ረቡዕ 26 ዲሴምበር 2012

ፖሊስና ህብረተሰብ



ንጉሱ  ለአንድ ሃገር መንገዶች ወሳኝነት አላቸዉና መንገድ አሰርተዋል መንገዱ ላይ የሚመላለሱት መኪኖች ለማስተናበር በአዲስ አበባው ከንቲባ ፖሊሶች (ትራፊክ ፖሊስ) ተመድበው በትዕግሥትና በንቃት ያስተናብሩ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ፖሊሶች።
ü የሚጫሙት ጫማ ሳይኖራቸው ባዶ እግራቸውን ነበሩ፡ ህዝቡ(ባላገሩ) በእግረኛው መንገድ እንዲጠቀም ለማስተማር በሚያደርገው ጥረት፣ አልሰማ ሲሉት «በንጉስ ኃይለ ሥላሴ በቀኝ በኩል ይሂዱ» እያለ ይለምን ነበር።
ይህንን ቀደምት ታሪክ ያገኘሁት በአዶልፍ ፖርሊስክ «የሃበሻ ጀብ» ከሚለው መጽሐፍ ነበር።
    እንግዲህ በንጉስ ዘመነ ንግሥና የፖሊስና የህብረተሰብን ግንኙነት ሥንመለከት ይህንን የመሰለ ሥነ-ሥርዓት የተሞላበት በትህትና የታጀበ መልካምነት የተሞላበት አገልጋይና ተገልጋይ ነበር። የፖሊስ መሠረታዊ ሥራ ከጥንት ከመሰረቱ ህዝብን ለማገልገል፣ መኪኖችን ለማስተናበር፣ህገመንግሥቱን አክብሮና ጠብቆ ለማስከበርና ለማስጠበቅ … ወዘተ ነው፤ ከዚህ የተለየ ዓለማ የለውም። ከህብረተሰቡ መካከል የወጣ በመሆኑ የህብረተሰቡ ችግር የሚገባው፣ የህብረተሰቡን ጠንካራና ደካማ ጎን (በጎና መጥፎ ጎን) ጠንቅቆ የሚያውቅ በትምህርትና በሥልጠና የዳበረ እውቀት ያለው ነው። ለዚህ  ህብረተሰብን ለማገልገል ለፖሊስነት ሲታጭና ሲመለመል በሥነ-ምግባር የታነፀከተለያዩ ሱሶች የፀዳ፣ የቀለም ትምህርት ዝግጅት ያለው፣ ሙሉ ጤናማ የሆነ፣ ለህገ-መንግሥቱ ታማኝ የሆነ... ወዘተ መሆን አለበት ተብሎ ይገመታል፤ መሆንም አለበት የሚል እምነት አለኝ። ነውም።
    ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚያሳዝነው ነገር እንደዛሬ ግዜውን ለተለየየ ነገር ባልተመቻቸበት ወቅት (ዘመን) አንስቶ ለፖሊስ የምንሠጠው ግንዛቤ አናሳ ነው። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ከህብረተሰብ ጋር ያላቸው ትስስር እጅግ የጠበቀ ቢሆንም ለህብረተሰቡ የሚሰጡትም ጥቅም ትስስር እጅግ የጠበቀ ቢሆንም ለህብረተሰቡ የሚሰጡትም ጥቅም እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዝም ብዬ ስጠራጠር ህብረተሰቡም ይሁን ባለድርሻ አካል ጥቅማቸውን የተገነዘበው አይመስለኝም ምነው ቢሉ በንጉሱም ዘመን ቢሆን አስቀድመን በመነሻችን እንዳየነው አንዱ የፖሊስ መገለጫ የነበረው « የሚጫሙት ጫማ ሳይኖራቸው ባዶ እግራቸውን ነበሩ» ወደ ዛሬ ከመጣንም ምን አላቸው? ምንም ለማለት ያስደፍራል። አንድ ነገር ትዝ አለኝ በደርግ ዘመን መንግስት ምንም እንኳን ሥለ ሥርዓቱ እዚህጋ ማንሳት ባያስፈልግና ቦታውም ባይሆን አንድ ነገር ግን ማንሳት ግድ ይለናል።። በወቅቱ የነበሩት የፖሊስ  ሰራዊትም ሆኑ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በልብስና በጫማ በኩል ችግር ያለባቸው አልነበሩም። ምናልባት ከነበረው የሰራዊት ቁጥር አንጻር ሊሆን ይችላል ቢሆንም ግን ዛሬ ዓለም አንድ መንደር እንደመሆኗ መጠን ዓለምም በአሸባሪዎች ሰላምን በሚያደፈርሱ ፀረ - ሰላም ሃይሎች እየተናወጠች በሚገኝበት አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ በወቅቱ የነበሩት ፖሊሶች «ፊልድ ጃኬት» የሚባል ወይም በጣም ወፍራም የሆነ ካፖርት ይሰጣቸው ስለነበር ይህ ልብስ ዛሬ ላይ ሲታሰብ እንኳን ሊገኝ ይቅርና አይታሰብም ድፍረት አይሁንብኝና ፖሊሶቹም የሚያውቁትና የሚናፍቁት አይመስለኝም። ያኔ ግን (በደርግ ጊዜ ማለቴ ነው) አንኳን ፖሊስ ይቅርና የፖሊስ ቤተዘመድ እንኳን የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኙ ነበር። ዛሬ ግን በምሽት የህብረተሰቡን ሰላም ለማስቀጠል የአገርን ፀጥታ ለማስፈን ከላይ ታች የሚሯሯጡትን ፖሊሶች ስንመለከት የአየር ፀባዩ በሚለዋወጥበት ከዚህ ዘመን ቀን ከሚለብሱት የተለየ ለምሽት የሚሆን ካፖርትም ሆነ ፊልድ ጃኬት የሚታሰብ ጉዳይ ኣይደለም ያቺው የፈረዳባት ከክረምት በጋ የምታገለግል ሻማ ነገር በቀር ይህንን በምልበት ሰኣት ልቤ እጀግ ያዝናል እግረ መንገዴን ለሚመለከተው አካልም ሆነ ሕብረተሰብ የአደራ መልዕክቴን እባካችሁ አትኩሮት ሥጧቸው እላለሁ።
            በመቀጠልም የልብስ ጉዳይ ሲገርመን የባሰ ከመግረም አልፎ የሚያሳዝነው ከአንዳንዶች አለፎ አብዛኞች ጥንድ ጥንድ እየሆኑ የምናያቸው ከበትር ወይም አጭር ከፕላስቲክ የተሰራች ዱላ በቀር ምንም የላቸውም። ክፉን ያርቅልንና እንዲሁም ከሥነ-ምግባር አኳያ ሲጀምር ለመደባደብ የወጡ አየደሉም እንጂ ባዶ እጃቸውን እንኳንስ ሰው ሊያስጥሉ ይቅርና እነርሱንም እግዚአብሔር ነውየሚጠብቃቸው፤ ለዚህ ነው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን የሆነው በመዲናችን በአዲስ አበባ የቀድሞ ባላቤቷ ውድ ባለቤቱን የልጆቹን እናት እወድሻለሁ አፍቅርሻለሁ አከብራሻለሁ ይላት የነበረችውን የቀድሞ ሚስቱን በመኪና እያሳደደ በመኪና እናቷን ከጋቢና አስቀምጣ እያመለጠች ባለችበት ወቅት እነዚህን ፖሊሶች የአገርን ሰላም የህብረተሰብን ሰላምና ጤና የሚያስከብሩ ሥትመለከት አቁማ አስጥሉኝ ብላ ስትማፀን አንድ ግለሰብ የፀብ መንጃ መሳሪያ በመያዙ ፖሊሶቹ ግን ሰላም የሚያስከብሩበት አጥፊዎችንና ጠላትን የሚከላከሉበት መሳሪያ ባለመያዛቸው በጥይት ደብድቦ የገደላትና ሌሎችንም ሊያቆስልና ሊጎዳ የቻለው።
