1. ሰው መምረጥ
*በብቃቱ፣ በክህሎቱ፣ በተሠጥኦው፣ በትምህርት ዝግጅቱ፣ ወዘተ ከአላማችን ጋር የሚቀራረብ ግባችን ለማሳካት የሚያስችል ሰው መምረጥ አስፈላጊ ነው።
ተቋማት የሥራ እድልን ከመፍጠር ጎን ለጎን ተቋምን ሊያሳድጉ ስኬትን ሊያስመዘግቡ የሚችሉ እና የአገርን ሥም በአለም መድረክ ጭምር ሊያስጠሩ የሚችሉ ሠራተኞችን ከጅምሩ ከላይ በተዘረዘሩት መሥፈርቶች መመልመል ይኖርባቸዋል።
ይህ ሠው ታድያ ግላዊ ጉዳዩን ወደ ጎን ያደረገ የአገር ፍቅር ለወገን ክብር ያለውና ሥራውን እሴት ጨምሮ የሚሰራ ተደርጎ መሠራት አለበት።
የማይረካ፣ የመማር፣ የመሥራት፣ ሁሌም ጀማሪ የሆነ፣ ሁሌም ለአዲስ ነገር ጉጉ የሆነ፣ ዘወትር ለውጥን አሻግሮ የሚያይ፣ ሁሌም ለሥራ የሚሮጥ፣ ጥማት ያለበት ሰው መምረጥ ይኖርብናል።
ሰዉ በመምረጥ
ሂደት ዉስጥ መዘንጋት የሌለብን ነገር ምናልባት ከቦታዉ ጋር የሚሄድ ካልሆነ በቀር አለበለዚያም የትምህርት ዝግጅቱ ከመለያየቱ
በቀር ‹‹የማይረባ›› የሚባል ሰዉ እንደሌለ ልብ ልንል ይገባል፡፡
2. ሰው መሥራት/መፍጠር/
የአንድ ሰው ዋጋ እጅግ ውድ እና በምንም የመገበያያ ገንዘብ ሊተመን የማይችል ነው፤ በአንድ ተቋም ውስጥ ከሰው የሚበልጥ ነገር የለም።
ስለዚህ የሰራተኛን አመለካከት፣ የሰራተኛን ችሎታ፣ የሰራተኛውን አቅም ማሳደግ ከሁሉ ነገር መቅደም ይገባዋል።
ለውጤታማነቱ ተከታታይነት ያለው ክትትል በጥንቃቄ ሊተገበር ይገባል።
እርስ በርስ ፍሬያማ የሆነ ውድድር እንዲኖር አዎንታዊ የእርስ በርስ ተቋማዊ ውድድር እንዲኖር ማድረግ አንዱ ሰው የምንሰራበት መሣሪያ ነው።
ሰው በዚህ መልኩ በጥሩ ሁኔታ ከተገነባ ጠንካራ የሰው ሃይል ስኬታማ ተቋምንም ሆነ አገርን መገንባት ይቻላል።
አገርንም ሆነ ተቋምን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመመስረት የሴቶች ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ አለው፤ ሴቶች ትውልድን በመቅረጽ ላይ ትልቁን ሚና ስለሚጫወቱ።
አገራትም ሆኑ ተቋማት የሴቶችን ቁጥር በመጨመር ለዘላቂ ስኬት መትጋት ይኖርባቸዋል።
በምሳሌ ላስረዳ: - ሴት ከሁሉም የሰው ፍጥረት ጋር ቀዳሚ እና ዘላቂ ቁርኝነት ስላላት ሚናዋ ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም ሴት ልጅ የወንድ ልጅ የተፈጥሮ አጋር ከመሆኗ ባሻገር እናት ነች፣ (ልጇን በስነምግባር አንጻ ለስኬት ብቁ አድርጋ መቅረጽ ትችልበታለች) ሞግዚት ናት፣ (ጤናማ እና በአካል የዳበረ ለትምህርት እና ለሥራ ዝግጁ የሆነ ዜጋ መፍጠር ትችላለች)፣ የሥራ ሃላፊ ነች፣( በቅርበት በእናትነት እና በእህትነት ጸጋ የሥራ ባልደረቦቿን የተጣመመውን አቃንታ የተበላሸውን አስተካክላ ለመጓዝ የሚያክላት እና ከርሷ የተሻለ ልምድ ያለው የለም)፣ ሚስት ናት፣( ባለቤቷን ለተሳካ ውሎ በደስታ እና በተነቃቃ መንፈስ ከቤት መሸኘት የምትችል በውሎው ደስተኛና ስኬታማ እንዲሆን የምታስችል መግነጢሳዊ ጸጋ የተላበሰች ነች) እህት ናት፣( ትንሽ ሆና ትልቅ በእድሜ አንሳ አስተሳሰቧ ትልቅና ሐላፊነትን መሸከም የሚችል ነው።)
ይህ ሁሉ ሴትን ልጅ የዚህ አለም ማጣፈጫ ጨው ናት ብንል ማጋነን አይሆንብንም ሰው መሥራት ትችላለችና።
ስለ ሰው መፍጠር/መሥራት/ ካነሣን ሰውየውን መሥራት ከቤት እስከ መሥሪያ ቤት ድረስ ከጠባቂነት መንፈስ
አላቆ የተሟላ የሙያ ባለቤት ማድረግ ነው።
አንዲት አንቀጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ጸሐፊ መጠበቅ፣ የሆነ ቦታ ደርሶ ለመመለስ ሹፌር መፈለግ፣ የሥራ አከባቢው ጽዱ እንዲህን የጽዳት ሠራተኛን ደጅ መጥናት፣ ቁርሱን በልቶ ፣ ሸሚዙን ተኩሶ ለብሶ ለመውጣት፣ ለልጆቹ አስፈላጊውን ነገር አድርጎ ትምህርት ቤት ሸኝቶ ለመውጣት፣ የትዳር አጋሩን አለበለዚያ የቤት ሠራተኛውን ድጋፍ ከመጠበቅ ወዘተ አስተሳሰብ አስወግዶ ሁለገብና ሙሉ ሰው አድርጎ መሥራት አስፈላጊ ነገር ነው።
እጅን አጣጥፎ በተማርኩት/በተመረኩበት መሥክ ብቻ ልስራ የሚል አመለካከትን ማኮላሸት። አንድ በሥራ አመራር የተመረቀ የሥራ ኃላፊ ጸሐፊነቱንም ሹፍርናውንም አሰልጣኝነትን ደርቦ ቢሰራ ክብር እንጂ ውርደት እንዳልሆነ አምኖ የሚቀበል ማንነት ማሥረጽ።
ካመንክ ትችላለህ ዋናው በአቅምህ መተማመን ነው የጎደለህን እየሞላህ፣ የጀመርከውን እየጨረስክ፣ ሰው የደረሰበት እየደረስክ፣ ሙሉ ሰው እየሆንክ ታድጋለህ።
ሰው መሥራትም ሆነ መሰራት/መፈጠር ከዚህ የዘለለ አይደለም። እራስህን በራስ መተማመን ላይ ዳግም ከሰራህ ሌላውን በውስጡ የተዳፈነ እሳት ጭረህ አሳየው ሲቀጣጠልለት ማን እንደሆነ ይገባዋል። እሳቱ ዓለምን እንዳልነበረች አድርጎ የሚያጠፋ የሚባላ እሳት፣ አልያም
ዓለምን እንደሚፈልጋት አድርጎ የሚሰራበት ኃይል እንደሆነ ብቻ አስገንዝበው ከዚያ በኋላ የሚያስቆመው አንዳች ነገር አይኖርም።
አንዱ ሰዉ የሚሰራዉ/ተሰራ
ተብሎ የሚታመነዉ ብዙ መስፈርቶች ቢኖሩትም እና በጥናት የተደገፈ ይሄ ነዉ የሚባል ነገር ባይኖርም በእኔ አረዳድ አንዱና ዋነኛዉ
ነገር ብዬ የማምነዉ ሥነሥርዓት ( Deiscipline)
ነዉ፤ የዲስፕሊንን ጥቅምና ሰዉ በመስራት ላይ ያለዉን ፋይዳ በምሳሌ አስረዳለዉ፡፡
1ኛ.
