ሐሙስ 8 ኖቬምበር 2012

“ላላ”


ላላ
እኔም እንዳሻኝ  እናንተም እንደሻችሁ ከፈለኩ አጥብቄ ሲያሻኝ አላልቼ አነበዋለሁ! ላላ! (ላላን አላልተዉ ያንብብቡት) አለች ፋጤ፤ የሰፈራችን ሰዎች ሞያ ብለው ተያይዘውታል ልጆቻቸውን ወደ “ቻቻ”(ቻቻ የሚለዉ ቋንቋ ከሚላዉ የአማርኛ ኮሜዲ የተወሰደ ነዉ)ልጅ አገር ልጆቻቸዉን መላክ አንዷም የእማማ አፀዱ ልጅ ከች(መጥታለች ማለት በአራዳ ቋንቋ) ብላለች ከወደዚያው፣ እናላችሁ እንኳን የኛ ሰፈር ሠው የአገራችን ሠው ETV እንደሚለዉ “አንዳንዶች’’ ካልሆኑ በቀር 80 ሚሊዮኑም የዋህ ነው፡፡  ‘’እንኳን ደስ ያሎት’’ ለማለት ቤቱን ብቻ ሳይሆን ልጃቸው ገንዘብ ልካ ያስገጠመችው“French door’’  ሣይቀር Busy  ሆኗል: ተበርግዶ:: አንዳንዶችም መቸስ ለወሬ  የሚሄዱ  አይጠፉም የሰፈራችንን እማማ አፀዱንእንኳን ደስ ሎት  ብሎ ሙዝ፣ ቡርትኳን፣ የአበሻ አረቄ፣…. ይዞ ከሚመጣው ከፊሉ “ምን ይዛልዎት መጣች?” ብሎ እንደወንጀል መርማሪ የሚያደርቃቸው አልጠፋም በጥፊና በእርግጫ አላጣቸውም እንጂ፡፡ እማማ አፀዱም ያለመሰላቸትና መታከት መልስ በመስጠት ተጠምደዋል፡፡  እኔም ከመጣሁ አይቀር እንዴት ነው ሰላም መጣች? ድካሙ እንዴት ነው በረታች መቸስ ረጅም መንገድ መሄድ ያደክማል፣ አየሩን  ምግብና መጠጡንስ  ለመደችሎት ... ካልኩ በኃላ እኔም ምን አፌላይ እንደጣለው የማላውቀው እንዴት ነው ምን ይዛ መጣች ብዬ እርፍ አይገርምም መቸስ የኔ ሲሆን አይገርምም እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ እኔ ግን ገርሞኛል፡፡  እማማ አፀዱም በመገረም በረጅሙ ከተነፈሱ በኃላ ወደጆሮዬ ጠጋ ብለው “ያገር ላላ” ይዛ መታለች አሉኝ፤ ልቤ በደስታ ተሞላ ለርሳቸው አለፈላቸው ለእኛም  ያው … አንዳንድ ይደርስናለ ብዬ ልቤ ፈነደቀ፡፡ ቶሎ ብዬ በብር ማሰሪያ ላስቲክ ጠፍሬ ያሰርኳትን የቻይና ሞባይል ተመለከትኩ ምናልባት ላላ የሚባል የሞባይል ቀፎ ሊሆን ይችላል በማለት፤ ተጫወት የኔ ልጅ ማነሽ? ትዴ ነይና አጫውችው እንጂ የምን ስልክ ሲያወሩ መዋል ነው አንዳንዴም ሥልኩን አቋርጠሽ እንግዳ አጫውቺ በማለት የመመሪያ ዓይነት ትዕዛዝ አዘል መልዕክት አስተላለፉ፡፡ አቤት ቁልምጫ ትደነቂያለሽ  ሲቆላመጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ሠማሁ  ማሚ መጣሁ አንዴ ሥልክ ይዤ ነው፤ እያወራች ወደኔ ቀረብ ብላ በማላውቀው  ቋንቋ የሆነ ነገር ብላ ሥልኩን አቋርጣ ጉንጮቼን ግራናቀኝ በጉንጯ እያስነካች ጡዋ ጡዋ ጡዋ የሚሉ ድምፆች በጆሮግንዴ በሽቶ ያበዱ መዓዛዎቿን በአፍንጫዬ አስረጫጨቻቸው፡፡ ደስ አለኝ! ወደያው ወደአቋረጠችው ስልክ ተመለሰች ጆሮዬ በተደጋጋሚ አንድ ነገር መስማት ጀመረ ላላ የሚሉ ቃላት ከትደነቂየለሽ አንደበት ውስጤ  አንድ ነገር ጠረጠረ እማማ አፀዱ ያሉኝ የአገር ላላ ይዛ መጥታለች  የሚለው አባባል ውስጠ ወይራ እንደሆነ፡፡
     እማማ አፀዱ በሉ ደህና ዋሉ ልሂድ እንግዲህ፣
v  በል እግዚአብሔር ያክብርልኝ፣….እነርሱ እንደዚህ ናቸው ልባቸው ወደ አገራቸው እስኪመለስ በሥልክ እንጂ በአካል እንዲህ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚላቸውን ቁጭ  ብለው አያወሩም  ከዚህ በፊትም ብዙ ልጆች  ሠፈራችን ሲመጡ ጐረቤት ሲማረርባቸው እሰማለሁና ደግፍኳቸው፤እሳቸውም በር ድረስ  ሊሽኙኝ  ወጡ እኔም እየፈራሁ ላላ ምንድን ነው?አልኳቸው፡፡ 
v  እስካሁን ሥታወራ አሥሬ ላላ ሥትል አልሠማሃትም እንግዲህ ምኑን አውቄ ዝምብዬ በደንቆሮ አዕምሮዬ ስጠረጥር “አይሆንም/አይደለም” ማለት ይመስለኛል፡፡
ታዲያ ቅድም ምንድን ነው አመጣችልኝ ያሉት?
