ብዙ መልኮችና ብዙ ስሞች ያሉዋት አዲስ አበባ አንዱ መጠሪያዋ አራዳ
ነበር፤ አራዳና አዲስ አበባ ተነጣጥለዉ የሚታዩ አልነበሩም፡፡ በአንድ
ወቅት ታላቁ ሰዉ አቶ ይድነቃቸዉ ተሰማ ስለ አዲስ አበባ በሬድዮ ፕሮግራም ተጠይቆ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለዉ፡- ‹‹ የአዲስ
አበባዉ ስታድየም አሁን አለበት ቦታ እንዲሠራ ሐሳብ ሲቀርብ ኳስ ሜዳዉን ከከተማ ዉጭ አደረጋችሁት ተብለን ተወቀሰን ነበር፤
›› እንግዲህ በወቅቱ አዲስ አበባ ምን ያህል ጠባብና ስንት ህዝብ ይኖርባት እንደነበር መገመት ቀላል ነዉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ
ስታድየምን ያህል ነገር ሲሰራ ከከተማ ወጥቷል ከተባለ የስልጣኔ ጥጓ ምን ያህል ድረስ እንደነበረ መገመትም አይዳግትም፡፡ በቅርቡ
እንኳን በ 20 እና በ 30 አመታት ጊዜ ዉስጥ እንኳን የነበራትን ገጽ ብንመለከት አዲስ አበባ እንኳንስ የዓለም አቀፍ ተቋማት
መቀመጫ ልትሆን ይቅርና ለዋና ከተማነት እንኳን የምትመረጥ አልነበረችም፤ ካረጁ ቤቶቿ እና ከፈራረሱ መንገዶቿ አንፃር፡፡ በዚህ
የታሪክ አጋጣሚ በ1879 ዓ.ም. የቆረቆሯት አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ተነስተዉ የትናንትናዋን ባለጎፈሬዋን እና የዛሬዋን ‹ዉብና
ድንቅ› እንዲሁም ሰፊ ከተማ በወቅቱ ከነበረዉ ጋር ለማነጻጸር ‹‹ ዕድል ›› ቢገጥማቸዉ ምን ይሰማቸዉ ይሆን? ያስብላል፡፡
እንደዉ የሚሉትን ነገር ገምቱ ብንባል ዘና ለማለትና በዚያዉም ምሳ
ነገር ለመጋበዝ የቀድሞዉን ‹‹ኢምፔሪያል›› የዛሬዉን ‹‹ ጣይቱ
ሆቴል›› ዉሰዱኝ ሳይሉ እንደማይቀሩ እንገምታለን፤ እኛም መቸስ የጠየቁትን አንነፍጋቸዉም እንወስዳቸዋለን፡፡ መቸስ ስለ ጣይቱ ሆቴል
ከተነሳ አንድ እዉነት ልንገራችሁ፡- በራዲዮ የቀረበ ነዉ፤ እኔም ከ100ኛ ዓመት በዓል መዘከሪያ መጽሔት ላይ ያገኘሁት ነዉ፡፡
ላዲላስ
ፋራጎ ይባላል፡፡ ጋዜጠኛ ነዉ፡፡ላዲስ ፋራጎ ከለገሃር ባቡር ጣቢያ ተነስቶ ጣይቱ ሆቴል ይሄዳል፡፡ከጅቡቲ፣ከድሬደዋና ከአዋሽ ተሸክሞት
ከመጣዉ አዋራና ላብ ለመገላገል ቸኩሎ ነበር፡፡
ከመኝታ ቤቱ ሲገባ ግሩም የሆነ የገላ መታጠቢያ ገንዳ (ባኞ) በማግኘቱ
እጅግ ተደስቶ ቦዩን ጠራና ‹‹ ገላዬን ስለምታጠብ ገንዳዉን ሙላልኝ ›› ይለዋል፡፡
ቦዩም (አስተናጋጁ) ስንት ታንካ (ጀሪካን) ዉሃ ላስመጣልዎ ›› ይለዋል፡፡
ፈረንጁ ግራ ይገባዉና ‹‹ ገንዳዉን ሙላልኝ ነዉ የምልህ፡፡ ቧንቧዉን
ክፈተዉ፡፡›› ይለዋል፡፡
አሁንም
ቦዩ ይመልስና ‹‹ ገላዎን መታጠብ ከፈለጉ የሚፈልጉትን የዉሃ መጠን ይንገሩኝ፡፡ ያንዱ ታንካ ዉሃ ዋጋ አራት ግርሽ (ጠገራ ብር
ወይም ማርያቴሬዛ) ነዉ፡፡ ›› ይላል፡፡ (ገንዳዉን የሚሞላዉ ስድስት
ታንካ (108 ሊትር) ዉሃ ነዉ፡፡) ላዲስላስ ፋራጎ ቀጠለና ‹‹ እንዴ? የቧንቧዉን ዉሃ በታኒካ ልክ ታስከፍላላችሁ ማለት ነዉ?››
ሲል ቦዩን ጠየቀዉ፤
ቦዩም ‹‹ አይደለም! ዉሃዉ የሚመጣዉ ከፍል ዉሃ ነዉ፡፡ ኩሊዎ (ተሸካሚ)
ይላኩና ፍልዉሃ ሄደዉ ታኒካዉን በፈላ ዉሃ ከሞሉ በኋላ ተሸክመዉ ያመጡታል፡፡ አንድ ኩሊ ዳዉን 6 ታኒካ ዉሃ ይሞላዋል፡፡ ገላዎን
አንዴ ታጥበዉ መለቅለቅ ከፈለጉ ደግሞ ተጨማሪ ታኒካ ዉሃ ማስመጣት ያስፈልጋል ›› አለዉ፡፡
‹‹ገንዳችሁ ላይስ የተተከለዉ ቧንቧ?››
‹‹ እንዳልኩዎት ዉሃዉ የሚመጣዉ ክፍል ዉሃ ነዉ፡፡››
ላዲስላስ ፋራጎ ገባዉ፡፡ ገንዳዉ ላይ የተተከለዉ ቧንቧ ለጌጥ ነበር፡፡