ቢቻላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ
#######################
ደረሰ ረታ
ክፍል አንድ
የሰው ልጅ በምድራዊ አኗኗሩ ከሰው ጋር ሲኖር አኗኗሩን የሚለካበት ሶስት ዋና ዋና ሥፍራዎች አሉት።
1. በመኖሪያ ቤት እና አካባቢው
2. በመሥሪያ ቤት
3. በቤተክርስቲያን
ከነዚህ የአኗኗር ዘይቤ የወጣ ማንነት የለንም። ምናልባት እውነተኛዎች በረኸኛ መናኒ ባህታውያን ካልሆኑ በቀር፤ የከተማ ባሕታውያንን ሳይጨምር።
ከላይ ለተጠቀሱት እንደ ሰው የምንኖርባቸው ሥፍራዎች ዋና መሰረቱ መቻቻልና መከባበር ናቸው ከዚህ የወጣ አላማ የለውም።
በጥቂቱ ለመዳሰስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባሻገር ሁለት መጻሕፍትን ዋቢ አድርገን ዳሰሳችንን እንቀጥላለን። "ክርስትና በማኀበራዊ ኑሮ" ኅሩይ ስሜ እና ዳዊት ደስታ ያዙጋጇቸው እንዲሁም "በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል አለን?" በብጹዕ አባኑ ሳሙኤል የተዘጋጁ።
መልካም አኗኗር ለመልካም አስተዳደር ትልቅ ሚና ስለሚጫወት አሰናስለን እንመለከታለን።
የሰው ልጅ ከ22ቱ ሥነ ፍጥረት የሚለይበት አንዱና ዋነኛው ነገር በሕግ እና በሥርአት መኖሩ እና አንዱ የሌላኛውን መብት እና ነጻነት አክብሮ መኖሩ ነው።
ከሌላው ዓለም ኢትዮጵያውያንን ለየት የሚያደርገን ባህሪይ እና ባህል አለን። ባህላችን እንግዳ ተቀባይ ሕጋችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሰውን አክባሪ መሆናችን ነው።
ለነዚህም ተግባራችን እንደ ምሳሌ በቀዳሚነት የምንመለከተው "ኢትዮጵያውያን የሰውን ሰብአዊ መብት በመጠበቅ አንፃር በመልካም አስተዳደር ሂደት በ70 ዓ.ም በጥጦስ አማካኝነት የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሲፈርስና ኢየሩሳሌም ስትወረር በርካታ አይሁዳውያን ፈላሻዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ኖረው ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የክርስትናን ሃይማኖት ገና በ34 ዓ.ም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ብትቀበልም (የሐዋርያት ሥራ 8:29) አይሁድ ክርስቶስን የሰቀሉ ናቸው በማለት ማረፊያ አልተከለከሉም።"
የሰው ልጅን አክባሪነቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ የመነጨ ነው፦ የራሱን ፈቃድ ሲፈጽም የሌላውን ወገኑንም ሆነ ባለጋራውን (ጠላቱን) ጨምሮ ህሊና ጠብቆ የሚኖር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 8:11 " ሰዎች በአንተ ላይ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን ነገር እንዲሁ በባልንጀራህ ላይ አትፈጽም ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትሹትን በሙሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው" በሚል መርህ የሚመራ ነው።
ከሕግም አንጻር የእያንዳንዱን ግለሰብ ተፈጥሯዊ እና መሠረታዊ የሆኑትን መብቶች ያከብራል። ለማስከበርም ይጥራል። እነዚህም፦
1. ፖለቲካዊ ነጻነት
2. ማህበራዊ ነጻነት
3. ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ናቸው።
ከሕግ አግባብ እነዚህን ሶስት ነጻነቶች በጠንካራ መሠረት ላይ ከታነጹ ሕዝብም አገርም አትናወጽምና።
ለክርስቲያኖች ቅድስት ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ ከሙሴ ሕግ ጀምሮ እስከ አዲስ ኪዳን ሕግ ድረስ ትምህርቷ ፍቅር፣ ሠላም፣አንድነት፣እኩልነት ነው። "ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ" በሚል አስተምሮ ታንጻለች።
ከዚህ በመነሳት የሌሎች አገራት ዜጎችና መሪዎች እምነት ተከታዮች ሳይቀር ይሰደዱባታል፤ ይጠለሉባታልም። የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን፣ የፖለቲካ መሪው ኒንሰን ማንዴላ፣ ማህተመ ጋንዲ፣ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ማሳያዎች ናቸው። በግንባራችን እንጂ በጀርባችን ጥይት አይመታንም ያሉ ጀግኖች አባቶቻችን ይህችን ድንቅ አገር እስከ ሙሉ ክብሯ አስረክበውናል። እኛስ?