v  ይኸንኑ ነዋ ላላ ሲሉ መዋል እኔ ያየሁት ነገር የለም፤ ይኸው ስንት ቀኗ ይመሻል ይነጋል ተነስታ ይዤ የመጣሁት የሠው ዕቃ አለ እያለች መሔድ ነው በነጋ በጠባ ቁጥር፡፡ የማልምልበት ነገር አንድ ሽቶ እና አንድ ሞባይል አይቻለሁ እንግዲህ አሁን እነዚህ ነገሮች ለኔ ምኔ ናቸው? ከኩሽናዬ ጭስ ወዲያ ሽቶ፤ ከሰፈራችን ወሬኞች ወዲያ ሞባይል፤ ምን ሊሰራልኝ …በሉ ደና ዋሉ ብዬ ጥያቸው እግር አውጪኝ አልኩ የሞባይሌን ላስቲክ ጠበቅ እያደረኩ፣
     ጐበዝ ነቄ በሉና ሽል በሏቸው ላላ እያሉ የሚያደነቁሯችሁን የአረብ አገር አራዶችን እንደነገርኳችሁ አኛ ሰፈር ዕድሜያችን ለአቅመ ፓስፓርት ሲደርስ ወደ ኤሚግሬሽን መጓዝ ነው፤ ከዚያ ሴቱ  ለግርድና ወንዱ ለሹፍርና ወይም ለማጣበስ/ለማቀላጠፍ/ እንሰደዳለን አሁን ሠፈሩን የሞላነው እኔና ፓስፓርታቸው disqualify የሆነባቸው /የተሰረዘባቸው/ ነን፡፡  የኔ ሥራ በቋሚነት የሚሄዱትን ቦሌ አየር ማረፍያ ድረስ ሄዶ መሸኘት የሚመጡትን የሰፈራችን ድንጋይ ላይ ቁጭ ብዬ መቀበል ነው፡፡
አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ መቸሰ ከተማ ለዚያውም እኛ ሠፈር ተወልዶ ማደግ ችግር  ነዉ፤ ከባላገር የሚፈልሱ ሴቶች  እርጥብ ወደብ መሆን ነው፡፡ አንዴ በሌሊት ወረፋ ለመያዝኢሜግሬሽን፣ አንዴ ደላላ ቤት አንዴ ለምርመራ ሐኪም ቤት፡ ፎቶ ቤት፣ ፎቶኮፒ ቤት፣ብቻ ምናለፋችሁ  ሲዞሩ  መክረም ነው፤  እናላችሁ አንዴ የሆነች የዘመድ ልጅ ከገጠር መጣችና እንደልማዴ ከደላላ ቤት ደላላቤት ይዣት ስዞር አንዱ ደላላ ገና ሲያያት ለጉዲፈቻ ነው ወይሥ ለግርድና ነው ብሎ አያላግጥብኝም!! በሠው እንጀራ መግባት ይሆናል  ብዬ እንጂ በኛ ሠፈር እስታየል ሙልጭ አድርጌ ብሰድበው ደስ ባለኝ ነበር፡፡ እየተዘባነነ ቁጭ በሉ አለን፡፡  ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለን ለመዋል /ለመቀመጥ/ ወደ መቀመጫችን አመራን ችኳ በመገረም  ነበር የምትከልመው ሥትሾፍ ገጌ ብላ ስለነበር መጣሁ  አልኩና እጥፍ አልኩ ወደበሩ፡፡ ያገር ባለገር ከች አይልም፣ … ወይኔ ሲያሳዝኑ  አየተግተለተሉ ገቡ ወረፋ አያውቁም …  አስትናጋ መጠየቅ ጀመረች ሥም ምናምን ተሞላ ዕድሜ 25 ቀና ብላ አየቻት ሥንት ነው ያልሽው  25 ዓመት ያንቺነኮ ነው የምጠይቅሽ አዎ የራሴ ነው ብላ ድርቅ አለች፡፡ በትዕግሥት መጠየቁን ቀጠለች አይዞሽ ከመሄድ አትቀሪም 25 ዓመቱን ትደርሽበታለሽ የማይደረስበት ነገር የለም ያኔ ባልደረሰ የምትይበት ቀን ይመጣል ለማንኛውም እውነተኛውን ንገሪኝ ብላ መለመን ጀመረች ከብዙ ድርድር በኃላ 15 ዓመት መሆኗን ነገረቻት ግትርነቷ የሚገርም ነው የዕድሜው በዚህ ተጠናቀቀና የትነው የምትሄጂው? አለቻት /ጐጃም በረንዳ/ ብትል ምን ይላችኃል፡፡ በቃ ቤቱ በአንደዚህ ዓይነት የተፈጥሮ ኮሜደያን የተሞላ ነው እንዲህ ሆነው ነው እንግዲህ ሲመጡ ላላ እያሉ የሚያደነቁሩን አቦ ይመቻቸው እነርሱ ባይሄዱ ኖሮ እንኳን ፍሬንችዶር ይቅርና ሠፈራችን የለስላሳ ጠርሙስ ስባሪ ዝር አይልም ነበር፡፡  ዕድሜ ለአረብ አገር፡ ዕድሜ ለደላላ፡ ኧረ ቆይ ከዚያ በፊት የሚቀድም አለ …  የመሰደድን መብት የደነገገልን መንግሥታችን ይመስገን፡፡

