ትቶ እና ችሎ
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ
የቤተእምነት አባቶች እንደ የ ደረጃቸው ይህ አይነት አስተዋይነት በመሪነታቸው ወቅት ይጠበቅባቸዋል። መንጋውን ለመጠበቅም ይሁን ለአስተዳደራዊ ውሳኔ ሰጪነታቸው ይህን መንገድ መከተል ግድ ነው።
በመንግሥት ደረጃም ያሉ ባለስልጣናት (የክልልም ሆነ የፌዴራል) ሕዝባቸውን ሲያስተዳድሩ፣ ውሳኔ ሲሰጡ፣ ግጭቶችን ሲፈቱ፣ ይህ የሚጠበቅባቸው ጉዳይ ነው።
የተቋማት አስተዳዳሪዎች በየእርከናቸው ሰራተኞቻቸውን ሲመሩ እና ሲያስተዳድሩ፣ ውሳኔ ሲያሳልፉ እና ልዩነቶችን የመፍትሔ አቅጣጫ ሲጠቁሙ በማስተዋል ሊሆን እንደሚገባ አስተማሪ ተግባር የሚሻ ቃል ነው ትቶ እና ችሎ መኖር።
ሰው ከብቸኝነት ወጥቶ ሁለት እና ከዚያ በላይ ሆኖ ሲኖር፣ በትዳር ሲጣመር፣ የጋራ ዓላማ ካለው ወዘተ ሁሌም ሁሉም ወገን አንድ ነገር ያስባል፤ በአንድ ነገር ላይ በእኩል ያምናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
አብሮ ለመኖር፣ የጀመሩትን ለማስቀጠል፣ ልዩነቶችን ለማጥበብ፣ ግጭቶችን ለማስቀረት አማራጭ ከሌላቸው መፍትሔዎች አንዱ ትቶ እና ችሎ መኖር ነው።
ትቶ እና ችሎ ሲባል የምንተወው እና የምንችለው ነገር የማይጠቅም እና የሚቻል ሆኖ አይደለም። ነገር ግን ሁለቱም ከአብሮነት ስለማይበልጡ እንጂ። አንድም በማጣት ውስጥ ማግኘት ስላለ እንጂ። አንድም በዚህ የተነሳ የምናገኘው ከምናጣው ነገር ስለማይበልጥ እንጂ።
በዓለም ላይ መንግሥታት ሆኑ ሁለት ተደራዳሪዎች ችግሮችን የሚፈቱት ወደ አንድ የሚመጡት win win በሆነ መንገድ ነው። win win ሲባል ሁለቱም አሸናፊ በሚሆኑበት መንገድ ነው። አሸናፊነት ስንል ሁሌም ማግኘት ማጣት የሌለበት ማለታችን አይደለም። የተወሰነ ሰጥት የተወሰነውን ተቀብሎ፤ የሆነውን ነገር እየተወ የሆነለትን አስከብሮ መሄድ እንጂ።
ለምሳሌ በትዳር ውስጥ እውነቱን ከተነጋገርን አብዛኛውን ጊዜ ከምንግባባበት የማንግባባበት ይበልጣል። ምክንያቱ ግን ስለምንጠላላ አይደለም። ከሁለት ዓለም፣ ከሁለት ቤተሰብ የአስተዳደግ ሁኔታ ውስጥ፣ ከተለያየ ልማድ እና አስተሳሰብ ካለው ማኀበረሰብ ውስጥ፣ ከተለያየ አመለካከት እና አረዳድ ውስጥ ስለመጣን እንጂ።
በየተቋማቱ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ከሚመሯቸው እና ከሚያስተዳድሯቸው ጋር የሐሳብ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ልዩነትን በተለመደ ቋንቋ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይጠበቅባቸዋል። (በጠረጴዛ ዙሪያ ሲባል ጠረጴዛ ችግሩን ይፈታዋል ማለት ሳይሆን በአንድ ጉዳይ ላይ ወደ አንድ ነጥብ ላይ መስማማትን መግባባትን ለማመላከት ነው።) በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ መሰባሰብ ችግር መፍታት እንደማይችሉ ዓለም ላይ የተከናወኑ የጠረጴዛ ውይይቶች ማሳያ ናቸው።
በጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት የሚቀመጡ ወገኖች ሊሸነፉበት የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አምነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ይህንንም ሲያደርጉ ከበስተጀርባ የሚመሩትን ሕዝብ (ሰራተኛ ) ጥቅምና እና ጉዳት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል።
እንደዚህ አይነቱ ልዩነት ጤናማ ነው። ከሁለት የሚወጣ አንድ ጥሩ እና ጠንካራ ነገር ስለሚገኝ። ይኽ እስኪሆን ደግሞ የሚያለያየንን ጉዳይ በመተው እና በመቻል ማሳለፍ ይጠበቅብናል። እኔ ብቻ የበላይ ልሁን እኔ ብቻ ላሸንፍ የምንል ከሆነ በዚህም መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ከምናገኘው/ልናስከብር ወይም ልናስፈጽም ከምንችለው በላይ እናጣለን።
ስለዚህ ነገሮችን መቋጨት ያለብን በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆን አለበት። ይህ መርህ ሁለቱንም ወገን አሸናፊ ያደርጋል።
ካልሆነስ ነው?
