ንጉሱ ለአንድ ሃገር መንገዶች ወሳኝነት አላቸዉና መንገድ አሰርተዋል መንገዱ ላይ
የሚመላለሱት መኪኖች ለማስተናበር በአዲስ አበባው ከንቲባ ፖሊሶች (ትራፊክ ፖሊስ) ተመድበው በትዕግሥትና በንቃት ያስተናብሩ ነበር።
ይሁን እንጂ እነዚህ ፖሊሶች።
ü የሚጫሙት ጫማ ሳይኖራቸው ባዶ እግራቸውን
ነበሩ፡፡ ህዝቡ(ባላገሩ) በእግረኛው መንገድ
እንዲጠቀም ለማስተማር በሚያደርገው ጥረት፣ አልሰማ ሲሉት «በንጉስ ኃይለ ሥላሴ በቀኝ በኩል ይሂዱ» እያለ ይለምን ነበር።
ይህንን ቀደምት
ታሪክ ያገኘሁት በአዶልፍ ፖርሊስክ «የሃበሻ ጀብዹ» ከሚለው መጽሐፍ ነበር።
እንግዲህ በንጉስ ዘመነ ንግሥና የፖሊስና የህብረተሰብን ግንኙነት ሥንመለከት
ይህንን የመሰለ ሥነ-ሥርዓት የተሞላበት በትህትና የታጀበ መልካምነት የተሞላበት አገልጋይና ተገልጋይ ነበር። የፖሊስ መሠረታዊ ሥራ
ከጥንት ከመሰረቱ ህዝብን ለማገልገል፣ መኪኖችን ለማስተናበር፣ህገመንግሥቱን አክብሮና ጠብቆ ለማስከበርና ለማስጠበቅ … ወዘተ ነው፤
ከዚህ የተለየ ዓለማ የለውም። ከህብረተሰቡ መካከል የወጣ በመሆኑ የህብረተሰቡ ችግር የሚገባው፣ የህብረተሰቡን ጠንካራና ደካማ ጎን
(በጎና መጥፎ ጎን) ጠንቅቆ የሚያውቅ በትምህርትና በሥልጠና የዳበረ እውቀት ያለው ነው። ለዚህ ህብረተሰብን ለማገልገል ለፖሊስነት ሲታጭና ሲመለመል በሥነ-ምግባር የታነፀከተለያዩ
ሱሶች የፀዳ፣ የቀለም ትምህርት ዝግጅት ያለው፣ ሙሉ ጤናማ የሆነ፣ ለህገ-መንግሥቱ ታማኝ የሆነ... ወዘተ መሆን አለበት ተብሎ
ይገመታል፤ መሆንም አለበት የሚል እምነት አለኝ። ነውም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚያሳዝነው ነገር እንደዛሬ ግዜውን ለተለየየ ነገር
ባልተመቻቸበት ወቅት (ዘመን) አንስቶ ለፖሊስ የምንሠጠው ግንዛቤ አናሳ ነው። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ከህብረተሰብ ጋር
ያላቸው ትስስር እጅግ የጠበቀ ቢሆንም ለህብረተሰቡ የሚሰጡትም ጥቅም ትስስር እጅግ የጠበቀ ቢሆንም ለህብረተሰቡ የሚሰጡትም ጥቅም
እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዝም ብዬ ስጠራጠር ህብረተሰቡም ይሁን ባለድርሻ አካል ጥቅማቸውን የተገነዘበው አይመስለኝም ምነው
ቢሉ በንጉሱም ዘመን ቢሆን አስቀድመን በመነሻችን እንዳየነው አንዱ የፖሊስ መገለጫ የነበረው « የሚጫሙት ጫማ ሳይኖራቸው ባዶ እግራቸውን
ነበሩ» ወደ ዛሬ ከመጣንም ምን አላቸው? ምንም ለማለት ያስደፍራል። አንድ ነገር ትዝ አለኝ በደርግ ዘመን መንግስት ምንም እንኳን