     ቦሌ ሄጄ ሸኝቼ እንጂ ተቀብዬ የማላውቀው ሠውዬ አንድ ቀን ሲያንቀዠቅዡኝ የማላውቃት አክስቴ ከ15 ዓመት በኃላ ትመጣለች ተብዬ አንድ ሚኒባስ ሞልተን ቦሌን አጥለቀለቅነው፤ ከስንት ሱበዔ በኃላ  ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ዘግይታ ሳይሆን ሰንብታ መጣች ሻንጣ በሻንጣ ላይ ቆልላ ማሽ አላህ እያለች መጣች ብዙዎቻችን በመገረም ቆመን አየናት ላየን ሰው ባለስልጣን  የምንቀበል ሚኒስተሮች ነበር የምንመስለው ፍዘታችን፣ ተመልከቱ እንግዲህ  የኛ ሠፈር ሠው ሲፈዝ ለአክስት ቺኩ የመጣች ሠው እንዴት ሊሆን ነው በአፈጉባኤም እናታችን መሪነት እገሌ …  እገሌ ይባላሉ አያለች ታስተዋውቀን ጀመር ተራው እኔ ላይ ሲደርስ ይሔ ደሞ ጭንቅሎ ነው ብላ … መቸስ አታውቂውም  አይደል ያኔ ገና  ህፃን ነበረ፡፡  ሹ!፣ ሚን!  የማን ልጅ ነው?/ጉድ በል ጐንደር አለ ኮማኪው አይገርምም አማረኛ  ሣታጣራ ሄዳ መፃፍ ማንበብ የማትችልም አክስቴ በፅሁፍ የማታቃትን  ሥትጠራት እማዬም የኔው ጉድ ነዋ! ብላ ማርዳት;“ማሽ አላህ” ብላ አቅፋ ሳመችኝ እኔም ወገቧ ላይ እንደቤታችን ቁንጫ ጥምጥም ብዬ ሙጭጭ …  ፍቅር በፍቅር ሆንን ሜትሮሎጂ መቸስ ሥለፍቅር አይዘግብም እነጂ የዕለቱ ታላቅ ፎንቃ ተብሎ ይመዘገብልኝ ነበር፡፡ላላ አሳነስኩት አይደል ጊነስ ቡክ ላይ ይመዘገብልኝ ነበር ካልሆነም የቦሌ ልጆች በፌስ ቡክ ይለቁት ነበር፡፡
      ሰላምታው በድል ከተጠናቀቀ በኃላ ጉዞ ከቦሌ ወደ ጉለሌ:አሰፋፈራችንን አስቀድሞ እንጂ የሠፈሩ ኩታራበጠቅላላ  እኔና ማሚን ሳይጨምር ወደ ሚኒባሱ እኔ ማሚ አንድ ቀድማ የመጣች የአክስቴ ጓደኛ  አክስቴ በቦሌዋ ላዳ ቃ ዋናዋናው ከላዳው ላ ሌላው በሚኒባስ፣ ዝርዝር  አሰላለፍ ማሚ ጋቢና እኔ እንደተለጠፍኩ ከአክስቴ በቀኝ ክን
ፍ፣ያቺኛዋ ጀለስ በግራ ክንፍ በሚኒባሱ እየተመራን ወደቤት፡፡
     መቸስ ከአረብ አገር ስለመጣች ሠሞኑን ታስከብረኛለች ብዬ እንጂ እንዴት ጭራ እንዳሰበቀለችኝ ልነግራችሁ አልችልም ሠፈር እስክንደርስ አንዲት ነገር አላናገረችንም ከጀለሷ ጋር ግራ ቀኙን እያዩ  ሙድ እየያዙብን  አገራችን ዱባይ ሆና የለ እንዴ? ትላለች ፎቆቹን እያየች ገና መች አየሽና መንገዱስ ብትይ ቆይ ይኼ ሁሉ መቼ  ነው የተሰራው እዛኮ የሚወራው ሌላ ነው ደግሞ ይሄ ሁሉ ፎቅ ምን ይሰራል? ቀበል አድርጌ ሠፈራችን ፈርሶ እዚህ ልንገባ ነው ምነው በሠላም? አለች እንደመደንገጥ ብላ::እናቴ እርር ብላ ተዛዝለለን እንዳልኖርን ልጆቻችን አዝለን እንዳላደግን መንግሥታችን ዛሬ ደግም ዕድገት ተዛዝላችሁ ሙቱ ሲለን  ይኸን ሠርቶ ህዝቡን እዚህ እያጠራቀመ ነው ስሙ ደሞ ኮንደም ነው የሚባለው  አክስቴ እንደውሽት አትቁጠሩብኝና እግሯን አንስታ ነው የሳቀችው ያው ያላነሳችው ታክሲዋ እግር ለማንሳት አይደለም ለማንቀሳቀስ ስለማትመች ነው፤ ሣቃቸው ገርሟትም አናዷትም ዞር ብላ ሥታየን ሰው ሣትሆን አራስ ነብር ነው የምትመስለው ሥትናደድ ሥኳሯ ፡ደም ግፊቷ፣ ልብ ምቷ፣… ባንድ ላይ እንዳይነሱባት ብዬ ቶሎ አልኩና ሥህተቱን እርማት  ሠጠሁበት እማዬ ኮንደም ያለችው ኮንደምንዬም ለማለት ፈልጋ እንጂ ኮንደም መለየት አቅቷት አይደለም  አልኩ፡፡ ሠው ሠፈር የሙዝ ልጣጭ ሲያዳልጥ እኛ ሠፈር ሠውን ለአካል ጉዳተኝነትና ለቁም ነገር የዳረገው የወዳደቁ ኮንደሞች ስለሆኑ ከታዳጊ እስከ አዳጊ ሁላችንም ሥለምናውቀው በእፍረት አክስቴና ጓደኛዋ አፋቸውን በመያዝ እንደመሣቅ አሉ፡፡
     በእቅፋ ሥር እንዳለሁ የትምህርት ቤት ሥምህ ማነው? ብላ ጠየቀችኝ ሠፈርም ትምህርት ቤትም የምታወቀው ጭንቅሎ ነው እኔ ግን የፈተና ወረቀት ላይ ንጉሱ ብዬ እሞላለሁ ንጉሱ ሲባል ግን ማንም አይገርመውም ምን ሆነህ ነው ቀጫጫ የሆንከው? አሁንኮ አይደለም ሲፈጠርም ቀጫጫ ነኝ ባይሆን ኖሮማ የሠፈራችን አሽማጣጮች  ጆከር ስቦ ዱቤ እየጠበቀ ነው ይሉኝ ነበር፡፡
እማዬ ስለኔ ቀጫጫነት ማስረዳት ጀመረች 
ምን እባክሽ ዝም ብሎ ያመዋል፡
አድዬ በስለት ነው እንዴ የወለድሽው? ጉድ በል የጉለሌ ሠው አዳነች ተቆላመጠች አልኩ በልቤ እነዚህ የአረብ አገር ሴቶች ከቁልምጫ ወዲያ የሚያዉቁት ነገር የለም እንዴ? አልኩ በፈረደባት ሆዴ፣
 ምናቃለሁ ብለሽ ነው?ይሆናላ!