በደርግ ሥርአተ መንግሥት ወታደሩ እና መሪዉ ኮነሬል መንግሥቱ በወታደርነታቸዉም ሆነ በመሪነታቸዉ አገር የሚመሰክርላቸዉ የባንዲራ
(ሰንደቀላማ) ክብር እና የአገር ፍቅር ነዉ፤ ሁለቱ የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር፣ የጠላት ጦር ሲመጣ
ጀርባን ሳይሆን ግንባር ለመስጠት እስከ ህይወት መስዋእትነት ከፍለዉ የተዋጉት/ የሚዋጉት/ እንዲዋጉ የሚያደርጋቸዉ የወታደርነት
ሥነሥርአቱ ነበር፡፡
ወታደር
ሰንደቀላማ ሲወጣም ሆነ ሲወርድ የነበረዉ ሥነሥርአት ከአገር ፍቅሩ ጋር በአንድነት የተገመደ ነበር፣ አይደለም ወታደሩ ህዝቡ
የሰንደቀላማ ክብር ስለነበረዉ እንደወታደሩ ሁሉ በተጠንቀቅ ቆሞ የኢትዮጵያን የህዝብ መዝሙር ይዘምራል፡፡ በዚህ ወቅት ጉንዳን ቢነቅሰዉ፣
እባብ ቢድፈዉ፣ ዝናብ ቢመታዉ፣ እሳተ ጎመራ ቢፈነዳ፣ ወዘተ አንዳች ነገር አይነቀንቀዉም፡፡ ሥነሥርአቱ ዉልፍት እንዳይል አንፆታልና፡፡
ወታደሩ
ለዚህ ሥነሥርአት እና ሥነምግባር (ethics) ሞቷል፣ አካሉን ገብሯል፣ ዳር ድንበርም አስከብሯል ( በእርስ በርስ ጦርነት ዓላማዉ
ቢጠለፍም)
2ኛ.
የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሠራተኛ ለአርማዉ፣ ለተቋሙ፣ ለአገልግሎቱ፣ የሚጠበቅበትን
ዋጋ ከፍሎ በመላዉ ኢትዮጵያ የዛሬዉ የቴሌኮም ተደራሽነት አሻራዉን አሳርፏል፡፡ የነበረዉ ዲሲፕሊን ቃላት አይገልጠዉም፡፡ እንዲሁ
ትንሽ ትንሽ በምሳሌ ለማንሳት ያህል ካልሆነ በቀር፡- ፍቅሩን ‹‹እምዬ መስሪያ ቤቴ ›› እያለ
ይገልጠዋል፣ የተቋሙን አርማ በጣት ቀለበቱ፣ በአንገት ሃብሉ፣ በሚለብሱ ልብሱ ላይ ያትመዋል፡፡ የስልክ ገመዱ ተበጥሶ ምሰሶዉ
ወድቆ ካየዉ መፍትሔ ሳያበጅ አንድ እርምጃ አይራመድም ነበረ፡፡ እነዚህ የሥነሥርአቱ (የዲሲፕሊኑ) መገለጫዎች ነበሩ፡፡
3ኛ.
