ማክሰኞ 3 ዲሴምበር 2024

ትቶ እና ችሎ

 ትቶ እና ችሎ

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ


በደረሰ ረታ

ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። በምክራቸውም ይሁን በሕይወታቸው ያስተማሩን ይህንን ነው። በዘመናቸው የመጡትን ፈተናዎች በመተው እና በመቻል ነበረ ያሳለፉት። የሚተወውም ሆነ የሚቻለው ነገር እንዲህ ቀላል ሆኖ አልነበረም። ሁሉን በሚችል/በሚያስችል በአምላካቸው ቸርነት ችለውት እንጂ። የአባታችን በረከታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን።
የቤተእምነት አባቶች እንደ የ ደረጃቸው ይህ አይነት አስተዋይነት በመሪነታቸው ወቅት ይጠበቅባቸዋል። መንጋውን ለመጠበቅም ይሁን ለአስተዳደራዊ ውሳኔ ሰጪነታቸው ይህን መንገድ መከተል ግድ ነው።
በመንግሥት ደረጃም ያሉ ባለስልጣናት (የክልልም ሆነ የፌዴራል) ሕዝባቸውን ሲያስተዳድሩ፣ ውሳኔ ሲሰጡ፣ ግጭቶችን ሲፈቱ፣ ይህ የሚጠበቅባቸው ጉዳይ ነው።
የተቋማት አስተዳዳሪዎች በየእርከናቸው ሰራተኞቻቸውን ሲመሩ እና ሲያስተዳድሩ፣ ውሳኔ ሲያሳልፉ እና ልዩነቶችን የመፍትሔ አቅጣጫ ሲጠቁሙ በማስተዋል ሊሆን እንደሚገባ አስተማሪ ተግባር የሚሻ ቃል ነው ትቶ እና ችሎ መኖር።
ሰው ከብቸኝነት ወጥቶ ሁለት እና ከዚያ በላይ ሆኖ ሲኖር፣ በትዳር ሲጣመር፣ የጋራ ዓላማ ካለው ወዘተ ሁሌም ሁሉም ወገን አንድ ነገር ያስባል፤ በአንድ ነገር ላይ በእኩል ያምናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
አብሮ ለመኖር፣ የጀመሩትን ለማስቀጠል፣ ልዩነቶችን ለማጥበብ፣ ግጭቶችን ለማስቀረት አማራጭ ከሌላቸው መፍትሔዎች አንዱ ትቶ እና ችሎ መኖር ነው።
ትቶ እና ችሎ ሲባል የምንተወው እና የምንችለው ነገር የማይጠቅም እና የሚቻል ሆኖ አይደለም። ነገር ግን ሁለቱም ከአብሮነት ስለማይበልጡ እንጂ። አንድም በማጣት ውስጥ ማግኘት ስላለ እንጂ። አንድም በዚህ የተነሳ የምናገኘው ከምናጣው ነገር ስለማይበልጥ እንጂ።
በዓለም ላይ መንግሥታት ሆኑ ሁለት ተደራዳሪዎች ችግሮችን የሚፈቱት ወደ አንድ የሚመጡት win win በሆነ መንገድ ነው። win win ሲባል ሁለቱም አሸናፊ በሚሆኑበት መንገድ ነው። አሸናፊነት ስንል ሁሌም ማግኘት ማጣት የሌለበት ማለታችን አይደለም። የተወሰነ ሰጥት የተወሰነውን ተቀብሎ፤ የሆነውን ነገር እየተወ የሆነለትን አስከብሮ መሄድ እንጂ።
ለምሳሌ በትዳር ውስጥ እውነቱን ከተነጋገርን አብዛኛውን ጊዜ ከምንግባባበት የማንግባባበት ይበልጣል። ምክንያቱ ግን ስለምንጠላላ አይደለም። ከሁለት ዓለም፣ ከሁለት ቤተሰብ የአስተዳደግ ሁኔታ ውስጥ፣ ከተለያየ ልማድ እና አስተሳሰብ ካለው ማኀበረሰብ ውስጥ፣ ከተለያየ አመለካከት እና አረዳድ ውስጥ ስለመጣን እንጂ።
በየተቋማቱ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ከሚመሯቸው እና ከሚያስተዳድሯቸው ጋር የሐሳብ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ልዩነትን በተለመደ ቋንቋ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይጠበቅባቸዋል። (በጠረጴዛ ዙሪያ ሲባል ጠረጴዛ ችግሩን ይፈታዋል ማለት ሳይሆን በአንድ ጉዳይ ላይ ወደ አንድ ነጥብ ላይ መስማማትን መግባባትን ለማመላከት ነው።) በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ መሰባሰብ ችግር መፍታት እንደማይችሉ ዓለም ላይ የተከናወኑ የጠረጴዛ ውይይቶች ማሳያ ናቸው።
በጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት የሚቀመጡ ወገኖች ሊሸነፉበት የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አምነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ይህንንም ሲያደርጉ ከበስተጀርባ የሚመሩትን ሕዝብ (ሰራተኛ ) ጥቅምና እና ጉዳት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል።
እንደዚህ አይነቱ ልዩነት ጤናማ ነው። ከሁለት የሚወጣ አንድ ጥሩ እና ጠንካራ ነገር ስለሚገኝ። ይኽ እስኪሆን ደግሞ የሚያለያየንን ጉዳይ በመተው እና በመቻል ማሳለፍ ይጠበቅብናል። እኔ ብቻ የበላይ ልሁን እኔ ብቻ ላሸንፍ የምንል ከሆነ በዚህም መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ከምናገኘው/ልናስከብር ወይም ልናስፈጽም ከምንችለው በላይ እናጣለን።
ስለዚህ ነገሮችን መቋጨት ያለብን በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆን አለበት። ይህ መርህ ሁለቱንም ወገን አሸናፊ ያደርጋል።
ካልሆነስ ነው?
አያድርግብንና ከሆነ ምላሹ የከፋ ነው። አንድነት ይከፈላል፣ ትዳር ይበተናል፣ ቤተሰብ ይፈርሳል፣ ልጆች ወላጅ (እናት/አባት) አልባ ይሆናሉ፣ ጠንካራ የነበረው የኑሮ ደረጃ ይናጋል፣ አገር ማህበረሰብ ዘመድ አዝማድ መሠረቱ ይናጋል።
በጥቂት የቃላት ጦርነት የተጀመረ አለመግባባት ነፍጥ አስመዝዞ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል። ጸብ ይፈጠራል። ሥራ ይበደላል። ኢኮኖሚው ይናጋል። የሰው አኗኗር ይበላሻል። ሕይወት ይቀጠፋል። ንብረት ይወድማል። አካል ይጎድላል። እንደዚህ ሲሆን ሊተመን የማይችል ኪሳራ ይደርሳል።
መሰል ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በጥልቅ አስተዋይነት እና በበሳል አመራርነት ነው። በሳል አመራርነት እኔ ይድላኝ፣ እኔ ያልኩት ይሁን፣ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ፣ ወዘተ ሳይሆን የሚለው በመሸነፍ ለማሸነፍ ከእኔ ይቅር በማለት እያወቀ ይተዋል። ይሸነፋልም።
በትዳር ውስጥ ለሚከሰቱ ልዩነቶች በጎ አስተዋጽኦ ያላቸው ሰዎች እንዳሉት ሁሉ ተግባራቸው ከሰይጣን የሚብሱ አሉ። በሰው ቁስል እንጨት እየቆሰቆሱ የራሳቸውን የሚኖሩ ነገር ግን በሌላው ላይ ከዳር ሆነው የሚፈርዱ አሉ። ልዩነቶቻቸውን በማስፋት፣ ግጭታቸውን በማጉላት እርባና ቢስ የሆነ ፍርድ የሚሰጡ አሉ።
አጀማመሩ ትንሺ የሚመስል አፀፋው ግን ከባድ የሆነ ችግር ይዞ ይመጣል። የስነልቦና ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ወዘተ ይዞ ይመጣል። ስለዚህ ሁሉም ሰው ከእንዲዚህ አይነት ክስተት ከሚመጣ ጉዳት ራሱን ለመታደግ አስቀድሞ የሥነልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ደግ አሳቢ መስለው የተለኮሰው ላይ ቤንዚን የሚረጩ እና የሚያቀጣጥሉትን በንቃት መከታተልና ሊከላከላቸው ይገባል።
እንዲህ አይነት ተግባራት በአገራችን እንኳን በፖለቲካው፣ በየ ቤተ እምነቱ፣ በትዳር ውስጥ፣ ወዘተ ክስተቶችን መታዘብ ከጀመርን ከረምረም ብለናል። አሁንም ለነዚህ ተግባራት የሚተውን ትቶ የሚቻለውን ችሎ በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር መፍታት የሰጥቶ መቀበልን መርህን መከተል ግድ ነው። ካልሆነ ውጤቱ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል።
ሁላችንንም እግዚአብሔር ይርዳን፤ ያጋጠሙንን ችግሮች የምንተውበትን እና የምንችልበትን ጸጋ ያድለን።
ይቆየን።

