ረቡዕ 8 ኖቬምበር 2017

ትዳር ክፍል 3



ከዚህ ቀደም በሁለት ክፍሎች ስለትዳር መነጋገራችን ይታወሳል፤ ክፍል ሶስትን እነሆ፡፡
"ሰዉ እናቱንና አባቱን ይተዋል፤ … " ባል ከሚስቱ ሚስትም ከባሏ ጋር ይተባበራሉ ሁለቱም አንድ ስጋ ናቸዉና፡፡ በትዳር ዓለም ዉስጥ በባህልም በሃይማኖትም የምንስተዉ ስህተት ይህ ነዉ አንድ አለመሆናችን አለመተባበራችን፡፡ ትዳር አዲስ አለም መመስረት እንደመሆኑ መጠን ሁሉ ከአዲስ መንደር ባልተናነሰ መልኩ ብዙ መሟላት ያለባቸዉ የህይወት መሰረተ ልማቶች አሉ፡፡ እስካልተሟላ ድረስ ችግሮች መኖራቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡ ወደ አንድ የሚያመጣ የፍቅር መንገድ፣ ቁጣን የሚያበርድ የትዕግስት ዉሃ፣ ብዥታን የሚያጠፋ የመተማመን ብርሃን (መብራት)፣ አረፍተ ዘመን እስኪገታን ስንቅ የሚሆን የፍቅር ምግብ፣ አንዳችን ለአንዳችን መከታ ሆነን የምንኖርበት የተስፋ መጠለያ፣
… ወዘተ ግድ ያስፈልጉናል፤ ይህን ጊዜ ሰዉ እናት እና አባቱን ይተዋል፡፡
ባል/ሚስት ይህን መሰረተ ልማት (ትዳር) ሲያጡ የፍቅር ረሃብ ለማስታገስ እናታቸዉ ጋር፣ ተስፋ በማጣት መከታ ወደ ሆነ አባት መሄድ ግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለነዚህ ችግሮች መፍትሔ ሁለቱም ግዴታ አለባቸዉ፡፡ በመሰረቱ እነዚህ ጎደሉ ተብሎ የትም አይኬድም፤ ስንጀምር እንዳነሳነዉ በባህልም በሃይማኖትም የምንስተዉ ስህተት ስለሆነ እንጂ፡፡
ብዙሃን ኢትዮጵያዊያን ትዳር የምንመሰርተዉ እስከቤተሰቦቻችን ስለሆነ አብዝቶ ችግሩ ይስተዋላል፤ ባልም ሚስትን ቤተሰቦቼንማ አትንኪብኝ፣ ሚስትም ባልን በቤተሰቤማ አትምጣብኝ፣ ወዘተ መባባሉን ይጀምራሉ፡፡ ችግሮችን በጋራ እንደመፍታት ችግር ለመፍጠር እንደተደራጀ ቡድን እለት እለት ጭቅጭቅ እና ንዝንዝ የበዛበት ህይወት ይመራሉ፡፡
ቤተሰብም ትዳርን እንደማያዉቅ ወጣኒ (ወጣት) ባለትዳሮች ቤት መመላለስን፣ በእነርሱ ዉሳኔ መካከል ጣልቃ መግባትን፣ አልፎ ተርፎ የሚስት ቤተሰብ ባልን መናገር /ማስቆጣት/ የባልም ቤተሰብ እንደዛዉ አይነት አመል መኖር፡፡ ከዚህም ባሻገር አማችነትን እንደመጦርያ የሚያዩ እና ባለትዳሮችን የሚያስቸግሩ ቤተሰቦች አሉ፡፡
