‹‹ዘመኑ እ.ኢ.አ 1972 ዓ.ም
ነው፡፡ ረጅሙ ሌሊት አልፎ አዲሱ ቀን ሰኔ 8 ሊነጋጋ ቀርበዋል፡፡ ሽምቅ ተዋጊዎች በሰሜን ቬትናም ግዛት ውስጥ እየተሽሎከለኩ እልህ
አስጨራሽ ውጊያቸውን ተያይዘውታል፡፡
በዚያን ቀን ሰኔ
8 1972 ዓ.ም ጠዋት በነዛ መንደሮች ላይ ከሰማይ ያናባል ቦንብ መዐት ወረደባቸው ፡፡ እነርሱም እንደ ሚፍለቀለቅ እሳተ ጎመራ
ሆነው መንቀልቀል ጀመሩ፡፡ በምንም አይነት መንገድ ከዚህ እሳተ ጎመራ ውስጥ ማንም ማውጣት እንደማይቻለው ቢታወቅም ታምእራዊ
በሆነ መንገድ በቁጥር አምስት የሚሆኑ ሕፃናቶች ከሚንቀሳቀሰው
እሳት ውስጥ አምልጠው እየሮጡ ሲወጡ ታዩ፤ ከእነርሱም መካከል አንዷ ትራንግ ባንግ ከሚባለው መንደር አምልጣ የወጣች የዘጠኝ ዓመቷ
ሕፃን ፋን ቲህ ኪምፋክ ነበረች፡፡ ኪም ፋክ ቦንቡ ጀርባዋን እና ክንዶቿን ጎድቷት ስለነበረ እና የለበሰችውን
ልብስ በእሳት ተቀጣጥሎ ስለነበር፤ ልብሷን አውልቃ እራቁቷን ለመሮጥ ተገደደች፡፡
በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ጦርነቱን ይዘግቡ የነበረው የአሶሴቲድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ካሜራውን አነጣጥሮ
እየተቃጠለች እራቁቷን የምትሮጠው ኪምን በመቅረጽ ምስሉ ቀርጾ አስቀራት፡፡ ኪም ወደ ጋዜጠኛው እና በሱ ዙሪያ ወዳሉት ወታደሮች
ስትደርስ ‹‹ተቃጠልኩ! ተቃጠልኩ! ‹‹Nong qua, Nong qua,” ‘too
hot, too hot” እያለች ታለቅስ ነበር፡፡
… ጋዜጠኛው ከምንና አብረዋት የተረፉትን
ህፃናት ሳይጎን ወደ ሚባል ከተማ ወስዶ በሆስፒታል ውስጥ እርዳት እንዲሰጣቸው አደረገ፡፡ ኪም ብዙ የቦንብ ፍንጥርጣሪ በሰውነቷ
ውስጥ ስለገባ በሆስፒታል ውስጥ ባደረገቸው የ14 ወር ቆይታ 17 ጊዜ ወደ ቀዶ ጥገና ተደርጎላታል፡፡ ደስ የሚለው ነገር ኪም ከዚህ
ሁሉ ስቃይ እና መከራ በኋላ ድና ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅላለች፡፡
ዶ /ር ኪም ፉክ አሁን በካናዳ አገር
እርሷ የተባበሩት መንግስታት የሰላም መልክተኛ ናት›› ትልቅም የሕጻናት መረጃ ማዕከል በስሟ ከፍታለች፡፡ የሁለት ልጆችም እናት
ናት፡፡
…. ጆን ፕሎሚር ፤ ኪም ካናዳ እንዳለች
ሰማ ፈልጎም አገኛት›› ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት በኪም ፊት ተንበርክኮ እዲህ አላት ‹‹ኪም ፉክ ያንን ሁሉ ጥፋት እንዲሆን ትዕዛዙን
የሰጠሁት እኔ ነኝ›› በሰራሁት ነገር ተጸጽቻለሁ! ከመሞቴ በፊት አንቺን አግኝቼ ይቅርታ ልጠይቅሽ እመኝ ነበር፡፡ ስላገኘሁሽ እና
ይቅርታ ልጠይቅሽ ስለቻልኩ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ኪም ይቅር ትይኛለሽ?...›› ኪም ህፃን ናት፤ ደግሞም ሰላማዊ ሰውናት፤ በተራንግ ባንግ መንደር ላይ የናፖል ቦንብ ሲጣል ብዙ ሰላማዊ
ሰዎች በተገኙበት ተቃጥለው አልቀዋል፡፡ ኪም ወገኖቿን ሁሉ አጥታለች፤ የአደጋው ጠባሳ ዛሬም በገላዋ ላይ ይታያል፤ በሞት እና በሕይወት
መካከል ሆና እርቃኗን ለዓለም ሁሉ ታይታለች ፡፡ በእውነት ኪም ጆን ፖሎሜርን ይቅር ትለው ይሆን?
… ኪም በ1996 ዓ.ም በቬትናም ጦርነት መታሰቢያ ቀን ላይ እንዲህ ብላ ተናግራ ነበር፡፡ ‹‹ያለፈውን
አንድ ጊዜ የሆነውን ነገር መለወጥ አንችልም! ነገር ግን እያንዳንዳችን ለወደፊቱ ሰላማዊነት ተባብረን ልንሰራ እንችላለን!!!››
እናም ኪም በፊቷ የተንበረከከውን ጆን
ፕሎሜርን ብድግ አርጋ በማቀፍ እንባዋ በዓይኖቿ እየፈሰሱ ‹‹ይቅር ብዬሃለሁ!›› አለችው፡፡ ይህ ይቅርታ በዓለም ላይ በጦርነት
ለተደረጉ በደሎች ሁሉ የተበደሉት ህዝቦች ይቅርታ ሆኖ ተመዘገበ ፡፡
‹‹ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው÷ቢጸጸትም ይቅር በለው፡፡›› ሉቃስ 17፡3
ይህን እውነተኛ ታሪክ ምንጭ ሆኖ ያገኘሁት መንገድ ላይ ትራንስፖርት እየጠበኩ ባለሁበት ሰዓት
እንደነበር ከጋበዙኝ አንድ የእምነት ተቋም በራሪ ወረቀት ላይ ነው፡፡
‹‹ይቅርታ›› ለአለም ህዝብ ወሳኝ ጥልን
ድል የምናደርግበት በእጅ የማይዳሰስ በዓይን የማይታይ መሳሪያ ነው፡፡ ታላቁ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ሌሎች መጽሐፎች ታላላቅ
ሰዎች፣ ሙሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት መምህራን ዘወትር በጽሑፋቸውም ይሁን በትምህርታቸው የሚያነሱት አብሮ ርዕሰ ጉዳይ
ነው፡፡ ዛሬም ፀሐፊው ማንሳት የፈለገው ስለዚሁ ዓብይ ጉዳይ ይቅርታ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ይቅርታ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሥለ ይቅርታ ሲጠይቀው እንዲህ ብሎት ነበር፡፡ ‹‹…..ጌታ ሆይ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ
ሰባት ጊዜን? አለው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለው፡- አስከ ሰባት ጊዜ ሰበት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም፡፡›› ይህ ቃል የሚያስመለክተን
ከይቅርታ አስፈላጊነት ባሻገር ምን ያህል ጊዜ ይቅር ልንል እና ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብን ነው፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግ ነው መሰለኝ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የዛሬ ‹ኢትዮ
ቴሌኮም? (እኔም ይቅርታ የአማርኛ ቃል ሥላልሠጡት አንድም መጠቀም ስላልፈለጉ የሥልጣኔ፤ የዕድገት ምልክት መሆኑ ነው መሰለን የእንግሊዘኛውም
የተጠቀሙት እንዳለ ተጠቅሜአለሁ) መስሪያ ቤት መቼ እንደሚስተካከል የማይታወቀው የኔትወርኩን ችግር ‹‹¸ይቅርታ የደወሉላቸው ደንበኛ
አሁን ማግኘት አይችሉም…..››፤ ‹‹sorry the network is busy …….››፤‹‹ይቅርታ ይቅርታ….›› ተጠቃሚውን ህብረተሰብ
ያሰለች ትልቁ የቴሌኮም ችግር ነው ነገር ግን ሊቀርፈው ያልቻለው ከአሥር ዓመት በላይ ተሸክመነው የዘለቅነው ችግር ነው ምንም እንኳን
መጽሐፍ በጥሬ ለ490 ያህል ጊዜ ሥህቱቱን ይቅር ማለት ቢገባንም የቴሌኮም ሥህተት በዛ፣ ይቅርታውም የምህረት ልመና ሳይሆን ማደንቆሪያ