ዛሬ ከላይ የጠቅስናቸው ተግባራትና መገለጫችን እየቀጨጩ ይገኛሉ። እኛ ዘመን ጋር ሲደርሱ ለምን ይህ ሆነ?
ዘመኑን ካየን የዘመነ፣ የሰለጠነ፣ በእውቀት የመጠቅንበት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዝንበት ሲሆን ደካሞች ነን።
• ከባቢያዊ ግጭቶች በርክተዋል
• ሽብራዊ አመጽ በተለያዩ ሥፍራ ይቀሰቀሳል
• የጦር መሣሪያ ዝውውር በርክቷል
• ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው በሽታዎች/ወረርሽኞች ተበራክተዋል።
ነገር ግን ይህንን ማስቀረት አልቻልንም። ለምን?
ዲሞክራሲ የብዙሃን የበላይነት የሚረጋገጥበት የአናሳዎች መብቶች የሚከበርበት ሥርዓት ሲሆን ሥልጣንን መሰረት በማድረግ አናሳዎች የበላይነት እየወሰዱ የሚገኙበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በፖለቲካ ሴራ የብሔር ግጭት፣ የሃይማኖት ግጭት፣ እየተከሰተ ይገኛል። ሲፈተሽ ችግሩ የመልካም የማኀበራዊ ኑሮ አኗኗር ችግር/ውስንነት እንደሆነ ይታመናል። ይህም ተጽዕኖ በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ጠባሳውን ያሳርፋል ብሎም የፍርድ መጓደልን የድሃ መበደልን ያስከትላል። ይህ ሆኖ ሲገኝ እንኳን የዲሞክራሲን መኖር ማረጋገጥ ይቅርና ወጥቶ መግባት በስጋት ይሆናል። እኩልነት ቀርቶ የጥቂቶች የበላይነት ይሰፍናል። የብሔረሰብ እኩልነት፣ የእምነት ተቋማት እኩልነት፣ የባህል እኩልነት፣ የፖለቲካ እኩልነት፣ ኢኮኖሚያዊ እኩልነት፣ ማህበራዊ እኩልነት፣ የአስተዳደር እኩልነት አይኖርም። ልማትና ሠላም አይኖርም።
ስለዚህ ቅድስት ቤተክርስቲያን እና ምእመናን በአንድነት በሃይማኖታዊ እና በማሕበራዊ ተግባራት በብቃት ልትወጣ ይገባታል። ከፖለቲካ አስተዳደር ውጭ የሆነ የራሷ አስተዳደር ሊኖራት ይገባል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ፦
• ራሷ በክርስቶስ ሠላም ውስጥ መኖርዋን ስታረጋግጥ
• መልካም አስተዳደር በውስጧ ሲጎለብት
• የውስጥ ችግሮችዋን በራሷ መፍታት ስትችል፣መከባበር፣ መደማመጥ ሲኖር፣
• ቤተክርስቲያኒቱ ያለባትን ኃላፊነት በግልጽ በማጤን በውስጧ ተሰግስገው ሰማያዊ ሳይሆን ምድራዊ ዓላማ ይዘው የሚጓዙትን ጠርጎ ሲያስወጣ
• ቤተክርስቲያንን የመጠበቅ ግዴታ የምእመኑም በመሆኑ በክርስትና እምነት አስተምሮ የታነጸ ሲሆንና ተሳትፎአቸውን ይበልጥ በማጎልበት የአሠራር ግልጽነትን በማስፈን ወዘተ ብቻ የሚሆን ነው።
ቤተክርስቲያን ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት ስትችል መልካም አስተዳደር ይሰፍናል፤ መንፈሳዊነት ይጸናል።
"የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ።" 1ኛ ቆሮንቶስ 3:10
እኛም እንደ ምእመን እንዴት በጥንቃቄ መኖር እንዳለብን እንመለከታለን።
ክፍል ሁለት ይቀጥላል
@deressereta
እኔን ለማግኘት ጽሁፎቼን ለመከታተል ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁሉ ወደ'ኔ ይመሩዎታል።
My Facebook page link (በፌስቡክ ገጽ እንገናኝ)
https://www.facebook.com/deresse2020/
Main facebook account (ዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ይቀላቀሉት)
https://www.facebook.com/DeresseReta
Follow me through telegeram (በቴሌግራም ሊከታተሉኝ ከፈቀዱ) ሁሉም ምልከታዬን የማጋራባቸው ማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው።