ማክሰኞ 25 ሜይ 2021

የጌታ ቃል ትዝ አለው

 " የጌታ ቃል ትዝ አለው " የሉቃስ ወንጌል 22፥61

በደረሰ ረታ

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስን ክርስቶስን " ሌሎች ቢክዱህ እንኳን እኔ አልክድህም " ብሎት ነበረና ጌታም " ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ " አለው።

ጊዜው ሲደርስ ጌታን ያዙት ወደ ሊቀካህናቱ ቤትም ወሰዱት

• ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር።
• ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ።
• ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች።
• አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ።
• አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ፡ አለው።
• ጴጥሮስ ግን፡— አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም፡ አለ።
• ሌላው አስረግጦ፡— እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ፡ አለ።
• ጴጥሮስ ግን፡— አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም፡ አለ።
• ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ።
• ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤
• ጴጥሮስም፡— ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው።
• ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
የቅዱስ ጴጥሮስ አቋም ከችኩልነቱ የተነሳ ወላዋይ ይመስላል፤ ችኩልነቱ እና ባለማገናዘብ የሚመልሳቸው መልስ ከፍቅር የመነጨ ነው።

መጠራጠር እና ክህደቱ የተፈጠረው ግን በፍርሃት፣ ከነበረበት ስፍራ፣ ከወቅታዊ ሁኔታው የተነሳ ነበር።

1. ጌታን ሲይዙት ርቆት መከተሉ
2. ሲበርደው እሳት ለመሞቅ ጌታን ከያዙት ወገን ከመካከላቸው መቀመጡ
3. የጌታን ወደዚህ ዓለም የመምጣት ዓላማ በአግባቡ ሳይለይ የልብ መሻቱ
እነዚህ ተደማምረው ቅዱስ ጴጥሮስ መጀመሪያ ጌታን አላውቀው፣ ቀጥሎ ራሱን ክዶ አይደለሁም፣ በመጨረሻም ጌታን ሊክደው እና አላውቀውም እንዲል አድርጎታል።

ከዘረኛ ጋር ስንውል ዘረኛ፣ ከነፍሰ ገዳይ ጋር ስንውል ነፍሰ ገዳይ፣ ከመንፈሳዊ ጋር ስንውል መንፈሳዊ እንሆናለን። ወፍጮ ቤት የዋለ አይደለም የገባ ሰው ዱቄት ሳይነካው አይወጣምና።

" ቃሌ ከሚያልፍ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል " ያለ አምላካችን ያለው ቃል ተፈጸመ። ዶሮ ሳይጮኽ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ሶስቴ ካደው።

ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው።

ጴጥሮስም የጌታ ቃል ትዝ አለው፦ ።" ዶሮ ሳይጮኽ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ "

ጴጥሮስም ወደ ውጪ ወጥቶ (ከወንበዴዎቹ ተለይቶ፣ ጌታን ሊገሉት ከሚፈልጉት አጠገብ ርቆ፣ እሳት ከሚሞቅበት ቦታ ተነስቶ ) ምርር ብሎ አለቀሰ።

የቅዱስ ጴጥሮስ መራር ለቅሶ የንሰሐ ለቅሶ ነበረ።

እኛስ?

ከቅዱስ ጴጥሮስ የሕይወት ተሞክሮ ምን ተማርን?

ጌታን በቅርበት ነው የምንከተለው ወይንስ በርቀት?

ውሎአችን ከነማን ጋር ነው?

አውቀን አምነን ነው እየተከተልነው ያለነው፣ በስሜት ነው፣ ከቤተሰቦቻችን ስለወረስን ነው፣ ወይንስ እንዴት ነው?

አሁናዊ ማንነታችን ምን ይመስላል?

ብዙዎቻችን የቅዱስ ጴጦሮስ አይነት ሕይወት ያለን ይመስለኛል፤ መመላለስ ነገር ግን መራር የንሰሐ ሕይወት የሌለን። እንደዛ ከሆነ እንመለስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰማነው የጌታ ቃል ትዝ ይበለን።

አካሄዳችንን እናቅና ( ቤተክርስቲያን መሄድ የምንፈራ፣ ማስቀደስ የምንጠላ፣ መጾም የማንችል፣ የጸሎት ሕይወት የሌለን፣ ማመን የማይታይብን፣ ውሎና አዳራችን ከማይመስሉን ጋር የሆነ፣ ከማያምኑት ጋር ወዳጅነት የመሰረትን ) እንመለስ።

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታውን እንዲክድ ያደረገው፦
መፍራቱ፣
ከማያምኑት ጋር መቀመጡ፣
ጽኑ እምነት አለመኖሩ፣
ወዘተ ናቸው ለመካድ እና መሪር እንባን እንዲያነባ ያደረጉት።

ስለዚህ እኛም ፍርሃትን የሚያርቅ ጽኑ ፍቅር እንዲኖረን ጌታን ቀርበን እንወቀው። ከማያምኑት ጋር ውሎአችንን አናድርግ፣ ( ከላም ጋር የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትመጣለች እንዲባል) ውሎአችንን እናስተካክል።

አንዳንዶቻችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት፣ አምላክነት፣ አማላጅ አለመሆኑን፣ ማመናችንን፣ ክርስቲያን መሆናችንን ለመደበቅ እንጥራለን፣ የአንገት ማኅተማችንን እንደብቃለን፣ መጾማችንን ሳይቀር እንዋሻለን። ( የዘፈን ዳርዳሩ ... እንደሚባለው እንዳይሆን እፈራለሁ። )

በጌታ ቃል ራሳችንን እንመልከት። አንዳንዶቻችን ታሪክ ቀመስ እንሆናለን በልጅነቴ ሰንበት ተማሪ ነበርኩ፣ ዘማሪ ነበርኩ፣ ዲያቆን ነበርኩ፣ ቆራቢ ነበርኩ፣ መምህር/ አባ እገሌን አውቀዋለሁ፣ የቄስ ልጅ ነኝ ወዘተ እንላለን። አሁን የት ነን? እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ራሳችንን እንይ። እሳት ሐጢያትን እየሞቅን፣ ጌታን አሳልፈው ከሰጡ፣ ከሸጡ፣ ከገደሉ ጋር ነን? ወይስ ቃሉ ከሚነገርበት አትሮኑስ ስር ነን?

በጌታ ቃል ራሳችንን ካየነው ምንም ጥያቄ የለውም በድለናል። ( ሁሉ በደለ እንዲል የአምላካችን ቃል። ) ክደናል የሚያስብል ደረጃ ላይ ነን። እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ፈጥኖ የሚመለስ ልብ፣ የሚጸጸት ልብ፣ ወደ ንሰሐ የሚመለስ ልብ ካለን ንሰሐ እንግባ፣ አምርረን እናልቅስ፣ ያሳለፍነው ዘመን ይበቃናል እንበል።

የቀማን መልሰን፣ የበደልን ክሰን ወደ ንሰሐ ሕይወት እንገስግስ።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምህረት ዐይኑ ይመልከተን።

አሜን።
ይቆየን።

መልካም የሕማማት ሳምንት ይሁንላችሁ።
❤❤######################❤❤

የእለት ተለት ጽሑፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች ባሉት ሁሉ እገኛለሁና ይከታተሉኝ። ከተመቸዎት ለሌሎች ያጋሩት።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)

https://www.facebook.com/deresse2020/

Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)

https://www.facebook.com/DeresseReta

Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።

https://t.me/deressereta

ከአሥር አመት በላይ ከ50ሺ በላይ አንባቢዎች ያሉት መጦመሪያም አለ።

www.deressereta.blogspot.com

https://anchor.fm/deresse-reta/episodes/ep-ev5j5o

ሥራን አውቆ መሥራት

 ሥራን አውቆ መስራት


አንድ ሰው በቅርስ ጥበቃ ተቋም በጥበቃ አገልግሎት ተቀጥሮ እየሰራ ሳለ አንድ ቀን በቅርስ ማዕከሉ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ብዙ ዘመናትን (1500ዓመታት) ያስቆጠረ ብርጭቆ ሰበረ።

ተቆጣጣሪው በጣም ተበሳጩ ተቆጡ ጥበቃው ምን እንደሚያበሳጫቸው ግራ በመጋባት ጠየቀ።

ኃላፊው እንዴ ብርጭቆኮ ነው የሰበርከው ብርጭቆው ደግሞ 1500 ዓመት ያስቆጠረ ትልቅ ቅርስ ነው አሉት።
ጥበቃውም ግራ ከመጋባት ውስጥ ወጥቶ ዘና በማለት እንደውም እንዲህ ያረጀ ብርጭቆ እዚህ ምን ይሰራል። እንደውም በአዲስ እተካዋለሁ አይጨነቁ በማለት ሊያረጋጋቸው ሞከረ።

ሰውየውም እጅግ ተበሳጩ። ቁጣቸው ጨመረ።

የሥራ ኃላፊውን ያስቆጣቸው ጥበቃውን ያረጋጋው ጉዳይ ምንድነው?