    የሆነው ሆኖ የተፈፀመው ተፈፅሞ የጠፋውም ጠፍቶ የለማውም ለምቶ እንዲህ እንዲህ ስንል ዛሬ ደርሰናል። የፖሊስና የህብረተሰቡ ቁርኝት ምን ይመስላል ግንዛቤውስ? ቁርኝቱ ከፊት ይልቅ የጠበቀ ቢሆንም አንዳቸው ለአንዳቸው (ፖሊስ ለህብረተሰቡ፡ህብረተሰቡ ለፖሊስ) ያለው ግንዛቤ ተመናምኗል። ሁሉንም ባይባል እጅግ ጥቂት የሚባሉት ፖሊሶች የፖሊስነት ሙያን የተላበሱት ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲባል መሆኑን ህብረተሰቡም የሞቀ ቤቱ ሰላማዊ እንቅልፋን ተኝቶ ሲያድር ሃብትና ንብረቱን በሜዳ በትኖ እንዳሻው ሆኖ ወጥቶ የሚገባዉ ሃለፊነቱን ወስዶ የሚጠብቀው ፖሊስ መሆኑን የዘነጉ ጥቂት የማይባሉ ህብተሰቦች አይታጡም ። ይህ ደግሞ ክፍተት እንዳለ ያመለክተናል እንኳንስ የፖሊስ ክብርና ፍቅር ሊኖር ይቅርና የፖሊስ ፕሮግራም በቴሌቪዥን ማየት የሚያስጠላው ሞልቷል። ለምን?. ማለታችን አይቀሬ ነው በህብረተሰቡ መካከል በጉምጉመታ መልክና በተባራሪ የሚዳመጠው ፀሐፊውም እንታዘበውና እንደጠረጠረው አንዳንድ ችግሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል የህብረተሰቡን መንፈስ ለመግለጽ በአንድ ወቅት የገጠመኝን ነገር ልንገራችሁና ሃሳቡን ለመረዳት የተሻለ ይመስለኛል በመረጃ:: ለቅሶ ቤት ሆኜ ነዉ የለቅሶ ቤት የሄድነው ደግሞ ሟች የባል ሚስት ወንድም ነው ባል የፖሊስ አባል ነው ። በዚህ የተነሳ ብዙ የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ አባላት ለቅሶ ለመድረስ በቦታዉ ተገኝተዋል፡ ባልደረባቸውን ለማጽናናት:: በድንገት በሥፍራው የታደሙ አባት ድንገት ባዩት ነገር መነሻነት በከተማው የሚታዩ የፖሊስ ሰራዊት ቁጥር መብዛቱን ለመግለጽ «መንገዱን ሞልተውት የለ እንዴ» በማለት ይገልፁታል አንድ አባት ቀበል አድርገው «ምን ይገርማል ዩኒፎርም ለበሱ እንጂ በፊትስ መንገድ ላይ አልነበሩ አንዴ? በማለት ጣል ያደርጋሉ። ግራ የገባው ማብራሪያ መጠየቅ፡ የገባውም የአሽሙር ሳቅ መሳቅ ገሚስሙም አንዴ ፖሊሶቹን እያየ አንዴ ደግሞ እርስበእርስ እየታየ አፉን በእጁ ይይዛል እኚሁ መናገር የጀመሩ አባት ለጥያቄ ማብራሪያቸው እንዲህ በማለትቀጠሉ «... ማለቴ ድሮም እየተማሩም ትምህርታቸውን ጨርሰውም በየሱቁ ደጃፍ በየመንገዱ ሲገተሩ ልጃገረዶችን አላስወጣ አላስገባ ያሉ ገሚሶቹም ጨለማን ተገን በማድረግ በመቧደንም ሞባይሉ ሲቀሙ የነበሩ፣ ... ናቸው። እንግዲህ እዚህ ላይ ጥቂት የማናውቃቸው ተጨምረው ይኸው ሰልጥነው ግማሹ እስከ አመሉ ግማሹ  ጠባዩን ቀይሮ ግማሹ መሐል ሰፍሮ አብዛኛው ለህብረተሰቡ  ጥቂቱ ደግሞ ለራሱ ዮኒፎርሙን ለብሶ ከተማውን ሞልቷል።  በቃ ይኸው ነው የበለጠ ማብራሪያ ከፈለጋችሁ አሉና አንድ የሚያውቁትን በሠፈራቸው አስቸጋሪ የነበረ  ኋላ ግን እኛን ሲያስቸግር እነደነበረው ለመንግስትም አስቸግሯል መሰል «ይብለኝ የወለደሽ ያገባሽስ ይፈታሻል » አይደል የሚባለው እስከ ነተረቱ እየተከታተልክ ዝርፍ ብሎ አባረረው ብለው አስረዱ።
    ከላይ ከተጠቀሰው ታሪክ የምንረዳው ሕብረተሰብን ለማገልገል የሚመለመሉተ ፖሊሶች መካከል ከብስል መካከል ጥሬ እንዳለ ሁሉ በሥነ -ምግባር ታንፀው በብቃት ሰልጥነው የወጡት ፖሊሶች መካከል የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ፖሊሶች እንዳሉ ይጠቁማል ። ለምን? ጥሩ ጥያቄ ነዉ፡-
 አንደኛ ሲመለመል ጀምሮ ችግር አለ፤
ሁለተኛ ብቁ ስልጠና አልተሰጠውም
ሶስተኛ ሙያውን የሚያስከብር ጥቅም ስላላገኘ ሊያከብረውና በታማኝነት ሊያገለግል አልቻለም። የሚጫሙት ጫማ ሳይኖራቸው ባዶ እግራቸውን ነበሩና» አንድም ዛሬም ከዕለት ድካማቸው ይልቅ የወር ገቢያቸው እጅግ ያንሳልና፣ አንድም ወርቅና ዶላር እየጠበቁ ጥቂት ብሮች ናቸውና የሚከፈላቸው፡፡ አንድም ሰዉ ሰላማዊ እንቅልፋን እንዲተኛ እያስቻሉ እነርሱ ብርድ እንኳን የሚከላከልላቸው የዓመት ልብስ የላቸውምና፡ አንድም የህብረተሰቡን ሰላም እያስከበሩ የነርሱ ቤተሰብ ግን ከገቢው ማነስ ከጥቅማ ጥቅማቹ አርኪ ያለ መሆን የተነሳ ቤተሰባቸው ሲፈናቀል ትዳራቸው ሲፈርስ ኑሮአቸው ሲናጋ የሚያምራቸው እንጂ የሚያገኙት ጥቂት በመሆኑ፡ አንድም ይህችን ድንግልና ለምለም ምድር እየጠበቁና እንዳትደፋር እያደረጉ የነርሱ ኪሲና ጎጆ ግን ቀዳዳና ገዳዳ ሆኖ ሊወድቅ አዘንብሏልና የሚጠበቅባቸውን አይሰጡም «በንፍሮ የደለሉት ሆድ/ጉልበት/ በዳገት ይለግማልና»። ከዚህ ማሳያ በላይ ሌላ መጨመርም አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም ፖሊስና ህብረተሰብ መካከል ያለውን ክፍተት ለማመላከት።
    እስኪ የህብረተሰቡን ችግር እንመልከት አንድ ጥያቄ ነክ ነገር ላንሳ በኛ አመላካከት በቤት ዘበኛና በፖሊስ መካከል ያለውን ልዩነት እናውቃለን? እኔንጃ አይመስለኝም። ፖሊስነት አንድ ፕሮፌሽን ሥነ - ምግባር ፣ ሳይንስ፣ ዲሲፕሊን፣ መሆኑን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? ፖሊስ ሲባል ከልጆች ማስፈራሪያነት የዘለለ የምንጠቀምበት ልጆቻችን ፖሊስ እንዲሆኑ የምናጫቸው ስንቶቻችን ነን? ለነገሩ እንኳንስ ለማናውቀው የፖሊስነት ሙያ ይቅርና ዓለምን እንደ እርሳስ የቀረጿት የዓለም መቅረጫ የመምህርነት ሙያ እንኳንክብርና ፍቅር የመሆን ምኞት የለንም ልጆቻችንም እንዲሆኑም አንፈልግም። በዓለም ላይ ትልቁ ሞያ ግን መምህርነት እና ፖሊስ እንደሆኑ ልመሰክርና ሳስገነዝብ እወዳለሁ።
    ለምንድን ነው ህብረተሰቡ ለፖሊሱ ክብር የነፈገው ጥሩ አመለካከትስ ያጣው? ብለን ካልን ጥቂት ነገር ማንሳት ይቻላል። በአንደኛ ደረጃ አስቀድመን ያነሳነው ታሪክ ሙሉ በሙሉ ስለተቀየረ በንጉሱ ዘመን የነበሩት ፖሊሶች (ትራፊኮች) «ህዝቡ (ባላገሩ) በእግረኛው መንገድ እንዲጠቀም ለማስተማር በሚያደርጉት ጥረት አልሰማ ሲሉት በንጉስ ኃይለ ሥላሴ በቀኝ በኩል ይሂዱ እያለ ይለምን ነበር » የሚለው በትህትና በመሆን በአክበሮት ለምኖ /ደብድቦ አይደለም ገላምጦም አይደለም/ ያገለግለው የነበረው አገልግሎቱ  በመቅረቱ። በሁለተኛ ደረጃ በጥፋተኛነቱ ተጠርጥሮ አለበለዚያም እጅ ከፍንጅ ተይዞ እስር ቤት የገባ ተጠርጣሪ ሰብአዊ ክብሩና መብቱ ተጠብቆ አስፈላጊው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ በህጉ መሰረት በሃያ አራት /24/ ሰዓት ውስጥ ለፍርድ መቅረብ ሲገባው መብቱ ተጥሶ ሰብአዊነቱ ተገፎ ሊከበር ሲገባው ተረግጦ በመያዙ እንደ ጠላት  በመተያየት ከመደጋገፍና ወንጀልን በጋራእንደመከላከል ተጠማምደው «ሌባና ፖሊስ ጨዋታ እንደ አይጥና ድመት እየተጫወቱ ይገኛሉ። ካነሳነው አይቀር አንድን የህግ ታራሚም ሆነ ለፍርድ ያልቀረበ ተጠርጣሪ ፖሊስ መደብደቡ ክበሩን መንካት ከየት የመጣ መብት ነው? ብዙ ገጠመኞች ቢኖሩትም አንድ ቀን በአንድ ምሽት በተከታይ ያጋጠመኝን ገጠመኝ ልንገራችሁ ምሽት 1፡30 ፒያሳ (ማዘጋጃ ቤት) ወይም በተለምዶ ሸዋ ዳቦ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ላይ ተክለሃይማኖት አብነት ጦርሃይሎች ታክሲ መያዣ ጋር ሰው ለመሸኘት ቆሜያለሁ ምን እንደተፈጠረ በማላውቀው ሁኔታ ዱላ ተጀመረ ጥሎብኝ ማጣራት እወዳለሁ ጠጋ ብዬ የዱላውን ምክንያትና ማንነት