አክስቴ በስለት ሳይሆን በሰህተት ነዉ የተፈጠርኩት! አሁን ማን ይሙት እኛ ቤት ሠው መፈጠር አለበት? ሲታመም ፀበል ባይኖር ኖሮ ኃኪም ቤት የማይኬድበት ቤት ውስጥ ለዚያውም እኔ ንጉሳዊ ሥርዓት  ተገርስሶ ፓርላሚንታዊ ሥርዓት በሰፈነበት አገር ንጉስ ላልሆን“ንጉሱ” መባልስ ነበረብኝ?  እስኪ ፍረጂኝ!
     አክስቴ አረብ አገር መንገድ የለም መሰለኝ በተሠራው መንገድ ገርሟት እቤት ሣትደርስ መንገድ ላይ ልትሞት ነው የሰፈራችንን ኮብል እስቶን ሲታይ የኮብልስቶን ቴክኖሎጀ አረብ አገር እንዳልደረሰ አረጋግጥኩ በግርምት ተመልክታ ሥትጠይቀኝ ምንድን ነው ይሄ? ብላ ጥያቄ ብጤ ለሁላችንም አሻማችን፡፡
     የድንጋይ ዳቦ ዘመን ተመልሶ ነው ዳቦ ነው አልኳት ጓደኛው ሆዷን ይዛ ትስቃለች  አክስቴ በብዙ ጥፋትና ድካም መንገድ መሆኑን ደረሰችበት እኔም ሥሙ ኮብል እስቶን መሆኑን አረደኃት፡፡
አገራችን በጣም ተሻሽሏል መንግድ በመንገድ ሆኖ የለንዴ?
መንግሥታችን መሄድ ስለሚያበረታታ ነው፡፡
አንተ አሽማጣጭ ሆነህ የለንዴ!
    እናቴ ቀበል አርጋ ምን አሽሟጣጭ  ይህ ቆንጅት ነው ጡንጅት የሚባለው በ97 ዓ.ም. አገራችን ከገባ በኃላ ህፃኑ ሁላ ተቃዋሚ ሆኗል፡፡ መንግሥትማ ምን ያልሠራው ነገር አለ ብለሽ  ነው እኛ በእድሜያችን አይተን የማናውቀውን ፎቅ አሥፋልት ምንድን ነው ቅድም  ስትባባሉ  የነበረው መንገድ፣ መብራት፣ ኧረ ስንቱ እነርሱ ግን ይሄን ያህል ዓመት ሙሉ ገዝቶ ይሄ ብቻ  አይበቃም ባይ ናቸው ታላቅየውማ ሀይለኛ ቦለቲካኛ ሆኖልሻል ከኔ ጋር  ጦርነት ሊገጥም  ትንሽ ነው የሚቀረው አንድ መቶ ሺ የቀበሌ ቤት አፍርሶ 10 ሺ ኮንደም … ማን ነበር ስሙ መገንባት ልማት አይደለም ይላል፡፡  ሠው የሚበላ የሚጠጣ የለው መንገድ ምን ይሰራለታል ይላል ይሄ ገፊ ነገር ሊያመጣብኝ፡፡
      ላላ  መንገድማ መሠረታዊ ነገር ነው: መንገድ ከሌለ እድገት የለም:ሌሎችአገሮችኮ ያደጉት መንገድ ስላላቸው ነው፡፡
አክስቴኢህአዴግ ነሽነዴ? ዕድገት በአስፋልት ላይ ነው የሚመጣው ያለሽ ማነው? ከማለቴ እናቴ  ይድፋህ አፍህን አትዘጋም  የሰው ማንነት ሣታውቅ ብላ ፊቷን ቅጭም በማድረግ ወደ ሾፌሩ አመለከተችኝ፡፡
     ለካስ ሠውን ማመን አፍን ዘግቶ ነው የሚሉት ጓደኞቼ ወደው አይደለም ዝም ብዩ መቀደዴን ሣሥበው ወደቤታችን የምንሄድ ሳይሆን ወደ 3ኛ የሚወስደን ያህል ነዘረኝ፡፡  ጐመን በጤና ብለን የላዳዋን ሳሎንና ጓዳ ጭር አደረግናት ፀጥ ብለን፤ ወንድሜ ያለኝ ታወሰኝ መቸስ ስለመንግሥት ደና ነገር አያወራ ለአራት ሚሊዮን የአዲስ አበባ ነዋሪ የአዲስ አበባ ፓሊስንና ፌዴራል ፓሊስን  ሣይጨምር ስንት መቶ ደህንነት ነበር አለ ያለው ሠውየው ደህንነት መሰለኝ አሥሬ  በውስጥ መስታወት  ሾፍ  ሲያደርገኝ፡፡ ለነገሩ አክስቴንና ጓደኛዋን እየከለማቸው ይሆናል፣ እኔን አስሬ ቢያየኝ የጨው ማስቀመጫ አያደርገኝ ምናስፈራኝ ከሆነም ከቁም እስር ወደ ተከበረ  እስር ቤት መሄድ ነው ከግማሽ እንጀራ ወደ ታሰረ ሳህን ሽግግር አደርጋለሁ መንግስቱን አሻፈረኝ ቢል  ንጉሱ ምን ይገደዋል፡፡  ላላ ን ተወት አርገን መንገዳችንን ጠበቅ ጉዞ  ወደ ሰፈር !! ቸር ይግጠመን! ሴቶቻችንን ከፎቅ ላይ ከመወርወር ይጠብቅልን! ላላ፡፡
የደረሰ ረታ እይታዎች

ቅዳሜ 3 ኖቬምበር 2012

ይቅርታ!