ሰዉ እናትና አባቱን ይተዋል ከተባለ ሰዉ ስለትዳሩ መምከር፣ መወሰን፣ ችግሮች መፍታት፣ … ያለበት በራሳቸዉ ነዉ እንጂ ለቤተሰብ እና ለጓደኛ በማዋየት እና ጣልቃ በማስገባት ትዳር መምራት አስቸገሪ ይሆናል፤ አደጋም አለዉ፡፡ ይህ ማለት ግን ከቤተሰባችን እና ከጓደኞቻችን ግንኙነታችን ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል ማለት አይደለም፡፡ ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ እንደቤተስብነታቸዉ ሊከበሩ እና ሊወደዱ እንዲሁም በተጋቢዎች ዘንድ መልካም ስም እና ቦታ ሊኖራቸዉ እንጂ የጋብቻቸዉ ጠንቅ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ሁለቱም እንደአስፈላጊነቱ ጥንዶች በጋራ መፍታት ያልቻሉት እና የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ካስፈለገ ብቻ እና ብቻ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
ሚስት ለባሏ ባል ለሚስቱ መሆን ያለባቸዉ ምንድን ነዉ? አንዳንዴም ሳይሆን ብዙ ጊዜ በማህበረሰባችን " እናት የሆነች ሚስት/አባት የሆነ ባል/ የሚባሉ የባለትዳሮች ተቀፅላ ስም አለች፤ ይህ ስም አግባብነት የሚኖረዉ / የማይኖረዉ ጊዜ አለ፡፡ ሰዉ ትዳር ሲመሰርት እናት ወይንም አባት ለመሆን ሳይሆን ሚስት ወይንም ባል ለመሆን ብቻ ነዉና፡፡ይህንን  እንደ " ባህል "  እንኳን እናስቀጥለዉ ብንል ከወላጅ አባት የተሻለ አባት ባል አይገኝም፣ ከወላጅ እናት የተሻለች እናት ሚስት አትገኝም እና ባል አባት ከመሆን ባልነት ሚስትም እናት ከመሆን ሚስትነት ስለሚያዋጣቸዉ በዚሁ ቢቀጥሉ ይሻላል፡፡ይህንን ድርሻ መጫወት ከፈለጉ ግን ጥንዶች ለልጆቻቸዉ መልካም አባት እና መልካም እናት መሆን ይችላሉ፡፡ይህን ቢሹ ኖሮ ሁለቱም አዲስ ህይወት ከመመስረት ይልቅ የሞቀ የእናት እና የአባታቸዉ ቤት ቢቀመጡ ይሻላቸዉ ነበር፡፡ትዳር ግን እንደዚያ አይደለም " … አጋር እንፍጠርለት" ተብሎ የተመሰረተ ድንቅ ህይወት እንጂ፡፡
በትዳር ዉስጥ ያለን ተቃርኖ እንዴት ነዉ መፍታት ያለብን? ከወላጆቻችን ልንወርስ ከተገባ መዉረስ ያለብን ድንቅ ጥበብ አለ፤ እነርሱ ፍቅራቸዉንና ሌላ ነገራቸዉን በአደባባይ ሲያደርጉ ችግሮቻቸዉን ከሰዉ ደብቀዉ መኝታ ቤታቸዉን ዘግተዉ፣ ድምፃቸዉን ዝቅ አድርገዉ፣ በመደማመጥ እና በመከባበር ችግሮችን የሚፈቱበትን መንገድ መዉረስ አዋጭ ነዉ፡፡ዛሬ በአደባባይ፣ በጓደኛ፣ በዘመድ/ቤተሰብ፣ በልጆችና በቤት ሰራተኛ ፊት የሚደረጉ አፀያፊ ጭቅጭቅና ፀብ ባያስቀርም ሊቀንስ ይችላልና፡፡ችግሮች መኖራቸዉ የማይቀር እና ወደፊትም የሚኖር ነገር ቢሆንም ቅሉ ሁላችንም ወደ መፍትሔ ከመምጣታችን ትልቁ ሃይል መሆን የሚገባዉ መደማመጥ ነዉ ሰዉ ፈቃደኛ ሆኖ ለማዳመጥ ራሱን ካላዘጋጀ ዉሃ ቢወቅጡት እንቦጭ አይነት ነገር ነዉ የሚሆነዉ፡፡