ሳጣራ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የትራፊክ ፖሊስ በዱላ የተቀጠቀጡ አጆቹን ይዘው ገፍትረው መኪና ውስጥ ከተቱት ትራፊኩ ጋቢና ሁለቱ ፖሊሶች ከኋላ ገቡ በጥፋት ላይ ጥፋት የአሽከርካሪው መደብደብ ሳያንስ የባለንብረቱ ንብረት ህብረተሰብን ለማገልገል የአገርን ሰላም ግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ጥሪት በትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ ቢሰማራም በነዚህ  ሥነ-ምግባር የጎደላቸዉና ግዴታቸውን መወጣት በተሳናቸው ባለሙያዎች ሳይሆን ጉልበተኞች የጎን መመልከቻ መሥታወቱ (እስፖኪዮ) ተሰበረ። የሚገርመው መኪናውንና ሹፌሩን ይዘውት ሲሄዱ ረዳቱን (ገንዘብ ያዡን) ይዘው መሄድ አልፈለጉም ጥለውት ሄዱ፤ ማን ይሆን የዚህን ህብረተሰብ መብት የሚያከብረውና የሚያስከብረው? ፖሊስ? መጨራሻውን ማየት አልናፈቀኝም የምሸኘውን ሰው ሸኝቼ ወደ ማዘጋጃ ቤት በኢየሩሳሌም መታሰቢያ ህንፃ በኩል አድርጌ ወደ ሚኒልክ አደባባይ ሳመራ አንድ የጦር መሳሪያ የያዘ ፖሊስ ይመስለኛል የመዘጋጃ ቤቱ ሰላም አስከባሪ (ተረኛ ጠባቂ) ነው አንዱን ሶፍትና ማስቲካ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ በመሸጥ ላይ ያለ ወጣት በሽመል እየደበደበ  እንደከብት ይነደዋል።(በአንድ ምሽት የሆነ ነገር ነዉ የምነግራችሁ) በወቅቱ የነበሩ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ፖሊሱን ምን አደረገህ? እያሉ ይወተውቱታል አላዳመጣቸውም አንዴ በዱላ ሌላ ጊዜ በተጫማው ከስክስ ጫማ እንደጠላት ይከሰክሰዋል። መነሻ ጉዳዩን ባላውቅም የመጠየቁም ዕድል ባይኖረኝም እስኪ እንበልና ይህ ተደብዳቢ የመንገድ ላይ ህገ -ወጥ ነጋዴ፣ ለመንግሥት ታክስ የማይከፍል፣ ልማትን የሚያደናቅፍ፣ አለበለዚያም የጎዳና ላይ ንግድን ተገን በማድረግ አሸባሪ ነው ከፈለግንም በማህበር በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ለመካተት ፍቃደኛ ባለመሆኑ፣ወይንም ለዓባይ ከገቢው ላይ ወጪ አላደረገም ካሽንም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ምክንያት በማህበርም ይሁን በግል የተሰማውን ሀዘን በመጠነኛ ቢል ቦረድ መልኩ ያልሰቀለ ፀረ-ሰላም ፣ተቃዋሚ... ወዘተ እንበል የአገሪቱ ህግ ግን በዱላ፣  በፖሊስ  ከስክስ የመከስከስ ግዴታ ጥሎበታል  ወይ? ፖሊሱስ ቢሆን መንግሥት የህብረተሰቡንና የአገርን ሠላም እንዲያስከብር በቀጠረው ጊዜ የውል  ስምምነቱ ላይ በአጣና አጥንቱን ከሰባበርክ በከስክስ ከከሰከስ በሰይፍ ጉኖን በቡጢጥርሱን ካራገፍክ ደሞዝ ይጨመርልሃል ብሎ ይሆን? ወይስ ደሞዙ እኛን ማስጨነቅ ይሆን? ለሰሚ ግራ የሆነ ነገር ይላሉ እትዬ ግራ ሲገባቸው።
    ታዲያ እነዲህ ከሆነ ነገሩ ፖሊስና ህብረተሰብ ምንና ምነድን ናቸው ትላላችሁ?
Ø እሳትና ጭድ?
Ø የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ?
Ø ሌባና ፖሊስ?
Ø ዓይጥና ድመት?
Ø ኢራቅና ኢራን?
Ø አንድ አካል አንድ አምሳል?
Ø የሁለት ዓለም ሠዎች?
Ø መ- መልሱ የለም?
ግራ የገባ ነገር ነው፤
        መቸስ ፖሊስ ስንል ከትራፊክ እንደልነጠልን ግልጽ ነው ይሁን እንጂ እስኪ ትራፊክን ነጥሉና እንየው ጳጳሱ መጡ ይላሉ የታክሲ ሹፌሮች የተረት አባቶች ደግሞ ራሱ ነጭ እጁ ነጭ ከመንገድ ቆሞ የሰው ኪስ የሚሞልጭ ይላሉ፡ ትራፊክን በነገር ለመንካት ሲፈልጉ፡፡ ምናልባት እንደካህን መመሰሉ ካህን ከቤት ከመጣ ቀኖና ሳይሰጥ አይሄድምና የትራፊኩን ቅጣት ከዚያ አያይዘውታል ነጭ ደፍቶ ነጭ ለብሶ ከመንገድ ዳር ቆሞ የሚገባው ምንም እንኳን ለመንግሥት ቢገባ መነጨቱን አይተው መተረቻ አድርገውታል እኔን የሚገርመኝ ከአሽከርካሪ ጋር ያላችው ፀብ ነው(ለዚያዉም ከታክሲዉ ሹፌር ጋር) አስቁመው ሰላምታ ሲሰጡ እንኳንስ የማስተማር ጥረት የተፈታ ፊት የላቸውም ፊታቸውን ጥለው ወይም ጀርባቸውን ሰጥተው ጥፋቱን ሳይገልጡለት መንጃ ፍቃድ»  ይላሉ ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመኝና የሚያናድደኝ ተሳፋሪ ጭኖ እያየ የአሽከርካሪው ቀርቶ የህብረተሰቡን መብት ወይም መጉላላት ከመጤፍ ሳይቆጥሩ መንጃ ፈቃዱን ወሰደውበት የትናየት ሲጓዙ የማየው ነገር ሙስና እንደሌበት እጠረጥራለሁ ምክንያቱም አሽከርካሪው ወርዶ ለምኖ ለምኖ ሲመጣ ሳይቀጣ መንጃ ፍቃዱን ተቀብሎ ይመጣልና አያስጠረጥርም ትላላቸሁ? እንጃ እኔ ፈርዶብኝ ጠርጣሪ ሆኜ እንደሆነ ፈጣሪ ይወቀው ጠርጣሬአለሁ እንዲያውም ልቤ አሥር ብር ተቀብሏል ይለኛል።
        አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ ቀኑንም አልቀውም ስንት ሰዐት እንደሆነም ዘንግቼዋለሁ ብቻ መሽቷል 3፡00 ሰዓት ገደማ ነው ዝም ብዬ ስጠረጥር ታክሲ አጥተን በስንት ጥበቃ አንድ ከሌላ መስመር የመጣ ታክሲ ጠቅጥቆን ይጓዝ ጀመር አንዲት ሴት ህፃን ይዛ በእግሯ እየተጓዘች ለመነችው የተረፈ የንፋስ ማስገቢያ ቦታ ነበረውና አንድም አዝኖላት አንድም የሚመጣው ሳንቲም የማይናቅ ጥቅም አለውና ያልተፈቀደ ቦታ ላይ (ምልክት ላይ) ጫናት ይኸን ጊዜ «የነጋበት ጅብ» አሉ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ሥራውን አጠናቆ ወደ ቤት በመግባት ላይ ያለ ትራፊክ ያጋጥመዋል አስቆመውና እንደተለመደው መንጃ ፈቃድ በማለት ተቀበለው አሽከርካሪው በአንድም ይሁን በሌላ እንደሚያስቀጣው አምኗል ለመለመን ዝግጁ ሳይሆን ለቅጣት ተሰናዳ። ህብረተሰቡ ግን ትራፊኩን በመስኮት ለመኑት ትራፊክ ኣሻፈረኝ አለ የሚገርመው መቅጫ አልያዘም ነበር እንኳን መቅጫ ፊሽካ አልያዘም (አይታይም)። መቸስ ትራፊክ ጠያቂ የለውም አይደል? መንጃ ፈቃዱን ይዞት አራግፍና መጥተህ ውሰደው አለው ለጥቂት ደቂቃ ያለውን ለማድረግ አልፈቀደም  አሽከርካሪዉ እየቆየ ሲያየው ያ! የነጋበት ጅብ ያሉት ትራፊክ ረጅም መንገድ ተጓዘ አሽከርካሪውም ነገ ሌላ ቀን ነውና እኛን አራግፎ ረዳቱን መኪና እንዲጠብቅ አዞት ትራፊኩን ተከተለው የት ይገናኙ ይሆን? ምንስ ይቀጣው ይሆን?  እኛስ በአንድ እብሪተኛ ትራፊክ በየመንገዱ የማንጉላላው መቼ ይሆን? የትራንስፖርት ችግርስ የሚቀረፈው መቼ ይሆን? ህጉ የሚተገበረው መቼ ይሆን? ትራፊክ ፖሊስና ህብረተሰብ ትራፊክ ፖሊስና አሽከርካሪ ምንና ምን ናቸው?ፖሊስና ህብረተሰብስ? ቸር ይቆየን፡ ፖሊስንና ህብረተሰቡን እግዜርና ምንግስት በፍቅር ይጥመዱን፡፡