ሥለ ሥርዓቱ እዚህጋ ማንሳት ባያስፈልግና ቦታውም ባይሆን አንድ ነገር ግን ማንሳት ግድ ይለናል።። በወቅቱ የነበሩት የፖሊስ ሰራዊትም ሆኑ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በልብስና በጫማ በኩል ችግር ያለባቸው
አልነበሩም። ምናልባት ከነበረው የሰራዊት ቁጥር አንጻር ሊሆን ይችላል ቢሆንም ግን ዛሬ ዓለም አንድ መንደር እንደመሆኗ መጠን ዓለምም
በአሸባሪዎች ሰላምን በሚያደፈርሱ ፀረ - ሰላም ሃይሎች እየተናወጠች በሚገኝበት አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ወደተነሳንበት
ጉዳይ ስንመለስ በወቅቱ የነበሩት ፖሊሶች «ፊልድ ጃኬት» የሚባል ወይም በጣም ወፍራም የሆነ ካፖርት ይሰጣቸው ስለነበር ይህ ልብስ
ዛሬ ላይ ሲታሰብ እንኳን ሊገኝ ይቅርና አይታሰብም ድፍረት አይሁንብኝና ፖሊሶቹም የሚያውቁትና የሚናፍቁት አይመስለኝም። ያኔ ግን
(በደርግ ጊዜ ማለቴ ነው) አንኳን ፖሊስ ይቅርና የፖሊስ ቤተዘመድ እንኳን የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኙ ነበር። ዛሬ ግን በምሽት የህብረተሰቡን
ሰላም ለማስቀጠል የአገርን ፀጥታ ለማስፈን ከላይ ታች የሚሯሯጡትን ፖሊሶች ስንመለከት የአየር ፀባዩ በሚለዋወጥበት ከዚህ ዘመን
ቀን ከሚለብሱት የተለየ ለምሽት የሚሆን ካፖርትም ሆነ ፊልድ ጃኬት የሚታሰብ ጉዳይ ኣይደለም ያቺው የፈረዳባት ከክረምት በጋ የምታገለግል
ሻማ ነገር በቀር ይህንን በምልበት ሰኣት ልቤ እጀግ ያዝናል እግረ መንገዴን ለሚመለከተው አካልም ሆነ ሕብረተሰብ የአደራ መልዕክቴን
እባካችሁ አትኩሮት ሥጧቸው እላለሁ።
በመቀጠልም የልብስ ጉዳይ ሲገርመን የባሰ ከመግረም አልፎ የሚያሳዝነው
ከአንዳንዶች አለፎ አብዛኞች ጥንድ ጥንድ እየሆኑ የምናያቸው ከበትር ወይም አጭር ከፕላስቲክ የተሰራች ዱላ በቀር ምንም የላቸውም።
ክፉን ያርቅልንና እንዲሁም ከሥነ-ምግባር አኳያ ሲጀምር ለመደባደብ የወጡ አየደሉም እንጂ ባዶ እጃቸውን እንኳንስ ሰው ሊያስጥሉ
ይቅርና እነርሱንም እግዚአብሔር ነውየሚጠብቃቸው፤ ለዚህ ነው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን የሆነው በመዲናችን በአዲስ አበባ የቀድሞ ባላቤቷ
ውድ ባለቤቱን የልጆቹን እናት እወድሻለሁ አፍቅርሻለሁ አከብራሻለሁ ይላት የነበረችውን የቀድሞ ሚስቱን በመኪና እያሳደደ በመኪና
እናቷን ከጋቢና አስቀምጣ እያመለጠች ባለችበት ወቅት እነዚህን ፖሊሶች የአገርን ሰላም የህብረተሰብን ሰላምና ጤና የሚያስከብሩ ሥትመለከት
አቁማ አስጥሉኝ ብላ ስትማፀን አንድ ግለሰብ የፀብ መንጃ መሳሪያ በመያዙ ፖሊሶቹ ግን ሰላም የሚያስከብሩበት አጥፊዎችንና ጠላትን
የሚከላከሉበት መሳሪያ ባለመያዛቸው በጥይት ደብድቦ የገደላትና ሌሎችንም ሊያቆስልና ሊጎዳ የቻለው።
የሆነው ሆኖ የተፈፀመው ተፈፅሞ የጠፋውም ጠፍቶ የለማውም ለምቶ እንዲህ