መፍትሔ ለማምጣት እዉቀት ሳይሆን መሰረቱ የልብ መዘጋጀት ስለሆነ ስለዚህ ሁለቱም ወገን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመቀመጣቸዉ በፊት ለመፍትሔ የተዘጋጀ ልብ ያሻል፡፡ ለዚህ መሰለኝ አለም ላይ ሰላም የሚጠፋዉ/የጠፋዉም ምክንያቱም መሪዎች መፍትሔ ፍለጋ በወንበሮች ዙሪያ ሲሰባሰቡ የአገራቸዉን ጦር ድንበር ላይ አቁመዉ ነዉና እንዲህ ደግሞ መፍትሔ/ሰላም ሳይሆን የሚመጣዉ በልባቸዉ ያለዉ ጦርነት ይቀርባል፡፡ እንደዉም ዛሬ ዛሬ ከመገናኛ ብዙሃን እንደምንሰማዉ መሪዎች በአዉሮፕላናቸዉ ሚሳኤል ማምከኛ እየጫኑ መሄድ እየተለመደ ነዉ፤ ይህ ደግሞ የሚያመላክተን በልባቸዉ ያለዉ ምን እንደሆነ ነዉ፡፡ጥንዶችም ለምፍትሔ ሲነጋገሩ ከበስተጀርባ ያሉ ቱባ ዘመዶቻቸዉን እና ጡንቻዎቻቸዉን ሳይሆን የሚመጣዉን ሰላም ቢሆን መልካም ነዉ፡፡ፍቺን፣ ፀብን፣ ሃብትን፣ … በማሰብ ከሆነ ግን አደጋ አለዉ፡፡
ሰዉ እናትና አባቱን ሲተዉ ምን ሊጠብቀዉ ይገባል? ትዳር የሁሉ መዳረሻ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ነገሮች ሊደረጉ እና ሊጠበቁ ይችላሉ በዋናነት ግን ባል ሚስቱን በንፁህ ፍቅር ሊያፈቅራት ሚስትም ለባሏ ልትታዘዘዉ ይገባል፡፡ እንዲህ ስንል መፎካከር በሌለበት አጉል "ዘመናዊነት" ባልተንሰራፋበት ንፁህ መንፈስ ማለት ነዉ፡፡ጥንዶች ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ስለሚበላ ስለሚጠጣ ነገር መጨነቅ የለባቸዉም በዚህ የተነሳም ልባቸዉ ወደኋላ ሊል አይገባዉም፣ ልብስና መጫሚያ መጠለያ እና ቁሳቁስ የመነጋገሪያ ርዕስ መሆን የለበትም፣ ሰርተዉና ተነጋግረዉ የሚፈቱት ስለሆነ… አንድም ባል ይህን ሊያደርግ ካልቻለ ትዳር መመስረቱ አስፈላጊነቱ አይታየኝምና፡፡ ምክንያቱም ባል የቤቱ ራስ ስለሆነ፤ ከጊዜ በኋላ የመጣ ከሆነ ግን ሚስት ይህን ግምት ዉስጥ በማስገባት ልትረዳዉ እና ልታግዘዉ ይገባል፡፡ሚስት ከሞቀ ቤቷ ከሚወዷት ቤተሰቦቿ መካከል ትዳሬን ብላ ተነጥላ ስለመጣች እንክብካቤ ያስፈልጋታል፣ ባልም አንቺ ትብሺብኛለሽ ብሎ እርሷን ስለመረጠ ክብር ይገባዋል፣ … በጋብቻ ከተሳሰሩ ቤተሰብ ከሆኑ በኋላ ወደ ኋላ ማለት ግን ሞፈር ጨብጦ ወደኋላ እንደሚያይ ገበሬ መሆን ነዉ፡፡
የጥንዶች ተግባር እና ዓላማ ምንድን ነዉ? በዋነኛነት ይህን ህብረት የፈጠሩበት ዋና ምክንያት 1ኛ. ዘር ለመተካት 2ኛ. ለመተጋገዝ 3ኛ. ከፍትወት (ከዝሙት) ራስን ለመጠበቅ ነዉ ስለዚህ በምክክር እና በእቅድ ዘርን መተካት (ልጅ መዉለድ) ይጠበቅባቸዋል፣ ኑሮንም ሆነ ሌሎሽ ሸክሞችን በሃሳብም ሆነ በተግባር መተጋገዝ አለባቸዉ፣ አታመንዝር የሚለዉን የፈጣሪ ቃል ለመጠበቅ ወደ ሌላ በማየት እንዳይመኙ እና ስሜታቸዉን ልቅ እንዳያደርግ በሚያስችል መልኩ ተጠብቀዉ እንዲኖሩበት የተሰጠ የፈጣሪ መልካም ፈቃድ ነዉ፡፡
