ክርስቲያናዊ ሕይወት እና ሥነምግባር
ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁልጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡
1.
ሕገ እግዚአብሔር
መጀመሪያውና ዋነኛው የክርስቲያን ሥነ ምግባር መለኪያው ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ አንድ ሰው ምናልባትም ሕይወቱ በሰው ፊት ሲታይ የሚያስደስት በአፍአ ያለው ጠባዩ እንከን የማይወጣለት ሊሆን ይችላል፡፡ በሕገ እግዚአብሔር ተመዝኖ ካላለፈ ዋጋ የለውም። በሰው ፊት መልካም ሆኖ የሚታይ ምግባር እግዚአብሔርን ሊያስደስት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ፡፡” ኤፌሶን.6፥6
ፈሪሳውያን ከእነርሱ ውጪ የሆነውን ሁሉ የናቁ ያለእኛ ሕገ እግዚአብሔርን አክባሪ ከእኛም በላይ ጻድቅ የለም ባዮች ነበሩ፡፡ነገር ግን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችና ሥራቸው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ እንዲያውም “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ማቴ.5፥20 በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቀ፡፡
እንዲያውም ከእነርሱ እርሾ /ትምህርት/ እንዲጠበቁ አስጠነቀቃቸው፡፡ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ማቴ.16፥6 አለ፡፡