እንዲህ ስንል ዛሬ ደርሰናል። የፖሊስና የህብረተሰቡ ቁርኝት ምን ይመስላል ግንዛቤውስ? ቁርኝቱ ከፊት ይልቅ የጠበቀ ቢሆንም አንዳቸው
ለአንዳቸው (ፖሊስ ለህብረተሰቡ፡ህብረተሰቡ ለፖሊስ) ያለው ግንዛቤ ተመናምኗል። ሁሉንም ባይባል እጅግ ጥቂት የሚባሉት ፖሊሶች የፖሊስነት
ሙያን የተላበሱት ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲባል መሆኑን ህብረተሰቡም የሞቀ ቤቱ ሰላማዊ እንቅልፋን ተኝቶ ሲያድር ሃብትና ንብረቱን በሜዳ
በትኖ እንዳሻው ሆኖ ወጥቶ የሚገባዉ ሃለፊነቱን ወስዶ የሚጠብቀው ፖሊስ መሆኑን የዘነጉ ጥቂት የማይባሉ ህብተሰቦች አይታጡም ።
ይህ ደግሞ ክፍተት እንዳለ ያመለክተናል እንኳንስ የፖሊስ ክብርና ፍቅር ሊኖር ይቅርና የፖሊስ ፕሮግራም በቴሌቪዥን ማየት የሚያስጠላው
ሞልቷል። ለምን?. ማለታችን አይቀሬ ነው በህብረተሰቡ መካከል በጉምጉመታ መልክና በተባራሪ የሚዳመጠው ፀሐፊውም እንታዘበውና እንደጠረጠረው
አንዳንድ ችግሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል የህብረተሰቡን መንፈስ ለመግለጽ በአንድ ወቅት የገጠመኝን ነገር ልንገራችሁና ሃሳቡን
ለመረዳት የተሻለ ይመስለኛል በመረጃ:: ለቅሶ ቤት ሆኜ ነዉ የለቅሶ ቤት የሄድነው ደግሞ ሟች የባል ሚስት ወንድም ነው ባል የፖሊስ
አባል ነው ። በዚህ የተነሳ ብዙ የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ አባላት ለቅሶ ለመድረስ በቦታዉ ተገኝተዋል፡ ባልደረባቸውን ለማጽናናት::
በድንገት በሥፍራው የታደሙ አባት ድንገት ባዩት ነገር መነሻነት በከተማው የሚታዩ የፖሊስ ሰራዊት ቁጥር መብዛቱን ለመግለጽ «መንገዱን
ሞልተውት የለ እንዴ» በማለት ይገልፁታል አንድ አባት ቀበል አድርገው «ምን ይገርማል ዩኒፎርም ለበሱ እንጂ በፊትስ መንገድ ላይ
አልነበሩ አንዴ? በማለት ጣል ያደርጋሉ። ግራ የገባው ማብራሪያ መጠየቅ፡ የገባውም የአሽሙር ሳቅ መሳቅ ገሚስሙም አንዴ ፖሊሶቹን
እያየ አንዴ ደግሞ እርስበእርስ እየታየ አፉን በእጁ ይይዛል እኚሁ መናገር የጀመሩ አባት ለጥያቄ ማብራሪያቸው እንዲህ በማለትቀጠሉ
«... ማለቴ ድሮም እየተማሩም ትምህርታቸውን ጨርሰውም በየሱቁ ደጃፍ በየመንገዱ ሲገተሩ ልጃገረዶችን አላስወጣ አላስገባ ያሉ ገሚሶቹም
ጨለማን ተገን በማድረግ በመቧደንም ሞባይሉ ሲቀሙ የነበሩ፣ ... ናቸው። እንግዲህ እዚህ ላይ ጥቂት የማናውቃቸው ተጨምረው ይኸው
ሰልጥነው ግማሹ እስከ አመሉ ግማሹ ጠባዩን ቀይሮ ግማሹ መሐል ሰፍሮ
አብዛኛው ለህብረተሰቡ ጥቂቱ ደግሞ ለራሱ ዮኒፎርሙን ለብሶ ከተማውን
ሞልቷል። በቃ ይኸው ነው የበለጠ ማብራሪያ ከፈለጋችሁ አሉና አንድ