ማክሰኞ 18 ዲሴምበር 2012

ከድል ማግስት


        አያ ሆ÷÷ ማታ ነው ድሌ፣
          ድሌ ማታ ነው ድሌ
እያሉ መጨፈር ከዘመናት ጀምሮ ዛሬ ድረስ የድል አድራጎቶችን ጭፈራ ነው። ትዝ ይለኛል ልጅ ሳለሁ ክረምት ሲገባ ሰፈር በሚገኙት ትናንሽ ሜዳዎች ጭቃ በጭቃ በሆነች በካልሲ በተጠቀለለች ፌስታሎች ውስጧን በሞሏት የጨርቅ ኳስ ጭቃ መስለን  ጭቃ አክለን፣ ጭቃ በጭቃ በሆነ ሜዳ ተጫውተን አመሻሽ ላይ ድል ቀንቶን የተወራረድንበትን ቆርኪ በልተን ከሲጋራ ማሸጊያ የውስጠኛው ክፍል (አልሙንየም) የተሰራ ዋንጫ ተሸልመን ሰፈሩን «አያ ሆ ሆ ማታ ነው ድሌ ፣……» በሚለው ጭፈራ ስንቀውጠው ቡድናችንን ጮቤ ስናስረግጥ ተጋጣሚ ቡድናችንን አንገት ስናስደፋና ስናሸማቅቅ፣ የተሸነፍን ቀን ደግሞ በለስ የቀናቸው እንዲሁ በተራቸው ሲያሸማቅቁን ፣ ለሌላኛው ቀን ውድድር በድል ማግስት ባሉት ቀናት በዚያኔው የእግር ኳስ  ሜዳ ቋንቋ ኮንዲሽን(condition) እየተባለ የምናገኛትን ቅራሪ ከተገኘም ጠላ ከመጠጣት ታቅበን የቡድናችንን ድል ለማስጠበቅ ከተቻለም ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ ተመካክረን፣ ስፖርት ሰረተን፣ ተጨማሪ ስልጠና ከኛ ከፍ በሚሉ ወንደሞቻችን ወስደን ፣ከዚያች የጨርቅ ኳስ ሻል ያለ ኳስ ለመስራት አሮጌ አንድ እግር ካልሲ ቃል ተገብቶልን፣ ድጋሚ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ በልበ ሙሉነት እንገባ ነበር። በቃ የትናንት ነገር በሙሉ ነበር አይደል የሚባለው የታሪክ መኅደር ላይ ሰፍሮ ታሪክ እሰኪሆን የሚገርመው ነገር «ነበር» የሚለው ነገር በኛ ዘመን ብቻ ሳይሆን በኛም ሰፈር ይሁን ከኛ ሠፈር ወጭ አገርም እንበል ጥሎብን የጨወታ ነገር ሲነሳ እግር ኳስ አልተሳካልንም እንዲያውም አሁን በቅርቡ በተካሄደው ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችው ከ30 ዓመት በኃላ በመሆኑ ደስታችን የዓለም ዋንጫ የበላን መስሎብን ነበር፣ የዚህ ደስታ ምሥጢሩ ይህ ሁሉ ወጣት እንደ እኔ የልጅነት ጊዜ በሰፈር ጫወታ ከሲጋራ ወረቀት ከተሰራ ዋንጫ በቀር አንስቶ ስለማያውቅ ነው። ግዴለም አይሳካ የዋንጫ ነገር እድላችን ወይም ዕዳ ክፍላችን አይደለም ምናልባት ከኛ ሰፈር ቢቀር ከሌላ ሰፈር እርሱም ይቅር ከኛ አገር ቢጠፋ ከሌላ አገር ከአማራ ከኦሮሞው ከጉራጌው ከደቡብ ከትግሬው ከሰፈር አንዳንድ ሰው ያቺን የጨርቅ ኳስ ሲረግጥና ሲራገጥ ዋንጫ ሲያነሳ ሲጥል፣ ሲጨዋት ሲያጫወት፣ የመስመር የመሀል ዳኛ ሆኖ ሲዳኝ ካደገው ትውልድ ብዙ አይደለም ይኸንን 30 ዓመት ሙሉ አስራ አንደ ሰው ይጥፋ? ምናለ የሰው ልጅ መገኛ ከምንሆንና የቺው ሉሲም የኛ አገር ሰው ሆና ከምታስቅቀን፣ሄዳ ቀረች ብለን ከምታጨናንቀን የእግር ኳስ  አገር በሆንን። እንደው ዝም ብለን የአውሮፓና የእንግሊዝ፣ የአርሰናልና የማንችስተር ደጋፊ አገር እንሁን? ኧረ ምነዉ ፈጣሪስ ምነው ዝም አለን? ቸሩ መድኃኒአለም የነገሩህን የማትረሳ የለመኑንህ የማትነሳ ብዙ አይደለም እባክህ ለአፍሪካ ዋንጫ አስራ አንድ ሰው ሥጠንና ተጠባባቂ ይቆይ ግደለም ከዛም የአፍሪካን ዋንጫ በልተን ከድል ማግስት ስለትህን አንድ ባኮ ሻማ ለማምጣት አብቃን። ጎበዝ ስለትህን ይሰማህ በሉኝ። አሜን ይስማን።
          ወደ ባለፈው ድላችን ወደ «ጀግኖች» ልጆቻችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዝና፣ ከ30 ዓመት በኃላ እነ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ደምሴ ዳምጤ፣... ኧረ ስንቱ ደግሞ የናፈቁትን ድልና ደስታ ሳያዩት እኛ በስታድዮም ተገኝተን በቴሌቪዥን ተመልክተው ደስ እንዲለን ያደረጉት የጀግኖቹ ታሪክ አይረሴ ነው። አዳነ ግርማንና ሳልሃዲን ሰይድ እግዜር ይስጣቸው እነርሱ ባይፈጠሩ በዚያች የጨርቅ ኳስ ተጫውተው ባያድጉ ለዚህ ታላቅ ብሔራዊ ቡድን ባይታጩ ምን ይዉጠን ነበር? ኧረ የሆነው ሆነና የአፍሪካው ዋንጫ እንዴት ሆነ? ቀኑ ቀርቧል አሁንም የድል ማግስቱን ደስታ እንጂ ከድል በኋላ ያለውን የአፍሪካ ዋንጫን የተመለከተ ዝግጅትም ይሁን የወዳጅነት ጨዋታ የለም። እነ ናይጄሪያን የመሰሉ የኛ ተጋጣሚዎች ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትም የወዳጅነት ግጥሚያም አውሮፓ እንዲገቡ እስከ ዋንጫውም በዚያው ዝግጅት እንደሚያደርጉም ሚዲያዎቻችን ያለ መታመኑ ጠዋት ማታ እየዘገቡ ይገኛሉ የኛዎቹስ የት ነው ያሉት? እንደሚባለው (ወሬ አርጎ ያስቀረውና) እንደ ሴካፋው ዋንጫ እንደ ጨርቅ ኳስ እንኳን ከቅራሪና ጠላ መታቀብ አቅቷቸዋል የሚባለው እውነት ይሆን? ኮንዲሽን፣ትሬንግ፣ የወንድማማችነት ግጥሚያ ምናምን ቀረ እንዴ? እንደከዚህ በፊቱ ወር ሳምንታት ሲቀሩት ይሆን ብሔራዊ ቡዱኑ ተሰባስቦ ተለማምዶ ለድል የሚበቃው? ሰዎች ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራና ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብቻ ተሯርጦ አሰልጥኖ ባለሃብቶች ከአሸነፋችሁ ብለው ቃል ገብተው ሸልመዉና ጋብዘው ብቻ ታሪክ ይቀየር፣ ድል ይገኝ ይሆን? አይታየኝም።
          ለኢትዮጵያ ህዝብ 30 ዓመት ጠብቆ በ31ኛ ዓመቱ ለዋንጫ ማጣሪያ ማለፍ ብቻ በቂ ድል አይደለም፤ ደስታችን በዚህ መቆም የለበትም። ትልቅ የታሪክ የቤት ሥራ (የአፍሪካ ዋንጫን) አስቀምጠን መጠቶ ቤት ልንገኝ የተጣለብን ኃላፊነት አይፈቅድም ቆይ ምን ተገኘና ነው ስፖርተኛ መጠጥ ጠጪ፣ሰካራም የሚሆን እንዴትስ ሆኖ ነው የ80 ሚሊየን ህዝብ አደራ ተሸክሞ ሲጠጣ የሚመሸው እንዴትስ ነው መጠጥ ቤት የሚገባው? ለመሆኑ ጉሮሮአችን እንኳን አልኮል ሊንቆረቆርበትና ልንሰክር ይቅርና እንቅልፍ በዓይናችን ሊመጣ ሃይልና ብርታት ይኖረዋል? ወይንስ ይህ ድል ሆነና በቅቶን ነጋና ጮቤ እንረግጣለን? ሌላው ይቅር ደስታችንንም ይተውት የሆነው ሁሉ ሆኖ ምኑ ነው የመጠጥ ደስታው? እንዴት ልንመርጠው ቻልን? መስከሩን ነው? መንገዳገዱንና በሰው ፊት መቅለሉን ነው? ወድቆ መጎዳቱን አዕምሮን መቆጣጠር ተስኖን ከሰው ጋር መጋጨትና ማስቀየሙን  ነው ወይንስ ምኑን ወደድንለት?