ሰኞ 29 ጁላይ 2024

ሊንኩን subscribe ታደርጉ ዘንድ …

 በመላዉ ዓለም ያላችሁ የዚህ ገጽ ተከታታዮች ተደራሽነቴን ለማስፋት ያግዘኝ ዘንድ በዩቲዩብ ልመጣ ስለሆነ በቅንነት subscribe እንድታደርጉ ሊንኩን አስቀምጫለሁ፡፡

https://www.youtube.com/channel/UCAr1hYmoE-E5Cu1p8Ba8B5g




ሐሙስ 28 ማርች 2024

የጋብቻ እና የቤተሰባዊ ሕይወት ትምህርት

  •  

የጋብቻ እና የቤተሰባዊ ሕይወት ትምህርት

ትንሿ ቤተክርስቲያን

ቤተክርስቲያን፡-

1.     የምዕመናን አንድነት

2.     እያንዳንዱ ክርስቲያን

3.     ሕንጻ ቤተክርስቲያን

3.1  ሥጋዉ እና ደሙ የሚፈተትበት

3.2  ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምንወለድበት

3.3  ቃለ እግዚአብሔር የምንሰማበት

3.4  በእግዚአብሔር ደም የተመሰረተች

የዚህ ትምህርት ዓላማ

Ø  ቤተሰብ ስንመሰርት ትልቅ ተቋም እንደመመስረታችን ስለዚህ ተቋም ግንዛቤ እንዲኖረን ነዉ

Ø  ሠላማችን፣ የአገር ሠላም፣ የተቋማት ሠላም፣ የፖለቲከኛ እና የፖለቲካዉ ሠላም እንዲመለስ

Ø  በዚህ ተቋም ፍሬ አፍርተን ለልጆቻችንም እንድናወርስ (እንድናስገነዝብ) የትዳር ሕይወታችን በበጎ ጎኑ የሚነበብ መጽሐፍ እንድንሆን

Ø  ጥያቄዎቻችን መልስ እንዲያገኙ እንዲሁም ተጀምሮ የሚያልቅ ትምህርት የለምና ይህ መርሐግብር እንደማስጀመሪያ ሆኖ ለቤተሰብ የመወያያ እና የመማማሪያ መድረክ  ማስጀመሪያ እንዲሆን

Ø  የሚታየዉን ክፍተት (የፍቺ ጉዳይ) በአንፃራዊነት በመጠኑም ቢሆን ችግሩን ከሥሩ ለማቅናት የታሰበ ነዉ፤ በከተማችን ባለ መረጃ ከጋብቻ ባልተናነሰ መጠን ወሳኝ ኩነት በፍቺ ጉዳይ ተጠምደዋልና (መረጃዉ እንደ ክፍለ ከተtማዉ እና እንደ ወቅቱ ስለሚለያይ አሃዛዊ መረጃን ማቅረብ ይከብዳል፤ የሚያመላክተዉ ግን ከፍተኛ የትዳር ፍቺ እንዳለ ነዉ፡፡)

Ø  በትዳርና በባለ ትዳር መካከል ለሚነሱ ጥያቄዎች በጋራ በመነጋገር እንደ ቤተክርስቲያን አስተምሮ ምላሽ ለመስጠት

ü  ጋብቻ ምንድን ነዉ?

ü  ለምን ዓላማ ተሰጠ?

ü  እንዴትስ ይኖራል?