የሚያውቁትን በሠፈራቸው አስቸጋሪ የነበረ ኋላ ግን እኛን ሲያስቸግር
እነደነበረው ለመንግስትም አስቸግሯል መሰል «ይብለኝ የወለደሽ ያገባሽስ ይፈታሻል » አይደል የሚባለው እስከ ነተረቱ እየተከታተልክ
ዝርፍ ብሎ አባረረው ብለው አስረዱ።
ከላይ ከተጠቀሰው ታሪክ የምንረዳው ሕብረተሰብን ለማገልገል የሚመለመሉተ
ፖሊሶች መካከል ከብስል መካከል ጥሬ እንዳለ ሁሉ በሥነ -ምግባር ታንፀው በብቃት ሰልጥነው የወጡት ፖሊሶች መካከል የሥነ-ምግባር
ችግር ያለባቸው ፖሊሶች እንዳሉ ይጠቁማል ። ለምን? ጥሩ ጥያቄ ነዉ፡-
አንደኛ ሲመለመል ጀምሮ ችግር አለ፤
ሁለተኛ ብቁ
ስልጠና አልተሰጠውም
ሶስተኛ ሙያውን
የሚያስከብር ጥቅም ስላላገኘ ሊያከብረውና በታማኝነት ሊያገለግል አልቻለም። የሚጫሙት ጫማ ሳይኖራቸው ባዶ እግራቸውን ነበሩና» አንድም
ዛሬም ከዕለት ድካማቸው ይልቅ የወር ገቢያቸው እጅግ ያንሳልና፣ አንድም ወርቅና ዶላር እየጠበቁ ጥቂት ብሮች ናቸውና የሚከፈላቸው፡፡
አንድም ሰዉ ሰላማዊ እንቅልፋን እንዲተኛ እያስቻሉ እነርሱ ብርድ እንኳን የሚከላከልላቸው የዓመት ልብስ የላቸውምና፡ አንድም የህብረተሰቡን
ሰላም እያስከበሩ የነርሱ ቤተሰብ ግን ከገቢው ማነስ ከጥቅማ ጥቅማቹ አርኪ ያለ መሆን የተነሳ ቤተሰባቸው ሲፈናቀል ትዳራቸው ሲፈርስ
ኑሮአቸው ሲናጋ የሚያምራቸው እንጂ የሚያገኙት ጥቂት በመሆኑ፡ አንድም ይህችን ድንግልና ለምለም ምድር እየጠበቁና እንዳትደፋር እያደረጉ
የነርሱ ኪሲና ጎጆ ግን ቀዳዳና ገዳዳ ሆኖ ሊወድቅ አዘንብሏልና የሚጠበቅባቸውን አይሰጡም «በንፍሮ የደለሉት ሆድ/ጉልበት/ በዳገት
ይለግማልና»። ከዚህ ማሳያ በላይ ሌላ መጨመርም አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም ፖሊስና ህብረተሰብ መካከል ያለውን ክፍተት ለማመላከት።
እስኪ የህብረተሰቡን ችግር እንመልከት አንድ ጥያቄ ነክ ነገር ላንሳ በኛ
አመላካከት በቤት ዘበኛና በፖሊስ መካከል ያለውን ልዩነት እናውቃለን? እኔንጃ አይመስለኝም። ፖሊስነት አንድ ፕሮፌሽን ሥነ - ምግባር
፣ ሳይንስ፣ ዲሲፕሊን፣ መሆኑን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? ፖሊስ ሲባል ከልጆች ማስፈራሪያነት የዘለለ የምንጠቀምበት ልጆቻችን ፖሊስ
እንዲሆኑ የምናጫቸው ስንቶቻችን ነን? ለነገሩ እንኳንስ ለማናውቀው የፖሊስነት ሙያ ይቅርና ዓለምን እንደ እርሳስ የቀረጿት የዓለም
መቅረጫ የመምህርነት ሙያ እንኳንክብርና ፍቅር የመሆን ምኞት የለንም ልጆቻችንም እንዲሆኑም አንፈልግም። በዓለም ላይ ትልቁ ሞያ
ግን መምህርነት እና ፖሊስ እንደሆኑ ልመሰክርና ሳስገነዝብ እወዳለሁ።
ለምንድን ነው ህብረተሰቡ ለፖሊሱ ክብር የነፈገው ጥሩ አመለካከትስ ያጣው?