 ‹‹ዘመኑ እ.ኢ.አ 1972 ዓ.ም ነው፡፡ ረጅሙ ሌሊት አልፎ አዲሱ ቀን ሰኔ 8 ሊነጋጋ ቀርበዋል፡፡ ሽምቅ ተዋጊዎች በሰሜን ቬትናም ግዛት ውስጥ እየተሽሎከለኩ እልህ አስጨራሽ ውጊያቸውን ተያይዘውታል፡፡
        በዚያን ቀን ሰኔ 8 1972 ዓ.ም ጠዋት በነዛ መንደሮች ላይ ከሰማይ ያናባል ቦንብ መዐት ወረደባቸው ፡፡ እነርሱም እንደ ሚፍለቀለቅ እሳተ ጎመራ ሆነው መንቀልቀል ጀመሩ፡፡ በምንም አይነት መንገድ ከዚህ እሳተ ጎመራ ውስጥ ማንም ማውጣት እንደማይቻለው ቢታወቅም ታምእራዊ በሆነ መንገድ በቁጥር አምስት የሚሆኑ ሕፃናቶች ከሚንቀሳቀሰው እሳት ውስጥ አምልጠው እየሮጡ ሲወጡ ታዩ፤ ከእነርሱም መካከል አንዷ ትራንግ ባንግ ከሚባለው መንደር አምልጣ የወጣች የዘጠኝ ዓመቷ ሕፃን ፋን ቲህ ኪምፋክ ነበረች፡፡ ኪም ፋክ ቦንቡ ጀርባዋን እና ክንዶቿን ጎድቷት ስለነበረ እና የለበሰችውን ልብስ በእሳት ተቀጣጥሎ ስለነበር፤ ልብሷን አውልቃ እራቁቷን ለመሮጥ ተገደደች፡፡
        በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ጦርነቱን ይዘግቡ የነበረው የአሶሴቲድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ካሜራውን አነጣጥሮ እየተቃጠለች እራቁቷን የምትሮጠው ኪምን በመቅረጽ ምስሉ ቀርጾ አስቀራት፡፡ ኪም ወደ ጋዜጠኛው እና በሱ ዙሪያ ወዳሉት ወታደሮች ስትደርስ ‹‹ተቃጠልኩ! ተቃጠልኩ! ‹‹Nong qua, Nong qua,”    ‘too hot, too hot” እያለች ታለቅስ ነበር፡፡
        … ጋዜጠኛው ከምንና አብረዋት የተረፉትን ህፃናት ሳይጎን ወደ ሚባል ከተማ ወስዶ በሆስፒታል ውስጥ እርዳት እንዲሰጣቸው አደረገ፡፡ ኪም ብዙ የቦንብ ፍንጥርጣሪ በሰውነቷ ውስጥ ስለገባ በሆስፒታል ውስጥ ባደረገቸው የ14 ወር ቆይታ 17 ጊዜ ወደ ቀዶ ጥገና ተደርጎላታል፡፡ ደስ የሚለው ነገር ኪም ከዚህ ሁሉ ስቃይ እና መከራ በኋላ ድና ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅላለች፡፡
        ዶ /ር ኪም ፉክ አሁን በካናዳ አገር እርሷ የተባበሩት መንግስታት የሰላም መልክተኛ ናት›› ትልቅም የሕጻናት መረጃ ማዕከል በስሟ ከፍታለች፡፡ የሁለት ልጆችም እናት ናት፡፡
        …. ጆን ፕሎሚር ፤ ኪም ካናዳ እንዳለች ሰማ ፈልጎም አገኛት›› ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት በኪም ፊት ተንበርክኮ እዲህ አላት ‹‹ኪም ፉክ ያንን ሁሉ ጥፋት እንዲሆን ትዕዛዙን የሰጠሁት እኔ ነኝ›› በሰራሁት ነገር ተጸጽቻለሁ! ከመሞቴ በፊት አንቺን አግኝቼ ይቅርታ ልጠይቅሽ እመኝ ነበር፡፡ ስላገኘሁሽ እና ይቅርታ ልጠይቅሽ ስለቻልኩ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ኪም ይቅር ትይኛለሽ?...››      ኪም ህፃን ናት፤ ደግሞም ሰላማዊ ሰውናት፤ በተራንግ ባንግ መንደር ላይ የናፖል ቦንብ ሲጣል ብዙ ሰላማዊ ሰዎች በተገኙበት ተቃጥለው አልቀዋል፡፡ ኪም ወገኖቿን ሁሉ አጥታለች፤ የአደጋው ጠባሳ ዛሬም በገላዋ ላይ ይታያል፤ በሞት እና በሕይወት መካከል ሆና እርቃኗን ለዓለም ሁሉ ታይታለች ፡፡ በእውነት ኪም ጆን ፖሎሜርን ይቅር ትለው ይሆን?