ከሆነ ሰነባበተ ምክንያቱም በሰላምና በጤና አጠገብዎ ያለውን ደንበኛ ‹‹ይቅርታ ›› ደንበኛዎን ሊያገኟቸው አይችሉም››፣ ይቅርታ
መስመሮቹ ሁሉ ተይዘዋል፡፡›› ‹‹ይቅርታ ደንበኛው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው›› ወዘተ… ይባላሉ፡፡ እሺ እንደ መጽሐፉ
ይህ ወዳጃችን ብቸኛው አገር በቀል ድርጅታችን በደለን ይቅርታ ጠየቀን መቼ ነው ተስተካክሎ ችግሩን አስወግዶ ‹ይቅርታ› መጠየቁን
የሚያቆመው? ለነገሩ በኮምፒውተር የተቀረጸው (የተቀዳው) የድምጽ መልዕክት ለማደናገር (ለማደናቆር) ‹ይቅርታ› ትበል እንጂ ተቋሙ
ለስራው ሥህተት ለበደለው በለድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ አያውቅም፡፡
የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ፣ የቀሙትን
መልስ ምህረት ማግኘት ትልቁ የኢትዮጵያን ሐብት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅር ማለት ፋሽን ያለፈበት፣ ኋላቀር
አስተሳሰብ እየሆነ ከመጣ ሰነባበተ፡፡ መምህራኑ ሃይማኖት፣ ሳይቀሩ ይቅር መባባልን፣ ምዕመናንን ይቅርታ መጠየቅ እንደ ውርደት እየቆጠሩት
መጥተዋል፡፡ ቤተ እምነቶችንም የሚያስተምሩት የማያደርጉ መምህራን ማፍራት ከጀመረች ሰነባበተች ምዕመኑም ‹‹ይቅርታ አድርግልኝና….››
እያለ እያስፈቀደ ማስቀየም ጀምሯል፡፡ ‹‹ይቅርታ ይበለን እንጂ…›› እያለ ማማትንም የተቀደሰ ሥራ አድርጎታል ፡፡
ይቅርታ ያሥተማሩ ይቅርታንም በተግባር
የተገበሩ በሥውር የበደሉትን በአደባባይ በአብራክ ህሊና ተንበርክከው ይቅርታ የጠየቁና አርአያ የሆኑ አልታጡም፡፡ አንዱ ጀግና ደፍሮ
በአደባባይ ይቅርታ ሲጠይቅ ያጥፋም አያጥፋም ብዙዎችን ምሳሌ በመሆን አስተምሯል ብዙዎች ግን አንዱን ይቅርታ አልጠየቁም ዲ.ዳንኤል
ክብረትን ምናልባት በደል አልተገኘባቸው ይሆናል፡፡ እርሱ ግን በአፈ መንፈስ ቅዱስ ይቅር መባል ይገባዋል፡፡ ይቅርታ ጠይቋልም ይቅርታንም
አስተምሯልም፡፡ ኢትዮጵያዊው ጆን ፕሎሜር ያለጥፋት ወይም ጥቂት ጥፋት ትልቁን ይቅርታ የጠየቀ ትንሿ እርሾ ብዙውን ሊጥ ታቦካዋለችና፡፡
በምድራችን በኢትዮጵያ ብዙዎች የጥቃት
ሰለባ የሆነ በአካለ መጠን ጨቅላ የሆኑ በጦርነት የእሳት እራት የሆኑ ነበሩ፡፡ ሃማሴናውያን የት/ት ቤት ተማሪዎች፡፡
በረሃብ አለንጋ ተገርፈው የረገፈ አሉ
በ1977 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድርቅ በበሽታ የሚሰቃዩና ህክምና በማጣት የሚረግፉና በጨቅላነታቸው የሚቀጠፉ ህጻናት ቁጥር የትዬለሌ
ነው፡፡
ወላጆቻቸውን በወባ፣ በቲቢ፣ በH.I.V. ኤድስ ያጡ የህፃናት ቁጥር ቤት ይቁጠረው……ወዘተ፡፡ ለዚህ
ጥፋት፣ መነሻነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሰው እጅ አለበት፤ ታዲያ የትኛው ጀግና የይቅርታ መምህር ይሆን ‹‹…. ያንን ሁሉ
ጥፋት እንዲሆን ትዕዛዙን የሠጠሁት እኔ ነኝ፡፡ በሰራሁት ነገር ተጸጽቻለሁ! …. ይቅርታ!›› በማለት ትውልድን ይቅርታ የሚጠይቅ?
በህፃናት ሥም የሚመጣውን እርዳታ (ገንዘብ፣ እህል፣ መድሐኒት፣ ቁሳቁስ፣ ወዘተ…) ለሌላ ጉዳይ ወይም ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ
የመንግስትና የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ባለሥልጣናት የሆኑ?የሐይማኖት ትምህርት በማስተማር በዓለም ላይ ሰላምን በማምጣት
የላቀ ሚናቸው መጫወት ሲገባቸው በዘረኝነትና በፖለቲካ ክፉ ሥራ ተጠምደው የህፃናቱን ለቅሶና ዋይታ፣ ህመምና ሥቃይ ወደ ጎን የተው
የሃይማኖት መምህራንና መሪዎች ይሆኑ? በሥልጣን ጥማት የተነሳ የሥልጣን ዘመኔ ይራዘምልኝ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ እያሉ እርስ
በርስ ባለመስማማት ጦርነትን በህጻናት ላይ ሳይቀር የሚያውጁ ሰይፍ የሚመዙ ቦንብ የሚያፈነዱ መርዝ የሚረጩ የመንግስት ባለሥልጣናትና
ጋሻ ጀግሬ(አጫፋሪዎች) ይሆኑ? ትርፉን በማሳደድ በቃኝን ባለማወቅና ያለኝ ይበቃኛል በጥቂቱ አትርፌ ህዝቤን ልጥቀም የሚል አስተሳሰብ
በማጣት በየዕለቱ በህፃናት ምግብ፣ አልባሳት፣ የህክምና መድኃኒት…….ወዘተ ላይ ከፍተኛ ጭማሪን በመጨመር ሥቃያቸውን የሚያረዝሙት፣
ህመማቸውንና ጣራቸውን የሚያበዙት፣ ጩኸታቸውን፣ ለቅሶአቸውን፣ የድረሱልኝ ድምጻቸውን ….የመሥሚያ ጊዜ ያጡት ነጋዴዎች(መላው ህብረተሰብ)
ይሆኑን? እንጃ ፣ የትኛው ወገን የእነ ኪምን ለቅሶ፣ ዋይታ፣ ሰቆቃ፣ ህመም፣ አልፎ ተርፎም ሞት በመስማትና በማየት ግፍ መዋል
በቃኝ ያጠፋሁት ጥፋትና እልቂት፣በቃኝ እስከ ዛሬ ለነበረው ነገር ሁሉ ተጠያቂ እኔ ነኝ፣ …. ይቅርታ የሚለው የቱ ይሆን???