v  ስለዚህ ስለ ጋብቻ እና ቤተሰባዊ ሕይወት ምንነት እንዲሁም ዓላማ በትክክል ተመልክቶ ለመወሰን ከመጀመሪያዉ ከገነት አንስቶ በምድር አልፎ እስከ መንግሥተ ሰማያት ድረስ ያለዉን ሒደት ባለትዳር ከቤተክርስቲያን ትምህርት ባሕር ዉስጥ ገብቶ እንደ አቅሙ ቀድቶ መጎንጨት አለበት፡፡

v  በአጠቃላይ ምን? ለምን? እንዴት? የሚለዉን ጥያቄ ለራሳችን እንመልሳለን፡፡

v  በአጭሩ ጋብቻን መመስረት ትንሿን ቤተክርስቲያን ማነጽ ነዉ፡፡

v  ጋብቻን ስናስብ

o   ቅድመ ጋብቻ (የእጮኝነት ጊዜ)

o   በጋብቻ ጊዜ እና በትዳር ዉስጥ (ሁለት ጥንዶች ትዳር መስርተዉ ባለበት ጊዜ)

o   ከጋብቻ በኋላ (ልጆች ወልደን ቤተሰብ በመሰረትን ጊዜ) ስለሚመጣዉ ማወቅ ነገሩን ሙሉ ያደርገዋል፡፡

*     እነዚህ ከላይ የነደፍናቸዉ የመወያያ እና የመማማሪያ ርዕሰ ጉዳዮች ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ዓመት እንደሚፈጁ ይገመታል፡፡ ነገር ግን በዚህ ምድር የምንኖርበት እንዲኖረንም ላይ ታች የምንልለት ቤት ታቅዶ ከተጀመረ ይህን ያህል ጊዜ አይፈጅም፡፡

ማሳሰቢያ፡- ይህ ትምህርት ከቤተክርስቲያን እና እዉነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወት የተቀዳ የቤተክርስቲያን መምህራን የሚያስተምሩት የንስሐ አባቶቻችን ከሚመክሩን እና ከሚያስተምሩን ጥቂቱ እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል፡፡

መግቢያ

የሰዉ ልጅ ከዉድቀት በፊት

ü  ግዚአብሔር የሰዉ ልጅን ሲፈጥረዉ እንደ መላእክት (ለባዊ፣ ሥጋዊ መሻት የሌለባቸዉ፣ ከኋጢያት የነጹ) አድርጎ ነዉ፡፡

ü  የሰዉ ልጅ ሲፈጠር ምንም እንኳን ሥጋን የለበሰ ቢሆንም ያልተለመደ ዓይነት መልአክ ሆኖ ነዉ የተፈጠረዉ፡፡

ü  ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ " ሁለት መላእክት " ይላቸዋል፡፡

ü  የሰዉ ልጅ ይህ ድንቅ አፈጣጠር ( ምንም እንኳን ሥጋን የለበሰ ቢሆንም እንደ ረቂቃን መላእክት መኖሩ በአንድ ጊዜ ረቂቅና ግዙፍ ፍጥረት መሆኑ ) ሳጥናኤልን (ዲያቢሎስን) አስቀናዉ፡፡

ü  ይህ ሰዉ ለሞት የተፈጠረ አልነበረም ማለት ሞት የሚስማማዉ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቆ ( የመጀመሪያዉ ሰዉ አዳም አትብላ የተባለዉዉ ዕፀ በለስ ባይበላ) ቢኖር አይሞትም፡፡

ü  ሰዉ ዉብ፣ ለባዊ፣ መልካም ሥራዎችን ለመስራት አቅም ያለዉ ሆኖ የተፈጠረ ነዉ፡፡

ü  ስለዚህ ግሩም አፈጣጠር ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሲናገር " ከዚህ ክብር የሚበልጥ ምን ክብር አለ? ከዚህስ ትምክህት የሚበልጥ ምን የሚያስመካ ነገር አለ? … ሰዉን በእርሱ አምሳል እንደ ፈጠረዉ እንዲመሰክር ከመሆን የበለጠ የሚያስመካ ምን ነገር አለ? " ይላል፡፡

                                                                        ሐይማኖተ አበዉ 36÷12 (ዘፍጥረት 1÷26)

ü  የሰዉ ልጅ ሞት ሕማምና ድካም የመጣበት ከዚህ መልካም ሥፍራ ከገነት የተባረረዉ ከነበረበት የንጽህና ሕይወት ፈቀቅ በማለቱ ነዉ፡፡

ü  የሰዉ ልጅ መዋቲ የሆነዉ ከበደለ በኋላ ነዉ፡፡

ü  የሰዉ ልጅ አፈጣጠሩ ከአራቱ ባህሪያተ ሥጋ

·       ነፋስ

·       እሳት

·       ዉኃ እና

·       መሬት

                                          ከሦስቱ ባሕሪያተ ነፍስ

o   ለባዊት፣

o   ነባቢት፣

o   ሕያዊት

ነዉ፡፡ ቢሆንም ክብሩ ግን ሰማየዊ ነበር፡፡

ü  እንዲህ ከመፈጠሩ የተነሳ ስለሚበላዉ ስለሚጠጣዉ ስለሚለብሰዉ ስለ እንቅልፍ ስለመስራት ስለ አጠቃላይ ኑሮን በተመለከተ የሚጨነቅ አልነበረም፡፡