ጥበቃው ቅርስን ያህል ነገረ ሰብሮ እንዲህ ያረጋጋው ምን አይነት የጤና ሁኔታ ላይ ቢሆን ነው? ትሉ ይሆናል።

እስኪ ስለ እነዚህ ሁለት ሰወች በማውራት ጊዜ ከምናባክን ስለ እያንዳንዳችን እናስብ።

እኛ ምን አይነት ሰወች ነን?

ቁጡ?

ግዴለሽ?

ዝምተኛ?

እስኪ ምን ያስቆጣናል? ምንስ ዝም ያስብለናል? ግዴለሽ የሚያስደርገንስ ምንድን ነው?

ግድየለሽነት የጤናማነት ምልክት አይሆንም ሲወድቅም፣ ሲሰበርም፣ ሲጠፋም ግዴለሽ ከሆንን ጥቅሙ አልገባንም አልያም ችግር አለ።

አንዳንዶች ምናልባት ተስፋ ከመቁረጥ ግድየለሽ ሊሆኑ ይችላሉ። የፈለጉትን ከማጣት፣ በጣም የተማመኑበት ነገር ሲከዳቸው፣ ቃል ሲታጠፍባቸው፣ አምነው ሲከዱ ወዘተ ለግድየለሽነት ምንጭ ሊሆን ይችላል።

ምን ያስቆጣናል?

በተለምዶ እውነተኛ ሰው እውነቱን በምሬት ሲናገር ቁጡ ይባላል። ሌሎች ደግሞ " የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ አድርቅ " እንዲሉ ጥፋታቸውን ለመደበቅ ይቆጣሉ። ጥቂቶች ደግሞ የግንባራቸው ሥጋ ቅርጽ (መሸብሸብ/ ኮስተር እንደ ማለት) ቁጡ ያስብላቸዋል።

እኔን መሰሎች ደግሞ ስራ ሲበላሽ እና ያለ አግባብ ሲሰራ በተለይ እንደ ቅርስ ጥበቃው ሰራተኛ ለደሞዝ ብቻ ገብተው በሚወጡ፤ ነገር ግን የሚሰሩት ሥራ ዓላማው ካልገባቸው ሥራቸውን በአግባቡ ካልተወጡት ያስቆጣል።

ዝምተኞችን ስንመለከት በአጭሩ ለመፈረጅ ቢያስቸግርም ሥራው ቢሰራ ባይሰራ፣ ቢበላሽ ባይበላሽ ምንም የማይመስላቸው "ያው በገሌ ነው" ብለው እንደ ድመት የሚያስቡ። ተናግሬ ሰው ከሚቀየመኝ ዝም ብዬ ተመሳስዬ አልኖርም ብለው የሚያስቡ ናቸው። እንደዚህ አይነት ለኔ ልዝብ ነው።

ለነገሩ ሁሉም ነገር ስለተናገሩት፣ ዝም ስላሉት አይፈታም አንዳንዴ ሲናገሩ የሚፈታ እንዳለ ሁሉ ዝም ሲሉት የሚፈታም አለና።

እኛ እንደ ተቋም እንደ አገር የተሰጠንን ሥራ የምንሰራው እንዴት ነው? እንደ ጥበቃው ሳይገባን ነው ወይስ እንደ ቅርስ ጥበቃ መስሪያ ቤት ኃላፊ በያገባኛል፣ በኔነት፣ ሥራው ገብቶን ነው?

ከትንሣኤ ማግስት

 የትንሣኤ ማግስት ቀናት

በደረሰ ረታ

ሰኞ ፦ ማዕዶት መሻገር ማለፍ በሲኦል ወደ ገነት በጨለማ ወደ ብርሃን የመሻገራችን ነፍሳት ከሲኦል የመውጣታቸው መታሰቢያ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የመምጣቱ አላማ ይኸው ነውና።

በባህሪው ሞት በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት አምላክ የሞተው ለዚህ ነውና።

በዚህ በትንሣኤ ማግሥት ሰኞ በዚህ ዕለት በፋሲካችን በክርስቶስ ትንሣኤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከሃሳር ወደ ክብር መሻገራችንን እናስባለን፡፡