          ፌዴሬሽኑስ ምን እያደረገ ነው? ሥለጠና አያስፈልግም? በጀት የለው ይሆን እንዴ? ማን ያውቃል? ወይ እንደ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችን የዜግነት ችግር ይኖርባቸው ይሆናል? (በሌላው ዘርፍ የሆነ ችግር ሲነሳ ሀሜት ከተማዋን ሲንጣት እንደዚህኮ የሆነው እገሌ የተባለ ሚኒስተር ወይም ዴኤታ በአባቱ ወይም በእናቱ ኤርትራዊ ስለሆነ ነው የሚባል የልማት እንቅፋት የሆነ ልማታዊ ቀልድ አለ፤) ታዲያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ራሱ የኢትዮጵያዊነት ችግር ይኖርበት ይሆን? መቸስ ያን ሰሞን ማነች ይህቺ ሱዳን ከምትባለው ጉረቤት አገር ልነጋጠም ያልን ሰሞን 31 ዓመት ከመጠበቃችን ይልቅ የዕሁድ ሠዓት እንደረዘመብን ባያውቁ ሳይሰሙ አይቀሩም፤ ለነርሱም ቢሆን በዘመናቸው የተሰራ የሚመዘገብ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ አልፈለጉ ይሆን? ማን ይህን ከድልማግስት እዚም ያደረገባቸው? ለነገሩ ድልና የድል ማግስት በኢትዮጵያ ችግር አለባቸው ሰሞኑን ሰፈራችን አንድ ነገር ሲገርመኝ ነበር የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ለማሰራት ገንዘብ ለማዋጣት ተስማምተን ማዋጣት ከአሥር ዓመት በላይ ይሆነዋል፣ ረጅም ጊዜ እንዲያውም በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች በቃ ገንዘባቸውን ይመለስልን እያሉ ሲማረሩ ከርመው አሁን መንገዱ ከተሰራ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል እንኳንስ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ መንገድ ብሩ ከመበላት አምልጦ መንገዱ ተሰርቶ ሲያልቅ ይቅርና ልጁ KG ጨርሶ አንደኛ ክፍል ሲገባ ይመረቃልና እኛም የአሥር ዓመት ተቀማጭ ገንዘባችን ለቁም ነገር ሲውል የማያገባቸው ግን በገቡበት ሰው አማካኝነት ሊመረቅ ሁለት ሁለት መቶ ብር ከአመት በፊት ተዋጣ ቀን ይመርቁት ሌሊት ሳናውቅ ተራዝሟልም ሳንባል ከረምን። እርም ብለን የተውነውን የመንገድ ምርቃት እንደ አዲስ ከቀበሌ መጥተው ከአንድ ጎረቤቴ ጋር ቆመን እየተጫወትን «መዋጮ» ማለት ሰውየዉ«የምን መዋጮ» ዓይናቸውን በጨው የታጠቡትም (የመንገድ ማስመረቂያ» ሰውየው ከረር በማለት (መክረር እኛ ሠፈር ብርቅ አይደለም ኑሮ ያለከረረው ማን አለና) «የትኘውን የቀለበት መንገድ እየፈረሰ ያለውን ከመስቀል አደባባይ ሳሪስ ያለው የሚፈርስ መንገድ የማስረሻ ምርቃት » በማለት በአሽሙር መልክ ጎሸም አደረጓት።
«አይ አይደለም የሰፈራችሁን»
«ከሁለት ዓመት በፊት የተሰራውን»
«አዎ » እያለች ስለተረዷት ፈገግ አለች።
«ታዲያ ለምን አዋጣለሁ»
«ለምርቃቱ ነዋ ሰሞኑን ባለሥልጣኖች መጥተው ይመርቁታል»
«ድጋሚ.» ብለው ከዓመት በፊት የከፈሉበትን ደረሰኝ ከኪሳቸው አውጥተው አሳዮዋት፤ ነገሩ ሥላልተሳካ
«ይቅርታ» ብላቸው ለመሄድ ስትል 
«ቆይ ነይ ወደዚህ፤ ለመሆኑ ማን ነው የሚመጣው»
እየሳቀች «እኔንጃ ማን እንደሚመጣ እንኳን አላውቅም»
«እኛንም ይፈሩናል እንዴ ማንነታቸውን ሳያሳውቁ ድግስ ደግሱና ድንኳን ጥላችሁ ጠብቁን የሚሉት? እኛኮ የልማት አጋሮቻቸውኮ ነን እነርሱ ያቅዳሉ እኛ አዋጥተን እንሰራለን ነው ወይስ እንደ ቻይና ማበደር ነበረብን? ለማንኛውም የሚመጣውን ባለሥልጣን አትመርቅ ርገመው አደራህን ረግመኸው ሂድ የመረቃችሁትን አንድም የረባ ነገር የለምና በይልኝ ጎሽ የኔ ልጅ ።»
          የቀበሌዋ የመዋጮ መልዕክተኛ እየሳቀች (እየፈራች ነበር የምትስቀው ነገሩ የሚያስቅ ሆኖባት ነው እንጂ) ወደ ቀጣዩ ቤት አመራች፤
          በዚህ ሰሞን የኛ ሰፈር የዉስጥ መንገድ ተመረቀ፣ ቶታል ጎጃም መውጫ ከውንጌት ጋር የሚገጥመው ቀለበት መንገድ ተመረቀ፣ ሰሜን መናፈሻ ጋር ቀበሌው ውስጥ የተሰራው ህነፃ ተመረቀ፣ ከሰሜን ሆቴል ዝቅ ብሎ ያለው 3ኛ እየታባለ የሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ተመረቀ ሌላም እኔ የማላውቅ ምርቃት በየሰፈሩ ክፍለ ከተማውና በየክልሉ ይኖራል ግድ የለም ይመረቅ እንኳንስ ተሰርቶ ያለቀ ነገር መመረቅ ይቅርና የማይሰራ ነገርስ መሰረት ድንጋይ ይጣልበት የለ፤ (እንዲያውም ነገርን ነገር ያነሳዋልና እኛ ሰፈር አንዴ የበሬ ግንባር የምታክል ሜዳ አለች አንዳንዴ ባለሃብቶች ህንፃ ሲገነቡ ሌሊት ሌሊት በድብቅ አፈር ይደፋባታል ጠዋት ጠዋት ወጣቶች ስፖርት ሲሰሩ ኳስ ሲጫወቱ አፈሩ እየደናቀፋቸው ይደፋበታል እሁድ እሁድ ደግሞ ኸየቦታው ጎረምሶች መጥተው በየቡድን በየቡድኑ ይራኮቱባታል። ከዚህ ሁሉ የሚገርመኝ ለምን እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ የመሰረት ድንገይ ተጥሎበታል ያኔ የመንገድ ምርቃቱ ቀን የሆነ  ነገር ጨርቅ ለብሶ ተሰቅሎ አየሁና ነገሩ እንዴት ነው ብዬ ወሬ ለመቃረም ጠጋ ብዬ የሰፈር ሰው ጠየኩ ምን እንደሆነ የሚያውቅ አጣሁ አሁንም ፈቅ አልኩና የሰፈር ሱቅ በር ላይ የቆሙ ምንድን ነው አልኳቸው እነርሱም በፊት የነበረውን በእመነ በረድ የተጻፈውን ማንሳታቸውን እንጂ አዲሱ ደሞ ምን እንደሆነ ምን እናውቃለን ያው እንደለመዱት ሊበሉበት ይሆናል በማለት ምሬት ሲጀምሩ ነገርና ምሬት እንደ ጦር ስለምፈራ የምወዳትን ወሬ ፍለጋ ተመልሼ ወደዚያው ወደተሰቀለው ተመለስኩ ይኼ ሁላ ለወሬ ምንድን ነው እንደዚህ መሆን? ትሉኝ ይሆናል ታዲያ እኔ ቃርሜ ካላመጣሁ ማን ያወራችኃል። ለማንኛውም ያቺ የተሰቀለችዋን ነገር ጨርቁን ንፋስ  ሲያወዛውዛት የሚገርም ትልቅ ፎቶ ግራፍ አየሁ ምን አትሉም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እስታዲዮም  ልብ በሉ እኛ ሰፈር ውስጥ እዚያች የበሬ ግንባር የምታክል ሜዳ ላይ፡ ተስፋ ቆረጥኩና ቦታውን በሊዝ ቢሸጡት ይሻላል እያልኩ እየተማረርኩ ጥዬው ሄድኩ እርሱም የመሰረት ድንጋይ ተጣለ አሉ አንድ ነገር ልበላችሁና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባና ቅንፉን እንዝጋው ዞሮዞሮ ከቤት አይደል የሚባለው ዛሬ ዛሬ ወደሰፈር ስመለስ ያ ተሰቅሎ ያየሁት የእስቲዲየም የጨርቅ ላይ ዕቅድ እንደ ጠዋት ጤዛ ጠፍቶ አገኘሁት ታዲያወገኔ እውነት ይህ እስቴዲየም ይሰራል ትሉኛላችሁ? አትጨነቁ ሆዴ ነግሮኛል አይሰራም።)
          መመረቁን ይመረቅ መሰረቱም ቢሰራም ባይሰራም ይጣል ግድየለም ባይሆን እመነ በረዱን ለሚያዘጋጁት ሊሾውን የሚሰሩት የስራ እድል ተፈጥሯልና ግን አንድ ጥያቄ አለኝ አንድ ቦታ ላይ ሁለት ሶስት የመሰረት ድንጋይ ከሚጥሉ ሌላ መጣያ ቦታ የለም ወይ? ከጠፋ ከጠፋ አዲስ አበባ ውስጥ ስንቱ ቤት የመሰረት ችግር አለበት አይደል እንዴ እርሱን ለምን አያጠብቁበትም። (ኢትዮጵያዊ ምክሬ ነው ተግሳፅ አይደለም) ወይስ ግራውንድ ፕላስ የሚሰራ ልማት ይኖረዋል እንደኮንደምንዬም? ጥያቄ ቁጥር ሁለት እኔ አልኩት አላልኩት የምርቃቱ ሥነ -ሥርዓት አይደነቀፍም እንዲያው ለነገሩ አንድ ሥራ ሥንሰራ እንዳልተንከረፈፍንና የሰው ጨጓራ እንዳልመለጥን ለምርቃ እነዲህ ማጣደፍ ምን የሚሉት ነው? አንድም ደግሞ ትንሽ ነገር በሰራን ማግስት የምርቃቱ ሽርጉድ ሳያንስ የመዲናውን ኔትወርክ ስለርሱ በማውራት ማጨናነቅ ምን የሚሉት ነው? ያካበደን አልመሰለንም? ወይስ ከዚህ በኋላ የምንሰራው ነገር የለም? ይህ  እንዴት የአንድን ታላቅ መሪ ራዕይ ማሳካት የምርቃት የፌሽታ የደስታ ጋጋታ ነው እንዲህ ነው ፈለግ መከተል? ቆይ እኛ ኢትዮጵያን ከድል ማግስት ለሌላ ድል ከመዘጋጀት ይልቅ ያቺኑ ድል ይዘን አርባና ሰማንያዋን እያወጣን ጮቤ የምንረግጠው ለምንድን ነው? እስከመቼሰ ይቀጥላል?