ጥንዶች መለያየት ይችላሉ ወይ? ዛሬ የሁላችንም ራስ ምታት የሆነ ሰዉንም ፈጣሪንም ያሳዘነ ጉዳይ ቢኖር የፍቺ እና የቤተሰብ መበተን ጉዳይ ነዉ፡፡ጉልበትን በጎመን ቢደልሉት በዳገት ይለግማል እንዲሉ ከጋብቻ በፊት ያልተደረገ ጥልቅ ዝግጅት ትዳር ዉስጥ መሰረት የሚያናጋ አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ተጋቢዎች ለጋብቻ ምስረታ ያላቸዉን ቀላል አመለካከት ትዳርን ለማፅናት ወይንም ግጭትን ለመፍታት አንጠቀምበትም/ እናካብዳለን/፡፡ለመጋባት የምናደርገዉን ጥድፊያ ለፍቺም እንተገብረዋለን፤ የትዳር / ጋብቻ ጥድፊያ ቤትን በአሸዋ ላይ እንደመመስረት ሲሆን ትዳርን ማፍረስ ትዉልድን በጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ማጥፋት ያህል ከባድ ነገር ነዉ፡፡ስንጠቀልለዉ ትዳርን ማፍረስ ግንኙነትን መበተን የሚቻለዉ በሁለት ምክንያት ብቻ ነዉ አንደኛ በሞት ሁለተኛ በዝሙት ምክንያት ሆኖ ያንን ጥንዶች ተቀብለዉ በቀኖና / በንስሐ/ ተመልሰዉ አብረዉ መኖር የማይችሉ ከሆነ ነዉ፡፡
ቤተሰብ ፣ ጓደኛ ፣ ተጋቦዎች … ይህን ሁለት ሰዉ አንድ የሚሆንበትን ምሥጢር ማፍረስ አይችልም፡፡በቃ ተለያዩ ስለተባለ፣ በቃ አብረን መኖር አልቻልንም ስላን ብቻ፣ … መለያየት አይቻልም፡፡ምናልባት ዛሬ የምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ በእያንዳንዳችን መኝታ ቤት ስለገባ መልሶ መላልሶ ወደ ህሊናችን ስለሚመጣ እንደመፍትሔ እየተጠቀምን ያለነዉ መለያየትን ነዉ፡፡ከዚህም ባሻገር ዘመናችን ኑሮን የሚያቀሉ የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን ስላጎናፀፈን ሁሉንም ነገር ካልቀለለ አይመቸንም ይህ ደግሞ አሉታዊ ነገር እንዳለዉ ሁሉ አዎንታዊ ነገርም አለዉና በህይወታችን ነገሮችን ሩቅ መንገድ ሄደን መፍትሔ ማምጣት አንወድም፡፡ይህ ዘመኑ የወለደዉ ነቀርሳ ነዉ፡፡
"መጠናናት" ዘመናዊያን አሊያም ዘምነናል ያሉ ሰወች በመጠናናት ስም ዕድሜያቸዉን ከማባከናቸዉ ባሻገር ግቡን ሊመታ የማይችል ጉንጭ አልፋ ልፋት ሲዳክሩ ይታያል፤ በመሰረታዊነት መጠናናት ምንድን ነዉ? ምንድን እናጠናለን? ማንን እናጠናልን? አጥኚዉ ማነዉ? የጥናቱ መስፈርት እና መለኪያ ምንድን ነዉ? አስፈላጊነቱስ?የት መጣዉስ?ዉጤቱስ? 
ይህንን እና ሌሎችን በክፍል አራት እንመለስበታለን መልካም ጊዜ፡፡



ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...