አያድርግብንና ከሆነ ምላሹ የከፋ ነው። አንድነት ይከፈላል፣ ትዳር ይበተናል፣ ቤተሰብ ይፈርሳል፣ ልጆች ወላጅ (እናት/አባት) አልባ ይሆናሉ፣ ጠንካራ የነበረው የኑሮ ደረጃ ይናጋል፣ አገር ማህበረሰብ ዘመድ አዝማድ መሠረቱ ይናጋል።
በጥቂት የቃላት ጦርነት የተጀመረ አለመግባባት ነፍጥ አስመዝዞ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል። ጸብ ይፈጠራል። ሥራ ይበደላል። ኢኮኖሚው ይናጋል። የሰው አኗኗር ይበላሻል። ሕይወት ይቀጠፋል። ንብረት ይወድማል። አካል ይጎድላል። እንደዚህ ሲሆን ሊተመን የማይችል ኪሳራ ይደርሳል።
መሰል ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በጥልቅ አስተዋይነት እና በበሳል አመራርነት ነው። በሳል አመራርነት እኔ ይድላኝ፣ እኔ ያልኩት ይሁን፣ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ፣ ወዘተ ሳይሆን የሚለው በመሸነፍ ለማሸነፍ ከእኔ ይቅር በማለት እያወቀ ይተዋል። ይሸነፋልም።
በትዳር ውስጥ ለሚከሰቱ ልዩነቶች በጎ አስተዋጽኦ ያላቸው ሰዎች እንዳሉት ሁሉ ተግባራቸው ከሰይጣን የሚብሱ አሉ። በሰው ቁስል እንጨት እየቆሰቆሱ የራሳቸውን የሚኖሩ ነገር ግን በሌላው ላይ ከዳር ሆነው የሚፈርዱ አሉ። ልዩነቶቻቸውን በማስፋት፣ ግጭታቸውን በማጉላት እርባና ቢስ የሆነ ፍርድ የሚሰጡ አሉ።
አጀማመሩ ትንሺ የሚመስል አፀፋው ግን ከባድ የሆነ ችግር ይዞ ይመጣል። የስነልቦና ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ወዘተ ይዞ ይመጣል። ስለዚህ ሁሉም ሰው ከእንዲዚህ አይነት ክስተት ከሚመጣ ጉዳት ራሱን ለመታደግ አስቀድሞ የሥነልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ደግ አሳቢ መስለው የተለኮሰው ላይ ቤንዚን የሚረጩ እና የሚያቀጣጥሉትን በንቃት መከታተልና ሊከላከላቸው ይገባል።
እንዲህ አይነት ተግባራት በአገራችን እንኳን በፖለቲካው፣ በየ ቤተ እምነቱ፣ በትዳር ውስጥ፣ ወዘተ ክስተቶችን መታዘብ ከጀመርን ከረምረም ብለናል። አሁንም ለነዚህ ተግባራት የሚተውን ትቶ የሚቻለውን ችሎ በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር መፍታት የሰጥቶ መቀበልን መርህን መከተል ግድ ነው። ካልሆነ ውጤቱ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል።
ሁላችንንም እግዚአብሔር ይርዳን፤ ያጋጠሙንን ችግሮች የምንተውበትን እና የምንችልበትን ጸጋ ያድለን።
ይቆየን።