        … ኪም በ1996 ዓ.ም በቬትናም ጦርነት መታሰቢያ ቀን ላይ እንዲህ ብላ ተናግራ ነበር፡፡ ‹‹ያለፈውን አንድ ጊዜ የሆነውን ነገር መለወጥ አንችልም! ነገር ግን እያንዳንዳችን ለወደፊቱ ሰላማዊነት ተባብረን ልንሰራ እንችላለን!!!››
እናም ኪም በፊቷ የተንበረከከውን ጆን ፕሎሜርን ብድግ አርጋ በማቀፍ እንባዋ በዓይኖቿ እየፈሰሱ ‹‹ይቅር ብዬሃለሁ!›› አለችው፡፡ ይህ ይቅርታ በዓለም ላይ በጦርነት ለተደረጉ በደሎች ሁሉ የተበደሉት ህዝቦች ይቅርታ ሆኖ ተመዘገበ ፡፡
‹‹ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው÷ቢጸጸትም ይቅር በለው፡፡›› ሉቃስ 17፡3
       ይህን እውነተኛ ታሪክ ምንጭ ሆኖ ያገኘሁት መንገድ ላይ ትራንስፖርት እየጠበኩ ባለሁበት ሰዓት እንደነበር ከጋበዙኝ አንድ የእምነት ተቋም በራሪ ወረቀት ላይ ነው፡፡
        ‹‹ይቅርታ›› ለአለም ህዝብ ወሳኝ ጥልን ድል የምናደርግበት በእጅ የማይዳሰስ በዓይን የማይታይ መሳሪያ ነው፡፡ ታላቁ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ሌሎች መጽሐፎች ታላላቅ ሰዎች፣ ሙሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት መምህራን ዘወትር በጽሑፋቸውም ይሁን በትምህርታቸው የሚያነሱት አብሮ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬም ፀሐፊው ማንሳት የፈለገው ስለዚሁ ዓብይ ጉዳይ ይቅርታ ነው፡፡
        ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ይቅርታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥለ ይቅርታ ሲጠይቀው እንዲህ ብሎት ነበር፡፡ ‹‹…..ጌታ ሆይ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለው፡- አስከ ሰባት ጊዜ ሰበት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም፡፡›› ይህ ቃል የሚያስመለክተን ከይቅርታ አስፈላጊነት ባሻገር ምን ያህል ጊዜ ይቅር ልንል እና ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብን ነው፡፡
        ይህንን መሰረት በማድረግ ነው መሰለኝ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የዛሬ ‹ኢትዮ ቴሌኮም? (እኔም ይቅርታ የአማርኛ ቃል ሥላልሠጡት አንድም መጠቀም ስላልፈለጉ የሥልጣኔ፤ የዕድገት ምልክት መሆኑ ነው መሰለን የእንግሊዘኛውም የተጠቀሙት እንዳለ ተጠቅሜአለሁ) መስሪያ ቤት መቼ እንደሚስተካከል የማይታወቀው የኔትወርኩን ችግር ‹‹¸ይቅርታ የደወሉላቸው ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…..››፤ ‹‹sorry the network is busy …….››፤‹‹ይቅርታ ይቅርታ….›› ተጠቃሚውን ህብረተሰብ ያሰለች ትልቁ የቴሌኮም ችግር ነው ነገር ግን ሊቀርፈው ያልቻለው ከአሥር ዓመት በላይ ተሸክመነው የዘለቅነው ችግር ነው ምንም እንኳን መጽሐፍ በጥሬ ለ490 ያህል ጊዜ ሥህቱቱን ይቅር ማለት ቢገባንም የቴሌኮም ሥህተት በዛ፣ ይቅርታውም የምህረት ልመና ሳይሆን ማደንቆሪያ ከሆነ ሰነባበተ ምክንያቱም በሰላምና በጤና አጠገብዎ ያለውን ደንበኛ ‹‹ይቅርታ ›› ደንበኛዎን ሊያገኟቸው አይችሉም››፣ ይቅርታ መስመሮቹ ሁሉ ተይዘዋል፡፡›› ‹‹ይቅርታ ደንበኛው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው›› ወዘተ… ይባላሉ፡፡ እሺ እንደ መጽሐፉ ይህ ወዳጃችን ብቸኛው አገር በቀል ድርጅታችን በደለን ይቅርታ ጠየቀን መቼ ነው ተስተካክሎ ችግሩን አስወግዶ ‹ይቅርታ› መጠየቁን የሚያቆመው? ለነገሩ በኮምፒውተር የተቀረጸው (የተቀዳው) የድምጽ መልዕክት ለማደናገር (ለማደናቆር) ‹ይቅርታ› ትበል እንጂ ተቋሙ ለስራው ሥህተት ለበደለው በለድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ አያውቅም፡፡
የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ፣ የቀሙትን መልስ ምህረት ማግኘት ትልቁ የኢትዮጵያን ሐብት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅር ማለት ፋሽን ያለፈበት፣ ኋላቀር አስተሳሰብ እየሆነ ከመጣ ሰነባበተ፡፡ መምህራኑ ሃይማኖት፣ ሳይቀሩ ይቅር መባባልን፣ ምዕመናንን ይቅርታ መጠየቅ እንደ ውርደት እየቆጠሩት መጥተዋል፡፡ ቤተ እምነቶችንም የሚያስተምሩት የማያደርጉ መምህራን ማፍራት ከጀመረች ሰነባበተች ምዕመኑም ‹‹ይቅርታ አድርግልኝና….›› እያለ እያስፈቀደ ማስቀየም ጀምሯል፡፡ ‹‹ይቅርታ ይበለን እንጂ…›› እያለ ማማትንም የተቀደሰ ሥራ አድርጎታል ፡፡