ብለን ካልን ጥቂት ነገር ማንሳት ይቻላል። በአንደኛ ደረጃ አስቀድመን ያነሳነው ታሪክ ሙሉ በሙሉ ስለተቀየረ በንጉሱ ዘመን የነበሩት
ፖሊሶች (ትራፊኮች) «ህዝቡ (ባላገሩ) በእግረኛው መንገድ እንዲጠቀም ለማስተማር በሚያደርጉት ጥረት አልሰማ ሲሉት በንጉስ ኃይለ
ሥላሴ በቀኝ በኩል ይሂዱ እያለ ይለምን ነበር » የሚለው በትህትና በመሆን በአክበሮት ለምኖ /ደብድቦ አይደለም ገላምጦም አይደለም/
ያገለግለው የነበረው አገልግሎቱ በመቅረቱ። በሁለተኛ ደረጃ በጥፋተኛነቱ
ተጠርጥሮ አለበለዚያም እጅ ከፍንጅ ተይዞ እስር ቤት የገባ ተጠርጣሪ ሰብአዊ ክብሩና መብቱ ተጠብቆ አስፈላጊው የወንጀል ምርመራ
ተደርጎ በህጉ መሰረት በሃያ አራት /24/ ሰዓት ውስጥ ለፍርድ መቅረብ ሲገባው መብቱ ተጥሶ ሰብአዊነቱ ተገፎ ሊከበር ሲገባው ተረግጦ
በመያዙ እንደ ጠላት በመተያየት ከመደጋገፍና ወንጀልን በጋራእንደመከላከል
ተጠማምደው «ሌባና ፖሊስ ጨዋታ እንደ አይጥና ድመት እየተጫወቱ ይገኛሉ። ካነሳነው አይቀር አንድን የህግ ታራሚም ሆነ ለፍርድ ያልቀረበ
ተጠርጣሪ ፖሊስ መደብደቡ ክበሩን መንካት ከየት የመጣ መብት ነው? ብዙ ገጠመኞች ቢኖሩትም አንድ ቀን በአንድ ምሽት በተከታይ ያጋጠመኝን
ገጠመኝ ልንገራችሁ ምሽት 1፡30 ፒያሳ (ማዘጋጃ ቤት) ወይም በተለምዶ ሸዋ ዳቦ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ላይ ተክለሃይማኖት አብነት
ጦርሃይሎች ታክሲ መያዣ ጋር ሰው ለመሸኘት ቆሜያለሁ ምን እንደተፈጠረ በማላውቀው ሁኔታ ዱላ ተጀመረ ጥሎብኝ ማጣራት እወዳለሁ ጠጋ
ብዬ የዱላውን ምክንያትና ማንነት ሳጣራ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የትራፊክ ፖሊስ በዱላ የተቀጠቀጡ አጆቹን ይዘው ገፍትረው መኪና ውስጥ
ከተቱት ትራፊኩ ጋቢና ሁለቱ ፖሊሶች ከኋላ ገቡ በጥፋት ላይ ጥፋት የአሽከርካሪው መደብደብ ሳያንስ የባለንብረቱ ንብረት ህብረተሰብን
ለማገልገል የአገርን ሰላም ግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ጥሪት በትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ ቢሰማራም በነዚህ ሥነ-ምግባር የጎደላቸዉና ግዴታቸውን መወጣት በተሳናቸው ባለሙያዎች ሳይሆን
ጉልበተኞች የጎን መመልከቻ መሥታወቱ (እስፖኪዮ) ተሰበረ። የሚገርመው መኪናውንና ሹፌሩን ይዘውት ሲሄዱ ረዳቱን (ገንዘብ ያዡን)
ይዘው መሄድ አልፈለጉም ጥለውት ሄዱ፤ ማን ይሆን የዚህን ህብረተሰብ መብት የሚያከብረውና የሚያስከብረው? ፖሊስ? መጨራሻውን ማየት
አልናፈቀኝም የምሸኘውን ሰው ሸኝቼ ወደ ማዘጋጃ ቤት በኢየሩሳሌም መታሰቢያ ህንፃ በኩል አድርጌ ወደ ሚኒልክ አደባባይ ሳመራ አንድ
የጦር መሳሪያ የያዘ ፖሊስ ይመስለኛል የመዘጋጃ ቤቱ ሰላም አስከባሪ (ተረኛ ጠባቂ) ነው አንዱን ሶፍትና ማስቲካ መንገድ ዳር ቁጭ
ብሎ በመሸጥ ላይ ያለ ወጣት በሽመል እየደበደበ እንደከብት ይነደዋል።(በአንድ