          አንድ ነገር ስጠረጥር ድሮ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለን የመጀመሪያውን ፈተና እንደምንም አሥር ከአስር አለበለዚያም ዘጠኝ ወይንም ስምንት ካመጣን እርሷን ለቤተሰብ እናሳያለን ጉራችን መከራ ነው ቤተሰብም ልጄ ጎበዝ ነው አስር ከአስር አመጣ ብሎ ሰፈር ውስጥ ለቅሶና ድገስ ላይ ሳይቀር ያወራል። ከረሜላ ወይም የሆነ ነገር እንሸለማለን አባትም እርሱን አትናገሩብኝ እናትም ከሌሎች ልጆቿ ለይታ ለዚያ ልጅ ምርጥ ምርጡን ስትል ልጅየው ድጋሚ አስር ለማምጣት አይጥር፣ ፈተናም እንዳለበት የሚናገረው ተው አጥና ብሎ የሚመክረው የለም እንዲያውም የተቆጣውን ሰዉ ተመልሰን በቁጣ እናስደነግጠዋለን የምንባንነው ወላጅ አምጣ የተባለ ቀን አለበለዚያም ሰኔ 30 መጥቶ የልጆች ውጤት ተሰጥቶ መውደቁን የሰማን ቀን ምን ማድረግ እንዳለበት ከቤት አልፎ አክስትና አጎት ጉረቤት ድረስ መነጋገሪያ ይሆናል ይህንንም የታደለው ነው ባኖ ወደ መፍትሄና ጥፋትን ወደማረም የሚመጣው የባሰበት በመምህራንና በትምህርት ቤት ያመካኛል፣እኔ ልጄን አውቀዋለሁ እያሉ ከአስር አስር የመጣበትን ውጤት አንጠልጥለው ይጮሃሉ ከዘጠና ግን ሥንት እንዳመጣ በጭራሽ አያውቁም ያጥና አያጥና አያውቁም፣ክፍል ገብቶ ይማር አይማር የቤት ሥራ ይስራ አይስራ አያውቁም፡ ሌላው ቀርቶ ያንን አስር ከአስር እንኳን እንደመጣ አያውቁም የእግር ኳሱም ይሁን የልማቱ ጉዳይ ብዙም አይለይም አንድ ናቸው። ለመሆኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ማለፋችንን እንጂ እንዴት እንዳለፍን በጠቅላላ ካስገባነው ይልቅ የገባብን ጠቅላላ ግብ ስንት እንደሆነ ሁሉንም ትተን ከሱዳን ጋር በተጫወትን ምሽት የመጨረሻዋ ፊሽካ ስትነፋ የገባችሁ ግብ ተቆጥራ ቢሆን ኖሮ ድል አልነበረም ልማታችንን ስናስበው የክሊኒኩ መገንበታ እንጂ ሲገነባ ስንት እንደፈጀ ፣ መንገዱ ሲዘረጋ መንገዱ ማለቁን እንጂ ስንት ዓመት እንደፈጀ ብናስብ እንኳንስ ጮቤ ልንረግጥና ልንፈነጥዝ ይቅርና ባለሥልጣኑ በቦታው ቆሞ  ባልመረቀ ስለዛ መንገድም ደግሞ አንስተው በሚዲያ ባላወሩት ነበር። ነገር ግን እንደትልቅ ድል ሌላውን ልማት አቁመን በዚህ ድል መጨፈርን ሞያ አድርገናል።
          ከዚህ ቀደም ካለው ስህተታችን ተምረን ለነገ ተግተን የምንሰራ ቢሆን ኖሮ በደርግ ዘመን(በ1977 ዓ.ም) የነበረውን ድርቅ ተመልከተን በኢህአዴግም ደርቅ ተምሶ ባልመጣ ነበር፤ በአንዱ ክልል ያስቸገረ አገር የፈታ የወባ ወረርሽኝ እዚያው  እንዳለ በቅጡ ተረባርበን እንደሚሆን አድርገነው ቢሆን ዛሬ በአራቱም ማዕዘን ፋታ አይነሳንም ነበር። ድሮ በአባቶቻችን ዘመን ጣሊያንን በጨበጣ ድል ማድረጋችንን መታሰቢያ ባናደርግና ተምረንበት ቢሆን ከአርባ ዓመት በኃላ ተመልሳ ጣሊያን ባለደፈረችን፣ በደርግም ከሱማሌ ጋር የነበረው ችግር ከትናንት መማር ቢኖርበት እስከ ኢህአዴግ ዘመን ባልዘለቀ ነበር፣ አሁንም በዘመነ ኢህአዴግ ከኤርትራ ጋር በባድመ ምክንያት ያ ሁሉ ደም የፈሰሰው ያ ሁሉ ወጣት የተሰዋው ያ ሁሉ የአገር ሃብትና ንብረት ጊዜን ጨምሮ በከንቱ የወደመው ኢህአዴግ ከደርግ ውደቀት በኋላ መማር ተስኖት በድል ማግስት ባሳየው ደካማ ጎን ምክንያት ነው።
          ለኢትዮጵያ ህዝብ ለኢትዮጵያ ወጣት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ የነማንችስተር (ዩናይትድና ሲቲ) የአርሰናልና የባርሴሎና፣ የቼልሲና የሊቨርፑል...ድልና ዋንጫ ምናችን ነው? የደቡብ አፍሪካ የኢፓርታይድ ነጻነት ፣ የአሜሪካ ሰላማዊና ዲሞክራሲያው ምርጫ፣ የቻይናና የኮርያ ፈጣን እድገት... ምናችን ነው? እኛን የራበን፣ እኛን ያመመን፣ እኛን ያናፈቀን የራሳችን የአገራችን የህዝባችን የወገናችን የሆነ ልማት፣ ዲሞክራሲ፣ፈጣን ዕድገት ሰላማዊ ምርጫ፣ ዘለቄታ ያለው ድል (ተከታታይነት ያለው) ሰላም ነዉ።የሃይማኖት ነፃነት፡ የፖለቲካ እኩልነት…..ወዘተ ናቸዉ፡፡ከድል ማግሰት ሌላም ዉድድር እንዳለብን ከመዘንጋት ይሰዉረን፡፡

ለቀጣይ ትውልድ ምን እናውርስ?


          አንድ ትውልድ ለመፍጠር ቢያንስ ሃያ እና ሰላሳ ዓመት ያስፈልገዋል። ዓብይ ርዕሳችን ምንም እንኳን ሥለትውልድ ቢያወሳ ርዕሰ ጉዳያችን ግን በጥቂት ሶስት ነገረ ልብ ልንል ግድ ይላል።  ቀጣዩ ማለት ማን ነው? የትኛውስ  ትውልድ ነው? ቀጣዩ ትውልድ የምንለው ጊዜስ በራሱ ከመቼ ይጀምራል? የሚሉት ጥቂቶች ናቸው። ለምን ይህንን ጉዳይ እንዳነሳ ያስገደደኝን ነገር ማካፈሉ ጥቂት ሥለተነሳሁበት ነገር ማብራሪያ የሚሰጥ ይመስለኛል። ጊዜው ምሽት 3፡15 ሠዓት ነው የሰዉ ልጅ ወደቤት ለሚሰባሰብበት ተጠናቆ የሚገባበት ሰዓት ነው (በጊዜ ወደ ቤታቸዉ የሚገቡትን አይመለከትም፤ ችግር፣የማያስገባቸውንም የመጠለያ ችግር አጋጥቸው መኖሪያቸውን ጎዳና ያደረጉትንም አያከትትም።) ይህንና የሚገቡትን ይዘን የማይገቡትን ትተን ጎዞ በታክሲ ወደ ቤት፡፡ የአብዛኞቻችንን መጓጓዣ የሆነውን ታክሲ ወይም ሌሎች የትራንሰፖርት አገልግሎት መስጫዎችን ተጠቅሞ መሄድ ግድ ይላል፡፡ ጎዞዉ ሊጀመር  ሰው መላት ግድ ይላል ታክሲዉ  ከያዛቸው ሰዎች መካከል በአንድ መቀመጫ ላይ የተቀመጥነው አራት ነበርን ሶስት ትናንሽ ልጆች በግምት እድሚያቸው አምስት፤ ስድስት እና ዘጠኝ አመት ናቸው። ከሥራ ነበር የሚመለሱት መቼስ በጠፋ ስራ እለት እለት የስራ አጥ ቁጥር በሚጨምረበትና ኮብልስቶን ለማንጠፍ ለዪኒቨርስቲ ተማራቂዎች ሞያ በጠየቀበት አዲስ አበባ እደሜያቸው ከአስር አመት በታች በሆኑ ህፃናት ከስራ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኃላ ወደ ቤት መግባት አጃኢብ የሚያስብል ጉዳይ ነው። ነገሩ ወዲህ ነው የዘጠኝ አመቱ ልጅ የመጣው ከጎጃም ነው አመት ከመንፈቅ ሆኖታል አዲስ አበባን ሀገሩ ካደረገ ወላጆቹ ይህን አለም መሰናበታቸውን እንጂ መቼ እንዳረፉ ጊዜውን በውል አያውቀውም ድሮ ነው የሞቱት ይላል የወላጆቹ በሕይወት አለመኖር ሲገልፅ ሁለቱ ጨቅላ  ህፃናት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ የአክስትና የአጎት ልጆች ናቸው እንደሱ አገላለፅ በእነሱ ትከሻ ላይ ነው ያለሁትም ብሎኛል፡ በአክስቱና በአጎቱ ላይ ሁለቱ ህፃናት ግራና ቀኝ ጉልበቱ ላይ ተኝተዋል፡፡ እሱ በሚያንቀላፋበት ሰዓት እሱ ተሽሎ የሁለት ህፃናትን እንቅልፍ በእቅፉ ለማስተናገድ ሕይወት አስገድደዋለች።
          ላወራቸው የምፈልገው ጉዳይ ስለነበረ ቀሰቀስኳቸው
ከየት ነው የምትመጡት?