ü  ይበላ የነበረ ቢሆንም ጥሮ ግሮ የሚበላ አልነበረም፡፡ ዛሬ እርቃኑን የሚሸፍንበት ልብስም ያኔ አልነበረም (የክብር ልብስ ነበረዉ እንጂ)

ü  አዳም ይለብሰዉ የነበረዉን የክብር ልብስ አይደለም ሌሎች ፍጥረታት ዲያቢሎስ እንኳን ማየት አይቻለዉም ነበረ፡፡

ü  አሁን የምንለብሰዉ ልብስ ለዚያ የክብር ልብስ ያልተገባን ሆነን ባለመገኘታችን ብቻ ሳይሆን ላለማመናችን፣ ላለመታዘዛችን ማዘከሪያ እንዲሆን የተሰጠን ነዉ፡፡

ü  ፍርሐት እና መንቀጥቀጥ የመጣበት ከበደል በኋላ ነዉ፡፡ ሔዋን ከእባብ ጋር መነጋገሯ ይህን የሚያሳይ ነዉ፡፡

ü  የሰዉ ልጅ ከመበደሉ በፊት አዋቂ፣ ጠቢብ፣ ነፃነትም የነበረዉ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔርም ጋር አፍ ለአፍ ይነጋገር ነበር፡፡

ጋብቻ ከዉድቀት በፊት

§  በገነት ዉስጥ የነበረዉ የአዳም እና የሔዋን አንድነት አሁን ከምናዉቀዉ የባልና ሚስት አንድነት የሚለይ ነበር፡፡

§  በገነት ዉስጥ የነበረዉ የአዳም እና ሔዋን አንድነት ምሥጢራዊ አንድነት ነዉ፡፡ ( ከፍትወት ነፃ የሆነና መንፈሳዊ ነበር)

§  የሔዋን ረዳትነት የአሁኑ ዓይነት ረዳትነት አይደለም፡፡ (እንዳታዋራዉ፣ እኩል ክብሩን እንድትጋራዉ፣ በሁለንተናዉ እርሱን እንድትመስል፣ እግዚአብሔር የሰጣቸዉን ትዕዛዝ ከመጠበቅ ረገድ እንዲተጋገዙ ነበር፡፡)

§  አሁን ያለዉ ጋብቻ የመዋትያን ጋብቻ ነዉ፡፡ አንዳቸዉ በሞት እስኪለዩ ድረስ አብረዉ የሚኖሩበት፡፡

§  የሩካቤ ፍላጎት፣ ፅንስ፣ ምጥ፣ ልጅ መዉለድ፣ እና ሁሉም ዓይነት ሙስና (ሥጋዊ መከራ) ከነፍሶቻቸዉ ዉስጥ አልነበሩም፡፡

§  ለሰባት ዓመት እንደ መላእክት ኖሩ፡፡ ኩፋሌ 4÷14-16፣ 5÷6 (ይህንን ያጣነዉን ክብር ትንሣኤ ዘጉባኤ ይመልስልናልና በዚያን ጊዜ ማግባት መጋባት የለምና)

§  አዳምና ሔዋን በገነት በንጽሕና በድንግልና ይኖሩ ነበረ ስንል የነበራቸዉ ድንግልና አሁን ካለዉ ድንግልና በእጅጉ ይለያል፡፡ አሁን ያሉት ደናግላን በነቢብ፣ በገቢር፣ ድንግል ቢሆኑ በሐልዮ ደናግል አይሆኑምና፡፡ (የእመቤታችን ድንግልና ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ጸኒስ (ከመጽነሷ አስቀድሞ)፣ ጊዜ ጸኒስ/በወለደች ጊዜ (በጸነሰች ጊዜ)፣ ከወለደችም በኋል ድንግል ነበረችና፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ በሃልዮ፣ በነቢብ፣ በገቢር ድንግል ነች፡፡ ከሰዉ ልጅ ተፈጥሮ እስከ ዛሬ እንደ እርሷ ዐይነት ድንግልና ያለዉ የለም፡፡)