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጢያራዉ (አዉሮፕላኑ) የኢትዮጵያን ሰንደቀላማ ለጥፎ በሰማይ ላይ ሲበር ከልጅ እስከ አዋቂ አንጋጦ የሚያየዉ
ወዶ አይደለም ለአገሩ ክብር እና ፍቅር የላቀ አስተዋፅኦ ስለሚያደርግ፣ የአፍሪካም ኩራት ስለሆነ እንጂ፡፡
ይህ
ሁሉ መገለጫዉ ሥነሥርአት (ዲሲፕሊን) ነዉ፤ አንድ ተቋም ሲመሰረት ሰራተኞቹን ሲመለምል እና ለስራ ሲደለድል ከምንም በፊት ሠራተኛዉ
ለአርማዉ ክብር ለተቋሙ ፍቅር እንዲኖራቸዉ የሚያደርግ ሥነሥርአት ማስጨበጥ አለበት፡፡
ሰራተኛዉ
ዲሲፕሊን ሲኖረዉ ዓላማዉን ለማሳካት አገልግሎቱ ላይ እሴት (value) እንዲጨምር ይረዳዋልና፡፡
*ስልጠናዎች:
- ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው አሥቀድሞ እና ወደ ሥራ እንደተሠማሩም የተግባር ስልጠናዎች ሊሠጣቸው ይገባል። ምክንያቱም አንድ ሰራተኛ ወደ ተቋም ሲቀላቀል አስፈላጊውን ሥልጠና ከወሰደ ከሰራተኛው ጋር ሲቀላቀል እና ሥራውን ሲጀምር በራስ መተማመኑ እየጨመረ በሥራውም ስኬትን እያስመዘገበ ይመጣል።
እንደ አገርም ሆነ እንደ ተቋም አዲስ ተቀጣሪዎች ቀጥታ ወደ ሥራ ከማስገባት ይልቅ የአመለካከት እና የእውቀት ሥልጠና ላይ ማሰማራት ለስኬት አይነተኛ ሚና አለው።
በስልጠና ወቅት ሠልጣኞች ከአሰልጣኞችም ሆነ ከሰልጣኞች ጥሩ ተግባቦትን ይፈጥራሉ፤ እርስ በርስ ከመተዋወቅ የጀመረ ውህድ ወደ ተግባር ሲገባ ከስኬታማነት ውጭ አማራጭ የለውም።
የኛ አገር ተሞክሮ ግን በተቃራኒው ነው ከጽሁፍ እና ቃለመጠይቅ ፈተና በኋላ መሟላት ያለበት ነገር ተሟልቶ እንዳለቀ ቀጥታ ወደ ሥራ ይሆናል። ሥራን የሚተገብረው አዲስ አከባቢ አዲስ ሰወች ውስጥ ይሆናል። ውሎው በማያውቃቸው ሰወች መካከል ይሆናል። በዚህ አካሄድ እንኳን ሥራው ውሎው ያማረ አይሆንም።
መተዋወቅን የመሰለ መንገድ ጠራጊ አጋጣሚ በህይወት ዘመን ውስጥ አይገኝም። ይህ እድል የሚገኘው በስልጠና ወቅት ነው።
የስልጠና ቦታ ላይ መገኘት በራሱ አስተማሪ ነው ለምን እዚያ ስፍራ እንደተገኘህ ታስባለህ፣ ስራውን በምን መልኩ ማከናወን እንዳለብህ ታውቃለህ፣ ድርሻህ ምን እንደሆነ ይገባሃል፣ ራእይ ይኖርሃል፣ በአጭሩ ከህልምህ ጋር ትገናኛለህ።
ትንሹ እርሾ ብዙውን ሊጥ እንዲያቦካው የጥቂት ቀን ስልጠና ብዙውን እምቅ አቅማችንን ለትልቅ ስኬት እንድናወጣውና እንድንጠቀምበት ይረዳናል።
*ራስን
ማብቃት/ማጎልበት: - ተቋማትን ለሠራተኞቻቸው ሥራን ብቻ ማቅረብ ሣይሆን ሠራተኞች የራሳቸውን አቅም የሚያጎለብቱበትን እድል ማመቻቸት መሠረታዊ ነገር ነው። ለምሳሌ ቤተመጻሕፍት፣ ቤተሙከራ፣ የበይነ መረብ (Internet) አቅርቦት
ወዘተ ሰውን ለመስራት ምቹ ሁኔታ ነው።
የሰው ልጅ ከትምህርት ቤት በሚገኝ እውቀት ብቻ ብቁ እሆናለሁ በማለት እጅና እግሩን አጣጥፎ የሚቀመጥ ከሆነ መጨረሻው እንደ ቲማቲም ይሆናል። (ቲማቲም አብስለን ለምግብነት የማንጠቀምበትና ዝም ብለን የምናስቀምጠው ከሆነ እንደነበረ አይገኝም ይፈርሳል, ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ተቀይሮ ከመኖር ወደ አለመኖር ይቀየራል።) እውቀትም እንዲሁ ነው እለት እለት ልንመረምር፣ ልናነብ፣ ልንጠይቅ፣ልንማር ካልቻልን
እዉቀታችን ነበር ይሆናል።
አንድ ወግ እዚህ ላይ መጨመር ጉዳዩን አጽንኦት ይሰጠዋል።
‹‹ አንድ
አባት ወደ አንድ በየቀኑ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ የሚዉል ወጣት
ዘንድ ይሄዱና ልጄ ስወጣ ስገባ እዚህ ድንጋይ ላይ ተቀምጠህ ነዉ የማይህ እዚህ ከምትዉል እንደ ባልንጀሮችህ ለምን አትማርም? ይሉታል እርሱም ሥራ የለኝ፣ ገቢ የለኝ፣ የሚረዳኝ የለኝ ምን እየበላሁ በምኔስ ልማር? ይላቸዋል እርሳቸውም ብልህ ሰው ነበሩና ልጄ ለመማር ይህ ሁሉ ጉድለት ካገዱህና እንዳትማር ካደረጉህ ታድያ ከጠዋት እስከ ማታ እዚህ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለህ የምትደድበው ምን እየበላህ? ማንስ እየረዳህ ነው?