ከሥራ፤
የምን ሥራ?
ማስቲካ ስንሸጥ ቆይተን
ለምን ትሸጣላችሁ? (አይባልም ግን ጥያቄ ማንሳቴ ካልቀረ ብዬ ቀጠልኩ እንጂ) ተቀባብለው በሚያሳዝን ሁኔታ መለሱልኝ ያሉኝን አልነግራችሁም ሁሉም ቤት አለና።
ስንት ሸጣችሁ?
ለሶስት ሰላሳ ብር ( ልብ በሉ ጠቅላላ ገቢያቸው ሰላሳ ብር ነው ዋናው ስንት እንደሆነ ትርፉ ስንት እንደሆነ ሂሳቡን ምቱልኝ እነዚህ ልጆች ስንት ሰዓት ነው የወጡት? ምን በልተው ዋሉ? እራታቸውንስ ምን ይበሉ ይሆን?... እግዚአብሔር ይወቀው።)
ስንተኛ ክፍል ነህ? (ለትልቁ ልጅ ያቀረብኩለት ጥያቄ ነው)
አራተኛ ክፍል
ጎጃም እያለህ ትማር ነበር ?
አልማርም ወላጆቼ ከሞቱ ቆይተዋል ብዬህ የለ?
ታዲያ እንዴት አራተኛ ክፍል ገባህ?
አምና (2004 ዓ.ም) አንደኛ ስገባ የትምህርት ሁኔታዬን አይተው አሳለፉኝ አሁንም ጎበዝ መሆኔን ሲያዩ ሶስተኛ ክፍል ገባሁ መጨረሻ ላይ ግን የሚቀጥለው አራተኛ ትገባለህ አሉኝ አሁን (በ2005 መሆኑ ነው) አራተኛ ክፍል እየተማርኩ ነበር ።
          ታጠናለህ ወይ እንዴት ጎበዝ ልትሆን ቻልክ?
(ለኔ ጥያቄ ነበር የእኔንና የእሱን ጥያቄ ከፊሉ ሰው እያዳመጠ ነው።)
          አጠናለሁ አሁን ስገባ እነሱ ይተኛሉ (የተኙትን ሁለት ህፃናት እያመለከተ) እኔ ወደ ጥናት ነው የምሄደው( እዚህ ጋር የራት ነገር አልተነሳም እራት ይበላ ይሆን ካልበላ በምን አቅሙ ያጠናል ጥናት እንደሆነ በልቶም አልሆነም «ጎበዝ» ብዬ ነበር ማለፍ የምችለው ከዚህ ወዲያ አቅሙ የለኝምና)
          አዲስ አበባ እንዴት ልትመጣ ቻልክ?
ጠፍቼ አጎቴን ተከትዬ ነው የመጣሁት
          ለምን ? እንዴት?
(ታሪኩ ብዙ ነው የነገረ ለፅሁፍ እንዲመች ግን ላሳጥረው)
ከእነሱ ጋር ለመኖር ሰው የለውምና አንድም የሚያበላው አንድም የሚያስተምረው ከሀገሩ ተሰደደ በምሽት አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከኑሮ ጋር ትግልን ማስቲካ በመሸጥ ተያያዘው።
          ኑሮ ኖርክ ተብሎ የእለት ጉርሱን የአመት ልብሱን መሸፈኛ ሊያመጣ ነጋዴ ሆነ፤ መምጣት ሳያሻው ህይወት ወደዚህ ምድር ጠርታዉ ፍዳውን ሊያል፤ እንደ ሰው ተፈጥሮ እንደ ሰው ሳይከበር ሊኖር ትንቅንቅ ተያይዞታል ፍጥጫውን ቀጥሏል እድሜህ ስንት ነው? የሚለው ጥያቄ እንኳን በቂ ምላሽ አልነበረውም እኔንጃ አላውቀውም ከማለት ውጭ።
          አለም ለህጻናት መብት ይከበር፣ ጉልበታቸው አይበዝበዝ፣ ግፍ አይዋልባቸው፣እነሱ ለመኖር፣ለመብላት፣ለመማር መብት...ወዘተ አላቸው፣ በሚባልበት 21ኛው ክ/ዘመን በሺህ የሚቆጠሩ ህፃናት ግን ጉልበታቸው ያለአግባብ እየተበዘበዘ፣ የመማር፣የመብላትና የመጠጣት መብታቸዉ እየተነፈገ፣በበሽታ እየተጠቁ፣ ለስደት እየተዳረጉ፣... ይገኛሉ።
          ይህንን አስከፊ ጉዳይ በምን እንቀይረው? እንዴትስ እንቀይረው? ቀጣዩን ትውልድ ምን እናወርሰው? ...
          ይህ ትውልድ ወደድንም ጠላንም ተፈጥሯል ህይወቱን ልናስቀጥለው ግድ ይላል፤ ከጨቅላዎች ህፃናት እስከ ወጣቱ ትውልድ ድረስ ያሉት የነገውን አለም ተሳታፊና ተረካቢዎች ናቸው። ታዲያ ይህ ትውልድ መጪው የዚች አለም ዕጣ ፋንታ በእጅ ያለ ከሆነ ዓለሙን የሚያስቀጥለው እሱ ከሆነ አንድም የትኛውን ዓለም እናውርሰው? በሌላ በኩልም እራሱ ትውልድስ ከእኛ የሚወርሰው ያዘጋጀንለት ምን ነገር አለ? ረሃብ፣ጦርነት፣ድርቅ፣ስደት፣የጎዳና ላይ ኑሮ፣ልመና፣ለጉልበት ብዝበዛ፣ወይም የተሻለች ብሩህና፡ ልምላሜ፡ እድገትና ብልፅግና የሞላባት ዓለም???
          ለእነዚህ ሶስት ህፃናት ከአንድ ቤት ጉልበታቸው መበዝበዝ፣በምሽት ጎዳና ላይ ማስቲካ መሸጥ፣ ሲደክሙ አምሽተው 30 ብር ብቻ ይዘው መምጣት፣ሳይበሉ መዋልና ማደር፣ወዘተ ምንን ያመለክታል? ፍትህ መኖሩን? የህፃናት መብት መከበሩን? ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ ፍሰት መኖሩ ወይስ ደሃና ረሃብተኛ አገር መሆኗን በሁለት ዲጂት አኮኖሚያችን ማደጉስ? ለእነዚህ ህፃናት ትርጉሙ ምንድነው? ለተከታያይ አመታት አኮኖሚያችን ማደጉ ለቀጣዩ ትውልድ ለምግብ ፍላጎት ካላሟላ ማደግ ቢቀርስ? ማደግ ማለት ለህንፃ መገተር ይሆን? ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው «ማከራየት ጀምረናል» የሚል ፅሁፍ የተለጠፈበት ህንፃ ነው?