ማግሰኞ፦ ማግስተ ሰኞ ቶማስ ሲባል ቶማስ ጌታን አይቶ ማመኑ ጌታዬ አምላኬ ብሎ መመሥከሩ

እንደምናውቀው ቶማስ በጌታችንም ሆነ በእመቤታችን ትንሣኤ ወቅት በአገልግሎት ምክንያት አልነበረም ወንድሞቹ ሐዋርያት ነበሩ ስለ ትንሣኤዋ የነገሩት ነገር ግን አላመነም። በጌታ ትንሣኤ ጌታን ቢጠራጠር እርሱ ስለመሆኑ ጌታ ማረጋገጫ የሰጠው ሲሰቀል የተወጋ ጎኑን እንዲያይ ነበረ። እጁን ወደ ተቸነከረበት ቢሰደው ጣቶቹ እሳት እንዳየ ጎማ ተኮማተሩበት። አምኖም መሰከረ። ዮሐ. 20፡27-29

በዚህ እለት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለማመናችንን እንዲረዳ፣ አምነንም እንድንመሰክር እንዲረዳን እናስበዋለን።

ረቡዕ፦ አልአዛር ሲባል ጌታ አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው እናስባለን።

አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው ስናስብ ክርስቶስ የሞትን ስልጣን የሻረ የሕይወት ራስ፤ የመቃብርን ሥርዓት ያጠፋ ትንሣኤ፡ ድልም ያረገ ዘለአለማዊ ንጉሥ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በብዙ ጭንቅና መከራ፣ በሞትና በሕይወት መካከል ስለምንገኝ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን እንደ ጉም በንኖ እየጠፋ ስለሆነ ጌታችን ለእኛም ትንሣኤ ልቡና እንዲያድለን እንለምነዋለን።


ሐሙስ፦ አዳም ሐሙስ ይባላል ለአዳም የሰጠው ተስፋና የተገባለት ኪዳን እንደተፈጸመ አዳምና ልጆቹ ነጻ እንደወጣን ይታሰብበታል።

በበለስ ምክንያት ከገነት እንደወጡ ሁሉ የአለም መድኀኒት ጌታችን ለአለመ ድህነት ከወጣንበት ገነት እንመለስ ዘንድ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ለአዳም በገባው ቃል መሠረት አድኖናልና።

አርብ ፦ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይባላል ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ መመስረቷ ይሰበካል።

በዕለት አርብ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሱ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ ቤተክርስቲያንን እንዳከበራት ይነገራል፡፡

ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን ሳይሆን አማኞችን ነው፤ ክርስቶስ ለሕንፃ አልሞተምና፡፡

ቅዳሜ፦ ቅዱሳት አንስት ሲባል የጌታን አካል ሽቱ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸው፣ ትንሳኤውን ቀድመው ማየታቸው ይሰበክባታል።

እሁድ፦ ዳግም ትንሳኤ ሲባል ለደቀ መዛሙርቱ ለ3ተኛ ጊዜ መገለጡንና ሰላምን መስበኩ ይሰበካል።

ማጠቃለያ

እንደ ክርስቲያን በአብይ ጾም ወቅት የምናሳየው መንፈሳዊ ማንነት ፍሬ የሚያፈራበት ነው። ከአብይ ጾም በኋላ ከትንሣኤው ማግሥት በቤተክርስቲያን ምሥጢር ብዙ መታሰቢያ ነገሮች አሉት አንዱ ሐምሳው ቀናት ከጾም የምንከለከልበትና አርብ እና ረቡዕ ሳይቀር የፍስክ ምግቦችን የምንመገብበት ነው።

ከዚህ በቀረው ከላይ የዘረዘርናቸው ምሥጢራትን ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያው ሳምንት ስያሜ ሰጥታ አመሥጥራ ታስተምራለች።

እኔም ከብዙ በጥቂቱ፣ ከረጅም በአጭሩ፣ አምልቼ አስፍቼ ሳይሆን በማይም አቅሜ አቅርቤያለሁ።

እንደ ክርስትናችን የሁለት ወር መንፈሳዊ ተግባራችን የሚያፈራበት ነው። ጾም፣ ጸሎታችን፣ ስግደት፣ ምጽዋታችን፣ መውደቅ መነሳታችን ያበቃለት ሳይሆን በእምነት የዘራነው መንፈሳዊ ዘር አብቦ የሚያፈራበት ነው።

ነገር ግን አብዛኞቻችን መንፈሳዊነት ያለቀ ሥጋዊነት የተጀመረ እናስመስለዋለን። ፋሲካ ሲሆን ሥጋዊነት እንዲሰለጥንብን አይደለም።

ጾም እና ንሰሐ ገብቶ ቀኖና መቀበል ቢቀር ሌሎች ተግባራት አይቀሩም። ስለዚህ የትንሣኤ ማግሥት የልቡና ትንሣኤ እንዲሆንልን እመኛለሁ።

ይቆየን።
አሜን።

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...