§  አዳምና ሔዋን በሐልዮ (በሐሳብ) ፣ በነቢብ (በንግግር)፣ በገቢር (በተግባር) ደናግላን ነበሩና የነርሱ ድንግልና ዛሬ ካለነዉ ሰዎች ይለያል፡፡

የሰዉ ልጅ ከዉድቀት በኋላ

·       የሰዉ ልጅ የተለወጠዉ በእግዚአብሔር ላይ ሲያምፅ ነዉ፡፡ አመፃዉም አታድርግ የተባለዉን ማድረጉ ነዉ ይኸዉም ዕጸ በለስን ቀጥፎ መብላቱ ነዉ፡፡ በዚህን ጊዜ ፡-

o   መንፈስ ቅዱስ ተለየዉ

o   የክብር ልብሱ ተወሰደበት

o   ሐፍረትና ዉርደት አገኘዉ

o   ከመላእክት ሕይወት ወረደ የዚህ ዓለም ጭንቀት የሚገዛዉ ሆነ

o   ጥሮ ግሮ የሚበላ ሆነ

o   የፀጋ ልብሱ ተገፍፎ ልብስ ከእንስሳት ቆዳ የሚገኝ ቆዳ ሆነ

o   ፍትወታት እና ሥጋዊ መሻቶች የሚጸኑበት ሆነ

o   የሚርበዉ፣ የሚጠማዉ፣ የሚደክምና የሚሞት ሆነ

o   እንደ እንስሳት የሚኖር አላዋቂ ሆነ (የሰዉ ልጅ የመጨረሻ ዉርደት)

o   ባሪያ እና እጅግ አሳዛኝ ሆነ

ጋብቻ ከዉድቀት በኋላ

*     አሁን የምናዉቀዉ ጋብቻ ‹‹ ሰዉ አባቱን እና እናቱን ይተዋል በሚስቱም ይጣበቃል›› ዘፍጥረት 2÷24

*     ሰዉ ማለቱ ወንድ ልጅ ቅድሚያ የሚወስደዉ መሆኑን የሚገልጽ መሆኑን ያስገነዝባል

*     በመጀመሪያ ከአምላኩ በመቀጠልም ከመላእክት ማህበር እንደተለየ ከሔዋንም እንዳይለይ ሲል ትዳርን (ጋብቻን) ሰጠዉ

                                               ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ

*     ‹‹ ከሴት ተለይተህ ንጽሕ ጠብቀህ መኖር ከከበደህ እንኪያስ ቀላልና ደኁን የሆነዉን የጋብቻ ሕይወት አለልህ›› ይላል፡፡

 

ጥያቄ

ጥንቱን አሁን የምናዉቀዉ ዓይነት ጋብቻ ካልነበረ የሰዉ ልጅ እንዴት ይበዛ ነበረ?

ይቆየን

በክፍል ሁለት እንቀጥላለን

ረቡዕ 24 ጃንዋሪ 2024

"ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ"

 

"ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ገላትያ 6÷14

ይህን መልእክት የጻፈልን ከሐዋርያት ጋር ለሐዋርያነት ያልተመረጠው ይልቁን ሐዋርያትን በማሳደድ የሚተባበረው ከሐዋርያት መካከል እንደ አንዱ የሚቆጠረው ቅዱስ ጳውሎስ ነው።

መልዕክቱ የተጻፈው በገላትያ ቤተክርስቲያን ለሚገኙ ምዕመናን ነው። ገላትያ፦ ቱርክ ውስጥ የምትገኝ አንድ አውራጃ ነች።

ቱርክ ቅዱስ ጳውሎስ ለወንጌል አገልግሎት ሲሰማራ ካገኛቸው ከተሞች አንዷ ነች።

በገላትያ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት በቅዱስ ጳውሎስ የተመሰረቱ ናቸው።

የገላትያ ሰዎች ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሯቸው ከሄደ በኋላ ካስተማራቸው ትምህርት ቢያፈገፍጉም (ስለግርዘት ተምረው ነበረ ያፈገፈጉት) በመጨረሻም ተጸጽተው ተመልሰዋል።

ይህ መልዕክት የመጀመሪያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት እንዳልሆነ ይነገራል። መልዕክቱ ጠጠር ያለ እና ከበድ ያለ መልእክት ነው።

የመነሻ ቃላችን ሙሉው እንዲህ ይላል።

 

ቃና ዘገሊላ

 ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡



የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡

በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ?

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...