ይቅርታ ያሥተማሩ ይቅርታንም በተግባር የተገበሩ በሥውር የበደሉትን በአደባባይ በአብራክ ህሊና ተንበርክከው ይቅርታ የጠየቁና አርአያ የሆኑ አልታጡም፡፡ አንዱ ጀግና ደፍሮ በአደባባይ ይቅርታ ሲጠይቅ ያጥፋም አያጥፋም ብዙዎችን ምሳሌ በመሆን አስተምሯል ብዙዎች ግን አንዱን ይቅርታ አልጠየቁም ዲ.ዳንኤል ክብረትን ምናልባት በደል አልተገኘባቸው ይሆናል፡፡ እርሱ ግን በአፈ መንፈስ ቅዱስ ይቅር መባል ይገባዋል፡፡ ይቅርታ ጠይቋልም ይቅርታንም አስተምሯልም፡፡ ኢትዮጵያዊው ጆን ፕሎሜር ያለጥፋት ወይም ጥቂት ጥፋት ትልቁን ይቅርታ የጠየቀ ትንሿ እርሾ ብዙውን ሊጥ ታቦካዋለችና፡፡
        በምድራችን በኢትዮጵያ ብዙዎች የጥቃት ሰለባ የሆነ በአካለ መጠን ጨቅላ የሆኑ በጦርነት የእሳት እራት የሆኑ ነበሩ፡፡ ሃማሴናውያን የት/ት ቤት ተማሪዎች፡፡
        በረሃብ አለንጋ ተገርፈው የረገፈ አሉ በ1977 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድርቅ በበሽታ የሚሰቃዩና ህክምና በማጣት የሚረግፉና በጨቅላነታቸው የሚቀጠፉ ህጻናት ቁጥር የትዬለሌ ነው፡፡
        ወላጆቻቸውን በወባ፣ በቲቢ፣ በH.I.V. ኤድስ ያጡ የህፃናት ቁጥር ቤት ይቁጠረው……ወዘተ፡፡ ለዚህ ጥፋት፣ መነሻነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሰው እጅ አለበት፤ ታዲያ የትኛው ጀግና የይቅርታ መምህር ይሆን ‹‹…. ያንን ሁሉ ጥፋት እንዲሆን ትዕዛዙን የሠጠሁት እኔ ነኝ፡፡ በሰራሁት ነገር ተጸጽቻለሁ! …. ይቅርታ!›› በማለት ትውልድን ይቅርታ የሚጠይቅ? በህፃናት ሥም የሚመጣውን እርዳታ (ገንዘብ፣ እህል፣ መድሐኒት፣ ቁሳቁስ፣ ወዘተ…) ለሌላ ጉዳይ ወይም ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ የመንግስትና የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ባለሥልጣናት የሆኑ?የሐይማኖት ትምህርት በማስተማር በዓለም ላይ ሰላምን በማምጣት የላቀ ሚናቸው መጫወት ሲገባቸው በዘረኝነትና በፖለቲካ ክፉ ሥራ ተጠምደው የህፃናቱን ለቅሶና ዋይታ፣ ህመምና ሥቃይ ወደ ጎን የተው የሃይማኖት መምህራንና መሪዎች ይሆኑ? በሥልጣን ጥማት የተነሳ የሥልጣን ዘመኔ ይራዘምልኝ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ እያሉ እርስ በርስ ባለመስማማት ጦርነትን በህጻናት ላይ ሳይቀር የሚያውጁ ሰይፍ የሚመዙ ቦንብ የሚያፈነዱ መርዝ የሚረጩ የመንግስት ባለሥልጣናትና ጋሻ ጀግሬ(አጫፋሪዎች) ይሆኑ? ትርፉን በማሳደድ በቃኝን ባለማወቅና ያለኝ ይበቃኛል በጥቂቱ አትርፌ ህዝቤን ልጥቀም የሚል አስተሳሰብ በማጣት በየዕለቱ በህፃናት ምግብ፣ አልባሳት፣ የህክምና መድኃኒት…….ወዘተ ላይ ከፍተኛ ጭማሪን በመጨመር ሥቃያቸውን የሚያረዝሙት፣ ህመማቸውንና ጣራቸውን የሚያበዙት፣ ጩኸታቸውን፣ ለቅሶአቸውን፣ የድረሱልኝ ድምጻቸውን ….የመሥሚያ ጊዜ ያጡት ነጋዴዎች(መላው ህብረተሰብ) ይሆኑን? እንጃ ፣ የትኛው ወገን የእነ ኪምን ለቅሶ፣ ዋይታ፣ ሰቆቃ፣ ህመም፣ አልፎ ተርፎም ሞት በመስማትና በማየት ግፍ መዋል በቃኝ ያጠፋሁት ጥፋትና እልቂት፣በቃኝ እስከ ዛሬ ለነበረው ነገር ሁሉ ተጠያቂ እኔ ነኝ፣ …. ይቅርታ የሚለው የቱ ይሆን???
        ህፃናት እንዳ ኪም በጣሊያን ጦርነት፣ በግራኝ መሐመድና በዮዲት ጉዲት ጦርነት፣ አያት ቅድመ አያቶቻቸውን፣ በደርግና በወያኔ(ኢህአዴግ) ጦርነት፣ በኢህአዴግና በሻቢያ(በኢትዮጵ ኤርትራ) ጦርነት አባቶቻቸውን አጥተዋል ዛሬ በራሳቸው ዘመን ላይ በመሆን እነርሱን ለማጥፋት የጥፋት ኃይል እጁን ከጠብ መንጃ አፈሙዝ ላይ በማንሳት ህይወታቻቸውን ይታደጋቸው ጥፋትን ሳይሆን ምህረትን የሚያውጅ የፕሮፓጋንዳ ሥራን(አሉታዊ የሆነውን) በመሥራት ብቻ የተጠመደው ሰላምን በመስበክ ‹‹ተቃጠልን!››፣ ‹‹ተራብን››፣ ‹‹ታመምን››፣ ‹ወላጅ አልባ ሆነን››፣ ‹‹የሙቀት መጠን ጨመረብን››፣ ‹‹ንፁህ አየር አጣን፣››፣ ወዘተ የሚሉትን ጨቅላ ህጻና ወደ አስፈላጊውን ስፍራ ሊወሰዱ የተሰናዱ ጋዜጠኞች አገራችን ያሥፈልጋታል የሃሰት ሰይፋቸውን ጥለው እውነት የሚያወራ ብዕራቸው ሊጨብጡ ስለሰላም ስለ አንድነት ስለ እርቅ ሊዘምሩና ሊያሸበሽቡ ይገባል፤ ለባለሥልጣናትና ለባለጊዜዎች ማራገብ ይቅር፡፡ የጥፋት ኃይሎችን ገበና ያጋልጡ፡፡ በመምከርና በማስተማር ለህብረተሰቡም በማሳወቅ ከመንገዳቸው ይመልሱ፡፡
