል ገነት አሜሪካ!
          ጊዜ ገንዘብ ነው ይላሉ 16 እና ከዚያ በላይ ሠዓት ሰርቶ አደሮች (አበዶች አላልኩም) በአሜሪካ፡፡ በቅርቡ ከአሜሪካ የመጣ አንድ የጉደኛዬ ወንድም እንደሰማሁት ከሆነ ለፈሱ ጊዜ የለዉም አሉ አሜሪካ ከሄደ ጀምሮ ይሰራል ይሰራል ይሰራል... ግን ኖሮ አያውቅም ሰዎች (አሜሪካ ያላችሁ) እናንተ አገር 24 ካራት ወርቅ ነው የምትበሉት ወይስ ውሏችሁ አሜሪካ አዳራችሁን ፕላኔት ላይ ነው? እንደዚህ የምትሰሩት ለሥራ ተከፍሏችሁ ለመኖር የሚያስከፍሏችሁ ከሆነ እባካችሁ ተመልሳችሁ ኑ! ምድራችን ሠፊ ናት አየር መንገዳችንም ቀጥታ በራራ ከጀመረ ሰንብቷልና (መረጃ ከሌላችሁ)። አልሰማችሁ እንደሆነ ልንገራችሁ ዓለም የሰማውን እናንተ በሥራ ተጠምዳችሁ ካልሰማችሁ የአቡኑን እና የመሪዎቻችንን ETV «ደማቅ» ያለውን የቀብር ሥነ-ሥርዓት ለዚያም አባቱን በጓዸኞቹ ላስቀብረውም ንገሩት ቀብር ክብር እንዳለው እናንተ ለግማሽ ቀን በዛ አንድ ቀን ሰልስት ለሌላው ለቅሷችሁ እኛ 15 ቀን ሙሉ አስክሬን አስቀምጠን ሥራ ፈተን እንደምንቀብር፣ ለሟች ክብርና ፍቅር እንዳለን። አሁን ታዲያ እናንተ ተመልሳችሁ ኢትዮጵያዊ ትሆናለችሁ? እንጃ! ለነገሩ እንኳን የሚያዝን ልብና የምታነቡት እንባ ጊዜም አይኖራችሁ፤ ተውት! እኛ እንዳተፈጠረን እናዝናለን። እንዴት ሰው ለወለደው አባቱ ቀብር ጊዜ የለኝም ይላል! ነው ወይስ ዘመናዊነት እንዲህ ሆኖ ቀረ ወይስ ጉድ ሳትሰሙ መስከረም አይጥባ ብሎ ፈጣሪ ፈርዶብን ነው።???
ለነገሩ ለቅሶን አነሳን እንጂ ኑሮስ መች ተመቻቸዉ? አንዴ ሄደናል ብለዉ እፍረት ተሰምቸዉ እንጂ ለነገሩ ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል ብለዋል ቾች፡፡

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...