          ይዘው የመጡት 30 ብር ዋናውን ጨምሮ የቤተሰብ እራት ያበላቸዋል ወይስ የኑሮ ሥጋት ይጨምራባቸዋል? ይህ 30 ብር የዚህን ቤት ህይወት ይታደግ ይሆን? ይሕ ህፃን ለትምህርት ብሎ የተሰደደውን ስደት ድካም ዋጋ ይከፍለው ይሆን? እንደእኔ እይታ ከዚህ ባሻገር አንድ ነገር ተመለከትኩ ምን? አትሉኝም ከንቱ ልፋት እንጂ ተመጣጣኝ ክፍያ እንደማይከፈለን ማነው በስራው መጠን ኢትዮጵያ ምድር ላይ የተከፈለው ከሌባ ከሙሰኛ እና ከአጭበርባሪ በቀር ለምንድን ነው ለመንግስት ሰራተኛ በስራው እርካታ የሌለው ለምንድነው ዛሬ ዛሬ የቤት ሰራተኛ ማግኘት አዲስ አበባ ላይ ችግር የሆነውና ወጣት ሴቶች ከገጠርና ከከተማ ወደ አረብ አገር የሚፈልሱት? ሰው ከመስሪያ ቤት  መስሪያቤት ለምን ይፈልሳል? ክፍያ ስለማይከፈለው ነው? ይህንኑ ነው እነዚህ ሶስት ነፍስ ያላወቁ ህፃናት ላይ ያየነው  ጉልህ ነገር። እንዲያውም በአንድ ሰሞን ዐብይ መወያያ የነበረው የአየር መንገዳችን ፈጣን እድገት የመጣው በስራ ብቻ ሳይሆን ለሰራተኞቹ  የድካማቸውን ያህል ተመጣጣኝ ክፍያ ባለመክፈሉና ጉልበታቸውን በመበዝበዙ ነው የሚል ተቃዉሞ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር። እውን አየር መንገድ ብቻ ነው? የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ወዘተ...ውስጣቸው ቢፈተሽ የሰራተኞቻቸው ብሶት ቢፈተሽ ደሞዝ አይከፈለንም ነው ጥያቄው ባንኮቸስ ብንል ኧረ ስንቱን ሆድ ይፍጀው። በኢትዮጵያ ጉልበት ብዝበዛ፣ በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሥራ አጥ፣ ረሃብ፣በሽታ፣ስደት፣...
          የሆነዉ ሆነ ቀጣዩን ትውልድ ምን እናውርስ? እርስ በርስ የተከፋፈለች አገር? በሽታና ጦርነት ያደቀቃት አገር ? መቼስ የቀጣዩ ትውልድ ልመናን አናወርስም ቃል ገብተናልና ልማትን እንደምናወርሳቸው እርግጠኞች ነን እኔ ፍርሃት አለብኝ እኛ ነገ እንደክማለን፣እናረጃለን እናልፋለን፣ ... ይህ ትውልድ ግን ያለኃጢአቱ ወላጁን በወባ፣በካንሰር፣በቲቢ፣በHIV ኤድስ ወዘተ ከማጣቱ ወላጅ አልባ ከመሆኑ ባሻገር የበሽታው ተጋላጭ የሆነው ጥቂት አይደለም እድሜ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የቀረቱንስ ማን ሰብስቦ ያሳድጋቸው? ማን ነገን ያውርሳቸው? ማን የነገ ተተኪና ወራሽ እንዲሆኑያስችላቸዉ? ማን ዛሬን ብርታት ይሁናቸው? ሳይሰደዱ ባህር ማዶ ሳይናፍቁ አገሬን ብለው እዚች ወንዝ ዳር አስቀምጣ ለምታስጠማ፣ ለም መሬት ላይ አስቀምጣ ለምታስርብ ኢተዮጵያን አልምተው በልተው  ጠግበው ጠጥተው እረክተው እንዲኖሩባት ከመንገድና ከህንፃ ባሻገር የተለየ ልማት ማን ያሳያቸው? ቀጣዩ ትውልድ እንደባለፈው ተስፋ ሳይሆን ምልክት ተጨባጭ ነገርን ይሻልና። ንጉሱም ደርግም ተስፋ በተስፋ ሲያደርጉን አልፈዋል ከኢህአዲዴግም ተስፋ ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ የሚዳስስ ይፈልጋል፡እንፈልጋለን፡፡ በዘጠኝ በአስር በአስር አንድ በመቶ ኢኮኖሚ የማደጉ ዜና ሳይሆን በቀን ሶስቴ መብላትን በምግብና በመጠጥ እራስን መቻል ትውልዱ ይሻል። እንፈጽማለን፡እናስፈፅማለን፡ እናስቀጥላለን የሚሉ ተስፋዎች ሳይሆን የተፈጸመና የሚቀጥል ነገር ሊወርስ ይገባዋል ይህ መጪ ትውልድ።
          እርግጥ ነው መንገዱ ተገንብቷል ህንፃዎች ተሰርል ትምህርት ቤቶች፣ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ታንፀዋል ነገር ግን ቀጣዩን ትውልድ ለመንገድ ርዝማኔ ሳይሆን የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍለት ይሻል፤ ህንፃዎች መገንባት ብቻ ሳይሆን ለመጠለያ ችግር መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እንዲዳረስ ይፈለጋል። እንዲሁ የተገነቡት ትምርህት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርት የተስተካከለ የትምህርት መርሃ ግብር እንዲሰጠው በጉጉት ይጠባበቃል ሆስፓተሎቹም ሆኑ ኪሊኒኮቹ በቂ አገልግሎት ለሁሉም ከተሟላ መሳሪያና ባለሙያ ከተገቢው መድሃኒት ጋርና በመልካም አስተዳደር የመጠበቅ ጉዳይ ነው አለበዚያ ለህንጻ መገተር ጤና አይሆንም ከምንም በላይ ከመሰረታዊ ነገሮች አንዱ ንጹ ውኃ  ያለው አካባቢ ልናወርሰው ይገባናል ውሃ ለማግኘት ወረፋ፣ ዳቦ ለመግዛት ወረፋ፣ ለትራንስፖርት ይዘን ለመሄድ ሰልፍ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊዘልቅ አይገባም ለሁሉም ሰው መልእክት ነው።
          ለቀጣዩ ትውልድ ልናወርሰው ከሚገባቸው አንገብጋቢ ጉዳይ ውስጥ እንደ ዳቦና ውኃ በሰልፍ ብዛትና በወረፋ የሚገኘውን የፍትህ ጉዳይ መንግሥት አትኩሮት ሊሠጠው ይገባል። ወላጆች በህገ መንግሥቱ መሰረት በ24 ሠዓት ውስጥ የፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት አለበት ከሚለው አንስቶ ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ ፍርድ ሊያገኙ ይገባል የሚለውን በማጣት ከየመንገዱ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እየታፈሱ በመግባት በ24 ሠዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ባለመቅረብ፣ በማስረጃ እጦት እና ባልተስተካከለ የፍትሀ ሂደት በማረሚያ ቤት በመጉላላት ለሶስትና አራት አመታት በእስር በመንገላታት አልፎ ተርፎ በጤና መታወክ ሳይፈረድላቸውና ሳይፈረድባቸው እዛው የሞቱበት ፡ይህንን የተሳብረ የፍርድ ሂደት ይዘው መቀጠል አይፈልግም። ቀልጣፋና ለህገ መንግስቱ የታመነ፡ ለህብረተሰቡ ዘብ የቆመ፡ የፍትህ አካል ሊኖረው ግዴታ አለብን።
          ዓለማችን አይደለም ለህፃናት ለአዋቂ አመቺ ወደአለመሆኑ እየመጣች ባለበት በዚህ ወቅት የሙቀት መጠኗ፣የአየር መበከልን የሚያመጣውን ችግር ልንቀንስ በኑሮ የተመቻቸ  ዓለምን ልናወርሳቸው ግድ ይለናል።
          ከምንም በላይ የዓለም ህዝብ ከሰባት ቢለ.ዮን በላይ በሆነበት በዚህ ዘመን የቤተሰባችንን ቁጥር በአጋጣሚ ሳይሆን በእቅድ ልንወስን ይገባናል። መግበናቸው የምናሳድግበትን፣ አስተምረን የምናንፅበትን፣ወልደን አሳድገን የምናኖርበትን ምቹ ስፍራ ወዘተ አስቀድመን ልናቅድና ልናዘጋጅላቸው ይገባል። በዕድላቸው ይደጉ፣ሲወለዱ የእነሱ የሚሆነው ይዘው ይመጣሉ የሚለውን አጉል ፈሊጥ... በጥሞና ልናጤነውና ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳቸውን ነገር ልናስብ ይገባል። ለቀጣዩ ትውልድ የሚታይ የቆመ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ብቻ በቂ አይደለም። ጤናማ ህይወት ያስፈልጋቸዋል፣ በመልካም ስነ -ምግባር ላይ የተመሰረተና አርአያ ሆኖ ሊያሳድጋቸውና ከፊለፊታቸው ያለውን ብሩህ ዓለም የሚያሳያቸው ቀዳሚ ትውልድ ይፈልጋሉ።
          የእነዚህ ሶስት ህፃናት አጭር ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው ይህ ታሪካችንን ለመቀየር ታጥቀን እንነሳ የበለፀገች፡ ለምለም ኢትዮጵያን፡ በረሃብ ሳይሆን በስልጣኔዋ በስነ ምግባሯ የታወቀች ኢትዮጵያን እንፍጠር። ይህቺ በሀይማኖቶች የከበረች፡ በብሔር ብሔረሰቦች ያጌጠች በመከባበርና በመቻቻል የተመሰረተች ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ፍትህ ልማት ብልፅግና ሰላምና ጤና ሰፍኖባት እናዳማረባት ለቀጣዩ ትውልድ እናውርሳቸው።ከምንም በላይ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ነፃነት ለቀጣዩ ትዉልድ ያስፈልገዋልና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በጥንቃቄ ሊወገድ ይገባል፡ ምክንያቱም በሃይማኖትና በፖለቲካ ነፃነት ትዉልድ አገርን ለመረከብ ብቁ ይሆናልና፡፡ቸር ይቆየንለቀጣዩ ትዉልድ ልማትን፡ መከባበርን፡የሃይማኖት ነፃነትን፡የፖለቲካ እኩልነትን፡ የኢኮኖሚ በእኩል መከፋፈልን … እናዉርሳቸዉ፡፡

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...