›› አሉት ይባላል።
የሰው ልጅ ዘወትር ራሱን ለማብቃት የማይታትር ከሆነ መደደቡ አይቀሬ ነው። ለመማር ተነሳሽነት እንጂ እርዳታ አስፈላጊነቱ ያን ያህል ነው ለማለት ነው።
እኛ ከየትኛው ወገን ነን?
ዘወትር ማንበብ፣ መጠየቅ፣መወያየት፣ ይገባናል።
በመማርህ ትናንት ታውቅ ነበረ የነገን እውቀት ግን ማወቅህን ለማወቅ የዛሬ ውሎህ ይወስነዋል። ስለዚህ ራስህን በእውቀት ለመገንባት ከእውቀት አትራቅ።
*እውቀት
ማወራረድ (knowledge transfer): -ሰው ለመማር ዝግጁ ከሆነ ከሥነፍጥረትም መማር ይቻላልና አንደኛው ከሌላኛው እንዲማር የእውቀት ሽግግር ማድረግ እጅግ ወሳኝ ነው።
አንዱ እርሱ ብቻ ብርቱ ስለሆነ ተቋም ስኬታማ አይሆንም፤ ይልቁንም እውቀትን ለሌሎች ማሸጋገር የማይተካ ሚና አለው። በአገራችን ተቋማት ተሞክሮ ይህ ጉዳይ በስሱም ቢሆን አይታይም። የቅርብ አለቆችም ልማዳቸው አንድን ጠንካራ ሰራተኛ እንደ ሸንኮራ አገዳ አቅሙን መጥጦ መትፋት እንጂ እውቀትን በማወራረድ የመላ ሰራተኛቸውን እውቀትና ክህሎት አሟጦ መጠቀም ላይ እስከዚህም ናቸው። የራሳቸውንም ተሞክሮ ሲያሸጋግሩ ከማየት ይልቅ ሲያልፉ የሟች የህይወት ታሪክ ላይ
እንዲህ ነበሩ እየተባለ ሲዘረዘር መስማትን ነው ያዳበርነው።
በእውቀት ማወራረድ ውስጥ ሊኖር የሚገባ መርህ
፩. የባለቤትነት ስሜት መፍጠር፤ ጠባቂ አለመሆን።
፪. ዘወትር ንቁ ተማሪ መሆን፤ አውቃለሁ የሚል እሳቤን ማስወገድ።
፫. መሪ ቃል መኖር (ገቢ
ግብር የሚሰበስብ አካል ለምሳሌ በትንሹ ቀስቅሰን/አንቅተን በብዙ እንሰበስባለን) hard working vs work hard (እዚህ መሪ ቃል ዉስጥ አሰልቺና ከባድ ነገር አልተጠቀምንም ስለዚህ
ተግባሩንም ቀላል ያደርገዋል፡፡)
፬. ሙያተኛ ነኝ ብሎ በማሰብ ከተቀጣሪነት መንፈስ መውጣት። ሁሉን በራስ አቅም የመወጣት ብቃት ማዳበር።
፭. እኔ ስቀየር አከባቢው ይቀየራል፤ አከባቢ ሲቀየር አገር ተጠቃሚ ትሆናለች የሚል አስተሳሰብ ማበልጸግ።
፮. ካመጣነው ውጤት በላይ የምንጠብቅ ከሆነ ከዚያ በላይ የላቀ አስተሳሰብ መገንባት ይጠበቃል፡፡
for more information join my telegram channel
https://t.me/deressereta
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