ህፃናት እንዳ ኪም በጣሊያን ጦርነት፣ በግራኝ መሐመድና በዮዲት ጉዲት ጦርነት፣ አያት ቅድመ አያቶቻቸውን፣
በደርግና በወያኔ(ኢህአዴግ) ጦርነት፣ በኢህአዴግና በሻቢያ(በኢትዮጵ ኤርትራ) ጦርነት አባቶቻቸውን አጥተዋል ዛሬ በራሳቸው ዘመን
ላይ በመሆን እነርሱን ለማጥፋት የጥፋት ኃይል እጁን ከጠብ መንጃ አፈሙዝ ላይ በማንሳት ህይወታቻቸውን ይታደጋቸው ጥፋትን ሳይሆን
ምህረትን የሚያውጅ የፕሮፓጋንዳ ሥራን(አሉታዊ የሆነውን) በመሥራት ብቻ የተጠመደው ሰላምን በመስበክ ‹‹ተቃጠልን!››፣ ‹‹ተራብን››፣
‹‹ታመምን››፣ ‹ወላጅ አልባ ሆነን››፣ ‹‹የሙቀት መጠን ጨመረብን››፣ ‹‹ንፁህ አየር አጣን፣››፣ ወዘተ የሚሉትን ጨቅላ ህጻና
ወደ አስፈላጊውን ስፍራ ሊወሰዱ የተሰናዱ ጋዜጠኞች አገራችን ያሥፈልጋታል የሃሰት ሰይፋቸውን ጥለው እውነት የሚያወራ ብዕራቸው ሊጨብጡ
ስለሰላም ስለ አንድነት ስለ እርቅ ሊዘምሩና ሊያሸበሽቡ ይገባል፤ ለባለሥልጣናትና ለባለጊዜዎች ማራገብ ይቅር፡፡ የጥፋት ኃይሎችን
ገበና ያጋልጡ፡፡ በመምከርና በማስተማር ለህብረተሰቡም በማሳወቅ ከመንገዳቸው ይመልሱ፡፡
በቤተ እምነቶች ካህናት፣ አስመላኪዎች፣
ሼኮች… ሥራቸውን በእውነት ላይ የተመረኮዘ ትውልድን የሚታደግ ለባለጊዜዎች የሚያደላ እና ህጻናት በተለያየ አቅጣጫ (በርሃብ፣ በብሽታ፣
በጦርነት፣ ወላጆቻቸውን በግፍ በማጣት፣ በዓለም ሙቅት ጨመር ምክንያት ሲጨነቁ …እና ሌሎች ህይወታቸውን የሚቀጥፉ እድገታቸውን የሚያጨናግፉ
ነገሮች በመመልከት ተጠቂ ሲሆኑ ዝም ብሎ ከማየትና ዝምታን ከመምረጥ ለህጻናቱ ወግኖ መሟገት ለዚህ ዓለም የሚበጀውን ሰለምን መስበክ፣
‹‹ኃጢአት መጥፎ ነገርን ብቻ ማድረግ ሳይሆን በጎ ነገር ማድረግ ሲችሉ አለማድረግም ኃጢአት ነውና፡፡››
በህጻናት ዕልቂት ምክንያትነ ከተለያዩ
አላማት ግብረሰናይ ድርጅቶች በልግስና ሥም የሚመጡትን እርዳታዎች (መድኃኒቶች፣ ገንዘቦች…. ወዘተ) ለግል ጥቅማቸው፣ ላልተፈለገ
ምግባሮች (ለጦር መሳሪያ መግዣ፣ ለወታደሮች ማደራጃ ለቢሮ ህንጻ፣ ግንባታ ለባለሥልጣን የመኪና መግዣ የቢሮ ቄሳቁሶች (ቋሚ አላቂ
እቃዎች) ፣ የተለያየ ክፍሎች ሥራ ማስፈጸሚያ በጀት) ማዋል ትልቅ በህጻናቶች ላይ የሚደርስ በደል ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የህጻናቶችና
የወላድ እናቶች ማዋለጃና መንከባከቢያ ሆስፒታሎችን በማስፋፋት የእናቶችንና የህጻናትን ሞት መቀነስ ሲገባ የተያዘውን በጀት በባዶ
ሜዳ በማስታወቂያ (ለትላልቅ ቢል ቦርዶች፣ማሰሪያ፣ለቴለቭዥንና ሬዲዮ ድራማዎች ማስታወቂያ እስፖንሰር ለተለያዩ ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች
ቲሸርትና ኮፍያ፣ ውኃና ኩኪሲ፣ ሻይ፣ ቡና ላይ…) ከማባከን ቀጥታ ከሞት የሚድኑበትን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥራ ቢሰሩ የተሻለ ብዙ
ኪሞችን በሕይወት በማትረፍ፣ የነገ ትውልድ ተረካቢ ዜጎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ የዛሬ ህጻናት የነገ ተስፋ ሰጪ ታሪክ ቀያሪ (ዶክተሮች፣
መምህራኖች፣ሰላም አስከባሪ ኃይሎች፣ ኢንጂነሮች፣ አርቲስቶች፣ ፓይለቶች፣ ሳይንሲስቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ የሀገር መሪዎች፣ በዓለም
ላይ እርቀ ሰላም የሚያመጡ ብዙ ኒልሰን ማንዴላዎች፣ አብርሃም ሊንከንን ÷ወዘተ…) ማፍራት ይቻላል፡፡ ህጻናትን ልናደርግላቸው ከሚገቡት
ጥቅሞቻቸው ባሻገር እያደረግንባቸው ጥቂቶችን እናቁም (ጉልበታቸውን ብዝበዛ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ለሥዳትና ለጉዳና ተዳዳሪነት መዳረግ፣
ለልመና ማሰማራት….)
የህጻናት አዕምሮን ባዶ ወረቀት አንድ ነውና መልካም ነገር እንቅረፅባቸው ዛሬ ያስፈርንባቸው ትንሽ
መልካም ነገር የነገ የትውልድ ትልቅ ተስፋ ይሆናል፡፡ የዛሬ በደላችን ነገ ይቅርታ ያገኛልና፡፡ ዛሬ ጦርነት፣ ስደት፣ ርሃብ፣ ፍቅር
ማጣት፣ ድኅነት፣በሽታ፣ ድርቅ… ያኩራመታት ዓላማችን ነገ በነዚህ አዲስ ተስፋ ስንቀው በሚመጡ ጨቅላ ህጻናት እንድታገግም፣ የተኳረፍን
እንድንታረቅባት፣ የተከፋፈልን አንድ እንድንሆንባት፣ በጎን በቋንቋ በብሔር በቀለም በፖለቲካ፣ በሃይማኖት ተከፋፍለን የተበታተንነው
አንድ ህዝብ አንድ አገር እንድንሆንባት በነዚህ አዲስ ትውልድ አዲስ ዓለም ለመፍጠር የተበላሸ ታሪክ፣ ውሸትን፣ ጠማማ፣ የፖለቲካ
አካሄድንና አመራርን፣ ሥራ የተለየው ዲሞክራሲን፣ አናውርሳቸው የእኛን መጥፎ ገጽታ እንዲወርሱ አናድርጋቸው፡፡ በአዲስ የህጻናት
አዕምሮ ሰላም፣ ፍቅር፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ ከግል ጥቅም የጋራ ጥቅምን፣ የአገርን ጥቅም እንፃፍባቸው፡፡
‹‹ያለፈውን አንድ ጊዜ የሆነውን ነገር
መለወጥ አንችልም ነገር ግን እያንዳንዳችን ለወደፊቱ ሰላማዊነት ተባብረን ልንሰራ እንችላለን!›› ኪም የተናገረቸው ነበር በቬትናም
ጦርነት መታሰቢያ ቀን ላይ ዛሬም ኢትዮጵያውያን አፍሪካዊያን የዓለም ህጻናት ያለፉትን አሰቃቂ ጦርነቶችና ጥቂቶች በማሰብ ‹‹ያለፈውን
መለወጥ አንችልም፤ለወደፊቱ ሰላማዊነት ተባብረን እንስራ›› ይላሉና፡፡ ደግሞ ጨለማ ሥራችንን በቀለም ከማስዋብ ይልቅ ከትናንት ጥፋታችን
ተመልሰን እውነተኛ ሥራ እንስራ ስህተትና ጥፋትን መማሪያ እንጂ ታሪካችን አናድርግ እርቀ ሰላም እንፍጠር ይቅር እንባባል፡፡ይቅርታ!