        በቤተ እምነቶች ካህናት፣ አስመላኪዎች፣ ሼኮች… ሥራቸውን በእውነት ላይ የተመረኮዘ ትውልድን የሚታደግ ለባለጊዜዎች የሚያደላ እና ህጻናት በተለያየ አቅጣጫ (በርሃብ፣ በብሽታ፣ በጦርነት፣ ወላጆቻቸውን በግፍ በማጣት፣ በዓለም ሙቅት ጨመር ምክንያት ሲጨነቁ …እና ሌሎች ህይወታቸውን የሚቀጥፉ እድገታቸውን የሚያጨናግፉ ነገሮች በመመልከት ተጠቂ ሲሆኑ ዝም ብሎ ከማየትና ዝምታን ከመምረጥ ለህጻናቱ ወግኖ መሟገት ለዚህ ዓለም የሚበጀውን ሰለምን መስበክ፣ ‹‹ኃጢአት መጥፎ ነገርን ብቻ ማድረግ ሳይሆን በጎ ነገር ማድረግ ሲችሉ አለማድረግም ኃጢአት ነውና፡፡››
        በህጻናት ዕልቂት ምክንያትነ ከተለያዩ አላማት ግብረሰናይ ድርጅቶች በልግስና ሥም የሚመጡትን እርዳታዎች (መድኃኒቶች፣ ገንዘቦች…. ወዘተ) ለግል ጥቅማቸው፣ ላልተፈለገ ምግባሮች (ለጦር መሳሪያ መግዣ፣ ለወታደሮች ማደራጃ ለቢሮ ህንጻ፣ ግንባታ ለባለሥልጣን የመኪና መግዣ የቢሮ ቄሳቁሶች (ቋሚ አላቂ እቃዎች) ፣ የተለያየ ክፍሎች ሥራ ማስፈጸሚያ በጀት) ማዋል ትልቅ በህጻናቶች ላይ የሚደርስ በደል ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የህጻናቶችና የወላድ እናቶች ማዋለጃና መንከባከቢያ ሆስፒታሎችን በማስፋፋት የእናቶችንና የህጻናትን ሞት መቀነስ ሲገባ የተያዘውን በጀት በባዶ ሜዳ በማስታወቂያ (ለትላልቅ ቢል ቦርዶች፣ማሰሪያ፣ለቴለቭዥንና ሬዲዮ ድራማዎች ማስታወቂያ እስፖንሰር ለተለያዩ ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች ቲሸርትና ኮፍያ፣ ውኃና ኩኪሲ፣ ሻይ፣ ቡና ላይ…) ከማባከን ቀጥታ ከሞት የሚድኑበትን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥራ ቢሰሩ የተሻለ ብዙ ኪሞችን በሕይወት በማትረፍ፣ የነገ ትውልድ ተረካቢ ዜጎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ የዛሬ ህጻናት የነገ ተስፋ ሰጪ ታሪክ ቀያሪ (ዶክተሮች፣ መምህራኖች፣ሰላም አስከባሪ ኃይሎች፣ ኢንጂነሮች፣ አርቲስቶች፣ ፓይለቶች፣ ሳይንሲስቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ የሀገር መሪዎች፣ በዓለም ላይ እርቀ ሰላም የሚያመጡ ብዙ ኒልሰን ማንዴላዎች፣ አብርሃም ሊንከንን ÷ወዘተ…) ማፍራት ይቻላል፡፡ ህጻናትን ልናደርግላቸው ከሚገቡት ጥቅሞቻቸው ባሻገር እያደረግንባቸው ጥቂቶችን እናቁም (ጉልበታቸውን ብዝበዛ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ለሥዳትና ለጉዳና ተዳዳሪነት መዳረግ፣ ለልመና ማሰማራት….)
        የህጻናት አዕምሮን ባዶ ወረቀት አንድ ነውና መልካም ነገር እንቅረፅባቸው ዛሬ ያስፈርንባቸው ትንሽ መልካም ነገር የነገ የትውልድ ትልቅ ተስፋ ይሆናል፡፡ የዛሬ በደላችን ነገ ይቅርታ ያገኛልና፡፡ ዛሬ ጦርነት፣ ስደት፣ ርሃብ፣ ፍቅር ማጣት፣ ድኅነት፣በሽታ፣ ድርቅ… ያኩራመታት ዓላማችን ነገ በነዚህ አዲስ ተስፋ ስንቀው በሚመጡ ጨቅላ ህጻናት እንድታገግም፣ የተኳረፍን እንድንታረቅባት፣ የተከፋፈልን አንድ እንድንሆንባት፣ በጎን በቋንቋ በብሔር በቀለም በፖለቲካ፣ በሃይማኖት ተከፋፍለን የተበታተንነው አንድ ህዝብ አንድ አገር እንድንሆንባት በነዚህ አዲስ ትውልድ አዲስ ዓለም ለመፍጠር የተበላሸ ታሪክ፣ ውሸትን፣ ጠማማ፣ የፖለቲካ አካሄድንና አመራርን፣ ሥራ የተለየው ዲሞክራሲን፣ አናውርሳቸው የእኛን መጥፎ ገጽታ እንዲወርሱ አናድርጋቸው፡፡ በአዲስ የህጻናት አዕምሮ ሰላም፣ ፍቅር፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ ከግል ጥቅም የጋራ ጥቅምን፣ የአገርን ጥቅም እንፃፍባቸው፡፡
        ‹‹ያለፈውን አንድ ጊዜ የሆነውን ነገር መለወጥ አንችልም ነገር ግን እያንዳንዳችን ለወደፊቱ ሰላማዊነት ተባብረን ልንሰራ እንችላለን!›› ኪም የተናገረቸው ነበር በቬትናም ጦርነት መታሰቢያ ቀን ላይ ዛሬም ኢትዮጵያውያን አፍሪካዊያን የዓለም ህጻናት ያለፉትን አሰቃቂ ጦርነቶችና ጥቂቶች በማሰብ ‹‹ያለፈውን መለወጥ አንችልም፤ለወደፊቱ ሰላማዊነት ተባብረን እንስራ›› ይላሉና፡፡ ደግሞ ጨለማ ሥራችንን በቀለም ከማስዋብ ይልቅ ከትናንት ጥፋታችን ተመልሰን እውነተኛ ሥራ እንስራ ስህተትና ጥፋትን መማሪያ እንጂ ታሪካችን አናድርግ እርቀ ሰላም እንፍጠር ይቅር እንባባል፡፡ይቅርታ!

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...