ምሽት የሆነ ነገር ነዉ የምነግራችሁ) በወቅቱ የነበሩ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ፖሊሱን ምን አደረገህ? እያሉ ይወተውቱታል አላዳመጣቸውም
አንዴ በዱላ ሌላ ጊዜ በተጫማው ከስክስ ጫማ እንደጠላት ይከሰክሰዋል። መነሻ ጉዳዩን ባላውቅም የመጠየቁም ዕድል ባይኖረኝም እስኪ
እንበልና ይህ ተደብዳቢ የመንገድ ላይ ህገ -ወጥ ነጋዴ፣ ለመንግሥት ታክስ የማይከፍል፣ ልማትን የሚያደናቅፍ፣ አለበለዚያም የጎዳና
ላይ ንግድን ተገን በማድረግ አሸባሪ ነው ከፈለግንም በማህበር በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ለመካተት ፍቃደኛ ባለመሆኑ፣ወይንም
ለዓባይ ከገቢው ላይ ወጪ አላደረገም ካሽንም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ምክንያት በማህበርም ይሁን በግል የተሰማውን ሀዘን በመጠነኛ
ቢል ቦረድ መልኩ ያልሰቀለ ፀረ-ሰላም ፣ተቃዋሚ... ወዘተ እንበል የአገሪቱ ህግ ግን በዱላ፣ በፖሊስ ከስክስ
የመከስከስ ግዴታ ጥሎበታል ወይ? ፖሊሱስ ቢሆን መንግሥት የህብረተሰቡንና
የአገርን ሠላም እንዲያስከብር በቀጠረው ጊዜ የውል ስምምነቱ ላይ
በአጣና አጥንቱን ከሰባበርክ በከስክስ ከከሰከስ በሰይፍ ጉኖን በቡጢጥርሱን ካራገፍክ ደሞዝ ይጨመርልሃል ብሎ ይሆን? ወይስ ደሞዙ
እኛን ማስጨነቅ ይሆን? ለሰሚ ግራ የሆነ ነገር ይላሉ እትዬ ግራ ሲገባቸው።
ታዲያ እነዲህ ከሆነ ነገሩ ፖሊስና ህብረተሰብ ምንና ምነድን ናቸው ትላላችሁ?
Ø እሳትና ጭድ?
Ø የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ?
Ø ሌባና ፖሊስ?
Ø ዓይጥና ድመት?
Ø ኢራቅና ኢራን?
Ø አንድ አካል አንድ አምሳል?
Ø የሁለት ዓለም ሠዎች?
Ø መ- መልሱ የለም?
ግራ የገባ ነገር ነው፤
መቸስ ፖሊስ ስንል ከትራፊክ እንደልነጠልን ግልጽ ነው ይሁን እንጂ
እስኪ ትራፊክን ነጥሉና እንየው ጳጳሱ መጡ ይላሉ የታክሲ ሹፌሮች የተረት አባቶች ደግሞ ራሱ ነጭ እጁ ነጭ ከመንገድ ቆሞ የሰው
ኪስ የሚሞልጭ ይላሉ፡ ትራፊክን በነገር ለመንካት ሲፈልጉ፡፡ ምናልባት እንደካህን መመሰሉ ካህን ከቤት ከመጣ ቀኖና ሳይሰጥ አይሄድምና
የትራፊኩን ቅጣት ከዚያ አያይዘውታል ነጭ ደፍቶ ነጭ ለብሶ ከመንገድ ዳር ቆሞ የሚገባው ምንም እንኳን ለመንግሥት ቢገባ መነጨቱን
አይተው መተረቻ አድርገውታል እኔን የሚገርመኝ ከአሽከርካሪ ጋር ያላችው ፀብ ነው(ለዚያዉም ከታክሲዉ ሹፌር ጋር) አስቁመው ሰላምታ
ሲሰጡ እንኳንስ የማስተማር ጥረት የተፈታ ፊት የላቸውም ፊታቸውን ጥለው ወይም ጀርባቸውን ሰጥተው ጥፋቱን ሳይገልጡለት መንጃ ፍቃድ» ይላሉ ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመኝና የሚያናድደኝ ተሳፋሪ ጭኖ እያየ የአሽከርካሪው
ቀርቶ የህብረተሰቡን መብት ወይም መጉላላት ከመጤፍ ሳይቆጥሩ መንጃ ፈቃዱን ወሰደውበት የትናየት ሲጓዙ የማየው ነገር ሙስና እንደሌበት
እጠረጥራለሁ ምክንያቱም አሽከርካሪው ወርዶ ለምኖ ለምኖ ሲመጣ ሳይቀጣ መንጃ ፍቃዱን ተቀብሎ ይመጣልና አያስጠረጥርም ትላላቸሁ?
እንጃ እኔ ፈርዶብኝ ጠርጣሪ ሆኜ እንደሆነ ፈጣሪ ይወቀው ጠርጣሬአለሁ እንዲያውም ልቤ አሥር ብር ተቀብሏል ይለኛል።
አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ ቀኑንም አልቀውም ስንት ሰዐት እንደሆነም
ዘንግቼዋለሁ ብቻ መሽቷል 3፡00 ሰዓት ገደማ ነው ዝም ብዬ ስጠረጥር ታክሲ አጥተን በስንት ጥበቃ አንድ ከሌላ መስመር የመጣ ታክሲ
ጠቅጥቆን ይጓዝ ጀመር አንዲት ሴት ህፃን ይዛ በእግሯ እየተጓዘች ለመነችው የተረፈ የንፋስ ማስገቢያ ቦታ ነበረውና አንድም አዝኖላት
አንድም የሚመጣው ሳንቲም የማይናቅ ጥቅም አለውና ያልተፈቀደ ቦታ ላይ (ምልክት ላይ) ጫናት ይኸን ጊዜ «የነጋበት ጅብ» አሉ አንዳንድ
ተሳፋሪዎች ሥራውን አጠናቆ ወደ ቤት በመግባት ላይ ያለ ትራፊክ ያጋጥመዋል አስቆመውና እንደተለመደው መንጃ ፈቃድ በማለት ተቀበለው
አሽከርካሪው በአንድም ይሁን በሌላ እንደሚያስቀጣው አምኗል ለመለመን ዝግጁ ሳይሆን ለቅጣት ተሰናዳ። ህብረተሰቡ ግን ትራፊኩን በመስኮት
ለመኑት ትራፊክ ኣሻፈረኝ አለ የሚገርመው መቅጫ አልያዘም ነበር እንኳን መቅጫ ፊሽካ አልያዘም (አይታይም)። መቸስ ትራፊክ ጠያቂ
የለውም አይደል? መንጃ ፈቃዱን ይዞት አራግፍና መጥተህ ውሰደው አለው ለጥቂት ደቂቃ ያለውን ለማድረግ አልፈቀደም አሽከርካሪዉ እየቆየ ሲያየው ያ! የነጋበት ጅብ ያሉት ትራፊክ ረጅም መንገድ
ተጓዘ አሽከርካሪውም ነገ ሌላ ቀን ነውና እኛን አራግፎ ረዳቱን መኪና እንዲጠብቅ አዞት ትራፊኩን ተከተለው የት ይገናኙ ይሆን?
ምንስ ይቀጣው ይሆን? እኛስ በአንድ እብሪተኛ ትራፊክ በየመንገዱ
የማንጉላላው መቼ ይሆን? የትራንስፖርት ችግርስ የሚቀረፈው መቼ ይሆን? ህጉ የሚተገበረው መቼ ይሆን? ትራፊክ ፖሊስና ህብረተሰብ
ትራፊክ ፖሊስና አሽከርካሪ ምንና ምን ናቸው?ፖሊስና ህብረተሰብስ? ቸር ይቆየን፡ ፖሊስንና ህብረተሰቡን እግዜርና ምንግስት በፍቅር
ይጥመዱን፡፡